በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያህል ማዘኔ የጤና ነው?

ይህን ያህል ማዘኔ የጤና ነው?

ምዕራፍ 16

ይህን ያህል ማዘኔ የጤና ነው?

በዚህ ምዕራፍ ላይ ትኩረት የተደረገው የወላጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም በሚቻልበት መንገድ ላይ ቢሆንም የተጠቀሱት ሐሳቦች ሌላ የቤተሰብ አባል ወይም የቅርብ ጓደኛ መሞቱ የሚያስከትለውን ሐዘን ለመቋቋምም ይረዳሉ።

“እማዬ ስትሞት የምይዘው የምጨብጠው ጠፍቶኝና ባዶነት ተሰምቶኝ ነበር። የቤታችን ምሰሶ እሷ ነበረች።”—ካረን

ወላጅን በሞት ማጣት በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙ በጣም የሚጎዱ ነገሮች አንዱ ነው። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ከዚያ በፊት ተሰምቶህ የማያውቅ ዝብርቅርቅ ያለ ስሜት ይመጣብህ ይሆናል። የ13 ዓመት ልጅ ሳለ አባቱ በልብ ሕመም ድንገት የሞተበት ብራየን “የአባቴን ሞት በሰማንበት ምሽት ተቃቅፈን ከማልቀስ በስተቀር ምንም ማድረግ አልቻልንም” ብሏል። አባቷ በካንሰር ሲሞት የአሥር ዓመት ልጅ የነበረችው ናታሊ ደግሞ “ምን ተሰምቶኝ እንደነበር መግለጽ ይቸግረኛል፤ ደንዝዤና በድን ሆኜ ነበር” በማለት ተናግራለች።

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚፈጥረው ስሜት ከሰው ሰው ይለያያል። መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው የራሱ ‘ጭንቀትና ሕመም’ እንዳለው ይናገራል። (2 ዜና መዋዕል 6:29) ይህን በአእምሮህ ይዘህ ከወላጆችህ አንዱን በሞት ስታጣ ምን እንደተሰማህ ለማሰብ ሞክር። ከታች ባለው ክፍት ቦታ ላይ (1) የተፈጠረውን ሁኔታ ልክ እንዳወቅህ ምን እንደተሰማህ እና (2) አሁን ምን እንደሚሰማህ ጻፍ። *

1 ․․․․․

2 ․․․․․

ከላይ የሰጠኸው መልስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እንደተረጋጋህ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። እርግጥ፣ መረጋጋትህ የሞተውን ወላጅህን እንደረሳኸው የሚያሳይ አይደለም። በሌላ በኩል ደግሞ ጨርሶ እንዳልተረጋጋህ እንዲያውም ሐዘኑ ይበልጥ እንደከበደህ አስተውለህ ይሆናል። ምናልባትም ሐዘንህ በድንገት እንደሚነሳ ማዕበል በየጊዜው እያገረሸ ያስቸግርህ ይሆናል። ይህም ቢሆን ያለ ነገር ነው፤ ከወላጆችህ አንዱን በሞት ካጣህ ዓመታት ቢያልፉም እንኳ እንዲህ ሊሰማህ ይችላል። ያም ሆነ ይህ አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘ከሐዘንህ መጽናናት የምትችለው እንዴት ነው?’ የሚል ነው።

ማልቀስ ሲያሰኝህ አልቅስ! ማልቀስ ሐዘንህ ቀለል እንዲልልህ ይረዳል። በሌላ በኩል ግን፣ እንደ አሊሺያ ዓይነት ስሜት ይኖርህ ይሆናል። እናቷ ስትሞት የ19 ዓመት ልጅ የነበረችው አሊሺያ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች ስቅስቅ ብዬ ሳለቅስ ካዩኝ እምነት እንደሌለኝ አድርገው እንደሚመለከቱኝ ተሰምቶኝ ነበር።” ይሁን እንጂ እስቲ ይህን አስብ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት የነበረው ፍጹም ሰው ነበር። የሚወደው ጓደኛው አልዓዛር በሞተበት ወቅት ግን ያዘኑትን ሰዎች ሲያይ ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐንስ 11:35) ስለዚህ ማልቀስ ካሰኘህ ከማልቀስ ወደኋላ አትበል። ማልቀስህ እምነት እንደጎደለህ አያሳይም! አሊሺያ “ውሎ አድሮ ግን ማልቀሴ አልቀረም፤ በየቀኑ ለረጅም ሰዓት አለቅስ ነበር” በማለት ተናግራለች። *

ጥፋተኛ እንደሆንክ አይሰማህ። እናቷ በሞተችበት ወቅት የ13 ዓመት ልጅ የነበረችው ካረን እንዲህ ብላለች፦ “ማታ ማታ ከመተኛቴ በፊት እማዬን ሁልጊዜ እስማት ነበር። አንድ ቀን ግን ይህን ሳላደርግ ቀረሁ። በማግስቱ እማዬ ሞተች። ያን ዕለት ምሽት እናቴን አለማየቴና በማግስቱ የሆነው ነገር ከሞቷ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ባውቅም የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል። አባዬ ለሥራ ከከተማ ሲወጣ እማዬን እንድንንከባከባት ለእኔና ለእህቴ ነግሮን ነበር። ይሁንና በማግሥቱ አርፍደን ነቃን። እማዬን ለማየት ወደ መኝታ ክፍሏ ስሄድ መተንፈስ አቁማ ነበር። አባዬ ከቤት ሲወጣ ደህና ስለነበረች በጣም አዘንኩ!”

አንተም ልክ እንደ ካረን ሳታደርግ የቀረኸውን ነገር ስታስብ በመጠኑም ቢሆን የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። እንዲያውም “እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ” የሚለው ሐሳብ አእምሮህን ይበጠብጠው ይሆናል። ለምሳሌ፣ ‘አባዬን ሐኪም ቤት እንዲሄድ ብገፋፋው ኖሮ’ ወይም ‘እማዬን ቀደም ብዬ አይቻት ቢሆን ኖሮ’ እያልክ ራስህን ትወቅስ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ሐሳቦች እረፍት የሚነሱህ ከሆነ ልታስታውሰው የሚገባ ነገር አለ፦ ‘ምነው እንዲህ ባደረግሁ’ ብሎ መቆጨት ሁሉም ሰው የሚያደርገው ነገር ነው። በእርግጥ ምን እንደሚከሰት ብታውቅ ኖሮ አሁን ከወሰድከው የተለየ እርምጃ ትወስድ ነበር። ይሁንና ምን እንደሚከሰት አስቀድመህ አላወቅህም። በመሆኑም ጥፋተኛ እንደሆንክ ሊሰማህ አይገባም። አባትህ ወይም እናትህ የሞቱት በአንተ ጥፋት አይደለም! *

ስሜትህን ለሌሎች ተናገር። ምሳሌ 12:25 ‘መልካም ቃል ሰውን ደስ ያሰኛል’ ይላል። ስሜትህን አምቀህ መያዝ ከሐዘንህ መጽናናት ከባድ እንዲሆንብህ ሊያደርግ ይችላል። በሌላ በኩል ግን ስሜትህን ለምታምነው ሰው ከገለጽክ በሐዘን በምትዋጥበት ወቅት ግለሰቡ “መልካም ቃል” በመናገር ሊያጽናናህ ይችላል።

የሚሰማህን ለአምላክ ንገረው። በጸሎት አማካኝነት ለይሖዋ አምላክ ‘ልብህን ስታፈስስ’ እፎይታ እንደሚሰማህ ጥርጥር የለውም። (መዝሙር 62:8) ጸሎት የምታቀርበው ስሜትህን በመግለጽ እፎይታ ለማግኘት ብቻ አይደለም። ጸሎት ስታቀርብ “የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነው ይሖዋ እንዲረዳህ እየጠየቅህ ሲሆን እሱም “በማንኛውም ዓይነት መከራ ውስጥ ያሉትን ማጽናናት” ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) አምላክ እኛን የሚያጽናናበት አንዱ መንገድ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነው። (ሮም 15:4) ታዲያ የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ጽፈህ ለምን ቅርብ ቦታ አታስቀምጣቸውም? *

ከሐዘንህ ለመጽናናት ጊዜ ያስፈልግሃል። ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጽናና ተስፋ ይዞልናል፤ አምላክ ወደፊት እንደሚያመጣው ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ “ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ . . . አይኖርም።” (ራእይ 21:3, 4) እንደዚህ ባሉት ተስፋዎች ላይ ማሰላሰልህ ወላጅህን በሞት ማጣትህ ካስከተለብህ ሐዘን እንድትጽናና ሊረዳህ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.6 ለእነዚህ ጥያቄዎች አሁን መልስ መስጠት ከከበደህ ሌላ ጊዜ ልታደርገው ትችላለህ።

