በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተጨማሪ መረጃ

የማስተርቤሽንን ልማድ ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

የማስተርቤሽንን ልማድ ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

ማስተርቤሽን አምላክን የሚያሳዝን መጥፎ ልማድ ሲሆን አንድ ሰው የራሱን ስሜት ስለ ማርካት ብቻ የሚያስብ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ አእምሮን ይበክላል። * በተጨማሪም ይህ ልማድ የተጠናወተው ሰው፣ ሌሎችን የጾታ ስሜትን ለማርካት የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ብቻ እንደሆኑ አድርጎ መመልከት ሊጀምር ይችላል። ይህ ሰው የጾታ ግንኙነትን የሚመለከተው ሁለት ሰዎች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር የሚገልጹበት መንገድ እንደሆነ አድርጎ ሳይሆን ቅጽበታዊ ደስታ የሚገኝበትና የጾታ ስሜት የሚፈጥረውን ውጥረት የሚያስታግስ ተግባር እንደሆነ አድርጎ ነው። ይሁን እንጂ ስሜቱን የሚያስታግሰው ለጊዜው ብቻ ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ማስተርቤሽን እንደ “ዝሙት፣ ርኩሰት፣ [ተገቢ ያልሆነ] የፆታ ምኞት” ያሉትን ዝንባሌዎች ከመግደል ይልቅ ይበልጥ ያነሳሳቸዋል።—ቆላስይስ 3:5

ሐዋርያው ጳውሎስ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ . . . ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ፤ እንዲሁም አምላካዊ ፍርሃት በማሳየት ቅድስናችንን ፍጹም እናድርግ” ሲል ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ጳውሎስ የሰጠውን ይህን ምክር መፈጸም አስቸጋሪ ከሆነብህ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ ምንጊዜም ‘ይቅር ለማለትና’ አንተን ለመርዳት ዝግጁ ነው። (መዝሙር 86:5፤ ሉቃስ 11:9-13) አንዳንድ ጊዜ ይህ ልማድ የሚያገረሽብህ ቢሆን እንኳ ልብህ የሚኮንንህ መሆኑ ወይም ራስህን መውቀስህ እንዲሁም ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ ጥረት ማድረግህ ጥሩ ዝንባሌ እንዳለህ ያሳያል። በተጨማሪም “አምላክ ከልባችን ይበልጥ ታላቅ ነው፤ ደግሞም ሁሉንም ነገር ያውቃል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አስታውስ። (1 ዮሐንስ 3:20) አምላክ የሚያየው ኃጢአታችንን ብቻ ሳይሆን ሁለንተናችንን ነው። ይህም በምሕረት ዓይኑ እንዲመለከተን የምናቀርበውን ምልጃ በርኅራኄ እንዲሰማ ያስችለዋል። በመሆኑም ችግር በገጠመው ቁጥር ወደ አባቱ እንደሚሮጥ ልጅ፣ አንተም በትሕትና ወደ ይሖዋ በመቅረብ ከልብህ እሱን ከመማጸን ወደኋላ አትበል። ይሖዋ ንጹሕ ሕሊና በመስጠት ይባርክሃል። (መዝሙር 51:1-12, 17፤ ኢሳይያስ 1:18) እርግጥ ነው፣ ከጸሎትህ ጋር የሚስማሙ አስፈላጊ እርምጃዎችን መውሰድ ይኖርብሃል። ለምሳሌ፣ ከማንኛውም ዓይነት የብልግና ፊልሞችና ምስሎች እንዲሁም ከመጥፎ ባልንጀሮች ለመራቅ የተቻለህን አድርግ። *

ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ከተቸገርክ ስለ ጉዳዩ ክርስቲያን ከሆነው ወላጅህ ወይም በመንፈሳዊ ከጎለመሰና ከሚያስብልህ ወዳጅህ ጋር ብትወያይ ጥሩ ይሆናል። *ምሳሌ 1:8, 9፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14፤ ቲቶ 2:3-5

^ አን.1 ማስተርቤሽን፣ የራስን የጾታ ብልት በማሻሸት የጾታ ስሜትን የማርካት ልማድ ነው።

^ አን.2 ብዙ ቤተሰቦች፣ ኮምፒውተራቸውን የቤተሰቡ አባላት ወጣ ገባ በሚሉበት ግልጽ ቦታ ላይ በማስቀመጥ፣ በኮምፒውተር አጠቃቀማቸው ረገድ ገደብ ለማበጀት የሚያስችሏቸውን እርምጃዎች ወስደዋል። በተጨማሪም አንዳንዶች መጥፎ ነገሮችን አጣርቶ የሚያስቀር ፕሮግራም ኮምፒውተራቸው ላይ ጭነዋል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ ልንተማመንበት የምንችል የኮምፒውተር ፕሮግራም ማግኘት አይቻልም።

^ አን.1 ይህን ልማድ ለማሸነፍ የሚረዱህ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦችን ለማግኘትበኅዳር 2006 ንቁ! ላይ የወጣውን “ የወጣቶች ጥያቄ . . . ይህን ልማድ ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?” የሚለውን ርዕስ እንዲሁም ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶችጥራዝ 1 ከተባለው መጽሐፍ ላይ ገጽ 178-182ን ተመልከት።