በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ስለ ሲጋራ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ስለ ሲጋራ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ምዕራፍ 33

ስለ ሲጋራ ምን ማወቅ ይኖርብኛል?

ከእነዚህ ነጥቦች መካከል የአንተን ስሜት በሚገልጸው ላይ ✔ አድርግ።

□ የማወቅ ጉጉት አለኝ

□ ውጥረት በዝቶብኛል

□ ተቀባይነት ማግኘት እፈልጋለሁ

□ ክብደት መቀነስ እፈልጋለሁ

በገጽ 237 ላይ ከተዘረዘሩት ነጥቦች ቢያንስ በአንዱ ላይ ምልክት አድርገሃል? ከሆነ ሲጋራ የሚያጨሱ ወይም ለማጨስ የሚያስቡ እኩዮችህም እንደ አንተ ይሰማቸዋል። * እነዚህ ወጣቶች ከተናገሩት ሐሳብ አንዳንዶቹን እንደ ምሳሌ እንመልከት፦

የማወቅ ጉጉት። “ማጨስ ምን ስሜት እንደሚፈጥር ማወቅ ስለፈለግሁ በትምህርት ቤት ከአንዲት ልጅ ሲጋራ ተቀብዬ በድብቅ አጨስኩ።”—ትሬሲ

ውጥረትን መቋቋምና ተቀባይነት ማግኘት። “በትምህርት ቤት ያሉ ልጆች ውጥረት ሲበዛባቸው ‘ሲጋራ ባገኘሁ’ ይላሉ፤ ከዚያም ካጨሱ በኋላ ‘አሁን ቀለል አለኝ!’ በማለት ይናገራሉ። እኔም ውጥረት ሲያጋጥመኝ እንዲህ ማድረግ ያምረኛል።”—ኒኪ

ክብደት መቀነስ። “አንዳንድ ሴቶች የሚያጨሱት ላለመወፈር ስለሚፈልጉ ነው፤ ይህ ዘዴ ምግብ ለመቀነስ ከመሞከር ይበልጥ ቀላል ነው!”—ሳማንታ

አንተም ማጨስ ለመጀመር እያሰብህ ይሆናል፤ አሊያም ስታጨስ ቆይተህ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆነ ይህ ሲጋራ ከመለኮስህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። መንጠቆ ላይ የተንጠለጠለን ምግብ ለመብላት እንደሚቸኩል ዓሣ አትሁን። ዓሣው ምግቡን መቅመስ ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ሕይወቱን ስለሚያጣ አተርፍ ባይ አጉዳይ መሆኑ አይቀርም! ከዚህ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በመከተል ‘በትክክል ማሰብህ’ የተሻለ ነው። (2 ጴጥሮስ 3:1) እስቲ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች መልስ ስጥ።

ስለ ሲጋራ ምን ያህል ታውቃለህ?

እውነት ወይም ሐሰት በል።

ሀ. ማጨስ ውጥረትን ይቀንሳል።

□ እውነት □ ሐሰት

ለ. የሲጋራውን ጭስ እንዳለ አወጣዋለሁ።

□ እውነት □ ሐሰት

ሐ. ወጣት ስለሆንኩ ማጨስ ጤንነቴን አይጎዳውም።

□ እውነት □ ሐሰት

መ. ባጨስ ተቃራኒ ፆታን መማረክ እችላለሁ።

□ እውነት □ ሐሰት

ሠ. ባጨስ የምጎዳው ራሴን ብቻ ነው።

□ እውነት □ ሐሰት

ረ. የእኔ ማጨስ አለማጨስ አምላክን ያን ያህል አያሳስበውም።

□ እውነት □ ሐሰት

መልስ

ሀ. ሐሰት። ማጨስ የውጥረት ስሜትን በተወሰነ መጠን ቢቀንስም በሲጋራ ውስጥ ያለው ኒኮቲን በውጥረት ጊዜ ሰውነታችን የሚያመነጫቸውን ሆርሞኖች መጠን ከፍ እንደሚያደርገው የሳይንስ ሊቃውንት ደርሰውበታል።

