በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 9

ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ካረን ግብዣው ቦታ ከደረሰች አሥር ደቂቃ እንኳ ሳይሞላ ሁለት ወጣቶች የተሸፈነ ነገር ይዘው ገቡ። የያዙት ነገር ምን እንደሆነ ለማወቅ ያን ያህል አልተቸገረችም። ቀደም ሲል እነዚሁ ልጆች በግብዣው ላይ መጠጥ እንደ ልብ እንደሚኖር ሲናገሩ ጆሮዋ ጥልቅ ብሎ ነበር።

በድንገት “አንቺ፣ ምን ሆነሽ ነው እዚህ የተገተርሺው? አታስደብሪና!” የሚል ድምፅ ከኋላዋ ሰማች። ካረን ዘወር ስትል ጓደኛዋ ጄሲካ ሁለት የተከፈቱ ቢራዎች ይዛ ቆማለች። ከዚያም አንዱን ቢራ እየሰጠቻት “ለመጠጣት አልደረስኩም እንዳትዪኝ ደግሞ!” አለቻት።

ካረን ቢራውን መቀበል አልፈለገችም። ያም ሆኖ ጫናው ካሰበችው በላይ ከበዳት። ካረን፣ ደባሪ መባል አልፈለገችም። በዚያ ላይ ጄሲካ ጓደኛዋ ናት፤ እንዲሁም ጥሩ ከሚባሉት ልጆች አንዷ ነች። በመሆኑም ካረን ‘ታዲያ እሷ ከጠጣች እኔስ ብጠጣ ምናለበት? ደግሞም ቢራ መጠጣት ያን ያህል የሚካበድ ነገር አይደለም፤ ዕፅ ውሰጂ ወይም የፆታ ብልግና ፈጽሚ አላለችኝ’ ብላ አሰበች።

ወጣቶች የተለያዩ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ብዙውን ጊዜ ፈተናዎቹ ከተቃራኒ ፆታ ጋር የተያያዙ ናቸው። ራሞን የተባለ የ17 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “በትምህርት ቤታችን ያሉት ሴቶች በጣም ፈጣጦች ናቸው። ሊያሻሹህ ይሞክራሉ፤ እንዲሁም እስከ ምን ድረስ ዝም እንደምትላቸው ማየት ይፈልጋሉ። ‘እረፉ’ ብትላቸው እንኳ አይሰሙህም!” የ17 ዓመቷ ዲያናም ተመሳሳይ ነገር አጋጥሟታል። እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ወቅት፣ አንድ ልጅ መጣና አቀፈኝ። እኔም በኃይል ገፈተርኩትና ‘ምን እየሆንክ ነው? የት ታውቀኛለህ?’ ብዬ ጮኽኩበት።”

አንተም ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል፤ ምናልባትም ከእነዚህ ሁኔታዎች ማምለጥ እንደማትችል ይሰማህ ይሆናል። በተደጋጋሚ የሚያጋጥም ፈታኝ ሁኔታ በርህን ያለማቋረጥ ከሚያንኳኳ ሰው ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ በሩን መክፈት ባትፈልግም ሲንኳኳ መስማትህ አይቀርም። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በተደጋጋሚ ያጋጥምሃል? ለምሳሌ ያህል፣ ከሚከተሉት መካከል ፈታኝ የሚሆንብህ ነገር አለ?

□ ሲጋራ

□ የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች

□ መጠጥ

□ የፆታ ግንኙነት

□ ዕፅ

□ ሌላ ․․․․․

ከላይ ከተጠቀሱት መካከል ✔ ያደረግህበት ካለ ‘ክርስቲያን ለመሆን ብቃቱ የለኝም’ ብለህ አትደምድም። መጥፎ ምኞቶችን መቆጣጠርና ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም የምትችለው እንዴት እንደሆነ መማር ትችላለህ። በእርግጥ ይህን ለማድረግ እነዚህ ነገሮች ፈታኝ እንዲሆኑብህ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ማወቅ ያስፈልግሃል። እስቲ ሦስቱን ተመልከት።

