በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወንዶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?

ወንዶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?

ምዕራፍ 27

ወንዶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?

ብዙ ወንዶች እንደሚወዱኝ ስለነገርኩት ምን ያህል ተፈላጊ እንደሆንኩ ይገባዋል። አንዳንዶቹ ጓደኞቼ የሚሠሩትን የሞኝ ሥራ ስነግረው በሳቅ ነው የፈረሰው! ነቃ ያልኩ መሆኔንም ሳያስተውል አልቀረም፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ሲሳሳት አርሜዋለሁ። መቼም የሴት ጓደኛው እንድሆን ዛሬ ነገ ሳይል እንደሚጠይቀኝ አልጠራጠርም።

ስትታይ ብታምርም ምንም ቁም ነገር ያላት አትመስልም! በዚያ ላይ ለመናገር እንኳ ፋታ ልትሰጠኝ አልቻለችም። ለመናገር ስሞክር ደግሞ ታርመኛለች! ባገኘኋት ቁጥር እንዴት እንደምገላገላት ሐሳብ ይሆንብኛል።

‘ወንዶች አይወዱኝም’ ብለሽ ትጨነቂያለሽ? ብዙ ወጣቶች ሌላው ቀርቶ በዚህ ረገድ ምንም ችግር እንደሌለባቸው የምታስቢያቸው ሴቶች እንኳ ይህ ጉዳይ ያስጨንቃቸዋል! ጆአን የተባለችውን ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጆአን የደስ ደስ ያላትና አስተዋይ ስትሆን ሐሳቧን ለመግለጽም አትቸገርም። ሆኖም እንዲህ ትላለች፦ “ብዙ ጊዜ ወንዶች እንደማይወዱኝ ይሰማኛል። የወደድኳቸው አንዳንድ ወንዶች መጀመሪያ ላይ የሚፈልጉኝ ቢመስሉም ትንሽ ቆይተው ግን ይዘጉኛል!”

ወንዶች የሚወዱት ምን ዓይነት ሴቶችን ነው? አንዲትን ወጣት እንዳይወዷት የሚያደርጓቸው ነገሮችስ ምንድን ናቸው? ጨዋ የሆነ አንድ ወንድ እንዲወድሽ ምን ማድረግ ትችያለሽ?

ማድረግ ያለብሽ ነገር

ራስሽን እወቂ። የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከደረስሽበት ጊዜ ጀምሮ ለወንዶች ልዩ ትኩረት መስጠት እንደጀመርሽ ታውቆሽ ይሆናል። ምናልባትም የተለያዩ ወንዶች ይማርኩሽ ይሆናል። ይህ ያለ ነገር ነው። ይሁን እንጂ መጀመሪያ ዓይንሽ ውስጥ ለገባው ወንድ ልብሽን ሰጥተሽ ቢሆን ኖሮ ስሜትሽም ሆነ መንፈሳዊነትሽ ሊጎዳ ይችል የነበረ ከመሆኑም ሌላ እየበሰልሽ እንዳትሄጂ እንቅፋት ይሆንብሽ ነበር። መልካም ባሕርያት ለማዳበር፣ ‘አእምሮሽን ለማደስ’ ማለትም መንፈሳዊ አመለካከት ለመያዝ እንዲሁም አንዳንድ ግቦችሽ ላይ ለመድረስ ጊዜ ያስፈልግሻል።—ሮም 12:2፤ 1 ቆሮንቶስ 7:36፤ ቆላስይስ 3:9, 10

እውነት ነው፣ ብዙ ወንዶች የሚፈልጉት ጠንካራ አቋም የሌላቸው ወይም ‘ምንም የማያውቁ’ ሴቶችን ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ወንዶች በዋነኝነት የሚማርካቸው የአንዲት ሴት ማንነት ሳይሆን ቁመናዋና መልኳ ነው። በሌላ በኩል ግን አስተዋይ የሆነ ወንድ የሚፈልገው ጠንካራ ጎኖች ያሏትና ጥሩ አጋር የምትሆነው ሴት ነው።—ማቴዎስ 19:6

ወንዶች ምን ይላሉ? “የራሷ አመለካከትና አቋም ያላት እንዲሁም በራሷ የምትተማመን ሴት ትማርከኛለች።”—ጄምስ

“ያልኩትን ሁሉ ዝም ብላ ከመቀበል ይልቅ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ስሜቷን በግልጽ የምትናገር ሴት ደስ ትለኛለች። አንዲት ልጅ ቆንጆ ብትሆንም እንኳ እኔ መስማት የምፈልገውን ብቻ የምትናገር ከሆነ አትማርከኝም።”—ዳረን

ገጽ 189 ላይ የተጠቀሱት ወንዶች የሰጡትን ሐሳብ ስታነቢ ምን ተሰማሽ?

