በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ለምን አስፈለገ?

መጽሐፍ ቅዱስን መመርመር ለምን አስፈለገ?

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ታውቃለህ? በታሪክ ዘመናት ሁሉ የዚህን አስደናቂ መጽሐፍ ያህል በስፋት የተሰራጨ ሌላ መጽሐፍ የለም። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው መልእክት በየትኛውም ባሕል ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች መጽናኛና ተስፋ ሰጥቷቸዋል፤ መጽሐፉ የሚሰጠው ምክርም በዕለታዊ ሕይወታቸው ጠቅሟቸዋል። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ያላቸው እውቀት ውስን ነው። አንተም ሃይማኖተኛ ሰው ሆንክም አልሆንክ፣ ስለዚህ መጽሐፍ የማወቅ ጉጉት ይኖርህ ይሆናል። ይህ ብሮሹር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት አጠቃላይ ይዘት ማወቅ እንድትችል ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ከመጀመርህ በፊት ስለዚህ መጽሐፍ የተወሰኑ ነገሮችን ማወቅህ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ቅዱሳን መጻሕፍት በመባልም የሚታወቅ ሲሆን የመጽሐፉ የመጀመሪያ ክፍል ከሆነው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ የዮሐንስ ራእይ እስከሚባለው እስከ መጨረሻው ክፍል ድረስ 66 መጻሕፍትን ይዟል።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ምንጭ ማን ነው? ይህ ትኩረት የሚስብ ጥያቄ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት ከ1,600 ዓመታት በሚበልጥ ጊዜ ውስጥ በኖሩ 40 የሚያህሉ ሰዎች ነው። የሚገርመው ነገር ግን እነዚያ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ምንጭ እንደሆኑ አልተናገሩም። ከጸሐፊዎቹ አንዱ “ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው” በማለት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16) ሌላው ጸሐፊ ደግሞ “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ተናገረ፤ ቃሉ በአንደበቴ ላይ ነበረ” ብሏል። (2 ሳሙኤል 23:2) ከዚህ ለመመልከት እንደምንችለው ጸሐፊዎቹ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው መልእክት ምንጭ የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ተናግረዋል። ጸሐፊዎቹ እንደገለጹት አምላክ፣ ሰዎች ወደ እሱ እንዲቀርቡ ይፈልጋል።

መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ሌላም አስፈላጊ የሆነ ነገር አለ። የቅዱሳን መጻሕፍት አጠቃላይ ጭብጥ አንድ ሲሆን ይኸውም አምላክ በሰማይ ባቋቋመው መንግሥቱ አማካኝነት የሰው ዘርን የመግዛት መብቱ መረጋገጡ ነው። ይህ ጭብጥ ከዘፍጥረት እስከ ራእይ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ውስጥ በሙሉ እንዴት እንደተገለጸ በሚቀጥሉት ርዕሶች ላይ መመልከት ትችላለህ።

ከላይ የተገለጹትን ነጥቦች በአእምሮህ በመያዝ በዓለም ላይ ካሉት መጻሕፍት ሁሉ ይበልጥ ታዋቂ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን መልእክት እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።

^ አን.9 ዘመን የሚገለጽባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። በዚህ ብሮሹር ላይ ዓ.ዓ. (ዓመተ ዓለም) ሲባል ከክርስቶስ ልደት በፊት ያለውን ዘመን ያመለክታል፤ ዓ.ም. (ዓመተ ምሕረት) ሲባል ደግሞ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለውን ዘመን ያመለክታል። በየገጾቹ ግርጌ ላይ ከሚገኘው የዘመናትን ቅደም ተከተል የሚያሳይ መስመር ይህንን መመልከት ትችላለህ።