በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያህል ታማሚ የሆንኩት ለምንድን ነው?

ይህን ያህል ታማሚ የሆንኩት ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 8

ይህን ያህል ታማሚ የሆንኩት ለምንድን ነው?

“ወጣት ስትሆን ምንም የሚደርስብህ አይመስልህም። በድንገት ስትታመም ግን ‘ለካ ይሄም አለ’ ትላለህ። በአንድ ጀምበር እንዳረጀህ ሆኖ ይሰማሃል።”​—ያሶን

ያሶን አቅም የሚያሳጣና ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትል ክሮንስ የተባለ የአንጀት በሽታ እንዳለበት ያወቀው በ18 ዓመቱ ነበር። ምናልባት አንተም ሥር በሰደደ ሕመም ትሠቃይ ይሆናል፤ ወይም በያዘህ በሽታ ምክንያት አካል ጉዳተኛ ልትሆን ትችላለህ። በመሆኑም እንደ መልበስ፣ መብላት ወይም ትምህርት ቤት መሄድ ያሉትን ብዙዎች እንደ ቀላል የሚያዩአቸውን ተግባሮች ማከናወን ከፍተኛ ጥረት ይጠይቅብህ ይሆናል።

ሥር የሰደደ የጤና ችግር ካለብህ እስር ቤት የገባህ ያህል ነፃነትህ እንደተገደበ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። እንዲሁም የብቸኝነት ስሜት ያጠቃህ ይሆናል። ‘እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የደረሰብኝ አምላክን ምን ብበድለው ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል፤ ወይም አምላክ ታማኝነትህን ለማየት የተለየ ፈተና እንዳመጣብህ ሊሰማህ ይችላል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ በክፉ ነገሮች ሊፈተን አይችልም፤ እሱ ራሱም ማንንም አይፈትንም” ይላል። (ያዕቆብ 1:13) የሰው ልጆች በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካሉ ድረስ ከበሽታ ነፃ ሊሆኑ አይችሉም፤ ከዚህም በተጨማሪ ሁላችንም “መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች” ያጋጥሙናል።​—መክብብ 9:11 NW

ደስ የሚለው ነገር፣ ይሖዋ አምላክ “ታምሜአለሁ” የሚል ሰው የማይኖርበት አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 33:24) ሙታንም እንኳ ትንሣኤ አግኝተው በአዲሱ ዓለም ውስጥ የመኖር አጋጣሚ ያገኛሉ። (ዮሐንስ 5:28, 29) እስከዚያው ድረስ ግን አሁን ባለህበት ሁኔታ ሕይወትህን ጥሩ አድርገህ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው?

ብሩህ አመለካከት ለመያዝ ጣር። መጽሐፍ ቅዱስ “ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው” ይላል። (ምሳሌ 17:22) አንዳንዶች፣ አንድ ሰው በጠና ታምሞ እያለ መሳቅ መጫወት ተገቢ እንዳልሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና ከሌሎች ጋር ስትሆን ለዛ ያለው ጨዋታ መጫወትህና ከሰዎች ጋር አስደሳች ጊዜ ማሳለፍህ አእምሮህ እንዲታደስና የመኖር ተስፋህ እንዲለመልም ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ ሕይወትህ ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ምን ማድረግ እንደምትችል አስብ። አምላካዊ ባሕርይ የሆነው ደስታ ከአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ መሆኑን አስታውስ። (ገላትያ 5:22) የአምላክ መንፈስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ደስተኛ ሆነህ ሕመምህን እንድትቋቋም ሊረዳህ ይችላል።​—መዝሙር 41:3

ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ። መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” ይላል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ምክንያታዊነትን ማዳበርህ ግድ የለሽ አሊያም ጭንቀታም ከመሆን ይጠብቅሃል። ለምሳሌ ያህል፣ ሁኔታህ የሚፈቅድልህ ከሆነ ተገቢ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግህ ጤንነትህ እንዲሻሻል አስተዋጽኦ ሊያበረክት ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ የሕክምና ተቋማት ወጣት ሕመምተኞችን ለመርዳት ሰውነትን የሚያፍታቱ የሕክምና ዘዴዎችን የሚጠቀሙት ለዚህ ነው። በብዙ ሰዎች ላይ እንደታየው አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከሕመም ቶሎ ለማገገም ብቻ ሳይሆን ብሩህ አመለካከት ለመያዝም ይረዳል። ዋናው ነጥብ፦ ሁኔታህን በሐቀኝነት ከመረመርክ በኋላ ልትደርስባቸው የምትችላቸው ግቦች አውጣ።

ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖርህ አድርግ። አንዳንዶች ያለህበትን ሁኔታ በተመለከተ አሳቢነት የጎደለው ነገር ቢናገሩስ? መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰዎች በሚናገሩት ቃል ሁሉ’ ላይ ትኩረት እንዳናደርግ ይመክረናል። (መክብብ 7:21) አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ የተሻለው አማራጭ ነገሩን በቸልታ ማለፍ ነው። አሊያም ደግሞ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አስተያየት ከመስጠት እንዲቆጠቡ ማድረግ ትችል ይሆናል። ለምሳሌ፣ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ሲያዩ ጭንቅ የሚላቸው ከመሰለህ ቀለል እንዲላቸው ለማድረግ ጥረት አድርግ። አንዱ አማራጭ፣ ሰላምታ በመስጠት ጭውውት ከጀመርክ በኋላ በተሽከርካሪ ወንበር ለመጠቀም የተገደድክበትን ምክንያት መንገር ሊሆን ይችላል።

ተስፋ አትቁረጥ። ኢየሱስ ከባድ መከራ ውስጥ በነበረበት ጊዜ ወደ አምላክ ጸልዮአል እንዲሁም በእሱ ታምኗል፤ ከዚህም በላይ ትኩረት ያደረገው በሚደርስበት ሥቃይ ላይ ሳይሆን ወደፊት በሚጠብቀው ደስታ ላይ ነበር። (ዕብራውያን 12:2) ኢየሱስ ከደረሰበት መከራ ትምህርት አግኝቷል። (ዕብራውያን 4:15, 16፤ 5:7-9) እርዳታና ማበረታቻ ባስፈለገው ጊዜ ከመቀበል ወደኋላ አላለም። (ሉቃስ 22:43) የደረሰበትን ሥቃይ ከማዳመጥ ይልቅ ይበልጥ ያሳሰበው የሌሎች ደኅንነት ነበር።​—ሉቃስ 23:39-43፤ ዮሐንስ 19:26, 27

ይሖዋ ‘ስለ አንተ ያስባል’

በሽታህ ምንም ይሁን ምን አምላክ እምብዛም እንደማትጠቅም አድርጎ እንደሚመለከትህ ሊሰማህ አይገባም። እንዲያውም ይሖዋ እሱን ለማስደሰት የሚጥሩ ሰዎችን ውድ እንደሆኑና የላቀ ዋጋ እንዳላቸው አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሉቃስ 12:7) በግለሰብ ደረጃ ‘ስለ አንተ የሚያስብ’ ከመሆኑም በላይ ሕመምተኛ ወይም የአካል ጉዳተኛ ብትሆንም እንኳ በአገልግሎቱ ሊጠቀምብህ ይፈልጋል።​—1 ጴጥሮስ 5:7

እንግዲያው ፍርሃት ወይም የጥርጣሬ ስሜት፣ ማድረግ የምትፈልጋቸውንም ሆነ ልታደርጋቸው የሚገቡህን ነገሮች ከመፈጸም ወደኋላ እንድትል ሊያደርጉህ አይገባም። ምንጊዜም እርዳታ ለማግኘት ወደ ይሖዋ አምላክ ዘወር በል። እሱ የሚያስፈልጉህን ነገሮች የሚያውቅ ከመሆኑም ሌላ ስሜትህን ይረዳልሃል። ከዚህም በላይ ሁኔታህን ተቋቁመህ መጽናት እንድትችል ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነውን ኃይል’ ሊሰጥህ ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አንተም ጢሞቴዎስ እንደተባለው ወጣት አዎንታዊ አመለካከት ልታዳብር ትችላለህ፤ በ17 ዓመቱ ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም የተባለ ኃይለኛ ድካም የሚያስከትልና አቅም የሚያሳጣ በሽታ እንዳለበት ያወቀው ጢሞቴዎስ እንዲህ ብሏል፦ “በ⁠1 ቆሮንቶስ 10:13 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ መከራ እንዲደርስብን አይፈቅድም። በመሆኑም ፈጣሪዬ ይህንን ፈተና ልቋቋመው እንደምችል ከተማመነብኝ ‘አልችልም’ ብዬ ሙግት ለመግጠም እኔ ማን ነኝ?”

