በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

ምዕራፍ 7

ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?

“አሁንም የምኖረው ከወላጆቼ ጋር መሆኑ ሰዎች ለእኔ ያላቸው አክብሮት እንዲቀንስ እንደሚያደርግ አንዳንድ ጊዜ ይሰማኛል፤ ራሴን ችዬ መኖር ካልጀመርኩ በቀር እንደ ትልቅ ሰው የሚቆጥሩኝ አይመስልም።”—ኬቲ

“አሁንም ከወላጆቼ ጋር ስለምኖር ሕይወቴን በምፈልገው መንገድ መምራት አልችልም፤ ይህ ደግሞ ያናድደኛል። ከቤት ወጥቼ ራሴን ችዬ ለመኖር አስቤያለሁ።”—ፊዮና

የራስህን ሕይወት ለመምራት የተመኘኸው ከቤት ወጥተህ ለመኖር የሚያስችል ዕድሜ ላይ ከመድረስህ ከረጅም ጊዜ በፊት ሊሆን ይችላል። በእርግጥ እንዲህ ያለው ስሜት ተፈጥሯዊ ነው። ደግሞም በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ላይ እንደተገለጸው አምላክ መጀመሪያውኑም ያሰበው ወጣቶች ሲያድጉ አባታቸውንና እናታቸውን በመተው የራሳቸውን ቤተሰብ እንዲመሠርቱ ነው። (ዘፍጥረት 2:23, 24፤ ማርቆስ 10:7, 8) ይሁንና ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ ነህ? ይህን ለማወቅ ልታስብባቸው የሚገቡ ሦስት አስፈላጊ ጥያቄዎችን ተመልከት። የመጀመሪያው ጥያቄ . . .

ምክንያቴ ምንድን ነው?

እስቲ ከታች የተዘረዘሩትን ሐሳቦች ተመልከት። ከዚያም ከቤት ወጥተህ ራስህን ችለህ ለመኖር እንድታስብ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነህ ከሚሰማህ ጀምሮ እንደ ቅደም ተከተላቸው ደረጃ ስጣቸው።

․․․․․ በቤት ውስጥ ካሉት ችግሮች ለመገላገል

․․․․․ የበለጠ ነፃነት ለማግኘት

․․․․․ ጓደኞቼ የበለጠ እንዲያከብሩኝ ለማድረግ

․․․․․ ጓደኛዬ አብሬው እንድኖር ስለፈለገ

․․․․․ ወደ ሌላ አካባቢ ሄጄ ሰዎችን ለመርዳት

․․․․․ ራሴን ችዬ ለመኖር የሚያስችል ልምድ ለመቅሰም

․․․․․ ወላጆቼ ላይ ሸክም ላለመሆን

․․․․․ ሌላ ․․․․․

ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ ከቤት ለመውጣትና ራስህን ችለህ ለመኖር ብታስብ ስህተት ነው ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ ከቤት ወጥተህ ብቻህን ለመኖር የፈለግህበትን ትክክለኛ ምክንያት ቆም ብለህ ልታስብበት ይገባል። ለምሳሌ ያህል፣ የበለጠ ነፃነት ለማግኘት ብለህ ከቤት ብትወጣ ያልጠበቅከው ነገር ሊያጋጥምህ ይችላል!

በ20 ዓመቷ ለተወሰነ ጊዜ ከቤት ወጥታ የነበረችው ዳንየል ካጋጠማት ነገር ብዙ ተምራለች። እንዲህ ትላለች፦ “ሁላችንም ብንሆን ነፃነታችንን በሆነ መንገድ የሚገድብብን ነገር እንዳለ የታወቀ ነው። ከቤት ወጥተህ ለብቻህ ስትኖር የሥራህ ባሕርይ ወይም የገንዘብ አቅምህ የምትፈልገውን ነገር እንዳታደርግ ሊገድብህ ይችላል።” ለስድስት ወራት ወደ ሌላ አገር ሄዳ የነበረችው ካርመን ደግሞ እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ማግኘቴ ቢያስደስተኝም ለራሴ የሚሆን ጊዜ አልነበረኝም። ቤት ማጽዳት፣ አንዳንድ ነገሮችን መጠገን፣ የግቢውን አትክልት መንከባከብ፣ ልብስ ማጠብ፣ ወለሉን ማጽዳትና እነዚህን የመሳሰሉ የተለመዱ የቤት ውስጥ ሥራዎችን ማከናወን ነበረብኝ።”

