በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አባቴ የዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኛ ቢሆንስ?

አባቴ የዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኛ ቢሆንስ?

ምዕራፍ 23

አባቴ የዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኛ ቢሆንስ?

“አባዬ መኪናውን ለመጠገን እንደሚሄድ ነግሮን ነበር፤ ሆኖም ቀኑን ሙሉ ድምፁን አጥፍቶ ዋለ። እማዬ በተደጋጋሚ ብትደውልለትም ስልኩን አላነሳውም። በዚህ ጊዜ ሁኔታው ስላስጨነቃት ፊቷ መለዋወጥ ጀመረ። ከዚያም ‘እስቲ አባትሽን ልፈልገው’ ብላኝ ለመውጣት ተነሳች።

“ብዙም ሳይቆይ እማዬ ተመለሰች፤ ሆኖም ብቻዋን ነበረች። ‘አባዬ መኪናው ጋ አልነበረም አይደል?’ አልኳት። ‘አዎ’ አለችኝ።

“በዚያች ቅጽበት፣ አባዬ እንደ ድሮው እኛን ማታለል እንደጀመረ ገባኝ። ባለፈውም ልክ እንዲህ ነበር ያደረገው። ምን መሰላችሁ፣ አባቴ የዕፅ ሱሰኛ ነው። አባዬ ወደ ቤት ሲመለስ እኔና እማዬ በጭንቀት ናላችን ዞሮ ነበር። በነገሩ በጣም ስለተበሳጨሁ በማግስቱ ዘግቼው ዋልኩ፤ በኋላ ላይ ግን እንዲህ በማድረጌ በጣም ተሰማኝ።”​—ካረን፣ 14

በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወጣቶች ከወላጆቻቸው አንዱ የዕፅ ወይም የአልኮል ሱሰኛ በመሆኑ እያንዳንዱን ቀን የሚያሳልፉት በችግር ነው። አባትህ ወይም እናትህ የሱስ ተገዢ ከሆኑ በእነሱ ታፍርና ትበሳጭ ይሆናል፤ አልፎ ተርፎም ሁኔታው ሊያስቆጣህ ይችላል።

ለምሳሌ የሜሪ አባት በሌሎች ፊት ሲሆን ጥሩና ደግ ሰው ይመስል ነበር። ይሁንና ያልታወቀበት የአልኮል ሱሰኛ ነበር፤ ቤት ሲሆን በቤተሰቡ ላይ በተለያየ መንገድ በደል ያደርስባቸው ብሎም ጸያፍ ነገር ይናገራቸው ነበር። “ሰዎች በጣም ጥሩ አባት እንዳለንና ዕድለኞች እንደሆንን ይነግሩን ነበር” ስትል ሜሪ በምሬት ታስታውሳለች። *

አባትህ የአልኮል አሊያም የዕፅ ሱሰኛ ከሆነ ይህን ችግር መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? *

ሱሰኛ የሆነበትን ምክንያት መረዳት

በመጀመሪያ ደረጃ አባትህ ስላለበት ችግር በተወሰነ መጠን ለመረዳት መሞከሩ ጠቃሚ ነው። “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ” በማለት ምሳሌ 1:5 ይናገራል። ስለዚህ ሱስ ምን እንደሆነ እንዲሁም ለአልኮል ወይም ለዕፅ ሱሰኝነት የሚጋለጡት እነማን እንደሆኑና ሱሰኛ የሚሆኑት ለምን እንደሆነ ማወቅህ ጥሩ ነው።

ለምሳሌ፣ አንድ ሰው የአልኮል ሱሰኛ የሚባለው አልፎ አልፎ ከልክ በላይ ስለጠጣ አይደለም። ከዚህ በተቃራኒ ግለሰቡ ሥር የሰደደ ከመጠን በላይ የመጠጣት ችግር አለበት። ከመጠጥ ሌላ የሚታየው ነገር የለም፤ እንዲያውም ያለ መጠጥ መንቀሳቀስ አይችልም። ከዚህም በላይ አንድ ጊዜ መጠጣት ከጀመረ ማቆም ይከብደዋል። ይህ ሱስ ከቤተሰቡ፣ ከሥራውና ከጤንነቱ ጋር በተያያዘ ከባድ ችግር ይፈጥርበታል።