^ አን.10 ማዘንህን ለማሳየት የግድ ማልቀስ እንዳለብህ ሊሰማህ አይገባም። ሰዎች ሐዘናቸውን የሚገልጹበት መንገድ ይለያያል። በሌላ በኩል ግን እንባህ ከተናነቀህ “ለማልቀስ ጊዜ አለው” የሚለውን ጥቅስ አስታውስ።—መክብብ 3:4

^ አን.12 እንዲህ ያለ የጥፋተኝነት ስሜት ለረጅም ጊዜ የሚያስጨንቅህ ከሆነ በሕይወት ላለው ወላጅህ ወይም ለሌላ አዋቂ ሰው ስሜትህን ተናገር። በጊዜ ሂደት፣ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እያዳበርህ ትሄዳለህ።

^ አን.14 የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች አንዳንዶችን አጽናንተዋቸዋል፦ መዝሙር 34:18፤ 102:17፤ 147:3፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ዮሐንስ 5:28, 29

ቁልፍ ጥቅስ

“[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:4

ጠቃሚ ምክር

የሚሰማህን ነገር በማስታወሻህ ላይ ጻፍ። በሞት ስላጣኸው ወላጅህ የሚሰማህን ነገር መጻፍህ ሐዘንህን እንድትቋቋም ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።

ይህን ታውቅ ነበር?

አንድ ሰው ስላለቀሰ ደካማ ነው ማለት አይደለም። እንደ አብርሃም፣ ዮሴፍና ዳዊት ያሉ መንፈሰ ጠንካራ ሰዎችም እንኳ ሐዘን ሲያጋጥማቸው አልቅሰዋል።—ዘፍጥረት 23:2፤ 50:1፤ 2 ሳሙኤል 1:11, 12፤ 18:33

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በሐዘን በምዋጥበት ጊዜ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ እናቴን ወይም አባቴን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● በሞት ካጣኸው ወላጅህ ጋር ስላሳለፍከው አስደሳች ጊዜ መለስ ብለህ ማሰብህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

● የሚሰማህን ነገር በጽሑፍ ማስፈርህ ሐዘንህን ለመቋቋም የሚረዳህ እንዴት ነው?

[በገጽ 112 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስሜቴን አፍኜ ይዤው ነበር። ይሁንና የሚሰማኝን ለሌሎች ብናገር ኖሮ ይበልጥ መረጋጋት እችል ነበር። ለጤንነቴም የተሻለ ከመሆኑም በላይ ሐዘኑን ለመቋቋም ይረዳኝ ነበር።”—ዴቪድ

[በገጽ 113 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቻንቴል

“አባቴ ለአምስት ዓመታት ያህል ታምሞ የነበረ ሲሆን ጤንነቱ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ ነበር። በመጨረሻም ሕይወቱን አጠፋ፤ በወቅቱ የ16 ዓመት ልጅ ነበርኩ።

ይህ ከሆነ በኋላ እናቴ ለእኔና ለታላቅ ወንድሜ እያንዳንዱን ነገር ትነግረን ጀመር። ሌላው ቀርቶ ከአባቴ የቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር በተያያዘ በተደረጉት ውሳኔዎች ላይ እንድንካፈል ፈቀደችልን። እንዲህ ማድረጓ በጣም ጠቅሞናል። ልጆች፣ ወላጆቻቸው አንዳንድ ነገሮችን በተለይም ይህን የመሳሰሉ ከባድ ጉዳዮችን እንዲደብቋቸው አይፈልጉም። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ስለ አባቴ ሞት በግልጽ ማውራት ቻልኩ። ማልቀስ ስፈልግ አንድ ጓደኛዬ ጋር ሄጄ ወይም ለብቻዬ ሆኜ አለቅሳለሁ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ለደረሰባቸው ሰዎች የምሰጠው ምክር ቢኖር ‘ስለ ሐዘናችሁ ማውራት ከፈለጋችሁ ለቤተሰባችሁ አባላት ወይም ለጓደኞቻችሁ የሚሰማችሁን ንገሯቸው። ሐዘናችሁ እንዲወጣላችሁ የሚረዳችሁን ነገር አድርጉ’ የሚል ነው።”