ሌሎች ስለገፋፉህ ብቻ ከቤት ለመውጣት አትቸኩል። (ምሳሌ 29:20) ከቤት ለመውጣት እንድታስብ የሚያደርግ አጥጋቢ ምክንያት ቢኖርህም እንኳ ይህ ብቻውን በቂ አይሆንም። ራስህን ችለህ ለመኖር አንዳንድ አስፈላጊ ችሎታዎችን ማዳበር ይኖርብሃል፤ ይህ ደግሞ ወደ ሁለተኛው ጥያቄ ይመራናል። ይህም . . .

ዝግጁ ነኝ?

ራስን ችሎ መኖር አገር ለማየት ከከተማ ራቅ ወዳለ አካባቢ ከመሄድ ጋር ይመሳሰላል። ድንኳን መትከል፣ እሳት ማቀጣጠል፣ ምግብ ማብሰል ወይም ካርታ ማንበብ ሳትችል ወደ ገጠራማ አካባቢ ጉዞ ለማድረግ ትነሳለህ? እንደማታደርገው የታወቀ ነው! ሆኖም ብዙ ወጣቶች በቤት አያያዝ ረገድ በቂ ችሎታ ሳይኖራቸው ከቤት ይወጣሉ።

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል” በማለት ተናግሯል። (ምሳሌ 14:15) ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆን አለመሆንህን ማወቅ እንድትችል ቀጥለው ከቀረቡት ነጥቦች አንጻር ራስህን ገምግም። ከዚያም ከነጥቦቹ መካከል በአግባቡ እንደምትወጣው በሚሰማህ ላይ ✔ አድርግ፤ ማሻሻያ ማድረግ በሚያስፈልግህ ላይ ደግሞ ✘ አድርግ።

የገንዘብ አያያዝ፦ የ19 ዓመቷ ሴሪና እንዲህ ብላለች፦ “ለምንም ነገር ራሴ ከፍዬ አላውቅም። ከቤት ብወጣ ገንዘቤን ለተለያዩ ወጪዎች አብቃቅቼ መኖር ያቅተኛል ብዬ እፈራለሁ።” ታዲያ ስለ ገንዘብ አያያዝ መማር የምትችለው እንዴት ነው?

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ” ይላል። (ምሳሌ 1:5) አንተም አንድ ሰው በየወሩ የቤት ኪራይ ወይም የባንክ ዕዳ ለመክፈል፣ ለምግብ፣ ለመኪና ወጪ ወይም ለመጓጓዣ ምን ያህል እንደሚያስፈልገው ለምን ወላጆችህን አትጠይቃቸውም? ከዚያም ወላጆችህን ባጀት ማውጣትና ገንዘብህን አብቃቅተህ የተለያዩ ወጪዎችህን መሸፈን የምትችለው እንዴት እንደሆነ ጠይቃቸው። *

የቤት አያያዝ፦ የ17 ዓመቱ ብራያን ከቤት ወጥቶ ስለ መኖር ሲያስብ በጣም የሚያስጨንቀው ነገር የራሱን ልብስ ማጠብ እንደሆነ ተናግሯል። አንተስ ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? የ20 ዓመት ወጣት የሆነው አሮን የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ለአንድ ሳምንት ያህል ራስህን ችለህ ለብቻህ እንደምትኖር አድርገህ አስብ። ምግብህን ለመሥራት የሚያስፈልጉህን ነገሮች ገበያ ሄደህ በራስህ ገንዘብ ግዛ፤ ከዚያም ራስህ አብስለው። ልብሶችህን ራስህ አጥበህ ተኩስ። ክፍልህን ራስህ አጽዳ። እንዲሁም የትም ቦታ ስትሄድ ሌሎች እንዲያደርሱህ ወይም እንዲመልሱህ አትጠይቅ።” ይህን ሐሳብ መከተልህ ሁለት ጥቅሞች ያስገኝልሃል፦ (1) ጠቃሚ የሆኑ ችሎታዎችን ለማዳበር ይረዳሃል፤ (2) ወላጆችህ የሚያደርጉልህን ነገር ይበልጥ እንድታደንቅ ያስችልሃል።

