በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መለያየታችን የፈጠረብኝን ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

መለያየታችን የፈጠረብኝን ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 31

መለያየታችን የፈጠረብኝን ስሜት መቋቋም የምችለው እንዴት ነው?

“ለአምስት ዓመት ጓደኛሞች የነበርን ሲሆን ለስድስት ወራት ያህል ደግሞ ስንጠናና ቆይተናል። ከእኔ ጋር ያለውን ግንኙነት ለማቆም ሲወስን ግን ሊነግረኝ እንኳ አልፈለገም። እንዲሁ በድንገት ዘጋኝ። ነገሩ ስሜቴን በጣም ጎዳው። ልቤ በሐዘን ተሰበረ። ‘ምን አድርጌው ይሆን?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር።”—ሬቸል

ከፍቅር ጓደኛ ጋር መለያየት አንድን ሰው ደስታውን ሊያሳጣውና በሐዘን እንዲዋጥ ሊያደርገው ይችላል። ለሁለት ዓመት ያህል ሲጠናኑ የቆዩትን ጄፍንና ሱዛንን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በዚህ ጊዜ ውስጥ ጄፍና ሱዛን እየተዋደዱ መጡ። ጄፍ በቀን ውስጥ በርካታ የፍቅር መልእክቶችን በሞባይል ይልክላታል። ከዚህም በተጨማሪ እንደሚወዳት ለማሳየት አንዳንድ ጊዜ ስጦታዎች ይሰጣታል። ሱዛን እንዲህ ብላለች፦ “ጄፍ ትኩረት ሰጥቶ የሚያዳምጠኝ ከመሆኑም ሌላ ስሜቴን ይረዳልኝ ነበር። እንዲሁም እንደምወደድ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር።”

ብዙም ሳይቆይ ጄፍና ሱዛን ትዳር ስለ መመሥረት ብሎም ከተጋቡ በኋላ ስለሚኖሩበት ቦታ ማውራት ጀመሩ። ሌላው ቀርቶ ጄፍ ቀለበት ሊያስርላት እንዳሰበ ሱዛን አውቃለች። ይሁንና ጄፍ በድንገት ከእሷ ጋር ያለውን ግንኙነት አቆመ! በዚህ ጊዜ ሱዛን ልቧ ተሰበረ። ስሜቷ በጣም በመጎዳቱ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዋን ታከናውን የነበረው በደመ ነፍስ ነበር። “አእምሮዬም ሆነ ሰውነቴ ደንዝዞ ነበር” በማለት ተናግራለች። *

መለያየት ልብ የሚሰብረው ለምንድን ነው?

አንቺም እንደ ሱዛን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞሽ ከሆነ ‘ይህን ሁኔታ አልፌ እንደ ድሮዬ መሆን እችል ይሆን?’ ብለሽ ራስሽን ትጠይቂ ይሆናል። እንዲህ ቢሰማሽ የሚያስገርም አይደለም። ንጉሥ ሰለሞን “ፍቅር እንደ ሞት የበረታች . . . ናት” ሲል ጽፏል። (ማሕልየ መሓልይ 8:6) ከወንድ ጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ በሕይወትሽ ውስጥ ካጋጠሙሽ ሁኔታዎች ሁሉ የበለጠ ስሜትሽን ጎድቶት ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች መለያየት የሞት ያህል ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። አንቺም እንዲህ ይሰማሽ አሊያም ከታች እንደተጠቀሱት ያሉ ሌሎች ስሜቶች ይፈራረቁብሽ ይሆናል።

ነገሩን አለመቀበል። ‘በፍጹም ሊሆን አይችልም! ነገ ከነገ ወዲያ ሐሳቡን መቀየሩ አይቀርም።’

ንዴት። ‘እንዴት እንዲህ ያደርገኛል? ከአሁን በኋላ ዓይኑን ማየት አልፈልግም!’

በጭንቀት መዋጥ። ‘እኔን ማንም አይወደኝም። ከእንግዲህ የሚፈልገኝ አይኖርም።’

እውነታውን አምኖ መቀበል። ‘ግንኙነታችን መቋረጡ ስሜቴን የጎዳው ቢሆንም ይህ ሁሉ አልፎ እንደ ድሮው ደህና መሆኔ አይቀርም።’

ደስ የሚለው ግን ሁሉም ነገር አልፎ እውነታውን አምነሽ ወደ መቀበል ደረጃ መድረስ የምትችዪ መሆኑ ነው። እርግጥ ነው፣ እዚህ ደረጃ ላይ ለመድረስ የሚወስድብሽ ጊዜ በተለያዩ ነገሮች ላይ የተመካ ነው፤ በመጠናናት ረጅም ጊዜ ቆይታችሁ ከሆነና በጣም ተቀራርባችሁ ከነበረ መለያየታችሁን ለመቀበል ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድብሽ ይችላል። ታዲያ የተሰበረውን ልብሽን ለመጠገን ምን ማድረግ ትችያለሽ?

