በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ትምህርት 6

ዳዊት አልፈራም

ዳዊት አልፈራም

ፍርሃት ሲሰማህ ምን ታደርጋለህ?— እርዳታ ለማግኘት ወደ አባትህ ወይም ወደ እናትህ ትሄድ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሊረዳህ የሚችል ሌላም አካል አለ። እሱ ከማንም የበለጠ ኃይል አለው። ይህ አካል ማን እንደሆነ ታውቃለህ?— አዎ፣ ይሖዋ አምላክ ነው። እስቲ ዳዊት ስለተባለ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ ወጣት እንመልከት። ዳዊት ምንጊዜም ይሖዋ እንደሚረዳው ስለሚያውቅ አይፈራም ነበር።

ዳዊት ይሖዋን እንዲወድ ወላጆቹ ከልጅነቱ ጀምሮ አስተምረውታል። ይህም አስፈሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት እንኳ እንዳይፈራ ረድቶታል። ይሖዋ ወዳጁ እንደሆነና እንደሚረዳው ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት ዳዊት በጎች እየጠበቀ ሳለ አንድ ትልቅ አንበሳ መጥቶ አንዷን በግ ወሰደበት። ዳዊት ምን እንዳደረገ ታውቃለህ? አንበሳውን አሳድዶ ገደለው፤ ይህን ሲያደርግ በእጁ ምንም መሣሪያ የያዘ አይመስልም። በሌላ ጊዜ ደግሞ ድብ በጎቹን ሊወስድ ሲሞክር ዳዊት እሱንም ገደለው! ዳዊትን የረዳው ማን ይመስልሃል?— አዎ፣ ይሖዋ ነው።

ዳዊት ደፋር መሆኑን ያሳየበት ሌላም አጋጣሚ ነበር። እስራኤላውያን ፍልስጥኤማውያን ከሚባሉ ሕዝቦች ጋር ይዋጉ ነበር። ከፍልስጥኤማውያን ወታደሮች አንዱ በጣም ረጅምና ግዙፍ ሰው ነበር! ስሙ ጎልያድ ይባላል። ይህ ግዙፍ ሰው በእስራኤላውያን ወታደሮችና በይሖዋ ላይ ያሾፍ ነበር። ጎልያድ፣ እስራኤላውያን ወታደሮችን ከእሱ ጋር እንዲዋጉ ጠየቃቸው። ሆኖም ጎልያድን ሊገጥም የደፈረ አንድም እስራኤላዊ አልነበረም። ዳዊት፣ ጎልያድ ያለውን ሲሰማ ‘እኔ ከአንተ ጋር እዋጋለሁ! ይሖዋ ስለሚረዳኝ አሸንፍሃለሁ!’ አለው። ዳዊት ደፋር እንደሆነ ይሰማሃል?— አዎን፣ በጣም ደፋር ነበር። ዳዊት ከዚያ በኋላ ምን እንዳደረገ ማወቅ ትፈልጋለህ?

ዳዊት ወንጭፉንና አምስት ድቡልቡል ድንጋዮችን ይዞ ግዙፉን ጎልያድ ለመግጠም ሄደ። ጎልያድ፣ ዳዊት ትንሽ ልጅ መሆኑን ሲያይ አሾፈበት። ዳዊት ግን ‘አንተ ሰይፍ ይዘህ መጥተሃል፤ እኔ ግን በይሖዋ ስም እመጣብሃለሁ!’ አለው። ከዚያም ዳዊት ወንጭፉ ላይ ድንጋይ አድርጎ ወደ ጎልያድ እየሮጠ በመሄድ አስወነጨፈው። ድንጋዩም ጎልያድን ግንባሩ ላይ መታው! ግዙፉ ሰው መሬት ላይ ተዘረረና ሞተ! ፍልስጥኤማውያንም በጣም ስለፈሩ ሁሉም ሸሹ። እንደ ዳዊት ያለ ወጣት ልጅ ግዙፉን ፍልስጥኤማዊ ማሸነፍ የቻለው እንዴት ነው?— ይሖዋ ስለረዳው ነው፤ አምላክ ከዚህ ግዙፍ ሰው የበለጠ ኃያል ነው!

ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚረዳው ስለሚያውቅ አልፈራም

ከዳዊት ታሪክ ምን ትምህርት ታገኛለህ?— ይሖዋ ከማንም የበለጠ ኃይል አለው። ለአንተም ወዳጅህ ነው። በመሆኑም የሚያስፈራ ነገር ሲያጋጥምህ፣ ደፋር እንድትሆን ይሖዋ እንደሚረዳህ አስታውስ!

የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