በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህ ሰው ይሆነኛል?

ይህ ሰው ይሆነኛል?

ምዕራፍ 3

ይህ ሰው ይሆነኛል?

የሚከተሉትን ጥያቄዎች በደንብ አስቢባቸውና መልስ ስጪ፦

አሁን ካለሽ አመለካከት አንጻር፣ የምታገቢው ሰው ሊኖሩት ይገባል የምትያቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ከታች ከተዘረዘሩት መካከል በጣም አስፈላጊ እንደሆኑ በሚሰሙሽ በአራቱ ላይ ✔ አድርጊ።

□ ቆንጆ □ መንፈሳዊ

□ ተግባቢ □ የሚታመን

□ ተወዳጅ □ ጨዋ

□ ተጫዋች □ የዓላማ ሰው

በዕድሜ ለጋ በነበርሽበት ወቅት የወረት ፍቅር ይዞሽ ያውቃል? ከላይ ከተዘረዘሩት መካከል በዚያ ወቅት ግለሰቡን በጣም እንድትወጂው ባደረገሽ ባሕርይ ላይ ✘ አድርጊ።

ከላይ ከተጠቀሱት ባሕርያት መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ መጥፎ አይደሉም። ሁሉም የራሳቸው የሆነ ደስ የሚል ነገር አላቸው። ሆኖም የወረት ፍቅር ይዞሽ በነበረበት ወቅት ይበልጥ ያተኮርሽው በስተግራ በኩል እንደተዘረዘሩት ባሉ ውጫዊ ነገሮች ላይ ነበር ቢባል አትስማሚም? *

አንድ ሰው በዕድሜ እየበሰለ ሲሄድ ግን በማስተዋል ችሎታው በመጠቀም በስተቀኝ በኩል እንደተጠቀሱት ዓይነት በጣም አስፈላጊ ባሕርያት ያሉት ግለሰብ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ይጀምራል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወጣት በሰፈሩ ውስጥ በጣም ቆንጆ የምትባለው ልጅ የምትታመን እንዳልሆነች ሊያስተውል ይችላል፤ አሊያም ደግሞ አንዲት ወጣት በክፍሏ ውስጥ በጣም ተወዳጅ የሆነው ልጅ ጨዋ እንዳልሆነ ትገነዘብ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች አፍላ የጉርምስና ዕድሜን ካለፉ በኋላ “ይህ ሰው ይሆነኛል?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ይበልጥ የሚያተኩሩት ከውጪ በሚታዩ ባሕርያት ላይ ሳይሆን በውስጣዊ ማንነት ላይ ይሆናል።

በቅድሚያ ራስን ማወቅ ያስፈልጋል

ለትዳር የሚሆንሽን ሰው ለማግኘት ከመሞከርሽ በፊት ራስሽን በሚገባ ማወቅ ይኖርብሻል። ራስሽን ይበልጥ ለማወቅ እንድትችዪ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስቢባቸው፤ ከዚያም መልስሽን ክፍት ቦታው ላይ አስፍሪ፦

ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ? ․․․․․

ደካማ ጎኖቼስ የትኞቹ ናቸው? ․․․․․

የማገባው ሰው እንዴት እንዲይዘኝ እፈልጋለሁ? በመንፈሳዊነቴ ረገድስ ምን ደረጃ ላይ መድረስ እፈልጋለሁ? ․․․․․

ራስሽን ማወቅ ቀላል እንዳልሆነ ባይካድም ከላይ እንደሰፈሩት ባሉ ጥያቄዎች በመጠቀም እንደዚህ ማድረግ ትችያለሽ። ራስሽን ይበልጥ እያወቅሽ በሄድሽ መጠን፣ ከድክመትሽ ይልቅ በጠንካራ ጎንሽ ላይ በማተኮር የተሻልሽ ሰው እንድትሆኚ የሚረዳሽን ሰው ለማግኘት የሚያስችል ብቃት እያዳበርሽ ትሄጃለሽ። * እንዲህ ዓይነት ሰው እንዳገኘሽ የሚሰማሽ ከሆነስ?

ማንኛውም ሰው ሊሆነኝ ይችላል?

