በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እውነተኛ ፍቅር መሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

እውነተኛ ፍቅር መሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

ምዕራፍ 29

እውነተኛ ፍቅር መሆኑን እንዴት አውቃለሁ?

የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ፦

1. “እውነተኛ ፍቅርን” እንዴት ትገልጸዋለህ? ․․․․․

2. “የወረት ፍቅርን” እንዴት ትገልጸዋለህ? ․․․․․

3. በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ምን ይመስልሃል? ․․․․․

ከላይ ያሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ያን ያህል አልተቸገርክ ይሆናል። ጉዳዩ አንተን የሚመለከት እስካልሆነ ድረስ በእውነተኛ ፍቅርና በወረት ፍቅር መካከል ያለውን ልዩነት መናገሩ ብዙ አይከብድህም።

የምትፈልጋት ዓይነት ሴት ስታገኝ ግን ሁሉ ነገር ይለወጣል። በፍቅር ክንፍ ስለምትል ሌላ ነገር አይታይህም። ልብህ እስኪጠፋ ትወዳታለህ። ሆኖም እስቲ ቆም ብለህ አስብ፦ የያዘህ እውነተኛ ፍቅር ነው ወይስ የወረት ፍቅር? ይህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? መልሱን ለማወቅ እስቲ በቅድሚያ ለተቃራኒ ፆታ ያለህ አመለካከት ልጅ ከነበርክበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል እንደተለወጠ እንመልከት። ለምሳሌ ያህል፣ ለሚከተሉት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ?

● የአምስት ዓመት ልጅ እያለህ ስለ ተቃራኒ ፆታ ምን ይሰማህ ነበር?

አሁንስ ስለ ተቃራኒ ፆታ ምን ይሰማሃል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች የሰጠኸው መልስ፣ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ስትደርስ ለተቃራኒ ፆታ ያለህ አመለካከት እንደተለወጠ የሚጠቁም መሆኑ አይቀርም። የ12 ዓመቱ ብራያን “አሁን አሁን ሴቶች ልጆች ቆንጆ ሆነው ይታዩኝ ጀምሯል” ብሏል። የ16 ዓመቷ ኢሌይንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተቃራኒ ፆታ ያላት አመለካከት እንደተለወጠ ተሰምቷታል። እንዲህ ብላለች፦ “ጓደኞቼ በሙሉ ወሬያቸው ስለ ወንዶች ሆነ። እኔም ያየሁት ወንድ ሁሉ ይማርከኝ ጀመር።”

ታዲያ አንተስ በዚህ ለውጥ የተነሳ በውስጥህ የሚፈጠረውን ኃይለኛ ስሜት መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው? እንዲህ ያለውን ስሜት እንደሌለ አድርገህ መቁጠሩ ስሜቱ እንዲያይል ከማድረግ በቀር የሚፈይደው ነገር የለም፤ በሌላ በኩል ግን ይህን ሁኔታ በተቃራኒ ፆታ ስለ መማረክ፣ ስለ ወረት ፍቅር እንዲሁም ስለ እውነተኛ ፍቅር ለማወቅ እንደሚያስችል ግሩም አጋጣሚ አድርገህ ልትመለከተው ትችላለህ። ከፍቅር ጋር በተያያዘ እነዚህን ሦስት ነገሮች መረዳትህ ከብዙ ሥቃይ የሚጠብቅህ ከመሆኑም ሌላ ውሎ አድሮ እውነተኛ ፍቅር ለማግኘት ይረዳሃል።

መማረክ መልክ

“እኔና ጓደኞቼ ሁልጊዜ የምናወራው ስለ ሴቶች ነው። ስለ ሌሎች ጉዳዮች እያወራንም እንኳ አንዲት ቆንጆ ልጅ በአጠገባችን ስታልፍ ወሬያችንን ሁሉ ረስተን ስለ እሷ ማውራት እንጀምራለን!”—አሊክስ

