በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 1

“መንግሥትህ ይምጣ”

“መንግሥትህ ይምጣ”

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የሰጠውን ትምህርት መመርመር

1, 2. ሦስቱ የኢየሱስ ሐዋርያት ይሖዋ ራሱ ሲናገር የሰሙት ነገር ምንድን ነው? ምን ምላሽስ ሰጡ?

 ይሖዋ አምላክ ራሱ አንድ ነገር እንድታደርግ ቢያዝህ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር? ትእዛዙ ምንም ይሁን ምን መመሪያውን ተግባራዊ ለማድረግ እንደምትጓጓ ምንም ጥርጥር የለውም!

2 በ32 ዓ.ም. የፋሲካ በዓል ከተከበረ ብዙም ሳይቆይ ሦስቱ የኢየሱስ ሐዋርያት ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። (ማቴዎስ 17:1-5ን አንብብ።) ከጌታቸው ከኢየሱስ ጋር “ወደ አንድ ረጅም ተራራ” ከወጡ በኋላ ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ ሲገዛ የሚኖረውን ክብር በራእይ ተመለከቱ። ራእዩ በእውን እየተፈጸመ ያለ ይመስል ስለነበር ጴጥሮስ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ሐሳብ አቀረበ። ጴጥሮስ እየተናገረ ሳለ ደመና ጋረዳቸው። ከዚያም ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ሐዋርያት፣ ጥቂት ሰዎች ብቻ ያገኙትን መብት ይኸውም ይሖዋ ራሱ ሲናገር የመስማት አጋጣሚ አገኙ። ይሖዋ፣ ኢየሱስ ልጁ መሆኑን አስረግጦ ከተናገረ በኋላ “እሱን ስሙት” የሚል ግልጽ መመሪያ ሰጣቸው። ሐዋርያቱ ይህን መለኮታዊ መመሪያ አክብረዋል። ኢየሱስ ያስተማረውን የሰሙ ከመሆኑም ሌላ ሌሎች ሰዎች ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ አሳስበዋል።—ሥራ 3:19-23፤ 4:18-20

ኢየሱስ ከየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ ስለ አምላክ መንግሥት በሰፊው አስተምሯል

3. ይሖዋ ልጁን እንድንሰማው የሚፈልገው ለምንድን ነው? የትኛውን ርዕሰ ጉዳይ መመርመራችንስ የተገባ ነው?

3 እኛም ተጠቃሚዎች መሆን እንችል ዘንድ “እሱን ስሙት” የሚሉት ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበዋል። (ሮም 15:4) እሱን መስማት ያለብን ለምንድን ነው? ኢየሱስ የይሖዋ ቃል አቀባይ ስለሆነና ምንጊዜም ያስተምር የነበረው አባቱ ለእኛ እንዲተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ስለሆነ ነው። (ዮሐ. 1:1, 14) ኢየሱስ ከየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ይበልጥ ስለ አምላክ መንግሥት ማለትም በክርስቶስ ኢየሱስና በ144,000ዎቹ ተባባሪ ገዢዎች ስለተዋቀረው መሲሐዊ መንግሥት ሰፊ ትምህርት ስለሰጠ ይህን ወሳኝ ርዕስ በጥንቃቄ መመርመራችን የተገባ ነው። (ራእይ 5:9, 10፤ 14:1-3፤ 20:6) በመጀመሪያ ግን ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ብዙ ትምህርት የሰጠው ለምን እንደሆነ እንመርምር።

“በልብ ውስጥ የሞላውን . . .”

4. ኢየሱስ ለአምላክ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ ያሳየው እንዴት ነው?