“ብንጠናና ምን ይመስልሻል?” እንዲህ ያለ ጥያቄ ቢቀርብልሽ በጣም ትጨነቂ አሊያም ደግሞ በደስታ ትፈነድቂ ይሆናል፤ ይህን የሚወስነው የጠየቀሽ ሰው ማንነት ነው። መልስሽ ‘እሺ’ ነው እንበል። ታዲያ በምትጠናኑበት ጊዜ ይህ ሰው ይሆንሽ እንደሆነ ማወቅ የምትችይው እንዴት ነው?

አዲስ ጫማ ለመግዛት አስበሻል እንበል። አንድ ሱቅ ስትገቢ ዓይንሽ አንድ ጫማ ላይ አረፈ። የሚያናድደው ግን ጫማውን ስትሞክሪው በጣም ጠበበሽ። ምን ታደርጊያለሽ? የፈለገው ይሁን ብለሽ ጫማውን ትገዢዋለሽ? ወይስ ሌላ ጫማ ለማግኘት ትሞክሪያለሽ? የሚያዋጣሽ ጫማውን ወደ ቦታው መልሰሽ ሌላ መፈለግ ነው። የማይሆንሽን ጫማ አድርገሽ መሄድ ሞኝነት ይሆናል!

የትዳር ጓደኛ ከመምረጥ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ቀልብሽን የሚስቡ የተለያዩ ወንዶች ያጋጥሙሽ ይሆናል። ያም ቢሆን ግን ማንኛውም ሰው ይሆንሻል ማለት አይደለም። ደግሞስ የምትፈልጊው የሚመችሽ ይኸውም ከባሕርይሽ ጋር የሚጣጣምና እንደ አንቺ ዓይነት ግብ ያለው ሰው አይደለም? (ዘፍጥረት 2:18፤ ማቴዎስ 19:4-6) ታዲያ እንደዚህ ዓይነት ሰው አግኝተሻል? ከሆነ ይህ ሰው እንደሚሆንሽ ማወቅ የምትችይው እንዴት ነው?

ውጫዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ከማተኮር መቆጠብ

ግለሰቡ ይሆንሽ እንደሆነ በምትገመግሚበት ወቅት ስሜታዊ ላለመሆን ጥንቃቄ አድርጊ! ምክንያቱም ማየት የምትፈልጊውን ብቻ ወደ ማየት ልታዘነብዪ ትችያለሽ። ስለዚህ አትቸኩዪ፤ የግለሰቡን እውነተኛ ባሕርያት ለማወቅ ጥረት አድርጊ። ይህን ለማድረግ ብዙ ልፋት ይጠይቅብሽ ይሆናል። ሆኖም ይህ የሚያስገርም አይደለም። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ወጣት መኪና ለመግዛት አሰበ እንበል። መኪናውን ምን ያህል በጥንቃቄ መፈተሽ ያለበት ይመስልሻል? የመኪናውን ውጫዊ መልክ ብቻ ከመመልከት አልፎ ውስጡን መፈተሹ ምናልባትም ሞተሩ ስላለበት ሁኔታ የተቻለውን ያህል ለማወቅ መሞከሩ ተገቢ አይሆንም?

የትዳር ጓደኛ ማግኘት መኪና ከመምረጥ ይበልጥ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። ያም ሆኖ መጠናናት የጀመሩ ብዙ ወጣቶች ከውጫዊ ነገሮች አልፈው አይመለከቱም። ቶሎ የሚታዩዋቸው ከወደዱት ሰው ጋር የሚያመሳስሏቸው ነገሮች ናቸው። ለምሳሌ ‘የሙዚቃ ምርጫችን አንድ ዓይነት ነው፣’ ‘የምንመርጣቸው የጊዜ ማሳለፊያዎች ተመሳሳይ ናቸው፣’ ‘በሁሉም ነገር እንስማማለን!’ ማለት ይቀናቸዋል። አንቺ ግን ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በእርግጥ አፍላ የጉርምስና ዕድሜን አልፈሽ ከሆነ የሚማርኩሽ ውጪያዊ የሆኑ ነገሮች አይሆኑም። ምክንያቱም የግለሰቡን “የተሰወረ የልብ ሰው” ለማወቅ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ትገነዘቢያለሽ።​—1 ጴጥሮስ 3:4፤ ኤፌሶን 3:16

