በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ግብረ ሰዶም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዴት ላስረዳ?

ስለ ግብረ ሰዶም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዴት ላስረዳ?

ምዕራፍ 23

ስለ ግብረ ሰዶም መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እንዴት ላስረዳ?

በሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ታዋቂ የሆኑ ሁለት ሴት ተዋንያን ከመድረክ ሆነው ከንፈር ለከንፈር በመሳሳም ሰላምታ ሲለዋወጡ የተሰበሰበው ሕዝብ ጩኸቱን አቀለጠው! አንዳንዶች በድንጋጤ አፋቸውን ከፍተው ቀሩ፤ በኋላ ላይ ግን እነሱም ድጋፋቸውን ገለጹ። ግብረ ሰዶማውያን ይህ ታላቅ ድል እንደሆነ ተሰማቸው። ሌሎች ደግሞ ትኩረት ለመሳብ የተደረገ እንደሆነ ተናገሩ። ያም ሆነ ይህ፣ ተዋንያኑ ሲሳሳሙ የሚያሳየው ቪዲዮ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ይታያል፤ በኢንተርኔት ላይም ስለሚለቀቅ በቀጣዮቹ ቀናት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቪዲዮውን ማየታቸው አይቀርም።

ከላይ የቀረበው ሁኔታ እንደሚያሳየው ታዋቂ ሰዎች፣ ግብረ ሰዶማውያን እንደሆኑ አሊያም ለሁለቱም ፆታዎች የፍቅር ስሜት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር በይፋ ካደረጉ ድርጊታቸው ከምንም ነገር በላይ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ይስባል። አንዳንዶች እንዲህ ያሉ ሰዎችን በድፍረታቸው ሲያደንቋቸው ሌሎች ግን ድርጊታቸው ጸያፍ እንደሆነ በመግለጽ ያወግዟቸዋል። ከሁለቱም ጽንፍ ያልሆኑና ግብረ ሰዶምን እንደ አንድ አማራጭ የሚመለከቱ በርካታ ሰዎችም አሉ። የ21 ዓመቱ ዳንኤል እንዲህ ብሏል፦ “ተማሪ በነበርኩበት ወቅት፣ አንድ ሰው ግብረ ሰዶምን ከተቃወመ ግብረ ሰዶማዊ ያልሆኑት ልጆች እንኳ ጭፍን ጥላቻ እንዳለውና ራሱን እንደሚያመጻድቅ ይሰማቸው ነበር።”

በተለያየ ዘመን የኖሩ ሰዎች ስለ ግብረ ሰዶም የተለያየ አመለካከት ሊኖራቸው ይችላል፤ ሰዎች በዚህ ረገድ ያላቸው አመለካከት ከአገር ወደ አገርም ይለያይ ይሆናል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ‘በማንኛውም የትምህርት ነፋስ እየተንገዋለሉ ወዲያና ወዲህ አይሉም።’ (ኤፌሶን 4:14) ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ በጥብቅ ይከተላሉ።

ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይላል? በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንብ የምትመራ ከሆነ ጭፍን ጥላቻ እንዳለህ፣ በሌሎች መፍረድ እንደሚቀናህና ግብረ ሰዶማውያንን እንደምትጸየፍ አድርገው ለሚያዩህ ሰዎች መልስ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡት ዓይነት ጥያቄዎች ወይም ሐሳቦች ሲሰነዘሩ ምን መልስ መስጠት እንደምትችል እስቲ እንመልከት።

“መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን ይላል?”

“የአምላክ ዓላማ የፆታ ግንኙነት በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ እንዲፈጸም መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ዘሌዋውያን 18:22፤ ምሳሌ 5:18, 19) መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙትን ያወግዛል፤ ይህም ተመሳሳይ ፆታ ባላቸው መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ግንኙነትም ሆነ ተቃራኒ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ብልግና ያካትታል።” *ገላትያ 5:19-21

“ስለ ግብረ ሰዶም ምን አመለካከት አለህ?”

“ግብረ ሰዶማውያንን አልጠላቸውም፤ ይሁን እንጂ ተግባራቸውን አልደግፍም።”

ልብ ልትለው የሚገባ ነገር፦ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንብ የምትመራ ከሆነ ይህ የግል ምርጫህ ነው፤ ደግሞም እንዲህ ዓይነት ምርጫ ማድረግ መብትህ ነው። (ኢያሱ 24:15) በዚህ አመለካከትህ ልታፍር አይገባም።—መዝሙር 119:46

“ሰዎች ግብረ ሰዶማዊ ሆኑም አልሆኑ፣ ክርስቲያኖች ሁሉንም ሰው በአክብሮት መያዝ አይገባቸውም?”

