በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 10

እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

1. እውነተኛው ሃይማኖት አንድ ብቻ ነው?

‘ከሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ።’—ማቴዎስ 7:15

ኢየሱስ ተከታዮቹን ያስተማራቸው ስለ አንድ ሃይማኖት ብቻ ሲሆን እሱም እውነተኛው ሃይማኖት ነው። ይህ እውነተኛ ሃይማኖት ወደ ዘላለም ሕይወት ከሚወስድ መንገድ ጋር ይመሳሰላል። ኢየሱስ ይህን መንገድ አስመልክቶ “የሚያገኙትም ጥቂቶች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:14) አምላክ የሚቀበለው፣ የእውነት ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተን አምልኮ ብቻ ነው። ሁሉም እውነተኛ አምላኪዎች እምነታቸው አንድ መሆኑ በመካከላቸው አንድነት እንዲኖር አድርጓል።​—ዮሐንስ 4:23, 24ን፣ 14:6ን እና ኤፌሶን 4:4, 5ን አንብብ።

አምላክ ሁሉንም ሃይማኖቶች ይቀበላል? የሚለውን ቪዲዮ ተመልከት

2. ኢየሱስ ስለ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ምን ብሏል?

“አምላክን እንደሚያውቁ በይፋ ይናገራሉ፤ ሆኖም በሥራቸው ይክዱታል።”—ቲቶ 1:16

ኢየሱስ ሐሰተኛ ነቢያት ክርስትናን እንደሚበክሉ አስጠንቅቆ ነበር። እነዚህ ነቢያት ከውጭ ሲታዩ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ይመስላሉ። እንዲሁም ክርስቲያኖች እንደሆኑ ይናገራሉ። ይሁንና የእነዚህን ሰዎች ትክክለኛ ማንነት ማወቅ ይቻላል። እንዴት? እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይተው የሚያሳውቋቸውን ባሕርያትና ተግባራት ማየት የሚቻለው በእውነተኛው ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ብቻ ነው።​—ማቴዎስ 7:13-23ን አንብብ።

3. እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይተህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው?

አምስት መለያ ምልክቶችን እስቲ እንመልከት፦

  • እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች መጽሐፍ ቅዱስን እንደ አምላክ ቃል አድርገው ይቀበላሉ። በውስጡ ከሚገኙት መመሪያዎች ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። በመሆኑም እውነተኛው ሃይማኖት በሰብዓዊ አስተሳሰብ ላይ ከተመሠረተ ሃይማኖት ይለያል። (ማቴዎስ 15:7-9) እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች፣ አኗኗራቸው ከሚሰብኩት ትምህርት ጋር አይጋጭም።​—ዮሐንስ 17:17ን እና 2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17ን አንብብ።

  • የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ይሖዋ የሚለውን የአምላክ ስም ያከብራሉ። ኢየሱስ የአምላክ ስም እንዲታወቅ በማድረግ ስሙን አክብሮታል። ሰዎች አምላክን እንዲያውቁ እንዲሁም ስለ አምላክ ስም መቀደስ እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:9) አንተ በምትኖርበት አካባቢ የአምላክን ስም የሚያሳውቀው ሃይማኖት የትኛው ነው?​—ዮሐንስ 17:26ን እና ሮም 10:13, 14ን አንብብ።

  • እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ አምላክ መንግሥት ይሰብካሉ። አምላክ ኢየሱስን ወደ ምድር የላከው የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብክ ነው። የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት ነው። ኢየሱስ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ስለ አምላክ መንግሥት ይናገር ነበር። (ሉቃስ 4:43፤ 8:1፤ 23:42, 43) ተከታዮቹም ስለ አምላክ መንግሥት እንደሚሰብኩ ተናግሯል። አንድ ሰው ስለ አምላክ መንግሥት ሊነግርህ ከመጣ የየትኛው ሃይማኖት ተከታይ ሊሆን ይችላል ብለህ ታስባለህ?​—ማቴዎስ 24:14ን አንብብ።

  • የኢየሱስ ተከታዮች የዚህ ክፉ ዓለም ክፍል አይደሉም። በፖለቲካ ጉዳዮችም ሆነ በማኅበራዊ ግጭቶች ውስጥ ጣልቃ የማይገቡ በመሆናቸው ለይተህ ልታውቃቸው ትችላለህ። (ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) በተጨማሪም በዓለም ላይ የሚታዩትን ጎጂ ድርጊቶችና ዝንባሌዎች አይኮርጁም።​—ያዕቆብ 4:4ን አንብብ።

  • እውነተኛ ክርስቲያኖች እርስ በርሳቸው ከልብ ይዋደዳሉ። ምንም ዓይነት ዘር ይኑረው ማንኛውንም ሰው ማክበር እንዳለባቸው ከአምላክ ቃል ተምረዋል። ብዙውን ጊዜ የሐሰት ሃይማኖቶች በብሔራት መካከል የሚደረጉ ጦርነቶች ቀንደኛ ደጋፊዎች ቢሆኑም እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች ግን እንዲህ ለማድረግ ፈቃደኞች አይደሉም። (ሚክያስ 4:1-3) ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ክርስቲያኖች ጊዜያቸውንና ንብረታቸውን ምንም ሳይቆጥቡ ሌሎችን ለመርዳትና ለማበረታታት ይጠቀሙበታል።​—ዮሐንስ 13:34, 35ን እና 1 ዮሐንስ 4:20ን አንብብ።

4. እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተህ ማወቅ ትችላለህ?

ምንጊዜም በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ ትምህርት የሚያስተምረው፣ የአምላክን ስም የሚያከብረውና የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ የሚያውጀው ሃይማኖት የትኛው ነው? እርስ በርስ የሚዋደዱና ፈጽሞ በጦርነት የማይካፈሉ አባላት ያሉት ሃይማኖት የትኛው ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች ምን መልስ ትሰጣለህ?​—1 ዮሐንስ 3:10-12ን አንብብ።