ሐዘኑን ለመቋቋም የሚረዱ እርምጃዎች

ጊዜ የማይሽረው ቁስል እንደሌለ ሲነገር ሰምተሽ ይሆናል። ከወንድ ጓደኛሽ ጋር በተለያየሽ ሰሞን ይህ አባባል ብዙም ትርጉም አይሰጥሽ ይሆናል። ምክንያቱም የጊዜ ማለፍ ብቻውን መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ነገር ቢቆርጥሽ ቁስሉ ከጊዜ በኋላ መዳኑ እንደማይቀር ታውቂያለሽ፤ ያም ቢሆን ግን በወቅቱ ማመሙ አይቀርም። በመሆኑም መድማቱን ለማስቆምና ሕመሙን ለማስታገስ አንድ ነገር ማድረግ ይኖርብሻል። በተጨማሪም ቁስሉ እንዳያመረቅዝ ጥንቃቄ ማድረግ አለብሽ። ስሜት በሚጎዳበት ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። መጀመሪያ ላይ በውስጥሽ የሚሰማሽ ሥቃይ ይኖራል። ይሁንና ሥቃዩን ለማስታገስ እንዲሁም ቁስሉ እንዳያመረቅዝ በሌላ አባባል በውስጥሽ ጥላቻ እንዳይፈጠር አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችያለሽ። ጊዜ እያለፈ መሄዱ በራሱ የሚያመጣው ለውጥ አለ፤ እስከዚያው ድረስ ግን አንቺ ምን ማድረግ ትችያለሽ? የሚከተሉትን እርምጃዎች ለመውሰድ ሞክሪ፦

ስሜትሽን አምቀሽ አትያዢ። ሐዘንሽ እንዲወጣልሽ ብለሽ ብታለቅሺ ምንም ስህተት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስም ቢሆን “ለማልቀስ ጊዜ አለው” እንዲሁም “ዋይ ለማለት ጊዜ አለው” ይላል። (መክብብ 3:1, 4 የ1954 ትርጉም) ማልቀስ የድክመት ምልክት አይደለም። ደፋር ተዋጊ የነበረው ዳዊትም እንኳ ስሜቱ በጣም ተጎድቶ በነበረበት ወቅት “ሌሊቱን ሁሉ በልቅሶ ዐልጋዬን አርሳለሁ፤ መኝታዬንም በእንባዬ አሾቃለሁ” ሲል ተናግሯል።—መዝሙር 6:6

ጤንነትሽን ተንከባከቢ። የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግና የተመጣጠነ ምግብ መመገብ፣ ስሜትሽ በመደቆሱ የተሟጠጠው ኃይልሽ እንዲታደስ ይረዳሻል። መጽሐፍ ቅዱስ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል” ይላል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8

ከጤንነትሽ ጋር በተያያዘ ለየትኞቹ ነገሮች ትኩረት መስጠት ያስፈልግሻል?

․․․․․

ራስሽን በተለያዩ ነገሮች አስጠምጂ። የሚያስደስቱሽን ነገሮች ከማድረግ አትቆጠቢ። በተለይ በዚህ ወቅት ራስሽን ማግለል አይኖርብሽም። (ምሳሌ 18:1) ከሚያስቡልሽ ሰዎች ጋር መቀራረብሽ አዎንታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ እንድታተኩሪ ይረዳሻል።

ምን ዓይነት ግቦች ልታወጪ ትችያለሽ?

․․․․․

ለአምላክ ስሜትሽን አውጥተሽ ንገሪው። ይህን ማድረግ ይከብድሽ ይሆናል። እንዲያውም አንዳንዶች ከፍቅር ጓደኛቸው ጋር ሲለያዩ አምላክ እንደተዋቸው ሆኖ ይሰማቸዋል። ‘ለእኔ የሚሆነኝ ሰው እንዲሰጠኝ አምላክን ደጋግሜ ለምኜዋለሁ፤ መጨረሻው ግን ይሄ ሆነ!’ በማለት በምሬት ይናገራሉ። (መዝሙር 10:1) ይሁንና አምላክ የትዳር ፈላጊዎች አገናኝ እንደሆነ አድርጎ ማሰብ ተገቢ ነው? በፍጹም! ደግሞም አንደኛው ወገን ግንኙነቱን ለመቀጠል ፈቃደኛ ባይሆን አምላክ በዚህ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ይሁን እንጂ በእርግጠኝነት መናገር የምንችለው ነገር አለ፤ ይሖዋ ‘ስለ አንቺ ያስባል።’ (1 ጴጥሮስ 5:7) በመሆኑም የሚሰማሽን ሁሉ በጸሎት ንገሪው። መጽሐፍ ቅዱስ “ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከማሰብ ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል” ይላል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7

ከወንድ ጓደኛሽ ጋር መለያየትሽ ያስከተለብሽን ሐዘን ለመቋቋም በምታደርጊው ጥረት ይሖዋ እንዲረዳሽ ስትጸልዪ የትኞቹን ነገሮች መጥቀስ ትችያለሽ?

