በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?

ምዕራፍ 35

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የምችለው እንዴት ነው?

የዕፅ ሱሰኛ ነህ? ከሆነ ይህ ሱስ አእምሮህንም ሆነ ሰውነትህን እንደሚጎዳ ሳታውቅ አትቀርም። ምናልባትም ዕፅ መውሰድህን ለማቆም ብትሞክርም ሱሱ እያገረሸብህ ተቸግረህ ይሆናል። ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የቻሉ ሰዎች አሉ፤ አንተም ብትሆን እንዲህ ማድረግ ትችላለህ! የኋላ ታሪካቸው በጣም የተለያየ ሦስት ሰዎች ከዕፅ ሱስ እንዴት እንደተላቀቁ እንድታነብ እንጋብዝሃለን።

ስም ማርታ

የቀድሞ ሕይወቴ እናቴ የወለደችኝ ሳታገባ በመሆኑ እኔንና እህቴን ያሳደገችን ያለ አባት ነው። ዳንስ በጣም ትወድ ከነበረች አክስቴ ጋር ወደ ጭፈራ ቤቶች መሄድ የጀመርኩት በ12 ዓመቴ ነው። በተፈጥሮዬ ተግባቢ ስለሆንኩ መጥፎ ልማድ ካላቸው ሰዎች ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ጊዜ አልወሰደብኝም። በ13 ዓመቴ ዕፅ መውሰድ ጀመርኩ። ኮኬይንም ጭምር እወስድ ነበር። ዕፅ መውሰድ መጀመሪያ ላይ ደስታ ቢሰጠኝም እያደር ግን መቃዠት የጀመርኩ ሲሆን ሁሉ ነገር ያስፈራኝ ነበር። ዕፅ በማልወስድበት ጊዜ ደግሞ ራሴን ለማጥፋት አስብ ነበር። ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅ ብፈልግም ቁርጥ አድርጌ መተው አልቻልኩም።

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የቻልኩት እንዴት ነው? ስለ አምላክ አስብ ነበር፤ ቤተ ክርስቲያን የሄድኩባቸው ጊዜያትም ነበሩ። ይሁን እንጂ ነገሮች ይበልጥ ተስፋ አስቆራጭ ሆኑብኝ። አሥራ ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ከወንድ ጓደኛዬ ጋር መኖር የጀመርኩ ሲሆን ልጅም ወለድኩ። የልጅ እናት መሆኔ አኗኗሬን ለመለወጥ ይበልጥ አነሳሳኝ። በዚህ መሃል አንድ የቀድሞ ጓደኛዬ በአቅራቢያችን መኖር ጀመረች፤ ቤቴ ስትመጣ ስለ ሕይወቴ ጠየቀችኝ። እኔም በውስጤ ያለውን ሁሉ ዝክዝክ አድርጌ ነገርኳት። ጓደኛዬ የይሖዋ ምሥክር እንደሆነች ከነገረችኝ በኋላ አብሬያት መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ጋበዘችኝ። እኔም በሐሳቧ ተስማማሁ።

አኗኗሬ አምላክን እንደማያስደስትና እሱን ለማስደሰት ከፈለግሁ ዕፅ መውሰድና ሲጋራ ማጨስ ማቆም እንዳለብኝ ተማርኩ። ይሁንና የነበረብኝ የዕፅ ሱስ በቀላሉ ሊለቀኝ አልቻለም። ይሖዋ አምላክ ከዚህ መጥፎ ልማድ ለመላቀቅ እንዲረዳኝ በየቀኑ ደጋግሜ እማጸነው ነበር። እሱን ማስደሰት እፈልግ ነበር። (ምሳሌ 27:11) መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ከጀመርኩ ከስድስት ወራት በኋላ ከዕፅ ሱስ መላቀቅ ቻልኩ። በአሁኑ ወቅት ትርጉም ያለው ሕይወት እየመራሁ ነው። በትካዜ እዋጥ የነበረበት ወቅት አልፏል። እንዲሁም ግሩም ባሕርያት ያሉት አንድ ክርስቲያን አግብቻለሁ። ልጄንም በመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ኮትኩቼ ማሳደግ ችያለሁ። ይሖዋ ጸሎቴን ሰምቶ ስለረዳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ!

