በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 25

እምነትን፣ ምግባርንና ፍቅርን በተመለከተ የተሰጠ ምክር

እምነትን፣ ምግባርንና ፍቅርን በተመለከተ የተሰጠ ምክር

ያዕቆብ፣ ጴጥሮስ፣ ዮሐንስና ይሁዳ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ለማበረታታት ደብዳቤዎች ጻፉ

ያዕቆብ እና ይሁዳ የኢየሱስ ወንድሞች ናቸው። ጴጥሮስና ዮሐንስ ደግሞ ከኢየሱስ 12 ሐዋርያት መካከል ናቸው። እነዚህ አራት ሰዎች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙ ሰባት ደብዳቤዎችን ጽፈዋል። እያንዳንዱ ደብዳቤ የሚጠራው በጸሐፊው ስም ነው። እነዚህ ሰዎች በመንፈስ መሪነት በጻፏቸው ደብዳቤዎች ውስጥ የሚገኘውን ማሳሰቢያ የሰጡት ክርስቲያኖች ለይሖዋና ለመንግሥቱ ታማኝ እንዲሆኑ ለመርዳት አስበው ነው።

ክርስቲያኖች እምነት ሊያሳዩ ይገባል። ክርስቲያኖች እምነት እንዳላቸው መግለጻቸው ብቻውን በቂ አይደለም። እውነተኛ እምነት ለተግባር ያነሳሳል። ያዕቆብ እንደጻፈው ‘እምነት ያለ ሥራ የሞተ ነው።’ (ያዕቆብ 2:26) አንድ ክርስቲያን ፈተናዎች ሲያጋጥሙት በእምነት እርምጃ መውሰዱ ጽናትን እንዲያዳብር ይረዳዋል። በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆን ከፈለገ ጥበብ እንዲሰጠው አምላክን መለመን ያስፈልገዋል፤ በሚጸልይበት ጊዜ ግን መጠራጠር የለበትም። መጽናት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኛል። (ያዕቆብ 1:2-6, 12) አንድ የይሖዋ አገልጋይ በእምነት ንጹሕ አቋሙን ጠብቆ ከተመላለሰ አምላክም አይተወውም። ያዕቆብ “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ብሏል።—ያዕቆብ 4:8

አንድ ክርስቲያን የሚያጋጥሙትን ፈተናዎችና ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽም የሚደረጉበትን ተጽዕኖዎች ለመቋቋም እንዲችል ጠንካራ እምነት መገንባት ያስፈልገዋል። ይሁዳ፣ በወቅቱ ተስፋፍቶ የነበረውን መጥፎ ሥነ ምግባር በመመልከት ክርስቲያን ባልንጀሮቹ ‘ለእምነት ብርቱ ተጋድሎ እንዲያደርጉ’ አሳስቧቸዋል።—ይሁዳ 3

ክርስቲያኖች ንጹሕ ምግባር ሊኖራቸው ይገባል። ይሖዋ፣ አምላኪዎቹ ቅዱስ እንዲሆኑ ማለትም በሁሉም የሕይወታቸው ዘርፎች ንጹሕ እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እናንተም ራሳችሁ በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ፤ ምክንያቱም ‘እኔ [ይሖዋ] ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ልትሆኑ ይገባል’ ተብሎ ተጽፏል።” (1 ጴጥሮስ 1:15, 16) በዚህ ረገድ ክርስቲያኖች ሊከተሉት የሚችሉት ጥሩ አርዓያ አላቸው። ጴጥሮስ “ክርስቶስም . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ለእናንተ መከራ ተቀብሏል” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 2:21) ክርስቲያኖች በአምላክ መሥፈርቶች በመመራታቸው መከራ ሊደርስባቸው ቢችልም “ጥሩ ሕሊና” ይኖራቸዋል። (1 ጴጥሮስ 3:16, 17) ክርስቲያኖች የአምላክን የፍርድ ቀን እንዲሁም ይሖዋ ቃል የገባውን ‘ጽድቅ የሰፈነበት’ አዲስ ዓለም መምጣት ሲጠባበቁ ቅዱስ ሥነ ምግባር እንዲከተሉና ለአምላክ ያደሩ መሆናቸውን የሚያሳዩ ተግባሮችን እንዲፈጽሙ ጴጥሮስ አሳስቧቸዋል።—2 ጴጥሮስ 3:11-13

“ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።” ያዕቆብ 4:8

ክርስቲያኖች ፍቅር ሊያሳዩ ይገባል። ዮሐንስ “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት ጽፏል። አምላክ “ለኃጢአታችን . . . መሥዋዕት እንዲሆን” ኢየሱስን በመላክ ለሰው ዘር ያለውን ታላቅ ፍቅር እንዳሳየ ሐዋርያው ጠቁሟል። ታዲያ ክርስቲያኖች ለዚህ ፍቅር ምን ምላሽ መስጠት ይኖርባቸዋል? ዮሐንስ እንዲህ ብሏል፦ “የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ አምላክ የወደደን በዚህ መንገድ ከሆነ እኛም እርስ በርሳችን የመዋደድ ግዴታ አለብን።” (1 ዮሐንስ 4:8-11) እንዲህ ያለውን ፍቅር ማንጸባረቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ ለእምነት ባልንጀሮቻችን የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት ነው።—3 ዮሐንስ 5-8

ይሁንና የይሖዋ አምላኪዎች ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንዴት ማሳየት ይችላሉ? ዮሐንስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጠናል፦ “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነውና፤ ትእዛዛቱ ደግሞ ከባዶች አይደሉም።” (1 ዮሐንስ 5:3፤ 2 ዮሐንስ 6) በዚህ መንገድ አምላክን የሚታዘዙ ሰዎች ‘የዘላለም ሕይወትን’ ተስፋ በማድረግ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጡ መኖር እንደሚችሉ ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል።—ይሁዳ 21

በያዕቆብ፤ በ1 ጴጥሮስ፤ በ2 ጴጥሮስ፤ በ1 ዮሐንስ፤ በ2 ዮሐንስ፤ በ3 ዮሐንስ እንዲሁም በይሁዳ መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ።