በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝን ውጥረት እንዴት ልቋቋመው?

በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝን ውጥረት እንዴት ልቋቋመው?

ምዕራፍ 18

በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝን ውጥረት እንዴት ልቋቋመው?

“በትምህርት ቤት የሚያጋጥመኝ ሁኔታ በጣም የሚያጨናንቅ ከመሆኑ የተነሳ በውጥረት ልፈነዳ የምደርስበት ጊዜ አለ፤ አንዳንድ ጊዜ ማልቀስ ይቃጣኛል እንዲሁም ‘ጩኺ ጩኺ’ ይለኛል።”—ሻረን

“በትምህርት ቤት የሚያጋጥምህ ውጥረት እያደግህ ስትሄድ መልኩን ይለውጥ ይሆናል እንጂ መቼም አይቀንስም።”—ጄምስ

በትምህርት ቤት ምን ያህል ውጥረት እንዳለብህ ወላጆችህ ጨርሶ እንደማይረዱልህ ይሰማሃል? ወላጆችህ ‘አንተ ምን አለብህ? እንዴት አድርጌ የባንክ ዕዳ ልክፈል፣ ቤተሰቤን ላስተዳድር ወይም አለቃዬን ላስደስት አትል!’ ይሉህ ይሆናል። አንተ ግን በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙህ ሁኔታዎች ከወላጆችህ ባልተናነሰ ወይም ከዚያ በላይ ውጥረት እንደሚፈጥሩብህ ይሰማህ ይሆናል።

ወደ ትምህርት ቤት ስትሄድ ወይም ከዚያ ስትመለስ የሚያጋጥምህ ነገር ብቻ እንኳ ውጥረት ሊፈጥርብህ ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖረው ታራ እንዲህ ብላለች፦ “ትምህርት ቤት በሚያመላልሰን አውቶቡስ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ልጆች ይደባደባሉ። በዚህ ጊዜ ሹፌሩ መኪናውን ያቆምና ሁላችንም እንድንወርድ ያደርጋል። በመሆኑም ትምህርት ቤት የምንደርሰው ግማሽ ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ አርፍደን ነው።”

ትምህርት ቤት ከደረስክ በኋላስ ውጥረቱ ይቀንስ ይሆን? እንዲያውም ይብሳል! ምናልባትም እንደሚከተሉት ያሉ ሁኔታዎች ያጋጥሙህ ይሆናል፦

አስተማሪዎች የሚፈጥሩት ውጥረት

“አስተማሪዎቼ ጠንክሬ በመሥራት የላቀ ውጤት እንዳመጣ ይጠብቁብኛል። እነሱን ለማስደሰት የማደርገው ጥረት ደግሞ ውጥረት ይፈጥርብኛል።”—ሳንድራ

“አስተማሪዎች፣ በተለይም ተማሪዎቻቸው ጎበዝ እንደሆኑ ካስተዋሉ በትምህርታቸው ከሌሎች ልቀው እንዲገኙ ከፍተኛ ጫና ያደርጉባቸዋል።”—ኤፕርል

“ለራስህ ያወጣሃቸው ጥሩ ግቦች ቢኖሩህም አንዳንድ አስተማሪዎች እነሱ እንደሚፈልጉት በትምህርት ከፍተኛ ቦታ ለመድረስ ግብ የማታወጣ ከሆነ ዋጋ እንደሌለህ እንዲሰማህ ያደርጉሃል።” *—ናኦሚ

አስተማሪዎችህ ውጥረት እንደሚፈጥሩብህ ይሰማሃል? ከሆነ ይህ ምን ተጽዕኖ አሳድሮብሃል?

․․․․․

እኩዮችህ የሚፈጥሩት ውጥረት

“የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች የበለጠ ነፃነት ያላቸው ሲሆን ይበልጥ ዓመፀኞችም ናቸው። እነሱን ካልመሰልክ ኋላቀር እንደሆንክ አድርገው ይቆጥሩሃል።”ኬቭን

“መጠጥ እንድጠጣና የፆታ ግንኙነት እንድፈጽም ነጋ ጠባ ይጨቀጭቁኛል። እነሱን ላለመምሰል ከራሴ ጋር በጣም መታገል የሚያስፈልገኝ ጊዜ አለ።”አሮን

“አሥራ ሁለት ዓመት ከሆነኝ ጊዜ ጀምሮ ከምንም በላይ ውጥረት የሚፈጥርብኝ የወንድ ጓደኛ እንድይዝ የሚደረግብኝ ግፊት ነው። በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ሁሉ ‘የወንድ ጓደኛ የማትይዢው እስከ መቼ ነው?’ ይሉኛል።”—አሊግዛንድሪያ

“የወንድ ጓደኛ እንድይዝ ጫና ይደረግብኝ ነበር። እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆኔ የሴት ፍቅረኛ እንዳለኝ ይወራ ጀመር። በዚያን ጊዜ ገና የአሥር ዓመት ልጅ ነበርኩ!”ክሪስታ

እኩዮችህ ውጥረት እንደሚፈጥሩብህ ይሰማሃል? ከሆነ ይህ ምን ተጽዕኖ አሳድሮብሃል?

․․․․․

ውጥረት የሚፈጥሩ ሌሎች ነገሮች። ከታች ከተዘረዘሩት ነገሮች መካከል ይበልጥ ውጥረት በሚፈጥርብህ ላይ ✔ አድርግ፤ ወይም ውጥረት የፈጠረብህ ሌላ ነገር ካለ ጻፍ።

□ ፈተና መድረሱ

□ የቤት ሥራ

□ ወላጆችህ ከአንተ ብዙ የሚጠብቁ መሆናቸው

□ ከራስህ ብዙ የምትጠብቅ መሆኑ

□ አካላዊ ጥቃት ወይም ፆታዊ ትንኮሳ

□ ሌላ ․․․․․

ውጥረትን ለመቀነስ የሚረዱ አራት ነጥቦች

ትምህርት ቤት እስካለህ ድረስ ውጥረት የሚፈጥር ሁኔታ ማጋጠሙ የማይቀር ነው። በእርግጥ ከመጠን ያለፈ ውጥረት ጭንቅ እንዲልህ ሊያደርግህ ይችላል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም) ይሁንና እንዲህ ዓይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር መከላከል ትችላለህ። ቁልፉ ውጥረትን መቋቋም የምትችልበትን መንገድ ማወቅ ነው።

ውጥረትን መቋቋም ክብደት ከማንሳት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ክብደት የሚያነሳ ሰው ስኬታማ ለመሆን ከፈለገ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ አለበት። ከአቅሙ በላይ የሆነ ክብደት ከማንሳት የሚቆጠብ ከመሆኑም ሌላ የሚችለውን ክብደት የሚያነሳውም በትክክለኛው መንገድ ነው። እንዲህ ካደረገ ሰውነቱን ሳይጎዳ ጡንቻውን ማዳበር ይችላል። እነዚህን ጥንቃቄዎች የማያደርግ ከሆነ ግን ጡንቻው ሊጎዳ አልፎ ተርፎም አጥንቱ ሊሰበር ይችላል።

አንተም በተመሳሳይ የሚያጋጥምህን ውጥረት መቋቋምና ማከናወን ያለብህን ሥራ ራስህን ሳትጎዳ ማከናወን ትችላለህ። እንዴት? የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር፦

1. የውጥረቱን መንስኤ ማወቅ። አንድ ጥበብ ያዘለ ምሳሌ “ብልኅ ሰው አደጋ ሲመጣ አይቶ ይሸሸጋል። ማስተዋል የጎደለው ሰው ግን ሰተት ብሎ ወደ መከራ በመግባት ይጎዳል” ይላል። (ምሳሌ 22:3 የታረመው የ1980 ትርጉም) ሆኖም ውጥረት የሚፈጥርብህ ነገር ምን እንደሆነ ካላወቅህ መሸሸግ ወይም ሁኔታውን ማስወገድ አትችልም። እስቲ በገጽ 130 ላይ ✔ ያደረግህበትን ነገር መለስ ብለህ ተመልከት። በአሁኑ ወቅት ይበልጥ ውጥረት የሚፈጥርብህ ሁኔታ የትኛው ነው?

2. ምርምር ማድረግ። የቤት ሥራ ተከምሮብሃል እንበል፤ ይህ ውጥረት ፈጥሮብህ ከሆነ በዚህ መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች ተመልከት። አብረውህ የሚማሩ ልጆች የፆታ ብልግና እንድትፈጽም ጫና የሚያደርጉብህ ከሆነ ደግሞ በጥራዝ 2 ምዕራፍ 25 እና 15 ላይ ጠቃሚ ምክር ማግኘት ትችላለህ።

3. ዛሬ ነገ አለማለት። ጊዜ የሚፈታቸው ችግሮች በጣም ጥቂት ናቸው። አብዛኞቹ ችግሮች ችላ ከተባሉ እየባሱ ሊሄዱና ይበልጥ ውጥረት እንዲሰማህ ሊያደርጉ ይችላሉ። ውጥረት የፈጠረብህን ሁኔታ እንዴት ልታስወግደው እንደምትችል ካወቅህ እርምጃ ለመውሰድ ዛሬ ነገ አትበል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት እንደምታደርግ የታወቀ ነው፤ በመሆኑም ማንነትህን ለማሳወቅ አትዘግይ። እንዲህ ማድረግህ የሚሰማህን ውጥረት ይቀንሰዋል። የ20 ዓመቷ ማርሼ እንዲህ ትላለች፦ “በየዓመቱ ልክ ትምህርት ቤት ሲከፈት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን አቋሜን ለመናገር መንገድ የሚከፍቱልኝን ጉዳዮች አንስቼ ውይይት ለመጀመር ጥረት አደርጋለሁ። የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ሳልናገር ጊዜ ባለፈ ቁጥር ማንነቴን መግለጽ የዚያኑ ያህል ከባድ እንደሚሆንብኝ ተገንዝቤያለሁ። አቋሜን ማሳወቄና ዓመቱን ሙሉ በዚያ መሠረት መኖሬ በጣም ረድቶኛል።”

4. እርዳታ መጠየቅ። ክብደት የሚያነሳ ሰው ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆን ሊያነሳ የሚችለው ክብደት ውስን ነው። አንተም ብትሆን አቅምህ ውስን ነው። በመሆኑም ያለብህን ሸክም ብቻህን መሸከም የለብህም። (ገላትያ 6:2) ወላጆችህ ወይም የጎለመሱ ክርስቲያኖች እንዲረዱህ ለምን አትጠይቅም? ቀደም ሲል በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ለቀረቡት ጥያቄዎች የሰጠኸውን መልስ አሳያቸው። እንዲሁም ያጋጠመህን ውጥረት እንዴት መቋቋም እንደምትችል ሐሳብ እንዲሰጡህ ጠይቃቸው።

ጠቃሚ ሊሆን ይችላል?

ለማመን ሊከብድህ ቢችልም በተወሰነ መጠን ውጥረት የሚሰማህ መሆኑ ጥሩ ነገር ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ውጥረት የሚሰማህ መሆኑ ታታሪ እንደሆንክና ሕሊናህ እንዳልደነዘዘ የሚጠቁም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምንም ጉዳይ የማይጨነቅን ሰው እንዴት አድርጎ እንደገለጸው ልብ በል፦ “ምንም ሳትሠራ እስከ መቼ ትተኛለህ? ከእንቅልፍህስ መቼ ትነሳለህ? ትንሽ ማንቀላፋት፤ ትንሽ ማሸለብ፤ እጅን አጣጥፎ ያለ ሥራ መቀመጥ፤ በታጠቀ ዘራፊ እንደተወሰደብህ ያህል በድንገት ሁሉንም ነገር ታጣለህ።”—ምሳሌ 6:9-11 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርዥን

የ16 ዓመቷ ሃይዲ እንደሚከተለው በማለት ነጥቡን ጥሩ አድርጋ ገልጻዋለች፦ “ትምህርት ቤት በጣም መጥፎ ቦታ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ወደፊት ወደ ሥራው ዓለም ስትገቡም ውጥረት የሚፈጥሩ ተመሳሳይ ነገሮች ያጋጥሟችኋል።” ውጥረትን መቋቋም ቀላል እንዳልሆነ አይካድም። ሆኖም የሚያጋጥምህን ውጥረት መቋቋም ከቻልክ አትጎዳም። እንዲያውም ይበልጥ ጠንካራ ሰው መሆን ትችላለህ።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

በትምህርት ቤት ከሚያጋጥሙህ ችግሮች ለመገላገል መፍትሔው ትምህርት ማቋረጥ ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 20⁠ን ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“የሚያስጨንቃችሁንም ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።”—1 ጴጥሮስ 5:7

ጠቃሚ ምክር

ውጥረት የሚፈጥሩብህን ነገሮች ለሁለት ክፈላቸው፤ በአንደኛው ምድብ ሥር መፍትሔ ልትሰጣቸው የምትችላቸውን በሌላኛው ምድብ ሥር ደግሞ ከአቅምህ በላይ የሆኑትን ሁኔታዎች ጻፍ። በመጀመሪያ፣ መፍትሔ ልታገኝላቸው የምትችላቸውን ችግሮች ለማስተካከል ጥረት አድርግ። እነዚህን ችግሮች በሙሉ ማስተካከል ከቻልክ ከአቅምህ በላይ ስለሆኑት ችግሮች መጨነቁን ከዚያ በኋላ ትደርስበታለህ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በየቀኑ በቂ እንቅልፍ ማግኘት ማለትም ቢያንስ ለስምንት ሰዓት ያህል መተኛት ውጥረትን ለመቋቋም የሚረዳህ ከመሆኑም ሌላ የማስታወስ ችሎታህን ያሻሽልልሃል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ያለብኝን ውጥረት ለመቋቋም እንዲረዳኝ ሁልጊዜ ․․․․․ ሰዓት ላይ ለመተኛት እሞክራለሁ።

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከራስም ሆነ ከሌሎች ብዙ መጠበቅ ውጥረትን ከማባባስ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም የምንለው ለምንድን ነው?

● ውጥርጥር እንዳልክ ሲሰማህ እርዳታ ለማግኘት ማንን ልታማክር ትችላለህ?

[በገጽ 132 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አባቴ በየቀኑ ትምህርት ቤት ሲያደርሰኝ አብሮኝ ይጸልያል። ይህም ውስጤ እንዲረጋጋ ይረዳኛል።”—ሊዝ

[በገጽ 131 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክብደትን በትክክለኛው መንገድ ማንሳት ሰውነትን እንደሚያጠነክር ሁሉ ውጥረትን በተገቢው መንገድ መቋቋምም መንፈሰ ጠንካራ እንድትሆን ይረዳሃል