በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በግል ጉዳዬ ሌሎች እንዳይገቡ ብፈልግ ስህተት ነው?

በግል ጉዳዬ ሌሎች እንዳይገቡ ብፈልግ ስህተት ነው?

ምዕራፍ 15

በግል ጉዳዬ ሌሎች እንዳይገቡ ብፈልግ ስህተት ነው?

የሚከተሉት ሁኔታዎች ቢያጋጥሙህ በምትሰጠው ምላሽ ላይ ✔ አድርግ፦

1. ክፍልህ ውስጥ እያለህ ታናናሾችህ በሩን ሳያንኳኩ ዘው ብለው ገቡ።

□ ‘ችግር የለውም፤ እኔም አንዳንዴ እንደዚያ አደርጋለሁ።’

□ ‘ይሄማ በጣም ያናድዳል! ልብሴን እየቀየርኩ ቢሆንስ?’

2. ገና ቤት ከመግባትህ ወላጆችህ በጥያቄ ያዋክቡህ ጀመር። “የት ነበርክ? ምን ስታደርግ ነበር? ከማን ጋር ነበርክ?”

□ ‘ችግር የለውም፤ ከእነሱ የምደብቀው ነገር የለም።’

□ ‘በጣም እበሽቃለሁ! ወላጆቼ ጨርሶ አያምኑኝም ማለት’ኮ ነው!’

ትንሽ ልጅ እያለህ ሌሎች በግል ሕይወትህ መግባታቸው ያን ያህል አያሳስብህም ነበር። ታናናሾችህ የክፍልህን በር በርግደው ቢገቡ አይከፋህ ይሆናል። ወላጆችህ አንድ ነገር ሲጠይቁህ ምንም ቅር ሳይልህ መልስ ትሰጥ ነበር። በዚያን ጊዜ፣ ልክ ተገልጦ እንደተቀመጠ መጽሐፍ ስለ አንተ ማወቅ በጣም ቀላል ነበር። አሁን ግን መጽሐፉን መክደን በሌላ አባባል አንዳንድ ነገሮችን ሌሎች እንዳያውቁብህ ማድረግ ትፈልግ ይሆናል። “በሕይወቴ ውስጥ ሰዎች እንዳያውቋቸው የምፈልጋቸው ነገሮች አሉ” በማለት የ14 ዓመቱ ኮሪ ይናገራል። ሌሎች በግል ሕይወትህ እንዳይገቡ ማድረግ ተፈታታኝ ሊሆን የሚችልባቸውን ሁለት ነገሮች እስቲ እንመልከት።

ብቻህን መሆን ስትፈልግ

ብቻህን መሆን የምትፈልግባቸው በርካታ ምክንያቶች ይኖሩ ይሆናል። ምናልባት “ትንሽ አረፍ” ማለት ፈልገህ ይሆናል። (ማርቆስ 6:31) ወይም ደግሞ፣ ኢየሱስ “ስትጸልይ ወደ ክፍልህ ግባ፤ በርህንም ዘግተህ በስውር ወዳለው አባትህ ጸልይ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠውን ምክር መከተል ፈልገህ ሊሆን ይችላል። (ማቴዎስ 6:6፤ ማርቆስ 1:35) ችግሩ ግን የክፍልህን በር (የራስህ ክፍል ካለህ) ስትዘጋ ወላጆችህ እየጸለይክ እንደሆነ ላያስቡ ይችላሉ! እህቶችህና ወንድሞችህ ደግሞ ብቻህን መሆን እንደፈለግህ ላይገባቸው ይችላል።

ምን ማድረግ ትችላለህ? በዚህ ጉዳይ ላይ ከቤተሰብህ ጋር ከመነታረክ ይልቅ የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

● ብቻህን መሆን በምትፈልግበት ጊዜ ወንድሞችህና እህቶችህ እንዳይረብሹህ ምክንያታዊ የሆኑ አንዳንድ ደንቦችን አውጡ። አስፈላጊ ከሆነ ወላጆችህ በዚህ ረገድ እንዲረዱህ ጠይቃቸው። *