ስም ማርስዮ

የቀድሞ ሕይወቴ ያደግሁት በሳኦ ፓውሎ፣ ብራዚል በምትገኝ ሳንቱ አንድሬ የተባለች ከተማ ነው፤ የምንኖረው በሕዝብ በተጨናነቀችው በዚህች ከተማ ጫፍ ነበር። ትንባሆና ዕፅ መውሰድ እንዲሁም ዝርፊያ የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው። አብዛኞቹ ጓደኞቼ መኪና ይሰርቁ እንዲሁም ዕፅ ያዘዋውሩ ነበር። አንዱ ጓደኛዬ በአካባቢያችን ላሉ ወጣቶች ዕፅ በነፃ ይሰጣቸው ነበር። ሱስ ከያዛቸው በኋላ ግን ሳይወዱ በግዳቸው ይገዙታል።

ፖሊሶች ከአካባቢያችን ጠፍተው አያውቁም፤ እኔም በቀላል ወንጀሎች የተነሳ ብዙ ጊዜ ታስሬያለሁ፤ እንዲሁም በአንድ ወቅት በዕፅ አዘዋዋሪነት ተጠርጥሬ እስር ቤት ገብቻለሁ። ወሮበሎች ዘርፈው ያመጧቸውን ንብረቶችና መሣሪያዎቻቸውን ብዙ ጊዜ ቤቴ አስቀምጥላቸው ነበር።

ሰዎች ይፈሩኝ ነበር። ዓይኖቼ ደም የሚመስሉ ከመሆኑም ሌላ ፊቴ ተፈትቶ አያውቅም። ሲያዩኝ ነፍሰ ገዳይ እመስል ነበር። በሄድኩበት ሁሉ ሁከት እፈጥር ስለነበር “ቱፋውን” (ኃይለኛ አውሎ ነፋስ) የሚል ቅጽል ስም ወጣልኝ። ከዚህም ሌላ በጣም እጠጣ ነበር፤ ሕይወቴም በሥነ ምግባር ያዘቀጠ ነበር። በርካታ ጓደኞቼ ሕይወታቸው አልፏል አሊያም ወኅኒ ወርደዋል። በሕይወቴ በጣም ተስፋ ቆርጬ ስለነበር ዛፍ ላይ ገመድ አስሬ ራሴን ለመስቀል ሞክሬ አውቃለሁ።

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የቻልኩት እንዴት ነው? አምላክ እንዲረዳኝ በጸሎት ጠየቅኩት። ከጊዜ በኋላ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘሁና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ እንዲሁም አምላክ በመሥፈርቶቹ ለመኖር ከልባቸው የሚጥሩ ሰዎችን እንደሚያስብላቸውና እንደሚረዳቸው ተማርኩ። (መዝሙር 83:18 NW፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7) በሕይወቴ ውስጥ ብዙ ለውጦች ማድረግ ነበረብኝ። በጣም ከከበዱኝ ነገሮች አንዱ ፈገግ ማለትን መልመድ ነበር።

ይሖዋ እንዲረዳኝ አዘውትሬ እጠይቀው የነበረ ከመሆኑም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በተግባር ለማዋል ጥሬያለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ ከቀድሞ “ጓደኞቼ” ራቅሁ፤ መጠጥ ቤት መሄድም ተውኩ። ከዚህ ይልቅ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ከሚመሩ ሰዎች ጋር መቀራረብ ጀመርኩ። እነዚህን ለውጦች ማድረግ በጣም ቢያታግለኝም አሁን እንደ ድሮው ቀማኛ ወይም አሸባሪ አይደለሁም። እንዲሁም ዕፅ ከወሰድኩ ከአሥር ዓመት በላይ ሆኖኛል።

ስም ክሬይግ

የቀድሞ ሕይወቴ ያደግሁት በደቡብ አውስትራሊያ ሲሆን ቤተሰቦቼ በግብርና ሥራ ተሠማርተው ነበር። አባቴ የአልኮል ሱሰኛ ነበር፤ የስምንት ዓመት ልጅ እያለሁ አባቴና እናቴ ተለያዩ። እናቴም እንደገና አገባች፤ አሥራ ሰባት ዓመት እስኪሆነኝ ድረስ የኖርኩት ከእሷ ጋር ነው። ከዚያም በጎችን መሸለት ተማርኩና ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ከሚሠሩ በግ ሸላቾች ጋር መኖር ጀመርኩ። በዚህ ወቅት የተለያዩ ዕፆችን እወስድና ከመጠን በላይ እጠጣ ጀመር። ፀጉሬን ያስረዘምኩ ሲሆን አንድ ላይ ገምጄ ጨሌ አንጠለጥልበት ነበር። ቀናተኛና ጋጠወጥ ብሎም ግልፍተኛ ሰው ሆንኩ። በተደጋጋሚ ጊዜያት ወኅኒ ቤት ወርጃለሁ።

