በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ችግር አለው?

ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ችግር አለው?

ምዕራፍ 34

ከመጠን በላይ መጠጣት ምን ችግር አለው?

ከታች ላሉት ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ? መልስህ ላይ ✔ አድርግ።

ከእኩዮችህ መካከል ዕድሜያቸው ሳይደርስ የሚጠጡ ወይም ከመጠን በላይ የሚጠጡ አሉ?

□ አዎ □ አይ

እኩዮችህ እንድትጠጣ ገፋፍተውህ ያውቃሉ?

□ አዎ □ አይ

አንተስ ከመጠን በላይ ጠጥተህ ታውቃለህ?

□ አዎ □ አይ

አንዳንዶች ከመጠን በላይ መጠጣት የሚባለው እስኪሰክሩ መጠጣት እንደሆነ ይናገራሉ። በዩናይትድ ስቴትስ አልኮልን አላግባብ ስለ መጠቀምና ስለ አልኮል ሱሰኝነት ጥናት የሚያደርገው ብሔራዊ የምርምር ተቋም ከመጠን በላይ መጠጣት የሚለውን አገላለጽ ሲፈታው እንዲህ ብሏል፦ “ለወንዶች አምስት ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ ለሴቶች ደግሞ አራት ብርጭቆ ወይም ከዚያ በላይ አከታትሎ መጠጣትን ያመለክታል።” *

ከመጠን በላይ ለመጠጣት ተፈትነህ ታውቃለህ? አሊያም ደግሞ ዕድሜህ ባይደርስም እንኳ መጠጣት አምሮህ ያውቃል? ከሆነ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ብዙ ወጣቶች ዕድሜያቸው ሳይደርስ መጠጣት ይጀምራሉ ወይም ከልክ በላይ ይጠጣሉ። * ይሁን እንጂ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘መጠጣት የምፈልገው ለምንድን ነው? አልኮል ስለሚያስከትለው ጉዳት ምን ያህል አውቃለሁ?’ ለምሳሌ ያህል ከታች ለቀረቡ ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ? መልስህ ላይ ✔ አድርግ፤ ከዚያም ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ልብ በል።

ሀ. በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች የሚጠጡት የመጠጡን ጣዕም ስለሚወዱት ብቻ ነው።

□ እውነት □ ሐሰት

ለ. በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች ገና ወጣትና ጤናማ ስለሆኑ አልኮል በብዛት ቢጠጡም የአዋቂዎችን ያህል አይጎዱም።

□ እውነት □ ሐሰት

ሐ. ከመጠን በላይ ስለጠጣህ አትሞትም።

□ እውነት □ ሐሰት

መ. መጽሐፍ ቅዱስ አልኮል መጠጣትን ይከለክላል።

□ እውነት □ ሐሰት

ሠ. ከመጠን በላይ መጠጣት ጉዳት የሚያስከትለው በጤንነት ላይ ብቻ ነው።

□ እውነት □ ሐሰት

ሀ. በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች የሚጠጡት የመጠጡን ጣዕም ስለሚወዱት ብቻ ነው። መልስ—ሐሰት። በአውስትራሊያ የአልኮል መጠጥን አስመልክቶ በተካሄደ ጥናት ላይ ጥያቄ ከቀረበላቸው ወጣቶች መካከል 36 በመቶ የሚሆኑት የሚጠጡበት ዋነኛ ምክንያት በግብዣዎች ላይ ከጓደኞቻቸው የተለዩ ሆነው መታየት ስለማይፈልጉ እንደሆነ ገልጸዋል። በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ጥናት ደግሞ 66 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች የሚጠጡት እኩዮቻቸው ስለገፋፏቸው እንደሆነ ተናግረዋል። በጥናቱ ከተካፈሉት ውስጥ ከግማሽ የሚበልጡት የሚጠጡት ችግሮቻቸውን ለመርሳት ሲሉም ነው።

ለ. በአሥራዎቹ ዕድሜ ያሉ ልጆች ገና ወጣትና ጤናማ ስለሆኑ አልኮል በብዛት ቢጠጡም የአዋቂዎችን ያህል አይጎዱም። መልስ—ሐሰት። ዲስከቨር በተሰኘ መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንደገለጸው “ወጣቶች ከመጠን በላይ ሲጠጡ ራሳቸውን ለአደጋ እንደሚያጋልጡ አዳዲስ ጥናቶች ያሳያሉ።” እንዴት? “በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች በሃያዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሲሆኑም አንጎላቸው ማደጉን ስለማያቆም ከመጠን በላይ የሚጠጡ ከሆነ የማሰብ ችሎታቸው በከፍተኛ መጠን ሊጎዳ ይችላል።”

ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ከሚያስከትላቸው ጉዳቶች መካከል የብጉር መብዛት፣ ያለ ዕድሜ የሚመጣ የቆዳ መሸብሸብ፣ የክብደት መጨመር፣ መጠጥ ሳይቀምሱ ሥራን ለማከናወን መቸገር እንዲሁም የዕፅ ሱሰኛ መሆን ይገኙበታል። ከዚህም በተጨማሪ የነርቭ ሥርዓትን ያቃውሳል እንዲሁም በጉበትና በልብ ላይ ከባድ ጉዳት ያደርሳል።