ማኅበራዊ ሕይወት፦ ከወላጆችህ እንዲሁም ከወንድሞችህና ከእህቶችህ ጋር ተስማምተህ ትኖራለህ? ካልሆነ ከቤት ብትወጣና ከጓደኛህ ጋር ብትኖር ሕይወት ቀላል እንደሚሆንልህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ የ18 ዓመቷ ኢቭ የተናገረችውን ልብ በል፦ “ሁለት ጓደኞቼ ራሳቸውን ችለው አብረው መኖር ጀመሩ። አንድ ላይ መኖር ከመጀመራቸው በፊት በጣም የሚቀራረቡ ጓደኛሞች የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን ተስማምተው መኖር አቃታቸው። አንደኛዋ ቤቱን በንጽሕናና በሥርዓት የምትይዝ ሲሆን ሌላዋ ግን ዝርክርክ ናት። አንዷ መንፈሳዊ ሰው ስትሆን ሌላዋ ግን እስከዚህም ነበረች። በጭራሽ ሊስማሙ አልቻሉም!”

ታዲያ መፍትሔው ምንድን ነው? የ18 ዓመቷ ኤሪን እንዲህ ብላለች፦ “ከሌሎች ጋር ተስማምተህ መኖር ስለምትችልበት መንገድ ከወላጆችህ ጋር እያለህ ብዙ መማር ትችላለህ። ችግሮችን መፍታትን እንዲሁም ለሰላም ሲባል አንዳንድ ነገሮችን ለመተው ፈቃደኛ መሆንን ልትማር ትችላለህ። ከወላጆቻቸው ጋር የሚፈጠረውን አለመግባባት ለመሸሽ ብለው ከቤት የሚወጡ ወጣቶች አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት እንደሚችሉ አይማሩም፤ ከዚህ ይልቅ ከሌሎች ጋር ሲጋጩ መሸሽ እንደሚቀናቸው ተመልክቻለሁ።”

መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች፦ አንዳንዶች ከቤት የሚወጡት ወላጆቻቸው በሚያከናውኗቸው ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ስለማይፈልጉ ነው። ሌሎች ደግሞ ከቤት ሲወጡ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በማከናወን ረገድ ያላቸውን ፕሮግራም ይዘው ለመቀጠል ቢያስቡም ብዙም ሳይቆይ ይህን ማድረግ ያቅታቸዋል። ታዲያ እምነትህ “ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ” እንዳይጠፋ ምን ማድረግ ትችላለህ? *1 ጢሞቴዎስ 1:19

ይሖዋ አምላክ፣ ሁላችንም የምናምንበትን ነገር ራሳችን መርምረን እንድናረጋግጥ ይፈልጋል። (ሮም 12:1, 2) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን የምታጠናበትና ሌሎች መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የምታከናውንበት ጥሩ ፕሮግራም ይኑርህ፤ እንዲሁም ይህን ፕሮግራም በጥብቅ ተከተል። መንፈሳዊ ነገሮችን የምታከናውንበትን ፕሮግራም በቀን መቁጠሪያህ ላይ ጻፍ፤ ከዚያም ያለ ወላጆችህ ጉትጎታ ለአንድ ወር ያህል ይህን ፕሮግራም መከተል ትችል እንደሆነ ራስህን ፈትን።

ልታስብበት የሚገባው ሦስተኛው ጥያቄ ደግሞ . . .

ግቤ ምንድን ነው?

ራስህን ችለህ ለመኖር የፈለግከው ቤት ውስጥ ካሉ ችግሮች ለመገላገል ወይም ከወላጆችህ ቁጥጥር ነፃ ለመውጣት ነው? ከሆነ ትኩረት ያደረግከው ትተኸው እየሄድክ ባለኸው ላይ እንጂ ከፊት ለፊትህ በሚጠብቅህ ነገር ላይ አይደለም። እንዲህ ማድረግ መኪና ስታሽከረክር በኋላ መመልከቻ መስታወት እያየህ ለመንዳት ከመሞከር ጋር ይመሳሰላል፤ ትኩረትህ ሁሉ ያረፈው ትተኸው በምትሄደው ነገር ላይ በመሆኑ ከፊት ለፊትህ ሊያጋጥምህ የሚችለው ነገር አይታይህም። ከዚህ የምታገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ከወላጆችህ ቤት ስለ መውጣት ብቻ ከማሰብ ይልቅ ከዚያ በኋላ ስለምታደርገው ነገር በግልጽ የተቀመጠ ግብ ይኑርህ።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች በአገራቸው ውስጥ ወይም በሌሎች አገሮች የአምላክን ቃል ለመስበክ ሲሉ ከቤተሰቦቻቸው ተለይተው ሄደዋል። ሌሎች ደግሞ የአምልኮ ቦታዎችን በመገንባቱ ሥራ ለመካፈል ወይም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ለማገልገል ሲሉ ከቤት ይወጣሉ። ትዳር ከመመሥረታቸው በፊት ለተወሰነ ጊዜ ከቤት ወጥተው ለብቻቸው መኖር እንዳለባቸው የሚሰማቸውም አሉ። *

