በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወላጆቼ እንደገና ቢያገቡ ሁኔታውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ወላጆቼ እንደገና ቢያገቡ ሁኔታውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 5

ወላጆቼ እንደገና ቢያገቡ ሁኔታውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

እናትህ በሠርጓ ቀን በደስታ ተውጣለች። * አንተ ግን እናትህ እንደገና በማግባቷ በጣም ከፍቶሃል! እንዲህ የተሰማህ እናትህ ማግባቷ ከአባትህ ጋር እንደሚታረቁ የነበረህን ተስፋ ስላጨለመብህ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ እናትህ ያገባችው አባትህ ከሞተ ብዙም ሳይቆይ ከሆነ ነገሩ የበለጠ ስሜትህን ሊጎዳው ይችላል።

እናትህ እንደገና ስታገባ ምን ተሰማህ?

የአንተን ስሜት በሚገልጸው ሐሳብ ላይ ✔ አድርግ።

□ ደስ አለኝ

□ ስጋት አደረብኝ

□ እንደተረሳሁ ተሰማኝ

□ በእንጀራ አባቴ ቀናሁ

□ የእንጀራ አባቴን ስለወደድኩት ወላጅ አባቴን እንደከዳሁት ተሰማኝ

ወላጅ አባትህን እንደከዳኸው ያሰብከው የእሱን ቦታ ለእንጀራ አባትህ እንደሰጠኸው ስለተሰማህ ሊሆን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፣ ከላይ ከተጠቀሱት ስሜቶች አንዳንዶቹ በውስጥህ የሚሰማህን ሥቃይ ለማስታገስ ስትል ጎጂ የሆኑ ድርጊቶች እንድትፈጽም ያደርጉህ ይሆናል።

ለምሳሌ ያህል፣ ሁልጊዜ የእንጀራ አባትህን የሚያበሳጭ ነገር ታደርግ ይሆናል። እንዲያውም እናትህንና የእንጀራ አባትህን በማጣላት እንዲለያዩ ለማድረግ ትሞክር ይሆናል። ይሁንና ጥበብ የተንጸባረቀበት አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ቤተ ሰቡን የሚያውክ ሰው ነፋስን ይወርሳል” በማለት እንዲህ ያለ ድርጊት ምንም ትርፍ እንደሌለው ይገልጻል። (ምሳሌ 11:29) አንተም በዚህ ወጥመድ እንዳትወድቅ ተጠንቀቅ። ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ሳታደርግ የሚሰማህን የስሜት ሥቃይ መቋቋም ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችልባቸውን አንዳንድ መንገዶች እስቲ እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ የእንጀራ አባትህን ሥልጣን መቀበል

ወላጅ አባትህ ያልሆነን ሰው ሥልጣን መቀበል ቀላል አይደለም። የእንጀራ አባትህ አንድ ነገር እንድታደርግ ሲጠይቅህ ‘አንተ’ኮ አባቴ አይደለህም!’ ለማለት ይቃጣህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት መልስ በመስጠትህ ለጊዜው አንጀትህ ይርስ ይሆናል፤ ሆኖም ይህን ማድረግህ ብስለት እንደጎደለህ የሚጠቁም ነው።

በሌላ በኩል ግን የእንጀራ አባትህን ሥልጣን መቀበልህ “በአስተሳሰባችሁ የበሰላችሁ ሁኑ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር እንደተከተልክ የሚያሳይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 14:20 የ1980 ትርጉም) የእንጀራ አባትህ የወላጅ አባትህን ኃላፊነት እየተወጣ ስለሆነ ልታከብረው እንደሚገባ ጥርጥር የለውም።—ምሳሌ 1:8፤ ኤፌሶን 6:1-4

ብዙውን ጊዜ የእንጀራ አባትህ የሚቀጣህ ስለሚወድህ እና ስለሚያስብልህ ነው። (ምሳሌ 13:24) ኢቮን የተባለች የ18 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የእንጀራ አባቴ ተግሣጽ ይሰጠናል፤ ደግሞም ይህ ማንኛውም አባት የሚያደርገው ነገር ነው። እሱ ምክር ሲሰጠኝ ቅር መሰኘት፣ ባለፉት ዓመታት ሁሉ ለእኛ የሚያስፈልገውን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ነገር በማቅረብ ያደረገልንን እንክብካቤ ከምንም አለመቁጠር እንደሆነ ይሰማኛል። ይህ ደግሞ ምስጋና ቢስ መሆን ነው።”

ያም ቢሆን ቅር እንድትሰኝ የሚያደርግ በቂ ምክንያት ይኖርህ ይሆናል። እንዲህ ከሆነ በቆላስይስ 3:13 ላይ ያለውን “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” የሚለውን ሐሳብ ተግባራዊ በማድረግ ‘በሳል’ መሆንህን አሳይ።

የእንጀራ አባትህ ካሉት መልካም ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹን ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

