በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

“ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን በድፍረት” ተናገሩ

“ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን በድፍረት” ተናገሩ

ጳውሎስና በርናባስ ትሕትና፣ ጽናትና ድፍረት አሳይተዋል

በሐዋርያት ሥራ 14:1-28 ላይ የተመሠረተ

1, 2. ጳውሎስና በርናባስ በልስጥራ በነበሩበት ጊዜ ምን ነገሮች ተከሰቱ?

 በልስጥራ ከፍተኛ ሁካታ ተፈጥሯል። ሁለት ፀጉረ ልውጥ ሰዎች፣ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረን አንድ ሰው ፈውሰዋል፤ ሰውየው ከደስታው የተነሳ እየዘለለ ነው። ሕዝቡ በጣም ተገርሟል፤ አንድ የዙስ ካህን፣ ሕዝቡ እንደ አማልክት ለቆጠራቸው ለእነዚህ ሁለት ሰዎች የአበባ ጉንጉን ይዞ መጣ። ካህኑ በሬዎች አምጥቶ ለመሥዋዕት ማዘገጃጀት ጀመረ። ጳውሎስና በርናባስ ይህን ሲያዩ እየጮኹ ድርጊቱን አጥብቀው ተቃወሙ። ልብሳቸውን ቀድደው እየሮጡ ሕዝቡ መሃል ገቡ፤ እንዳያመልኳቸው ይማጸኗቸውም ጀመር፤ ያም ሆኖ ሕዝቡ ይህን እንዳያደርግ ያስጣሉት በብዙ ችግር ነበር።

2 ከዚያም ተቃዋሚ የሆኑ አይሁዳውያን ከጵስድያዋ አንጾኪያና ከኢቆንዮን መጡ። የሐሰት ወሬ በማስወራትም የልስጥራን ሕዝብ አእምሮ መረዙ። ጳውሎስንና በርናባስን ካላመለክናቸው ብለው ግብ ግብ የገጠሙት ሰዎች አሁን ጳውሎስን ከበቡት፤ ራሱን እስኪስት ድረስም በድንጋይ ወገሩት። ንዴታቸውን ከተወጡበት በኋላ የቆሳሰለውን ጳውሎስን ከከተማዋ አውጥተው ጣሉት፤ ይህንም ያደረጉት የሞተ መስሏቸው ነበር።

3. በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 ለመሆኑ ሁኔታው ወደዚህ ያመራው እንዴት ነው? በዘመናችን ያሉ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪዎች ስለ በርናባስ፣ ስለ ጳውሎስና እንደ እስስት ተለዋዋጭ ስለነበረው የልስጥራ ሕዝብ ከሚገልጸው ዘገባ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ? በርናባስና ጳውሎስ “ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን በድፍረት እየተናገሩ” አገልግሎታቸውን በጽናት አከናውነዋል፤ ታዲያ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የእነሱን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?—ሥራ 14:3

“ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው” ሰዎች “አማኞች ሆኑ” (የሐዋርያት ሥራ 14:1-7)

4, 5. ጳውሎስና በርናባስ ወደ ኢቆንዮን የሄዱት ለምን ነበር? እዚያስ ምን አጋጠማቸው?

4 ከጥቂት ቀናት በፊት ጳውሎስና በርናባስ የሮማውያን ከተማ በሆነችው በጵስድያዋ አንጾኪያ ስደት ተነስቶባቸው ነበር፤ ተቃዋሚ የሆኑ አይሁዳውያን ከከተማዋ አባረሯቸው። ይሁንና የከተማዋ ነዋሪዎች መልእክቱን ስላልተቀበሏቸው ተስፋ አልቆረጡም፤ ከዚህ ይልቅ “የእግራቸውን አቧራ አራግፈው . . . ሄዱ።” (ሥራ 13:50-52፤ ማቴ. 10:14) አዎ፣ ጳውሎስና በርናባስ በሰላም አካባቢውን ለቅቀው ወጡ፤ ለሚደርስባቸው ነገር ተጠያቂዎቹ ራሳቸው መሆናቸውን ለተቃዋሚዎቻቸው በመግለጽ ፍርዱን ለአምላክ ትተው ተሰናበቱ። (ሥራ 18:5, 6፤ 20:26) ሁለቱ ሚስዮናውያን ደስ እያላቸው የስብከት ጉዟቸውን ቀጠሉ። በስተ ደቡብ ምሥራቅ 150 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጓዙ፤ ከዚያም በቶረስና በሱልጣን የተራራ ሰንሰለቶች መካከል ወደሚገኝ ለም የሆነ አምባ ደረሱ።

5 ጳውሎስና በርናባስ መጀመሪያ የሄዱት ወደ ኢቆንዮን ነው፤ ኢቆንዮን የግሪክ ባሕል ማዕከል ነች፤ የሮም አውራጃ በሆነችው በገላትያ ካሉት ዋና ዋና ከተሞችም አንዷ ናት። a በዚህች ከተማ ውስጥ፣ ተሰሚነት ያላቸው ብዙ አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች ይኖሩ ነበር። ጳውሎስና በርናባስም እንደ ልማዳቸው ወደ ምኩራብ ገብተው መስበክ ጀመሩ። (ሥራ 13:5, 14) “በዚያም ጥሩ ንግግር ስለሰጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያንና ግሪካውያን አማኞች ሆኑ።”—ሥራ 14:1

6. ጳውሎስና በርናባስ ውጤታማ አስተማሪዎች ሊሆኑ የቻሉት ለምንድን ነው? እኛስ የእነሱን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

6 ጳውሎስና በርናባስ የሰጡት ንግግር ውጤታማ የነበረው ለምንድን ነው? ጳውሎስ የካበተ የቅዱሳን መጻሕፍት እውቀት ነበረው። ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች፣ ከትንቢቶችና ከሙሴ ሕግ ላይ በዘዴ እያጣቀሰ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ያሳምን ነበር። (ሥራ 13:15-31፤ 26:22, 23) የበርናባስ አነጋገር ደግሞ ለሰዎች ያለውን ልባዊ አሳቢነት በግልጽ የሚያሳይ ነበር። (ሥራ 4:36, 37፤ 9:27፤ 11:23, 24) ሁለቱም በራሳቸው ማስተዋል ከመታመን ይልቅ “ከይሖዋ ባገኙት ሥልጣን” ይናገሩ ነበር። አንተስ በምትሰብክበት ጊዜ እነዚህ ሚስዮናውያን የተዉትን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነገሮች በማድረግ ነው፦ የአምላክን ቃል ጠንቅቀህ እወቅ፤ አድማጮችህን ይበልጥ ሊማርኩ የሚችሉ ጥቅሶችን ምረጥ፤ የምትሰብክላቸውን ሰዎች ልታጽናና የምትችልባቸውን መንገዶች ፈልግ፤ እንዲሁም የምታስተምረው ትምህርት በራስህ ጥበብ ሳይሆን ምንጊዜም በይሖዋ ቃል ላይ የተመሠረተ ይሁን።

7. (ሀ) የምሥራቹ መልእክት ምን ውጤት ያስከትላል? (ለ) በምሥራቹ ምክንያት በቤተሰብህ መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ ከሆነ ምን ማስታወስ ይኖርብሃል?

7 ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ በተናገሩት ነገር የተደሰቱት ሁሉም የኢቆንዮን ነዋሪዎች አይደሉም። ሉቃስ “ያላመኑት አይሁዳውያን ከአሕዛብ ወገን የሆኑትን ሰዎች በማነሳሳት በወንድሞች ላይ ጥላቻ እንዲያድርባቸው አደረጉ” በማለት ዘግቧል። ሆኖም ጳውሎስና በርናባስ በዚያ መቆየትና ለምሥራቹ ጥብቅና መቆም እንዳለባቸው ስለተገነዘቡ “በድፍረት እየተናገሩ በኢቆንዮን ረዘም ላለ ጊዜ ቆዩ።” ከዚህም የተነሳ “የከተማዋ ሕዝብ ተከፋፈለ፤ አንዳንዶቹ ከአይሁዳውያን ጎን ሲቆሙ ሌሎቹ ደግሞ ከሐዋርያት ጎን ቆሙ።” (ሥራ 14:2-4) በዛሬው ጊዜም የምሥራቹ መልእክት ተመሳሳይ ውጤት ያስከትላል። ለአንዳንዶች የአንድነት ኃይል ይሆናል፤ ለሌሎች ደግሞ የክፍፍል ምክንያት ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 10:34-36) ለምሥራቹ መልእክት ታዛዥ በመሆንህ ምክንያት በቤተሰብህ መካከል መከፋፈል ተፈጥሮ ይሆን? ከሆነ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ተቃውሞ የሚነሳው ባልተጨበጠ መረጃ ወይም አንዳንዶች ስም ለማጥፋት ብለው በሚያናፍሱት ወሬ የተነሳ መሆኑን አስታውስ። የምታሳየው መልካም ምግባር ለእንዲህ ዓይነቱ ተቃውሞ ማርከሻ ነው፤ ውሎ አድሮ የሚቃወሙህን ሰዎች ልብ ሊያለሰልስ ይችላል።—1 ጴጥ. 2:12፤ 3:1, 2

8. ጳውሎስና በርናባስ ኢቆንዮንን ለቅቀው የሄዱት ለምንድን ነው? እነሱ ከተዉት ምሳሌስ ምን እንማራለን?

8 ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በኢቆንዮን ያሉት ተቃዋሚዎች ጳውሎስንና በርናባስን ለመውገር ሴራ ጠነሰሱ። እነዚህ ሁለት ሚስዮናውያን ይህን ሲሰሙ ወደ ሌላ የአገልግሎት ክልል ለመሄድ ወሰኑ። (ሥራ 14:5-7) በዛሬው ጊዜ ያሉ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎችም ተመሳሳይ የሆነ የጥበብ እርምጃ ይወስዳሉ። ሰዎች የቃላት ጥቃት ሲሰነዝሩብን በድፍረት ምላሽ እንሰጣለን። (ፊልጵ. 1:7፤ 1 ጴጥ. 3:13-15) የኃይል ጥቃት የመሰንዘር አዝማሚያ እንዳለ ካስተዋልን ግን የራሳችንንም ሆነ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ነገር አናደርግም።—ምሳሌ 22:3

‘ሕያው የሆነውን አምላክ አምልኩ’ (የሐዋርያት ሥራ 14:8-19)

9, 10. ልስጥራ የምትገኘው የት ነበር? ስለ ከተማዋ ነዋሪዎችስ ምን የምናውቀው ነገር አለ?

9 ጳውሎስና በርናባስ ከኢቆንዮን በስተ ደቡብ ምዕራብ 30 ኪሎ ሜትር ገደማ ተጉዘው ልስጥራ ደረሱ፤ ልስጥራ የሮማውያን ቅኝ ግዛት የሆነች ከተማ ነች። ከጵስድያዋ አንጾኪያ ጋር ብዙ የሚያመሳስላት ነገር ቢኖርም በዚህች ከተማ ውስጥ ብዙ አይሁዳውያን አልነበሩም። የከተማዋ ነዋሪዎች ግሪክኛ መናገር ሳይችሉ አይቀሩም፤ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ግን የሊቃኦንያ ቋንቋ ነበር። በከተማዋ ውስጥ ምኩራብ ስለሌለ ሳይሆን አይቀርም ጳውሎስና በርናባስ በአደባባይ መስበክ ጀመሩ። ጴጥሮስ በኢየሩሳሌም፣ ሲወለድ ጀምሮ የአካል ጉዳተኛ የነበረ አንድ ሰው ፈውሷል። በዚህ ተአምር የተነሳም እጅግ ብዙ ሰዎች አማኝ ሆነው ነበር። (ሥራ 3:1-10) ጳውሎስ ደግሞ በልስጥራ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ሽባ የሆነ አንድ ሰው ፈውሷል። (ሥራ 14:8-10) ይሁን እንጂ ይህ ተአምር ያስገኘው ውጤት በኢየሩሳሌም ከተፈጸመው ተአምር ፈጽሞ የተለየ ነው።

10 የልስጥራ ነዋሪዎች አረማውያን አማልክትን የሚከተሉ ነበሩ፤ በመሆኑም በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ እንደተጠቀሰው ሽባ የነበረው ሰው ዘሎ ሲራመድ ባዩ ጊዜ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ደረሱ። በርናባስን የአማልክት አለቃ በሆነው በዙስ ስም ጠሩት፤ ጳውሎስን ደግሞ ሄርሜስ አሉት፤ ሄርሜስ የዙስ ልጅና የአማልክት ቃል አቀባይ ነው። (“ ልስጥራ እንዲሁም የዙስና የሄርሜስ አምልኮ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) ይሁን እንጂ በርናባስና ጳውሎስ ሕዝቡ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ አልፈለጉም፤ የተናገሩትም ሆነ ተአምር የፈጸሙት ብቸኛው እውነተኛ አምላክ በሆነው በይሖዋ ሥልጣን እንጂ አማልክት ስለሆኑ እንዳልሆነ ለማሳመን ቆርጠው ነበር።—ሥራ 14:11-14

‘እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን ሕያው አምላክ አምልኩ።’—የሐዋርያት ሥራ 14:15

11-13. (ሀ) ጳውሎስና በርናባስ ለልስጥራ ነዋሪዎች ምን ብለው ተናገሩ? (ለ) ጳውሎስና በርናባስ ከተናገሩት ነገር የምናገኘው አንዱ ትምህርት ምንድን ነው?

