በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?

ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?

ምዕራፍ 4

ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?

እውነት ወይስ ሐሰት?

መጠናናት የጀመሩ ሁለት ሰዎች በምንም ተአምር መነካካት የለባቸውም።

□ እውነት

□ ሐሰት

አንድ ወንድና አንዲት ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባይፈጽሙም ዝሙት እንደፈጸሙ የሚያስቆጥር ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።

□ እውነት

□ ሐሰት

መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት በመተቃቀፍ፣ በመደባበስ እና በመሳሳም ፍቅራቸውን ካልገለጹ ይዋደዳሉ ማለት አይቻልም።

□ እውነት

□ ሐሰት

ይህን ጉዳይ ብዙ ጊዜ አስበህበት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ከአንዲት ወጣት ጋር እየተጠናናህ ከሆነ ፍቅራችሁን የምትገልጹበት መንገድ ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ እንደሆነ ማወቅ አስቸጋሪ ሊሆንባችሁ ይችላል። እስቲ እውነት ወይም ሐሰት ብለህ እንድትመልስ ከላይ የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች እንመርምር፤ ከዚያም “ገደቡን አለፈ የሚባለው መቼ ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የአምላክ ቃል እንዴት እንደሚረዳን እንመለከታለን።

መጠናናት የጀመሩ ሁለት ሰዎች በምንም ተአምር መነካካት የለባቸውም።

ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ባለውና ተገቢ በሆነ መልኩ ፍቅርን መግለጽን አይከለክልም። ለምሳሌ ያህል፣ በጣም ስለሚዋደዱ አንዲት ሱላማጢስ ወጣትና አንድ እረኛ የሚናገር ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን። እነዚህ ወጣቶች የሚጠናኑት ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናቸውን ጠብቀው ነበር። ያም ሆኖ ከመጋባታቸው በፊትም ቢሆን በአንዳንድ መንገዶች አንዳቸው ለሌላው ፍቅራቸውን ይገልጹ እንደነበር ከታሪኩ በግልጽ መመልከት ይቻላል። (ማሕልየ መሓልይ 1:2፤ 2:6፤ 8:5) በዛሬው ጊዜም ለመጋባት የወሰኑ አንድ ወንድና ሴት ንጹሕ በሆነ መንገድ ፍቅራቸውን መግለጻቸው ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸው ይሆናል። *

ይሁንና የሚጠናኑ ሰዎች በዚህ ረገድ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል። መሳሳም፣ መተቃቀፍ ወይም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅስ ማንኛውንም ነገር ማድረግ የፆታ ብልግና ወደ መፈጸም ሊያመራ ይችላል። አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንዲህ ያሉትን የፍቅር መግለጫዎች የሚያሳዩት በንጹሕ ልቦና ተነሳስተው ቢሆንም እንኳ ስሜታቸውን መቆጣጠር ተስኗቸው በቀላሉ የፆታ ብልግና ሊፈጽሙ ይችላሉ።​—ቆላስይስ 3:5

አንድ ወንድና አንዲት ሴት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ባይፈጽሙም ዝሙት እንደፈጸሙ የሚያስቆጥር ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ።

እውነት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዝሙት” ተብሎ የተተረጎመው ፖርኒያ የተባለው የግሪክኛ ቃል ሰፊ ትርጉም አለው። ይህ ቃል ባልተጋቡ ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን ማንኛውንም ዓይነት የፆታ ግንኙነትና የፆታ ብልቶችን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጠቀምን ያመለክታል። በመሆኑም ዝሙት የሚለው ቃል የሚያመለክተው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ብቻ ሳይሆን በአፍና በፊንጢጣ የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸምና የሌላውን የፆታ ብልት እንደ ማሻሸት የመሳሰሉትን ድርጊቶች ጭምር ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚያወግዘው ዝሙት መፈጸምን ብቻ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የሥጋ ሥራዎች የታወቁ ናቸው፤ እነሱም፦ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ብልግና [ናቸው።] . . . እንዲህ ያሉትን ነገሮች የሚፈጽሙ የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።”​—ገላትያ 5:19-21

“ርኩሰት” ምንድን ነው? “ርኩሰት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በንግግርም ሆነ በድርጊት የጎደፉ መሆንን ያመለክታል። እጅን የሌላው ሰውነት ውስጥ ማስገባት፣ የሌላውን ልብስ ለማወላለቅ መሞከር ወይም ሊነኩ የማይገባቸውን የሰውነት ክፍሎች ለምሳሌ ጡትን መደባበስ ርኩስ ድርጊት እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጡትን መደባበስን የሚገልጸው በተጋቡ ሰዎች መካከል ብቻ ከሚፈጸሙ ድርጊቶች እንደ አንዱ አድርጎ ነው።​—ምሳሌ 5:18, 19