ለ. ሐሰት። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ወደ ውስጥ በምትስበው የሲጋራ ጭስ ውስጥ ከሚገኙት ንጥረ ነገሮች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት በሰውነትህ ውስጥ ይቀራሉ።

ሐ. ሐሰት። ማጨስ በጤንነትህ ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ብዙ ባጨስክ መጠን እየጨመረ የሚሄድ ቢሆንም አንዳንዶቹ ጉዳቶች ማጨስ ከጀመርክ ብዙም ሳይቆይ መታየት ሊጀምሩ ይችላሉ። አንዳንድ ሰዎች ሱስ የሚይዛቸው የመጀመሪያውን ሲጋራ እንዳጨሱ ነው። ሳንባህ አየር የመያዝ አቅሙ የሚቀንስ ሲሆን የማይለቅ ሳል ሊያስቸግርህ ይችላል። እንዲሁም ያለ ዕድሜህ ቆዳህ ይሸበሸባል። በተጨማሪም ማጨስ ለስንፈተ ወሲብ ሊያጋልጥህ እንዲሁም ድንገተኛ የሆነ የመሸበር ስሜትና የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትልብህ ይችላል።

መ. ሐሰት። ሎይድ ጆንስተን የተባሉ ተመራማሪ እንደገለጹት አብዛኞቹ ወጣቶች፣ ሲጋራ የሚያጨሱ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ተቃራኒ ፆታ ያላቸው ልጆች “ያን ያህል አይማርኳቸውም።”

ሠ. ሐሰት። በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ የማያጨሱ ሰዎች ለሲጋራ ጭስ በመጋለጣቸው ብቻ ለሞት ይዳረጋሉ፤ የአንተ ማጨስ ቤተሰቦችህን፣ ጓደኞችህን አልፎ ተርፎም የቤት እንስሳትህን ይጎዳል።

ረ. ሐሰት። አምላክን ማስደሰት የሚፈልጉ ሰዎች “ሥጋን . . . ከሚያረክስ ነገር ሁሉ” ራሳቸውን ማንጻት አለባቸው። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ማጨስ ሰውነትን እንደሚያረክስ ምንም ጥርጥር የለውም። ሲጋራ በማጨስ ሰውነትህን የምታረክስ እንዲሁም የራስህንም ሆነ የሌሎችን ጤንነት የምትጎዳ ከሆነ የአምላክ ወዳጅ መሆን አትችልም።—ማቴዎስ 22:39፤ ገላትያ 5:19-21

ተጽዕኖውን መቋቋም

ታዲያ አንድ ልጅ እንድታጨስ ቢጋብዝህ ምን ታደርጋለህ? ብዙውን ጊዜ “ይቅርብኝ፣ አላጨስም” የሚል አጭር ሆኖም ቁርጥ ያለ መልስ መስጠት ይበቃል። ልጁ መጎትጎቱን ቢቀጥል አልፎ ተርፎም ቢያሾፍብህ እንኳ ላለማጨስ የመምረጥ መብት እንዳለህ አስታውስ። እንዲህ ልትለው ትችላለህ፦

● “ሲጋራ ምን ያህል ጎጂ እንደሆነ ስለማውቅ ላለማጨስ ወስኛለሁ።”

● “ወደፊት ልደርስባቸው ያሰብኳቸው ግቦች ስላሉኝ ሳንባዬን እፈልገዋለሁ።”

● “የራሴን ምርጫ የማድረግ መብት የለኝም?”

ይሁንና በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ሁሉ አንተም ከሁሉ በላይ የሚከብድህ የራስህን ምኞት ማሸነፍ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ከታች በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ ይህን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳሃል፦

● ማጨሴ የሚያስገኝልኝ ጥቅም አለ? ለምሳሌ ያህል፣ በእኩዮቼ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ስል ማጨስ ብጀምር ሌላ የሚያመሳስለን ነገር እስከሌለ ድረስ ስላጨስኩ ብቻ ጓደኛቸው ያደርጉኛል? ደግሞስ ጤንነቴ ቢጎዳ ደንታ የማይሰጣቸው ልጆች ጓደኝነት ምን ይጠቅመኛል?