4 ኢየሱስ ለአምላክ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቃላት በልብ ውስጥ ምን እንዳለ ያሳያሉ፤ በሌላ አባባል የምንናገረው ነገር ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ጉዳይ ምን እንደሆነ ያሳያል። ኢየሱስ ራሱ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴ. 12:34) ኢየሱስ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለ አምላክ መንግሥት ይናገር ነበር። በአራቱ የወንጌል ዘገባዎች ላይ የአምላክ መንግሥት ከ100 ጊዜ በላይ የተጠቀሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹን የተናገረው ኢየሱስ ነው። የስብከቱ ጭብጥ የአምላክ መንግሥት በመሆኑ “ለሌሎች ከተሞችም የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው” ብሏል። (ሉቃስ 4:43) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም እንኳ ደቀ መዛሙርቱን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማሩን ቀጥሏል። (ሥራ 1:3) በእርግጥም ኢየሱስ ልቡ ለመንግሥቱ ባለው አድናቆት ተሞልቶ ነበር፤ ይህም ስለ መንግሥቱ እንዲናገር ገፋፍቶታል።

5-7. (ሀ) ይሖዋ ለመንግሥቱ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጥ እንዴት ማወቅ እንችላለን? በምሳሌ ግለጽ። (ለ) ለአምላክ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንደምንሰጥ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

5 ይሖዋም ለመንግሥቱ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ይሖዋ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም እንደላከው አስታውስ፤ ኢየሱስ የተናገረውንም ሆነ ያስተማረውን ነገር በሙሉ የተማረው ከአባቱ ከይሖዋ ነው። (ዮሐ. 7:16፤ 12:49, 50) ደግሞም ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት በሚናገሩት አራት የወንጌል ዘገባዎች ላይ የሰፈረው ሐሳብ ምንጭ ይሖዋ ነው። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ ቆም ብለህ አስብ።

እያንዳንዳችን ‘ለአምላክ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እሰጣለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው

6 የቤተሰብህን ፎቶዎች አልበም ውስጥ እየከተትክ ነው እንበል። ፎቶዎቹ በጣም ብዙ ናቸው፤ አልበሙ ደግሞ መያዝ የሚችለው የተወሰኑትን ብቻ ነው። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋለህ? አልበሙ ውስጥ የትኞቹን እንደምትከትት ትመርጣለህ። የወንጌል ዘገባዎችም የኢየሱስን ማንነት ቁልጭ አድርጎ እንደሚያሳይ የፎቶ አልበም ናቸው ሊባል ይችላል። ይሖዋ፣ የወንጌል ዘገባዎችን በመንፈስ መሪነት ባስጻፈበት ወቅት ጸሐፊዎቹ ኢየሱስ በምድር ላይ ሳለ የተናገረውንና ያደረገውን ነገር በሙሉ እንዲጽፉ አላደረገም። (ዮሐ. 20:30፤ 21:25) ከዚህ ይልቅ በጽሑፍ እንዲያሰፍሩ ያደረገው ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነበትን ዓላማ እንዲሁም ይሖዋ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ነገር እንድንገነዘብ የሚያስችሉንን ሐሳቦች ነው። (2 ጢሞ. 3:16, 17፤ 2 ጴጥ. 1:21) የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት ባስተማራቸው ትምህርቶች የተሞሉ ስለሆኑ ይሖዋ ለመንግሥቱ ትልቅ ትኩረት ይሰጣል ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን። ይሖዋ መንግሥቱ ለምን ዓላማ እንደተቋቋመ እንድናውቅ ይፈልጋል!

7 በመሆኑም እያንዳንዳችን ‘ለአምላክ መንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እሰጣለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ የተናገረውንና ያስተማረውን ነገር ይኸውም የመንግሥቱን አስፈላጊነት እንዲሁም መንግሥቱ የሚመጣው እንዴት እና መቼ እንደሆነ የተናገረውን ሐሳብ ለመስማት እንጓጓለን።

“መንግሥትህ ይምጣ”—እንዴት?

8. ኢየሱስ የመንግሥቱን አስፈላጊነት ጠቅለል አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?

