በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስብኝ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስብኝ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 32

ፆታዊ ጥቃት እንዳይደርስብኝ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?

በየዓመቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በፆታ ይነወራሉ ወይም ሌላ ዓይነት ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፤ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የዚህ ችግር ዋነኛ ሰለባዎች ወጣቶች ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፆታ ከተነወሩት ሰዎች መካከል ግማሽ የሚያህሉት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች እንደሆነ ይገመታል። ፆታዊ ጥቃት በጣም የተስፋፋ ከመሆኑ አንጻር ስለዚህ ጉዳይ ማወቅሽ አስፈላጊ ነው። *

“ሳላስበው አፈፍ አድርጎ ያዘኝና ወደ መሬት ወረወረኝ። ከእሱ ለማምለጥ ባለ በሌለ ኃይሌ ታገልኩ። የሚያቃጥል ነገር ከቦርሳዬ አውጥቼ ፊቱ ላይ ልነፋበት ስል ከእጄ ላይ አስጣለኝ። ለመጮኽ ብሞክርም ድምፄ አልወጣ አለኝ። በመገፍተር፣ በእጅና በእግሬ በመማታት እንዲሁም በመቧጨር ራሴን ለማስለቀቅ ሞከርኩ፤ ግን አልተሳካልኝም። በድንገት በስለት ሲወጋኝ ተሰማኝ። በዚህ ጊዜ መላ ሰውነቴ ዝልፍልፍ አለ።”—አኔት

ፆታዊ ጥቃት በዛሬው ጊዜ በጣም የተስፋፋ ሲሆን በአብዛኛው ዋነኞቹ ተጠቂዎች ወጣቶች ናቸው። ልክ እንደ አኔት አንዳንድ ወጣቶች ጥቃት የደረሰባቸው በማያውቁት ሰው ነው። ሌሎቹ ደግሞ በአቅራቢያቸው በሚኖር ሰው ጥቃት ደርሶባቸዋል። ናታሊ ገና የ10 ዓመት ልጅ እያለች እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል፤ ፆታዊ ጥቃት የፈጸመባት በአቅራቢያቸው የሚኖር አንድ ወጣት ነበር። “በጣም ፈርቼና አፍሬ ስለነበር ስለደረሰብኝ ነገር መጀመሪያ ላይ ለማንም አልተናገርኩም” ብላለች።

ብዙ ወጣቶች ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው የቤተሰባቸው አባል በሆነ ሰው ነው። ካርመን የተባለች ሴት እንዲህ ብላለች፦ “ከ5 ዓመቴ ጀምሮ 12 ዓመት እስኪሞላኝ ድረስ አባቴ ፆታዊ ጥቃት ይፈጽምብኝ ነበር። ሃያ ዓመት ሲሆነኝ ስለ ጉዳዩ አናገርኩት። አባቴ በድርጊቱ እንዳዘነ በመግለጽ ይቅርታ ጠየቀኝ፤ ከጥቂት ወራት በኋላ ግን ከቤት አባረረኝ።”

በጎረቤት፣ በጓደኛ አሊያም በቤተሰብ አባል የሚፈጸም ፆታዊ ጥቃት በዛሬው ጊዜ በጣም የተለመደ እየሆነ መጥቷል። * በእርግጥ በልጆች ላይ የሚፈጸም በደል እና ጥቃት በዚህ ዘመን የተጀመረ ነገር አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዘመንም እንደዚህ ዓይነቱ ዘግናኝ ድርጊት ይፈጸም ነበር። (ኢዩኤል 3:3፤ ማቴዎስ 2:16) የምንኖረው አስጨናቂ በሆነ ዘመን ነው። ብዙ ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር” ስለሌላቸው ልጆችን (ሴቶችንም ሆነ ወንዶችን) በፆታ ያስነውራሉ። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-3) እርግጥ ነው፣ ምንም ያህል ብትጠነቀቂ እንዲህ ያለ ጥቃት ፈጽሞ እንዳይደርስብሽ ማድረግ አትችዪ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ራስሽን ለመጠበቅ ማድረግ የምትችዪው ነገር አለ። ከዚህ ቀጥሎ ለቀረቡት ሐሳቦች ትኩረት ስጪያቸው፦