● ማጨስ ምን ያህል ወጪ ያስወጣኛል? ጤንነቴንና ሌሎች ለእኔ ያላቸውን ግምትስ የሚነካው እንዴት ነው?

● ለሲጋራ ብዬ ከአምላክ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ማበላሸት ያዋጣኛል?

ይሁንና በሲጋራ ሱስ ተጠምደህ ከሆነስ? ከሱስህ ለመላቀቅ ምን ማድረግ ትችላለህ?

ማቆም የሚቻልበት መንገድ

1. ራስህን አሳምን። ለማቆም ያነሳሱህን ምክንያቶች ጻፍ፤ ከዚያም እነዚህን ምክንያቶች በየጊዜው መለስ እያልክ ተመልከታቸው። በአምላክ ፊት ንጹሕ ሆነህ ለመገኘት ያለህ ፍላጎት ሱሱን ለማሸነፍ የሚያስችል ኃይል ይሰጥሃል።—ሮም 12:1፤ ኤፌሶን 4:17-19

2. እርዳታ ለማግኘት ሞክር። በድብቅ ታጨስ ከነበረ ሁኔታውን ለሌሎች ተናግረህ እንዲረዱህ ጠይቅ። ማጨስህን ደብቀሃቸው ለነበሩት ሰዎች አሁን ለማቆም እንዳሰብክና የእነሱን ድጋፍ እንደምትፈልግ ንገራቸው። አምላክን ለማገልገል የምትፈልግ ከሆነ እሱ እንዲረዳህ ጸልይ።—1 ዮሐንስ 5:14

3. የምታቆምበትን ቀን ወስን። ለዝግጅት የሚሆን ሁለት ሳምንት ወይም ከዚያ ያነሰ ጊዜ መድብና ለማቆም የወሰንክበትን ዕለት በቀን መቁጠሪያህ ላይ ምልክት አድርግበት። በዚያ ቀን እንደምታቆም ለቤተሰቦችህና ለጓደኞችህ ንገራቸው።

4. በደንብ ፈትሽ፤ ምንም ሳታስቀር አስወግድ። ለማቆም የወሰንክበት ቀን ከመድረሱ በፊት ክፍልህን፣ መኪናህንና ልብስህን በደንብ ፈትሽ። ሲጋራ ካገኘህ ጣለው። ላይተሮችን፣ ክብሪቶችንና መኮስተሪያዎችን አስወግድ።

5. ማጨስ በማቆምህ የሚኖርህን የሕመም ወይም ሌላ ዓይነት ስሜት ለመቋቋም የሚረዱህ መንገዶች ፈልግ። የፍራፍሬ ጭማቂ ወይም ውኃ በብዛት ጠጣ፤ እንዲሁም ለእንቅልፍ ተጨማሪ ጊዜ መድብ። በማቆምህ ምክንያት የሚፈጠርብህ መጥፎ ስሜት ጊዜያዊ መሆኑን፣ የምታገኛቸው ጥቅሞች ግን ዘላቂ መሆናቸውን አስታውስ!

6. እንዲያገረሽብህ ከሚያደርጉ ነገሮች ራቅ። አጭስ አጭስ የሚል ስሜት ከሚፈጥሩብህ ቦታዎችና ሁኔታዎች ራቅ። በተጨማሪም ከሚያጨሱ ሰዎች ጋር ያለህን ግንኙነት ማቋረጥ ሊያስፈልግህ ይችላል።—ምሳሌ 13:20

አትታለል

የትንባሆ ኩባንያዎች ለማስታወቂያ በየዓመቱ በብዙ ቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ያወጣሉ። እነዚህ ማስታወቂያዎች ይበልጥ የሚያነጣጥሩት በማን ላይ ነው? አንድ የትንባሆ ፋብሪካ የውስጥ ሰነድ “የዛሬዎቹ ወጣቶች የነገ ቋሚ ደንበኞቻችን ናቸው” ይላል።

