በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድ ሰው “አብሬው እንድወጣ” ቢጠይቀኝስ?

አንድ ሰው “አብሬው እንድወጣ” ቢጠይቀኝስ?

ምዕራፍ 26

አንድ ሰው “አብሬው እንድወጣ” ቢጠይቀኝስ?

“አንዳንድ ወጣቶች የፆታ ግንኙነት እስከ መፈጸም ይደርሱ እንደሆነ ለማየትና ከምን ያህል ሰዎች ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም እንደሚችሉ ለማወቅ ሲሉ ብቻ ካገኙት ሰው ጋር ይወጣሉ።”—ፔኒ

“ልጆቹ ስለዚህ ጉዳይ ሲያወሩ ትንሽ እንኳ አያፍሩም። የሴት ጓደኛ ብትኖራቸውም ከሌሎች ብዙ ሴቶች ጋር የፆታ ግንኙነት እንደፈጸሙ በጉራ ያወራሉ።”—ኤድዋርድ

በዛሬው ጊዜ ብዙ ወጣቶች የፍቅር ስሜት ወይም ግንኙነት ሳይኖራቸው ካገኙት ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት ይፈጽማሉ፤ እንዲያውም ስለዚህ ጉዳይ በኩራት ይናገራሉ። አንዳንዶች ደግሞ ፍቅረኛ መያዝ የሚያስከትለውን ኃላፊነት መሸከም ሳያስፈልጋቸው የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም ሲሉ ብቻ የሚቀርቧቸው ሰዎች ይኖሯቸዋል።

አንቺም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ሲቀርብልሽ ለመቀበል ትፈተኚ ይሆናል። * (ኤርምያስ 17:9) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኤድዋርድ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ወጣት ሴቶች የፆታ ግንኙነት እንድንፈጽም ይጠይቁኛል፤ በክርስትና ሕይወቴ ውስጥ በጣም የከበደኝ ፈተና ይህ ነው። አልፈልግም ማለት ቀላል አይደለም!” አንድ ሰው እንዲህ ያለ ጥያቄ ቢያቀርብልሽ ልታስቢባቸው የሚገቡ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች የትኞቹ ናቸው?

ስህተት የሆነበትን ምክንያት ማወቅ

ዝሙት ከባድ ኃጢአት ነው፤ እንዲያውም ይህን ድርጊት የሚፈጽሙ ሰዎች “የአምላክን መንግሥት አይወርሱም።” (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) ይህን ድርጊት የሚፈጽሙት ሰዎች “እንዋደዳለን” ይሉ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ በመካከላቸው የፍቅር ስሜት ላይኖር ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸማቸው ከባድ ኃጢአት ነው። በዚህ ረገድ የሚያጋጥምሽን ፈተና ለመቋቋም እንድትችዪ ዝሙትን በተመለከተ የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበር ይኖርብሻል።

“ይሖዋ የሚሰጠን መመሪያ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ እርግጠኛ ነኝ።”—ካረን፣ ካናዳ

“በፈተናው ብትሸነፉ ወላጆቻችሁ፣ ጓደኞቻችሁና የጉባኤያችሁ አባላት ምን ያህል እንደሚያዝኑ አስቡ።”—ፒተር፣ ብሪታንያ

ፍጹም ባለመሆንሽ ድርጊቱ አስደሳች እንደሆነ ይሰማሽ ይሆናል፤ ይሁንና ዝሙትን በተመለከተ ይሖዋ ያለው ዓይነት አመለካከት በማዳበር ‘ክፋትን መጥላት’ ትችያለሽ።—መዝሙር 97:10

በተጨማሪም፦ ዘፍጥረት 39:7-9⁠ን አንብቢ። ዮሴፍ ከፆታ ብልግና ጋር በተያያዘ ያጋጠመውን ፈተና በመቋቋም ያሳየውን ድፍረትና ይህን ለማድረግ ያስቻለው ምን እንደሆነ ልብ በዪ።

በምታምኚበት ነገር ኩሪ

አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ስለሚያምኑበት ነገር በኩራት ይናገራሉ። አንቺም የአምላክን መሥፈርቶች ከፍ አድርገሽ እንደምትመለከቺ በምግባርሽ የማሳየት ልዩ አጋጣሚ አለሽ። ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ትክክል እንዳልሆነ የምታምኚ መሆኑ ሊያሳፍርሽ አይገባም።

“የምትመሩበት የሥነ ምግባር መሥፈርት እንዳላችሁ ገና ከጅምሩ በግልጽ ተናገሩ።”—አለን፣ ጀርመን

“በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብረውኝ የሚማሩት ወንዶች አቋሜን ስለሚያውቁ እኔን ለማግባባት መሞከር ከንቱ ድካም መሆኑን ተገንዝበው ነበር።”—ቪኪ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ለምታምኚበት ነገር ጠንካራ አቋም መያዝሽ ጎልማሳ ክርስቲያን መሆንሽን ይጠቁማል።—1 ቆሮንቶስ 14:20

በተጨማሪም፦ ምሳሌ 27:11⁠ን አንብቢ። ትክክለኛውን ነገር ማድረግሽ የይሖዋን ልብ ምን ያህል እንደሚያስደስተው አስቢ!

ቆራጥ ሁኚ!

