በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበለጠ ነፃነት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

የበለጠ ነፃነት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 3

የበለጠ ነፃነት ማግኘት የምችለው እንዴት ነው?

“ወላጆቼ ወደተለያዩ ቦታዎች ብቻዬን እንድሄድ ቢፈቅዱልኝ ደስ ይለኝ ነበር።”—ሣራ፣ 18

“ከጓደኞቼ ጋር አንድ ቦታ መሄድ እንደምፈልግ ለወላጆቼ ስነግራቸው እምነት እንደማይጥሉብኝ አስተውያለሁ። ምክንያታቸው ምን እንደሆነ ስጠይቃቸው አብዛኛውን ጊዜ የሚሰጡኝ መልስ ‘አንቺን እናምንሻለን፤ የማናምነው ጓደኞችሽን ነው’ የሚል ነው።”—ክሪስቲን፣ 18

አንተም እንደ ሣራና ክሪስቲን፣ ወላጆችህ የበለጠ ነፃነት እንዲሰጡህ ትመኛለህ? የበለጠ ነፃነት ማግኘት እንድትችል ወላጆችህ እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ አለብህ። የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ ገንዘብ ከማግኘት ጋር ይመሳሰላል። ገንዘብ ማግኘት ከባድ ቢሆንም በቀላሉ ልናጣው እንችላለን፤ ደግሞም የቱንም ያህል ብዙ ገንዘብ ቢኖረን በቂ እንደሆነ ላይሰማን ይችላል። የ16 ዓመቷ ኢልያና እንዲህ ብላለች፦ “አንድ ቦታ መሄድ እንደምፈልግ ለወላጆቼ ስነግራቸው የጥያቄ መዓት ያዥጎደጉዱብኛል። የት እንደምሄድ፣ ከእነማን ጋር እንደምሄድ፣ ሄጄ ምን እንደማደርግና መቼ እንደምመለስ ይጠይቁኛል። ወላጆቼ ቢሆኑም እንኳ እንዲህ በጥያቄ ሲያጣድፉኝ ያበሳጨኛል!”

ወላጆችህ ይበልጥ እምነት እንዲጥሉብህና ተጨማሪ ነፃነት እንዲሰጡህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት፣ አመኔታ ማትረፍ በርካታ ወላጆችና ልጆች ብዙውን ጊዜ የማይስማሙበት ጉዳይ የሆነው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

እንደ አዋቂ ለመቆጠር የሚደረገው ትግል

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው ከአባቱና ከእናቱ እንደሚለይ’ ይገልጻል። (ዘፍጥረት 2:24) የጉርምስና ዕድሜ ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች፣ አዋቂ ሆነው ከቤት ሲወጡ ወይም የራሳቸውን ቤተሰብ መምራት ሲጀምሩ ለሚኖራቸው ኃላፊነት ብቁ እንዲሆኑ የሚዘጋጁበት ወሳኝ ወቅት ነው። *

ይሁን እንጂ ሙሉ ሰው ወደ መሆን መሸጋገር፣ የተወሰነ ዕድሜ ላይ ስትደርስ ዘው ብለህ እንደምትገባበት በር አይደለም፤ በሌላ አባባል የሆነ ዕድሜ ላይ ስትደርስ ድንገት አዋቂ ሰው ትሆናለህ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልክ ደረጃ እንደ መውጣት ቀስ በቀስ የሚከናወን ሂደት ነው፤ የጉርምስናን ዕድሜ እስክታልፍ ድረስ ደረጃውን አንድ በአንድ ትወጣዋለህ። እርግጥ ነው፣ ምን ያህል ደረጃ ወጥተሃል ይኸውም ምን ያህል እድገት አድርገሃል በሚለው ጉዳይ ላይ ከወላጆችህ ጋር ላትግባቡ ትችላላችሁ። በጓደኛ ምርጫ ረገድ ወላጆቿ እምነት እንደማይጥሉባት የሚሰማት ማሪያ “20 ዓመቴ ቢሆንም አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ አንስማማም” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ መጥፎ ሁኔታ ቢያጋጥመኝ ራሴን ለመጠበቅ የሚያስችል ጥንካሬ እንደሌለኝ ይሰማቸዋል። ከአሁን በፊት እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞኝ እንደሚያውቅና ራሴን መጠበቅ እንደቻልኩ ብነግራቸውም እምነት ሊጥሉብኝ አልቻሉም!”