አንዳንድ ሰዎች በተፈጥሯቸው መጠጥ ስለሚወዱ ለአልኮል ሱስ የተጋለጡ ሊሆኑ ቢችሉም ከስሜት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም ለዚህ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። እንዲያውም የአልኮል ሱሰኛ የሆኑ ብዙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለራሳቸው መጥፎ አመለካከት አላቸው። (ምሳሌ 14:13) አንዳንዶቹ ደግሞ ያደጉት የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠጡት በልጅነታቸው የደረሰባቸውን የስሜት ቁስል ለማደንዘዝ ሊሆን ይችላል። አንድ ሰው የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆን የሚያደርጉት ምክንያቶችም ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ።

እርግጥ ነው፣ መጠጣት ወይም ዕፅ መውሰድ አንድ ሰው ያለበትን ችግር ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም፤ እንዲያውም አስተሳሰቡ ይበልጥ እንዲዛባና ስሜቱ እንዲዘበራረቅ ያደርገዋል። በመሆኑም አባትህ ከሱሱ ለመላቀቅ እንዲችል ከባለሙያዎች ከፍተኛ እርዳታ ማግኘት ያስፈልገው ይሆናል።

በምትጠብቀው ነገር ረገድ ማስተካከያ አድርግ

አባትህ እንዲህ ያለ አሳፋሪ ድርጊት የሚፈጽመው ለምን እንደሆነ መረዳትህ በራሱ ችግሩን እንደማያስወግደው የታወቀ ነው። ያም ሆኖ አባትህ ስላለበት ችግር የተወሰነ ግንዛቤ ማግኘትህ ይበልጥ ርኅራኄ እንድታሳየው ሊያነሳሳህ ይችላል።

ለምሳሌ ያህል፣ አባትህ እግሩን ተሰብሮ ቢሆን አብሮህ እግር ኳስ እንዲጫወት ትጠብቅበታለህ? አባትህ ጉዳት የደረሰበት በራሱ ጥፋት እንደሆነ ብታውቅስ? ነገሩ እንደሚያበሳጭህ ምንም ጥርጥር የለውም። ያም ቢሆን አባትህ እግሩ እስኪድን ድረስ አብሮህ ሊጫወት እንደማይችል ትገነዘባለህ። ይህን ማወቅህ ከእሱ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ማስተካከያ እንድታደርግ ይረዳሃል።

በተመሳሳይም የአልኮል ወይም የዕፅ ሱሰኛ የሆነ ሰው በትክክል እንዳያስብና የተረጋጋ ስሜት እንዳይኖረው የሚያደርግ “ጉዳት” ደርሶበታል። እውነት ነው፣ አባትህ “ጉዳት” የደረሰበት በራሱ ጥፋት ነው። በመሆኑም አባትህ እንዲህ ያለ የሞኝነት ድርጊት በመፈጸሙ መበሳጨትህ ስህተት አይደለም። ያም ሆኖ አባትህ ከሱሱ “ለመዳን” የሚያስችለውን እርዳታ እስኪያገኝ ድረስ አንተን ለመንከባከብ ያለው አቅም በጣም ውስን ይሆናል። አባትህ ያለበትን ሱስ፣ እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀስ እንደሚያግደው የአካል ጉዳት አድርገህ መመልከትህ ከእሱ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ማስተካከያ እንድታደርግ ይረዳሃል።

ምን ማድረግ ትችላለህ?

አባትህ ባሕርይውን እስኪያስተካክል ድረስ ያለበት ሱስ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ተቀብለህ መኖርህ ግድ እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብሃል። ታዲያ ችግሩን ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችላለህ?