1. ፍጹም አለመሆንህ። የሰው ልጆች በሙሉ ፍጽምና ስለሚጎድላቸው መጥፎ ነገር የማድረግ ዝንባሌ አላቸው። ጎልማሳ ክርስቲያን የነበረው ሐዋርያው ጳውሎስም እንኳ “ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው” በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። (ሮም 7:21) ከዚህ በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጻድቅ የሆነ ሰውም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ‘የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት’ ፈተና ሊሆንበት ይችላል። (1 ዮሐንስ 2:16) መጥፎ ድርጊት እንድትፈጽም በሚገፋፉ ነገሮች ላይ ማውጠንጠን ደግሞ ፈተናው እንዲከብድህ ከማድረግ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ምኞት ከፀነሰች በኋላ ኃጢአትን ትወልዳለች።”—ያዕቆብ 1:15

2. ውጫዊ ተጽዕኖዎች። ተገቢ ያልሆነ ነገር እንድትፈጽም የሚገፋፉ ፈታኝ ሁኔታዎች በየትኛውም ቦታ ሊያጋጥሙህ ይችላሉ። ትሩዲ እንዲህ ብላለች፦ “በትምህርት ቤትም ሆነ በሥራ ቦታ ወሬው ሁሉ ስለ ፆታ ግንኙነት ነው። በቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና በፊልሞች ላይ የፆታ ግንኙነት በጣም የሚያጓጓና እጅግ አስደሳች እንደሆነ ተደርጎ ይቀርባል። እንዲህ ያለ ድርጊት መፈጸም የሚያስከትለውን መዘዝ ግን ጨርሶ አያሳዩም ማለት ይቻላል!” ትሩዲ እኩዮቿ እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን በዚህ ረገድ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ካጋጠማት ነገር ተገንዝባለች። እንዲህ ብላለች፦ “የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ ፍቅር እንደያዘኝ ተሰምቶኝ ነበር። እናቴ፣ በዚህ ሁኔታ የምቀጥል ከሆነ ማርገዜ እንደማይቀር ቁጭ አድርጋ ነገረችኝ። እንደዚያ ማሰቧ በጣም አስገርሞኝ ነበር! ይሁንና ከሁለት ወር በኋላ አረገዝኩ።”

3. ‘ከወጣትነት ዕድሜ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ምኞቶች።’ (2 ጢሞቴዎስ 2:22) ይህ ሐረግ ወጣቶች የሚኖሯቸውን ምኞቶች በሙሉ ለምሳሌ ተቀባይነት የማግኘት ወይም እንደ ትልቅ ሰው የመታየት ፍላጎትን ሊያመለክት ይችላል። እነዚህ ምኞቶች በራሳቸው ስህተት ባይሆኑም ቁጥጥር ካልተደረገባቸው መጥፎ ነገር ላለመፈጸም የምታደርገው ትግል ከባድ እንዲሆንብህ ያደርጋሉ። ለአብነት ያህል፣ እንደ ትልቅ ሰው ለመታየት ያለህ ጉጉት ወላጆችህ ያስተማሩህን ጥሩ የሥነ ምግባር ደንቦች ቀስ በቀስ ችላ እንድትል ሊያደርግህ ይችላል። ስቲቭ የ17 ዓመት ልጅ እያለ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “በወላጆቼ ላይ በማመፅ አታድርግ ያሉኝን ሁሉ ማድረግ ጀመርኩ፤ እንዲህ ማድረግ የጀመርኩት ከተጠመቅሁ ብዙም ሳይቆይ ነበር።”

ፈተናዎችን መቋቋም

ቀደም ሲል የተጠቀሱትን ተጽዕኖዎች መቋቋም ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ያም ሆኖ ፈታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ትችላለህ። እንዴት?

● በመጀመሪያ፣ በጣም ፈታኝ የሚሆንብህን ነገር ማወቅ ይኖርብሃል። (ምናልባትም በገጽ 65 ላይ ጠቅሰኸው ሊሆን ይችላል።)

● ቀጥሎም ‘ፈተናው ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመኝ መቼ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከሚከተሉት ውስጥ በአንዱ ላይ ✔ አድርግ፦

□ ትምህርት ቤት ስሆን

□ ብቻዬን ስሆን

□ ሥራ ቦታ ስሆን

□ ሌላ ․․․․․

ፈታኝ ሁኔታ ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥምህ መቼ እንደሆነ ማወቅህ ከእነዚህ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ለመራቅ ሊረዳህ ይችላል። እስቲ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ካረን በግብዣው ላይ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊያጋጥማት እንደሚችል የሚጠቁም ምን ነገር ነበር?