11 የሕዝቡ ያልተጠበቀ ምላሽ ከፍተኛ ትርምስ ፈጥሯል፤ ጳውሎስና በርናባስ ግን በዚህ ወቅትም እንኳ የአድማጮቻቸውን ልብ ለመንካት የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት አድርገዋል። ሉቃስ ያሰፈረው ይህ ዘገባ ምሥራቹን ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች መስበክ የሚቻልበትን ውጤታማ ዘዴ ያስተምረናል። ጳውሎስና በርናባስ የአድማጮቻቸውን ልብ ለመንካት ምን እንዳሉ ልብ በል፦ “እናንተ ሰዎች፣ እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን። ምሥራቹን እያወጅንላችሁ ያለነውም እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ ሰማይን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ የፈጠረውን ሕያው አምላክ እንድታመልኩ ነው። ባለፉት ትውልዶች፣ ሕዝቦች ሁሉ በራሳቸው መንገድ እንዲሄዱ ፈቀደላቸው፤ ይሁንና ለራሱ ምሥክር ከማቅረብ ወደኋላ አላለም፤ ከሰማይ ዝናብ በማዝነብና ፍሬያማ ወቅቶችን በመስጠት እንዲሁም የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባችሁን በደስታ በመሙላት መልካም ነገር አድርጓል።”—ሥራ 14:15-17

12 እኛስ ከዚህ ልብ የሚነካ አነጋገር ምን ትምህርት እናገኛለን? በመጀመሪያ ደረጃ ጳውሎስና በርናባስ፣ ራሳቸውን ከአድማጮቻቸው የተሻሉ አድርገው እንዳልቆጠሩ እናያለን። ያልሆኑትን ሆነው ለመታየት አልሞከሩም። ከዚህ ይልቅ እነሱም አረማዊ እንደሆኑት አድማጮቻቸው ሁሉ ድክመቶች እንዳሉባቸው በትሕትና ገለጹ። እውነት ነው፣ ጳውሎስና በርናባስ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፤ ደግሞም ከሐሰት ትምህርቶች ነፃ ወጥተዋል። ከክርስቶስ ጋር የመግዛት ተስፋም ተሰጥቷቸዋል። ይሁንና የልስጥራ ነዋሪዎችም ክርስቶስን ከታዘዙ እነዚህኑ ስጦታዎች ማግኘት እንደሚችሉ ተገንዝበው ነበር።

13 እኛስ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ምን ዓይነት አመለካከት አለን? ከእኛ ጋር እኩል እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን? በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት እንዲማሩ ሌሎችን በምንረዳበት ጊዜ የተለየ ውዳሴ እንዲቸረን ባለመፈለግ የጳውሎስንና የበርናባስን ምሳሌ እንከተላለን? የተዋጣለት አስተማሪ የሆነው ቻርልስ ቴዝ ራስል በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል፤ ራስል በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃና በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይመራ ነበር። ሆኖም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእኛም ሆነ ለምናዘጋጃቸው ጽሑፎች ሙገሳና ውዳሴ መቀበል አንፈልግም፤ ‘አባ’ ወይም ‘ረቢ’ ተብለን መጠራትም አንፈልግም።” አዎ፣ ወንድም ራስል ልክ እንደ ጳውሎስና በርናባስ ትሑት ነበር። እኛም የምንሰብከው ለራሳችን ክብር ለማምጣት ሳይሆን ሰዎች ‘ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲያመልኩ’ ለመርዳት ነው።

14-16. ጳውሎስና በርናባስ ለልስጥራ ነዋሪዎች ከተናገሩት ነገር የምናገኘው ሁለተኛና ሦስተኛ ትምህርት ምንድን ነው?