8 እስቲ ኢየሱስ ያስተማረውን የጸሎት ናሙና እንመልከት። ኢየሱስ ሐሳቡን ጥሩ አድርገው በሚገልጹ ያልተወሳሰቡ ቃላት ተጠቅሞ መንግሥቱ ምን እንደሚያከናውን በማስተማር የመንግሥቱን አስፈላጊነት ጠቅለል አድርጎ ገልጿል። ጸሎቱ ሰባት ነጥቦችን አካትቶ ይዟል። የመጀመሪያዎቹ ሦስት ልመናዎች ከይሖዋ ዓላማ ጋር የተያያዙ ናቸው፤ እነሱም ስሙ እንዲቀደስ፣ መንግሥቱ እንዲመጣና ፈቃዱ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲፈጸም የሚቀርቡ ልመናዎች ናቸው። (ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።) እነዚህ ሦስት ልመናዎች ተዛማጅነት አላቸው። መሲሐዊው መንግሥት ይሖዋ ስሙን ለማስቀደስና ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው።

9, 10. (ሀ) የአምላክ መንግሥት በሚመጣበት ጊዜ ምን ያከናውናል? (ለ) የትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሲፈጸም ለማየት ትጓጓለህ?

9 የአምላክ መንግሥት በሚመጣበት ጊዜ ምን ያከናውናል? “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን ስንጸልይ መንግሥቱ ወሳኝ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቃችን ነው። የአምላክ መንግሥት ሲመጣ ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ በምድር ላይ ያደርጋል። ሰብዓዊ መስተዳድሮችን ጨምሮ አሁን ያለውን ክፉ ሥርዓት በማስወገድ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ያመጣል። (ዳን. 2:44፤ 2 ጴጥ. 3:13) ከዚያም በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች። (ሉቃስ 23:43) አምላክ በትንሣኤ የሚያስባቸው ሰዎች ዳግመኛ ሕያው ሆነው ከሚወዷቸው ሰዎች ጋር በድጋሚ ይገናኛሉ። (ዮሐ. 5:28, 29) ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ፍጹም ሆነው የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ራእይ 21:3-5) በመጨረሻም፣ በምድር ላይ ያለው ሁኔታ በሰማይ ካለው ሁኔታ ጋር ሙሉ በሙሉ ተመሳሳይ ይሆናል፤ በምድር ላይ የይሖዋ አምላክ ፈቃድ ይፈጸማል! እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ሲፈጸሙ ለማየት አትጓጓም? የአምላክ መንግሥት እንዲመጣ በጸለይክ ቁጥር እነዚህ ግሩም ተስፋዎች እንዲፈጸሙ እየጸለይክ መሆኑን አትዘንጋ።

10 በጸሎት ናሙናው ላይ የተጠቀሰው፣ የአምላክ መንግሥት ‘እንዲመጣ’ የሚቀርበው ልመና ገና ምላሽ እንዳላገኘ ግልጽ ነው። ሰብዓዊ መስተዳድሮች አሁንም እየገዙ ሲሆን ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ገና አልመጣም። ይሁንና ከዚህ ጋር የተያያዘ አንድ ምሥራች አለ። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ እንደምንመለከተው የአምላክ መንግሥት ተቋቁሟል። በቅድሚያ ግን የአምላክ መንግሥት መቼ እንደሚቋቋምና መቼ እንደሚመጣ ኢየሱስ የተናገረውን እንመልከት።

የአምላክ መንግሥት የሚቋቋመው መቼ ነው?

11. ኢየሱስ የተናገረው ነገር የአምላክን መንግሥት መቋቋም በተመለከተ ምን ይጠቁማል?

11 ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንደማይቋቋም ጠቁሟል፤ ይሁንና አንዳንድ ደቀ መዛሙርቱ ይህ ይሆናል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር። (ሥራ 1:6) ሁለት ዓመት በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በተናገራቸው ሁለት የተለያዩ ምሳሌዎች ላይ ምን እንዳለ ተመልከት።

12. የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ የአምላክ መንግሥት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. አለመቋቋሙን የሚጠቁመው እንዴት ነው?