ለምሳሌ፣ በምትስማሙባቸው ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የማትስማሙባቸው ነገሮች ሲኖሩ ግለሰቡ ምን ዓይነት ባሕርይ እንደሚያሳይ ብታስተውዪ ስለ ውስጣዊ ማንነቱ ይበልጥ ማወቅ ትችያለሽ። በሌላ አባባል፣ ይህ ሰው አለመግባባቶች ሲፈጠሩ ምን ያደርጋል? እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ ይላል? ምናልባትም “በቁጣ መገንፈል” ወይም ‘መሳደብ’ ይቀናዋል? (ገላትያ 5:19, 20፤ ቆላስይስ 3:8) ወይስ ነገሩ የምርጫ ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ ሰላም ለመፍጠር ሲል የሌላውን ሐሳብ በመቀበል ምክንያታዊ መሆኑን ያሳያል?​—ያዕቆብ 3:17

ሌላም ልታስቢበት የሚገባ ጉዳይ አለ፦ ይህ ሰው የሚፈልገውን ነገር ለማግኘት ሲል ሊጫንሽ ይሞክራል? በትንሽ በትልቁ ይቀናል? የት ገባሽ የት ወጣሽ ያበዛል? ኒኮል የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንድ ጓደኛሞች፣ ‘የት እንዳለሽ ሁልጊዜ ልትነግሪኝ ይገባል’ በሚል እንደሚጨቃጨቁ እሰማለሁ። እንዲህ ያለው ባሕርይ ችግር መኖሩን የሚጠቁም ምልክት እንደሆነ ይሰማኛል።”​—1 ቆሮንቶስ 13:4

ከላይ እንደተጠቀሱት ያሉት ነጥቦች በጓደኛሽ ባሕርይና ምግባር ላይ ያተኮሩ ናቸው። ሌሎች ስለ ጓደኛሽ ምን አመለካከት እንዳላቸው ማወቅሽም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነው። ጓደኛሽ በሰዎች ዘንድ ምን ስም አትርፏል? ይህን ለማወቅ ግለሰቡን በደንብ የሚያውቁትን ሰዎች ለምሳሌ በጉባኤ ያሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖችን ማነጋገሩ ጠቃሚ ይሆናል። በዚህ መንገድ ጓደኛሽ “በመልካም ምግባሩ የተመሠከረለት” መሆን አለመሆኑን ማወቅ ትችያለሽ።​—የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2

እስካሁን ካየናቸው ነጥቦች አንጻር ጓደኛሽን ስትመዝኚው የተሰማሽን ነገር በጽሑፍ ማስፈርሽ ስለ እሱ ማንነት ሰፋ ያለ ግንዛቤ እንዲኖርሽ ይረዳሻል።

ባሕርያቱ ․․․․․

ምግባሩ ․․․․․

ያተረፈው ስም ․․․․․

ከዚህም በተጨማሪ በገጽ 39 ላይ ያለውን “ ጥሩ ባል ይሆነኛል?” የሚለውን ሣጥን ወይም በገጽ 40 ላይ የሚገኘውን “ ጥሩ ሚስት ትሆነኛለች?” የሚለውን ሣጥን መመልከቱም ጠቃሚ ነው። በእነዚህ ሣጥኖች ውስጥ የቀረቡት ጥያቄዎች አንዳችሁ ለሌላው ተስማሚ የትዳር ጓደኛ መሆን ትችሉ እንደሆነ ለመወሰን ይረዷችኋል።

ጉዳዩን በጥሞና ካሰብሽበት በኋላ ‘ይህ ግለሰብ አይሆነኝም’ የሚል ድምዳሜ ላይ ብትደርሺስ? በዚህ ወቅት ፈተና የሚሆንብሽ የሚከተለውን ጥያቄ መመለስ ይሆናል፦

ግንኙነታችንን ማቆም ይኖርብን ይሆን?