ማሪያ ከተናገረችው ሐሳብ ማየት እንደሚቻለው አመኔታ የማትረፍ ጉዳይ በወጣቶችና በወላጆች መካከል ከፍተኛ ውጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። በአንተና በወላጆችህ መካከል እንዲህ ያለ ሁኔታ እንዳለ ይሰማሃል? ከሆነ ወላጆችህ የበለጠ እምነት እንዲጥሉብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ተገቢ ያልሆነ ነገር በማድረግህ የወላጆችህን አመኔታ አጥተህ ከሆነ ደግሞ እንደገና እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

እምነት የሚጣልብህ መሆንህን በተግባር አሳይ

ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖች “ማንነታችሁን ለማወቅ ራሳችሁን ዘወትር ፈትኑ” በማለት ጽፎላቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 13:5) ስለዚህ አንድ ሰው ራሱን ከፈተነ በኋላ ማንነቱን ማወቅ እንዲሁም ለሌሎች በተግባሩ ማሳየት ይችላል። ጳውሎስ ይህን ሐሳብ በዋነኝነት የጻፈው በጉርምስና የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ መሠረታዊ ሥርዓቱ ለወጣቶችም ይሠራል። የምታገኘው ነፃነት አብዛኛውን ጊዜ የተመካው እምነት የሚጣልብህ በመሆንህ ላይ ነው። ይህ ሲባል ግን ፍጹም መሆን አለብህ ማለት አይደለም። ደግሞም የማይሳሳት ሰው የለም። (መክብብ 7:20) ይሁንና በጥቅሉ ሲታይ፣ ወላጆችህ በአንተ ላይ እምነት እንዳይጥሉ የሚያደርግ ባሕርይ አለህ?

ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን]” በማለት ጽፏል። (ዕብራውያን 13:18) እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘የት እንደምሄድ እንዲሁም ምን እንደማደርግ ስጠየቅ እውነቱን እንደምናገር ወላጆቼ ያውቃሉ?’ በዚህ ረገድ ራሳቸውን በሐቀኝነት ከመረመሩ በኋላ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባቸው የተሰማቸው አንዳንድ ወጣቶች የሰጡትን ሐሳብ ተመልከት። እነዚህ ወጣቶች የሰጡትን ሐሳብ ካነበብክ በኋላ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት ሞክር።

ሎሪ፦ “ከአንድ የምወደው ልጅ ጋር በሚስጥር ኢ-ሜይል እጻጻፍ ነበር። ወላጆቼ ይህን ሲያውቁ እንዳቆም ነገሩኝ። እኔም ከልጁ ጋር መጻጻፌን እንደማቆም ቃል ገባሁላቸው፤ ይሁን እንጂ ቃሌን መጠበቅ አልቻልኩም። እንደገና ከልጁ ጋር መልእክት ስላላክ ወላጆቼ ይደርሱብኛል፤ ከዚያም ለጥፋቴ ይቅርታ እጠይቅና ዳግመኛ ይህን ላለማድረግ ቃል እገባለሁ። እንደዚያም ሆኖ መጻጻፌን አላቆምም። ሁኔታው በዚህ መልኩ ለአንድ ዓመት ቀጠለ። በመሆኑም ወላጆቼ በእኔ ላይ ጨርሶ እምነት መጣል የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደረሱ!”

