በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 14

አቅኚዎች ምን ዓይነት የትምህርት አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል?

አቅኚዎች ምን ዓይነት የትምህርት አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል?

ዩናይትድ ስቴትስ

ጊልያድ ትምህርት ቤት፣ ፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ

ፓናማ

ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች ለረጅም ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች መለያ ሆነው ቆይተዋል። ሙሉ ጊዜያቸውን የስብከቱን ሥራ ለማከናወን የሚያውሉ ክርስቲያኖች ‘አገልግሎታቸውን በተሟላ ሁኔታ መፈጸም’ እንዲችሉ የሚረዷቸው ለየት ያሉ የትምህርት አጋጣሚዎች አሏቸው።—2 ጢሞቴዎስ 4:5

የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት፦ አንድ የዘወትር አቅኚ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት አንድ ዓመት ካሳለፈ በኋላ ስድስት ቀን የሚፈጅ ሥልጠና መውሰድ ይችላል፤ ትምህርት ቤቱ የሚካሄደው በአካባቢው ባለ የስብሰባ አዳራሽ ሊሆን ይችላል። የዚህ ትምህርት ቤት ዓላማ አቅኚዎች ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንዲቀርቡ፣ በሁሉም የአገልግሎታቸው ዘርፎች ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ እንዲሁም በታማኝነት በአገልግሎታቸው መጽናት እንዲችሉ መርዳት ነው።

የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት፦ ሁለት ወር የሚፈጀው ይህ ትምህርት ቤት፣ የሚኖሩበትን አካባቢ ትተው ይበልጥ እርዳታ ወደሚያስፈልግበት ቦታ ለመሄድ ፈቃደኛ የሆኑ ተሞክሮ ያላቸው አቅኚዎችን ለማሠልጠን የተዘጋጀ ነው። እነዚህ አቅኚዎች በምድር ላይ ከኖሩት ወንጌላውያን ሁሉ የላቀውን ወንጌላዊ ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመከተል “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” የሚሉ ያህል ነው። (ኢሳይያስ 6:8፤ ዮሐንስ 7:29) ከሚኖሩበት አካባቢ ርቀው መሄዳቸው አኗኗራቸውን ቀላል ማድረግ ይጠይቅባቸው ይሆናል። የሚሄዱበት አካባቢ ባሕል፣ የአየር ጠባይ እንዲሁም ምግብ ከለመዱት ፈጽሞ የተለየ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም አዲስ ቋንቋ መማር ያስፈልጋቸው ይሆናል። ትምህርት ቤቱ፣ ከ23 እስከ 65 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ነጠላ ወንድሞች፣ እህቶች እንዲሁም ባለትዳሮች በተመደቡበት ቦታ የሚያስፈልጓቸውን መንፈሳዊ ባሕርያት ብሎም ይሖዋና ድርጅቱ ይበልጥ እንዲጠቀሙባቸው የሚያስችሏቸውን ክህሎቶች እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።

ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት፦ “ጊልያድ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “የምሥክሮች ክምር” የሚል ትርጉም አለው። ትምህርት ቤቱ ከተቋቋመ ከ1943 ወዲህ ከጊልያድ የተመረቁ ከ8,000 በላይ ተማሪዎች ሚስዮናውያን እንዲሆኑ የተላኩ ሲሆን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ውጤታማ የሆነ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። (የሐዋርያት ሥራ 13:47) ለምሳሌ ያህል፣ ሚስዮናውያን መጀመሪያ ወደ ፔሩ ሲላኩ በዚያች አገር አንድም ጉባኤ አልነበረም። አሁን ግን ከ1,000 የሚበልጡ ጉባኤዎች አሉ። ሚስዮናውያኖቻችን መጀመሪያ ወደ ጃፓን ሲሄዱ በአገሪቱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች አሥር አይሞሉም ነበር። አሁን ግን ከ200,000 በላይ ሆነዋል። በጊልያድ የሚሰጠው የአምስት ወር ሥልጠና ተማሪዎቹ የአምላክን ቃል ጥልቀት ባለው መንገድ እንዲያጠኑ ያስችላቸዋል። ልዩ አቅኚዎች፣ በመስክ የሚያገለግሉ ሚስዮናውያን፣ በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚሠሩ ወይም በወረዳ ሥራ የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በትምህርት ቤቱ እንዲሠለጥኑ ይጋበዛሉ፤ በዚህ የሚሰጠው ጥልቀት ያለው ሥልጠና በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን ሥራ ለማጠናከር አስተዋጽኦ ያበረክታል።

  • የአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ዓላማ ምንድን ነው?

  • በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መሠልጠን የሚችሉት እነማን ናቸው?