ንቁ ሁኚ። መንገድ ላይ ስትሆኚ በአካባቢሽ ያለውን ሁኔታ በሙሉ በንቃት ተከታተዪ። አንዳንድ አካባቢዎች በተለይ ምሽት ላይ አደገኛ ናቸው። ስለዚህ በተቻለሽ መጠን ወደ እነዚህ አካባቢዎች አትሂጂ፤ መሄድ ካለብሽ ደግሞ ብቻሽን አትሁኚ።—ምሳሌ 27:12

የተሳሳተ መልእክት ላለማስተላለፍ ተጠንቀቂ። ወንዶችን ከማሽኮርመም ተቆጠቢ፤ እንዲሁም ሰውነትን የሚያጋልጥ ነገር አትልበሺ። በእነዚህ ነገሮች ረገድ ጥንቃቄ ካላደረግሽ የሚያዩሽ ሰዎች የፆታ ግንኙነት ለመፈጸም እንደምትፈልጊ አሊያም ድርጊቱን እንደማትቃወሚ ሊያስቡ ይችላሉ።—1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10

ገደብ አስቀምጪ። የፍቅር ጓደኛ ካለሽ ተገቢ ስለሆኑና ስላልሆኑ የፍቅር መግለጫዎች ከግለሰቡ ጋር ተነጋገሩ። * ይህን ካደረጋችሁ በኋላ ለአደጋ ሊያጋልጡሽ በሚችሉ ሁኔታዎች ውስጥ ላለመግባት ተጠንቀቂ።—ምሳሌ 13:10 NW

አቋምሽን ከመግለጽ ወደኋላ አትበዪ። የወንድ ጓደኛሽን “እንዲህ አታድርግ” ወይም “እጅህን ሰብስብ” ብለሽ ለመናገር አትፍሪ። ‘የወንድ ጓደኛዬን ባጣውስ’ የሚል ስጋት አይግባሽ። በዚህ ጉዳይ የተነሳ እንድትለያዩ ከፈለገ እንዲህ ዓይነት ጓደኛ ቢቀርብሽም የሚያስቆጭ አይደለም! የወንድ ጓደኛሽ ሊሆን የሚገባው አንቺንም ሆነ የምትመሪባቸውን መሥፈርቶች የሚያከብር ብስለት ያለው ወንድ ነው።

ኢንተርኔት ስትጠቀሚ ጥንቃቄ አድርጊ። ያለሽበትን ቦታ ለማወቅ የሚያስችሉ የግል መረጃዎችን ወይም ፎቶግራፎችን ኢንተርኔት ላይ አታስቀምጪ። * ከፆታ ጋር የተያያዘ ሥነ ምግባር የጎደለው መልእክት ከደረሰሽ ብዙውን ጊዜ የተሻለው እርምጃ ምንም ምላሽ አለመስጠት ነው። በኢንተርኔት በሚያገኟቸው ሰዎች ላይ የፆታ ጥቃት የሚፈጽሙ ግለሰቦች ምላሽ ካጡ ምንም ማድረግ አይችሉም።

ከላይ ያሉትን ጥንቃቄዎች ማድረግሽ ጥቃት እንዳይደርስብሽ ለመከላከል በተወሰነ መጠን ሊረዳሽ ይችላል። (ምሳሌ 22:3) እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ያሉ ጥንቃቄዎችን ማድረግ የምትችዪው ሁልጊዜ አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አደገኛ ከሆኑ አካባቢዎች መራቅ ወይም አብሮሽ የሚጓዝ ሰው ማግኘት የማትችዪበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል። እንዲያውም የምትኖሪው አደገኛ በሆነ አካባቢ ይሆናል።

ከአደገኛ ሁኔታዎች ለመራቅ የተቻለሽን ሁሉ ብታደርጊም አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙ እንደሚችሉ በራስሽ ላይ ከደረሰው ሁኔታ ተገንዝበሽ ይሆናል። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰችው እንደ አኔት ሳታስቢው ጥቃት ሊሰነዘርብሽና ግለሰቡ ከአንቺ የበለጠ ኃይል ስላለው ሊያሸንፍሽ ይችላል። ወይም ደግሞ እንደ ካርመን በልጅነትሽ ጥቃት ተፈጽሞብሽ ይሆናል፤ በዚያ ወቅት እንዲህ ያለ ድርጊት እንዳይፈጸምብሽ ለመከላከል አቅም አልነበረሽም፤ አሊያም ምን እየተፈጸመ እንዳለ እንኳ አልገባሽ ይሆናል። ፆታዊ ጥቃት የተፈጸመባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃያሉ፤ አንቺስ ይህን ስሜት ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችያለሽ?