የሎሪ ወላጆች፣ በልጃቸው ላይ እምነት መጣል ያልቻሉት ለምን ይመስልሃል? ․․․․․

አንተ በሎሪ ወላጆች ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ለምን? ․․․․․

ሎሪ፣ ወላጆቿ ችግሩን አስመልክተው ለመጀመሪያ ጊዜ ካነጋገሯት በኋላ እምነት የሚጣልባት መሆኗን ለማሳየት ምን ማድረግ ነበረባት? ․․․․․

ቤቨርሊ፦ “ወላጆቼ ከወንዶች ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ እምነት ሊጥሉብኝ እንደሚችሉ አይሰማቸውም ነበር፤ አሁን ሳስበው ግን ትክክል ነበሩ። በሁለት ዓመት ከሚበልጡኝ ሁለት ወንዶች ጋር አላግባብ እቀራረብ ነበር። በተጨማሪም ከእነሱ ጋር ለረጅም ሰዓታት በስልክ አወራለሁ፤ እንዲሁም ግብዣ በሚኖርበት ጊዜ ከእነዚህ ልጆች ጋር ካልሆነ በስተቀር ከማንም ጋር አልጫወትም ማለት ይቻላል። ወላጆቼ ለአንድ ወር ያህል ስልኬን የወሰዱብኝ ሲሆን እነዚህ ልጆች ወደሚኖሩበት ማንኛውም ቦታ እንዳልሄድ ከለከሉኝ።”

አንተ በቤቨርሊ ወላጆች ቦታ ብትሆን ኖሮ ምን ታደርግ ነበር? ለምን? ․․․․․

የቤቨርሊ ወላጆች በእሷ ላይ አንዳንድ ገደቦችን መጣላቸው ተገቢ ይመስልሃል? እንዲህ ያልከው ለምንድን ነው? ․․․․․

ቤቨርሊ የወላጆቿን አመኔታ መልሳ ለማግኘት ምን ማድረግ ትችላለች? ․․․․․

እንደገና አመኔታ ማትረፍ

ከላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ሁሉ አንተም በፈጸምከው ድርጊት የተነሳ የወላጆችህን አመኔታ አጥተህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህም እንኳ ወላጆችህ እንደገና እምነት እንዲጥሉብህ ማድረግ እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

እምነት ሊጣልብህ የሚችል መሆንህን በተደጋጋሚ ባሳየህ መጠን ወላጆችህም ይበልጥ እምነት ሊጥሉብህና ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡህ ይችላሉ። አኔት ይህ እውነት መሆኑን ከጊዜ በኋላ ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “በሌሎች ዘንድ አመኔታ ማትረፍ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ልጅ እያለሁ ሙሉ በሙሉ አይገባኝም ነበር። አሁን ከቀድሞው የበለጠ ኃላፊነት የሚሰማኝ ሰው ሆኛለሁ፤ በየትኛውም የሕይወቴ ክፍል በወላጆቼ ዘንድ ያለኝን አመኔታ የሚያሳጣኝ ነገር ላለማድረግ መጠንቀቅ እንዳለብኝ ይሰማኛል።” ታዲያ ከዚህ ምን ትማራለህ? ወላጆችህ እምነት ስላልጣሉብህ ከማማረር ይልቅ እምነት የሚጣልብህ ሰው በመሆን ረገድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ተጨማሪ ነፃነት ማግኘትህ አይቀርም።

ለምሳሌ ያህል፣ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ነገሮች ረገድ እምነት የሚጣልብህ ነህ? ማሻሻያ ማድረግ በሚያስፈልግህ ነጥቦች ላይ ✔ አድርግ።

□ በተባልኩት ሰዓት ቤት መግባት

□ ቃሌን መጠበቅ

□ ሰዓት ማክበር

□ ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም

□ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን

□ ያለ ጎትጓች ከእንቅልፌ መነሳት

□ ክፍሌን በንጽሕና መያዝ

□ እውነት መናገር

□ የስልክና የኮምፒውተር አጠቃቀም

□ ስህተትን ማመንና ይቅርታ መጠየቅ

□ ሌላ ․․․․․

ምልክት ባደረግህባቸው ነገሮች ረገድ ማሻሻያ በማድረግ እምነት የሚጣልብህ ሰው እንደሆንክ ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች በተግባር ለማዋል ጥረት አድርግ፦ “ከቀድሞ አኗኗራችሁ ጋር የሚስማማውን . . . አሮጌውን ስብዕናችሁን አውልቃችሁ መጣል አለባችሁ።” (ኤፌሶን 4:22) ቃላችሁ ‘አዎ ከሆነ አዎ ይሁን።’ (ያዕቆብ 5:12) “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ።” (ኤፌሶን 4:25) “በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ።” (ቆላስይስ 3:20) የምታደርገው እድገት ወላጆችህን ጨምሮ ለሰው ሁሉ እያደር መታየቱ አይቀርም።1 ጢሞቴዎስ 4:15

