በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 2

መንግሥቱ በሰማይ ተወለደ

መንግሥቱ በሰማይ ተወለደ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

አምላክ መንግሥቱ ለሚወለድበት ጊዜ ሕዝቡን አዘጋጀ

1, 2. በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቀው ክስተት ምንድን ነው? ሰዎች በዓይናቸው ያላዩት መሆኑ የማያስገርመውስ ለምንድን ነው?

 በታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያስከተሉ ክስተቶች በተከናወኑበት ወቅት መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? ብዙዎች እንዲህ ዓይነት ሐሳብ ወደ አእምሯቸው ይመጣል። እንዲህ ባለ ታሪካዊ ወቅት ኖረህ ቢሆን ኖሮ ለውጡን ያስከተሉትን ቁልፍ ክንውኖች በቀጥታ የማየት አጋጣሚ ይኖርህ ነበር? እንዲህ ዓይነቶቹን ክንውኖች የመመልከት አጋጣሚህ ጠባብ ሊሆን ይችላል። በታሪክ መጻሕፍት ላይ ሰፍረው የምናገኛቸው ለቀድሞ አገዛዞች መውደቅ ምክንያት የሆኑ ነገሮች አብዛኛውን ጊዜ ከሕዝብ እይታ የተሰወሩ ናቸው። በሌላ አባባል አብዛኛው ታሪካዊ ክስተት የሚፈጸመው ከመጋረጃ በስተጀርባ ይኸውም በቤተ መንግሥት፣ ዝግ ስብሰባ በሚካሄድበት ስፍራ ወይም በመንግሥት ቢሮዎች ውስጥ ነው። ሆኖም እንዲህ ያሉ ለውጦች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ይነካሉ።

2 በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ ስለማይታወቀው ክስተትስ ምን ማለት ይቻላል? ይህ ክስተት በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል። ይሁንና የተፈጸመው ከሰው እይታ ውጭ ነው። እየተናገርን ያለነው በሰማይ ስለተከናወነው የአምላክ መንግሥት መወለድ ነው፤ ይህ መንግሥት ከረጅም ጊዜ በፊት በትንቢት የተነገረለት መሲሐዊ መስተዳድር ሲሆን በቅርቡ መላውን የዓለም ሥርዓት ያጠፋል። (ዳንኤል 2:34, 35, 44, 45ን አንብብ።) ታዲያ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን የዚህን መንግሥት መወለድ ሰዎች ስላልተመለከቱ ይሖዋ ይህ ክንውን ለሰው ልጆች ሚስጥር እንዲሆን አድርጓል ብለን መደምደም ይኖርብናል? ወይስ ታማኝ ሕዝቡን ለዚህ ክንውን አስቀድሞ አዘጋጅቷል? እስቲ ጉዳዩን እንመርምር።

“መልእክተኛዬ . . . በፊቴ መንገድ ይጠርጋል”

3-5. (ሀ) ሚልክያስ 3:1 ላይ የተጠቀሰው “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ማን ነው? (ለ) “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” ወደ ቤተ መቅደሱ ከመምጣቱ በፊት ምን ይከናወናል?

3 ይሖዋ ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሕዝቡን ለመሲሐዊው መንግሥት መወለድ የማዘጋጀት ዓላማ ነበረው። ለምሳሌ ያህል፣ በሚልክያስ 3:1 ላይ ያለውን የሚከተለውን ትንቢት እንመልከት፦ “እነሆ፣ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ እሱም በፊቴ መንገድ ይጠርጋል። እናንተ የምትፈልጉት እውነተኛው ጌታ በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤ ደስ የምትሰኙበት የቃል ኪዳኑ መልእክተኛም ይመጣል።”

4 በጥቅሱ ላይ “ጌታ” ተብሎ የተጠራው ይሖዋ፣ በዘመናችን በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ምድራዊ አደባባይ የሚያገለግሉትን ለመመርመር የመጣው መቼ ነው? ትንቢቱ ይሖዋ የሚመጣው ‘ከቃል ኪዳኑ መልእክተኛ’ ጋር እንደሆነ ይገልጻል። እሱ ማን ነው? መሲሐዊ ንጉሥ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ ውጭ ማንም ሊሆን አይችልም! (ሉቃስ 1:68-73) አዲስ የተሾመ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን በምድር ላይ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች ይመረምራል፤ እንዲሁም ያጠራል።—1 ጴጥ. 4:17

5 ይሁንና በሚልክያስ 3:1 ላይ በመጀመሪያ የተገለጸው ሌላው “መልእክተኛ” ማን ነው? ይህ መልእክተኛ መሲሐዊው ንጉሥ ከመገኘቱ ከበርካታ ዓመታት በፊት ተልእኮውን ያከናውናል። ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ለመሲሐዊው ንጉሥ ‘መንገድ የጠረገ’ አለ?

6. የአምላክን ታማኝ ሕዝቦች ከፊታቸው ለሚጠብቋቸው ክንውኖች ለማዘጋጀት ቀድሞ በመምጣት ስለ ‘መልእክተኛው’ በትንቢት የተነገረውን ሚና የተወጣው ማን ነው?

6 ይህ መጽሐፍ ቀልብ የሚስበውን ዘመናዊ የይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ መሠረት በማድረግ እንዲህ ላሉ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። ይህ ታሪክ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ አስመሳይ ክርስቲያኖች በተንሰራፉበት መስክ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ያቀፈ አንድ አነስተኛ የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቡድን ብቅ እንዳለ ያሳያል። እነዚህ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ተብለው ይጠሩ ነበር። በመካከላቸው ሆነው አመራር ይሰጡ የነበሩት ቻርልስ ቴዝ ራስልና የቅርብ አጋሮቹ ለአምላክ ሕዝቦች መንፈሳዊ መመሪያ በመስጠትና ሕዝቡን ወደፊት ለሚፈጸሙት ክንውኖች በማዘጋጀት በትንቢት የተነገረለት “መልእክተኛ” ሆነው አገልግለዋል። ይህ “መልእክተኛ” ኃላፊነቱን የተወጣባቸውን አራት መንገዶች እንመልከት።

በእውነት ማምለክ

7, 8. (ሀ) ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ውሸት መሆኑን በ1800ዎቹ ዓመታት ማጋለጥ የጀመሩት እነማን ናቸው? (ለ) ቻርልስ ቴዝ ራስልና የቅርብ አጋሮቹ የትኞቹን ሌሎች የሐሰት ትምህርቶች አጋልጠዋል?