የጥፋተኝነት ስሜትን መቋቋም

አኔት እስካሁን ድረስ በጥፋተኝነት ስሜት ትሠቃያለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከሁሉ በላይ የሚከብደኝ ራሴን የምኮንን መሆኔ ነው። በዚያ ምሽት የተፈጸመውን ሁኔታ በአእምሮዬ እየመላለስኩ አውጠነጥናለሁ። ራሴን ለማስጣል ግለሰቡን ይበልጥ ልታገለው ይገባ እንደነበር ይሰማኛል። እርግጥ በስለት ከወጋኝ በኋላ በፍርሃት በድን ስለሆንኩ ምንም ማድረግ አልችልም ነበር። ሆኖም የሆነ ነገር ማድረግ እንደነበረብኝ አስባለሁ።”

ናታሊም ብትሆን የጥፋተኝነት ስሜት ያስቸግራታል። እንዲህ ብላለች፦ “በየዋህነት ሌሎችን ያን ያህል ማመን አልነበረብኝም። ወላጆቼ እኔና እህቴ ከቤት ውጭ ስንጫወት ሁልጊዜ አብረን እንድንሆን አዝዘውን ነበር፤ እኔ ግን የተባልኩትን አልሰማሁም። በመሆኑም ጎረቤታችን ጥቃቱን እንዲፈጽምብኝ አጋጣሚውን የፈጠርኩለት እኔው እንደሆንኩ ይሰማኛል። በተፈጠረው ነገር ቤተሰቤም በጣም ተጎድተዋል፤ ለዚህ ደግሞ ተጠያቂዋ እኔ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ይበልጥ የሚያሠቃየኝ ይህ ስሜት ነው።”

አንቺም እንደ አኔት ወይም ናታሊ የሚሰማሽ ከሆነ የጥፋተኝነት ስሜትን መቋቋም የምትችዪው እንዴት ነው? በፆታ ተነውረሽ ከሆነ ልታስታውሺው የሚገባው የመጀመሪያው ነገር ድርጊቱ የተፈጸመው በአንቺ ፈቃድ አለመሆኑን ነው። አንዳንዶች ጉዳዩን ለማቃለል ይሞክሩ ይሆናል፤ ለምሳሌ፣ “ያው ወንዶች ሲባሉ እንዲህ ናቸው” ብለው ይናገሩ ወይም ሴቶቹ እንዲህ ያለ ጥቃት የደረሰባቸው በራሳቸው ጥፋት እንደሆነ ይገልጹ ይሆናል። ይሁን እንጂ ተገድዶ መደፈር የትኛዋም ሴት ላይ ሊደርስ የሚገባ ነገር አይደለም። እንዲህ ያለ አስከፊ ድርጊት ተፈጽሞብሽ ከሆነ ጥፋተኛዋ በፍጹም አንቺ እንዳልሆንሽ አስታውሺ!

እርግጥ ነው፣ ጥፋተኛዋ አንቺ እንዳልሆንሽ ቢነገርሽም ይህን አምኖ መቀበል ቀላል ላይሆን ይችላል። አንዳንዶች የተፈጸመባቸውን በደል ለማንም ሳይናገሩ በውስጣቸው አምቀው በመያዝ በጥፋተኝነት ስሜትና በሌሎች አፍራሽ ስሜቶች ይሠቃያሉ። ይሁን እንጂ ዝም በማለትሽ የሚጠቀመው ማን ነው? አንቺ ወይስ ጥቃት የፈጸመብሽ ሰው? ጉዳዩን ደብቀሽ ከመያዝ ይልቅ የሚከተለውን እርምጃ ብትወስጂ ትጠቀሚያለሽ።