12 የስንዴውና የእንክርዳዱ ምሳሌ። (ማቴዎስ 13:24-30ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው በ31 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት ሳይሆን አይቀርም፤ ምሳሌውን ከተናገረ በኋላ ትርጉሙን ለደቀ መዛሙርቱ አብራርቶላቸው ነበር። (ማቴ. 13:36-43) የምሳሌው ፍሬ ሐሳብና ትርጉም ይህ ነው፦ ሐዋርያት ከሞቱ በኋላ ዲያብሎስ በስንዴው (“የመንግሥቱ ልጆች” ወይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች) መካከል እንክርዳድ (አስመሳይ ክርስቲያኖች) ይዘራል። ስንዴውም ሆነ እንክርዳዱ እስከ መከር ይኸውም “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” እስኪደርስ ድረስ አንድ ላይ እንዲያድጉ ይተዋሉ። የመከር ወቅት ከጀመረ በኋላ እንክርዳዱ ይሰበሰባል። ከዚያም ስንዴው ይሰበሰባል። በመሆኑም መንግሥቱ የሚቋቋመው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ሳይሆን እድገት የሚያደርጉበት ወቅት ካበቃ በኋላ እንደሆነ ምሳሌው ይጠቁማል። ደግሞም ስንዴው የሚያድግበት ወቅት ያበቃውና የመከር ወቅት የጀመረው በ1914 ነው።

13. ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላ ወዲያውኑ መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ እንደማይሾም በምሳሌ ያስረዳው እንዴት ነው?

13 የምናኑ ምሳሌ። (ሉቃስ 19:11-13ን አንብብ።) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው በ33 ዓ.ም. ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ በነበረበት ወቅት ነው። ከአድማጮቹ መካከል አንዳንዶቹ ኢየሩሳሌም እንደደረሱ መንግሥቱን የሚያቋቁም መስሏቸው ነበር። ይህን አስተሳሰባቸውን ለማስተካከልና መንግሥቱ የሚቋቋመው ከረጅም ጊዜ በኋላ መሆኑን ለማሳየት ኢየሱስ ራሱን “ንጉሣዊ ሥልጣኑን ተረክቦ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር” ከሄደ “አንድ መስፍን” ጋር አመሳስሎ ገልጿል። a በኢየሱስ ሁኔታ “ሩቅ አገር” የተባለው ሰማይ ነው፤ በዚያም የንግሥና ሥልጣኑን ከአባቱ ይረከባል። ይሁንና ኢየሱስ ወደ ሰማይ እንደተመለሰ ወዲያውኑ የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እንደማይሾም ያውቅ ነበር። ከዚህ ይልቅ የተወሰነው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ በአምላክ ቀኝ ተቀምጦ ይጠብቃል። የኋላ ኋላ ማየት እንደተቻለው መሲሑ ለበርካታ መቶ ዘመናት ሲጠብቅ ቆይቷል።—መዝ. 110:1, 2፤ ማቴ. 22:43, 44፤ ዕብ. 10:12, 13

የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው?

14. (ሀ) ኢየሱስ አራቱ ሐዋርያት ለጠየቁት ጥያቄ ምን መልስ ሰጥቷል? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት መፈጸሙ ስለ እሱ መገኘትና ስለ መንግሥቱ ምን ያስገነዝበናል?

14 ኢየሱስ ከመገደሉ ከጥቂት ቀናት በፊት ከሐዋርያቱ መካከል አራቱ “እስቲ ንገረን፣ እነዚህ ነገሮች የሚፈጸሙት መቼ ነው? የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር። (ማቴ. 24:3፤ ማር. 13:4) ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 24 እና 25 ላይ የሚገኘውን ዝርዝር ሐሳቦች የያዘ ትንቢት በመናገር ለጥያቄያቸው መልስ ሰጥቷል። ኢየሱስ እሱ ‘የሚገኝበትን’ ጊዜ የሚጠቁም ምልክት የሰጣቸው ሲሆን ይህ ምልክት በዓለም ዙሪያ የሚፈጸሙ ልዩ ልዩ ክስተቶችን ያቀፈ ነው። የእሱ መገኘት የሚጀምረው መንግሥቱ መግዛት በሚጀምርበት ጊዜ ሲሆን የእሱ መገኘት የሚያበቃው ደግሞ መንግሥቱ መላውን ምድር ሲገዛ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ከ1914 አንስቶ ፍጻሜውን እያገኘ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ አለን። b በመሆኑም በዚያ ዓመት፣ ኢየሱስ በሥልጣኑ ላይ የሚገኝበት ጊዜ ጀምሯል፤ የአምላክ መንግሥትም ተቋቁሟል።

15, 16. “ይህ ትውልድ” የሚለው አነጋገር እነማንን ያመለክታል?