14 ከዚህ ንግግር የምናገኘውን ሁለተኛ ትምህርት ደግሞ እስቲ እንመልከት። ጳውሎስና በርናባስ አቀራረባቸውን እንደ ሁኔታው ያስተካክሉ ነበር። የልስጥራ ነዋሪዎች፣ በኢቆንዮን እንዳሉት አይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎች አይደሉም፤ ስለ ቅዱሳን መጻሕፍትም ሆነ አምላክ ከእስራኤል ብሔር ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ይሁንና ጳውሎስንና በርናባስን ያዳምጧቸው የነበሩት እነዚህ ሰዎች በግብርና ሙያ የሚተዳደሩ ነበሩ። ልስጥራ ምቹ የሆነ የአየር ጠባይና ለም መሬት የታደለች ነበረች። በመሆኑም ነዋሪዎቿ የፈጣሪን ግሩም ባሕርይ ለማየት የሚያስችል ሰፊ አጋጣሚ ነበራቸው፤ ለምሳሌ ፍሬያማ የሆኑ ወቅቶችና በዙሪያቸው ያሉ ሌሎች ነገሮች ስለ ፈጣሪ የሚያስተምሯቸው ነገሮች አሉ፤ ሚስዮናውያኑም አድማጮቻቸው እንዲያመዛዝኑ ለመርዳት ይህን በጋራ የሚያስማማ ነጥብ ጠቅሰዋል።—ሮም 1:19, 20

15 እኛስ አቀራረባችንን እንደ ሁኔታው ለመለወጥ ጥረት እናደርጋለን? አንድ ገበሬ አንድ ዓይነት ዘር በተለያዩ ማሳዎች ላይ ሊዘራ ይችላል፤ መሬቱን ለማለስለስ የሚጠቀምበትን ዘዴ ግን እንደየሁኔታው መቀያየር ይኖርበታል። አንዳንዱ መሬት ቀድሞውንም ቢሆን የለሰለሰና ሊዘራበት የሚችል ይሆናል። ሌላው ደግሞ ለማለስለስ ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በተመሳሳይ እኛም የምንዘራው ዘር አንድ ዓይነት ነው፤ እሱም በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘው የመንግሥቱ መልእክት ነው። ይሁን እንጂ ጳውሎስና በርናባስ እንዳደረጉት ሁሉ የምንሰብክላቸውን ሰዎች ሁኔታና ሃይማኖት ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን። ከዚያም የመንግሥቱን መልእክት በምንናገርበት ጊዜ እነዚህን ነገሮች ግምት ውስጥ እናስገባለን።—ሉቃስ 8:11, 15

16 ስለ ጳውሎስና በርናባስ እንዲሁም ስለ ልስጥራ ነዋሪዎች ከሚናገረው ዘገባ የምናገኘው ሦስተኛ ትምህርትም አለ። የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ የዘራነው ዘር ተነጥቆ ሊወሰድ ወይም ድንጋያማ መሬት ላይ ሊወድቅ ይችላል። (ማቴ. 13:18-21) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ተስፋ መቁረጥ የለብንም። በኋላ ላይ ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት ደቀ መዛሙርት የሰጠውን ማሳሰቢያ እናስታውስ፤ የአምላክን ቃል የምናወያየውን ግለሰብ ጨምሮ “እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለአምላክ መልስ እንሰጣለን።”—ሮም 14:12

“ለይሖዋ አደራ ሰጧቸው” (የሐዋርያት ሥራ 14:20-28)

17. ጳውሎስና በርናባስ ከደርቤ ተነስተው ወዴት ሄዱ? ለምንስ?

17 ሕዝቡ ጳውሎስን ከልስጥራ እየጎተቱ ካወጡትና የሞተ መስሏቸው ትተውት ከሄዱ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ መጥተው ከበቡት፤ በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ተነስቶ ወደ ከተማዋ በመግባት በዚያ አደረ። በማግስቱ ጳውሎስና በርናባስ 100 ኪሎ ሜትር ርቃ ወደምትገኘው ወደ ደርቤ አቀኑ። ይህ አድካሚ ጉዞ ጳውሎስን ምን ያህል እንዳሠቃየው መገመት አያዳግትም፤ በድንጋይ የተወገረው ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት ስለሆነ ገና ቁስለኛ ነው። ያም ሆኖ እሱም ሆነ በርናባስ ምንም ነገር ጉዟቸውን እንዲያስተጓጉልባቸው አልፈቀዱም፤ ደርቤ በደረሱም ጊዜ “በርካታ ደቀ መዛሙርት [አፈሩ]።” ከዚያም መኖሪያቸው ወደሆነችው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ በአቋራጭ ከመመለስ ይልቅ “ወደ ልስጥራ፣ ወደ ኢቆንዮንና ወደ [ጵስድያዋ] አንጾኪያ ተመለሱ።” ይህን ያደረጉት ለምን ነበር? “በእምነት ጸንተው እንዲኖሩ በማበረታታት ደቀ መዛሙርቱን [ለማጠናከር]” ነበር። (ሥራ 14:20-22) በእርግጥም እነዚህ ሁለት ወንድሞች ግሩም ምሳሌ ይሆኑናል! ከራሳቸው ምቾት ይልቅ የጉባኤውን ጥቅም አስቀድመዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችና ሚስዮናውያን እነሱ የተዉትን ምሳሌ ይከተላሉ።