7 እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጸሎት እየታገዙ ያጠኑ ነበር፤ ግልጽ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች በተመለከተ የጋራ ስምምነት ላይ ይደርሱ እንዲሁም አንድ ላይ አጠናቅረው በጽሑፍ እንዲወጡ ያደርጉ ነበር። ለበርካታ መቶ ዘመናት ሕዝበ ክርስትና በመንፈሳዊ ጨለማ ተውጣ ነበር፤ ብዙዎቹ ትምህርቶቿ ከአረማውያን እምነት የመነጩ ነበሩ። ለዚህ ዓይነተኛ ምሳሌ የሚሆነው ነፍስ አትሞትም የሚለው ትምህርት ነው። ይሁንና በ1800ዎቹ ዓመታት፣ ቅን ልብ ያላቸው ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ ትምህርት ላይ ጥልቅ ምርምር ካደረጉ በኋላ የአምላክ ቃል ድጋፍ እንደሌለው ተገነዘቡ። ሄንሪ ግሩ፣ ጆርጅ ስቴትሰን እና ጆርጅ ስቶርዝ ይህ ሰይጣናዊ ትምህርት ውሸት መሆኑን በጽሑፍም ሆነ በንግግር በድፍረት አጋልጠዋል። a እነሱ ያደረጉት ጥረት በቻርልስ ቴዝ ራስል እና በቅርብ አጋሮቹ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።

8 አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያቀፈው ይህ ቡድን፣ ነፍስ አትሞትም ከሚለው ትምህርት ጋር የተያያዙ ሌሎች ትምህርቶችም ግራ የሚያጋቡና ውሸት መሆናቸውን ተረድቶ ነበር፤ ከእነዚህ መካከል ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ ወይም አምላክ የክፉዎችን ነፍስ በገሃነም እሳት ለዘላለም ያሠቃያል የሚሉት ትምህርቶች ይገኙበታል። ራስልና የቅርብ አጋሮቹ በተለያዩ መጻሕፍት፣ ቡክሌቶች፣ ትራክቶች እንዲሁም ጋዜጦች ላይ በሚወጡ ርዕሶችና ስብከቶች አማካኝነት እነዚህን ውሸቶች በድፍረት አጋልጠዋል።

9. የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የሥላሴን መሠረተ ትምህርት ውሸት መሆኑን ያጋለጠው እንዴት ነው?

9 በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ብዙዎች ትልቅ ቦታ የሚሰጡት የሥላሴ ትምህርት ውሸት መሆኑን አጋለጡ። የ1887 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ሐሳብ ሰንዝሮ ነበር፦ “ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋና ጌታችን ኢየሱስ ሁለት የተለያዩ አካላት እንደሆኑ በግልጽ የሚያመለክቱ ከመሆኑም ሌላ በመካከላቸው ያለውን ዝምድና በተመለከተ የማያሻማ መረጃ ይዘዋል።” አክሎም “ሦስትም አንድም፣ አንድም ሦስትም የሆነ አምላክ እንዳለ የሚገልጸው የሥላሴ ትምህርት ይህን ያህል ትልቅ ቦታና ሰፊ ተቀባይነት ሊያገኝ መቻሉ” የሚያስገርም እንደሆነ ተናግሯል። “ይሁንና ይህ መሆኑ ቤተ ክርስቲያን፣ ጠላት በተሳሳተ ትምህርት ተብትቦ ሲይዛት ምን ያህል አንቀላፍታ እንደነበር ያሳያል።”

10. መጠበቂያ ግንብ 1914 ልዩ ዓመት እንደሆነ የጠቆመው እንዴት ነው?

10 የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ የተሰኘው የመጽሔቱ ሙሉ ስም እንደሚጠቁመው ይህ መጽሔት የክርስቶስን መገኘት አስመልክቶ ለተነገሩ ትንቢቶች ከፍተኛ ትኩረት ይሰጥ ነበር። የመጽሔቱ አዘጋጆች የነበሩት ታማኝ ቅቡዓን፣ ዳንኤል ስለ “ሰባት ዘመናት” የተናገረው ትንቢት አምላክ ከመሲሐዊው መንግሥት ጋር በተያያዘ ያሉት ዓላማዎች ከሚፈጸሙበት ጊዜ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው ተገንዝበዋል። ገና በ1870ዎቹ ዓመታት፣ እነዚህ ሰባት ዘመናት የሚያበቁት በ1914 እንደሆነ አመልክተው ነበር። (ዳን. 4:25፤ ሉቃስ 21:24) በዚያን ዘመን የነበሩት ወንድሞቻችን ስለዚህ ልዩ ዓመት የተሟላ ግንዛቤ ባይኖራቸውም እንኳ ያወቁትን ነገር በስፋት አውጀዋል፤ እነሱ ያከናወኑት ሥራ ያስገኘው ውጤት እስከ ዘመናችን ድረስ ዘልቋል።

11, 12. (ሀ) ወንድም ራስል ላስተማረው ትምህርት መመስገን ያለበት ማን እንደሆነ ገልጿል? (ለ) ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ራስልና አጋሮቹ ያከናወኑት ሥራ ምን ጥቅም አስገኝቷል?

11 ራስልም ሆነ ታማኝ አጋሮቹ እነዚህን ወሳኝ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶች በመረዳታቸውና ለሌሎች በማሳወቃቸው ሊመሰገኑ የሚገባቸው እነሱ እንደሆኑ አልተሰማቸውም። ራስል ከእሱ በፊት ለነበሩት ሰዎች ትልቅ ግምት ነበረው። ይሁንና አገልጋዮቹ ማወቅ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በተገቢው ጊዜ ማወቅ እንዲችሉ በማድረግ ሕዝቡን የሚያስተምረው ይሖዋ አምላክ በመሆኑ ከማንም በላይ ሊመሰገን እንደሚገባው ገልጿል። በእርግጥም ይሖዋ እውነቱን ከውሸቱ አበጥረው እንዲያወጡ በመርዳት የራስልንና የአጋሮቹን ጥረት ባርኳል። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በእነሱና በሕዝበ ክርስትና መካከል ያለው ክፍተት ይበልጥ እየሰፋና ልዩነታቸውም እየጎላ መጥቷል።

ወንድም ራስልና የቅርብ አጋሮቹ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ጥብቅና ቆመዋል

12 እነዚህ ታማኝ ወንዶች ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ለእውነት ጥብቅና በመቆም ያከናወኑት ሥራ እጅግ አስደናቂ ነው! የኅዳር 1, 1917 የጽዮን መጠበቂያ ግንብና የክርስቶስ መገኘት አዋጅ ነጋሪ ከዚያ በፊት በነበሩት ዓመታት የተከናወኑትን ነገሮች አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የገሃነም እሳትና ሌሎች የሐሰት ትምህርቶች ካሳደሩባቸው ፍርሃት ተላቀዋል፤ . . . ከአርባ ከሚበልጡ ዓመታት በፊት የጀመረው የእውነት ማዕበል ያለማቋረጥ እየጨመረ ሲሆን መላዋን ምድር እስኪሸፍን ድረስ መጨመሩን ይቀጥላል፤ ተቃዋሚዎች እውነት በመላው ምድር ላይ እንዳይስፋፋ ለማገድ የሚያደርጉት ጥረት በትልቅ ውቅያኖስ ላይ የተነሱ ማዕበሎችን በመጥረጊያ ገፍቶ ለመመለስ የመሞከር ያህል ነው።”

13, 14. (ሀ) ‘መልእክተኛው’ መንገዱን ለመሲሐዊው ንጉሥ በማዘጋጀት ረገድ ምን አስተዋጽኦ አበርክቷል? (ለ) ከአንድ መቶ ዓመት በፊት ከነበሩት ወንድሞቻችን ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

13 እስቲ አስበው፦ የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስን ከአባቱ ከይሖዋ ለይተው ማወቅ ባይችሉ ኖሮ የክርስቶስ መገኘት የሚጀምርበትን ጊዜ ተዘጋጅተው መጠበቅ ይችሉ ነበር? በፍጹም! በተጨማሪም ያለመሞት ባሕርይ የክርስቶስን ፈለግ ለሚከተሉ የተወሰኑ ሰዎች ብቻ የሚሰጥ ውድ ስጦታ ሳይሆን ለሁሉም ሰው የሚታደል እንደሆነ አድርገው ቢያስቡ ኖሮ ዝግጁ ሆነው አይጠብቁም ነበር! አምላክ ሰዎችን ያለ ምንም ፋታ በገሃነም እሳት ለዘላለም የሚያቃጥል እንደሆነ አድርገው ቢያስቡ ኖሮም ዝግጁ ሆነው ሊጠብቁ አይችሉም ነበር! ‘መልእክተኛው’ ለመሲሐዊው ንጉሥ መንገድ እንዳዘጋጀ ምንም ጥርጥር የለውም!

14 ዛሬ የምንኖረውን ክርስቲያኖች በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ከመቶ ዓመት በፊት ከነበሩት ወንድሞቻችን ምን መማር እንችላለን? እኛም በተመሳሳይ የአምላክን ቃል በከፍተኛ ጉጉት ማንበብና ማጥናት ይኖርብናል። (ዮሐ. 17:3) ፍቅረ ነዋይ የተጠናወተው ይህ ዓለም በመንፈሳዊ ሁኔታ እየጫጨ ሲሄድ እኛ ግን ለመንፈሳዊ ምግብ ያለን ፍላጎት እየጨመረ እንዲሄድ እንመኛለን።1 ጢሞቴዎስ 4:15ን አንብብ።

“ሕዝቤ ሆይ . . . ከእሷ ውጡ”

15. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የኋላ ኋላ ምን ተገንዝበዋል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

15 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ በዓለም ካሉ አብያተ ክርስቲያናት መለየት አስፈላጊ መሆኑን ያስተምሩ ነበር። በ1879 መጠበቂያ ግንብ “የባቢሎን ቤተ ክርስቲያን” የሚል መግለጫ ተጠቅሞ ነበር። ይህን ሲል ጵጵስናን ማመልከቱ ይሆን? ወይስ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን? ፕሮቴስታንቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ውስጥ የተገለጸችው ባቢሎን የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን እንደምታመለክት ይናገሩ ነበር። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዘመናዊዋ “ባቢሎን” የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናትን በሙሉ እንደምታካትት እየተገነዘቡ መጡ። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሁሉም ከላይ እንዳየናቸው ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር። b የባቢሎን አብያተ ክርስቲያናት አባላት የሆኑ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሐሳብ ከጊዜ በኋላ በጽሑፎቻችን ላይ በግልጽ መውጣት ጀመረ።

16, 17. (ሀ) ሚሌኒያል ዶውን ጥራዝ 3 እና መጠበቂያ ግንብ ሰዎች ከሐሰት ሃይማኖት እንዲወጡ ማሳሰቢያ የሰጡት እንዴት ነው? (ለ) ቀደም ሲል የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ኃይል እንዳይኖራቸው ተጽዕኖ ያሳደረው ምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።)

16 ለምሳሌ ያህል፣ በ1891 የወጣው ሚሌኒያል ዶውን ጥራዝ 3 አምላክ ዘመናዊዋን ባቢሎን እንዳልተቀበላት ከገለጸ በኋላ “መላው ሥርዓት ይኸውም የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ተቀባይነት አጥተዋል” የሚል ሐሳብ ሰንዝሯል። አክሎም “ከሐሰት መሠረተ ትምህርቶቿና ልማዶቿ ጋር የማይስማሙ ሁሉ ከአሁን ጀምሮ ከእሷ እንዲለዩ ጥሪ እንደቀረበላቸው” ገልጿል።

17 የጥር 1900 መጠበቂያ ግንብ ከሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባልነት ስማቸውን ላላሰረዙና “ሙሉ በሙሉ ድጋፍ የምሰጠው ለእውነት ነው፤ ደግሞም በሌሎች ስብሰባዎች ላይ የምገኘው ከስንት አንድ ጊዜ ነው” ብለው ለድርጊታቸው ሰበብ ለሚያቀርቡ ግለሰቦች ምክር ሰጥቶ ነበር። ይኸው መጽሔት የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንስቷል፦ “ይሁንና ከባቢሎን ሙሉ በሙሉ ሳይወጡ እዚያም እዚህም መሆን ትክክል ነው? . . . [አምላክ] የሚፈልገው እንዲህ ያለ ታዛዥነት ነው? ይህ አምላክን ያስደስተዋል? በእሱስ ዘንድ ተቀባይነት አለው? በፍጹም። [አንድ ግለሰብ] የአንድ ሃይማኖት አባል ሲሆን፣ ከዚህ ሃይማኖት ጋር በይፋ ቃል ኪዳን የገባ በመሆኑ እምነቱን መተዉን ወይም ከአባልነት መሰረዙን በይፋ እስኪያሳውቅ ድረስ የቃል ኪዳኑን ግዴታዎች በሙሉ በታማኝነት አክብሮ መኖር ይጠበቅበታል።” ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይህ መመሪያ እየተጠናከረ መጣ። c የይሖዋ አገልጋዮች ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ያላቸውን ማንኛውም ግንኙነት ማቋረጥ ይጠበቅባቸው ነበር።

18. እውነተኛ ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን መውጣታቸው አስፈላጊ የነበረው ለምንድን ነው?

18 እውነተኛ ክርስቲያኖች ከታላቂቱ ባቢሎን እንዲወጡ እንዲህ ያሉ ማስጠንቀቂያዎች በየጊዜው ባይሰጡ ኖሮ አዲስ የተሾመው ንጉሥ ክርስቶስ በምድር ላይ ዝግጁ የሆነ የቅቡዓን አገልጋዮች ቡድን ይኖረው ነበር? እንደማይኖረው የታወቀ ነው፤ ምክንያቱም ይሖዋን “በመንፈስና በእውነት” ማምለክ የሚችሉት ከባቢሎን መዳፍ ነፃ የወጡ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። (ዮሐ. 4:24) በዛሬው ጊዜ የምንኖረው እኛስ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ንክኪ እንዳይኖረን ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል? “ሕዝቤ ሆይ . . . ከእሷ ውጡ” የሚለውን ትእዛዝ ማክበራችንን እንቀጥል።ራእይ 18:4ን አንብብ።

ለአምልኮ መሰብሰብ

19, 20. መጠበቂያ ግንብ የአምላክ ሕዝቦች ለአምልኮ እንዲሰበሰቡ ያበረታታው እንዴት ነበር?

19 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ሁኔታዎች የሚፈቅዱ እስከሆነ ድረስ ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ እንዳለባቸው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን አስተምረዋል። እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት ሃይማኖት መውጣታቸው ብቻ በቂ አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ በንጹሕ አምልኮ መካፈላቸው አስፈላጊ ነው። መጠበቂያ ግንብ ከመጀመሪያዎቹ እትሞች አንስቶ አንባቢዎቹን ለአምልኮ አንድ ላይ እንዲሰበሰቡ ሲያበረታታ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ወንድም ራስል ንግግር ለማቅረብ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዞ ከተመለሰ በኋላ በሐምሌ 1880 ባቀረበው ሪፖርት ላይ ስብሰባዎቹ ምን ያህል አበረታች እንደነበሩ ተናግሯል። ከዚያም አንባቢዎቹ እያደረጉ ስላለው እድገት የሚገልጽ ሪፖርት የያዘ ፖስት ካርድ እንዲልኩ ማበረታቻ ሰጠ፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ በመጽሔቱ ላይ ታትመው ይወጡ ነበር። ዓላማው ምን ነበር? “ጌታ ምን ያህል እየባረካችሁ እንደሆነ . . . ሁላችንም ማወቅ እንፈልጋለን፤ እንደ እናንተው ክቡር እምነት ካላቸው ጋር መሰብሰብ መቀጠል አለመቀጠላችሁን ማወቅ እንሻለን።”

ቻርልስ ራስል በኮፐንሃገን፣ ዴንማርክ ቀደምት ከሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር፣ 1909

20 በ1882 መጠበቂያ ግንብ ላይ “አንድ ላይ መሰብሰብ” የሚል ርዕስ ወጥቶ ነበር። ይህ ርዕስ ክርስቲያኖች “እርስ በርስ ለመማማር፣ ለመተናነጽና ለመበረታታት” እንዲሰበሰቡ ማበረታቻ ሰጥቷል። መጽሔቱ ይህን ሐሳብ ይዟል፦ “ከእናንተ መካከል የተማረ ወይም ልዩ ተሰጥኦ ያለው ሰው መኖር አለመኖሩ የሚያመጣው ለውጥ የለም። እያንዳንዳችሁ የራሳችሁን መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወረቀትና እርሳስ እንዲሁም እንደ ጥቅስ ማውጫ (ኮንኮርዳንስ) ያሉ . . . ማግኘት የምትችሏቸውን መሣሪያዎች ሁሉ ይዛችሁ ሂዱ። አንድ ርዕሰ ጉዳይ ምረጡ፤ ርዕሰ ጉዳዩን መረዳት እንድትችሉ የመንፈስን አመራር ለማግኘት ጸልዩ፤ ከዚያም አንብቡ፣ በጉዳዩ ላይ አስቡበት እንዲሁም ጥቅስን ከጥቅስ ጋር አወዳድሩ፤ እንዲህ ካደረጋችሁ መንፈስ ቅዱስ እውነትን እንድታገኙ እንደሚረዳችሁ ጥርጥር የለውም።”

21. በአሌጌኒ፣ ፔንስልቬንያ የነበረው ጉባኤ ከስብሰባዎችና ከእረኝነት ጋር በተያያዘ ምን አርዓያ ትቷል?

21 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ዋና መሥሪያ ቤት በአሌጌኒ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ይገኝ ነበር። በዚህ ስፍራ የነበሩ ክርስቲያኖች በዕብራውያን 10:24, 25 ላይ በሚገኘው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምክር መሠረት አንድ ላይ በመሰብሰብ ግሩም ምሳሌ ትተዋል። (ጥቅሱን አንብብ።) ቻርልስ ኬፐን የተባሉ አረጋዊ ወንድም ልጅ ሳሉ በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ይገኙ እንደነበር በማስታወስ ከብዙ ዓመታት በኋላ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “በማኅበሩ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ግድግዳ ላይ የተጻፈው ጥቅስ አሁንም ትዝ ይለኛል። ‘ጌታችሁ አንድ ይኸውም ክርስቶስ ነው፤ እናንተ ሁላችሁ ወንድማማቾች ናችሁ።’ ይህ ጥቅስ መቼም ቢሆን ከአእምሮዬ ጠፍቶ አያውቅም፤ በይሖዋ ሕዝብ መካከል ቀሳውስት፣ ምዕመናን የሚል ልዩነት የለም።” (ማቴ. 23:8) በተጨማሪም ወንድም ኬፐን የሚያነቃቃ መንፈሳዊ ምግብ የሚቀርብባቸውን ስብሰባዎች፣ የሚያገኙትን ሞቅ ያለ ማበረታቻና ወንድም ራስል ለእያንዳንዱ የጉባኤው አባል በግለሰብ ደረጃ እረኝነት ለማድረግ የሚያደርገውን ትጋት የተሞላበት ጥረት በማስታወስ ተናግረዋል።