መለያየት ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። ጂል የተባለች ወጣት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ አካባቢ የወንድ ጓደኛዬ የት እንዳለሁ፣ ምን እያደረግሁ እንደሆነ እንዲሁም ከማን ጋር እንደሆንኩ ሁልጊዜ ሲጠይቀኝ እንደሚጨነቅልኝ ስለሚሰማኝ ደስ ይለኝ ነበር። በኋላ ላይ ግን ከእሱ ጋር ብቻ ካልሆነ በቀር ከሌላ ሰው ጋር ለደቂቃ እንኳ ጊዜ ማሳለፍ ችግር ሆነ። ሌላው ቀርቶ ከቤተሰቤ ጋር በተለይ ደግሞ ከአባቴ ጋር ስሆን ይቀና ጀመር። ከእሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ሳቆም አንዳች ነገር ከላዬ ላይ የወረደልኝ ያህል ቅልል አለኝ!”

ሣራም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟታል። የወንድ ጓደኛዋ የነበረው ጆን፣ ሥርዓት የጎደለውና ምንም ቢደረግለት የማይደሰት ሰው መሆኑን እያደር አስተዋለች፤ ከዚህም በላይ በአሽሙር ይናገራት ነበር። ሣራ ያጋጠማትን ስታስታውስ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት ከቀጠሯችን ሦስት ሰዓት አርፍዶ መጣ! እናቴ በሩን ስትከፍትለት ዝግት አድርጓት ገባ። ከዚያም ‘እንሂዳ፣ አርፍደናልኮ!’ አለኝ። የሚገርመው ‘አርፍጃለሁ’ ከማለት ይልቅ ‘አርፍደናል’ ነበር ያለው። ይቅርታ መጠየቅ ወይም ያረፈደበትን ምክንያት መግለጽ ነበረበት። ከሁሉ በላይ ደግሞ ለእናቴ አክብሮት ሊያሳያት ይገባ ነበር!” እርግጥ ነው፣ ግለሰቡ አንድ ወቅት ላይ መጥፎ ጠባይ ስላሳየ ወይም የሚያበሳጭሽ ነገር ስላደረገ ብቻ ግንኙነታችሁ መቆም አለበት ማለት አይደለም። (መዝሙር 130:3) ሆኖም ሣራ፣ ጓደኛዋ ከላይ የጠቀሰችው ዓይነት ሥርዓት የጎደለው ጠባይ ያሳየው በአጋጣሚ እንዳልሆነና እንዲህ ማድረግ ልማዱ እንደሆነ ስትገነዘብ ግንኙነታቸውን ለማቆም ወሰነች።

አንቺም እንደ ጂልና እንደ ሣራ የወንድ ጓደኛሽ ተስማሚ የትዳር አጋር እንደማይሆንሽ ብትገነዘቢስ? እንዲህ ከሆነ ውስጥሽ የሚነግርሽን ማዳመጥ አለብሽ! ሁኔታውን አምኖ መቀበል እንደሚከብድሽ ባይካድም ግንኙነቱን ማቆም ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ ሊሆን ይችላል። ምሳሌ 22:3 “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንደኛው ወገን በገጽ 39 እና 40 ላይ ከተጠቀሱት “አደገኛ ምልክቶች” አንዱን እንኳ የሚያሳይ ከሆነ ቢያንስ ችግሩ እስኪስተካከል ድረስ ግንኙነቱን ማቋረጡ ጥበብ ይሆናል። እውነት ነው፣ ግንኙነቱን ማቋረጥ ቀላል ላይሆን ይችላል። ይሁንና ጋብቻ ዘላቂ ጥምረት እንደሆነ አስታውሺ። መለያየታችሁ ለተወሰነ ጊዜ ቢያሳዝንሽም ዕድሜ ልክሽን በጸጸት ስሜት ስትሠቃዪ ከመኖር ይሻልሻል!

ውሳኔን ማሳወቅ

ግንኙነታችሁን ማቆም እንደምትፈልጊ ማሳወቅ የሚኖርብሽ እንዴት ነው? በቅድሚያ ለመነጋገር አመቺ የሆነ ሁኔታ መምረጥ አለብሽ። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው? አንቺ በእሱ ቦታ ብትሆኚ ኖሮ ጉዳዩ እንዴት እንዲነገርሽ እንደምትፈልጊ አስቢ። (ማቴዎስ 7:12) በሌሎች ፊት ቢነገርሽ ደስ ይልሻል? ደስ እንደማይልሽ የታወቀ ነው። ከሁኔታዎች አንጻር እንዲህ ማድረጉ ጥበብ እንደሆነ ካልተሰማሽ በቀር በስልክ የመልእክት መቀበያ ማሽን ላይ መልእክት በመተው አሊያም በሞባይል ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት የጽሑፍ መልእክት በመላክ ውሳኔሽን ማሳወቅም ተገቢ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህንን ከባድ ጉዳይ ለመወያየት አመቺ የሆነ ጊዜና ቦታ ምረጪ።

አመቺ የሆነውን ሁኔታ ከመረጥሽ በኋላ ቀጣዩ ነገር ውሳኔሽን የምትናገሪው እንዴት ነው? የሚለው ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እርስ በርሳቸው ‘እውነትን እንዲነጋገሩ’ ክርስቲያኖችን አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 4:25) ስለዚህ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ጥብቅ አቋም እንዳለሽ በሚያሳይ ሆኖም ስሜቱን በማይጎዳ መልኩ ውሳኔሽን ማሳወቅ ነው። ግንኙነታችሁ እንደማያዛልቅ የተሰማሽ ለምን እንደሆነ በግልጽ ንገሪው። ድክመቶቹን መዘክዘክ ወይም የትችት መዓት ማዥጎድጎድ አያስፈልግሽም። “አንተ በፍጹም . . . አታደርግም” ወይም “አንተ መቼም ቢሆን . . . አታውቅም” በማለት ጣትሽን እሱ ላይ ከመቀሰር ይልቅ “እኔ የምፈልገው . . . ሰው ነው” ወይም “ግንኙነታችንን ማቆም እንደሚገባን የሚሰማኝ . . . ምክንያት ነው” እንደሚሉት ባሉ ምን እንደሚሰማሽ ለመግለጽ በሚያስችሉ ቃላት መጠቀም የተሻለ ይሆናል።

ይህ የምትወላውይበት ጊዜ አይደለም፤ ጓደኛሽ ሐሳብሽን እንዲያስቀይርሽ ልትፈቅጂ አይገባም። ግንኙነታችሁን ለማቆም የወሰንሽው አጥጋቢ ምክንያት ስላለሽ መሆኑን መዘንጋት የለብሽም። በመሆኑም ጓደኛሽ አሳማኝ የሚመስሉ ነጥቦችን በመደርደር ውሳኔሽን እንዳያስቀይርሽ ተጠንቀቂ። ሎሪ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “ከቀድሞ የወንድ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ካቆምኩ በኋላ በተገናኘን ቁጥር በጣም እንደተጎዳ የሚያስመስል ነገር ያደርግ ነበር። እንዲህ የሚያደርገው እንዳዝንለት ብሎ እንደነበረ ይሰማኛል። በእርግጥ አዝኜለት ነበር፤ ሆኖም ይህ ድርጊቱ አቋሜን እንዳላላ አላደረገኝም።” አንቺም እንደ ሎሪ ምን እንደምትፈልጊ ማወቅ ይኖርብሻል። ከአቋምሽ ፍንክች አትበይ። ቃልሽ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን።​—ያዕቆብ 5:12

መለያየት የሚያስከትለውን ጉዳት መቋቋም

ከጓደኛሽ ጋር ከተለያየሽ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በጣም ብትረበሺ ሊገርምሽ አይገባም። ምናልባትም “ዐንገቴን ደፋሁ፤ ጐበጥሁም፤ ቀኑንም ሙሉ በትካዜ ተመላለስሁ” በማለት እንደተናገረው መዝሙራዊ ይሰማሽ ይሆናል። (መዝሙር 38:6) አሳቢ የሆኑ አንዳንድ ጓደኞችሽ ለወንድ ጓደኛሽ ሌላ ዕድል እንድትሰጪው ሊያበረታቱሽ ይሞክሩ ይሆናል። ሆኖም ተጠንቀቂ! ዞሮ ዞሮ መዘዙ የሚተርፈው ለአንቺ እንጂ ለጓደኞችሽ እንዳልሆነ ማወቅ አለብሽ። በተከሰተው ነገር ውስጥሽ ቢያዝንም እንኳ በአቋምሽ ለመጽናት መፍራት የለብሽም።

በመለያየታችሁ የተጎዳው ስሜትሽ ውሎ አድሮ መጠገኑ አይቀርም። እስከዚያው ድረስ ግን ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችሉሽን እንደሚከተሉት ያሉ ጠቃሚ እርምጃዎች ለምን አትወስጂም?

ለምታምኚው ሰው ስሜትሽን አውጥተሽ ተናገሪ። * (ምሳሌ 15:22) ስለ ጉዳዩ ወደ ይሖዋ ጸልዪ። (መዝሙር 55:22) ራስሽን በሥራ አስጠምጂ። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ከሌሎች ራስሽን እንዳታገዪ ተጠንቀቂ! (ምሳሌ 18:1 የ1954 ትርጉም) ዛሬ ነገ ሳትዪ ከሚያንጹሽ ሰዎች ጋር ወዳጅነትሽን አጠናክሪ። አእምሮሽ አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አድርጊ።​—ፊልጵስዩስ 4:8

አንድ ቀን ሌላ ጓደኛ ማግኘትሽ አይቀርም። በዚህ ጊዜ ከአሁኑ የተሻለ ሚዛናዊ አመለካከት እንደሚኖርሽ ምንም ጥርጥር የለውም። ምናልባት በዚያ ወቅት “ይህ ሰው ይሆነኛል?” ለሚለው ጥያቄ አዎን የሚል መልስ ትሰጪ ይሆናል!

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 31 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

መጠናናት ጀምራችሁ ከሆነ አንዳችሁ ለሌላው ፍቅራችሁን በምትገልጹበት ወቅት እስከምን ድረስ መሄድ እንደምትችሉ መወሰን የምትችሉት እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

^ አን.17 ከዚህም በተጨማሪ ስለ ራስሽ ይበልጥ ለማወቅ በምዕራፍ 1 ላይ “ለማግባት ዝግጁ ነህ?” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ከቀረቡት ጥያቄዎች አኳያ ራስሽን መመርመር ትችያለሽ።

^ አን.45 ወላጆችሽ ወይም ሌሎች የጎለመሱ ሰዎች ለምሳሌ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሊረዱሽ ይችላሉ። ምናልባትም ወጣት በነበሩበት ወቅት ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟቸው እንደነበር ይነግሩሽ ይሆናል።

ቁልፍ ጥቅስ

“ሕፃን እንኳ ጠባዩ ንጹሕና ቅን መሆኑ፣ ከአድራጎቱ ይታወቃል።”​—ምሳሌ 20:11

ጠቃሚ ምክር

አንዳችሁ የሌላውን ባሕርያት ለማወቅ በሚያስችሏችሁ እንቅስቃሴዎች ተካፈሉ፦

● የአምላክን ቃል አብራችሁ አጥኑ።

● በጉባኤ ስብሰባዎች ተሳትፎ ስታደርጉና አብራችሁ ስታገለግሉ አንዳችሁ የሌላውን ባሕርይ ለማስተዋል ሞክሩ።

● በመንግሥት አዳራሽ ጽዳትና ግንባታ ተካፈሉ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በተደጋጋሚ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የተለያየ ሃይማኖት ያላቸው ሰዎች የሚመሠርቱት ጋብቻ በፍቺ የማክተሙ አጋጣሚ በጣም ሰፊ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የማያምን ሰው ወድጄ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

የወንድ ጓደኛዬ ምን ዓይነት ስም እንዳተረፈ ለማወቅ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

በትዳር ውስጥ ሊጠቅሙ የሚችሉ ምን ጥሩ ባሕርያት አሏችሁ?

የትዳር ጓደኛችሁ የሚሆነው ሰው የትኞቹ አስፈላጊ ባሕርያት እንዲኖሩት ትፈልጋላችሁ?

እምነታችሁን የማይጋራ ሰው ብታገቡ ምን ችግሮች ሊያጋጥሟችሁ ይችላሉ?