አባትህ ሱሰኛ መሆኑ ለሚያስከትለው ችግር ኃላፊነቱን አትውሰድ። አባትህ በሱስ ለመጠመዱ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበት እሱ ራሱ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም። ገላትያ 6:5 “እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል” ይላል። በመሆኑም አባትህ ከሱሱ እንዲላቀቅ የማድረግም ሆነ ሱሱ ከሚያስከትልበት ችግር የመታደግ ኃላፊነት የለብህም። ለምሳሌ፣ ሥራ ያልገባበትን ምክንያት በተመለከተ ለአለቃው የመዋሸት ወይም ጥንብዝ ብሎ ሰክሮ ሲመጣ ተሸክመህ አልጋው ላይ የማስተኛት ግዴታ የለብህም።

አባትህ እርዳታ ለማግኘት እንዲጥር አበረታታው። የአባትህ ዋነኛ ችግር፣ እርዳታ የሚያሻው ችግር እንዳለበት አምኖ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ ሊሆን ይችላል። አባትህ ስካሩ ሲበርድለትና ሲረጋጋ እናትህ በዕድሜ ከፍ ካሉት ልጆች ጋር በመሆን ይህ ጠባዩ ቤተሰቡን ምን ያህል እየጎዳው እንዳለና ምን ማድረግ እንደሚገባው ልትነግረው ትችል ይሆናል።

ከዚህም በተጨማሪ አባትህ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሱን በመጠየቅ መልሱን በጽሑፍ ማስፈሩ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል፦ መጠጣቴን ወይም ዕፅ መውሰዴን ከቀጠልኩ እኔም ሆንኩ ቤተሰቤ ምን ሊደርስብን ይችላል? ይህንን ልማዴን እርግፍ አድርጌ ብተው ምን ጥቅም አገኛለሁ? እርዳታ ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብኛል?

ግጭት ሊፈጠር እንደሆነ ከተሰማህ ከአካባቢው ራቅ። ምሳሌ 17:14 “ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር [“ከአካባቢው፣” NW] ራቅ” ይላል። ጥል ሲነሳ በመሃል ጣልቃ በመግባት ራስህን ለአደጋ አታጋልጥ። ከተቻለ ወደ ክፍልህ ግባ፤ አሊያም ወደ ጓደኛህ ቤት ሂድ። አባትህ አካላዊ ጥቃት የሚሰነዝር ከሆነ የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልግህ ይሆናል።

ራስህን አትኮንን። አንዳንድ ወጣቶች ሱሰኛ በሆነው አባታቸው በጣም የሚበሳጩ ሲሆን ይህ ደግሞ የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋቸዋል። በተለይ ደግሞ አባትህ ሱሰኛ በመሆኑ ምክንያት ተገቢውን ፍቅርና ድጋፍ የማይሰጥህ ከሆነ በተወሰነ መጠን በእሱ መበሳጨትህ የሚያስገርም አይደለም። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ወላጅህን የማክበር ግዴታ እንዳለብህ ይገልጻል። (ኤፌሶን 6:2, 3) ይሁንና “አክብር” የሚለው ቃል የአንድን ፖሊስ ወይም ዳኛ ሥልጣን እንደምታከብር ሁሉ የአባትህንም ሥልጣን ማክበር እንዳለብህ የሚጠቁም ነው። እንዲህ ለማድረግ አባትህ ሱሰኛ በመሆኑ መስማማት አለብህ ማለት አይደለም። (ሮም 12:9) አባትህ የመጠጥ ወይም የዕፅ ተገዢ መሆኑ ቢያስጠላህ መጥፎ ሰው ነህ ማለት አይደለም፤ ደግሞም የሱስ ተገዢ መሆን የሚያስጠላ ነገር ነው!​ምሳሌ 23:29-35

ከሚያንጹ ሰዎች ጋር ጊዜ አሳልፍ። ቤታችሁ የተበጣበጠ በሚሆንበት ጊዜ ሰላማዊ የቤተሰብ ሕይወት ምን ማለት እንደሆነ እንኳ ሊጠፋብህ ይችላል። ስለዚህ ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ካላቸውና ከተረጋጉ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ጠቃሚ ነው። የክርስቲያን ጉባኤ አባላት ከፍተኛ ማበረታቻና ድጋፍ ሊሰጡህ አልፎ ተርፎም በቤት ውስጥ ካለብህ ውጥረት ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እፎይታ እንድታገኝ ሊረዱህ ይችላሉ። (ምሳሌ 17:17) በጉባኤ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ቤተሰቦች ጋር ጊዜ ስታሳልፍ ጥሩ የቤተሰብ ሕይወት እንዳላቸው ስለምታስተውል ግሩም አርዓያ ይሆኑሃል፤ ይህ ደግሞ በቤትህ ውስጥ በምትመለከተው መጥፎ ምሳሌ እንዳትቀረጽ ይረዳሃል።

አንተም እርዳታ ለማግኘት ሞክር። ለአንድ ለምታምነው የጎለመሰ ሰው ስሜትህን አውጥተህ መናገርህ በጣም ይረዳሃል። የጉባኤ ሽማግሌዎች እርዳታ በሚያስፈልግህ ጊዜ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህ ወንዶች ‘ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብ መጠጊያ እንዲሁም በበረሃ እንደ ውሃ ምንጭ፣ በተጠማም ምድር እንደ ትልቅ ቋጥኝ ጥላ’ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይናገራል። (ኢሳይያስ 32:2) ስለዚህ ማጽናኛና ምክር ለማግኘት ወደ እነዚህ ወንድሞች መሄዱ ሊያስፈራህ ወይም ሊያሳፍርህ አይገባም።

ከላይ ከተጠቀሱት ስድስት ነጥቦች መካከል መጀመሪያ ተግባራዊ ልታደርገው የምትፈልገውን ጻፍ። ․․․․․

በቤታችሁ ውስጥ ያለውን ሁኔታ መለወጥ አትችል ይሆናል፤ ሆኖም ሁኔታው በአንተ ላይ በሚያሳድረው ተጽዕኖ ረገድ ለውጥ ማምጣት ትችላለህ። አባትህን ለመቆጣጠር ከመሞከር ይልቅ ልትቆጣጠረው በምትችለው ግለሰብ ይኸውም በራስህ ላይ ትኩረት አድርግ። “የራሳችሁን መዳን ለመፈጸም ተግታችሁ ሥሩ” በማለት ሐዋርያው ጳውሎስ ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 2:12) እንዲህ ማድረግህ አዎንታዊ አመለካከት እንድታዳብር ይረዳሃል፤ አባትህም ከሱሱ ለመላቀቅ እርዳታ እንዲሻ ሊያነሳሳው ይችላል።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ ነጋ ጠባ የሚጨቃጨቁ ቢሆንስ? ይህ ሁኔታ የሚፈጥርብህን የስሜት መረበሽ መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ወላጅ ካለህና በደል እያደረሰብህ ከሆነ እርዳታ ለማግኘት መጣር ይኖርብሃል። ለአንድ የምታምነው አዋቂ ሰው ጉዳዩን ንገረው። የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ክርስቲያን ማነጋገር ትችላለህ።

^ አን.8 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የአልኮል ወይም የዕፅ ሱሰኛ ተደርጎ የተገለጸው አባት ቢሆንም ነጥቦቹ ሱሰኛ የሆነች እናት ላላቸው ልጆችም ይሠራሉ።

ቁልፍ ጥቅስ

“ጥበብ ሰውን ታጋሽ ታደርገዋለች።”​—ምሳሌ 19:11

ጠቃሚ ምክር

መጥላት ያለብህ አባትህ የሚፈጽመውን መጥፎ ድርጊት እንጂ ራሱን አባትህን አይደለም።​—ምሳሌ 8:13፤ ይሁዳ 23

ይህን ታውቅ ነበር?