18. ሽማግሌዎች የሚሾሙት እንዴት ነው?

18 ጳውሎስና በርናባስ በቃልና ምሳሌ በመሆን ደቀ መዛሙርቱን ከማበረታታት ባሻገር “በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው።” ይህን የሚስዮናዊነት ጉዞ የጀመሩት “በመንፈስ ቅዱስ ተልከው” ቢሆንም ሽማግሌዎቹን ‘ለይሖዋ አደራ የሰጧቸው’ ጾመውና ጸልየው ነው። (ሥራ 13:1-4፤ 14:23) ዛሬም ያለው አሠራር ተመሳሳይ ነው። የሽማግሌዎች አካል አንድ ወንድም እንዲሾም ሐሳብ ከማቅረቡ በፊት፣ ሽማግሌዎቹ ወንድም ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ በጸሎት ይገመግማሉ። (1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9፤ ያዕ. 3:17, 18፤ 1 ጴጥ. 5:2, 3) ዋነኛው መመዘኛ ግለሰቡ በእውነት ቤት የቆየበት ጊዜ አይደለም። ግለሰቡ የመንፈስ ቅዱስን አመራር ምን ያህል ይከተላል የሚለውን የሚያሳየው አነጋገሩ፣ ምግባሩና በሌሎች ዘንድ ያተረፈው ስም ነው። የበላይ ተመልካቾች ሊያሟሏቸው የሚገቡ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሰፈሩ ብቃቶችን ካሟላ የመንጋው እረኛ ሆኖ ለማገልገል ብቁ ይሆናል። (ገላ. 5:22, 23) ከዚያም የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ሽማግሌ አድርጎ ይሾመዋል።—ከ1 ጢሞቴዎስ 5:22 ጋር አወዳድር።

19. ሽማግሌዎች ስለ ምን ነገር ተጠያቂዎች እንደሆኑ ያውቃሉ? የጳውሎስንና የበርናባስን ምሳሌ መከተል የሚችሉትስ እንዴት ነው?

19 የተሾሙ ሽማግሌዎች ጉባኤውን የሚይዙበትን መንገድ በተመለከተ በአምላክ ፊት ተጠያቂዎች እንደሆኑ ያውቃሉ። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች እንደ ጳውሎስና በርናባስ ሁሉ በስብከቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት ይካፈላሉ። የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በቃል ያበረታታሉ። ደግሞም ምንጊዜም ከራሳቸው ምቾት ይልቅ የጉባኤውን ጥቅም ለማስቀደም ፈቃደኞች ናቸው።—ፊልጵ. 2:3, 4

20. ወንድሞቻችን በታማኝነት ስላከናወኗቸው ሥራዎች የሚገልጹ ተሞክሮዎችን ማንበባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

20 በመጨረሻም ጳውሎስና በርናባስ ወደ መኖሪያቸው ወደ ሶርያዋ አንጾኪያ ተመለሱ፤ እዚያ ላሉት ወንድሞች “አምላክ በእነሱ አማካኝነት ያከናወናቸውን በርካታ ነገሮች እንዲሁም ለአሕዛብ የእምነትን በር እንደከፈተላቸው ተረኩ።” (ሥራ 14:27) እኛም ክርስቲያን ወንድሞቻችን በታማኝነት ስላከናወኑት ሥራ ማንበባችንና ይሖዋ ጥረታቸውን እንዴት እንደባረከ ማየታችን ‘ከይሖዋ ባገኘነው ሥልጣን በድፍረት መናገራችንን’ እንድንቀጥል ያበረታታናል።

a ኢቆንዮን—የፍርግያውያን ከተማ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።