ስለ ጓደኛችሁ ባሕርይና ምግባር እንዲሁም ስላተረፈው ስም ማወቅ የምትችሉባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

[በገጽ 37 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የፍቅር ጓደኛችሁ ቤተሰቡን የሚይዝበት መንገድ ወደፊት እናንተን እንዴት እንደሚይዛችሁ ይጠቁማል።”​—ቶኒ

[በገጽ 34 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ”

“ከማያምኑ ጋር አቻ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ።” ወጣቶች በ⁠2 ቆሮንቶስ 6:14 ላይ የሚገኘው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። ያም ቢሆን አንዳንዶች የማያምን ሰው ሊማርካቸው ይችላል። ምክንያቱ ምንድን ነው? አንዳንድ ጊዜ የሚማርካቸው የግለሰቡ መልክ ብቻ ሊሆን ይችላል። ማርክ የተባለ አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በስፖርት ክፍለ ጊዜ ሁሌ የማያት አንዲት ልጅ ነበረች። ልጅቷ ከእኔ ጋር ለማውራት የማታደርገው ጥረት አልነበረም። በመሆኑም ከእሷ ጋር ጓደኝነት መጀመር በጣም ቀላል ነበር።”

አንድ ወጣት የራሱን ፍላጎት በሚገባ የሚያውቅና የሚከተላቸው መንፈሳዊ መመሪያዎች ትክክል እንደሆኑ የሚተማመን ከሆነ ብሎም በስሜቱ ከመነዳት ይልቅ በሳል አስተሳሰብ ካዳበረ ምን ዓይነት ውሳኔ ማድረግ እንዳለበት ያውቃል። አንድ የማያምን ሰው የቱንም ያህል ቆንጆና የደስ ደስ ያለው ቢሆን ወይም ምንም ያህል ጨዋ ቢመስል ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት ለማጠናከር ሊረዳችሁ እንደማይችል ምንም ጥርጥር የለውም።​—ያዕቆብ 4:4

እርግጥ ነው፣ ከማያምን ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት መሥርታችሁ ከሆነ ግንኙነቱን ማቆም ቀላል ላይሆን ይችላል፤ ሲንዲ የተባለች ወጣት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟት ያውቃል። “በየቀኑ አለቅስ ነበር” ብላለች። “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችም ላይ እንኳ ሳይቀር ነጋ ጠባ ስለ ልጁ አስብ ነበር። በጣም እወደው ስለነበር በወቅቱ እሱን ከማጣ ሞቴን እመርጥ ነበር።” ሆኖም ሲንዲ ከማያምን ሰው ጋር የፍቅር ጓደኝነት መጀመሯ ተገቢ እንዳልሆነ እናቷ የሰጠቻት ምክር ጥበብ ያዘለ መሆኑን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አልወሰደባትም። “ከእሱ ጋር የነበረኝን ግንኙነት ማቆሜ ተገቢ ነበር። ይሖዋ የሚያስፈልገኝን እንደሚያሟላልኝ ምንም አልጠራጠርም” ብላለች።

እናንተም እንደ ሲንዲ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟችኋል? ከሆነ ሁኔታውን ለማስተካከል ብቻችሁን መታገል አያስፈልጋችሁም! ጉዳዩን ለወላጆቻችሁ ማማከር ትችላላችሁ። ጂም የተባለ ወጣት በትምህርት ቤቱ ካለች አንዲት ልጅ ጋር ፍቅር ይዞት በነበረበት ወቅት እንዲህ አድርጓል። “ወላጆቼ እንዲረዱኝ ጠየቅዃቸው። ለእሷ የነበረኝን የፍቅር ስሜት እንዳሸንፍ የረዳኝ ትልቁ ነገር እነሱን ማማከሬ ነበር” ብሏል። የጉባኤ ሽማግሌዎችም ሊረዷችሁ ይችላሉ። ታዲያ ወደ አንዳቸው ቀርባችሁ ስላጋጠማችሁ ሁኔታ ለምን አትነግሯቸውም?​—ኢሳይያስ 32:1, 2

 [በገጽ 39 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የመልመጃ ሣጥን

ጥሩ ባል ይሆነኛል?