․․․․․

ለሌሎች አክብሮት ይኑርሽ። አንቺ መወደድ እንደምትፈልጊ ሁሉ ወንዶችም መከበርን በጣም ይፈልጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ባል ሚስቱን መውደድ እንዳለበት ሚስት ደግሞ ባሏን “በጥልቅ ልታከብር” እንደሚገባ የተናገረው ያለምክንያት አይደለም። (ኤፌሶን 5:33) በመቶዎች በሚቆጠሩ ወንዶች ላይ የተደረገ አንድ ጥናትም ከላይ ያለውን ሐሳብ እውነተኝነት ያረጋግጣል፤ ጥናቱ ከተካሄደባቸው ወጣት ወንዶች መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከፍቅር የበለጠ ለአክብሮት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ገልጸዋል። ከጎልማሳ ወንዶች መካከል ደግሞ ከ70 በመቶ የሚበልጡት ተመሳሳይ ምርጫ እንዳላቸው ታውቋል።

አክብሮት ማሳየት ሲባል እሱ ያለሽን ሁሉ መቀበል ማለት አይደለም፤ በሌላ አባባል ከእሱ የተለየ አመለካከት ሊኖርሽ ይችላል፤ እንዲሁም ሐሳብሽን ልትገልጪ ትችያለሽ። (ዘፍጥረት 21:10-12) ይሁን እንጂ ሐሳብሽን የምትገልጪበት መንገድ አንድ ወንድ እንዲቀርብሽ ወይም እንዲርቅሽ ሊያደርግ ይችላል። አንድ ነገር በተናገረ ቁጥር ሐሳቡን የምትቃረኚ ወይም የምታርሚው ከሆነ ለእሱ አክብሮት እንደጎደለሽ ሊሰማው ይችላል። በሌላ በኩል ግን አመለካከቱን የምታከብሪለት እንዲሁም ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ሲናገር አድናቆትሽን የምትገልጪለት ከሆነ የአንቺን አመለካከት መቀበልም ሆነ ማክበር ቀላል ይሆንለታል። በተጨማሪም አስተዋይ የሆነ ወንድ ቤተሰብሽንም ሆነ ሌሎችን በአክብሮት የምትይዢ መሆን አለመሆንሽን ልብ ማለቱ አይቀርም።

ወንዶች ምን ይላሉ? “አንድ ወንድና አንዲት ሴት በግንኙነታቸው መጀመሪያ ላይ ይበልጥ የሚያስፈልጋቸው ነገር መከባበር እንደሆነ ይሰማኛል። ፍቅር እያደር ሊመጣ ይችላል።”—አድሪያን

“አንዲት ሴት ልታከብረኝ ከቻለች ልትወደኝ እንደምትችል አልጠራጠርም።”—ማርክ

ከላይ የተጠቀሱት ወንዶች የሰጡትን ሐሳብ ስታነቢ ምን ተሰማሽ?

․․․․․

ልከኛ አለባበስ ይኑርሽ፤ ንጽሕናሽንም ጠብቂ። አለባበስሽና አጋጌጥሽ ውስጣዊ ማንነትሽን እንዲሁም አመለካከትሽን በግልጽ ያሳያል። አንድ ወንድ ገና ምንም ሳትናገሪ አለባበስሽን አይቶ ስለ አንቺ ብዙ ማወቅ ይችላል። አለባበስሽ ሥርዓታማና ልከኛ ከሆነ ስለ አንቺ ጥሩ መልእክት ያስተላልፋል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9) የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይም ቅጥ ያጣ አለባበስ ግን ስለ አንቺ ጥሩ መልእክት እንደማያስተላልፍ ግልጽ ነው።

ወንዶች ምን ይላሉ? “የአንዲት ሴት አለባበስ ስለ አስተሳሰቧ ብዙ ይናገራል። ሰውነትን የሚያሳዩ ወይም ቅጥ ያጡ ልብሶችን የምትለብስ ከሆነ የሰውን ትኩረት ለማግኘት ስትል የማታደርገው ነገር እንደሌለ ይሰማኛል።”—አድሪያን