[በገጽ 113, 114 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ሊያ

የ19 ዓመት ልጅ እያለሁ እናቴ አንጎሏ ውስጥ ደም በመፍሰሱ በጠና ታመመች፤ ከሦስት ዓመት በኋላም ሕይወቷ አለፈ። እናቴ ከሞተች በኋላ እኔ መጠንከር እንዳለብኝ ተሰማኝ። ሐዘኑን መቋቋም ቢያቅተኝ አባቴ ይበልጥ እንደሚጎዳ አውቅ ነበር። ልጅ እያለሁ ሲያመኝ እማዬ ከጎኔ አትለይም ነበር። ትኩሳት እንዳለኝ ለማወቅ በእጇ ስትዳብሰኝ ምን ይሰማኝ እንደነበር አልረሳውም። አጠገቤ አለመኖሯን እንዳስታውስ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ብዙ ጊዜ ያጋጥሙኛል፤ በእነዚህ ጊዜያት በሐዘን እዋጣለሁ። የሚሰማኝን ነገር አውጥቼ አለመናገሬ እንደሚጎዳኝ ባውቅም ብዙውን ጊዜ ስሜቴን አልናገርም። አንዳንድ ጊዜ ግን ሆን ብዬ ፎቶግራፎችን አወጣና እነሱን እያየሁ አለቅሳለሁ። ከጓደኞቼ ጋር ማውራትም ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሞቱ ሰዎች ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ከሞት እንደሚነሱ ተስፋ ይሰጣል። (ዮሐንስ 5:28, 29) እናቴን እንደገና እንደማገኛት ሳስብ እንዲሁም በዚያን ጊዜ ለመኖር ማድረግ ባለብኝ ነገር ላይ ትኩረት ሳደርግ ሐዘኔ ቀለል ይልልኛል።”

[በገጽ 114 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ቤታኒ

“አባቴን ‘እወድሃለሁ’ እንዳልኩት ማስታወስ ብችል ደስ ይለኝ ነበር። በእርግጥ ነግሬው የማውቅ ይመስለኛል፤ ሆኖም እንደዚያ ማድረጌ ትዝ አይለኝም። ምክንያቱም አባቴ የሞተው ገና የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ ነበር። አባቴ ሌሊት ላይ ተኝቶ ሳለ በድንገት በጠና በመታመሙ በአፋጣኝ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። በማግሥቱ ጠዋት ስነሳ አባቴ እንደሞተ ተነገረኝ። ከዚያ በኋላ ስለ አባቴ ማውራት ይረብሸኝ ነበር፤ እያደር ግን ስለ እሱ መስማቴ ይበልጥ እንዳውቀው ስለሚረዳኝ ሰዎች ስለ አባቴ ሲያወሩ ደስ ይለኝ ጀመር። ወላጃቸውን በሞት ላጡ ሰዎች የምላቸው ነገር፦ ‘አብራችሁ ያሳለፋችሁትን ጊዜ ለማስታወስ ሞክሩ፤ እንዲሁም ያሏችሁን አስደሳች ትዝታዎች እንዳትረሷቸው በማስታወሻችሁ ላይ አስፍሯቸው። በተጨማሪም በሞት ያጣችሁት ወላጃችሁ አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ከሞት ሲነሳ እንድታገኙት እምነታችሁን አጠናክሩ።”’

[በገጽ 116 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመልመጃ ሣጥን

ምን እንደሚሰማህ ጻፍ

ስለ አባትህ ወይም ስለ እናትህ ያሉህን አስደሳች ትዝታዎች ጻፍ። ․․․․․

‘አባቴ ወይም እናቴ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ነግሬያቸው ቢሆን ኖሮ’ ብለህ የምታስበውን ነገር ጻፍ። ․․․․․

በደረሰባችሁ ሐዘን ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት የሚሰማው ታናሽ ወንድም ወይም እህት እንዳለህ አድርገህ አስብ። ከዚያም ታናሽህን ምን ብለህ ማጽናናት እንደምትችል ጻፍ። (ይህን ማድረግህ አንተ ራስህ የሚሰማህን የጥፋተኝነት ስሜት ለማሸነፍ ሊረዳህ ይችላል።) ․․․․․

በሞት ስላጣኸው ወላጅህ ማወቅ የምትፈልጋቸውን ሁለት ወይም ሦስት ነገሮች ጻፍ፤ ከዚያም በሕይወት ያለው ወላጅህ እነዚህን ነገሮች እንዲነግርህ ጠይቀው። ․․․․․

የሐዋርያት ሥራ 24:15⁠ን አንብብ። በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ተስፋ ሐዘንህን እንድትቋቋም የሚረዳህ እንዴት ነው? ․․․․․

[በገጽ 115 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሐዘን ስሜት ድንገት እንደሚነሳ ማዕበል ባላሰብከው ሰዓት ሊመጣ ይችላል