አንዳንድ ወጣቶች ያለምንም እፍረት የአምላክን መሥፈርቶች ይጥሳሉ። ሆን ብለው ገደቡን ያልፋሉ፤ አሊያም ስግብግብ በመሆን ካገኙት ሰው ሁሉ ጋር የፆታ ርኩሰት ለመፈጸም ይፈልጋሉ። እንደዚህ የሚያደርጉ ወጣቶች ሐዋርያው ጳውሎስ “ብልግና” ብሎ የጠራውን ድርጊት ፈጽመዋል ሊባል ይችላል። “ብልግና” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘ጋጠወጥነት፣ ልቅነት፣ ስድነት፣ ገደብ የለሽ የፆታ ፍላጎት’ የሚል ፍቺ አለው። “የሥነ ምግባር ስሜታቸው ስለደነዘዘ በስግብግብነት ማንኛውንም ዓይነት ርኩሰት ለመፈጸም ራሳቸውን ለብልግና አሳልፈው ሰጥተዋል” እንደተባሉት ሰዎች መሆን እንደማትፈልግ ግልጽ ነው።​—ኤፌሶን 4:17-19

መጠናናት የጀመሩ ወንድና ሴት በመተቃቀፍ፣ በመደባበስ እና በመሳሳም ፍቅራቸውን ካልገለጹ ይዋደዳሉ ማለት አይቻልም።

ሐሰት። አንዳንዶች ከሚያስቡት በተቃራኒ ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎች በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር አያደርጉም። ከዚህ ይልቅ በመካከላቸው መከባበርና መተማመን እንዳይኖር ያደርጋሉ። ሎራ የገጠማትን ሁኔታ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቀን እናቴ ባልነበረችበት ሰዓት የወንድ ጓደኛዬ ቴሌቪዥን ለማየት በሚል ሰበብ ቤታችን መጣ። መጀመሪያ ላይ እጄን ብቻ ነበር የያዘኝ። ይሁንና ሳላስበው ሰውነቴን ይደባብሰኝ ጀመር። እጁን እንዲሰበስብ ብነግረው ተበሳጭቶ ሊሄድ ይችላል ብዬ ስላሰብኩ ‘ተው’ እንዳልለው ፈራሁ።”

የሎራ የወንድ ጓደኛ ከልቡ የሚወዳት ይመስልሻል? ወይስ የሚፈልገው የራሱን ስሜት ለማርካት ብቻ ነበር? አንድ ሰው ርኩሰት እንድትፈጽሙ ሊያነሳሳሽ የሚሞክር ከሆነ ከልቡ ይወድሻል ማለት ይቻላል?

አንድ ወጣት፣ የሴት ጓደኛው ካገኘችው ክርስቲያናዊ ሥልጠና ጋር የሚጋጭና ሕሊናዋን የሚያቆሽሽ ድርጊት እንድትፈጽም የሚገፋፋት ከሆነ የአምላክን ሕግ የሚጥስ ከመሆኑም በላይ ለእሷ ያለው ፍቅር እውነተኛ መሆኑ አጠያያቂ እንዲሆን ያደርጋል። እንዲህ ያለው ድርጊት እንዲፈጸምባት የምትፈቅድ ወጣትም ብትሆን መጠቀሚያ እየሆነች ነው። ከዚህ የከፋው ደግሞ ርኩሰት መፈጸሟ ነው፤ አልፎ ተርፎም ዝሙት ልትፈጽም ትችላለች። *​—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አብጁ

እየተጠናናችሁ ከሆነ ተገቢ ያልሆኑ የፍቅር መግለጫዎችን ከማሳየት መቆጠብ የምትችሉት እንዴት ነው? ግልጽ የሆኑ ገደቦችን አስቀድሞ ማበጀት የጥበብ እርምጃ ነው። ምሳሌ 13:10 (NW) “እርስ በርስ በሚመካከሩ ሰዎች ዘንድ . . . ጥበብ አለ” ይላል። ተገቢ የሚባለው የፍቅር መግለጫ ምን ዓይነት እንደሆነ አስቀድማችሁ ተነጋገሩ። ስሜታችሁ ከተነሳሳ በኋላ ገደብ ለማበጀት መሞከር ቤታችሁ በእሳት ቢያያዝ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን ድረስ እርምጃ ሳትወስዱ እንደመቆየት ይሆናል።

እርግጥ ነው፣ በተለይ መጠናናት እንደጀመራችሁ አካባቢ እንዲህ ያለውን ውይይት ማድረግ ከባድ እንዲያውም የሚያሳፍር ሊሆንባችሁ ይችላል። ሆኖም አስቀድማችሁ ገደብ ማበጀታችሁ በኋላ ላይ ከባድ ችግር ውስጥ እንዳትገቡ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ገደቦች ማበጀታችሁ እሳት ሊያስነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን አስቀድሞ ከማስወገድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ስለ እነዚህ ጉዳዮች መወያየት መቻላችሁ ግንኙነታችሁ የሚያዛልቅ መሆኑን ይጠቁማል። ደግሞም በጋብቻ ውስጥ በፆታ ግንኙነት ለመደሰት ራስን መግዛትንና ትዕግሥትን ማዳበር እንዲሁም ራስ ወዳድነትን ማስወገድ እጅግ አስፈላጊ ነው።​—1 ቆሮንቶስ 7:3, 4

ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ያም ቢሆን ይሖዋ በሚሰጥህ ምክር መተማመን ትችላለህ። በኢሳይያስ 48:17 ላይ ይሖዋ “የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። ይሖዋ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኝ ይመኝልሃል!

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 24 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

አንዲት ወጣት ድንግልናዋን ጠብቃ ስለቆየች ችግር አለባት ማለት አይደለም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጓ የጥበብ አካሄድ ነው። እንዲህ የምንልበትን ምክንያት እስቲ እንመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.15 በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ያልተጋቡ ወንድና ሴት በሰዎች ፊት ፍቅራቸውን መግለጻቸው ሌሎችን ቅር የሚያሰኝ ከመሆኑም ሌላ እንደ ነውር ይቆጠራል። ክርስቲያኖች ሌሎችን የሚያሰናክል ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ አለባቸው።​—2 ቆሮንቶስ 6:3

^ አን.25 በዚህ አንቀጽ ላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች እንደሚሠሩ ግልጽ ነው።

ቁልፍ ጥቅስ

“ፍቅር . . . ተገቢ ያልሆነ ምግባር አያሳይም።”​—1 ቆሮንቶስ 13:4, 5

ጠቃሚ ምክር

ከፍቅር ጓደኛችሁ ጋር ለመጠናናት ስትገናኙ ሌሎችም እንዲኖሩ አድርጉ፤ አሊያም ቢያንስ አንድ ሰው አብሯችሁ መሆን ይኖርበታል። ችግር ውስጥ እንድትገቡ የሚያደርጉ ሁኔታዎችን አስወግዱ፤ ለምሳሌ የቆመ መኪና ወይም ቤት ውስጥ ብቻችሁን አትሁኑ።

ይህን ታውቅ ነበር?

ተጫጭታችሁ ከሆነ ከፆታ ግንኙነት ጋር የተያያዙ አንዳንድ ጉዳዮችን በግልጽ መነጋገር ያስፈልጋችኋል። ይሁን እንጂ በስልክ ስታወሩም ሆነ የጽሑፍ መልእክት ስትላላኩ የፆታ ስሜትን ለመቀስቀስ የታሰቡ ቃላትን መጠቀም ርኩሰት ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የሥነ ምግባር ብልግና ወደ መፈጸም ሊመሩ የሚችሉ ሁኔታዎችን ለማስወገድ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

የፍቅር ጓደኛዬ ተገቢ ያልሆነ ድርጊት እንድንፈጽም ሊገፋፋኝ ቢሞክር እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

ከፍቅር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ ስትሆኑ በመካከላችሁ በሚኖረው አካላዊ ቅርበት ረገድ ምን ዓይነት ገደብ ታበጃላችሁ?

በዝሙት፣ በርኩሰትና፣ በብልግና መካከል ያለውን ልዩነት አብራራ።

[በገጽ 46 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እኔና እጮኛዬ ሥነ ምግባራዊ ንጽሕናችንን ጠብቀን ስለመቆየት የሚገልጹ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አብረን አንብበናል። እነዚህ ጽሑፎች ንጹሕ ሕሊና እንድንይዝ እንደረዱን ይሰማናል።”​—ለቲሺያ

[በገጽ 44 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ገደቡን አልፋችሁ ብትሄዱስ?

ተገቢ ያልሆነ ነገር ከፈጸማችሁ ምን ማድረግ አለባችሁ? ችግሩን በራሳችሁ እንደምታስተካክሉት በማሰብ ራሳችሁን አታታልሉ። አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “‘ሁለተኛ እንዲህ እንዳናደርግ እርዳን’ ብዬ እጸልይ ነበር። ገደቡን ሳናልፍ በመመላለስ ረገድ አንዳንድ ጊዜ ቢሳካልንም የተሳሳትንባቸው ወቅቶችም ነበሩ።” ስለዚህ ጉዳዩን ለወላጆቻችሁ መንገር ያስፈልጋችኋል። መጽሐፍ ቅዱስም ‘የጉባኤ ሽማግሌዎችን እንድትጠሩ’ የሚያበረታታ ጠቃሚ ምክር ይሰጣል። (ያዕቆብ 5:14) እነዚህ ክርስቲያን እረኞች ከአምላክ ጋር ያላችሁን ግንኙነት ለማስተካከል የሚረዳችሁ ምክር፣ ተግሣጽና ወቀሳ ይሰጧችኋል።

[በገጽ 47 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቤታችሁ በእሳት ቢያያዝ እርምጃ ለመውሰድ እሳቱ ከቁጥጥር ውጭ እስኪሆን ትጠብቃላችሁ? በፍቅር መግለጫዎች ረገድ ገደብ ለማበጀትም ስሜታችሁ እስኪነሳሳ መጠበቅ የለባችሁም