በምዕራብ አውስትራሊያ ወደምትገኝ አነስተኛ ከተማ ተዘዋውሬ ከሴት ጓደኛዬ ጋር መኖር ጀመርኩ፤ የሴት ጓደኛዬ በአካባቢው ባለ ሆቴል ውስጥ የመጠጥ አስተናጋጅ ነበረች። ሁለታችንም የምናጨስና የምንጠጣ ከመሆኑም ሌላ ማሪዋና (ዕፀ ፋሪስ) የምናለማበት ቦታ ነበረን።

ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የቻልኩት እንዴት ነው? አንድ ቀን የይሖዋ ምሥክሮች ወዳረጀው ቤታችን መጡ፤ በወቅቱ የማሪዋና ምርታችንን ከሰበሰብን ብዙም አልቆየንም። የይሖዋ ምሥክሮች የነገሩኝን እንዲሁ ከመቀበል ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ትክክል መሆኑን በጊዜ ሂደት ራሴ መርምሬ አረጋገጥኩ። ከዚያም ያሉብኝን ችግሮች ቀስ በቀስ ማስወገድ ጀመርኩ።

ብዙም ሳይቆይ፣ ከማሪዋና ሱስ መላቀቅ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ይህ ምን ማድረግን እንደሚጨምር አስቡት። ማሪዋናውን ለማምረት ብዙ ለፍቼ ስለነበር ከማጠፋው ይልቅ ለሌላ ሰው ልሰጠው አሰብኩ። ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ስለተገነዘብኩ ምርቱን ለማጥፋት ወሰንኩ። ከዕፅ ሱስ ለመላቀቅና ከመጠን በላይ መጠጣቴን ለማቆም ጸሎት በጣም ረድቶኛል። እነዚህን ነገሮች ለመተው በማደርገው ትግል ማሸነፍ እንድችል አምላክ መንፈሱን እንዲሰጠኝ እጠይቀው ነበር። በተጨማሪም መጥፎ ልማዶችን መተው ከባድ እንዲሆንብኝ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር የነበረኝን ግንኙነት አቋረጥኩ። መጽሐፍ ቅዱስን መማሬና የተማርኩትን በተግባር ማዋሌ ያሉብኝን የባሕርይ ድክመቶች ለማሸነፍ የሚያስችል የመንፈስ ጥንካሬ ሰጠኝ። የሴት ጓደኛዬም መጽሐፍ ቅዱስን ያጠናች ሲሆን መጥፎ ልማዶችን ትታ አኗኗሯን አስተካከለች። ከዚያም ተጋባን። እኔና ባለቤቴ ካሉብን ሱሶች ተገላግለን ጤናማ ሕይወት መምራት ከጀመርን 21 ዓመታት አልፈዋል፤ እንዲሁም ከሁለት ልጆቻችን ጋር ደስተኛ ሕይወት እንመራለን። ይሖዋ አኗኗሬን እንዳስተካክል ባይረዳኝ ኖሮ ሕይወቴ ምን ሊሆን እንደሚችል ሳስበው ይዘገንነኛል።

ቁልፍ ጥቅስ

“ይሖዋ ብርታቴና ኃይሌ ነው።”—ኢሳይያስ 12:2 NW

ጠቃሚ ምክር

የሚቻል ከሆነ ዕፅ ትወስድ የነበረበትን ወቅት ከሚያስታውሱህ ሰዎች፣ ቦታዎችና ነገሮች ራቅ። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት እነዚህን ሰዎች፣ ቦታዎች ወይም ነገሮች ማየት ብቻ እንኳ ሱሱ እንዲያገረሽብህ መንገድ ሊከፍት ይችላል።

ይህን ታውቅ ነበር?

ዕፅ መውሰድ የአንጎልህን ቅርፅ ሊቀይረው ስለሚችል ጉዳት ያስከትላል።

ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች

ሱሱ ካገረሸብኝ እንዲህ አደርጋለሁ፦ ․․․․․

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ወላጆቼን ልጠይቃቸው የምፈልገው ነገር ․․․․․

ምን ይመስልሃል?

● ከዕፅ ሱስ መላቀቅ የሚፈልግ ሰው በአኗኗሩ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማድረግ የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል?

● ስለ አምላክ እውነቱን ማወቅ በዚህ ረገድ የሚረዳው እንዴት ነው?

[በገጽ 253 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“የመጽሐፍ ቅዱስን ላቅ ያሉ መሥፈርቶች በመከተሌ አስደሳችና ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ችያለሁ።”—ማርታ

[በገጽ 256 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከሱስ መላቀቅ እየተቃጠለ ካለ ቤት እንደ መሸሽ ነው፤ የምታጣው ነገር ቢኖርም ሕይወትህን ታተርፋለህ