․․․․․

ካረን በግብዣው ላይ የገጠማትን ፈታኝ ሁኔታ ለማስቀረት ቀድሞውኑም ምን ማድረግ ትችል ነበር?

․․․․․

● ፈታኝ የሚሆንብህን ነገር እና ብዙውን ጊዜ ሁኔታው የሚያጋጥምህ መቼ እንደሆነ አውቀሃል፤ በመሆኑም እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅተሃል ማለት ነው። በቅድሚያ ልትወስደው የሚገባው እርምጃ፣ ፈታኝ የሚሆንብህ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችልበትን አጋጣሚ መቀነስ ወይም ጭራሹኑ ማስቀረት የምትችልበትን መንገድ መፈለግ ነው። ምን ማድረግ እንደምትችል ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

(ምሳሌዎች፦ ሲጋራ እንድታጨስ የሚገፋፉህ ተማሪዎች የሚያጋጥሙህ ከትምህርት ቤት ስትመለስ ከሆነ ከእነሱ ጋር ላለመገናኘት መንገድ መለወጥ ትችል ይሆናል። ኢንተርኔት ስትጠቀም በኮምፒውተርህ ላይ የብልግና ምስሎች የሚመጡብህ ከሆነ እነዚህንና ሌሎች ተመሳሳይ ድረ ገጾችን የሚያግድ ፕሮግራም መጫን ትችል ይሆናል። በተጨማሪም ከኢንተርኔት ላይ መረጃ ለመፈለግ የምታስገባቸውን ቃላት በጥንቃቄ መምረጥ ይኖርብሃል።)

እርግጥ ነው፣ ፈታኝ ከሆኑ ሁኔታዎች በሙሉ መራቅ አትችልም። ፈጽሞ ባልጠበቅኸው ጊዜ ላይ በጣም ፈታኝ የሆነ ሁኔታ ሊያጋጥምህ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ለመቋቋም ምን ማድረግ አለብህ?

ዝግጁ ሁን

ኢየሱስ ‘ሰይጣን ሲፈትነው’ ምላሽ የሰጠው ወዲያውኑ ነበር። (ማርቆስ 1:13) ይህን ለማድረግ ያስቻለው ምንድን ነው? ሰይጣን ካነሳው ጉዳይ ጋር በተያያዘ ምን አቋም መውሰድ እንዳለበት አስቀድሞ ያውቅ ነበር። ፈተናው ከመምጣቱ በፊትም ቢሆን ምንጊዜም አባቱን ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አድርጎ ነበር። (ዮሐንስ 8:28, 29) ኢየሱስ “ከሰማይ የመጣሁት የእኔን ፈቃድ ሳይሆን የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ነው” በማለት መናገሩ ተገቢ ነበር።—ዮሐንስ 6:38

ብዙውን ጊዜ የሚያጋጥምህን ፈታኝ ሁኔታ መቋቋም ያለብህ ለምን እንደሆነ የሚገልጹ ሁለት ምክንያቶችን እንዲሁም ፈተናውን ለመቋቋም መውሰድ የምትችላቸውን ሁለት እርምጃዎች ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

ፈተናውን መቋቋም ያለብህ ለምንድን ነው?

1 ․․․․․

2 ․․․․․

ፈተናውን ለመቋቋም የሚረዱህ እርምጃዎች፦

1 ․․․․․

2 ․․․․․

ለሚያጋጥሙህ ፈተናዎች እጅ የምትሰጥ ከሆነ ለምኞቶችህ ባሪያ እንደምትሆን አስታውስ። (ቲቶ 3:3) ታዲያ ምኞትህ እንዲቆጣጠርህ ትፈልጋለህ? ምኞትህ እንዲቆጣጠርህ ከመፍቀድ ይልቅ ምኞትህን በመቆጣጠር የበሰልክ ሰው መሆንህን አሳይ። (ቆላስይስ 3:5) እንዲሁም ምኞቶችህን መቆጣጠር እንድትችል አዘውትረህ ጸልይ።—ማቴዎስ 6:13 *

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 15 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