ሐ. ከመጠን በላይ ስለጠጣህ አትሞትም። መልስ—ሐሰት። አልኮል ከመጠን በላይ መውሰድ አንጎል ኦክስጅን እንዲያጣ ስለሚያደርግ ወሳኝ የሆኑት የሰውነታችን ክፍሎችና ዑደቶች በደንብ መሥራት ሊያቅታቸው ወይም ከነጭራሹ መሥራት ሊያቆሙ ይችላሉ። ይህን ከሚጠቁሙ ምልክቶች መካከል ማስመለስ፣ ራስን መሳትና በጣም ዝግ ያለ ወይም ያልተስተካከለ አተነፋፈስ ይገኙበታል። ከመጠን በላይ መጠጣት አንዳንድ ጊዜም ሞት ሊያስከትል ይችላል።

መ. መጽሐፍ ቅዱስ አልኮል መጠጣትን ይከለክላል። መልስ—ሐሰት። መጽሐፍ ቅዱስ አልኮል መጠጣትን አይከለክልም፤ ወጣቶች ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸውንም አያወግዝም። (መዝሙር 104:15፤ መክብብ 10:19) እርግጥ ነው፣ መጠጥ ለመጀመር የሚፈቀድልህ ዕድሜ ላይ ሳትደርስ መጠጣት አይኖርብህም።—ሮም 13:1

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ መጠጣትን ያወግዛል። ምሳሌ 20:1 “የወይን ጠጅ ፌዘኛ፣ ብርቱ መጠጥም ጠበኛ ያደርጋል፤ በእነዚህ የሳተ ሁሉ ጠቢብ አይደለም” ይላል። የአልኮል መጠጥ ፌዘኛ እንድትሆን ወይም የሞኝነት ድርጊት እንድትፈጽም ሊያደርግህ ይችላል። መጠጥ ጊዜያዊ ደስታ እንደሚያስገኝ ባይካድም ከመጠን በላይ የምትጠጣ ከሆነ ‘እንደ እባብ ይነድፍሃል’፤ በሌላ አባባል ለብዙ ችግሮች ይዳርግሃል።—ምሳሌ 23:32

ሠ. ከመጠን በላይ መጠጣት ጉዳት የሚያስከትለው በጤንነት ላይ ብቻ ነው። መልስ—ሐሰት። የሰከረ ሰው ለተለያዩ ጥቃቶች ሊጋለጥ አልፎ ተርፎም ተገድዶ ሊደፈር ይችላል። ከዚህም ሌላ ባይጠጣ ኖሮ ፈጽሞ የማያስበውን ነገር ሊያደርግና በሌሎች ላይ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ ከጠጣህ “በትክክል ማሰብም ሆነ መናገር አትችልም” በማለት ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 23:33 የ1980 ትርጉም) በአጭሩ ራስህን ታቃልላለህ! ከልክ በላይ መጠጣት ሌሎች መዘዞችም አሉት፤ ለምሳሌ ጓደኞችህን እንድታጣ፣ በትምህርት ቤት ወይም በሥራ ቦታ ጥራት ያለው ሥራ ማከናወን እንዲያቅትህ፣ ወንጀል እንድትፈጽምና ለድህነት እንድትጋለጥ ሊያደርግህ ይችላል።—ምሳሌ 23:21

ከሁሉ በላይ ደግሞ ከአምላክ ጋር ባለህ ግንኙነት ረገድ የሚያስከትለውን ጉዳትም ልታስብበት ይገባል። ይሖዋ አምላክ በመጠጥ በደነዘዘ አእምሮ ሳይሆን “በሙሉ አእምሮህ” እንድታገለግለው ይፈልጋል። (ማቴዎስ 22:37) የአምላክ ቃል ‘ከልክ በላይ መጠጣትን’ ብቻ ሳይሆን ‘በፉክክር ብዙ መጠጣትንም’ ያወግዛል። (1 ጴጥሮስ 4:3) በመሆኑም ከመጠን በላይ መጠጣት አምላክን የሚያሳዝን ከመሆኑም ሌላ ከእሱ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዳትመሠርት እንቅፋት ይሆንብሃል።

ውሳኔህ ምንድን ነው?

እኩዮችህ ከመጠን በላይ ስለሚጠጡ ብቻ አንተም እነሱን ትከተላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “ለማንም ቢሆን እንደ ባሪያዎች ሆናችሁ ለመታዘዝ ራሳችሁን ካቀረባችሁ ለእሱ ስለምትታዘዙ የእሱ ባሪያዎች እንደሆናችሁ አታውቁም?” በማለት ይናገራል። (ሮም 6:16) ታዲያ የእኩዮችህ ወይም የመጠጥ ባሪያ መሆን ትፈልጋለህ?