“ፀጉሯን የምትንከባከብ እንዲሁም ደስ የሚል መዓዛና ለስላሳ ድምፅ ያላት ሴት ትስበኛለች። በአንድ ወቅት ከአንዲት ቆንጆ ልጅ ጋር ተዋውቄ ነበር፤ ልጅቷ ደስ ብትለኝም ንጽሕናዋን በደንብ ስለማትጠብቅ ራቅኳት።”—ራያን

“አንዲት ሴት አለባበሷ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ከሆነ የወንዶች ዓይን ውስጥ ቶሎ እንደምትገባ ግልጽ ነው። እኔ ግን ከእንዲህ ዓይነት ሴት ጋር የፍቅር ግንኙነት መጀመር አልፈልግም።”—ኒኮላስ

ከላይ የተጠቀሱት ወንዶች የሰጡትን ሐሳብ ስታነቢ ምን ተሰማሽ?

․․․․․

ማድረግ የሌለብሽ ነገር

አታሽኮርምሚ። ሴቶች ወንዶችን የመማረክ ኃይል አላቸው። ይህን ችሎታ ግን ለጥሩ ብቻ ሳይሆን ለመጥፎ ዓላማም ሊጠቀሙበት ይችላሉ። (ዘፍጥረት 29:17, 18፤ ምሳሌ 7:6-23) ያገኘሽውን ወንድ ሁሉ ለመማረክ የምትሞክሪ ከሆነ መጥፎ ስም ልታተርፊ ትችያለሽ።

ወንዶች ምን ይላሉ? “ከአንዲት ቆንጆ ልጅ አጠገብ መቀመጥ በራሱ አንድ ወንድ ልቡ በደስታ እንዲዘል ሊያደርግ ይችላል፤ በመሆኑም አንዲት ሴት ስታዋራህ አሁንም አሁንም የምትነካህ ከሆነ እንደ ማሽኮርመም እቆጥረዋለሁ።”—ኒኮላስ

“አንዲት ሴት ከወንዶች ጋር በምትሆንበት ጊዜ ሁሉ ሰበብ አስባብ እየፈለገች እጃቸውን የምትነካቸው ወይም ደግሞ አላፊ አግዳሚውን እያየች የምትሽኮረመም ከሆነ ትኩረት ለመሳብ እየሞከረች እንደሆነ ይሰማኛል፤ ይህ ደግሞ በጣም ይደብራል።”—ሆሴ

መፈናፈኛ አታሳጪው። አንድ ወንድና አንዲት ሴት ሲጋቡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “አንድ ሥጋ” ይሆናሉ። (ዘፍጥረት 2:24) በዚህ ወቅት ባልና ሚስቱ በነጠላነት ጊዜያቸው የነበራቸው ነፃነት ይቀንሳል፤ ምክንያቱም አንዳቸው ለሌላው ቅድሚያ ለመስጠት ቃል ገብተዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:32-34) ይሁን እንጂ ከአንድ ወንድ ጋር ገና መተዋወቅሽ ከሆነ ከትዳር ጓደኛ የሚጠበቀውን ያህል አንዳችሁ ከሌላው መጠበቅ የለባችሁም። * እንዲያውም ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፍ ነፃነት የምትሰጪው ከሆነ ከአንቺ ጋር መሆን ይበልጥ ያስደስተዋል። ደግሞም ይህን ነፃነቱን የሚጠቀምበትን መንገድ በመመልከት ስለ ማንነቱ ብዙ ማወቅ ትችያለሽ።—ምሳሌ 20:11

ወንዶች ምን ይላሉ? “አንዲት ልጅ እያንዳንዱን እንቅስቃሴዬን ለማወቅ የምትፈልግ ከሆነ እንዲሁም ከእኔ ጋር ካልሆነች በቀር ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎችንም ሆነ ሌሎች ነገሮችን ማከናወን እንደማትችል የምታስብ ከሆነ መፈናፈኛ እንዳሳጣችኝ ይሰማኛል።”—ዳረን

“በቅርብ የተዋወቅኋት አንዲት ወጣት ነጋ ጠባ በሞባይል መልእክት የምትልክልኝ እንዲሁም ከማን ጋር እንዳለሁ በተለይ ደግሞ አብረውኝ ያሉት ሴቶች እነማን እንደሆኑ የምትጠይቀኝ ከሆነ ይህ ከእሷ ጋር ስላለኝ ግንኙነት ቆም ብዬ ማሰብ እንዳለብኝ ይጠቁመኛል።”—ራያን

“አንዲት ሴት ከወንድ ጓደኞቼ ጋር ጊዜ እንዳሳልፍ የማትፈቅድልኝ እንዲሁም የሄድኩበት ሁሉ ካልወሰድኳት የምትበሳጭ ከሆነ መፈናፈኛ እያሳጣችኝ እንደሆነ ስለሚሰማኝ አትማርከኝም።”—አድሪያን

በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር የተጠቀሱት ወንዶች የሰጡትን ሐሳብ ስታነቢ ምን ተሰማሽ?