የእንጀራ አባትህ ስላሉት መልካም ባሕርያት ማሰብህ ይበልጥ እንድታከብረው ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

․․․․․

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ ያለህን ማካፈልና እሺ ባይ መሆን

አሮን የተባለ የ24 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ከእናቴ ሌላ ሁለት ጊዜ አግብቷል። በመሆኑም አባቴ እንደገና ባገባ ቁጥር ከእንጀራ እናቶቼና ከልጆቻቸው ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት ከብዶኝ ነበር። መጀመሪያ ላይ እነዚህ ሰዎች ለእኔ እንግዳ ነበሩ፤ ያም ቢሆን ልወዳቸው እንደሚገባ ይነገረኝ ስለነበር ምን እንደማደርግ ግራ ግብት ብሎኝ ነበር።”

አንተም በዚህ ረገድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ የቤቱ ትልቅ ልጅ ወይም ብቸኛ ልጅ በመሆንህ ይሰጥህ የነበረውን ቦታ ታጣ ይሆናል። ምናልባት ለረጅም ጊዜ እንደ ቤቱ አባወራ ሆነህ ቆይተህ ይሆናል፤ አሁን ግን ይህን ቦታ ለእንጀራ አባትህ መልቀቅ ይኖርብሃል። ወይም ደግሞ እንደ ኢቮን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል። ኢቮን እንዲህ ብላለች፦ “ወላጅ አባቴ እናቴን ዞር ብሎ አይቷት አያውቅም፤ በመሆኑም ከእኔ ጋር ብዙ ጊዜ ታሳልፍ ነበር። የእንጀራ አባቴ ግን እናቴን በደንብ ይንከባከባት ጀመር። አብረው ጊዜ የሚያሳልፉ ከመሆኑም ሌላ ይጨዋወቱ ስለነበር እናቴን እንደቀማኝ ሆኖ ተሰማኝ። ውሎ አድሮ ግን አመለካከቴን ማስተካከል ቻልኩ።”

አንተም እንደ ኢቮን አመለካከትህን ማስተካከል የምትችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚል ምክር ይሰጣል። (ፊልጵስዩስ 4:5) ‘ምክንያታዊነት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ‘እሺ ባይ መሆን’ የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን መብቴ ካልተከበረ ብሎ ድርቅ አለማለት የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (1) ያለፉትን ነገሮች እያሰብክ አትብሰልሰል። (መክብብ 7:10) (2) ያለህን ነገር ለእንጀራ አባትህ እና ለልጆቹ ለማካፈል ፈቃደኛ ሁን። (1 ጢሞቴዎስ 6:18) (3) እንደ ቤተሰብህ አድርገህ ተመልከታቸው።

ከላይ ከተጠቀሱት ነጥቦች መካከል ይበልጥ ልትሠራበት የምትፈልገው የትኛውን ነው? ․․․․․

ተፈታታኝ ሁኔታ 3፦ አድልዎ እንደተደረገብህ ሲሰማህ

ታራ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የእንጀራ አባቴ የራሱን ልጆች ከእኔና ከእህቴ በጣም አስበልጦ ይወዳቸዋል። የሚወዱትን ማንኛውንም ምግብ ይገዛላቸዋል፤ እንዲሁም የፈለጉትን ፊልም ይከራይላቸዋል። እነሱን ለማስደሰት ሲል የማያደርግላቸው ነገር የለም።” እንደዚህ ዓይነት አድልዎ እንደተደረገብህ ሲሰማህ ሊከብድህ እንደሚችል የታወቀ ነው። ታዲያ ሁኔታውን ለመቋቋም ምን ሊረዳህ ይችላል? የእንጀራ አባትህ አንተን ከራሱ ልጆች እኩል የማያይህ ለምን ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት ሞክር። ይህ የሆነው የሥጋ ዝምድና ስላላቸው ሳይሆን አብረው ብዙ ነገር በማሳለፋቸው ሊሆን ይችላል። አንተም ብትሆን ከእንጀራ አባትህ ይልቅ ወላጅ አባትህን መቅረብ እንደሚቀልህ የታወቀ ነው።

ይሁን እንጂ የእንጀራ አባትህ ለሁሉም ልጆች ተመሳሳይ ነገር አላደረገም ማለት አዳልቷል ማለት ላይሆን ይችላል። እያንዳንዱ ልጅ የየራሱ ባሕርይ ያለው ሲሆን የሚያስፈልገውም ነገር ይለያያል። ስለዚህ የእንጀራ አባትህ ከልጆቹ እኩል እንዳልያዘህ በማሰብ ከመብከንከን ይልቅ የሚያስፈልጉህን ነገሮች ለማሟላት ምን ያህል ጥረት እያደረገ እንደሆነ ለመመልከት ሞክር።

የእንጀራ አባትህ የትኞቹን የሚያስፈልጉህን ነገሮች ያሟላልሃል?

․․․․․

የእንጀራ አባትህ የትኞቹን ነገሮች እንዳላሟላልህ ይሰማሃል?