22. በታማኝነት ይመላለሱ የነበሩት ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለተሰጣቸው ማበረታቻ ምን ምላሽ ሰጡ? እኛስ ከእነሱ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

22 በታማኝነት ይመላለሱ የነበሩት ክርስቲያኖች ይህን ምሳሌ የተከተሉ ከመሆኑም ሌላ የተሰጣቸውን መመሪያ ተግባራዊ አድርገዋል። እንደ ኦሃዮና ሚሺገን ባሉ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ከዚያም በመላው ሰሜን አሜሪካና በሌሎች አገሮች ጉባኤዎች ተቋቋሙ። እስቲ አስበው፦ በታማኝነት እየተመላለሱ የነበሩ ሰዎች ለአምልኮ አንድ ላይ የመሰብሰብን አስፈላጊነት በተመለከተ በመንፈስ መሪነት የተሰጠውን ምክር እንዲታዘዙ ሥልጠና ባያገኙ ኖሮ ለክርስቶስ መገኘት ዝግጁ ይሆኑ ነበር? በፍጹም! ስለ እኛስ ምን ማለት ይቻላል? አንድ ላይ ሆነን ለማምለክና እርስ በርስ በመንፈሳዊ ለመበረታታት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በሙሉ በመጠቀም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል።

በቅንዓት መስበክ

23. መጠበቂያ ግንብ በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ እውነትን መስበክ እንዳለባቸው በግልጽ ያመለከተው እንዴት ነው?

23 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች በሙሉ እውነትን መስበክ እንዳለባቸው ያስተምሩ ነበር። በ1885 የወጣ መጠበቂያ ግንብ “እያንዳንዱ በመንፈስ የተቀባ ክርስቲያን ለመስበክ እንደተቀባ (ኢሳ. 61:1) ይኸውም ለአገልግሎት እንደተጠራ መርሳት አይኖርብንም” ብሏል። በ1888 የወጣ እትም ደግሞ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ይዞ ነበር፦ “ተልእኳችን ግልጽ ነው፤ . . . ይህን ቸል የምንልና ሰበብ አስባብ የምንደረድር ከሆነ ለተጠራንበት ከፍ ያለ መብት የማንበቃ ዳተኛ አገልጋዮች መሆናችንን እናሳያለን።”

24, 25. (ሀ) ራስልና የቅርብ አጋሮቹ ምሥራቹ እንዲሰበክ ከማበረታታት ባለፈ ምን አድርገዋል? (ለ) አንድ ኮልፖርተር መኪና እንደ ልብ ባልነበረበት ዘመን ያከናውኑ የነበረውን አገልግሎት የገለጹት እንዴት ነው?

24 ወንድም ራስልና የቅርብ አጋሮቹ፣ ምሥራቹ እንዲሰበክ በማበረታታት ብቻ አልተወሰኑም። ከዚህ ይልቅ ባይብል ስቱደንትስ ትራክትስ (ከጊዜ በኋላ ኦልድ ቲኦሎጂ ኳርተርሊ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል) የተባሉ ትራክቶችም ማዘጋጀት ጀመሩ። የመጠበቂያ ግንብ አንባቢዎች እነዚህን ትራክቶች ወስደው ለሕዝብ ያለ ክፍያ ያሰራጩ ነበር።

‘በሕይወቴ ውስጥ ለስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው

25 ሙሉ ጊዜያቸውን በአገልግሎት የሚያሳልፉ ሰባኪዎች ኮልፖርተር ተብለው ይጠሩ ነበር። ከእነዚህ መካከል ቀደም ሲል የተጠቀሱት ቻርልስ ኬፐን ይገኙበታል። ወንድም ኬፐን በዚያን ጊዜ የነበረውን ሁኔታ በማስታወስ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል፦ “የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የጂኦሎጂ ጥናት ያዘጋጀውን ካርታ በመጠቀም በፔንስልቬንያ የሚገኘውን የአገልግሎት ክልሌን እሸፍን ነበር። እነዚህ ካርታዎች ሁሉንም ጎዳናዎች የሚያሳዩ በመሆኑ በእያንዳንዱ ግዛት ወደሚገኙት አካባቢዎች በሙሉ በእግር ለመሄድ ያስችላሉ። አንዳንድ ጊዜ፣ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት በሚል ርዕስ በተከታታይ የወጣውን መጽሐፍ ትእዛዝ እየሰበሰብኩ ገጠር ውስጥ ለሦስት ቀናት ከተጓዝኩ በኋላ ፈረስና ጋሪ ተከራይቼ ጽሑፎቹን አደርስ ነበር። ብዙውን ጊዜ ለማረፍ በምገደድባቸው ቦታዎች ከገበሬዎች ጋር አድር ነበር። በወቅቱ መኪና እንደ ልብ የሚገኝ ነገር አልነበረም።”

አንድ ኮልፖርተር። ሠረገላው ላይ የተሳለውን “የዘመናት ሰንጠረዥ” ተመልከት

26. (ሀ) የአምላክ ሕዝቦች የክርስቶስን አገዛዝ ዝግጁ ሆነው ለመጠበቅ በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው? (ለ) ራሳችንን ምን ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው?

26 በዚያን ዘመን ምሥራቹን ለማዳረስ የሚደረገው ጥረት ድፍረትና ቅንዓት ይጠይቅ ነበር። እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለ ስብከቱ ሥራ አስፈላጊነት ትምህርት ባይሰጣቸው ኖሮ የክርስቶስን አገዛዝ ተዘጋጅተው መጠበቅ ይችሉ ነበር? በፍጹም! ደግሞም ይህ ሥራ የክርስቶስን መገኘት የሚጠቁም ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው የምልክቱ ገጽታ ነው። (ማቴ. 24:14) የአምላክ ሕዝቦች ይህ ሕይወት አድን ሥራ በሕይወታቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲይዝ ዝግጁ ሆነው መገኘት አስፈልጓቸው ነበር። እኛም ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ ‘በሕይወቴ ውስጥ ለስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ እሰጣለሁ? በዚህ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ መሥዋዕት እከፍላለሁ?’