“ዓይን ዓይኔን እያየ የሚያናግረኝ፣ ደስ የሚል ፈገግታ ያለውና ኮራ ብሎ የሚራመድ ወንድ ቀልቤን ይስበዋል።”—ሎሪ

ቆንጆ ሴት ወይም መልከ ቀና ወንድ ሲያዩ መማረክ ያለ ነገር ነው። ችግሩ ግን የአንድ ሰው ውስጣዊ ማንነት እንደ መልኩ ላይሆን ይችላል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም መልክ አሳሳች ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “በእርያ አፍንጫ ላይ እንደተሰካ የወርቅ ቀለበት፣ ማስተዋል የጐደላት ቆንጆ ሴት እንዲሁ ናት” ይላል። (ምሳሌ 11:22) ይህ አባባል ለወንዶችም እንደሚሠራ ጥርጥር የለውም።

የወረት ፍቅር ስሜት

“በ12 ዓመቴ ከአንድ ልጅ ጋር ፍቅር ይዞኝ ነበር፤ ልጁን ለምን እንደወደድኩት የገባኝ የያዘኝ የወረት ፍቅር ሲለቀኝ ነው። ጓደኞቼ በሙሉ የሚያስቡት ስለ ወንዶች ነበር፤ እኔም ልጁን ወንድ ስለሆነ ብቻ ወደድኩት። በቃ ምክንያቴ ይኸው ነበር!”—ኢሌይን

“ከተለያዩ ሴቶች ጋር የወረት ፍቅር ይዞኝ ያውቃል፤ በአብዛኛው የተማረክሁት መልካቸውን አይቼ ነው። ባሕርያቸውን ስመለከት ግን ያሰብኩትን ያህል እንደማንጣጣም ገባኝ።”—ማርክ

የወረት ፍቅር ሲይዝህ እውነተኛ ፍቅር የያዘህ ሊመስልህ ይችላል። ለነገሩ እውነተኛ ፍቅር የያዘው ሰውም ቢሆን ለሚወደው ሰው የተለየ ስሜት እንደሚኖረው የታወቀ ነው። ይሁንና ለእውነተኛ ፍቅር እና ለወረት ፍቅር መፈጠር ምክንያት የሚሆነው ነገር ይለያያል። አንድ ሰው የወረት ፍቅር የሚይዘው በመልክና በቁመና ተማርኮ ነው። በተጨማሪም የወረት ፍቅር የያዘው ሰው የወደዳት ሴት ድክመት ፈጽሞ የማይታየው ከመሆኑም ሌላ ጠንካራ ጎኖቿን አጋንኖ ይመለከታል። በመሆኑም የወረት ፍቅር የባሕር ዳርቻ ላይ በአሸዋ ቁልል እንደተሠራ ቤት ነው፤ ብዙም ሳይቆይ ውኃ አጥቦ ይወስደዋል። ፊዮና የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ያለው ፍቅር አይዘልቅም፤ ዛሬ ከአንዱ የዛሬ ወር ደግሞ ከሌላው ጋር እንዲህ ዓይነት ፍቅር ሊይዛችሁ ይችላል!”

እውነተኛ ፍቅር → እውቀት

“እውነተኛ ፍቅር ሲይዝህ አንድን ሰው የምትወደው በቂ ምክንያት ስላለህ እንጂ ስለ ራስህ ብቻ ስለምታስብ አይደለም።”—ዴቪድ

“እውነተኛ ፍቅር ቀስ በቀስ እያደገ የሚመጣ ነገር እንደሆነ ይሰማኛል። መጀመሪያ ላይ ከአንድ ሰው ጋር እንዲሁ ጥሩ ጓደኛሞች ልትሆኑ ትችላላችሁ። እያደር ግለሰቡን እያወቃችሁት ስትሄዱ ባሕርዩን ትወዱለታላችሁ፤ ከዚያም ቀደም ሲል ለዚያ ሰው ያልነበራችሁ ዓይነት ስሜት በውስጣችሁ ይፈጠራል።”—ጁዲት

