በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 13

አቅኚነት ምንድን ነው?

አቅኚነት ምንድን ነው?

ካናዳ

ከቤት ወደ ቤት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት

የግል ጥናት

“አቅኚ” የሚለው ቃል ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት ወደ አዲስ አካባቢ የሚሄዱ እንዲሁም ፈር ቀዳጅ በመሆን ለሌሎች መንገድ የሚጠርጉ ሰዎችን ለማመልከት ነው። ኢየሱስ፣ ሕይወት የሚያስገኝ አገልግሎት ለማከናወንና ወደ መዳን የሚመራውን በር ለመክፈት ወደ ምድር በመምጣቱ አቅኚ ሊባል ይችላል። (ማቴዎስ 20:28) በዛሬው ጊዜም ተከታዮቹ፣ ሰዎችን ‘ደቀ መዛሙርት በማድረጉ’ ሥራ የሚችሉትን ያህል ጊዜ በማሳለፍ የእሱን ምሳሌ እየተከተሉ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች ደግሞ የአቅኚነት አገልግሎት ብለን በምንጠራው መስክ ይካፈላሉ።

አቅኚዎች የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች የምሥራቹ አስፋፊዎች ወይም ሰባኪዎች ናቸው። አንዳንዶች ግን ፕሮግራማቸውን አስተካክለው በየወሩ 70 ሰዓት በስብከቱ ሥራ በማሳለፍ የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ያገለግላሉ። ብዙዎች ይህን ለማድረግ ሲሉ በሰብዓዊ ሥራቸው ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ይቀንሳሉ። ሌሎች ደግሞ የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ልዩ አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ የሚመደቡ ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ በየወሩ 130 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ያሳልፋሉ። አቅኚዎች ይሖዋ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንደሚያሟላላቸው ቅንጣት ታክል ስለማይጠራጠሩ ባላቸው በመርካት ቀለል ያለ ሕይወት ይመራሉ። (ማቴዎስ 6:31-33፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) ልዩ ወይም የዘወትር አቅኚ መሆን የማይችሉ ክርስቲያኖች ደግሞ በሚመቻቸው ወር ረዳት አቅኚዎች ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን በዚያ ወቅት በስብከቱ ሥራ በወር ውስጥ 30 ወይም 50 ሰዓት ያሳልፋሉ።

አቅኚዎች በዚህ መስክ እንዲሰማሩ የሚያነሳሳቸው ለይሖዋና ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ነው። ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ያሉበትን መንፈሳዊ ሁኔታ ሲመለከት አዝኖላቸው ነበር፤ እኛም በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ያሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ አሳዛኝ እንደሆነ እናስተውላለን። (ማርቆስ 6:34) በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለወደፊቱ ጊዜ አስተማማኝ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያደርግ እውቀት እንዳለን እንገነዘባለን፤ ይህ እውቀት በአሁኑ ጊዜም እንኳ ሊጠቅማቸው ይችላል። አቅኚዎች ለሰዎች ያላቸው ፍቅር ሌሎችን በመንፈሳዊ ለመርዳት ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ሳይቆጥቡ በስብከቱ ሥራ እንዲያሳልፉ ያነሳሳቸዋል። (ማቴዎስ 22:39፤ 1 ተሰሎንቄ 2:8) እንዲህ በማድረጋቸው እምነታቸው የሚጠናከርና ወደ አምላክ ይበልጥ የሚቀርቡ ከመሆኑም ሌላ ይህ ነው የማይባል ደስታ ያገኛሉ።—የሐዋርያት ሥራ 20:35

  • አቅኚነት ምንድን ነው?

  • አንዳንዶች በአቅኚነት እንዲካፈሉ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው?