በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ብቸኝነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ብቸኝነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 9

ብቸኝነትን ማሸነፍ የምችለው እንዴት ነው?

ደስ የሚል ቀን ነው፤ ሆኖም በዚህ ዕለት ልታደርገው ያሰብከው ምንም ነገር የለም። ጓደኞችህ ግን ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ፕሮግራም አላቸው። ሁሉም ወጣ ብለው እየተዝናኑ ነው። ዛሬም አንተን አልጠሩህም! ይህ በራሱ የሚያስከፋ ነገር ነው፤ ከዚያ የባሰው ደግሞ ለምን እንዳልጠሩህ ስታስብ የሚፈጠርብህ ስሜት ነው። ‘ሰዎች አብሬያቸው እንድሆን የማይፈልጉት አንድ ችግር ቢኖርብኝ ነው’ ብለህ ታስባለህ።

ከዚህ በፊት ባለው ገጽ ላይ የተጠቀሰው ዓይነት ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ አጋጥሞህ ሊሆን ይችላል። አንተና እኩዮችህ እንዳትቀራረቡ የሚያደርግ ሰፊ ገደል በመካከላችሁ እንዳለ ሆኖ ይሰማህ ይሆናል። ከእነሱ ጋር ለማውራት በሞከርክ ቁጥር አፍህ ይንተባተብብሃል። አብረሃቸው ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችል አጋጣሚ ስታገኝ ዓይናፋርነት በቀላሉ እንዳትቀላቀላቸው እንቅፋት ይሆንብሃል። ከሌሎች ጋር መጫወት ይህን ያህል አስቸጋሪ የሚሆንብህ ለምንድን ነው?

ከእኩዮችህ ጋር መቼም መቀላቀል እንደማትችል በማሰብ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ገደሉን ለመሻገር የሚያስችልህ ድልድይ ለምን አትሠራም? ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ገደል 1፦ ስለ ራስህ ያለህ አሉታዊ አመለካከት። አንዳንድ ወጣቶች ሁልጊዜ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ይመለከታሉ። ማንም ሰው እንደማይወዳቸውና ጨዋታ እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። አንተም ስለ ራስህ እንደዚህ ይሰማሃል? ከሆነ እንዲህ ያለ አሉታዊ አመለካከት መያዝህ በአንተና በእኩዮችህ መካከል ያለውን ገደል ይበልጥ ከማስፋት ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።

ድልድዩ፦ በጠንካራ ጎኖችህ ላይ ማተኮር። (2 ቆሮንቶስ 11:6) ‘ምን ጠንካራ ጎኖች አሉኝ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ያሉህን አንዳንድ ተሰጥኦዎች ወይም ግሩም ባሕርያት ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ከታች ጻፋቸው።

․․․․․

አንዳንድ ጉድለቶች እንደሚኖሩህ ግልጽ ነው፤ ደግሞም ጉድለቶችህን ማወቁ ጥሩ ነው። (1 ቆሮንቶስ 10:12) ይሁን እንጂ ብዙ ጥሩ ነገሮችም ይኖሩሃል። ጠንካራ ጎኖችህን ማወቅህ በራስ የመተማመን መንፈስ ለማዳበር ስለሚረዳህ ስለ ራስህ ያለህን አሉታዊ አመለካከት ለማስወገድ ያስችልሃል።

ገደል 2፦ ዓይናፋርነት። ከሌሎች ጋር መጫወት ትፈልጋለህ፤ ሆኖም አጋጣሚው ሲፈጠር አፍህ ስለሚተሳሰርብህ ምን እንደምትል ግራ ይገባሃል። የ19 ዓመቷ ኤልዛቤት ዓይናፋርነት አብሯት የኖረ ችግር እንደሆነ ትናገራለች። “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሰዎችን ቀርቦ ማነጋገር በጣም ይከብደኛል፤ እንዲህ ማድረግ የሚችሉ ሰዎችን በጣም ነው የማደንቃቸው!” ብላለች። አንተም እንደ ኤልዛቤት የምታስብ ከሆነ ይህንን ገደል መሻገር ፈጽሞ እንደማይቻል ይሰማህ ይሆናል።

ድልድዩ፦ ከሌሎች ጋር ለመግባባት ልባዊ ጥረት ማድረግ። ይህ ሲባል በጣም ተጫዋች ሰው መሆን አለብህ ማለት አይደለም። መጀመሪያ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ለመግባባት መሞከር ትችላለህ። ሆርሄ የተባለ አንድ ወጣት እንደተናገረው “ሰዎችን ይበልጥ ለማወቅ ስለ ደኅንነታቸው ወይም ስለ ሥራቸው መጠየቅ ብቻ እንኳ በቂ ሊሆን ይችላል።”