የታመመው በቅርብ የምታውቀው ሰው ቢሆንስ?

አንተ ጤነኛ ብትሆንም በቅርብ የምታውቀው አንድ ሰው ታማሚ ወይም የአካል ጉዳተኛ ቢሆንስ? ይህን ሰው ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው? ቁልፍ የሆነው ነገር ‘የሌላውን ስሜት መረዳት’ እና ‘ከአንጀት መራራት’ ነው። (1 ጴጥሮስ 3:8) ግለሰቡ ያለበትን ሁኔታ ለመረዳት እንድትችል ራስህን በእሱ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። ግለሰቡ የሚያጋጥሙትን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በአንተ ሳይሆን በእሱ ዓይን ለማየት ጥረት አድርግ። ከተወለደች ጀምሮ ስፓይና ቢፊዳ በተባለ ከወገብ በታች ሽባ የሚያደርግ ሕመም የምትሠቃየው ኒና እንዲህ ብላለች፦ “ሰውነቴ ደቃቃ ስለሆነና በተሽከርካሪ ወንበር ስለምጠቀም አንዳንድ ሰዎች የሚያዋሩኝ እንደ ልጅ ነው፤ ይህ ደግሞ ስሜቴን ይደቁሰዋል። ሌሎች ግን ፊት ለፊት እየተያየን ማውራት እንድንችል ቁጭ ብለው ሊያነጋግሩኝ ይሞክራሉ። እንዲህ ማድረጋቸው በጣም ያስደስተኛል!”

ግለሰቡ ካለበት የጤና ችግር ባሻገር መመልከት ከቻልክ ከሌላው ሰው የተለየ እንዳልሆነ ትገነዘባለህ። ደግሞም እንደዚህ ላለው ሰው በንግግርህ ‘መንፈሳዊ ስጦታ ልታካፍለው’ ትችላለህ! እንዲህ ስታደርግ ‘እርስ በርስ ስለምትበረታቱ’ አንተም ትጠቀማለህ።​—ሮም 1:11, 12

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 13 ተመልከት

ቁልፍ ጥቅስ

“በዚያ ጊዜ . . . ‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”​—ኢሳይያስ 33:23, 24

ጠቃሚ ምክር

እውቀት ማግኘትህ ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ ሊፈጠርብህ የሚችለውን ስጋት ያቀልልሃል። በመሆኑም ስለ ሕመምህ የተቻለህን ያህል ለማወቅ ጥረት አድርግ። ያልገባህ ነገር ካለ ሐኪሙን በግልጽ ጠይቀው።

ይህን ታውቅ ነበር?

ታማሚ ወይም አካል ጉዳተኛ የሆንከው አምላክ እየቀጣህ ስለሆነ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነት ችግር የሚደርስብን ሁላችንም ከአዳም በወረስነው አለፍጽምና የተነሳ ነው።​—ሮም 5:12

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ሥር የሰደደ ሕመም ቢኖርብኝም ወይም አካል ጉዳተኛ ብሆንም ብሩህ አመለካከት ይዤ መኖር እንድችል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ላወጣው የምችለው ምክንያታዊ ግብ ․․․․․

ያለሁበትን ሁኔታ በተመለከተ አንድ ሰው ደግነት የጎደለው ነገር ቢናገረኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

በዚህ ምዕራፍ ላይ በቀረበው ሐሳብ በመጠቀም አካል ጉዳተኛ የሆነን ወይም ሥር የሰደደ ሕመም ያለበትን ሰው መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?