․․․․․

ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማሰብ

መለያየታችሁ ያስከተለው የስሜት ቁስል እንዲሽር ጊዜ ከሰጠሽው በኋላ መለስ ብለሽ ስለነበራችሁ ግንኙነት ማሰብሽ ሊጠቅምሽ ይችላል። ይህን ለማድረግ የምትችይበት ደረጃ ላይ እንደደረስሽ ከተሰማሽ  በገጽ 224 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክሪ።

የፍቅር ግንኙነት ስትጀምሪ መጨረሻው ይህ እንደሚሆን እንዳልጠበቅሽ ጥያቄ የለውም። ሆኖም ልትረሺው የማይገባ ነገር አለ፤ ኃይለኛ ዝናብ እየጣለ ባለበት ወቅት በአብዛኛው ትኩረት የምናደርገው በጠቆረው ሰማይና በሚጥለው ዶፍ ላይ ይሆናል። ትንሽ ቆይቶ ግን ዝናቡ ማቆሙና ሰማዩ ጥርት ማለቱ አይቀርም። በተመሳሳይም በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ወጣቶች ያጋጠማቸውን ሁኔታ በጊዜ ሂደት መርሳት ችለዋል። አንቺም እንዲሁ ማድረግ እንደምትችዪ አትጠራጠሪ!

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስብሽ ራስሽን ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችያለሽ?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት በሙሉ ሴቶች ቢሆኑም ነጥቦቹ ለወንዶችም ይሠራሉ።

ቁልፍ ጥቅስ

“[ይሖዋ] ልባቸው የተሰበረውን ይፈውሳል፤ ቍስላቸውንም ይጠግናል።”—መዝሙር 147:3

ጠቃሚ ምክር

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰችው ሱዛን የተወሰኑ ጥቅሶችን ጽፋ በቀላሉ ልታገኘው የምትችልበት ቦታ አስቀምጣለች፤ በሐዘን ስሜት በምትዋጥበት ጊዜ ጥቅሶቹን እያወጣች ታነብባለች። አንቺም በዚህ ምዕራፍ ውስጥ ከተጠቀሱት ጥቅሶች አንዳንዶቹን በመጠቀም እንደ ሱዛን ማድረግ ትችያለሽ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሆነው የፍቅር ጓደኝነት የሚጀምሩ አብዛኞቹ ወጣቶች ግንኙነታቸው አይዘልቅም፤ ግንኙነታቸው ቀጥሎ ትዳር ቢመሠርቱ እንኳ በአብዛኛው ይፋታሉ።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

መለያየቱ ያስከተለብኝን ሐዘን ተቋቁሜ እንደ ቀድሞዬ መሆን እንድችል እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ወደፊት መጠናናት ስጀምር ጥሩ የፍቅር ጓደኛ ለመሆን ልሠራበት የሚገባ ነገር ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከፍቅር ጓደኛው ጋር የተለያየ ሰው ከዚህ ሁኔታ ስለ ራሱ ምን መማር ይችላል?

● ከተቃራኒ ፆታ ጋር በተያያዘስ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላል?

[በገጽ 227 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ውሎ ሲያድር ነገሮችን ይበልጥ ሚዛናዊ ሆኖ ማየት ይቻላል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ስሜታችሁ እየተረጋጋ መሄዱ አይቀርም፤ በመሆኑም ሁኔታውን ባልተዛባ መንፈስ መመልከትና ነገሩን አምናችሁ መቀበል ትችላላችሁ። ከዚህ በተጨማሪ ይህ ሁኔታ ስለ ማንነታችሁ፣ ከፍቅር ጓደኛችሁ ስለምትጠብቁት ነገር እንዲሁም ተመሳሳይ ስህተት እንዳትሠሩ ምን ዓይነት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባችሁ ይበልጥ ለማወቅ ያስችላችኋል።”—ኮሪና

[በገጽ 224 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 የመልመጃ ሣጥን

ከተፈጠረው ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት እችላለሁ?

እንድትለያዩ የፈለገበትን ምክንያት ነግሮሻል? ከሆነ ምክንያቱ አጥጋቢ እንደሆነ ባይሰማሽ እንኳ ጻፊው። ․․․․․

ጓደኝነታችሁ እንዲቋረጥ ምክንያት ሊሆን ይችላል ብለሽ የምታስቢው ሌላ ነገር አለ? ․․․․․

መለስ ብለሽ ስታስቢው ይህ ሁኔታ እንዳይፈጠር ልታደርጊ የምትችዪው ነገር እንደነበረ ይሰማሻል? ካለ ጻፊው። ․․․․․

እንዲህ ያለ ሁኔታ መከሰቱ መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ ብስለት እንዲኖርሽ በየትኞቹ አቅጣጫዎች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግሽ ጠቁሞሻል? ․․․․․

ወደፊት ከሌላ ሰው ጋር መጠናናት ብትጀምሪ በግንኙነታችሁ ረገድ ለውጥ ማድረግ ያለብሽ ነገር እንዳለ ይሰማሻል? ․․․․․

[በገጽ 223 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መለያየት የሚፈጥረው ስሜት ከቁስል ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ በወቅቱ ቢያምም በጊዜ ሂደት መዳኑ አይቀርም