“አዎ፣ ይገባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ’ ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ስለዚህ ክርስቲያኖች ለግብረ ሰዶማውያን ጥላቻ የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ግብረ ሰዶማውያንን ጨምሮ ለሁሉም ሰው ደግነት ያሳያሉ።”—ማቴዎስ 7:12

“ስለ ግብረ ሰዶማውያን ያለህ አመለካከት ጭፍን ጥላቻን የሚያበረታታ አይመስልህም?”

“በጭራሽ። እኔ የምጠላው ግብረ ሰዶምን እንጂ ግብረ ሰዶማውያንን አይደለም።”

አክለህ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “አንድ ምሳሌ ልስጥህ፤ እኔ ሲጋራ ማጨስ አልፈልግም። እንዲያውም ማጨስ የሚለውን ነገር ሳስበው ራሱ ይቀፈኛል። አንተ ግን ታጨሳለህ እንበል፤ በመሆኑም ስለ ማጨስ ያለህ አመለካከት ከእኔ የተለየ ነው። እንዲህ ዓይነት አቋም ስላለህ ግን እጠላሃለሁ ማለት አይደለም፤ አንተም ብትሆን ባለኝ አቋም የተነሳ ለእኔ ጭፍን ጥላቻ የሚኖርህ አይመስለኝም፤ አይደለም እንዴ? ስለ ግብረ ሰዶም ባለን የአመለካከት ልዩነት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።”

“ኢየሱስ መቻቻል እንዳለብን አስተምሮ የለም እንዴ? ታዲያ ክርስቲያኖች ግብረ ሰዶምን በተመለከተ የከረረ አቋም ሊይዙ ይገባል?”

“ኢየሱስ ማንኛውም ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ ተቀባይነት እንዳለው ለተከታዮቹ አላስተማረም። ከዚህ ይልቅ በእሱ ‘እንደሚያምን በተግባር ለሚያሳይ ሁሉ’ የመዳን መንገድ ክፍት እንደሆነ አስተምሯል። (ዮሐንስ 3:16) በኢየሱስ እንደምናምን በተግባር ማሳየት ሲባል አምላክ ካወጣቸው የሥነ ምግባር ደንቦች ጋር ተስማምቶ መኖር ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነትን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወግዛቸው አንዳንድ ምግባሮች መራቅን ያጠቃልላል።”—ሮም 1:26, 27

“አንድ ሰው ግብረ ሰዶማዊ የሚሆነው ተፈጥሮው ስለሆነ ነው፤ በመሆኑም ይህን ፍላጎቱን ሊቀይረው አይችልም።”

“መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማውያን አፈጣጠር የሚናገረው ነገር ባይኖርም አንዳንድ ልማዶች ሥር የሰደዱ እንደሆኑ ይገልጻል። (ሮም 7:23) አንዳንዶች እንደ ራሳቸው ዓይነት ፆታ ላለው ሰው የፍቅር ስሜት ቢኖራቸውም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ከግብረ ሰዶም እንዲርቁ ያዝዛል።”

እንዲህ አድርግ፦ ሰዎች ግብረ ሰዶም የመፈጸም ፍላጎት እንዲያድርባቸው የሚያደርገውን ምክንያት በተመለከተ አጉል ክርክር ውስጥ ከመግባት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶም መፈጸምን እንደሚከለክል ጎላ አድርገህ ግለጽ። ነገሩን በንጽጽር ለማስረዳት ያህል እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “ብዙ ሰዎች የግልፍተኝነት ባሕርይ በዘር ሊወረስ እንደሚችልና አንዳንዶች በቁጣ መገንፈል የሚቀናቸው ለዚህ እንደሆነ ይናገራሉ። (ምሳሌ 29:22) ይህ አስተያየት እውነት ነው እንበል። ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ በቁጣ መገንፈልን እንደሚያወግዝ ሳታውቅ አትቀርም። (መዝሙር 37:8፤ ኤፌሶን 4:31) አንዳንድ ሰዎች በቁጣ መገንፈል ስለሚቀናቸው ብቻ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት ተገቢ አይደለም ሊባል ይችላል?”

“አንድ ሰው እንደ ራሱ ዓይነት ፆታ ላለው ሰው የፍቅር ስሜት የሚያድርበት ከሆነ አምላክ ከግብረ ሰዶም እንዲርቁ ሰዎችን ማዘዙ ጭካኔ አይሆንም?”