የሚቀርቡልሽን ጥያቄዎች ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳልሆንሽ ብትናገሪም አንዳንዶች እየተግደረደርሽ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል።

“ሁሉ ነገራችሁ ማለትም አለባበሳችሁ፣ አነጋገራችሁ፣ የምትቀራረቧቸው ሰዎች እንዲሁም ሌሎችን የምትቀርቡበት መንገድ እንዲህ ያለውን ድርጊት ለመፈጸም ፈቃደኛ እንዳልሆናችሁ የሚያሳይ መሆን አለበት።”—ጆይ፣ ናይጄሪያ

“ጥያቄያቸውን እንደማትቀበሉ መቼም ቢሆን ግልጽ ልታደርጉላቸው ይገባል። እንዲሁም ሌላ ዓላማ ያላቸው ወንዶች የሚሰጧችሁን ስጦታ ፈጽሞ አትቀበሉ። ምክንያቱም በምላሹ አንድ ነገር እንድታደርጉላቸው ሊጠብቁባችሁ ይችላሉ።”—ላራ፣ ብሪታንያ

በአቋምሽ የምትጸኚ ከሆነ ይሖዋ ይረዳሻል። መዝሙራዊው ዳዊት ከግል ተሞክሮው በመነሳት ስለ ይሖዋ ሲናገር “ከታማኙ ጋር ታማኝ ትሆናለህ” ብሏል።—መዝሙር 18:25

በተጨማሪም፦ 2 ዜና መዋዕል 16:9⁠ን አንብቢ። ይሖዋ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ የሚጥሩ ሰዎችን ለመርዳት ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ልብ በዪ።

አስተዋይ ሁኚ

መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ይህን ምክር እንዴት በተግባር ማዋል ትችያለሽ? የማስተዋል ችሎታሽን በመጠቀም ነው!

“ስለ እንደዚህ ዓይነት ነገር ከሚያወሩ ሰዎች በተቻላችሁ መጠን ራቁ።”—ኔኦሚ፣ ጃፓን

“አድራሻችሁን ወይም ስልክ ቁጥራችሁን የመሳሰሉ የግል መረጃዎችን አትስጡ።”—ዳያና፣ ብሪታንያ

ስለ አነጋገርሽ፣ ስለ ምግባርሽ፣ ስለ ጓደኞችሽ እንዲሁም አዘውትረሽ ስለምትሄጂባቸው ቦታዎች ቆም ብለሽ አስቢ። ከዚያም ‘ሰዎች የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም እንዲጠይቁኝ የሚጋብዙ ነገሮችን ሳይታወቀኝ እያደረግሁ ይሆን?’ ብለሽ ራስሽን ጠይቂ።

በተጨማሪም፦ ዘፍጥረት 34:1, 2⁠ን አንብቢ። ዲና የተባለች አንዲት ወጣት ለፈተና ወደሚያጋልጥ ቦታ መሄዷ ምን መዘዝ እንዳስከተለባት ለማሰብ ሞክሪ።

“አብሮ መውጣት” በይሖዋ ፊት እንደ ቀላል የሚታይ ነገር እንዳልሆነ አስተውዪ፤ አንቺም ይህን ድርጊት አቅልለሽ ልትመለከቺው አይገባም። ትክክል ለሆነው ነገር አቋም ከወሰድሽ ንጹሕ ሕሊና እንዲሁም ለራስሽ አክብሮት ይኖርሻል። ካርሊ የተባለች አንዲት ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “የማንም ጊዜያዊ ስሜት ማርኪያ ለምን ትሆናላችሁ? በይሖዋ ፊት ያላችሁን ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ብዙ ጥረት አድርጋችኋል፤ ይህን አቋማችሁን እንዳታጡ ተጠንቀቁ!”

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወንዶች የሚወዱት ምን ዓይነት ሴቶችን ነው? ወንዶቹ ምን እንደሚሉ ስታነብቢ ትገረሚ ይሆናል!

ቁልፍ ጥቅስ]

“[በአምላክ] ፊት ቆሻሻና እድፍ ሳይኖርባችሁ በሰላም እንድትገኙ የተቻላችሁን ጥረት አድርጉ።”—2 ጴጥሮስ 3:14

ጠቃሚ ምክር

መልካም ባሕርያትን ለማፍራት ጥረት አድርጊ። (1 ጴጥሮስ 3:3, 4) እንዲህ ካደረግሽ የሚቀርቡሽም እንደ አንቺው ጥሩ ባሕርያት ያላቸው ሰዎች ይሆናሉ።

ይህን ታውቅ ነበር?

የፆታ ግንኙነት ይሖዋ በጋብቻ ውስጥ ደስታ እንድናገኝበት አስቦ ያደረገው ዝግጅት ነው፤ የተጋቡ ሰዎች፣ ዝሙት መፈጸም ከሚያስከትለው ጭንቀትና ጸጸት ነፃ ሆነው በፆታ ግንኙነት የሚገኘውን ደስታ ማጣጣም ይችላሉ።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ንጹሕ ሥነ ምግባር ይዞ በመኖር ረገድ እንደ ዮሴፍ ቆራጥ ለመሆን እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ዲና የሠራችውን ዓይነት ስህተት ላለመሥራት እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም አስደሳች ቢመስልም ይህን ማድረግ ትክክል ያልሆነው ለምንድን ነው?

● አንድ ሰው የፆታ ግንኙነት እንድትፈጽሙ ቢጠይቅሽ ምን ታደርጊያለሽ?

[በገጽ 185 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ቆራጥ መሆን ያስፈልጋል! አንድ ወጣት ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንዳደርግ ሊያባብለኝ ሲሞክር ‘እጅህን ሰብስብ!’ ካልኩት በኋላ ኮስተር ብዬ ጥዬው ሄድኩ።”—ኤለን

[በገጽ 187 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካገኙት ሰው ጋር የፆታ ግንኙነት መፈጸም ራስን ማራከስ ነው

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።