የአምላክ መንግሥት ተወለደ!

27, 28. ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ የተመለከተው ነገር ምንድን ነው? ሰይጣንና አጋንንቱ የአምላክ መንግሥት ሲወለድ ምን አደረጉ?

27 በመጨረሻም ታሪካዊው ዓመት 1914 ደረሰ። በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ እንደተገለጸው በሰማይ የተፈጸሙትን አስደናቂ ክንውኖች በዓይን የተመለከተ ሰው የለም። ይሁንና ሐዋርያው ዮሐንስ ሁኔታውን በምሳሌያዊ መንገድ የሚገልጽ ራእይ ተገልጦለት ነበር። ዮሐንስ በሰማይ “ታላቅ ምልክት” ሲመለከት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። የአምላክ “ሴት” ይኸውም በሰማይ የሚገኙ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈችው ድርጅት ፀነሰች፤ ከዚያም ወንድ ልጅ ወለደች። በምሳሌያዊ ሁኔታ የተገለጸው ይህ ልጅ በቅርቡ “ብሔራትን ሁሉ በብረት በትር” እንደሚገዛ ተነግሯል። ሆኖም ልጁ በተወለደ ጊዜ “ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።” በሰማይ አንድ ታላቅ ድምፅ እንዲህ አለ፦ “አሁን የአምላካችን ማዳን፣ ኃይልና መንግሥት እንዲሁም የእሱ መሲሕ ሥልጣን ሆኗል።”—ራእይ 12:1, 5, 10

28 ዮሐንስ የመሲሐዊውን መንግሥት መወለድ በራእይ እንደተመለከተ ግልጽ ነው። ይህ በእርግጥም ታላቅ ክንውን ነው፤ ይሁንና በዚህ ያልተደሰቱ ወገኖች አሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ፣ በሚካኤል ወይም በክርስቶስ አመራር ሥር ካሉ ታማኝ መላእክት ጋር ተዋጉ። ውጤቱስ ምን ሆነ? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ታላቁ ዘንዶ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ።”—ራእይ 12:7, 9

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ክርስቶስ በማይታይ ሁኔታ መገኘቱን የሚጠቁመውን ምልክት በ1914 ማስተዋል ጀምረው ነበር

29, 30. የመሲሐዊውን መንግሥት መወለድ ተከትሎ (ሀ) በምድር (ለ) በሰማይ፣ ሁኔታዎች የተለወጡት እንዴት ነው?

29 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች 1914 ከመድረሱ ከረጅም ጊዜ በፊት፣ ልዩ በሆነው በዚህ ዓመት የመከራ ወቅት እንደሚጀምር ተናግረው ነበር። ይሁንና እነሱም ቢሆኑ እንኳ ይህ ትንቢት ምን ያህል በትክክል እንደሚፈጸም ማወቅ አይችሉም ነበር። ሰይጣን ከዚያ ዓመት በኋላ በሰብዓዊው ኅብረተሰብ ላይ ከበፊቱ የበለጠ ተጽዕኖ ማሳደር እንደሚጀምር ዮሐንስ የተመለከተው ራእይ ጠቁሟል፦ “ምድርና ባሕር ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” (ራእይ 12:12) በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት የፈነዳ ሲሆን ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚጠቁም ምልክት በዓለም ዙሪያ መታየት ጀመረ። የዚህ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀናት’ ጀምረው ነበር።—2 ጢሞ. 3:1

30 በሰማይ ግን ደስታ ሰፈነ። ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከዚያ ተባርረዋል። ዮሐንስ “ስለዚህ እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ!” ሲል ዘግቧል። (ራእይ 12:12) ሰማያት ከጸዱና ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ መሲሐዊው መንግሥት በምድር ላይ ለሚገኙት የአምላክ ሕዝቦች ሲል እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጀ። የሚወስደው እርምጃ ምንድን ነው? በዚህ ምዕራፍ መጀመሪያ ላይ እንደተመለከትነው ክርስቶስ “የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ” እንደመሆኑ መጠን በቅድሚያ በምድር ላይ የሚገኙትን የአምላክ አገልጋዮች ያጠራል። ይህ ምን ማለት ነው?

የፈተና ወቅት

31. ሚልክያስ የማጥራት ሥራ ስለሚከናወንበት ወቅት ምን ትንቢት ተናግሮ ነበር? ትንቢቱ ፍጻሜ ማግኘት የጀመረውስ እንዴት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

31 ሚልክያስ የማጥራቱ ሥራ ቀላል እንደማይሆን በትንቢት ተናግሯል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እሱ የሚመጣበትን ቀን ሊቋቋም የሚችል ማን ነው? እሱ በሚገለጥበት ጊዜስ ማን ሊቆም ይችላል? እሱ እንደ አንጥረኛ እሳት፣ እንደ ልብስ አጣቢም እንዶድ ይሆናልና።” (ሚል. 3:2) ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል! ከ1914 አንስቶ በምድር የነበሩት የአምላክ ሕዝቦች የማያባራ ፈተናና መከራ አጋጥሟቸዋል። አንደኛው የዓለም ጦርነት በተፋፋመበት ወቅት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ኃይለኛ ስደት የገጠማቸው ከመሆኑም በላይ ለእስር ተዳረጉ። d

32. ከ1916 በኋላ ድርጅቱ ውስጥ ለውስጥ የታመሰው እንዴት ነው?

32 ድርጅቱም፣ ውስጥ ለውስጥ ታምሶ ነበር። በ1916 ወንድም ራስል ገና በ64 ዓመቱ ሞተ፤ በዚህ ጊዜ በርካታ የአምላክ ሕዝቦች በድንጋጤ ተዋጡ። የእሱ ሞት አንዳንዶች ምሳሌ ተደርጎ በሚታይ አንድ ግለሰብ ላይ ከሚገባው በላይ ትኩረት አድርገው እንደነበር አሳይቷል። ወንድም ራስል እንዲህ ዓይነት ልዩ አክብሮት የማግኘት ፍላጎት ያልነበረው ቢሆንም ለእሱ አምልኮ አከል ክብር ሰጥተውት ነበር። ብዙዎች እውነት ደረጃ በደረጃ መገለጡ እሱ ከሞተ በኋላ እንዳከተመ የተሰማቸው ሲሆን አንዳንዶች ደግሞ በቀጣይነት ሥራውን ለማስኬድ የሚደረጉ ጥረቶችን አምርረው ተቃውመዋል። ይህ አመለካከት ድርጅቱ እንዲከፋፈል ያደረገ ክህደት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

33. የአምላክ ሕዝቦች የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ ፈተና የሆነባቸው እንዴት ነው?