● ከወላጆችህ ጋር በተያያዘ ደግሞ ራስህን በእነሱ ቦታ ለማስቀመጥ ሞክር። “ወላጆቼ ምን እያደረግሁ እንደሆነ ለማወቅ የሚሞክሩበት ጊዜ አለ” በማለት የ16 ዓመቷ ሬቤካ ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ለመናገር እኔም በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ልጆች ቢኖሩኝ እንዲህ ማድረጌ አይቀርም፤ ምክንያቱም በዛሬው ጊዜ ያሉ ልጆች ምን ፈታኝ ሁኔታዎች እንደሚያጋጥሟቸው አውቃለሁ።” አንተም እንደ ሬቤካ፣ ወላጆችህ ስለ አንተ የሚጨነቁበትን ምክንያት ለመረዳት ለምን አትሞክርም?—ምሳሌ 19:11

● እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ራስህን በሐቀኝነት መርምር፦ ‘ወላጆቼ ክፍሌ ውስጥ ብቻዬን ስሆን የሆነ ነገር እንደማጠፋ እንዲጠረጥሩ የሚያደርግ ነገር አድርጌያለሁ? ወላጆቼ በተለያዩ ዘዴዎች ተጠቅመው ስለ እኔ ለማወቅ የሚሞክሩት በጣም ድብቅ ስለሆንኩ ይሆን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ‘አይ’ የሚል ቢሆንም እንኳ ወላጆችህ እምነት እንደማይጥሉብህ ከተሰማህ ስለ ጉዳዩ ረጋ ብለህ በአክብሮት አነጋግራቸው። ወላጆችህ ያሳሰባቸው ምን እንደሆነ ሲናገሩ ልብ ብለህ አዳምጥ፤ እንዲሁም ወላጆችህ እንዲጠራጠሩ የሚያደርግ ነገር ከመፈጸም ተቆጠብ።—ያዕቆብ 1:19

ጓደኞች ስትይዝ

በጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትሆን ከቤተሰብህ ውጭ ጓደኛ ለመያዝ መፈለግህ ያለ ነገር ነው። ወላጆችህም ቢሆኑ ጓደኞችህ እነማን እንደሆኑና ከእነሱ ጋር ስትሆን ምን እንደምታደርግ ለማወቅ መፈለጋቸው ስህተት አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ግን ወላጆችህ ስለ አንተ ከልክ በላይ እንደሚጨነቁ ይሰማህ ይሆናል። የ16 ዓመቷ ኤሚ “በሞባይል ሳወራ ወይም ኢ-ሜይል ስላላክ ወላጆቼ ከማን ጋር እያወራሁ ወይም እየተጻጻፍኩ እንደሆነ አሥር ጊዜ ባይጠይቁኝ ደስ ይለኛል” በማለት ተናግራለች።

ምን ማድረግ ትችላለህ? በጓደኞችህ ምክንያት ከወላጆችህ ጋር ከመጋጨት ይልቅ የሚከተሉትን ነጥቦች በተግባር ለማዋል ሞክር፦

● ጓደኞችህ እነማን እንደሆኑ ተናገር፤ እንዲሁም ከወላጆችህ ጋር አስተዋውቃቸው። ጓደኞችህ እነማን እንደሆኑ ለወላጆችህ ካልነገርካቸው እንደ ፖሊስ ቢከታተሉህ ምን ይገርማል? ወላጆችህ ከእነማን ጋር እንደምትውል ሲያውቁ ከጓደኛ ምርጫህ ጋር በተያያዘ የሚኖራቸው ስጋት እንደሚቀንስ አስታውስ።

● እስቲ ራስህን በሐቀኝነት መርምር፦ ወላጆችህ በግል ሕይወትህ የመግባታቸው ጉዳይ ያሳሰበህ ነፃነትህን እንዳላከበሩልህ ስለተሰማህ ነው ወይስ ከእነሱ መደበቅ የምትፈልገው ነገር ስላለ ነው? የ22 ዓመቷ ብሪታኒ እንዲህ ትላለች፦ “የምትኖሩት ከወላጆቻችሁ ጋር ከሆነና ስለ እናንተ እንደሚጨነቁ ካወቃችሁ ‘መጥፎ ነገር እስካላደረግሁ ድረስ ከወላጆቼ መደበቅ ምን አስፈለገኝ?’ ብላችሁ ልታስቡ ይገባል። በሌላ በኩል ግን የምታደርጉትን ነገር መደበቅ እንዳለባችሁ የሚሰማችሁ ከሆነ አንድ ችግር አለ ማለት ነው።”

አንተ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች

በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ ሌሎች ጣልቃ እንዳይገቡብህ ምን እርምጃዎች ልትወስድ እንደምትችል ለማሰብ ሞክር። ከዚያም ከታች ላሉት ጥያቄዎች የምትሰጠውን መልስ ጻፍ፦

እርምጃ 1፦ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ጻፍ። ሌሎች ጣልቃ እንዳይገቡብህ የምትፈልገው በየትኞቹ ጉዳዮች ነው?

․․․․․

እርምጃ 2፦ የወላጆችህን አመለካከት ለመረዳት ሞክር። ወላጆችህን በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ምን ይመስልሃል?

․․․․․

እርምጃ 3፦ መፍትሔ ፈልግ። ሳይታወቅህ ሁኔታውን እያባባስከው ይሆን? ከሆነ ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ለውጥ ልታደርግ ትችላለህ? ወላጆችህ ለሚያሳስብህ ነገር ምን ዓይነት መፍትሔ እንዲሰጡህ ትፈልጋለህ?

․․․․․

እርምጃ 4፦ ከወላጆችህ ጋር ተነጋገርበት። ጉዳዩን ለወላጆችህ እንዴት ልታነሳላቸው እንዳሰብክ ጻፍ።

․․․․․

በሚቀጥለው ምዕራፍ

እናትህ ወይም አባትህ በሞት አንቀላፍተዋል? ከሆነ መጽናኛ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.14 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 6⁠ን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ራስህን ተቀባይነት እንዳለውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።”—2 ጢሞቴዎስ 2:15

ጠቃሚ ምክር

ከወላጆችህ ጋር ስትነጋገር፣ ቅር ያሰኘህ ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ ምን እንደምትፈልግ ተናገር። እንዲህ ማድረግህ ምን ጥቅም አለው? ቅሬታህን ስትገልጽ ትኩረት የምታደርገው ወላጆችህ አጥፍተዋል ብለህ በምታስበው ነገር ላይ ነው። ምን እንደምትፈልግ መናገርህ ግን አንተም ሆንክ ወላጆችህ መፍትሔው ላይ እንድታተኩሩ ያደርጋችኋል።

ይህን ታውቅ ነበር?

ወላጆችህ ይበልጥ እምነት እንዲጥሉብህ ከፈለግህ አንተም ይበልጥ ግልጽ ልትሆንላቸው ይገባል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ወላጆቼ እምነት እንዲጥሉብኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ወላጆችህ ስለ አንተ እንዲሁም ስለምታደርጋቸው ነገሮች የማወቅ መብት አላቸው የምንለው ለምንድን ነው?

● ከወላጆችህ ጋር የመወያየት ችሎታ ለማዳበር ጥረት ማድረግህ ትልቅ ሰው ስትሆን ከሌሎች ጋር በሚኖርህ ግንኙነት ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 108 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ወላጆቻችሁ ምንም ዓይነት ክፉ ነገር እንዲደርስባችሁ ስለማይፈልጉ አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችሁ ጣልቃ እንደገቡ እንዲሰማችሁ የሚያደርግ እርምጃ ይወስዱ ይሆናል። በመሆኑም እንዳበዙት የሚሰማችሁ ጊዜ ሊኖር ይችላል። እውነቱን ለመናገር ግን፣ እኔም ወላጅ ብሆን ኖሮ እንዲሁ የማደርግ ይመስለኛል።”—አላና

[በገጽ 109 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አመኔታ ማትረፍ ደሞዝ ከማግኘት ጋር ይመሳሰላል፤ ሁለቱንም ለማግኘት ጥረት ይጠይቃል