ልብ ልትለው የሚገባ ነገር፦ በአንተ ዕድሜ ላይ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ብቻ ለመቀራረብ አትሞክር። በጣም ጥሩ ጓደኛሞች እንደነበሩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጹት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰፊ የዕድሜ ልዩነት ነበራቸው፤ ከእነዚህም መካከል ሩትና ኑኃሚን፣ ዳዊትና ዮናታን እንዲሁም ጢሞቴዎስና ጳውሎስ ይገኙበታል። (ሩት 1:16, 17፤ 1 ሳሙኤል 18:1፤ 1 ቆሮንቶስ 4:17) በተጨማሪም ጭውውት ሲባል ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች የሚያደርጉት የሐሳብ ልውውጥ እንጂ አንድ ሰው ብቻ የሚቆጣጠረው መድረክ አለመሆኑን አትዘንጋ። ሰዎች ከሚያዳምጣቸው ሰው ጋር መጨዋወት ደስ ይላቸዋል። በመሆኑም ዓይናፋር ከሆንክ አንድ ነገር አስታውስ፦ ከሰዎች ጋር ስትጨዋወት ብዙ ማውራት አይጠበቅብህም!

ይበልጥ ልታውቃቸው ከምትፈልጋቸው ትልልቅ ሰዎች መካከል የሁለቱን ስም አስፍር።

․․․․․

ስማቸውን ከጻፍካቸው ሰዎች ወደ አንዱ ቀረብ ብለህ ጨዋታ ለመጀመር ለምን አትሞክርም? ‘ከመላው የወንድማማች ማኅበር’ ጋር ይበልጥ በተቀራረብህ ቁጥር ብቸኝነቱ እየለቀቀህ መምጣቱ አይቀርም።​—1 ጴጥሮስ 2:17

ገደል 3፦ የማይመች ባሕርይ። ሁሉን አውቃለሁ ባይ የሆነ ሰው፣ ሌሎችን መንቀፍና መተቸት እንዲሁም በአሽሙር መናገር ይቀናዋል። በሌላ በኩል ደግሞ መከራከር የሚወድና እኔ ያልኩት ካልሆነ ብሎ ድርቅ የሚል ሰው አለ። እንዲህ ያለው ሰው “እጅግ ጻድቅ” ስለሚሆን የእሱን አስተሳሰብ የማይቀበልን ሰው ለመንቀፍ ይቸኩላል። (መክብብ 7:16) እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጋር መሆን እንደማያስደስትህ የታወቀ ነው። ይሁንና ከሌሎች ጋር እንዳትቀራረብ የሚያግድህ ገደል የተፈጠረው አንተ ራስህ እንዲህ ዓይነት ሰው በመሆንህ ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ “ሞኙም ቃልን ያበዛል” እንዲሁም “ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም” ይላል።​—መክብብ 10:14፤ ምሳሌ 10:19

ድልድዩ፦ ‘የሌላውን ስሜት መረዳት።’ (1 ጴጥሮስ 3:8) አንድ ሰው በሚናገረው ነገር ባትስማማም እንኳ በትዕግሥት አዳምጠው። ትኩረትህን በሚያግባቧችሁ ነጥቦች ላይ በማድረግ ሐሳብ ለመስጠት ጥረት አድርግ። በአንድ ጉዳይ እንደማትስማማ መግለጽ እንዳለብህ ከተሰማህ ሐሳብህን በዘዴና በረጋ መንፈስ ተናገር።

ሰዎችን የምታናግረው ሌሎች አንተን እንዲያናግሩህ በምትፈልግበት መንገድ ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ምንጊዜም ማንኛውንም ነገር ሳታጉረመርሙና ሳትከራከሩ አድርጉ” የሚል ምክር ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 2:14) አላስፈላጊ ክርክር መጀመር ወይም በሌሎች ላይ ማሾፍ እንዲሁም ራስን በማመጻደቅ ሌሎችን መተቸት ወይም መንቀፍ ሰዎች እንዲርቁህ ያደርጋል። ‘ንግግርህ ምንጊዜም ለዛ ያለው’ ከሆነ ግን ሰዎች የበለጠ ይወዱሃል።​—ቆላስይስ 4:6

የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው?

