በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 1

አስደሳች የሆነ ሚስጥር

አስደሳች የሆነ ሚስጥር

አንድ ሰው ሚስጥር ነግሮህ ያውቃል?— * መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ስለሆነ አንድ ሚስጥር ይናገራል፤ ይህን ሚስጥር “ቅዱስ ሚስጥር” በማለት ይጠራዋል። ቅዱስ የተባለው ከአምላክ የመጣ ስለሆነ ነው። ሚስጥር የተባለው ደግሞ በአንድ ወቅት ሰዎች ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ነገር ስላልነበረ ነው። መላእክት እንኳ ስለዚህ ሚስጥር ይበልጥ ለማወቅ ይጓጉ ነበር። አንተስ ይህ ሚስጥር ምን እንደሆነ ለማወቅ ትፈልጋለህ?—

መላእክቱ ለማወቅ የፈለጉት ነገር ምን ይመስልሃል?

ከረጅም ጊዜ በፊት አምላክ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ፈጠረ። እነዚህ ሰዎች አዳም እና ሔዋን ይባላሉ። አምላክ፣ ኤደን ገነት የተባለች ውብ መኖሪያ ሰጣቸው። አዳምና ሔዋን አምላክን ቢታዘዙ ኖሮ እነሱም ሆኑ ልጆቻቸው መላዋን ምድር እንደ ኤደን ውብ ገነት ያደርጓት ነበር። እንዲሁም በገነት ለዘላለም ይኖሩ ነበር። ሆኖም አዳምና ሔዋን ምን እንዳደረጉ ታስታውሳለህ?—

አዳምና ሔዋን አምላክን አልታዘዙም፤ ዛሬ በገነት ውስጥ የማንኖረው በዚያ ምክንያት ነው። ይሁን እንጂ አምላክ፣ መላዋን ምድር ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል፤ በተጨማሪም በዚያ የሚኖር ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኝና ደስተኛ እንደሚሆን ተናግሯል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ሰዎች ለረጅም ጊዜ አያውቁትም ነበር። ጉዳዩ ሚስጥር ነበር።

ኢየሱስ ወደ ምድር በመጣበት ወቅት ስለዚህ ቅዱስ ሚስጥር ለሰዎች ተናገረ። ይህ ሚስጥር ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገር መሆኑን ገለጸ። ኢየሱስ ይህ መንግሥት እንዲመጣ እንዲጸልዩም ሰዎችን አስተምሯል። ይህ መንግሥት ምድርን ውብ ገነት ያደርጋታል።

ይህን ሚስጥር በማወቅህ አልተደሰትክም?— በገነት የሚኖሩት ይሖዋን የሚታዘዙት ሰዎች ብቻ እንደሆኑ አስታውስ። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክን ስለታዘዙ ወንዶችና ሴቶች የሚናገሩ በርካታ ታሪኮችን ይዟል። ስለ እነዚህ ሰዎች ማወቅ ትፈልጋለህ?— እስቲ ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ እነማን እንደሆኑና እነሱን መምሰል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

^ አን.3 በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ታሪኮች ስታነቡ ከአንዳንድ ጥያቄዎች ቀጥሎ () ታገኛላችሁ። ልጃችሁ ለጥያቄው መልስ እንዲሰጥ እዚህ ጋ ቆም ማለታችሁ ጥሩ ነው።