የትንባሆ ኩባንያዎች ኪስህን እንዲያራቁቱት አትፍቀድ። በማባበያቸው ተማርከህ በወጥመዳቸው እንዳትያዝ ተጠንቀቅ። እነሱም ሆኑ የሚያጨሱ እኩዮችህ እንድታጨስ የሚገፋፉህ ለአንተ አስበው አይደለም። እነሱን ከመስማት ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በማዳመጥ ለአንተ “የሚበጅህ” ምን እንደሆነ እወቅ።—ኢሳይያስ 48:17

በሚቀጥለው ምዕራፍ

ጓደኞችህ እንድትጠጣ ይገፋፉሃል? በዚህ ረገድ ከልክ ማለፍ የሌለብህ ለምን እንደሆነ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.8 ይህ ምዕራፍ በዋነኝነት የሚያወሳው ሲጋራ ስለ ማጨስ ቢሆንም ትንባሆ የሚያኝኩ ሰዎችም በምዕራፉ ውስጥ የተብራሩት ችግሮችና አደጋዎች ያጋጥሟቸዋል።

ቁልፍ ጥቅስ

“ሥጋን . . . ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።”—2 ቆሮንቶስ 7:1

ጠቃሚ ምክር

‘አንዴ ብቻ ነው ሳብ የማደርገው’ እንደሚለው ያሉ ሰበቦችን በመፍጠር ራስህን አታታልል። ይህ ሱሱ እንደገና እንዲያገረሽብህ ሊያደርግ ይችላል።—ኤርምያስ 17:9

ይህን ታውቅ ነበር?

ሲጋራ ባያጨሱም ትንባሆን በሌላ መንገድ የሚወስዱ ለምሳሌ የሚያኝኩ ሰዎች ሲጋራ ከሚያጨሱ ሰዎች የበለጠ ኒኮቲን ወደ ሰውነታቸው ያስገባሉ፤ በዚህ መንገድ የሚወሰድ ትንባሆ ለጉሮሮና ለአፍ ካንሰር ይበልጥ የሚያጋልጡ ከ25 በላይ ንጥረ ነገሮችን የያዘ ነው።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

አብሮኝ የሚማር ልጅ እንዳጨስ ቢወተውተኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ሲጋራ አደገኛ እንደሆነ እያወቅህም ለማጨስ የምትፈተነው ለምን ሊሆን ይችላል?

● ማጨስ ጎጂ ነው የምትለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 240 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“እንዳጨስ ግብዣ ሲቀርብልኝ ሳቅ እልና ‘ይቅርብኝ፤ ካንሰር እንዲይዘኝ አልፈልግም’ ብዬ እመልሳለሁ።”—አላና

[በገጽ 241 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ማሪዋና ያን ያህል ጎጂ ነው?

በአየርላንድ የምትኖረው ኢሌን “አንዳንዶች ማሪዋና የሚወስዱት ችግራቸውን ለመርሳት እንደሆነና ይህን ማድረግ ምንም ጉዳት እንደሌለው ይናገራሉ” ብላለች። * አንተስ እንዲህ ዓይነት አባባሎችን ሰምተህ ታውቃለህ? ከማሪዋና ጋር በተያያዘ ብዙዎች ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ከእውነታው ጋር እንድታነጻጽር እንጋብዝሃለን።

የተሳሳተ አመለካከት። ማሪዋና አይጎዳም።

እውነታው። ማሪዋና ዘላቂ ጉዳቶች እንዳሉት ይታወቃል፤ በደንብ ከተረጋገጡት ወይም የማሪዋና ውጤት እንደሆኑ ከሚጠረጠሩት ጉዳቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦ የማስታወስና ትምህርት የመቀበል ችሎታን ይቀንሳል፤ በሽታ የመከላከል አቅምን ያዳክማል፤ እንዲሁም በወንዶችም ሆነ በሴቶች ላይ ስንፈተ ወሲብ ያስከትላል። ድንገተኛ ለሆነ የመሸበር ስሜትና ለአእምሮ ሕመም መንስኤ ሊሆን ይችላል። ማሪዋና የሚያጨሱ ሴቶች የሚወልዷቸው ልጆች ብዙውን ጊዜ የባሕርይ ችግር የሚታይባቸው ሲሆን ትኩረታቸውን መሰብሰብና ውሳኔ ማድረግ ይቸግራቸዋል።