․․․․․

አንዳንድ የሚያስፈልጉህ ነገሮች እንዳልተሟሉልህ ከተሰማህ ጉዳዩን ለእንጀራ አባትህ ለምን አታነሳለትም?

ትዕግሥት ይክሳል!

ብዙውን ጊዜ የእንጀራ አባትህና ልጆቹ ከአንተ ቤተሰብ ጋር ተቀላቅለው በመካከላችሁ መተማመን እስኪሰፍን እንዲሁም አንዳችሁ ሌላውን እንደ ቤተሰብ መመልከት እስክትጀምሩ ድረስ ዓመታት ሊወስድባችሁ ይችላል። የቤተሰቡ አባላት እያንዳንዳቸው የተለያዩ ባሕርያት ወይም ልማዶች ይኖሯቸዋል፤ ውሎ አድሮ ግን እነዚህን ነገሮች አጣጥመው ተስማምተው መኖር ይችላሉ። ስለዚህ ትዕግሥተኛ ሁን! ከአዲሶቹ የቤተሰባችሁ አባላት ጋር ወዲያውኑ እንደምትዋደዱ ወይም እንደ ቤተሰብ መተያየት እንደምትጀምሩ አትጠብቅ።

ቶማስ እናቱ እንደገና ስታገባ ጭንቅ ብሎት ነበር። እናቱ አራት ልጆች ያሏት ሲሆን የእንጀራ አባቱ ደግሞ ሦስት ልጆች ነበሩት። ቶማስ “እርስ በርስ እንጣላ፣ እንጨቃጨቅ፣ እንበጣበጥና እንኮራረፍ ነበር” በማለት ጽፏል። ታዲያ ስምምነት መፍጠር የቻሉት እንዴት ነው? ቶማስ “የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ስናደርግ ለችግሮቻችን መፍትሔ ማግኘት ቻልን” በማለት ተናግሯል።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ከገዛ ወንድሞችህና እህቶችህ ጋር ተስማምተህ መኖር ቢከብድህ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል።”—መክብብ 7:8

ጠቃሚ ምክር

ተቃራኒ ፆታ ካላቸው የእንጀራ አባትህ ልጆች ጋር መኖር ስትጀምር ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ተፈታታኝ ሁኔታ ሊገጥማችሁ ይችላል። በመሆኑም የፆታ ስሜት የሚያነሳሱ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ እንዳይመጡ ተጠንቀቅ፤ እንዲሁም አለባበስህም ሆነ የምታደርጋቸው ነገሮች የፆታ ስሜት የሚቀሰቅሱ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግሃል።

ይህን ታውቅ ነበር?

እናትህ ከሌላ ሰው ጋር ትዳር ስትመሠርት ከሁኔታው ጋር ለመላመድ የምትቸገረው አንተ ብቻ አይደለህም፤ የእንጀራ አባትህ ልጆችም አዲሱን የቤተሰብ ሕይወት መልመድ ሊከብዳቸው ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የእንጀራ አባቴ ለቤተሰባችን ያደረጋቸውን መልካም ነገሮች በማሰብ ለእሱ የበለጠ አክብሮት ለማዳበር እጥራለሁ (የእንጀራ አባትህ ካደረጋቸው ጥሩ ነገሮች መካከል ሁለቱን ጻፍ)፦ ․․․․․

የእንጀራ አባቴ ልጆች የሚያስከፋኝ ነገር ቢያደርጉ በሮም 12:21 ላይ ያለውን ምክር በመከተል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● የእንጀራ አባትህ ወይም ልጆቹ ከእናንተ ቤተሰብ ጋር ስለ መኖር ሲያስቡ ምን ዓይነት ስጋት ሊያድርባቸው ይችላል?

● ከአዲሱ ቤተሰብህ ጋር በተያያዘ የዛሬን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱንም ጭምር ማሰብህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 38 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እናቴ ለሁለተኛ ጊዜ የመሠረተችው ትዳር አልሰመረም። ሆኖም ከእንጀራ አባቴ ልጆች ጋር እስካሁንም ድረስ በጣም እንቀራረባለን። ከእነሱ ጋር በመተዋወቄ በጣም ደስተኛ ነኝ።”—ታራ

[በገጽ 39 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሁለት ቤተሰቦች አንድ ላይ መኖር ሲጀምሩ የሚኖረው ሁኔታ ውኃንና ሲሚንቶን ከማዋሃድ ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ ይህን ማድረግ ጊዜና ጥረት ቢጠይቅም መጨረሻ ላይ ግን ጠንካራና ምንም የማይበግረው ውህድ መፍጠር ይቻላል

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.3 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል ይህ ምዕራፍ እናት እንደገና ስታገባ ስለሚኖረው ሁኔታ የሚያወሳ ቢሆንም የተጠቀሱት ነጥቦች አባታቸው እንደገና ላገባ ወጣቶችም ይሠራሉ።