በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 6

ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ከክርስቲያን ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ማዳጋስካር

ኖርዌይ

ሊባኖስ

ጣሊያን

የበጋውን ሐሩርና የክረምቱን ቁር መቋቋም አሊያም ጥቅጥቅ ያለ ደን አቋርጠን መጓዝ ቢኖርብንም እንኳ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሳናሰልስ እንገኛለን። የዕለት ተዕለት ኑሮ ከሚያስከትለው ጫና በተጨማሪ ቀኑን ሙሉ በሥራ ተወጥረን መዋላችን ኃይላችንን ቢያሟጥጥብንም በስብሰባዎቻችን ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ለመሆን ይህን ያህል ጥረት የምናደርገው ለምንድን ነው?

ለደህንነታችን አስፈላጊ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በአእምሮው በመያዝ “አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” ብሏል። (ዕብራውያን 10:24) ይህ አገላለጽ አንዳችን ስለ ሌላው “በጥልቅ ማሰብ” ይኸውም እርስ በርስ በደንብ መተዋወቅ እንደሚኖርብን ያመለክታል። በሌላ አባባል ሐዋርያው፣ ስለ ሌሎች እንድናስብ እያበረታታን ነው። በጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ክርስቲያን ቤተሰቦች ጋር በደንብ ስንተዋወቅ አንዳንዶቹ እኛ ያጋጠመንን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ተቋቁመው እንዳለፉና እኛም እንዲህ እንድናደርግ ሊረዱን እንደሚችሉ እንገነዘባለን።

ዘላቂ የሆነ ወዳጅነት ለመመሥረት ያስችለናል። አብረውን ከሚሰበሰቡት ሰዎች ጋር ያለን ቅርርብ ከተራ ትውውቅ ያለፈ ነው፤ እነዚህ ሰዎች የቅርብ ወዳጆቻችን ናቸው። በሌሎች አጋጣሚዎችም አብረናቸው በመሆን አስደሳች ጊዜ እናሳልፋለን። እንዲህ ያለው ቅርርብ ምን ጥቅም ያስገኛል? አንዳችን የሌላውን ባሕርያት ይበልጥ እንድናደንቅ የሚያነሳሳን ሲሆን ይህም በመካከላችን የጠበቀ ፍቅር እንዲኖር ያደርጋል። እንዲህ ያለ ጠንካራ ወዳጅነት መመሥረታችን ደግሞ ባልንጀሮቻችን የሆነ ችግር ሲያጋጥማቸው ቶሎ እንድንደርስላቸው ይገፋፋናል። (ምሳሌ 17:17) ከሁሉም የጉባኤያችን አባላት ጋር በመቀራረብ ‘እርስ በርሳችን እኩል እንደምንተሳሰብ’ እናሳያለን።—1 ቆሮንቶስ 12:25, 26

አንተም የአምላክን ፈቃድ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ወዳጅነት እንድትመሠርት እናበረታታሃለን። እንደነዚህ ያሉ ወዳጆችን በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ታገኛለህ። ከእኛ ጋር እንዳትቀራረብ ምንም ነገር እንዲያግድህ አትፍቀድ።

  • በስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር መቀራረባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

  • በጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኝተህ ከእኛ ጋር የምትተዋወቀው መቼ ነው?