በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የባሕል ልዩነት—ተጽዕኖውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

የባሕል ልዩነት—ተጽዕኖውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 22

የባሕል ልዩነት—ተጽዕኖውን መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ወላጆችህ የምትኖርበት አገር ተወላጆች ናቸው?

□ አዎ □ አይ

የቤተሰባችሁ ቋንቋና ባሕል ትምህርት ቤት ካለው የተለየ ነው?

□ አዎ □ አይ

“ቤተሰቦቼ ጣሊያናውያን ስለሆኑ ፍቅራቸውንም ሆነ ስሜታቸውን በነፃነት ይገልጻሉ። አሁን የምንኖረው እንግሊዝ ውስጥ ነው። እዚህ ደግሞ ሰዎች በጣም ቁጥብ ናቸው። በመሆኑም እኔ ከሁለት ያጣ እንደሆንኩ ይሰማኛል፤ ወይ ጣሊያናዊ አልሆንኩ ወይ እንግሊዛዊ አልሆንኩ፤ መሃል ቤት ግራ ተጋብቻለሁ።”—ዦዝዌ፣ እንግሊዝ

“ትምህርት ቤት አስተማሪዬ ዓይን ዓይኑን እያየሁ እንዳነጋግረው ይፈልጋል። አባቴ ደግሞ ዓይን ዓይኑን እያየሁ ማናገር ነውር እንደሆነ ይነግረኛል። የትኛውን ባሕል መከተል እንዳለብኝ ግራ ገብቶኛል።”—ፓትሪክ፣ አልጄሪያዊ ወላጆች ያሉት በፈረንሳይ የሚኖር ወጣት

ወላጆችህ አሁን ወዳላችሁበት አገር ሲመጡ የተለያዩ ችግሮች አጋጥመዋቸው እንደሚሆን የታወቀ ነው። የሄዱበት አገር ቋንቋ፣ ባሕልና የሰዎች አለባበስ ከለመዱት የተለየ ይሆንባቸዋል። ከሌላው ሰው ለየት ብለው መታየታቸው አይቀርም። ሰዎች አክብሮት በጎደለው መንገድ ይዘዋቸው እንዲሁም መድልዎ አድርገውባቸው ይሆናል።

አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ነበር? እንደ አንተ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ያጋጠሟቸው አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከዚህ በታች ተዘርዘረዋል። ከተዘረዘሩት ነጥቦች መካከል አንተን በጣም በሚከብድህ ላይ ✔ አድርግ።

ፌዝ። ኑር ከቤተሰቧ ጋር ከዮርዳኖስ ወደ ሰሜን አሜሪካ የሄደችው ትንሽ ልጅ እያለች ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “አለባበሳችን የተለየ በመሆኑ ሰዎች ያሾፉብን ነበር። እኛም የአሜሪካውያን ቀልድ አይገባንም ነበር።”

የማንነት ጥያቄ። ናድያ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የተወለድኩት በጀርመን ነው። ወላጆቼ ጣሊያናውያን ስለሆኑ ጀርመንኛ ስናገር የጣሊያንኛ ቅላፄ አለኝ፤ በመሆኑም ትምህርት ቤት ልጆቹ ይሰድቡኝ ነበር። ጣሊያን ስሄድ ደግሞ የምናገረው ጣሊያንኛ የጀርመንኛ ቅላፄ እንዳለው አስተዋልኩ። በዚህም ምክንያት ለሁለቱም ባሕሎች እንግዳ እንደሆንኩ ይሰማኛል። የትም ብሄድ እንደ ባዕድ መታየቴ አይቀርም።”

ወላጆች ከአዲሱ ባሕል ጋር አለመላመዳቸው። አና ከቤተሰቧ ጋር ወደ እንግሊዝ በሄደችበት ወቅት የስምንት ዓመት ልጅ ነበረች። አና እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ወንድሜ የለንደንን ሕይወት ወዲያውኑ ለመድነው። ወላጆቼ ግን መዲራ በተባለችው አነስተኛ የፖርቱጋል ደሴት ውስጥ ለረጅም ጊዜ ስለኖሩ አዲሱን ሕይወት መልመድ ከበዳቸው።”

ቩን፣ የካምቦዲያ ዜግነት ያላቸው ወላጆቿ ወደ አውስትራሊያ ሲመጡ የሦስት ዓመት ልጅ ነበረች። ቩን እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ አዲሱን ባሕልና አካባቢ መላመድ ከብዷቸው ነበር። እንዲያውም አባቴ ስሜቱንና አመለካከቱን ስለማልረዳለት ብዙውን ጊዜ ይናደድብኝ ነበር።”

በቋንቋ አለመግባባት። ኢየን ከቤተሰቦቹ ጋር ከኢኳዶር ወደ ኒው ዮርክ ሲመጣ የስምንት ዓመት ልጅ ነበር። ኢየን በዩናይትድ ስቴትስ ለስድስት ዓመታት ከኖረ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “አሁን ከስፓንኛ ይልቅ እንግሊዝኛ መናገር ይቀናኛል። በትምህርት ቤት አስተማሪዎቼና ጓደኞቼ የሚናገሩት እንግሊዝኛ ነው፤ እኔና ወንድሜ የምንነጋገረውም በእንግሊዝኛ ነው። አሁን አሁን ደግሞ የማስበውም በእንግሊዝኛ ስለሆነ ስፓንኛን እየረሳሁ ነው።”

ካምቦዲያውያን ወላጆች ያሏትና በአውስትራሊያ የተወለደችው ሊ እንዲህ ብላለች፦ “ለወላጆቼ ስለ አንዳንድ ጉዳዮች ምን እንደሚሰማኝ ላስረዳቸው ስፈልግ ሐሳቤን በእነሱ ቋንቋ በደንብ መግለጽ ይቸግረኛል።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኑር እንዲህ ብላለች፦ “አባቴ ቤት ውስጥ በአረብኛ እንድንናገር ብዙ ጥረት አድርጎ ነበር፤ እኛ ግን በአረብኛ ማውራት አንፈልግም። አረብኛ መማር አላስፈላጊ ሥራ እንደሚጨምርብን ተሰምቶን ነበር። ጓደኞቻችን የሚያወሩት በእንግሊዝኛ ነው። የምናያቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች በሙሉ የሚተላለፉት በእንግሊዝኛ ነው። ታዲያ አረብኛ ማወቁ ምን ያደርግልናል?”

ምን ማድረግ ትችላለህ?

ከላይ የተጠቀሱት ወጣቶች ከሰጡት ሐሳብ ማየት እንደሚቻለው እንዲህ ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያጋጥምህ አንተ ብቻ አይደለህም። እነዚህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ከመጋፈጥ ይልቅ ‘የወላጆቼን ባሕል እርግፍ አድርጌ ትቼ በአካባቢዬ ካሉ ሰዎች ጋር ተመሳስዬ ብኖርስ!’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ ወላጆችህን ቅር እንደሚያሰኛቸው የታወቀ ነው፤ አንተም ብትሆን እንዲህ በማድረግህ ደስተኛ አትሆንም። ታዲያ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንዴት መቋቋም እንደምትችል መማር ብሎም ካለህበት ሁኔታ ጥቅም ለማግኘት መሞከር አይሻልም? እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት፦

ፌዝ ሲያጋጥምህ፦ ምንም ያህል ብትደክም በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት አትችልም። በሌሎች ላይ ማፌዝ የሚወዱ ሰዎች ምንጊዜም ይህን ለማድረግ የሆነ ምክንያት ማግኘታቸው አይቀርም። (ምሳሌ 18:24 NW) ስለዚህ የእነሱን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል አትድከም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “ፌዘኛ መታረምን ይጠላል” በማለት ጽፏል። (ምሳሌ 15:12) ፌዘኛ ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉት አመለካከታቸው የተዛባ ስለሆነ እንጂ የሚያፌዙበት ሰው የሆነ ችግር ስላለበት አይደለም።

የማንነት ጥያቄ ሲፈጠርብህ፦ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት መፈለግህ ያለ ነገር ነው፤ ለምሳሌ ያህል ከቤተሰብህ ጋር መመሳሰል ወይም የአካባቢውን ባሕል መከተል ትፈልግ ይሆናል። ማንነትህ የሚወሰነው በባሕልህ ወይም በቤተሰብህ እንደሆነ ማሰብ ግን ስህተት ነው። እነዚህ ነገሮች ሰዎች ለአንተ ባላቸው አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ይሆናል፤ የአምላክ አመለካከት ግን ከዚህ የተለየ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ “አምላክ እንደማያዳላ” ተናግሯል። አክሎም “ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና የጽድቅ ሥራ የሚሠራ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው” ብሏል። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35) ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ከልብህ ጥረት የምታደርግ ከሆነ እሱም እንደ ቤተሰቡ አባል አድርጎ ይመለከትሃል። (ኢሳይያስ 43:10፤ ማርቆስ 10:29, 30) ደግሞስ የአምላክ ቤተሰብ አባል ከመሆን የተሻለ ምን አለ?

ወላጆችህ አዲሱን ባሕል ለመልመድ ሲቸገሩ፦ በሁሉም ቤተሰቦች ውስጥ ማለት ይቻላል ወላጆች እና ልጆች የተለያየ አመለካከት የሚኖራቸው ጊዜ አለ። ምናልባት ይህ ሁኔታ በእናንተ ቤተሰብ ውስጥ እንደሚብስ ይሰማህ ይሆናል። ወላጆችህ የእነሱን ባሕል እንድትከተል ይፈልጉ ይሆናል፤ አንተ ደግሞ በምትኖርበት አካባቢ ያለውን ባሕል መከተል ልትፈልግ ትችላለህ። ያም ቢሆን ስኬታማ ሕይወት መምራት ከፈለግህ ‘አባትህንና እናትህን ማክበር’ ይኖርብሃል።—ኤፌሶን 6:2, 3

የወላጆችህን ባሕል ስለማትወደው ብቻ ባሕሉን ከመቃወም ይልቅ ወላጆችህ ባሕላቸውን ከፍ አድርገው የሚመለከቱት ለምን እንደሆነ ለመረዳት ሞክር። (ምሳሌ 2:10, 11) ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘የወላጆቼን ባሕል መከተሌ ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር እንድጋጭ ያደርገኛል? ካልሆነ ከእነሱ ባሕል የጠላሁት ምኑን ነው? ስለዚህ ጉዳይ የሚሰማኝን ነገር ለወላጆቼ በአክብሮት መግለጽ የምችለው እንዴት ነው?’ (የሐዋርያት ሥራ 5:29) እርግጥ ነው፣ የወላጆችህን ቋንቋ በደንብ ማወቅህ ለእነሱ አክብሮት ማሳየት ቀላል እንዲሆንልህ ያደርጋል፤ ቋንቋቸውን ካወቅህ የእነሱን አመለካከት መረዳትና ስሜትህን በሚገባ መግለጽ ትችላለህ።

የቋንቋ አለመግባባት ሲፈጠር፦ በአንዳንድ ቤተሰቦች ውስጥ ልጆች ቤት ውስጥ ሲሆኑ በወላጆቻቸው ቋንቋ ብቻ እንዲነጋገሩ ይደረጋል፤ ወላጆች እንዲህ ማድረጋቸው ልጆቹ ሁለት ቋንቋዎች መማር እንዲችሉ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። በእናንተ ቤትስ እንዲህ ለማድረግ ለምን አትሞክሩም? ከዚህም ሌላ ወላጆችህ ቋንቋቸውን መጻፍ እንዲያስተምሩህ ልትጠይቃቸው ትችላለህ። ጀርመን ውስጥ ያደገውና አፍ መፍቻ ቋንቋው ግሪክኛ የሆነው ስቴሊዮስ እንዲህ ብሏል፦ “በየዕለቱ ከወላጆቼ ጋር በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ እንወያይ ነበር። ጥቅሱን ጮክ ብለው ሲያነቡልኝ እኔ ደግሞ እጽፈዋለሁ። አሁን በግሪክኛም ሆነ በጀርመንኛ ማንበብና መጻፍ እችላለሁ።”

የወላጆችህን ቋንቋ መማር ሌላስ ምን ጥቅም አለው? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዦዝዌ እንዲህ ብሏል፦ “የወላጆቼን ቋንቋ የተማርኩት ከእነሱ ጋር ይበልጥ መቀራረብ እንዲሁም ስለ መንፈሳዊ ነገሮች ስንወያይ አመለካከታቸውን የበለጠ መረዳት ስለፈለግሁ ነው። ቋንቋቸውን መማሬ አንዳችን የሌላውን ስሜት መረዳት እንድንችል ረድቶናል።”

ድልድይ ወይስ እንቅፋት?

የወላጆችህ ባሕል ከሌሎች ጋር እንዳትቀራረብ እንቅፋት እንደሚፈጥርብህ ይሰማሃል? ወይስ ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ እንደሚረዳህ ድልድይ አድርገህ ትመለከተዋለህ? በርካታ ወጣት ክርስቲያኖች ሁለቱንም ባሕሎች ማወቃቸው ሌላም ጥቅም እንዳለው ተገንዝበዋል። ቋንቋቸው ከሚነገርበት አገር ለሚመጡ ሰዎች የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ አስችሏቸዋል። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) የአምስት ዓመት ልጅ እያለ ወደ ለንደን የመጣው ሳሎማኡ እንዲህ ብሏል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍትን በሁለት ቋንቋዎች ማስረዳት መቻል በጣም ትልቅ ነገር ነው! የመጀመሪያ ቋንቋዬን ረስቼው ነበር ማለት ይቻላል፤ አሁን ግን በፖርቱጋል ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ ስለሆንኩ እንግሊዝኛም ሆነ ፖርቱጋልኛ አቀላጥፌ እናገራለሁ።”

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኑር አረብኛ የሚናገሩ ወንጌላውያን እንደሚያስፈልጉ ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “አሁን አረብኛ እየተማርኩ ሲሆን የረሳሁትን ለማስታወስም እየጣርኩ ነው። አመለካከቴ ተቀይሯል። ቋንቋውን መማር ስለምፈልግ እርማት ሲሰጠኝ ቅር አይለኝም።”

የሁለት ሕዝቦችን ባሕል ማወቅህና ሁለት ወይም ከዚያ በላይ ቋንቋዎችን መናገርህ በጣም እንደሚጠቅምህ ምንም ጥርጥር የለውም። የሁለት ሕዝቦችን ባሕል ማወቅህ የሰዎችን ስሜት ይበልጥ ለመረዳት የሚያስችልህ ከመሆኑም ሌላ አምላክን አስመልክተው ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በተሻለ መንገድ መልስ ለመስጠት ይረዳሃል። (ምሳሌ 15:23) እንግሊዝ ውስጥ የተወለደችውና ሕንዳዊ ወላጆች ያሏት ፕሪቲ እንዲህ ብላለች፦ “ሁለቱንም ባሕሎች ስለማውቃቸው አገልግሎት ላይ ከሰዎች ጋር መግባባት ይቀለኛል። የሁለቱም አገር ሰዎች ያላቸውን አመለካከትና የሚያምኑባቸውን ነገሮች መረዳት እችላለሁ።”

አንተስ ያለህበትን ሁኔታ እንደ እንቅፋት ሳይሆን እንደ በረከት አድርገህ ትመለከተዋለህ? ይሖዋ አንተን የሚወድህ በማንነትህ ነው፤ አንተም ሆንክ ወላጆችህ የመጣችሁበት አካባቢ እሱ ለአንተ ያለውን ስሜት አይቀይረውም። ታዲያ በዚህ ምዕራፍ ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ያለህን እውቀትና ተሞክሮ ተጠቅመህ እንደ አንተ ዓይነት ባሕል እና ቋንቋ ላላቸው ሰዎች አፍቃሪ ስለሆነውና ስለማያዳላው ስለ ይሖዋ አምላክ ማስተማር ትችላለህ? እንዲህ ማድረግህ እውነተኛ ደስታ ያስገኝልሃል!—የሐዋርያት ሥራ 20:35

ቁልፍ ጥቅስ

“አምላክ [አያዳላም]።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34

ጠቃሚ ምክር

የሌላ አገር ሰው በመሆንህ እኩዮችህ ሲያሾፉብህ ከመበሳጨት ይልቅ ችላ ብለህ እለፈው። እንደማትናደድ ሲያዩ በአንተ ማሾፋቸውን ሊያቆሙ ይችላሉ።

ይህን ታውቅ ነበር?

ሁለት ቋንቋዎችን አቀላጥፈህ መናገር ከቻልክ ሥራ የማግኘት አጋጣሚህ ሰፊ ይሆናል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

የወላጆቼን ቋንቋ በደንብ ለመቻል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● የወላጆችህን ባሕል በደንብ ማወቅህ ስለ ማንነትህ ለሚነሱብህ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት የሚረዳህ እንዴት ነው?

● በሁለት የተለያዩ ባሕሎች ውስጥ ማደግህ ከሌሎች ወጣቶች በተለየ መልኩ ምን ጥቅሞች ያስገኝልሃል?

[በገጽ 160 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሌሎችን መርዳት መቻሌ ያስደስተኛል። ፈረንሳይኛ እንዲሁም የሩሲያና የሞልዶቫ ቋንቋ ለሚናገሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ማስረዳት እችላለሁ።”—ኦሌግ

[በገጽ 161 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወላጆችህን ባሕል ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ እንደሚረዳህ ድልድይ አድርገህ ልትመለከተው ትችላለህ