ሥር የሰደደ ሕመም ካለብህ አሁን ባለህበት ሁኔታ ሕይወትህን ጥሩ አድርገህ ልትጠቀምበት እንድትችል በየትኞቹ አዎንታዊ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ትችላለህ?

የሚደርስብህ መከራ የአምላክን ሞገስ እንዳጣህ የሚያሳይ አለመሆኑን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 75 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ደስቲን፣ 22

“ዕድሜ ልኬን ከተሽከርካሪ ወንበር እንደማልላቀቅ ሳውቅ እናቴ ላይ ጥምጥም ብዬ ያለቀስኩበት ቀን ትዝ ይለኛል። በወቅቱ ገና የስምንት ዓመት ልጅ ነበርኩ።

መስኪዩላር ዲስትሮፊ የተባለ ጡንቻን የሚያልፈሰፍስ በሽታ አለብኝ። ልብሴን ለመልበስ፣ ሰውነቴን ለመታጠብም ሆነ ለመመገብ የሰው እርዳታ ያስፈልገኛል። እጆቼን ወደላይ ማንሳት በፍጹም አልችልም። ያም ሆኖ ሕይወቴ አስደሳችና በሥራ የተጠመደ ነው፤ አመስጋኝ እንድሆን የሚያነሳሱኝ ብዙ ምክንያቶች አሉኝ። አዘውትሬ አገልግሎት የምወጣ ከመሆኑም ሌላ የጉባኤ አገልጋይ ነኝ። እንዲያውም ‘መከራ’ እንዳለብኝ ሆኖ አይሰማኝም። በይሖዋ አገልግሎት ስንጠመድ ምንጊዜም የምንሠራውና በጉጉት የምንጠብቀው ነገር አይጠፋም። ከምንም በላይ ደግሞ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ‘እንደ ሚዳቋ የምዘልበትን’ ጊዜ እናፍቃለሁ።”​—ኢሳይያስ 35:6

[በገጽ 75 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቶሞኮ፣ 21

“የአራት ዓመት ልጅ ሳለሁ ሐኪሙ ዕድሜ ልኬን ኢንሱሊን መወጋት እንደሚኖርብኝ ነገረኝ።

የስኳር ሕመምተኛ ለሆነ ሰው በደሙ ውስጥ ያለውን የስኳር መጠን መቆጣጠር አስቸጋሪ ነው። ብዙውን ጊዜ መብላት በምፈልግበት ወቅት መብላት አልችልም፤ በሌላ በኩል ደግሞ መብላት በማልፈልግበት ወቅት መብላት ይኖርብኛል። እስካሁን ድረስ 25,000 ያህል መርፌ ተወግቻለሁ፤ በዚህም የተነሳ ክንዴና ታፋዬ ላይ የምወጋበት አካባቢ ደድሯል። ይሁንና ወላጆቼ አሁን ባለሁበት ሁኔታ ሕይወቴን ጥሩ አድርጌ እንድጠቀምበት ረድተውኛል። ሁልጊዜ ደስተኞች ከመሆናቸውም በላይ ብሩህ አመለካከት አላቸው፤ እንዲሁም ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዲኖረኝ አድርገው አሳድገውኛል። ይሖዋ ደግ አምላክ መሆኑን በሕይወቴ ተመልክቻለሁ። አመስጋኝነቴን ለማሳየት ስለፈለግሁ የጤንነቴ ሁኔታ ሲፈቅድልኝ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።”