ማንነት

□ ያለውን ሥልጣን የሚጠቀምበት እንዴት ነው?​—ማቴዎስ 20:25, 26

□ ምን ግቦች አሉት?​—1 ጢሞቴዎስ 4:15

□ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ አሁን ጥረት እያደረገ ነው?​—1 ቆሮንቶስ 9:26, 27

□ ቤተሰቡን የሚይዘው እንዴት ነው?​—ዘፀአት 20:12

□ ጓደኞቹ እነማን ናቸው?​—ምሳሌ 13:20

□ ማውራት የሚቀናው ስለ ምንድን ነው?​—ሉቃስ 6:45

□ ለገንዘብ ምን አመለካከት አለው?​—ዕብራውያን 13:5, 6

□ ምን ዓይነት መዝናኛ ይወዳል?​—መዝሙር 97:10

□ ለይሖዋ ያለውን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት ነው?​—1 ዮሐንስ 5:3

ጠቃሚ ባሕርያት

□ ታታሪ ነው?​—ምሳሌ 6:9-11

□ ገንዘብ አያያዝ ይችላል?​—ሉቃስ 14:28

□ ጥሩ ስም አትርፏል?​—የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2

□ ለሌሎች አሳቢ ነው?​—ፊልጵስዩስ 2:4

አደገኛ ምልክቶች

□ ግልፍተኛ ነው?​—ምሳሌ 22:24

□ የፆታ ብልግና እንድንፈጽም ለማግባባት ይሞክራል?​—ገላትያ 5:19

□ በሌሎች ላይ አካላዊ ጥቃት ይሰነዝራል? ወይም ስሜት የሚያቆስል ነገር የመናገር ልማድ አለው?​—ኤፌሶን 4:31

□ ካልጠጣ በቀር የተዝናና አይመስለውም?​—ምሳሌ 20:1

□ ቀናተኛና ራስ ወዳድ ነው?​—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

 [በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የመልመጃ ሣጥን

ጥሩ ሚስት ትሆነኛለች?

ማንነት

□ በቤተሰብም ሆነ በጉባኤ ውስጥ ለሥልጣን ተገዢ መሆኗን የምታሳየው እንዴት ነው?​—ኤፌሶን 5:21, 22

□ ቤተሰቧን የምትይዘው እንዴት ነው?​—ዘፀአት 20:12

□ ጓደኞቿ እነማን ናቸው?​—ምሳሌ 13:20

□ ማውራት የሚቀናት ስለ ምንድን ነው?​—ሉቃስ 6:45

□ ለገንዘብ ምን አመለካከት አላት?​—1 ዮሐንስ 2:15-17

□ ምን ግቦች አሏት?​—1 ጢሞቴዎስ 4:15

□ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ አሁን ጥረት እያደረገች ነው?​—1 ቆሮንቶስ 9:26, 27

□ ምን ዓይነት መዝናኛ ትወዳለች?​—መዝሙር 97:10

□ ለይሖዋ ያላትን ፍቅር የምታሳየው እንዴት ነው?​—1 ዮሐንስ 5:3

ጠቃሚ ባሕርያት

□ ታታሪ ናት?​—ምሳሌ 31:17, 19, 21, 22, 27

□ ገንዘብ አያያዝ ትችላለች?​—ምሳሌ 31:16, 18

□ ጥሩ ስም አትርፋለች?​—ሩት 3:11

□ ለሌሎች አሳቢ ናት?​—ምሳሌ 31:20

አደገኛ ምልክቶች

□ ጨቅጫቃ ናት?​—ምሳሌ 21:19

□ የፆታ ብልግና እንድንፈጽም ለማግባባት ትሞክራለች?​—ገላትያ 5:19

□ ስሜት የሚያቆስል ነገር የመናገር ልማድ አላት? ወይም በሌሎች ላይ አካላዊ ጥቃት ትሰነዝራለች?​—ኤፌሶን 4:31

□ ካልጠጣች በቀር የተዝናናች አይመስላትም?​—ምሳሌ 20:1

□ ቀናተኛና ራስ ወዳድ ናት?​—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ማንኛውም ጫማ ልክሽ እንደማይሆን ሁሉ ጥሩ የትዳር ጓደኛ የሚሆንሽም ማንኛውም ሰው አይደለም

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መኪና በምትመርጥበት ጊዜ ውጫዊ መልኩን ብቻ ከመመልከት አልፈህ ውስጡን መፈተሽ አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል? የትዳር ጓደኛ መምረጥስ ከዚህ ይበልጥ በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ አይደለም?