በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይበልጥ በራሴ እንድተማመን ምን ማድረግ እችላለሁ?

ይበልጥ በራሴ እንድተማመን ምን ማድረግ እችላለሁ?

ምዕራፍ 12

ይበልጥ በራሴ እንድተማመን ምን ማድረግ እችላለሁ?

አዎ አይ

ራስህን በመስታወት ስትመለከት መልክህን ትወደዋለህ? □ □

በአንዳንድ ነገሮች ጎበዝ እንደሆንክ ይሰማሃል? □ □

የእኩዮች ተጽዕኖን መቋቋም ትችላለህ? □ □

ሌሎች የሚሰጡህን አስተያየት ለመቀበል ፈቃደኛ ነህ? □ □

ትችት ሲሰነዘርብህ ችለህ ታልፋለህ? □ □

ሌሎች እንደሚወዱህ ይሰማሃል? □ □

ጤንነትህን ትንከባከባለህ? □ □

ሌሎች ሲሳካላቸው ደስ ይልሃል? □ □

ስለ ራስህ ስታስብ ከሞላ ጎደል ስኬታማ እንደሆንክ ይሰማሃል? □ □

ከላይ ከተጠቀሱት ጥያቄዎች ውስጥ ለአብዛኞቹ የሰጠኸው መልስ “አይ” የሚል ከሆነ ይህ ለራስህ ጥሩ ግምት እንደሌለህና ጠንካራ ጎኖችህን ማየት እንደተሳነህ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል። ይህ ምዕራፍ ያሉህን ጠንካራ ጎኖች ማስተዋል እንድትችል ይረዳሃል!

አብዛኞቹ ወጣቶች ጥሩ ቁመና እንደሌላቸውና በአንዳንድ ነገሮች ጎበዝ እንዳልሆኑ ስለሚሰማቸው የበታችነት ስሜት ያድርባቸዋል፤ እንዲሁም ራሳቸውን ከእኩዮቻቸው ጋር ሲያወዳድሩ ከእነሱ እንደሚያንሱ ይሰማቸዋል። አንተም እንደነዚህ ወጣቶች ይሰማሃል? ከሆነ እንደ አንተ የሚሰማቸው ሌሎች ወጣቶች የተናገሩትን ተመልከት።

“የምሠራቸው ስህተቶች አንገቴን እንድደፋ አድርገውኛል። ብዙ ጊዜ የሚቀናኝ ራሴን መኮነን ነው።”—ሌቲስያ

“ምንም ያህል ቆንጆ ብሆን ከእኔ የበለጠ የሚያምሩ ሰዎች አሉ።”—ሄሊ

“ከሌሎች ጋር ስሆን ‘ስለ እኔ ምን ያስቡ ይሆን?’ እያልኩ ከልክ በላይ እጨነቃለሁ። ሰዎች ዝቅ አድርገው ይመለከቱኛል ብዬም እሰጋለሁ።”—ሬቸል

አንተም ከላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች የሚሰማህ ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። እርዳታ ማግኘት ትችላለህ። ስለ ራስህ ጥሩ ግምት እንዲኖርህ የሚረዱህን ሦስት ነገሮች ተመልከት።

ሌሎችን የሚጠቅም ነገር አድርግ

ቁልፍ ጥቅስ፦ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።”—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ምን ማለት ነው? ሌሎችን ስትረዳ ራስህም ትጠቀማለህ። እንዴት? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ “ለጋስ ይበለጽጋል፤ ሌሎችን የሚያረካም ራሱ ይረካል” ይላል። (ምሳሌ 11:25) ሌሎችን ስትረዳ ለራስህ ጥሩ ግምት እንደሚኖርህ ምንም ጥርጥር የለውም! *

“ለሌሎች ምን ማድረግ እንደምችል በማሰብ በጉባኤዬ ያሉ ወንድሞችና እህቶች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት እጥራለሁ። ለሌሎች ፍቅርና አሳቢነት ማሳየቴ ስለ ራሴ ጥሩ ስሜት እንዲኖረኝ ያደርገኛል።”—ብሪያና

“በክርስቲያናዊው አገልግሎት መካፈል የሚክስ ነው፤ ምክንያቱም ከራሳችሁ ይልቅ ስለ ሌሎች እንድታስቡ ያደርጋችኋል።”—ጄቨን

ማሳሰቢያ፦ ሌሎችን ለመርዳት የምትነሳው በምላሹ አንድ ነገር ለማግኘት ብለህ መሆን የለበትም። (ማቴዎስ 6:2-4) የተነሳሳህበት ምክንያት ትክክለኛ ካልሆነ ሌሎችን መርዳትህ ምንም አይጠቅምህም። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ሰዎች ዓላማህ ምን እንደሆነ ማስተዋላቸው አይቀርም!—1 ተሰሎንቄ 2:5, 6

ልታደርገው የምትችለው ነገር፦ እስቲ ከዚህ ቀደም አንድ ጠቃሚ ነገር ያደረግህለትን ሰው ለማሰብ ሞክር። የዚህን ሰው ስም እና ያደረግህለትን ነገር ጻፍ።

․․․․․

እንዲህ በማድረግህ ምን ተሰማህ?

․․․․․

አሁን ደግሞ ልትረዳው የምትችለው ሌላ ሰው ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ለዚህ ሰው ምን ልታደርግለት እንደምትችል ጻፍ።

․․․․․

ጓደኞች ይኑሩህ

ቁልፍ ጥቅስ፦ “ወዳጅ ምንጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል።”—ምሳሌ 17:17

ምን ማለት ነው? ጥሩ ጓደኛ ችግር በሚያጋጥምህ ጊዜ በተለያዩ መንገዶች ይደግፍሃል። (1 ሳሙኤል 18:1፤ 19:2) የሚያስብልህ ሰው እንዳለ ማወቅህ ብቻ እንኳ ስለ ራስህ ጥሩ እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 16:17, 18) ስለዚህ ስለ ራስህ ጥሩ አመለካከት እንዲኖርህ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ተቀራረብ።

“እውነተኛ ጓደኞች በተስፋ መቁረጥ ስሜት ስትዋጡ ያበረታቷችኋል።”—ዳነል

“አንዳንድ ጊዜ ከምንም በላይ የሚያስፈልጋችሁ ነገር ከልብ የሚያስብላችሁ ሰው እንዳለ ማወቅ ነው። ይህን ማወቃችሁ ዋጋ ቢስ እንዳልሆናችሁ እንዲሰማችሁ ሊያደርግ ይችላል።”—ሄዘር

ማሳሰቢያ፦ ከእነሱ ጋር ለመመሳሰል ስትል ያልሆንከውን እንድትሆን ከሚገፋፉ ጓደኞች ራቅ፤ ከዚህ ይልቅ በአንተነትህ የሚቀበሉህ ጓደኞችን ምረጥ። (ምሳሌ 13:20፤ 18:24፤ 1 ቆሮንቶስ 15:33) ሌሎችን ለማስደሰት ብለህ ተገቢ ያልሆነ ነገር መፈጸም በራስህ እንድታፍር ብሎም መጠቀሚያ እንደሆንክ እንዲሰማህ ያደርጋል።—ሮም 6:21

ልታደርገው የምትችለው ነገር፦ ለራስህ ትክክለኛ ግምት እንዲኖርህ ሊረዳህ የሚችል ጓደኛህን ስም ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

ከላይ ስሙን ከጠቀስኸው ጓደኛህ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ለምን ቀጠሮ አትይዝም? (ግለሰቡ የግድ እኩያህ መሆን እንደሌለበት አስታውስ።)

ስትሳሳት ተስፋ አትቁረጥ

ቁልፍ ጥቅስ፦ “ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል።”—ሮም 3:23

ምን ማለት ነው? ሁሉም ሰው ፍጽምና እንደሚጎድለው የማይታበል ሐቅ ነው። በመሆኑም ስህተት የሆኑ ነገሮችን መናገርህ ወይም ማድረግህ አይቀርም። (ሮም 7:21-23፤ ያዕቆብ 3:2) ጨርሶ ስህተት አለመሥራት ባትችልም ስህተት ስትሠራ የሚሰማህን ስሜት ግን መቆጣጠር ትችላለህ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቅ ሰባት ጊዜ እንኳ ቢወድቅ ይነሣል” ይላል።—ምሳሌ 24:16

“አንዳንድ ጊዜ የበታችነት ስሜት የሚሰማን የራሳችንን ደካማ ጎን ከሌሎች ጠንካራ ጎን ጋር ስለምናወዳድር ነው።”—ኬቨን

“ሁሉም ሰው ጥሩም ሆነ መጥፎ ጎን አለው። ባሉን ጥሩ ባሕርያት ልንኮራ፣ መጥፎ ባሕርያችንን ደግሞ ለማስተካከል ልንጥር ይገባል።”—ሎረን

ማሳሰቢያ፦ ፍጹም አለመሆንህ ኃጢአት ለመሥራት ሰበብ ሊሆንህ አይገባም። (ገላትያ 5:13) ሆን ብለህ መጥፎ ነገር መሥራት ፈጽሞ ልታጣው የማይገባው ወዳጅነት ማለትም ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህ ዝምድና እንዲበላሽ ያደርጋል!—ዕብራውያን 10:26, 27

ልታደርገው የምትችለው ነገር፦ ልታሻሽለው የምትፈልገውን ባሕርይ ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

ከጠቀስኸው ባሕርይ አጠገብ የዛሬውን ቀን አስፍር። ይህን ባሕርይ ማሻሻል የምትችልበትን መንገድ በተመለከተ ምርምር አድርግ፤ ከዚያም ከአንድ ወር በኋላ ምን ያህል ለውጥ እንዳደረግህ ለማወቅ ራስህን ገምግም።

በአምላክ ዘንድ ያለህ ቦታ

መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ከልባችን ይበልጥ ታላቅ” እንደሆነ ይናገራል። (1 ዮሐንስ 3:20) ይህም ሲባል አንተ የማታስተውላቸውን መልካም ባሕርያትህን ይመለከታል ማለት ነው። ይሁን እንጂ ፍጹም አለመሆንህ በአምላክ ዘንድ ባለህ ቦታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለ? እስቲ አንድ ምሳሌ እንውሰድ። ጫፉ ላይ ትንሽ የተቀደደ የ100 ብር ኖት አለህ እንበል። ብሩ ስለተቀደደ ትጥለዋለህ? ወይም ምንም ዋጋ እንደሌለው ይሰማሃል? እንዲህ እንደማታስብ ጥርጥር የለውም! ብሩ ተቀደደም አልተቀደደ ዋጋው አይቀንስም።

አምላክ ለአንተ ያለውን ግምት በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ድክመቶች ያሉህ መሆኑ ለአንተ ያለውን ግምት አይቀንሰውም። እሱን ለማስደሰት የምታደርገው ጥረት ከቁብ የማይቆጠር እንደሆነ ቢሰማህም እሱ ግን ያስተውለዋል፤ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል! መጽሐፍ ቅዱስም “[አምላክ] የምታከናውኑትን ሥራ እንዲሁም ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም” የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል።—ዕብራውያን 6:10

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ጥልቅ በሆነ የሐዘን ስሜት የምትዋጥበት ጊዜ አለ? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.21 የይሖዋ ምሥክር ከሆንህ የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማካፈል ታላቅ ደስታ እንደሚያስገኝልህ ሳትገነዘብ አትቀርም።—ኢሳይያስ 52:7

ቁልፍ ጥቅስ

“እያንዳንዱ ሰው የራሱን ሥራ ምንነት ፈትኖ ያሳይ፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያነጻጽር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ የሚመካበት ነገር ያገኛል።”—ገላትያ 6:4

ጠቃሚ ምክር

‘አንድም ነገር በትክክል መሥራት አልችልም’ ወይም ‘ምንም ነገር አይሳካልኝም’ አትበል። እንዲህ ያሉ የተጋነኑ ሐሳቦች ለራስህ ጥሩ ግምት እንዳይኖርህ ከማድረግ ሌላ የሚፈይዱት ነገር የለም። ድክመቶችህ ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ጠንካራ ጎኖች እንዳሉህም ለማስታወስ ሞክር።

ይህን ታውቅ ነበር?

ስለ ራስህ ያለህ አመለካከት ሌሎች ለአንተ በሚኖራቸው ግምት ሌላው ቀርቶ አንተን በሚይዙበት መንገድ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ታውቃለህ?

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

እኩዮቼ ትችት ሲሰነዝሩብኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ሁልጊዜ የሚታየኝ ድክመቴ ብቻ ከሆነ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ብዙውን ጊዜ ወጣቶች በራሳቸው መተማመን የሚያቅታቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

● ለራስህ ጥሩ ግምት ያለህ መሆኑ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 88 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በጣም የሚያምር ሰውም እንኳ አስቀያሚ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። ወይም ደግሞ ያን ያህል የማያምር ሰው በጣም ቆንጆ እንደሆነ ሊያስብ ይችላል። ልዩነቱ ያለው አመለካከታችን ላይ ነው።”—አሊሳ

[በገጽ 90 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንድ የብር ኖት ትንሽ ስለተቀደደ ብቻ ዋጋው እንደማይቀንስ ሁሉ ፍጹም አለመሆንህም አምላክ ለአንተ ያለው ግምት እንዲቀንስ አያደርግም