እውነተኛ ፍቅር የሚመጣው ስለ አንድ ሰው ጥንካሬና ድክመት በሚገባ ስታውቅ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርን ከስሜት ጋር ብቻ አያይዞ የማይጠቅሰው ለዚህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ፍቅር ታጋሽና ደግ ነው። . . . ሁሉን ችሎ ያልፋል፣ ሁሉን ያምናል፣ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፣ ሁሉን ነገር በጽናት ይቋቋማል። ፍቅር ፈጽሞ አይከስምም።” (1 ቆሮንቶስ 13:4, 7, 8) እውነተኛ ፍቅር የያዘው ሰው እነዚህን ነገሮች የሚያደርገው ጭፍን ስለሆነ ወይም ስለሚወደው ሰው ምንም ስለማያውቅ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ግለሰቡ ማንነት የተሟላ እውቀት ስላለው ነው።

የእውነተኛ ፍቅር ምሳሌ

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው የያዕቆብ እና የራሔል ታሪክ እውነተኛ ፍቅር ምን እንደሆነ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው። ያዕቆብ እና ራሔል መጀመሪያ የተገናኙት ራሔል የአባቷን በጎች ውኃ ልታጠጣ ወደ ውኃ ጉድጓድ በመጣችበት ወቅት ነበር። ብዙም ሳይቆይ ያዕቆብ በራሔል ተማረከ። የማረከው ምንድን ነው? ራሔል “ቁመናዋ ያማረ መልኳም የተዋበ” መሆኗ ነው።—ዘፍጥረት 29:17

ይሁንና ለእውነተኛ ፍቅር መሠረት የሚሆነው ነገር መልክና ቁመና ብቻ እንዳልሆነ አስታውስ። ያዕቆብ ከራሔል ውጫዊ ውበት ባሻገር ያየው ነገር አለ። መጀመሪያ ላይ በውበቷ ተማርኮ ነበር፤ ብዙም ሳይቆይ ግን ራሔልን ‘እጅግ እንደወደዳት’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 29:18 የ1980 ትርጉም

ታዲያ ታሪኩ በዚህ አበቃ ማለት ነው? በፍጹም! ያዕቆብ ራሔልን ለማግባት ሰባት ዓመት መጠበቅ እንዳለበት አባቷ ነገረው። የአባቷ ጥያቄ ተገቢ ሆነም አልሆነ፣ ይህ አጋጣሚ ያዕቆብ ለራሔል ያለውን ፍቅር የሚፈትን ነበር። ያዕቆብ የያዘው የወረት ፍቅር ከሆነ ይህን ያህል ጊዜ መጠበቅ አይችልም። በጊዜ ርዝመት ፈጽሞ የማይለወጠው እውነተኛ ፍቅር ብቻ ነው። ታዲያ ያዕቆብ ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ያዕቆብም ራሔልን ለማግኘት ሲል ሰባት ዓመት አገለገለ፤ አጥብቆ ይወዳትም ስለ ነበረ፣ ሰባት ዓመት እንደ ጥቂት ቀን ሆኖ ታየው።”—ዘፍጥረት 29:20

ከያዕቆብ እና ከራሔል ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ? እውነተኛ ፍቅር በጊዜ መርዘም አይቀዘቅዝም። በመልክና ቁመና ላይ ብቻ የተመሠረተም አይደለም። እንዲያውም ጥሩ የትዳር ጓደኛ የምትሆንህ ምናልባት መጀመሪያ ስታያት ያን ያህል ያልማረከችህ ሴት ልትሆን ትችላለች። እስቲ ባርባራ የተባለችውን ወጣት እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ባርባራ ከስቲቨን ጋር ስትተዋወቅ መጀመሪያ ላይ ያን ያህል እንዳልማረካት ተናግራለች። “ይበልጥ እያወቅሁት ስሄድ ግን አመለካከቴ ተቀየረ። ስቲቨን ለሌሎች ሰዎች የሚያስብና ምንጊዜም ከራሱ ይልቅ ሌሎችን የሚያስቀድም ሰው እንደሆነ ተመለከትኩ። እነዚህ ባሕርያት ያሉት ሰው ጥሩ ባል እንደሚሆን አውቃለሁ። በመሆኑም እየወደድኩት መጣሁ።” ባርባራና ስቲቨን አሁን ጥሩ ትዳር አላቸው።