ከላይ ከቀረቡት ነጥቦች አንጻር ራስህን ከመረመርክ በኋላ ከሌሎች ጋር እንዳትቀራረብ የሚያግድህን ገደል ለመሻገር የሚያስችል ድልድይ መሥራት የምትችልባቸው መንገዶች እንዳሉ አስተውለህ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ ምክንያታዊ መሆን ይኖርብሃል። ሁሉም ሰው እንዲወድህ መጠበቅ የለብህም። ኢየሱስ ትክክል የሆነውን የሚያደርጉ ሰዎችን እንኳ የሚጠሉ ግለሰቦች እንዳሉ ተናግሯል። (ዮሐንስ 15:19) ጓደኛ መያዝ የሕይወትና የሞት ጉዳይ እንዳልሆነ አስታውስ፤ ስለዚህ ማንኛውንም መሥዋዕትነት ከፍለህ ጓደኞች ለማፍራት ጥረት ማድረግ አያዋጣም።

ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ሳትጥስ በቀላሉ የምትቀረብ ሰው ለመሆን ጥረት ማድረግ ትችላለህ። በጥንት ዘመን የኖረው ሳሙኤል አምላክን የሚያስደስተውን ነገር ለማድረግ ቁርጥ አቋም ይዞ ነበር። በዚህም የተነሳ ‘በአምላክና በሰው ፊት ሞገስ ማግኘት’ ችሏል። (1 ሳሙኤል 2:26) አንተም የተወሰነ ጥረት ካደረግህ እንደ ሳሙኤል የአምላክንም ሆነ የሰውን ሞገስ ማግኘት ትችላለህ!

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ምዕራፍ 8 ተመልከት

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት “የወጣቶች ጥያቄ​—እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት የምችለው እንዴት ነው?” የተባለውን ዲቪዲ ተመልከት። ይህ ፊልም ከ40 በሚበልጡ ቋንቋዎች ይገኛል (በአማርኛ ግን አይገኝም)

በሚቀጥለው ምዕራፍ

በጣም የምትወደው ጓደኛህ በድንገት ቀንደኛ ጠላት ቢሆንብህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል።”​—ምሳሌ 11:25

ጠቃሚ ምክር

ከሌሎች ጋር ስታወራ ጭውውታችሁ ቀጣይ እንዲሆን አድርግ። ለምሳሌ፣ አንድ ሰው ቅዳሜና እሁድ ጥሩ ጊዜ አሳልፈህ እንደሆነ ቢጠይቅህ ‘አዎ’ ብለህ ብቻ አትመልስ። ከዚህ ይልቅ ጊዜህን እንዴት እንዳሳለፍክ ንገረው። ከዚያም ‘አንተስ ቅዳሜና እሁድን እንዴት አሳለፍክ?’ ብለህ ጠይቀው።

ይህን ታውቅ ነበር?

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚጠቁመው ሙሴ፣ ኤርምያስና ጢሞቴዎስ ዓይናፋር የነበሩ ይመስላል።​—ዘፀአት 3:11, 13፤ 4:1, 10፤ ኤርምያስ 1:6-8፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:6-8

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ጓደኛ እንዳላፈራ እንቅፋት የሚሆንብኝ ትልቁ ነገር ․․․․․

ይህን እንቅፋት ለመወጣት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● አንዳንድ ክርስቲያኖች ብቸኛ የሚሆኑት ለምን ሊሆን ይችላል?

● ስለ ራስህ አሉታዊ ነገሮችን በማሰብ ከመብሰልሰል ይልቅ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ምን ሊረዳህ ይችላል?

● ከብቸኝነት ስሜት ጋር የሚታገሉ ታናናሾች ካሉህ እንዴት ልታጽናናቸው ትችላለህ?

[በገጽ 88 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አንዲት ክርስቲያን፣ ጓደኛ ልታደርገኝ ብትሞክርም እኔ ግን መጀመሪያ ብዙም አላቀረብኳትም ነበር። በኋላ ላይ ስንቀራረብ ግን መጀመሪያውኑ ጓደኛ ስላላደረግኳት ቆጨኝ! በዕድሜ 25 ዓመት ብትበልጠኝም በጣም ከምወዳቸው ጓደኞቼ አንዷ ናት!”​—ማሪ

[በገጽ 87 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከእኩዮችህ ጋር እንዳትቀራረብ የሚያግድህን ገደል ለመሻገር ድልድይ መሥራት ትችላለህ