15 ይሁንና የአምላክ መንግሥት የሚመጣው መቼ ነው? ኢየሱስ መንግሥቱ የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ለይቶ አልተናገረም። (ማቴ. 24:36) ሆኖም ይህ ጊዜ በጣም መቅረቡን በእርግጠኝነት እንድናምን የሚያስችል ሐሳብ ሰንዝሯል። ኢየሱስ መንግሥቱ የሚመጣው “ይህ ትውልድ” የትንቢታዊውን ምልክት ፍጻሜ ካየ በኋላ መሆኑን አመልክቷል። (ማቴዎስ 24:32-34ን አንብብ።) “ይህ ትውልድ” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው እነማንን ነው? ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ እስቲ በጥልቀት እንመርምር።

16 “ይህ ትውልድ።” ኢየሱስ ይህን ሲናገር በአእምሮው ይዞ የነበረው አማኝ ያልሆኑ ሰዎችን ነው? አይደለም። ያዳምጡት የነበሩት እነማን እንደነበሩ ተመልከት። ኢየሱስ ይህን ትንቢት የተናገረው “ለብቻቸው ወደ እሱ መጥተው” ለነበሩት ጥቂት ሐዋርያት ነበር። (ማቴ. 24:3) ሐዋርያቱ በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር። ደግሞም የጥቅሱን አውድ ልብ በል። ኢየሱስ ስለዚህ “ትውልድ” ከመናገሩ በፊት የሚከተለውን ተናግሯል፦ “እንግዲያው ይህን ምሳሌ ከበለስ ዛፍ ተማሩ፦ ቅርንጫፎቿ ሲለመልሙና ቅጠሎቿ ሲያቆጠቁጡ በጋ እንደቀረበ ታውቃላችሁ። በተመሳሳይ እናንተም እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስታዩ የሰው ልጅ ደጃፍ ላይ እንደ ደረሰ እርግጠኞች ሁኑ።” ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት ፍጻሜ የሚመለከቱትና ትርጉሙን ይኸውም ኢየሱስ “ደጃፍ ላይ እንደ ደረሰ” የሚገነዘቡት አማኝ ያልሆኑ ሰዎች ሳይሆኑ ቅቡዓን ተከታዮቹ ናቸው። ስለሆነም ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲናገር በአእምሮው ይዞ የነበረው ቅቡዓን ተከታዮቹን ነው።

17. “ትውልድ” እና “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” የሚሉት አባባሎች ምን ትርጉም አላቸው?

17 “እነዚህ ነገሮች ሁሉ እስኪፈጸሙ ድረስ . . . ፈጽሞ አያልፍም።” እነዚህ ቃላት ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ማግኘት የምንችለው “ትውልድ” እና “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” የሚሉት ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው ስናውቅ ነው። “ትውልድ” የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ የሚያመለክተው በተለያየ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ሆኖም በተመሳሳይ ጊዜ ላይ በሕይወት የኖሩ ሰዎችን ነው። የአንድ ትውልድ የጊዜ ርዝመት በጣም ረጅም አይደለም፤ ደግሞም ማብቂያ አለው። (ዘፀ. 1:6) “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” የሚለው አገላለጽ ከ1914 እስከ ‘ታላቁ መከራ’ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከናወኑትን ኢየሱስ በእሱ መገኘት ወቅት እንደሚፈጸሙ በትንቢት የተናገራቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል።—ማቴ. 24:21

18, 19. ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ሲል የተናገረውን ሐሳብ እንዴት ልንረዳው ይገባል? ምን ብለንስ መደምደም እንችላለን?