ትዳር ለመመሥረት ደርሰሃል እንበል፤ ከአንዲት ሴት ጋር በምትጠናናበት ወቅት ለእሷ ያለህ ስሜት እውነተኛ ፍቅር መሆን አለመሆኑን እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ልብህ የሚለውን ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው አእምሮህ የሚነግርህን አዳምጥ። መልክና ቁመና ላይ ብቻ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ስለ ማንነቷ በደንብ ለማወቅ ጥረት አድርግ። ጊዜ ወስዳችሁ በደንብ መተዋወቃችሁ ጠንካራ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችላችኋል። የወረት ፍቅር እንደማይዘልቅ አስታውስ። እውነተኛ ፍቅር ግን ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ይበልጥ እየጠነከረ በመሄድ “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” ይሆናል።—ቆላስይስ 3:14

በመልክና በቁመና ብቻ ከመማረክ ወይም በስሜት ተመርተህ በወረት ፍቅር ከመውደቅ ይልቅ በውስጣዊ ማንነት ላይ ትኩረት የምታደርግ ከሆነ እውነተኛ ፍቅር እንደምታገኝ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። በሚቀጥሉት ሦስት ገጾች ላይ ያሉት ነጥቦች እውነተኛ ፍቅር ለማግኘት ይረዱሃል።

ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 1 እና 3 ተመልከት

በሚቀጥለው ምዕራፍ

እውነተኛ ፍቅር እንደያዘህ እርግጠኛ ነህ። ይሁንና ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ መሆንህን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

ቁልፍ ጥቅስ

“የውሃ ብዛት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፣ ፈሳሾችም አያሰጥሟትም።”—ማሕልየ መሓልይ 8:7

ጠቃሚ ምክር

ወጣቶች፣ የተማረኩበትን ሰው ምን ያህል እንደሚያውቁት ለመገምገም በዚህ መጽሐፍ ጥራዝ 2 ገጽ 39 (ለሴቶች) እና ገጽ 40 (ለወንዶች) ላይ ያሉትን መልመጃዎች መሥራታቸው ይጠቅማቸዋል።

ይህን ታውቅ ነበር?

የፍቅር ጓደኞችን እንደ ልብስ የሚቀያይሩ ወጣቶች ፍቺን “ከአሁኑ እየተለማመዱ” ያሉ ያህል ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ለአንድ ሰው ያለኝ ስሜት የወረት ፍቅር ይሁን እውነተኛ ፍቅር ለማወቅ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● አምላክ የሰው ልጆችን ሲፈጥር በተቃራኒ ፆታዎች መካከል ከፍተኛ መሳሳብ እንዲኖር ያደረገው ለምንድን ነው?

● በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ብዙ ወጣቶች “ፍቅር” የማይዘልቀው ለምንድን ነው?

[በገጽ 207 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እውነተኛ ፍቅር ማንኛውንም እንቅፋት ተቋቁሞ ማለፍ ይችላል፤ የወረት ፍቅር ግን ሁኔታዎች ሲለዋወጡ ወይም ችግሮች ሲፈጠሩ ይቀዘቅዛል። እውነተኛ ፍቅር የሚመጣው በጊዜ ሂደት ነው።”—ዳንዬላ

[በገጽ 209 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመልመጃ ሣጥን

አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊያለሽ?