33 ሌላው ፈተና ደግሞ የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም መቅረቱ ነበር። መጠበቂያ ግንብ በ1914 የአሕዛብ ዘመናት እንደሚፈጸሙ በትክክል የጠቆመ ቢሆንም ወንድሞች በዚህ ዓመት ምን እንደሚከሰት ገና አልተረዱም ነበር። (ሉቃስ 21:24) በ1914 ክርስቶስ የተቀቡትን የሙሽራዋ አባላት ከእሱ ጋር እንዲገዙ ወደ ሰማይ እንደሚወስዳቸው ጠብቀው ነበር። ይሁንና የጠበቁት ነገር ሳይፈጸም ቀረ። በ1917 መገባደጃ ላይ መጠበቂያ ግንብ 40 ዓመት የሚፈጀው የመከር ወቅት በ1918 የጸደይ ወራት እንደሚያበቃ አስታውቆ ነበር። ሆኖም የስብከቱ ሥራ አልተጠናቀቀም። ይህ ዓመት ካለፈም በኋላ ሥራው እየተስፋፋ ሄደ። መጽሔቱ የመከሩ ጊዜ በእርግጥ ማብቃቱን፣ የቃርሚያ ወቅት ግን ገና እንደሚቀር ጠቁሞ ነበር። እንደዚያም ሆኖ ብዙዎች ያሰቡት ነገር ሳይፈጸም በመቅረቱ ይሖዋን ማገልገላቸው አቆሙ።

34. በ1918 ምን አስደንጋጭ ፈተና ተከስቶ ነበር? ሕዝበ ክርስትና የአምላክ ሕዝቦች እንዳከተመላቸው ሆኖ የተሰማትስ ለምንድን ነው?

34 በ1918 አስደንጋጭ ፈተና አጋጠማቸው። የአምላክን ሕዝቦች ግንባር ቀደም ሆኖ ይመራ የነበረውን ቻርልስ ቴዝ ራስልን የተካው ጆሴፍ ፍራንክሊን ራዘርፎርድ ኃላፊነት ከነበራቸው ሌሎች ሰባት ወንድሞች ጋር ታሰረ። ፍትሕ በጎደለው ሁኔታ የብዙ ዓመት እስር ተፈርዶባቸው በአትላንታ፣ ጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ወደሚገኘው የፌዴራሉ ወህኒ ቤት ወረዱ። የአምላክ ሕዝቦች ያከናውኑት የነበረው ሥራ ለጊዜው ሙሉ በሙሉ የቆመ ያህል ሆኖ ነበር። ብዙዎቹ የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት በጣም ተደሰቱ። “መሪዎቹ” በመታሰራቸው፣ በብሩክሊን የሚገኘው ዋናው መሥሪያ ቤት በመዘጋቱና በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ በስብከቱ ሥራ ላይ ጥቃት በመሰንዘሩ እንደ መቅሰፍት የሆኑባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች “እንደሞቱ” በሌላ አባባል ስጋት መሆናቸው እንዳከተመ ተሰማቸው። (ራእይ 11:3, 7-10) ምንኛ ተሳስተው ነበር!

መልሰው አንሰራሩ!

35. ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ መከራ እንዲደርስባቸው የፈቀደው ለምንድን ነው? እነሱን ለመርዳትስ ምን እርምጃ ወስዷል?

35 የእውነት ጠላቶች፣ ኢየሱስ በተከታዮቹ ላይ እንዲህ ያለ መከራ እንዲደርስ የፈቀደው ይሖዋ “ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ” አንጥረኛ ሆኖ ስለተቀመጠ መሆኑን አልተገነዘቡም ነበር። (ሚል. 3:3) ይሖዋና ኢየሱስ፣ ታማኝ የሆኑት አገልጋዮች በእሳት በተመሰሉት ፈተናዎች በማለፍ ነጽተውና ጠርተው እንደሚወጡ እንዲሁም ለንጉሡ አገልግሎት የተሻለ ብቃት እንደሚኖራቸው እርግጠኞች ነበሩ። ከ1919 መጀመሪያ አንስቶ፣ የአምላክ መንፈስ ሕዝቦቹን የሚጠሉ ሰዎች ሊሆን አይችልም ብለው ያሰቡትን ነገር ማድረግ እንደቻለ በግልጽ ታይቷል። ታማኞቹ አገልጋዮች መልሰው አንሰራርተዋል! (ራእይ 11:11) በዚያን ጊዜ ክርስቶስ የመጨረሻዎቹን ቀኖች ለይቶ በሚያሳውቀው ምልክት ውስጥ የተካተተ አንድ ቁልፍ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጓል። ኢየሱስ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ የሾመ ሲሆን ይህ ባሪያ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ በሕዝቦቹ መካከል አመራር የሚሰጡ ጥቂት ቁጥር ያላቸው የተቀቡ ወንዶችን ያቀፈ ነው።—ማቴ. 24:45-47

36. የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ እያንሰራሩ መሆናቸውን ያመላከተው ነገር ምንድን ነው?

36 ወንድም ራዘርፎርድና የሥራ ባልደረቦቹ መጋቢት 26, 1919 ከእስር ተፈቱ። በዚያው ዓመት በመስከረም ወር ትልቅ ስብሰባ ለማድረግ ፕሮግራም አወጡ። በተጨማሪም ዘ ጎልደን ኤጅ የተባለ ሁለተኛ መጽሔት ለማዘጋጀት እቅድ ነደፉ። e ከመጠበቂያ ግንብ ጋር ጎን ለጎን የሚታተመው ይህ መጽሔት መስክ አገልግሎት ላይ እንዲሠራበት የተዘጋጀ ነበር። በዚያው ዓመት የመጀመሪያው ቡለቲን (በአሁኑ ጊዜ የክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን ስብሰባ አስተዋጽኦ ይባላል) ለኅትመት በቃ። ቡለቲን ከጅምሩ አንስቶ ለመስክ አገልግሎት የሚያነቃቃ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ከ1919 አንስቶ በግለሰብ ደረጃ ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ማገልገል ይበልጥ ትኩረት ይሰጠው ጀመር።

37. ከ1919 በኋላ በነበሩት ዓመታት አንዳንዶች ታማኝ አለመሆናቸው የታየው እንዴት ነው?

37 የስብከቱ ሥራ የክርስቶስን አገልጋዮች ማጥራቱን ቀጠለ፤ ምክንያቱም ኩሩና እብሪተኛ የሆኑት ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ትሕትና የሚጠይቅ ሥራ ለማከናወን ፈቃደኞች አልነበሩም። ለሥራው ድጋፍ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት፣ በታማኝነት ከሚያገለግሉት ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አቋረጡ። ከ1919 በኋላ ባሉት ዓመታት፣ በታማኝነት መጽናት ያልቻሉ አንዳንድ ሰዎች በጣም የተበሳጩ ከመሆኑም በላይ የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች ከሚያሳድዱት ጋር በመወገን በቃልና በጽሑፍ ስም ማጥፋታቸውን ተያያዙት።

38. በምድር ላይ የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች ያገኙት ስኬትና ድል ምን ያስገነዝበናል?

38 በምድር የነበሩት የክርስቶስ ተከታዮች እንዲህ ያለ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም በመንፈሳዊ እየተጠናከሩና እየጎለበቱ ሄዱ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያገኙት ስኬትም ሆነ የተቀዳጁት ድል በሙሉ የአምላክ መንግሥት እየገዛ እንደሆነ የሚያሳዩ አሳማኝ ማስረጃዎች ናቸው! ፍጽምና የጎደላቸው ጥቂት ሰዎች በሰይጣንና በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ በድል ላይ ድል መቀዳጀት የቻሉት አምላክ በልጁና በመሲሐዊው መንግሥቱ አማካኝነት ድጋፍ ስለሰጣቸውና ስለባረካቸው ነው!ኢሳይያስ 54:17ን አንብብ።

ወንድም ራዘርፎርድ ከእስር ቤት ከተፈታ ከጥቂት ወራት በኋላ በትልቅ ስብሰባ ላይ ቀስቃሽ ንግግር ሲያቀርብ

39, 40. (ሀ) ይህ መጽሐፍ ያሉት አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? (ለ) ይህን መጽሐፍ ማጥናትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

39 በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ የአምላክ መንግሥት በሰማይ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ባለፈው መቶ ዓመት ውስጥ በምድር ላይ ምን እንዳከናወነ እንመረምራለን። እያንዳንዱ የዚህ መጽሐፍ ክፍል መንግሥቱ በምድር ላይ ካከናወናቸው ሥራዎች መካከል አንዱን ለይቶ ያብራራል። በእያንዳንዱ ምዕራፍ ውስጥ የተካተተው የክለሳ ሣጥን የአምላክ መንግሥት በግለሰብ ደረጃ ለእኛ ምን ያህል እውን እንደሆነ መገንዘብ እንድንችል ይረዳናል። የመጨረሻዎቹ ምዕራፎች ደግሞ በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ክፉዎችን ለማጥፋትና ምድርን ገነት ለማድረግ ሲመጣ ምን ነገሮችን ያከናውናል ብለን መጠበቅ እንደምንችል ያብራራሉ። ይህን መጽሐፍ ማጥናትህ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

40 ሰይጣን በአምላክ መንግሥት ላይ ያለህን እምነት ለመሸርሸር ይፈልጋል። ይሁንና ይሖዋ ጠንካራ እምነት እንዲኖርህ ይፈልጋል፤ ጥበቃ ልታገኝና ልትጸና የምትችለው እምነትህ ጠንካራ ከሆነ ነው። (ኤፌ. 6:16) በመሆኑም ይህን መጽሐፍ በጸሎት እየታገዝክ እንድታጠና እናበረታታሃለን። ‘የአምላክ መንግሥት እውን ሆኖልኛል?’ እያልክ በየጊዜው ራስህን ጠይቅ። በአሁኑ ጊዜ መንግሥቱ ይበልጥ እውን ከሆነልህ፣ ሕያዋን ፍጥረታት ሁሉ የአምላክ መንግሥት እውን እንደሆነና እየገዛ እንዳለ በሚገነዘቡበት ቀን የመንግሥቱ ታማኝና ትጉ ደጋፊ ሆነህ የመገኘትህ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል!

a ስለ ግሩ፣ ስቴትሰን እና ስቶርዝ ይበልጥ ለማወቅ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 45-46 ተመልከት።

b የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የዓለም ወዳጆች ከሆኑ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች የመውጣትን አስፈላጊነት ቢገነዘቡም ለበርካታ ዓመታት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ባይሆኑም እንኳ በቤዛው እንደሚያምኑና ራሳቸውን ለአምላክ እንደወሰኑ የሚናገሩ ሰዎችን እንደ ክርስቲያን ወንድሞቻቸው አድርገው ይመለከቱ ነበር።

c ቀደም ሲል የተሰጡት እንዲህ ያሉ ማስጠንቀቂያዎች ኃይል እንዳይኖራቸው ተጽዕኖ ያሳደረው አንዱ ምክንያት ማስጠንቀቂያዎቹ በዋነኝነት የሚሠሩት 144,000ዎቹን ላቀፈው የክርስቶስ ትንሽ መንጋ እንደሆነ ይታሰብ የነበረ መሆኑ ነው። ከ1935 በፊት በራእይ 7:9, 10 ላይ የተጠቀሰው “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባላት እንደሚያጠቃልል ተደርጎ ይታሰብ እንደነበር በምዕራፍ 5 ላይ እንመለከታለን፤ እነዚህ ሰዎች በመጨረሻው ቀን ከክርስቶስ ጎን ስለሚቆሙ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው የሰማያዊ ክፍል አባላት የመሆን ሽልማት እንደሚያገኙ ተደርጎ ይታመን ነበር።

d የመስከረም 1920 ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ! ይባላል) ልዩ እትም በእንግሊዝ፣ በካናዳ፣ በዩናይትድ ስቴትስና በጀርመን የነበሩ ክርስቲያኖች በጦርነቱ ወቅት የደረሰባቸውን ስደት በዝርዝር አውጥቶ ነበር፤ አንዳንዱ ድርጊት በጣም የሚዘገንን ነው። በአንጻሩ ግን ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት ውስጥ እንዲህ ያለ ስደት እምብዛም አልነበረም።

e ለበርካታ ዓመታት መጠበቂያ ግንብ በዋነኝነት የሚዘጋጀው የታናሹ መንጋ አባላት ራሳቸውን በመንፈሳዊ እንዲመግቡ ለመርዳት ተብሎ ነበር።