ይሁንና የቻልከውን ያህል ጥረት ብታደርግም ወላጆችህ የሚገባህን ያህል ነፃነት እንዳልሰጡህ ቢሰማህስ? ስለ ጉዳዩ ለምን አታነጋግራቸውም? ‘ለምን አታምኑኝም’ ብለህ ቅሬታ ከማሰማት ይልቅ የእነሱን አመኔታ ለማትረፍ ምን ማድረግ እንደሚጠበቅብህ በአክብሮት ጠይቃቸው። እንዲሁም በዚህ ረገድ ምን ለማድረግ እንዳቀድህ ንገራቸው።

ወላጆችህ በአንተ ላይ የጣሉትን ገደብ ወዲያውኑ እንዲያነሱልህ አትጠብቅ። ወላጆችህ ቃልህን ትጠብቅ እንደሆነ ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ጥርጥር የለውም። በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመህ እምነት የሚጣልብህ መሆንህን አሳይ። ውሎ አድሮ ወላጆችህ ከበፊቱ የበለጠ እምነት ሊጥሉብህ እና ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጡህ ይችላሉ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ቤቨርሊም ይህን ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “የሌሎችን አመኔታ ማትረፍ ከባድ ቢሆንም በቀላሉ ልናጣው የምንችለው ነገር ነው። አሁን ወላጆቼ እምነት እየጣሉብኝ በመሆኑ ደስ ብሎኛል!”

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 22 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወላጆችህ ተፋትተዋል? በዚህ ምክንያት ሁሉ ነገር ሲተረማመስብህ ሚዛንህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 7⁠ን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ነፃነታችሁን . . . ለክፋት መሸፈኛ አታድርጉት።”—1 ጴጥሮስ 2:16

ጠቃሚ ምክር

ራስህን ከታላቅ ወንድምህ ወይም እህትህ ጋር በማወዳደር እነሱ የበለጠ ነፃነት እንደተሰጣቸው ከማሰብ ይልቅ ልጅ ሳለህ ያልነበረህንና አሁን ያገኘኸውን ነፃነት ለማሰብ ሞክር።

ይህን ታውቅ ነበር?

ወላጆች፣ ለልጆቻቸው ገደብ የለሽ ነፃነት መስጠታቸው ለእነሱ ግድ እንደሌላቸው እንጂ እንደሚወዷቸው የሚያሳይ አይደለም።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በእነዚህ ነገሮች ረገድ ይበልጥ እምነት የሚጣልብኝ ለመሆን እጥራለሁ፦ ․․․․․

የወላጆቼን አመኔታ ባጣ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● እምነት የሚጣልብህ መሆንህን ለማሳየት የቻልከውን ያህል ጥረት ብታደርግም ወላጆችህ የበለጠ ነፃነት ሊሰጡህ የማይፈልጉት ለምን ሊሆን ይችላል?

● ወላጆችህን የምታነጋግርበት መንገድ የበለጠ ነፃነት እንዲሰጡህ ሊያደርጋቸው የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ከወላጆቼ ጋር ሳወራ፣ ያጋጠሙኝን ችግሮችና የሚያሳስቡኝን ነገሮች በግልጽ እነግራቸዋለሁ። እንዲህ ማድረጌ የእነሱን አመኔታ ለማትረፍ እንደረዳኝ ይሰማኛል።”—ዳያና

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

እምነት የሚጣልበት ሙሉ ሰው ወደ መሆን መሸጋገር፣ ልክ ደረጃ እንደ መውጣት ቀስ በቀስ የሚከናወን ሂደት ነው፤ የጉርምስናን ዕድሜ እስክታልፍ ድረስ ደረጃውን አንድ በአንድ ትወጣዋለህ

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሙሉ ሰው

ጉርምስና

ልጅነት