[በገጽ 76 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ጄምስ፣ 18

“ሰዎች እንደ እኔ ከሌሎች ለየት ያለ ሁኔታ ያለው ግለሰብ ሲያዩ ግራ ይጋባሉ።

ድንክ ስሆን የእኔ ድንክነት ከተለመደው ለየት ያለ ነው። ሰዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት ለውጫዊ ገጽታ በመሆኑ ጎርናና ድምፅ ያለው ትንሽ ልጅ እንዳልሆንኩ ሁልጊዜ ማስረዳት ያስፈልገኛል። ሆኖም ‘ለምን እንዲህ ሆንኩ’ ብዬ ከመቆዘም ይልቅ ባሉኝ ነገሮች ላይ ለማተኮር እሞክራለሁ። በሕይወቴ ደስተኛ ነኝ። መጽሐፍ ቅዱስን አጠናለሁ እንዲሁም ይሖዋ እንዲረዳኝ እጸልያለሁ። ቤተሰቦቼ እኔን ለማበረታታት ምንጊዜም ከጎኔ ናቸው። አምላክ ሁሉንም ዓይነት የጤና እክል የሚያስወግድበትን ጊዜ በጉጉት እጠባበቃለሁ። እስከዚያው ድረስ ግን ያለብኝን የአካል ጉድለት ተቀብዬው እኖራለሁ፤ ሕይወቴን እንዲቆጣጠረው ግን አልፈቅድም።”

[በገጽ 76 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ዳኒትሪያ፣ 16

“አንድ ብርጭቆ ውኃ እንኳ ሳነሳ ከፍተኛ ሥቃይ ስለሚሰማኝ የሆነ ችግር እንዳለብኝ ጠርጥሬ ነበር።

ፋይብሮማያልጂያ፣ አካልን የሚያዝልና ሥቃይ የሚያስከትል ከባድ በሽታ ነው። ወጣት እንደ መሆኔ መጠን እንደ ጓደኞቼ መሆን ያምረኛል፤ ሆኖም ማንኛውንም ነገር ማድረግ ከቀድሞው ይበልጥ ከባድ ሆኖብኛል። እንቅልፍ እንኳ እስኪወስደኝ ዓመት ይፈጅብኛል! እንዲህ ዓይነት ችግር ቢኖርብኝም በይሖዋ እርዳታ አንዳንድ ነገሮችን ማከናወን ችያለሁ። ሌላው ቀርቶ ረዳት አቅኚ በመሆን በአገልግሎት ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ችያለሁ። ይህን ማድረግ ቀላል ባይሆንም ተሳክቶልኛል። አቅሜ የሚፈቅደውን ለማድረግ እጥራለሁ። ሰውነቴ የሚነግረኝን ‘ማዳመጥ’ እንዲሁም ከአቅሜ በላይ ላለማድረግ መጠንቀቅ እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ። አቅሜ ውስን መሆኑን ስዘነጋ ደግሞ እናቴ ገደቤን እንዳላልፍ ሁልጊዜ ታስታውሰኛለች!”

[በገጽ 77 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ኤሊስያ፣ 20

“ትምህርት ቤት እያለሁ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ። አሁን ግን አንድ ዓረፍተ ነገር እንኳ ማንበብ መከራ ነው፤ ይህ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በጭንቀት እንድዋጥ ያደርገኛል።

ክሮኒክ ፋቲግ ሲንድረም የተባለው በሽታ ቀላል የሚባሉ ነገሮችን ማከናወን እንኳ አስቸጋሪ እንዲሆን ያደርጋል። አብዛኛውን ጊዜ ከአልጋዬ መነሳት እንኳ ያቅተኛል። ያም ቢሆን ሕመሜ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲይዝ አልፈቅድም። ጥቂት ቁጥሮችን ብቻም ቢሆን በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን አነባለሁ፤ አሊያም ደግሞ ከቤተሰቤ አባላት አንዱ እንዲያነብልኝ አደርጋለሁ። ቤተሰቤ ለሚያደርግልኝ ድጋፍ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንዲያውም አባባ፣ እኔ በአውራጃ ስብሰባ ላይ እንድካፈል ለመርዳት ሲል በስብሰባው ላይ ኃላፊነት ወስዶ እንዲሠራ የተሰጠውን መብት ሳይቀበል ቀርቷል። እንዲህ በማድረጉም ቅር አላለውም። አባባ ቤተሰቡን ከመንከባከብ የሚበልጥ መብት እንደሌለ ይሰማዋል።”

[በገጽ 77 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ካትሱቶሺ፣ 20

“በድንገት መጮኽና መንዘፍዘፍ እጀምራለሁ፤ በኃይል ስለምፈራገጥ በአካባቢዬ ያሉትን ነገሮች ልጥል ወይም ልሰብር እችላለሁ።

የሚጥል በሽታ የያዘኝ የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። በሽታው በወር እስከ ሰባት ጊዜ ሊነሳብኝ ይችላል። በየቀኑ መድኃኒት መውሰድ አለብኝ፤ በዚህም ምክንያት በቀላሉ ይደክመኛል። ይሁን እንጂ ስለ ራሴ ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎችም ለማሰብ እጥራለሁ። በጉባኤያችን ውስጥ በእኔ ዕድሜ ያሉ ሁለት የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች አሉ፤ እነዚህ ወንድሞች ትልቅ እገዛ ያደርጉልኛል። ትምህርቴን ስጨርስ በአገልግሎት የበለጠ ተሳትፎ ማድረግ ጀመርኩ። ከዚህ በሽታ ጋር መኖሬ እያንዳንዱ ቀን ትግል እንዲሆንብኝ አድርጓል። ሆኖም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሲሰማኝ እረፍት ለማድረግ እሞክራለሁ። በንጋታው ጥሩ ስሜት ይኖረኛል።”

[በገጽ 78 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ማቲው፣ 19

“እኩዮችህ ‘ጤነኛ’ የሚሉት ዓይነት ሰው ካልሆንክ የእነሱን አክብሮት ማግኘት በጣም ከባድ ነው።

ስፖርት በጣም ብወድም በየትኛውም ዓይነት ስፖርት ለመካፈል ሁኔታዬ አይፈቅድልኝም። ሴረብረል ፖልዚ የሚባል በሽታ ስላለብኝ መራመድ እንኳ በጣም ይከብደኛል። ያም ቢሆን ግን ማድረግ ስለማልችለው ነገር እያሰብኩ አልብሰለሰልም። ከዚህ ይልቅ እንደ ንባብ ባሉት ላከናውናቸው በምችላቸው ነገሮች ራሴን አስጠምዳለሁ። በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ስሆን ‘ሰዎች ስለ እኔ ምን ያስባሉ’ ብዬ ሳልጨነቅ እንደ ልቤ መሆን እችላለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሚወደኝ በውስጣዊ ማንነቴ እንደሆነ ማወቄ ያጽናናኛል። እንዲያውም ሌሎች እምብዛም የማያጋጥሟቸውን ለየት ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች መቋቋም እንዳለብኝ እንጂ አካል ጉዳተኛ እንደሆንኩ አይሰማኝም።”

[በገጽ 78 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ሚኪ25

“በተለያዩ ስፖርቶች እካፈል ነበር። ይሁንና ገና በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ እንዳረጀ ሰው ሆንኩ።

ስወለድ ጀምሮ ኤትሪያል ሴፕታል የተባለ የልብ ሕመም ነበረብኝ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ስሆን ምልክቶቹ መታየት ጀመሩ። ከስድስት ዓመት በፊት ቀዶ ሕክምና ተደርጎልኝ ነበር፤ ያም ቢሆን አሁንም በቀላሉ የሚደክመኝ ከመሆኑም ሌላ ከባድ ራስ ምታት ያስቸግረኛል። በመሆኑም ልደርስባቸው የምችላቸው የአጭር ጊዜ ግቦች አወጣለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ችያለሁ፤ አብዛኛውን ጊዜ አገልግሎቴን የማከናውነው ደብዳቤ በመጻፍና በስልክ አማካኝነት ነው። ከዚህም ሌላ ሕመሜ ቀደም ሲል ያልነበሩኝን ባሕርያት እንዳዳብር ይኸውም አቅሜን የማውቅና ቻይ እንድሆን ረድቶኛል።”

[በገጽ 74 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥር የሰደደ የጤና ችግር ካለብህ እስር ቤት የገባህ ያህል ሆኖ ሊሰማህ ይችላል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ነፃ እንደምትወጣ ተስፋ ይሰጣል