በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 2

የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን የምንጠራው ለምንድን ነው?

ኖኅ

አብርሃምና ሣራ

ሙሴ

ኢየሱስ ክርስቶስ

ብዙ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለው መጠሪያ የአንድ አዲስ ሃይማኖት ስም ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ ከ2,700 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት እውነተኛው አምላክ፣ አገልጋዮቹን “ምሥክሮቼ” ብሏቸዋል። (ኢሳይያስ 43:10-12) እስከ 1931 ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል እንታወቅ ነበር። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለን መጠራት የጀመርነው ለምንድን ነው?

አምላካችንን ለይቶ ያሳውቃል። በጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ላይ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም በሺዎች በሚቆጠሩ ቦታዎች ይገኝ ነበር። በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ ይህ ስም እንደ ጌታ፣ አምላክ ወይም እግዚአብሔር (እንደ አማርኛው መጽሐፍ ቅዱስ) በመሳሰሉት የማዕረግ ስሞች ተተክቷል። ይሁን እንጂ እውነተኛው አምላክ ራሱን ለሙሴ ሲገልጥ “ይሖዋ” የሚለውን የግል ስሙን የነገረው ሲሆን “ይህ ለዘላለም ስሜ ነው” ብሎታል። (ዘፀአት 3:15) እውነተኛው አምላክ በዚህ መንገድ ራሱን ከሌሎች የሐሰት አማልክት ለይቷል። እኛም በአምላክ ቅዱስ ስም በመጠራታችን እንኮራለን።

ተልእኳችንን ይገልጻል። ከጻድቁ አቤል ጀምሮ የኖሩ በርካታ ሰዎች በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው መሥክረዋል። ከዚያ በኋላ በነበሩት ምዕተ ዓመታትም ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራ፣ ሙሴ፣ ዳዊትና ሌሎችም ከዚህ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” ጋር ተባብረዋል። (ዕብራውያን 11:4 እስከ 12:1) አንድ ግለሰብ የፍርድ ችሎት ፊት ቀርቦ ስለ አንድ ሰው ንጽሕና እንደሚመሠክር ሁሉ እኛም ስለ አምላካችን እውነቱን ለማሳወቅ ቆርጠን ተነስተናል።

የኢየሱስን ምሳሌ እንደምንከተል ያሳያል። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ታማኝና እውነተኛ ምሥክር” ይለዋል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ ራሱም ‘የአምላክን ስም እንዳሳወቀ’ እንዲሁም ስለ አምላክ ‘እውነቱን እንደመሠከረ’ ተናግሯል። (ዮሐንስ 17:26፤ 18:37) እንግዲያው የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች የሆኑ ሁሉ በይሖዋ ስም መጠራት እና ስሙን ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮችም ይህንን ለማድረግ ይጥራሉ።

  • የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ተብለው መጠራት የጀመሩት ለምንድን ነው?

  • ይሖዋ በምድር ላይ ምሥክሮች የነበሩት ከመቼ ጀምሮ ነው?

  • ከሁሉ የሚበልጠው የይሖዋ ምሥክር ማን ነው?