የደረሰብሽን በደል ተናገሪ

ጻድቁ ኢዮብ የደረሰበት መከራ በጣም ከብዶት በነበረበት ወቅት “ማጕረምረሜን ያለ ገደብ እለቃለሁ፤ በነፍሴም ምሬት እናገራለሁ” እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢዮብ 10:1) አንቺም እንዲህ ብታደርጊ ትጠቀሚያለሽ። ስለደረሰብሽ ነገር እምነት ለምትጥዪበት ሰው መናገርሽ እያደር ሁኔታውን መቀበልና መቋቋም እንድትችዪ እንዲሁም ጭንቀትሽን አውጥተሽ እፎይ እንድትዪ ይረዳሻል።

ክርስቲያን ከሆንሽ ደግሞ ስለ ሁኔታው ለጉባኤ ሽማግሌዎች መናገርሽ ጠቃሚ ነው። አፍቃሪ የሆኑት እነዚህ እረኞች የሚሰጡሽ ማጽናኛ ተገድደሽ በመደፈርሽ እንደረከስሽ ሊሰማሽ እንደማይገባና ኃጢአቱን የፈጸመው የደፈረሽ ግለሰብ እንደሆነ እንድትገነዘቢ ይረዱሻል። አኔት ሽማግሌዎችን ማናገር ያለውን ጥቅም ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ስለደረሰብኝ ነገር ለምቀርባት ጓደኛዬ ነገርኳት፤ እሷም በጉባኤ ያሉ ሽማግሌዎችን እንዳናግር አበረታታችኝ። ምክሯን ተግባራዊ በማድረጌ ደስተኛ ነኝ። ሽማግሌዎቹ በተደጋጋሚ ጊዜያት ያነጋገሩኝ ሲሆን ለተፈጠረው ነገር ተጠያቂ እንዳልሆንኩ በመግለጽ የሚያስፈልገኝን ማበረታቻ ሰጡኝ። በእርግጥም የደረሰብኝ ነገር በጭራሽ የእኔ ጥፋት አይደለም።”

ስለደረሰብሽ ነገር ለሌላ ሰው መናገርሽና ስሜትሽን አውጥተሽ መግለጽሽ በንዴትና በምሬት እንዳትዋጪ ይረዳሻል። (መዝሙር 37:8) ምናልባትም ለረጅም ጊዜ ሲያሠቃይሽ የቆየው ስሜት ቀለል እንዲልሽ ሊረዳሽ ይችላል። ናታሊ የደረሰባትን ጥቃት ለወላጆቿ ከተናገረች በኋላ ይህ እውነት መሆኑን ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ድጋፍ ሰጥተውኛል። ስለ ጉዳዩ እንዳወራ ያበረታቱኝ ሲሆን ይህም በውስጤ የታመቀው ሐዘንና ንዴት እንዲቀልልኝ ረድቶኛል።” ናታሊ ወደ አምላክ መጸለይዋም አጽናንቷታል። “በተለይ የሚሰማኝን ነገር ለሌሎች መናገር በሚከብደኝ ጊዜ ከአምላክ ጋር መነጋገሬ ረድቶኛል። ስጸልይ የልቤን አውጥቼ መናገር እችላለሁ። ጸሎት ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖረኝ ይረዳኛል” ብላለች። *

“ለመፈወስም ጊዜ አለው” የሚለውን ጥቅስ እውነተኝነት አንቺም በሕይወትሽ ልትመለከቺ ትችያለሽ። (መክብብ 3:3 የ1954 ትርጉም) ወዳጆችሽ የሚሰጡሽን እርዳታ ተቀበዪ፤ እነዚህ ሰዎች “ከነፋስ መከለያ፣ ከወጀብም መጠጊያ” እንደሆኑ ተደርገው እንደተጠቀሱት ሽማግሌዎች ሊረዱሽ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2) ጤንነትሽን ተንከባከቢ፤ እንዲሁም የደረሰብሽ ነገር ስሜትሽን እንዲደቁሰው አትፍቀጂ። በቂ እረፍት አድርጊ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የመጽናናት ሁሉ አምላክ የሆነውን የይሖዋን ድጋፍ ለማግኘት ሞክሪ፤ ይሖዋ በቅርቡ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ስለሚኖረው ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ሲናገር “ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ” ይላል።—መዝሙር 37:9

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ነጥቦች ለወንዶችም ይሠራሉ።

^ አን.7 አንዳንድ ሴቶችን አስገድዶ ወይም ዕፅ በመስጠት አደንዝዞ በፆታ የሚያስነውራቸው የወንድ ጓደኛቸው ሊሆን ይችላል።

^ አን.10 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 4 ተመልከቺ።

^ አን.12 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 11 ተመልከቺ።

^ አን.23 የፆታ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች አንዳንድ ጊዜ በከፍተኛ የመንፈስ ጭንቀት ይዋጣሉ። በዚህ ወቅት የሕክምና ባለሙያ ማማከራቸው ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የጭንቀት ስሜትን መቋቋም ስለሚቻልበት መንገድ ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 13 እና 14⁠ን ተመልከቺ።

ቁልፍ ጥቅስ

“በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ ይህን እወቅ። ምክንያቱም ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ፣ . . . ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ . . . ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ [ይሆናሉ]።”—2 ጢሞቴዎስ 3:1-3

ጠቃሚ ምክር

የፆታ ጥቃት ተፈጽሞብሽ ከሆነ ሊያጽናኑሽ የሚችሉ ጥቅሶችን ጽፈሽ አስቀምጪ። ለምሳሌ ያህል፣ እንደ መዝሙር 37:28፤ 46:1፤ 118:5-9፤ ምሳሌ 17:17 እና ፊልጵስዩስ 4:6, 7 ያሉት ጥቅሶች ሊያጽናኑሽ ይችላሉ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በዩናይትድ ስቴትስ ፆታዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ወጣቶች መካከል ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጥቃቱ የተፈጸመባቸው በሚያውቁት ሰው ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

በደረሰብኝ ጥቃት የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ሲያስቸግረኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● አንድ ሰው ስለተፈጸመበት የፆታ ጥቃት በግልጽ መናገሩ ምን ጥቅሞች አሉት?

● ጥቃት የደረሰበት ሰው ስለ ሁኔታው አለመናገሩ በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል?

[በገጽ 232 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ስለደረሰባችሁ ጥቃት መናገር በጣም ከባድ ነው፤ ይሁንና እንዲህ ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነው። ስለ ሁኔታው መናገራችሁ ሐዘናችሁና ንዴታችሁ ቀለል እንዲል እንዲሁም ኃይላችሁ እንዲታደስ ይረዳችኋል።”—ናታሊ

[በገጽ 230 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“ብትወጂኝ ኖሮ . . .”

የፆታ ጥቃት የሚፈጽሙ አንዳንድ ሰዎች በኃይል ከመጠቀም ይልቅ ሴቶችን በዘዴ ሊያታልሏቸው ይሞክራሉ። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? “የፆታ ግንኙነት የማይፈጽም የለም” ወይም “ማንም አያውቅብንም” ይሉ ይሆናል፤ አሊያም ደግሞ በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 24 ላይ እንደተገለጸው “ብትወጂኝ ኖሮ እሺ ትዪኝ ነበር” እንደሚለው ያሉ ማባበያዎችን ይጠቀማሉ። አንድ ወንድ፣ ፍቅር የሚገለጸው የፆታ ግንኙነት በመፈጸም እንደሆነ ሊያሳምንሽ ቢሞክር አትቀበዪው። እንደ እውነቱ ከሆነ እንዲህ የሚል ማንኛውም ወንድ የሚያስበው ስለ ራሱ ስሜት ብቻ ነው። ስለ አንቺ ስሜትም ሆነ ስለ ደኅንነትሽ ምንም ግድ የለውም። ከዚህ በተቃራኒ ብስለት ያለው ወንድ ከራሱ ይልቅ የአንቺን ፍላጎት የሚያስቀድም ከመሆኑም ሌላ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ለማክበር የሚያስችል ጥንካሬ አለው። (1 ቆሮንቶስ 10:24) እንዲህ ያለው ወንድ፣ ሴቶች የተፈጠሩት የወንዶችን የፆታ ስሜት ለማርካት እንደሆነ አያስብም። ከዚህ ይልቅ ‘ወጣት ሴቶችን እንደ እህቶቹ አድርጎ በፍጹም ንጽሕና ይይዛቸዋል።’—1 ጢሞቴዎስ 5:1, 2

[በገጽ 233 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የደረሰብሽ ጥቃት ያስከተለውን የስሜት ሥቃይ ብቻሽን መሸከም በጣም ከባድ ሊሆንብሽ ይችላል። ታዲያ ስለ ጉዳዩ በመናገር እርዳታ ለማግኘት ለምን አትሞክሪም?