․․․․․

ለራስሽ አክብሮት ይኑርሽ

የአንድን ወንድ ትኩረትና አድናቆት ለማግኘት ሲሉ ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ ሴቶችን ታውቂ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ የወንድ ጓደኛ አልፎ ተርፎም ባል ለማግኘት ሲሉ ብቻ ከአንድ ወንድ የሚጠብቁትን ነገር ከማያሟላ ሰው ጋር ለመሆን ፈቃደኞች ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ‘አንድ ሰው የዘራውን ያጭዳል’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በዚህ ጉዳይ ላይም ይሠራል። (ገላትያ 6:7-9) ለራስሽም ሆነ ሕይወትሽን ለምትመሪባቸው መሥፈርቶች አክብሮት ከሌለሽ የሚቀርቡሽ ወንዶችም አንቺንም ሆነ የምትመሪባቸውን መሥፈርቶች እንዲያከብሩ መጠበቅ አትችዪም።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሚወዱሽ ሁሉም ወንዶች ሊሆኑ አይችሉም፤ ደግሞም ይህ ጥሩ ነገር ነው! መልክና ቁመናሽን በመጠበቅ ብቻ ሳትወሰኚ ለውስጣዊ ውበትሽ ትኩረት የምትሰጪ ከሆነ “በአምላክ ዓይን ከፍተኛ ዋጋ” ይኖርሻል፤ እንዲሁም ለአንቺ የሚስማማሽን ወንድ ማግኘትሽ አይቀርም።—1 ጴጥሮስ 3:4

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ወንድ ከሆንክ ‘ሴቶች የማይወዱኝ ለምንድን ነው?’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.30 እርግጥ ነው፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት ከተጫጩ በኋላ አንዳቸው ከሌላው ተጨማሪ ነገር ቢጠብቁ ተገቢ ነው።

ቁልፍ ጥቅስ

“ውበት ሐሰት ነው፤ ቁንጅናም ይረግፋል፤ ይሖዋን የምትፈራ ሴት ግን ትመሰገናለች።”—ምሳሌ 31:30 NW

ጠቃሚ ምክር

ከልክ በላይ አትኳኳዪ! መዋቢያዎችን ማብዛት ስለ መልክ ከመጠን በላይ የምትጨነቂ አልፎ ተርፎም ‘እዩኝ እዩኝ’ የምትዪ እንደሆንሽ ሊያስቆጥርሽ ይችላል።

ይህን ታውቅ ነበር?

አንዲት ሴት፣ አንድን ወንድ መፈናፈኛ የምታሳጣው ከሆነ ግንኙነታቸው ሊበላሽ ይችላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ትኩረት ሰጥቼ ማሻሻያ ላደርግበት የምፈልገው ባሕርይ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ለአንድ ወንድ ሐሳቡን እንደምታከብሪለትና ስሜቱን እንደምትረጂለት ማሳየት የምትችዪው እንዴት ነው?

● ለራስሽ አክብሮት እንዳለሽ ማሳየት የምትችዪው እንዴት ነው?

[በገጽ 190 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ብዙ ጊዜ ቶሎ የሚማርኩኝ ቆንጆ ሴቶች እንደሆኑ አልክድም። ይሁን እንጂ አንዲት ልጅ በሕይወቷ ውስጥ ምን ማድረግ እንደምትፈልግ በትክክል የማታውቅ ከሆነችና ጥሩ ግቦች ከሌሏት ለእሷ የነበረኝ ስሜት ብዙም ሳይቆይ ይጠፋል። በሌላ በኩል ደግሞ በሕይወቷ ምን ማድረግ እንደምትፈልግ የምታውቅ እንዲያውም አንዳንድ ግቦቿ ላይ መድረስ የቻለች ሴት በጣም ትማርከኛለች።”—ዴሚየን

[በገጽ 191 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአንድ ብስክሌት ላይ እንዳሉ ሁለት ጎማዎች ሁሉ ፍቅርና አክብሮትም በጣም አስፈላጊ ናቸው