“እንዲህ ያለው አመለካከት የመነጨው ሰዎች የፆታ ስሜታቸውን ከማርካት ወደኋላ ማለት የለባቸውም ከሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ተገቢ ላልሆኑ የፆታ ፍላጎቶች ላለመሸነፍ ከልባቸው እስከፈለጉ ድረስ ከእነዚህ ነገሮች መራቅ እንደሚችሉ ማረጋገጫ በመስጠት አምላክ የሰው ልጆችን እንዳከበራቸው ይገልጻል።”—ቆላስይስ 3:5

“ግብረ ሰዶማዊ ባትሆንም እንኳ ስለ ግብረ ሰዶም ያለህን አመለካከት ማስተካከል ይኖርብሃል።”

“እስቲ አንድ ምሳሌ ልንገርህ፦ እኔ ቁማር መጫወት ተገቢ እንደሆነ አይሰማኝም፤ አንተ ግን ከእኔ የተለየ አመለካከት አለህ እንበል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቁማር ለመጫወት ስለሚመርጡ ብቻ ስለ ቁማር ያለኝን አመለካከት እንድለውጥ ብትጫነኝ ምክንያታዊ ይሆናል?”

ልብ ልትለው የሚገባ ነገር፦ ግብረ ሰዶማውያንን ጨምሮ አብዛኞቹ ሰዎች በሥነ ምግባር ረገድ የሚቀበሏቸው አንዳንድ መሥፈርቶች አሉ፤ ለምሳሌ ያህል እንደ ማጭበርበር፣ የፍትሕ መዛባት ወይም ጦርነት ያሉ ነገሮችን ይጠላሉ። መጽሐፍ ቅዱስም እነዚህን ነገሮች ያወግዛል፤ እንዲሁም ግብረ ሰዶምን ጨምሮ ከፆታ ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ የሚከለክላቸው አንዳንድ ድርጊቶች አሉ።—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10

መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊነት የጎደለው ወይም ጭፍን ጥላቻን የሚያስፋፋ መጽሐፍ አይደለም። የአምላክ ቃል ግብረ ሰዶማዊ ለሆኑም ሆነ ላልሆኑ ሰዎች “ከዝሙት ሽሹ” የሚል አንድ ዓይነት መመሪያ ይሰጣል።—1 ቆሮንቶስ 6:18

ደግሞም ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር የሚፈልጉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ግብረ ሰዶማዊ ያልሆኑ ሰዎች ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸውም ራሳቸውን ገዝተው መኖር ችለዋል። ከእነዚህም መካከል የማግባት አጋጣሚያቸው ጠባብ የሆነ በርካታ ያላገቡ ሰዎች እንዲሁም በአካል ጉዳት የተነሳ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የማይችል የትዳር ጓደኛ ያላቸው ብዙ ያገቡ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የፆታ ስሜታቸውን ማርካት ባይችሉም በደስታ መኖር ችለዋል። የግብረ ሰዶማዊነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ አምላክን ለማስደሰት ከልባቸው የሚፈልጉ ከሆነ እንዲሁ ማድረግ ይችላሉ።—ዘዳግም 30:19

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 28 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

አንዳንድ ሴቶች ከወንድ ጓደኛቸው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ይበልጥ እንደሚያቀራርባቸው ይሰማቸዋል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት “ዝሙት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ብቻ ሳይሆን የሌላን ሰው የፆታ ብልት እንደ ማሻሸት ወይም በአፍና በፊንጢጣ የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸም ያሉ ድርጊቶችን ጭምር ነው።

ቁልፍ ጥቅስ

“በምድራዊ የአካል ክፍሎቻችሁ ውስጥ ያሉትን ዝንባሌዎች ግደሉ፤ እነሱም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ የፆታ ምኞት፣ መጥፎ ፍላጎትና ጣዖት አምልኮ የሆነው መጎምጀት ናቸው።”—ቆላስይስ 3:5

ጠቃሚ ምክር

የሌሎች ድርጊት ቢረብሽህም ራስህን እንዳታመጻድቅ ተጠንቀቅ። አንተ የራስህን ምርጫ የማድረግ መብት እንዳለህ ሁሉ እነሱም የፈለጉትን አካሄድ የመከተል ነፃነት እንዳላቸው አትዘንጋ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ግለሰቦች፣ ክርስቲያን ከመሆናቸው በፊት ግብረ ሰዶም ይፈጽሙ የነበረ ቢሆንም ርኩስ የሆነውን አካሄዳቸውን በመተው በአምላክ ፊት ‘ታጥበው መንጻት’ ችለዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አንድ ሰው ‘መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም የሚናገረው ነገር ጊዜ ያለፈበት ነው’ ቢለኝ እንዲህ እለዋለሁ፦ ․․․․․

የምጠላው ግብረ ሰዶማውያንን ሳይሆን ግብረ ሰዶምን እንደሆነ በግልጽ ለማሳወቅ እንዲህ እላለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● አምላክ ለሰዎች የሥነ ምግባር ደንብ የማውጣት መብት አለው የምንለው ለምንድን ነው?

● በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የሥነ ምግባር ደንቦች በጥብቅ መከተልህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

[በገጽ 170 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በትምህርት ቤታችን ያለ አንድ ልጅ የእሱን አካሄድ እንደማልደግፍ ሲያውቅ በጣም መጥፎ ሰው እንደሆንኩ ተሰማው። ይሁንና የምጠላው ድርጊቱን እንጂ እሱን እንዳልሆነ ስነግረው እንዲሁም ግብረ ሰዶምን ብቻ ሳይሆን የሥነ ምግባር ብልግናን በአጠቃላይ እንደማልደግፍ ሲገነዘብ ያከብረኝ ጀመር፤ እንዲያውም ሌሎች በአቋሜ ምክንያት ሲቃወሙኝ ይከላከልልኝ ነበር።”—ኦብሪ

[በገጽ 168 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለሁለቱም ፆታዎች የፍቅር ስሜት ያላቸው ሰዎችስ?

እንዲህ ያለው ዝንባሌ በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ ሊታይ የሚችል ቢሆንም በይበልጥ በሴቶች ዘንድ እየተለመደ የመጣ ይመስላል። አንዳንዶች እንዲህ የሚያደርጉት አዲስ ነገር ለመሞከር ስለሚጓጉ ሊሆን ይችላል። የ26 ዓመቷ ሊሳ እንዲህ ብላለች፦ “ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ሙዚቃዎች ሴቶች መሳሳማቸውን እንደ ጥሩ ነገር አድርገው ሲያቀርቡ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች፣ በተለይ እንዲህ ያለው ድርጊት ስህተት እንደሆነ የማይሰማቸው ከሆነ ለመሞከር ይፈተናሉ።”

ሌሎች ደግሞ እንደ እነሱ ዓይነት ፆታ ላለው ሰው እውነተኛ የፍቅር ስሜት እንዳላቸው ይሰማቸዋል። የ13 ዓመቷ ቪኪ እንዲህ ብላለች፦ “በአንድ ግብዣ ላይ ከሁለት ሴቶች ልጆች ጋር ተዋወቅኩ፤ እነዚህ ልጆች ለሁለቱም ፆታዎች የፍቅር ስሜት አላቸው። በኋላ ላይ አንዲት ጓደኛዬ ልጆቹ እንደወደዱኝ ነገረችኝ። ከዚያም ከአንደኛዋ ጋር በሞባይል መልእክት መለዋወጥ ጀመርኩ፤ ውሎ አድሮ ከእሷ ጋር ፍቅር ያዘኝ።”

አንቺስ እንደ ቪኪ ተሰምቶሽ ያውቃል? ብዙዎች፣ ከሁለቱም ፆታዎች ጋር የፍቅር ግንኙነት ለመመሥረት ነፃነት እንዲሰማሽ እንዲሁም በዚህ ሳታፍሪ ማንነትሽን በግልጽ እንድትናገሪ ይገፋፉሽ ይሆናል። ይሁን እንጂ ከሌላ ሴት ጋር የሚይዝሽ ፍቅር በአብዛኛው ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ አለመሆኑን ማወቅ ይኖርብሻል። ቪኪ ይህ እውነት መሆኑን ተገንዝባለች። ሊዜት የምትባል የ16 ዓመት ወጣትም በዚህ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “ስለሚሰማኝ ነገር ለወላጆቼ በግልጽ መናገሬ ረድቶኛል። በተጨማሪም በባዮሎጂ ክፍለ ጊዜ፣ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሆርሞን መጠን በጣም ሊለዋወጥ እንደሚችል ተማርኩ። ወጣቶች ስለ ሰውነታቸው በደንብ ቢያውቁ ኖሮ ተመሳሳይ ፆታ ካለው ሰው ጋር የሚይዛቸው ፍቅር ጊዜያዊ ሊሆን እንደሚችል መገንዘባቸው ስለማይቀር ግብረ ሰዶማዊ ለመሆን አይነሳሱም።”

ስሜትሽ ከጉርምስና ዕድሜ ጋር ተያይዞ ከሚመጣ ጊዜያዊ ስሜት ያለፈና ይበልጥ ሥር የሰደደ እንደሆነ ብታስቢ እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ማንኛውንም ዓይነት መጥፎ ምኞት ማሸነፍ ትችያለሽ።

[በገጽ 169 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያኖች ከብዙኃኑ የተለየ አካሄድ ለመከተል አይፈሩም