18 ታዲያ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” ብሎ ሲናገር ምን ማለቱ ነበር? ይህ ትውልድ፣ በተመሳሳይ ወቅት የኖሩ ሁለት የቅቡዓን ክርስቲያኖች ቡድኖችን ያቀፈ ነው፤ የመጀመሪያው ቡድን አባላት በ1914 ምልክቱ መፈጸም ሲጀምር የተመለከቱት ቅቡዓን ሲሆኑ የሁለተኛው ቡድን አባላት ደግሞ ከመጀመሪያው ቡድን ጋር ለተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት የኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ናቸው። ከሁለተኛው ቡድን አባላት መካከል ቢያንስ የተወሰኑት በሕይወት ቆይተው ታላቁ መከራ ሲጀምር ይመለከታሉ። የእነዚህ ሁለት ቡድኖች አባላት እንደ አንድ ትውልድ ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ እንዲህ ሊባል የሚችለው በመንፈስ ከተቀቡ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በተመሳሳይ ወቅት ላይ የኖሩ በመሆናቸው ነው። c

19 ታዲያ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን? ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ መገኘቱን የሚጠቁመው ምልክት በዓለም ዙሪያ በግልጽ እንደታየ እናውቃለን። እንዲሁም የዚህ “ትውልድ” ክፍል የሆኑት በሕይወት ያሉ ቅቡዓን በዕድሜ እየገፉ እንደሆኑ እየተመለከትን ነው። ይሁንና ታላቁ መከራ ከመጀመሩ በፊት ሁሉም ሞተው አያልቁም። እንግዲያው የአምላክ መንግሥት የሚመጣበትና መላዋን ምድር የሚገዛበት ጊዜ በጣም ቀርቧል ብለን መደምደም እንችላለን! ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን ጸሎት ፍጻሜውን ሲያገኝ መመልከት ምንኛ አስደሳች ይሆን!

20. (ሀ) በዚህ መጽሐፍ ላይ የሚብራራው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚብራራው ምንድን ነው?

20 ይሖዋ ራሱ በሰማይ ሆኖ ልጁን በተመለከተ “እሱን ስሙት” ሲል የሰጠውን መመሪያ ፈጽሞ መርሳት አይኖርብንም። እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይህን መለኮታዊ መመሪያ የማክበር ከፍተኛ ፍላጎት አለን። ኢየሱስ ስለ አምላክ መንግሥት የተናገረውንና ያስተማረውን ነገር በሙሉ በትኩረት እንከታተላለን። ይህ መንግሥት እስካሁን ምን እንዳከናወነ እና ወደፊት ደግሞ ምን እንደሚያከናውን የሚገልጸው ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ርዕሰ ጉዳይ በዚህ መጽሐፍ ላይ ይብራራል። በሚቀጥለው ምዕራፍ ላይ፣ በሰማይ ከተቋቋመው የአምላክ መንግሥት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙትን አስደናቂ ክንውኖች እንመረምራለን።

a ኢየሱስ የተናገረው ምሳሌ አድማጮቹ የታላቁ ሄሮድስ ልጅ የነበረውን አርኬላዎስን ሳያስታውሳቸው አይቀርም። ሄሮድስ ከመሞቱ በፊት አርኬላዎስን በይሁዳና በሌሎች አካባቢዎች ላይ አልጋ ወራሽ አድርጎ ሾሞት ነበር። ይሁንና አርኬላዎስ መግዛት ከመጀመሩ በፊት እስከ ሮም ድረስ ተጉዞ አውግስጦስ ቄሳር ሹመቱን እንዲያጸድቅለት ማድረግ ያስፈልገው ነበር።

c በ1914 የተከሰተውን “የምጥ ጣር መጀመሪያ” የተመለከቱትና በመጀመሪያው የቅቡዓን ቡድን ውስጥ የታቀፉት ክርስቲያኖች በሙሉ ሞተው ካለቁ በኋላ በመንፈስ የተቀባ ማንኛውም ክርስቲያን ኢየሱስ በጠቀሰው “ትውልድ” ውስጥ አይካተትም።—ማቴ. 24:8