የተሳሳተ አመለካከት። ማሪዋና ማጨስ የሲጋራን ያህል አይጎዳም።

እውነታው። ትንባሆ ከሚያጨስ ሰው ይልቅ ማሪዋና በሚያጨስ ሰው የአየር መተላለፊያ ቱቦዎች ላይ አራት እጥፍ የሚሆን ጥላሸት የሚከማች ሲሆን በደሙ ውስጥም መርዛማ የሆነው የካርቦን ሞኖክሳይድ ጋዝ አምስት እጥፍ ያህል ይኖራል። አምስት ጥቅልል ማሪዋና ያጨሰ ሰው አንድ ሙሉ ፓኬት ሲጋራ ካጨሰ ሰው እኩል ለካንሰር የሚያጋልጡ መርዛማ ነገሮችን ወደ ሰውነቱ ያስገባል።

የተሳሳተ አመለካከት። ማሪዋና ሱስ አያስይዝም።

እውነታው። ከአእምሮና ከስሜት ጋር የተያያዙ ችግሮች ያሉባቸው ወጣቶች በቀላሉ የማሪዋና ሱስ ሊይዛቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ ለረጅም ጊዜ ማጨሳቸው ለሱስ ሊያጋልጣቸው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ማሪዋና የሚያጨሱ ወጣቶች እንደ ኮኬይን ያሉ ሱስ የሚያስይዙ ሌሎች ዕፆችን የመውሰድ አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።

[በገጽ 244 እና 245 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

ትንባሆ በአካልህ ላይ የሚያመጣው ጉዳት

በሲጋራ ማስታወቂያዎች ላይ የሚታዩት ሰዎች ጤነኛ ይመስሉ ይሆናል፤ ይሁንና ማጨስ በሰውነትህ ላይ ጉዳት ያስከትላል። እስቲ የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በል፦

አፍ እና ጉሮሮ፦ ካንሰር ሊያስከትል ይችላል

[ሥዕል]

በካንሰር የተጠቃ ምላስ

ልብ፦ የደም ቅዳ ቧንቧዎች እንዲደድሩና እንዲጠብቡ እንዲሁም ልብ በቂ ኦክስጅን እንዳያገኝ ያደርጋል፤ በልብ በሽታ የመያዝ አጋጣሚ በአራት እጥፍ ከፍ እንዲል ያደርጋል

[ሥዕል]

የጠበበ የደም ቅዳ ቧንቧ

ሳንባ፦ የአየር ከረጢቶችን ይጎዳል፤ የአየር መተላለፊያ ቧንቧዎች እንዲቆጡ ያደርጋል፤ እንዲሁም በሳንባ ካንሰር የመጠቃት አጋጣሚ በ23 እጥፍ እንዲጨምር ያደርጋል

[ሥዕል]

የሚያጨስ ሰው ሳንባ

አንጎል፦ አንጎል ውስጥ ደም የመፍሰሱ አጋጣሚ በአራት እጥፍ ከፍ እንዲል ያደርጋል

ቆዳ፦ ያለ ዕድሜ እንዲሸበሸብ ያደርጋል

ጥርስ፦ ያበልዛል

ጨጓራ፦ ካንሰር ያስከትላል

ጣፊያ፦ ካንሰር ያስከትላል

ፊኛ፦ ካንሰር ያስከትላል

ኩላሊት፦ ካንሰር ያስከትላል

[በገጽ 239 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መንጠቆ ላይ የተንጠለጠለን ምግብ ለመብላት እንደሚቸኩል ዓሣ ሁሉ የሚያጨስ ሰውም ጊዜያዊ ጥቅም ቢያገኝም አተርፍ ባይ አጉዳይ መሆኑ አይቀርም!

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.73 ማሪዋና እና ሀሺሽ፣ ዕፀ ፋሪስ (ካናቢስ) ከተባለው ተክል የሚገኙ አደገኛ ዕፆች ናቸው።