ያወጣኸው ግብ ምንም ይሁን ምን ውሳኔ ላይ ከመድረስህ በፊት በደንብ አስብበት። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “የትጕህ ሰው ዕቅድ ወደ ትርፍ ያመራል፤ ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል” ይላል። (ምሳሌ 21:5) ወላጆችህ የሚሰጡህን ምክር አዳምጥ። (ምሳሌ 23:22) ስለ ጉዳዩ ጸልይ። ውሳኔ ላይ ከመድረስህ በፊት ከላይ የተወያየንባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ከግምት አስገባ።

በእርግጥም ልታስብበት የሚገባው ጥያቄ ‘ራሴን ችዬ ለመኖር ደርሻለሁ?’ የሚል ሳይሆን ‘የራሴን ቤት ለማስተዳደር ዝግጁ ነኝ?’ የሚል ሊሆን ይገባል። ለሁለተኛው ጥያቄ የምትሰጠው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ ራስህን ችለህ ለመኖር ደርሰሃል ማለት ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.23 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 19 ተመልከት።

^ አን.27 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 34 እና 35 ተመልከት።

^ አን.32 በአንዳንድ ባሕሎች ልጆች በተለይም ሴቶች አግብተው እስኪወጡ ድረስ ከወላጆቻቸው ጋር መኖራቸው የተለመደ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በቀጥታ የሚናገረው ሐሳብ የለም።

ቁልፍ ጥቅስ

“ሰው ከአባትና ከእናቱ ይለያል።”—ማቴዎስ 19:5

ጠቃሚ ምክር

ብቻህን ብትኖር ለምግብ፣ ለቤት ኪራይና ለሌሎች ነገሮች በየወሩ ልታወጣ የምትችለውን ገንዘብ ለተወሰነ ጊዜ ለወላጆችህ ስጣቸው። ከወላጆችህ ጋር ሳለህ እነዚህን ወጪዎች መሸፈን ካልቻልክ ወይም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ካልሆንክ ራስህን ችለህ ለመኖር ዝግጁ አይደለህም ማለት ነው።

ይህን ታውቅ ነበር?

ከቤት ለመውጣት የተነሳሳህበት ምክንያት ራስህን ችለህ መኖር በምትጀምርበት ወቅት ደስተኛ በመሆንህ ወይም ባለመሆንህ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ራሴን ችዬ መኖር የምፈልገው የሚከተለው ግብ ላይ ለመድረስ ነው፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በቤተሰባችሁ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ቢኖርም ለተወሰነ ጊዜ ከወላጆችህ ጋር መኖርህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

● ከወላጆችህ ጋር ስትኖር ቤተሰብህን የሚጠቅም ብሎም ራስህን ችለህ ለምትኖርበት ጊዜ የሚያዘጋጅህ ነገር ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 52 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ራስን ችሎ ለመኖር መፈለግ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ከቤት ለመውጣት የፈለግከው ከወላጆችህ ቁጥጥር ነፃ ለመውጣት ከሆነ ይህ ራስህን ችለህ ለመኖር እንዳልደረስክ የሚያሳይ ነው።”—አሮን

[በገጽ 50 እና 51 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ራስን ችሎ መኖር አገር ለማየት ከከተማ ራቅ ወዳለ አካባቢ ከመሄድ ጋር ይመሳሰላል፤ ጉዞ ከመጀመርህ በፊት አንዳንድ አስፈላጊ ችሎታዎችን ማዳበር ይኖርብሃል