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “አክብር” የሚለው ቃል ሥልጣንን አምኖ መቀበልን ያመለክታል። (ኤፌሶን 6:1, 2) በመሆኑም ወላጅህን ማክበር አለብህ ሲባል ሁልጊዜ በድርጊቱ መስማማት ያስፈልግሃል ማለት አይደለም።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አባቴ ጸያፍ ንግግር የሚናገረኝ ወይም አካላዊ ጥቃት የሚያደርስብኝ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

አባቴ እርዳታ እንዲሻ ለማበረታታት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

አንዳንድ ሰዎች የአልኮል ወይም የዕፅ ሱሰኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ምክንያት ምንድን ነው?

አባትህ በሱስ ለመጠመዱ አንተ ኃላፊነቱን መወሰድ የማይኖርብህ ለምንድን ነው?

ካለህበት ሁኔታ አንጻር ለውጥ ማምጣት የምትችለው በየትኞቹ ነገሮች ላይ ነው? ይህንን ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው?

[በገጽ 192 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የወላጆቼ ሁኔታ ወደፊትም ቢሆን ሊያሸማቅቀኝ እንደሚችል አውቃለሁ፤ ሆኖም በይሖዋ እስከታመንኩ ድረስ ሁኔታውን ለመቋቋም የሚያስችለኝን ብርታት እንደሚሰጠኝም አውቃለሁ።”​—ማክስዌል

[በገጽ 198 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አባትህ ወይም እናትህ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቢያቆሙ

ከወላጆችህ አንዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መከተላቸውን ቢተዉ ምናልባትም የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆናቸውን እንዳቆሙ ቢገልጹ አንተ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ይሖዋ፣ በወላጆችህ ድርጊት አንተን ተጠያቂ እንደማያደርግህ ተገንዘብ። መጽሐፍ ቅዱስ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን” በማለት ይናገራል።​—ሮም 14:12

ከአንተ የተሻለ ሁኔታ ካላቸው ሌሎች ወጣቶች ጋር ራስህን አታወዳድር። (ገላትያ 5:26) አንድ ወጣት አባቱ ቤተሰቡን ትቶ ከሄደ በኋላ ምን እንዳደረገ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ ባሉ ሐሳቦች ከመብሰልሰል ይልቅ ሁኔታውን መቋቋም በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ማተኮሩ ይበልጥ ጠቃሚ ነው።”

አባትህ ወይም እናትህ መጥፎ ጎዳና ቢከተሉም ለእነሱ አክብሮት ማሳየትህን ቀጥል፤ እንዲሁም ከአምላክ መመሪያዎች ጋር የሚቃረን እስካልሆነ ድረስ የሚያዝዙህን ነገር ፈጽም። ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ይሖዋ የሰጣቸውን ትእዛዝ መፈጸም የሚኖርባቸው ወላጆቻቸው አማኝ ሲሆኑ ብቻ አይደለም። (ኤፌሶን 6:1-3) ወላጆችህ ድክመት ቢኖርባቸውም የምታከብራቸውና የምትታዘዛቸው ከሆነ ለይሖዋ ፍቅር እንዳለህ ታሳያለህ።​—1 ዮሐንስ 5:3

ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ተቀራረብ። በጉባኤ ውስጥ ትልቅ መንፈሳዊ ቤተሰብ ስለምታገኝ ጉባኤው የእረፍት ቦታ ይሆንልሃል። (ማርቆስ 10:30) ዴቪድ የተባለ አንድ ወጣት አባቱ ይሖዋን ማገልገሉን በማቆሙ የጉባኤው አባላት እሱንና ቤተሰቡን እንዳያገሏቸው ፈርቶ ነበር። ይሁንና ዴቪድ ፍራቻው መሠረተ ቢስ እንደነበረ ተገነዘበ። “የጉባኤው አባላት አላገለሉንም” ብሏል። “ይህም ጉባኤው በጥልቅ እንደሚያስብልን አረጋግጦልኛል።”

[በገጽ 194 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አባትህ ያለበትን ሱስ፣ እንደ ልብ እንዳይንቀሳቀስ እንደሚያግደው የአካል ጉዳት አድርገህ መመልከትህ ከእሱ በምትጠብቀው ነገር ረገድ ማስተካከያ እንድታደርግ ይረዳሃል