ይሁንና ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ካለህ ምን ማድረግ ትችላለህ? ዛሬ ነገ ሳትል ለወላጆችህ ወይም ብስለት ላላቸው ጓደኞችህ ጉዳዩን በመናገር እርዳታ ለማግኘት ሞክር። ወደ ይሖዋ አምላክ በመጸለይ እንዲረዳህ ለምነው። ደግሞም አምላክ “በሚደርስብን መከራ ሁሉ የቅርብ ረዳታችን ነው።” (መዝሙር 46:1) አብዛኛውን ጊዜ ወጣቶች ከመጠን በላይ እንዲጠጡና ያለ ዕድሜያቸው መጠጥ እንዲጀምሩ ግፊት የሚያደርጉባቸው እኩዮቻቸው ስለሆኑ በጓደኛ ምርጫህ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ያስፈልግህ ይሆናል። * እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ ቀላል ባይሆንም በይሖዋ እርዳታ ይሳካልሃል።

በሚቀጥለው ምዕራፍ

የዕፅ ሱስን ማሸነፍ የሚቻለው እንዴት ነው?

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 በዩናይትድ ስቴትስ አንድ ብርጭቆ መጠጥ የሚባለው 360 ሚሊ ሊትር ቢራ ወይም 150 ሚሊ ሊትር ወይን ሲሆን የዚህን ያህል መጠን ያለው የአልኮል መጠጥ 14 ግራም ኤታኖል አለው።

^ አን.11 በገጽ 249 ላይ የሚገኘውን “ ከመጠን በላይ የሚጠጡት እነማን ናቸው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.32 ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 8 እና 9⁠ን እንዲሁም የዚህን መጽሐፍ ጥራዝ 2 ምዕራፍ 15 ተመልከት።

ቁልፍ ጥቅስ

“ሰካራሞች . . . ድኾች ይሆናሉ።”—ምሳሌ 23:21

ጠቃሚ ምክር

መጠጣት የምትፈልገው ለምን እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። ዘና ለማለት ወይም ራስህን ለማረጋጋት የሚያስችሉህ ጤንነትህን የማይጎዱ ሌሎች አማራጮችን አስብ።

ይህን ታውቅ ነበር?

በዩናይትድ ስቴትስ የተካሄደ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው “አዘውትረው ከመጠን በላይ የሚጠጡ ተማሪዎች ትምህርት ቤት የመቅረት፣ የትምህርት ቤት ሥራቸውን ዘግይቶ የማስረከብ፣ በራሳቸውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት የማድረስ እንዲሁም ለጉዳት የመጋለጥ አጋጣሚያቸው” ከፍ ያለ ሲሆን እንዲያውም “ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሲነጻጸር በስምንት እጥፍ ይበልጣል።”

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

እኩዮቼ ከመጠን በላይ እንድንጠጣ ቢገፋፉኝ እንዲህ እላቸዋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከመጠን በላይ የሚጠጡ እኩዮችህ ሌሎችም አብረዋቸው እንዲጠጡ የሚፈልጉት ለምን ይመስልሃል?

● ከመጠን በላይ መጠጣት የተቃራኒ ፆታን ትኩረት ለመሳብ የሚያስችልህ ይመስልሃል? እንዲህ ያልኸው ለምንድን ነው?

[በገጽ 250 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“አብረውኝ የሚማሩ ልጆች እንድጠጣ ሲጋብዙኝ፣ ዘና ለማለት የግድ መጠጣት እንደማያስፈልገኝ እነግራቸዋለሁ።”—ማርክ

[በገጽ 249 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

 ከመጠን በላይ የሚጠጡት እነማን ናቸው?

በስኮትላንድ፣ በእንግሊዝና በዌልስ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ላይ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ከ13 እስከ 14 ዓመት ባለው ዕድሜ ከሚገኙ ልጆች መካከል 25 በመቶ የሚሆኑት “ቢያንስ አምስት ብርጭቆ መጠጥ እያከታተሉ ጠጥተው እንደሚያውቁ ተናግረዋል።” በጥናቱ ከተካፈሉት ከ15 እስከ 16 ዓመት ባለው ዕድሜ የሚገኙ ልጆች መካከል ግማሽ ያህሉም ተመሳሳይ ነገር ማድረጋቸውን ገልጸዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የጤና እና የሰብዓዊ አገልግሎቶች ክፍል ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው “ከ12 እስከ 20 ዓመት ከሚሆናቸው ወጣቶች መካከል 10.4 ሚሊዮን የሚያህሉት የአልኮል መጠጥ እንደሚወስዱ ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 5.1 ሚሊዮን የሚሆኑት ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ አላቸው፤ በአንድ ወር ውስጥ ቢያንስ አምስት ጊዜ ከመጠን በላይ እንደሚጠጡ የገለጹ 2.3 ሚሊዮን የሚያህሉ ኃይለኛ ጠጪዎችም በዚህ አኃዝ ውስጥ ይካተታሉ።” በአውስትራሊያ የተካሄደ ጥናት እንደሚያሳየው ከወንዶች ይልቅ ወጣት ሴቶች ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ያላቸው ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ13 እስከ 30 ብርጭቆ ሊጠጡ ይችላሉ!

[በገጽ 251 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአልኮል መጠጥ እንደ እባብ ይነድፋል