በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 12

ለሕይወት መመሪያ የሚሆን አምላካዊ ጥበብ

ለሕይወት መመሪያ የሚሆን አምላካዊ ጥበብ

የምሳሌ መጽሐፍ ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን መመሪያ የሚሆን በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የተጻፈ ምክር የተሰባሰበበት ጥራዝ ነው፤ የዚህን መጽሐፍ አብዛኛውን ክፍል የጻፈው ሰለሞን ነው

ይሖዋ ጥበበኛ ገዥ ነው? ለዚህ ጥያቄ በማያሻማ መልኩ መልስ ማግኘት የሚቻልበት አንዱ መንገድ እሱ የሚሰጠውን ምክር መመርመር ነው። ይሖዋ የሚሰጠው ምክር ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው? ምክሩን በሥራ ላይ ማዋል ይበልጥ ትርጉም ያለውና የተሻለ ሕይወት ለመምራት ይረዳል? ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሳሌዎችን ጽፏል። እነዚህ ምሳሌዎች ሁሉንም የሕይወት ዘርፍ የሚዳስሱ ናቸው ለማለት ይቻላል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

በአምላክ መተማመን። ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረት በእሱ መተማመን ወሳኝ ነገር ነው። ሰለሞን እንደሚከተለው በማለት ጽፏል፦ “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” (ምሳሌ 3:5, 6) የይሖዋን አመራር በመሻትና እሱን በመታዘዝ በአምላክ መተማመናችን ሕይወታችን ይበልጥ ትርጉም ያለው እንዲሆን ያደርጋል። አንድ ሰው እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ መከተሉ የአምላክን ልብ ደስ የሚያሰኝ ከመሆኑም ሌላ የይሖዋ ጠላት የሆነው ሰይጣን ላነሳቸው አከራካሪ ጉዳዮች መልስ ለመስጠት ያስችላል።—ምሳሌ 27:11

ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት በጥበብ መመላለስ። አምላክ ለባሎች፣ ለሚስቶችና ለልጆች የሰጠው ምክር ከምንጊዜውም ይበልጥ ዛሬ ወቅታዊ ነው። አምላክ “በልጅነት ሚስትህም ደስ ይበልህ” በማለት ባል ለሚስቱ ታማኝ እንዲሆን ይመክራል። (ምሳሌ 5:18-20) ያገቡ ሴቶች ደግሞ የባሏንና የልጆቿን አድናቆት ስላተረፈች አንዲት ባለሞያ ሚስት የሚገልጽ ግሩም ሐሳብ በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ያገኛሉ። (ምሳሌ ምዕራፍ 31) ልጆችም ወላጆቻቸውን እንዲታዘዙ የሚያሳስብ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። (ምሳሌ 6:20) በተጨማሪም አንድ ሰው ራሱን ማግለሉ ራስ ወዳድ ወደ መሆን ስለሚመራው ከሌሎች ጋር ወዳጅነት መመሥረት አስፈላጊ መሆኑን የምሳሌ መጽሐፍ ይጠቁማል። (ምሳሌ 18:1) ጓደኞች በጎም ሆነ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ስለሚችሉ ወዳጆቻችንን በጥበብ መምረጥ ያስፈልገናል።—ምሳሌ 13:20፤ 17:17

ጥበበኛ በመሆን ራሳችንን መንከባከብ። የምሳሌ መጽሐፍ የአልኮል መጠጥን ከመጠን በላይ ከመጠጣት እንድንቆጠብ፣ ለጤናችን የሚበጁ ባሕርያትን እንድናዳብርና ጎጂ የሆኑትን እንድናስወግድ እንዲሁም ታታሪ ሠራተኛ እንድንሆን የሚያበረታቱ በዋጋ የማይተመኑ ጠቃሚ ምክሮችን ይዟል። (ምሳሌ 6:6፤ 14:30፤ 20:1) ከአምላክ መመሪያዎች ጋር በማይስማሙ ሰብዓዊ ምክሮች መታመን ወደ ጥፋት እንደሚመራ ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 14:12) “የሕይወት ምንጭ” ልብ መሆኑን በማሳሰብ ውስጣዊ ማንነታችንን ማለትም ልባችንን ሊበክሉ ከሚችሉ ተጽዕኖዎች እንድንጠብቅ ይመክረናል።—ምሳሌ 4:23

በመላው ዓለም የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደነዚህ ባሉት ምክሮች መመራት የተሻለ ሕይወት እንደሚያስገኝ ተገንዝበዋል። በዚህም ምክንያት ይሖዋን እንደ ገዥያቸው አድርገው ለመቀበል በቂ ምክንያት እንዳላቸው ይሰማቸዋል።

በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ።