በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርቴን ባቋርጥ ይሻል ይሆን?

ትምህርቴን ባቋርጥ ይሻል ይሆን?

ምዕራፍ 19

ትምህርቴን ባቋርጥ ይሻል ይሆን?

እስከ ስንተኛ ክፍል መማር የሚኖርብህ ይመስልሃል? ․․․․․

ወላጆችህ እስከ ስንተኛ ክፍል እንድትማር ይፈልጋሉ? ․․․․․

ለሁለቱ ጥያቄዎች የሰጠኸው መልስ ተመሳሳይ ነው? መልሶችህ ተመሳሳይ ቢሆኑም እንኳ የምትፈልገው ክፍል ላይ ሳትደርስ ትምህርትህን ለማቋረጥ የምታስብበት ጊዜ ይኖር ይሆናል። ከዚህ በታች እንደተጠቀሱት ወጣቶች ተሰምቶህ ያውቃል?

“አንዳንድ ጊዜ በጣም ውጥረት ስለሚበዛብኝ ከአልጋዬ መውጣት እንኳ አልፈልግም። ‘በትምህርት ቤት የምማረውን አብዛኛውን ነገር ወደፊት ላልጠቀምበት ነገር ትምህርት ቤት ምን አስኬደኝ?’ ብዬ አስባለሁ።”—ሬቸል

“ትምህርት ቤት መሄድ ስለሚሰለቸኝ ትምህርቴን አቋርጬ ሥራ ለመያዝ ብዙ ጊዜ አስብ ነበር። ትምህርት ቤት መሄድ ምንም እንደማይጠቅመኝ ከዚህ ይልቅ ሥራ ይዤ ገንዘብ ባገኝ እንደሚሻለኝ ይሰማኝ ነበር።”—ጆን

“የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት በከተማው መሃል ባለ መጥፎ ሰፈር ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት በመሆኑ ጓደኞች ማግኘት ተቸግሬ ነበር። ትምህርት ቤት የሚሰጠን የቤት ሥራ ያን ያህል አልከበደኝም፤ ይሁን እንጂ ልጆቹ ስለሚያገልሉኝ ብዙውን ጊዜ የማሳልፈው ብቻዬን ነበር። ጓደኛ የሌላቸው ሌሎች ልጆች እንኳ ከእኔ ጋር መሆን አይፈልጉም! ከዚህ ሁሉ ለመገላገል ስል ትምህርቴን ማቋረጥ ቃጥቶኝ ነበር።”—ራያን

“በየምሽቱ የቤት ሥራ በመሥራት አራት ሰዓት ያህል አሳልፍ ነበር! የቤት ሥራዎች፣ ፕሮጀክቶችና ፈተናዎች በላይ በላዩ እየተደራረቡ በጣም ስለሚያጨናንቁኝ ትምህርቱ ከአቅሜ በላይ እንደሆነና ትቼው ብገላገል እንደሚሻል ተሰምቶኝ ነበር።”—ሲንዲ

“የቦምብ ጥቃት እንደሚፈጸምብን ማስፈራሪያ ደርሶን ያውቃል፤ ሦስት ተማሪዎች ራሳቸውን ለመግደል ሞክረዋል፤ አንድ ተማሪ ደግሞ ሕይወቱን አጥፍቷል፤ እንዲሁም በቡድን ሆነው የሚደባደቡ ወጣቶች ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎቹ ከአቅሜ በላይ እንደሆኑ ስለሚሰማኝ ከትምህርት ቤት መልቀቅ እፈልግ ነበር!”—ሮዝ

አንተም እንደዚህ ተሰምቶህ ያውቃል? ከሆነ ትምህርትህን ለማቋረጥ እንድታስብ ያደረገህ ምንድን ነው?

․․․․․

ምናልባትም ትምህርትህን ለማቋረጥ ወስነህ ይሆናል። ይሁንና ትምህርትህን ለማቋረጥ የወሰንከው እስከ አሁን የተማርከው በቂ እንደሆነ ስለተሰማህ ነው ወይስ ትምህርት ቤት ስለሰለቸህና መገላገል ስለፈለግህ? ይህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ትምህርት ማቋረጥ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።

ትምህርት ማቋረጥ ሲባል ምን ማለት ነው?

አንድ ሰው ትምህርቱን አቋርጧል የሚያስብለው ምን ይመስልሃል?

․․․․․

በአንዳንድ አገሮች አንድ ልጅ ከአምስት እስከ ስምንት ዓመት ከተማረ በቂ እንደሆነ ተደርጎ እንደሚታይ ታውቃለህ? በሌሎች አገሮች ደግሞ ተማሪዎች ቢያንስ አሥር ዓመት እንዲማሩ ይጠበቅባቸዋል። ሁኔታው ከአገር ወደ አገር ስለሚለያይ አንድ ልጅ በቂ ትምህርት አግኝቷል የሚባለው እስከ ስንት ዓመቱ ወይም እስከ ስንተኛ ክፍል ቢማር እንደሆነ የሚገልጽ በሁሉም አገሮች የሚሠራ መሥፈርት ማውጣት አይቻልም።

በተጨማሪም በአንዳንድ አገሮች አንድ ተማሪ ትምህርት ቤት መሄድ ሳያስፈልገው አንዳንዶቹን ወይም ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች ቤቱ ሆኖ መማር ይችላል። በመሆኑም ቤት ሆነው እንዲማሩ ወላጆቻቸው የፈቀዱላቸውና እገዛ የሚያደርጉላቸው ልጆች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል ሊባል አይችልም።

ይሁን እንጂ በትምህርት ቤትም ይሁን በቤትህ የምትከታተለውን ትምህርት ከመጨረስህ በፊት ለማቋረጥ እያሰብክ ከሆነ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች ልታስብባቸው ይገባል፦

የአገሩ ሕግ ምን ይላል? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ አንድ ተማሪ እስከ ስንተኛ ክፍል መማር እንዳለበት የሚወስኑት ሕጎች ከአገር ወደ አገር ይለያያሉ። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ያለው ሕግ የሚያዝዘው እስከ ስንተኛ ክፍል እንድትማር ነው? ታዲያ አንተ እዚያ ደረጃ ደርሰሃል? ‘ለበላይ ባለሥልጣናት ተገዙ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችላ ብለህ ሕጉ የሚጠብቅብህ የትምህርት ደረጃ ላይ ሳትደርስ መማር ብታቆም ትምህርትህን አቋርጠሃል ማለት ነው።—ሮም 13:1

ያወጣኋቸው ግቦች ላይ ደርሻለሁ? በትምህርት ቤት ቆይታህ የትኞቹ ግቦች ላይ መድረስ ትፈልጋለህ? እርግጠኛ አይደለህም? በዚህ ረገድ ግብ ሊኖርህ ይገባል! አለዚያ የት መሄድ እንደሚፈልግ ሳይወስን ባቡር ላይ እንደተሳፈረ መንገደኛ ነህ ማለት ነው። ስለዚህ በገጽ 139 ላይ “ የምማርበት ዓላማ” በሚለው ሣጥን ውስጥ የሚገኘውን መልመጃ ከወላጆችህ ጋር ሆነህ ሥራ። እንዲህ ማድረግህ ግቦችህ ላይ ትኩረት እንድታደርግ የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ እስከ ስንተኛ ክፍል መማር እንዳለብህ ከወላጆችህ ጋር ሆነህ ለመወሰን ያስችልሃል።—ምሳሌ 21:5

እርግጥ ነው፣ አስተማሪዎችህና ሌሎች ሰዎች እስከ ስንተኛ ክፍል ብትማር ጥሩ እንደሚሆን ምክር ይሰጡህ ይሆናል። ይሁንና የመጨረሻውን ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን ያላቸው ወላጆችህ ናቸው። (ምሳሌ 1:8፤ ቆላስይስ 3:20) የምትማርበትን ዓላማ በተመለከተ አንተም ሆንክ ወላጆችህ ያወጣችኋቸው ግቦች ላይ ከመድረስህ በፊት መማር ብታቆም ትምህርትህን አቋርጠሃል ማለት ነው።

ለማቋረጥ የፈለግሁት ለምንድን ነው? ራስህን እንዳታሞኝ ተጠንቀቅ። (ኤርምያስ 17:9) የሰው ልጆች ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ለመውሰድ ስንፈልግ በቂ ምክንያት እንዳለን አድርገን ሰበብ ማቅረብ ይቀናናል።—ያዕቆብ 1:22

ትምህርትህን ለማቋረጥ አጥጋቢ ምክንያቶች እንደሆኑ የምታስባቸውን ነገሮች ከታች ባለው ቦታ ላይ ጻፍ።

․․․․․

አሁን ደግሞ በቂ እንደማይሆኑ የሚሰሙህን ምክንያቶች ጻፍ።

․․․․․

አጥጋቢ እንደሆኑ የተሰሙህ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? ከጻፍካቸው ምክንያቶች መካከል ‘ሠርቼ ቤተሰቤን መርዳት’ ወይም ‘ስለ አምላክ በመስበኩ ሥራ የበለጠ መካፈል’ የሚሉት ይገኙበት ይሆናል። በቂ እንደማይሆኑ የሚሰሙህ ምክንያቶች ደግሞ ከፈተና ወይም የቤት ሥራ ከመሥራት መገላገል የሚሉት ሊሆኑ ይችላሉ። ተፈታታኝ የሚሆነው ጉዳይ ትምህርትህን ለማቋረጥ በዋነኝነት ያነሳሳህ ነገር አጥጋቢ ምክንያት ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለይቶ ማወቁ ነው።

ትምህርት ለማቋረጥ ምክንያት እንደሚሆኑህ ከላይ የጻፍካቸውን ነገሮች እስቲ መለስ ብለህ ተመልከታቸው፤ ከዚያም ዋነኛ ምክንያቴ ከምትለው ጀምረህ በሐቀኝነት በቅደም ተከተል ደረጃ ስጣቸው። (ከሁሉ ይበልጥ አሳሳቢ ለምትለው 5፣ ያን ያህል አሳሳቢ ላልሆነው ደግሞ 1 ስጥ።) ከችግሮች ለመሸሽ ብለህ ብቻ ትምህርትህን ብታቋርጥ ያላሰብከው ነገር ሊያጋጥምህ ይችላል።

ትምህርት ማቋረጥ ምን ችግር አለው?

ትምህርት ማቋረጥ፣ ያሰብክበት ቦታ ከመድረስህ በፊት ከባቡር ላይ ዘለህ እንደ መውረድ ሊቆጠር ይችላል። እርግጥ ባቡሩ ምቾት ላይኖረው ተሳፋሪዎቹ ደግሞ አስቸጋሪ ሊሆኑብህ ይችላሉ። ያም ሆኖ ከባቡሩ ላይ ዘለህ ብትወርድ ያሰብክበት ቦታ ሳትደርስ የምትቀር ከመሆኑም ሌላ ከባድ ጉዳት ሊያጋጥምህ ይችላል። በተመሳሳይም ትምህርትህን ብታቋርጥ የምትማርበትን ዓላማ ማሳካት የማትችል ከመሆኑም ሌላ አሁንም ሆነ ወደፊት ችግሮች ያጋጥሙሃል፤ ከእነዚህ መካከል፦

አሁን የሚያጋጥሙ ችግሮች፦ ሥራ ማግኘት ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ሥራ ብታገኝ እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ደሞዝህ ትምህርትህን ብትጨርስ ኖሮ ልታገኘው ከምትችለው ያነሰ ነው። በመሆኑም መሠረታዊ ፍላጎቶችህን ለማሟላት ስትል ተማሪ እያለህ ከነበርክበት በከፋ ሁኔታ ለረጅም ሰዓት መሥራት ይኖርብህ ይሆናል።

ወደፊት የሚያጋጥሙ ችግሮች፦ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ትምህርት አቋርጠው የወጡ ሰዎች ለጤና ችግሮች የመጋለጥና እስር ቤት የመግባት አጋጣሚያቸው ሰፊ ከመሆኑም ሌላ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን ድጋፍ ሳያገኙ መኖር ሊያቅታቸው ይችላል።

እርግጥ ነው፣ ትምህርትህን ማጠናቀቅህ እነዚህ ችግሮች እንደማያጋጥሙህ ማረጋገጫ ይሆናል ማለት አይደለም። ያም ቢሆን ግን ትምህርትህን በማቋረጥ ራስህን ለምን ጣጣ ውስጥ ትከታለህ?

ትምህርት አለማቋረጥ ያሉት ጥቅሞች

እርግጥ ነው፣ ፈተና ወድቀህ ወይም በትምህርት ቤት አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞህ ከሆነ ትምህርትህን ለማቋረጥ ትነሳሳ ይሆናል፤ እንዲያውም አሁን ባለህበት ሁኔታ ከመማረርህ የተነሳ ወደፊት ሊያጋጥሙህ የሚችሉ ችግሮች ላይታዩህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የተሻለ እንደሆነ የተሰማህን አማራጭ ከመውሰድህ በፊት በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ የተጠቀሱት ተማሪዎች ትምህርታቸውን ባለማቋረጣቸው ምን ያህል እንደተጠቀሙ የተናገሩትን ሐሳብ ተመልከት።

“ጽናትን ተምሬያለሁ፤ መንፈሰ ጠንካራ መሆን ችያለሁ። በተጨማሪም በምሠራው ሥራ ደስታ ማግኘት አለማግኘቴ የተመካው በአመለካከቴ ላይ እንደሆነ ተምሬያለሁ። ትምህርቴን መቀጠሌ ከተመረቅሁ በኋላ ልጠቀምበት የምችለውን የሥነ ጥበብ ሙያ እንዳዳብር ረድቶኛል።”—ሬቸል

“ጠንክሬ ከሠራሁ ግቦቼ ላይ መድረስ እንደምችል አሁን ተገንዝቤያለሁ። ወደፊት በኅትመት ማሽን ጥገና መስክ ለመሰማራት ስለምፈልግ አሁን በምማርበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ለዚህ ሙያ የሚያዘጋጀኝን ሥልጠና እየወሰድኩ ነው።”—ጆን

“ትምህርቴን ባለማቋረጤ ማንበብና መጻፍ ችያለሁ። ሌሎች የሚሰጡኝን አስተያየት መቀበልን እንዲሁም ሐሳቤን ግልጽና አሳማኝ በሆነ መንገድ መግለጽን ተምሬያለሁ፤ እነዚህ ችሎታዎች ደግሞ በክርስቲያናዊ አገልግሎቴ ጠቅመውኛል።”—ራያን

“በክፍል ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደምችል በትምህርት ቤት ሥልጠና አግኝቻለሁ። በትምህርት፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በሌሎች ጉዳዮች የሚያጋጥሙኝን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት መፍታት እንደምችል ያገኘሁት ሥልጠና ብስለት እንዲኖረኝ ረድቶኛል።”—ሲንዲ

“ትምህርት ቤት በሥራው ዓለም ለሚያጋጥሙኝ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አዘጋጅቶኛል። በተጨማሪም የማምንባቸው ነገሮች እውነት መሆናቸውን እንድመረምር የሚያነሳሱኝ በርካታ ሁኔታዎች በትምህርት ቤት ያጋጥሙኝ ስለነበር የትምህርት ቤት ሕይወቴ እምነቴ እንዲጠናከር ረድቶኛል።”—ሮዝ

ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 7:8) በመሆኑም ትምህርትህን ከማቋረጥ ይልቅ በትምህርት ቤት የሚያጋጥሙህን ችግሮች በትዕግሥት ለመወጣት ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ የትምህርት ቤት ሕይወትህ ፍጻሜው ያማረ ይሆናል።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ትምህርት ቤት እንዲያስጠላህ ያደረገህ አንዱ ምክንያት ከአስተማሪዎችህ ጋር መስማማት አለመቻልህ ነው? ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ቁልፍ ጥቅስ

“ችኰላም ወደ ድኽነት ያደርሳል።”—ምሳሌ 21:5

ጠቃሚ ምክር

በትምህርት ቤት ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ከሆነብህ ትምህርትህን ሳታቋርጥ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉ ማድረግ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ሐሳብ እንዲሰጡህ ወላጆችህን ጠይቃቸው።

ይህን ታውቅ ነበር?

በትምህርት ሰዓት ክፍል ያለመግባት ልማድ ያላቸው ተማሪዎች ትምህርታቸውን የማቋረጥ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አንድ የትምህርት ዓይነት ከከበደኝ ትምህርቴን ከማቋረጥ ይልቅ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ትምህርቴን ማቋረጥ የፈለግሁት ከፍተኛ ድካም ስለሚሰማኝ ከሆነ ሁኔታውን ለማሻሻል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● የማንበብና የመጻፍ ችሎታ እንዲሁም የሒሳብ እውቀት የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው?

● በትምህርት ልትደርስባቸው የምትችላቸው የአጭር ጊዜ ግቦች ማውጣትህ የትምህርት ቤት ቆይታህን በአግባቡ እንድትጠቀምበት ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?

● ትምህርትህን ከጨረስክ በኋላ በምን ዓይነት የሥራ መስክ መሰማራት እንደምትፈልግ አስቀድመህ ማሰብህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?

[በገጽ 140 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የትም ብትሄድ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች ማምለጥ አትችልም። የትምህርት ቤት ሕይወትህ ችግሮችን በራስህ መወጣትን እንድትማር ይረዳሃል፤ ይህ ደግሞ በሥራው ዓለምም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ይጠቅምሃል።”—ራሞና

[በገጽ 139 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 የመልመጃ ሣጥን

የምማርበት ዓላማ

የምትማርበት ዋነኛ ዓላማ ራስህን ለመቻል የሚረዳህ ሥልጠና ማግኘት ነው፤ ትምህርት ወደፊት ትዳር ከመሠረትክ ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን ለማሟላት የሚያስችል ሥራ ለመያዝም ሊረዳህ ይችላል። (2 ተሰሎንቄ 3:10, 12) በሥራው ዓለም በምን መስክ መሰማራት እንደምትፈልግ ወስነሃል? ታዲያ በምትፈልገው የሥራ መስክ ለመሰማራት ሊረዳህ የሚችል ትምህርት እየቀሰምክ ነው? የምትከታተለው ትምህርት ግብህ ላይ ለመድረስ ያስችልህ እንደሆነ ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ምን ተሰጥኦዎች አሉኝ? (ለአብነት ያህል፣ ከሌሎች ጋር የመግባባት ችሎታ አለህ? የእጅ ሙያ አለህ? ለምሳሌ አንዳንድ ነገሮችን መሥራት ወይም መጠገን ያስደስትሃል? የችግሮችን መንስኤ በማወቅና መፍትሔ በማግኘት ረገድ ጥሩ ችሎታ አለህ?) ․․․․․

ችሎታዬን መጠቀም የምችለው ምን ዓይነት ሥራ ብይዝ ነው? ․․․․․

በምኖርበት አካባቢ ምን ዓይነት ሥራዎችን መሥራት ይቻላል? ․․․․․

ወደፊት ሥራ ለማግኘት የሚረዳኝ ምን ትምህርት እየተከታተልኩ ነው? ․․․․․

አሁን ከምከታተለው ትምህርት በተጨማሪ ግቦቼ ላይ ለመድረስ የሚረዱኝ ምን ሌሎች ትምህርቶች አሉ? ․․․․․

በሌላ በኩል ደግሞ ወደ ሌላው ጽንፍ እንዳትሄድ ተጠንቀቅ። የምትማርበት ዓላማ ጥሩ ሥልጠና አግኝተህ ሥራ መያዝ መሆኑን አትርሳ። በመሆኑም ኑሮ የሚያመጣቸውን ሌሎች ኃላፊነቶች መሸከም ስለሚያስፈራህ ብቻ “ከባቡሩ” ሳትወርድ እንዳትቀር በሌላ አባባል ዕድሜ ልክህን ተማሪ እንዳትሆን ተጠንቀቅ። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.69 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 38 ተመልከት።

[በገጽ 138 እና 139 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ትምህርት ማቋረጥ፣ ያሰብክበት ቦታ ከመድረስህ በፊት ከባቡር ላይ ዘለህ እንደ መውረድ ሊቆጠር ይችላል