ማይክል እና ጁዲ የፍቅር ጓደኝነት ከጀመሩ ሦስት ወራት ተቆጥረዋል፤ ጁዲ በፍቅሩ ክንፍ እንዳለች ትናገራለች። ማይክልም ቢሆን ጁዲን በጣም ይወዳታል፤ በሌላ በኩል ግን እያንዳንዱን ነገር ሌላው ቀርቶ ምን እንደምትለብስና ከእነማን ጋር እንደምትውል እንኳ መቆጣጠር ይፈልጋል። ማይክል ጁዲን እንደ ልዕልት ይንከባከባታል፤ ባለፈው ሳምንት ግን ‘ከሌላ ወንድ ጋር ስታወሪ አገኘሁሽ’ በሚል በጥፊ አጮላት።

ማይክል፦ “ጁዲ እሷን አጥቼ መኖር እንደማልችል እንዲገባት እፈልጋለሁ። ሌላ ወንድ እሷን ሊነጥቀኝ እንደሚችል ማሰቡ እንኳ ሊያሳብደኝ ይደርሳል! እርግጥ በጥፊ ስለመታኋት ተሰምቶኛል። ይህን ያደረግሁት ግን ሌላ ወንድ ቀና ብላ ማየቷ እንኳ ውስጤን ቅጥል ስለሚያደርገው ነው። ደግሞም ይቅርታ ጠይቄያታለሁ!”

ጁዲ፦ “ወላጆቼ፣ ማይክል በጣም እንደሚቆጣጠረኝ ይነግሩኛል፤ እኔ ግን ይህን የሚያደርገው ከፍ ያለ የሥነ ምግባር አቋም ስላለው እንደሆነ ይሰማኛል። ለምሳሌ፣ ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንድንፈጽም ተጭኖኝ አያውቅም። በጥፊ የመታኝም ቢሆን ከሌላ ወንድ ጋር ሳወራ ስላየኝ ነው፤ በእርግጥ እንደመታኝ ለወላጆቼ አልነገርኳቸውም። የሚቀናውም እኮ በጣም ስለሚወደኝ ነው፤ እንዲያውም የሚቀና መሆኑ ደስ ይለኛል። ለማንኛውም አሁን ይቅርታ ጠይቆኛል፤ ደግሞም ሁለተኛ እንደማይደግመው ቃል ገብቶልኛል።”

አንቺ ምን ትያለሽ? የማይክል እና የጁዲ ግንኙነት ችግር እንዳለበት ይሰማሻል? ከሆነ ችግሩ ምንድን ነው? ․․․․․

ጁዲ ምን ማድረግ ያለባት ይመስልሻል? ․․․․․

አንቺ ብትሆኚ ምን ታደርጊያለሽ? ․․․․․

[በገጽ 210 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመልመጃ ሣጥን

አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?

ኤታን ከአሊሳ ጋር የፍቅር ጓደኝነት ከጀመረ ሁለት ወር ሆኖታል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ አሊሳ ከሌሎች ጋር በተለይም ከወላጆቿ ጋር መጨቃጨቅ እንደሚቀናት አስተውሏል። እንዲያውም አሊሳ ከወላጆቿ ጋር ነጋ ጠባ የምትነዛነዝ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ የእሷ ፍላጎት እንዲፈጸም ታደርጋለች። ወላጆቿ ከእሷ ጋር መጨቃጨቅ ሰልችቷቸው ካልተረቱላት በስተቀር አሊሳ ከአቋሟ ፍንክች አትልም። አሊሳ ወላጆቿን “እንደፈለገች እንደምታሽከረክራቸው” ለኤታን በኩራት ነግራዋለች።

ኤታን፦ “አሊሳ የተሰማትን ከመናገር ወደኋላ አትልም። እሷ እስካልመሰላት ድረስ የማንንም ሌላው ቀርቶ የወላጆቿን ሐሳብ እንኳ አትቀበልም። ለነገሩ አባቷ የሚያበሳጭ ሰው ነው፤ ስለዚህ በእሱ ላይ ብትጮኽበት ምንም አያስገርምም። ደግሞም አሊሳ ወላጆቿ ላይ ሁልጊዜ ትጮኽባቸዋለች ማለት አይደለም። አባትና እናቷ የምትፈልገውን እንዲያደርጉላት ስትል ልታለቅስ ወይም ልታኮርፍ ትችላለች፤ ይህም ካልሠራ ደግሞ በመለማመጥ አንጀታቸውን ለመብላት ትሞክራለች።”

