በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 8

ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

አይስላንድ

ሜክሲኮ

ጊኒ ቢሳው

ፊሊፒንስ

የይሖዋ ምሥክሮች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ ጥሩ አለባበስ እንደሚኖራቸው አስተውለሃል? በዚህ ብሮሹር ላይ ያሉትን ሥዕሎች ስትመለከትም ይህን ልብ ብለህ ይሆናል። ለአለባበሳችን ይህን ያህል ትኩረት የምንሰጠው ለምንድን ነው?

ለአምላካችን አክብሮት እንዳለን ለማሳየት። አምላክ ከውጫዊው ገጽታችን ባሻገር ልባችንን እንደሚመለከት የተረጋገጠ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7) ይሁን እንጂ አምላክን ለማምለክ በምንሰበሰብበት ወቅት ለእሱም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን አክብሮት ማሳየት እንፈልጋለን። ፍርድ ቤት ብንቀርብ ለዳኛው ሥልጣን አክብሮት እንዳለን በሚያሳይ መንገድ እንደምንለብስ የታወቀ ነው። በተመሳሳይም ወደ ስብሰባዎች ስንሄድ የሚኖረን አለባበስ “የምድር ሁሉ ዳኛ” የሆነውን ይሖዋ አምላክንና የአምልኮ ቦታውን ምን ያህል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ያሳያል።—ዘፍጥረት 18:25

የምንመራባቸውን እሴቶች በአለባበሳችን ለማሳየት። መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች “በልከኝነትና በማስተዋል” እንዲለብሱ ያበረታታል። (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) “በልከኝነት” መልበስ ሲባል አላስፈላጊ ትኩረት የሚስብ ይኸውም የይታይልኝ መንፈስ የሚንጸባረቅበት፣ የፆታ ስሜት የሚቀሰቅስ ወይም ሰውነት የሚያሳይ ልብስ አለመልበስ ማለት ነው። “በማስተዋል” መልበስ ሲባል ደግሞ የሚያምር ሆኖም ቅጥ ያጣ ወይም ዝርክርክ ያልሆነ አለባበስ ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። እርግጥ ነው፣ በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ብንመራም በአለባበስ ረገድ የየራሳችን የተለያዩ ምርጫዎች ይኖሩናል። አለባበሳችን የሚያምርና ሥርዓታማ መሆኑ ‘አዳኛችን የሆነውን አምላክ ትምህርት’ ያለ ምንም ቃል ‘ውበት የሚያጎናጽፈው’ ከመሆኑም ሌላ ‘አምላክን ያስከብራል።’ (ቲቶ 2:10፤ 1 ጴጥሮስ 2:12) ስብሰባ ስንሄድ ለአለባበሳችን ልዩ ትኩረት መስጠታችን ሌሎች ለይሖዋ አምልኮ ባላቸው አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ያም ሆኖ አለባበስህ ለስብሰባ እንደማይመጥን በማሰብ ወደ ስብሰባ አዳራሽ ከመምጣት ወደኋላ አትበል። ሥርዓታማ፣ ንጹሕና የሚማርክ ልብስ መልበስ ብዙ ገንዘብ አይጠይቅም።

  • ለአምላክ በምናቀርበው አምልኮ ረገድ አለባበሳችን ምን ቦታ አለው?

  • ከአለባበሳችን ጋር በተያያዘ የምንመራባቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች የትኞቹ ናቸው?