የድካም ስሜት ይሰማሃል? የተሻለ ጤንነት እንዲኖርህና ኃይልህ እንዲታደስ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.43 በተጨማሪም ምዕራፍ 33⁠ን እና 34⁠ን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“አምላክ ታማኝ ነው፤ ልትሸከሙት ከምትችሉት በላይ ፈተና እንዲደርስባችሁ አይፈቅድም፤ ከዚህ ይልቅ ፈተናውን በጽናት መቋቋም እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫ መንገዱን ያዘጋጅላችኋል።”—1 ቆሮንቶስ 10:13

ጠቃሚ ምክር

መጥፎ ነገር እንድታደርግ ሌሎች ተጽዕኖ ሲያደርጉብህ ምን ምላሽ እንደምትሰጥ አስቀድመህ ለመዘጋጀት ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 በተባለው መጽሐፍ ገጽ 132 እና 133 ላይ የሚገኘውን “የእኩዮችን ተጽዕኖ መቋቋም” የሚለውን ሣጥን ተጠቀም።

ይህን ታውቅ ነበር?

ኢየሱስ በታማኝነት እንደሚጸና አምላክ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፤ ያም ቢሆን ግን ኢየሱስ ታዛዥ የሆነው በራሱ ምርጫ እንጂ የተቀመጠለትን መመሪያ ብቻ እንደሚከተል ሮቦት ስለሆነ አይደለም። ኢየሱስ የራሱን ምርጫ ማድረግ የሚችል አካል ነው። በታማኝነት የጸናው እንዲህ እንደሚያደርግ አምላክ አስቀድሞ ስለወሰነለት ሳይሆን ታማኝ ለመሆን ስለመረጠ ነው። መከራ ውስጥ በነበረበት ጊዜ አጥብቆ የጸለየበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።—ዕብራውያን 5:7

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ፈተናዎችን ለመቋቋም ይበልጥ ዝግጁ እንድሆን እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ልርቃቸው የሚገቡ ሰዎች፣ ቦታዎች እና ሁኔታዎች ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ፍጹም የሆኑ ፍጥረታት መጥፎ ነገር ለመፈጸም ሊፈተኑ ይችላሉ?—ዘፍጥረት 6:1-3፤ ዮሐንስ 8:44

● ፈታኝ ሁኔታዎችን በጽናት መቋቋምህ ምን መልካም ውጤት ያስገኛል?—ምሳሌ 27:11፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:12

[በገጽ 68 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከማንም በላይ ኃያል የሆነው አካል እኔን ለመርዳት ፈቃደኛ እንደሆነና በፈለግሁት ጊዜ እርዳታውን ልጠይቅ እንደምችል ማወቄ ጠቅሞኛል!”—ክሪስቶፈር

[በገጽ 67 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ሙከራ

አንድ ኮምፓስ ውሰድና የኮምፓሱ ቀስት ወደ ሰሜን አቅጣጫ እንዲያመለክት ኮምፓሱን አስተካክለህ አስቀምጠው። ከዚያም ከኮምፓሱ ጎን ማግኔት አስቀምጥ። የኮምፓሱ ቀስት ምን ሆነ? ቀስቱ ትክክለኛውን አቅጣጫ ከማመልከት ይልቅ ወደ ማግኔቱ ዞረ አይደል?

ሕሊናህም ልክ እንደ ኮምፓሱ ነው። በሚገባ ከሠለጠነ ወደ “ሰሜን” ማለትም ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚያመለክት ሲሆን ጥበብ የተሞላባቸው ውሳኔዎች እንድታደርግ ይረዳሃል። ይሁን እንጂ ከመጥፎ ጓደኞች ጋር የምትገጥም ከሆነ ማግኔቱ የኮምፓሱ ቀስት አቅጣጫውን እንዲስት እንዳደረገ ሁሉ ጓደኞችህም የሥነ ምግባር አቋምህን ሊያዛቡብህ ይችላሉ። ታዲያ ከዚህ ምን ትማራለህ? የሥነ ምግባር አቋምህን ሊያበላሹብህ ከሚችሉ ሰዎችም ሆኑ ሁኔታዎች ለመራቅ ጥረት አድርግ!—ምሳሌ 13:20

[በገጽ 69 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለሚያጋጥሙህ ፈተናዎች እጅ የምትሰጥ ከሆነ ለምኞቶችህ ባሪያ ትሆናለህ