አሊሳ፦ “ማንም ቢሆን ወይም ምንም ዓይነት ሥልጣንና ቦታ ቢኖረው ለእኔ ግድ አይሰጠኝም፤ የመሰለኝን ነገር ፊት ለፊት ከመናገር ወደኋላ አልልም። ኤታንም ቢሆን ከወላጆቼ ጋር ሳወራ ስላየኝ ይህን ባሕርዬን ያውቃል።”

አንተ ምን ትላለህ? የኤታን እና የአሊሳ ግንኙነት ችግር እንዳለበት ይሰማሃል? ከሆነ ችግሩ ምንድን ነው? ․․․․․

ኤታን ምን ማድረግ ያለበት ይመስልሃል? ․․․․․

አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ? ․․․․․

[በገጽ 211 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የመልመጃ ሣጥን

እውነተኛ ፍቅር ነው ወይስ የወረት ፍቅር?

ከታች ካሉት ሐሳቦች የጎደለውን ማሟላት ትችላለህ? እውነተኛ ፍቅር ወይም የወረት ፍቅር የሚሉትን ሐረጎች በመጠቀም ክፍት ቦታዎቹን ለማሟላት ሞክር።

1. “․․․․․․ ዕውር ሲሆን ዓይናማ መሆንም አይፈልግም። እውነታውን ላለመቀበል ይሞክራል።”—ካልቪን

2. “ከወደድኳት ልጅ ጋር ስሆን ያልሆንኩትን ሆኜ ለመታየት የምጥር ከሆነ ይህ ․․․․․ ነው።”—ቶማስ

3. “․․․․․ ከሆነ የምትወዳት ልጅ፣ ደስ የማይልህ ባሕርይ ቢኖራትም እንኳ ግንኙነታችሁን ከማቋረጥ ይልቅ ለችግሩ መፍትሔ ለማግኘት ሁለታችሁም ጥረት ታደርጋላችሁ።”—ራያን

4. “․․․․․ ከሆነ የሚታዩህ ሁለታችሁን የሚያመሳስሏችሁ ነገሮች ብቻ ናቸው።”—ክሎዲያ

5. “․․․․․ የያዘው ሰው ማንነቱን ለመደበቅ አይሞክርም።”—ኢቭ

6. “․․․․․ ከሆነ የማስበው ስለ ራሴ ጥቅም ብቻ ነው፤ ምናልባትም ግንኙነቱን የጀመርኩት ‘የወንድ ጓደኛ አለኝ’ ለማለት ያህል ይሆናል።”—አሊሰን

7. “․․․․․ ከሆነ የምወደው ሰው ያሉትን ድክመቶች ላለማየት ዓይኔን አልጨፍንም፤ ከዚህ ይልቅ እነዚህን ድክመቶች ችዬ ለመኖር ፈቃደኛ እሆናለሁ።”—ኤፕርል

8. “․․․․․ በሚሆንበት ጊዜ አንዲትን ልጅ ‘ወደድኳት’ ከማለት ውጭ ለምን እንደወደድካት መግለጽ ይቸግርሃል።”—ዴቪድ

9. “․․․․․ ከሆነ የምወደው ሰው የሚሠራቸው ስህተቶች ፈጽሞ አይታዩኝም።”—ቼልሲ

10. “․․․․․ ሲይዝህ ለምትወዳት ሴት ታማኝ መሆን እንዳለብህ ስለሚሰማህ እንደ ድሮህ ለሌላ ሴት የፍቅር ስሜት አያድርብህም።”—ዳንኤል

መልስ፦ የወረት ፍቅር፦ 1, 2, 4, 6, 8, 9 እውነተኛ ፍቅር፦ 3, 5, 7, 10

[በገጽ 206 እና 207 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የወረት ፍቅር የባሕር ዳርቻ ላይ በአሸዋ ቁልል እንደተሠራ ቤት ነው፤ ብዙም ሳይቆይ ውኃው አጥቦ ይወስደዋል