በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 6

ምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች—ሰባኪዎች ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ

ምሥራቹን የሚሰብኩ ሰዎች—ሰባኪዎች ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቀረቡ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ንጉሡ የሰባኪዎች ሠራዊት አደራጀ

1, 2. ኢየሱስ ምን ታላቅ ሥራ እንደሚከናወን ትንቢት ተናግሮ ነበር? ምን አስፈላጊ ጥያቄስ ይነሳል?

 የፖለቲካ መሪዎች ብዙውን ጊዜ ቃል የገቡትን ነገር አይፈጽሙም። በጎ ዓላማ ያላቸው መሪዎችም እንኳ ቢሆኑ ቃላቸውን መጠበቅ ሊያቅታቸው ይችላል። ደስ የሚለው ግን መሲሐዊው ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንጊዜም ቢሆን ቃሉን ይጠብቃል።

2 ኢየሱስ በ1914 ሲነግሥ፣ ከ1,900 ዓመታት በፊት የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ዝግጁ ሆነ። ኢየሱስ ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” የሚል ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 24:14) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ማግኘቱ፣ ኢየሱስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ እንደተገኘ ከሚጠቁመው ምልክት ገጽታዎች አንዱ እየተፈጸመ እንደሆነ ያሳያል። ይሁንና ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ጥያቄ ይነሳል፦ በራስ ወዳድነት፣ ፍቅር በማጣትና በሃይማኖታዊ ግዴለሽነት በሚታወቀው በመጨረሻው ዘመን ንጉሡ፣ በፈቃደኝነት የሚሠሩ የሰባኪዎች ሠራዊት ማደራጀት የሚችለው እንዴት ነው? (ማቴ. 24:12፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) ይህ ጉዳይ ሁሉንም እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለሚመለከት ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት ያስፈልገናል።

3. ኢየሱስ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር? እንዲህ ያለ መተማመን ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ የተናገረውን ትንቢት እስቲ መለስ ብለን እንመልከት። “ይሰበካል” የሚለው ቃል ኢየሱስ ትንቢቱ እንደሚፈጸም እርግጠኛ መሆኑን ይጠቁማል? እንዴታ! በመጨረሻዎቹ ቀናት በፈቃደኝነት ሥራውን የሚደግፉ ሰዎች እንደሚኖሩ ኢየሱስ እርግጠኛ ነበር። እንዲህ ዓይነት መተማመን ሊኖረው የቻለው እንዴት ነው? ከአባቱ ስለተማረ ነው። (ዮሐ. 12:45፤ 14:9) ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ የፈቃደኝነት መንፈስ እንደሚያሳዩ የሚተማመን መሆኑን ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ተመልክቷል። ይሖዋ፣ በአገልጋዮቹ እንደሚተማመን ያሳየው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል”

4. እስራኤላውያን የትኛውን ሥራ እንዲደግፉ ይሖዋ ጋብዟቸው ነበር? እነሱስ ምን ምላሽ ሰጡ?

4 ይሖዋ፣ ለእስራኤል ብሔር የአምልኮ ማዕከል የሚሆነውን የማደሪያ ድንኳን እንዲሠራ ለሙሴ መመሪያ በሰጠው ወቅት የተፈጸመውን ሁኔታ አስታውስ። ሕዝቡ በሙሉ ይህን ሥራ እንዲደግፉ ይሖዋ በሙሴ በኩል ግብዣ አቀረበላቸው። ሙሴ ለሕዝቡ “ልቡ ያነሳሳው ማንኛውም ሰው . . . ለይሖዋ መዋጮ ያምጣ” አላቸው። ውጤቱስ ምን ሆነ? “ሕዝቡ . . . በየማለዳው የፈቃደኝነት መባ ወደ እሱ ያመጡ ነበር።” ሕዝቡ ያመጡት ስጦታ በጣም ብዙ በመሆኑ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘ምንም ነገር እንዳያመጡ ተገቱ’! (ዘፀ. 35:5፤ 36:3, 6) እስራኤላውያን፣ ይሖዋ በእነሱ ላይ እምነት መጣሉ ተገቢ እንደሆነ አስመሥክረዋል።

5, 6. በመዝሙር 110:1-3 ላይ በተተነበየው መሠረት ይሖዋ እና ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን እውነተኛ አምላኪዎች ምን ዓይነት መንፈስ እንደሚያሳዩ ይጠብቁ ነበር?

5 ይሖዋ፣ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ አምላኪዎቹ እንዲህ ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ ይኖራቸዋል ብሎ ይጠብቃል? አዎ! ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ ከ1,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ዳዊት፣ መሲሑ በሚነግሥበት ጊዜ ስለሚኖረው ሁኔታ ትንቢት እንዲናገር ይሖዋ በመንፈሱ መርቶት ነበር። (መዝሙር 110:1-3ን አንብብ።) አዲስ የተሾመው ንጉሥ ማለትም ኢየሱስ የሚቃወሙት ጠላቶች ይኖሩታል። ያም ቢሆን እሱን የሚደግፍ ሠራዊትም ይኖረዋል። እነዚህ ሰዎች ንጉሡን የሚያገለግሉት ተገድደው አይደለም። በመካከላቸው ያሉ ወጣቶች እንኳ ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀርባሉ፤ እነዚህ ወጣቶች እጅግ በጣም ብዙ ከመሆናቸው የተነሳ ማለዳ ላይ ምድርን ከሚሸፍነው ጤዛ ወይም ጠል ጋር ተመሳስለዋል። a

መንግሥቱን በፈቃደኝነት የሚደግፉት ሰዎች እንደ ጤዛ ብዙ ናቸው (አንቀጽ 5ን ተመልከት)

6 ኢየሱስ በመዝሙር 110 ላይ ያለው ትንቢት በእሱ ላይ እንደሚፈጸም ያውቅ ነበር። (ማቴ. 22:42-45) በመሆኑም በመላው ዓለም ምሥራቹን ለመስበክ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ታማኝ ደጋፊዎች እንደሚኖሩት ለመተማመን የሚያስችል በቂ ምክንያት ነበረው። ታዲያ ታሪክ ምን ያሳያል? ንጉሡ በመጨረሻዎቹ ቀናት ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ የሰባኪዎች ሠራዊት ማደራጀት ችሎ ይሆን?

“ይህንን መልእክት ማወጅ መብቴም ግዴታዬም ነው”

7. ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ፣ ተከታዮቹን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ሥራ ለማዘጋጀት ምን እርምጃዎች ወስዷል?

7 ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ብዙም ሳይቆይ፣ ተከታዮቹን ከፊታቸው ለሚጠብቃቸው ትልቅ ሥራ ለማዘጋጀት አንዳንድ እርምጃዎች ወሰደ። በምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው ከ1914 አንስቶ እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ የምርመራና የማጽዳት ሥራ አከናውኗል። (ሚል. 3:1-4) ከዚያም በ1919 ታማኙን ባሪያ፣ ተከታዮቹን እንዲመራ ሾመው። (ማቴ. 24:45) ይህ ባሪያ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ በሚቀርቡ ንግግሮችና በጽሑፎች አማካኝነት መንፈሳዊ ምግብ ማሰራጨት ጀመረ፤ ባሪያው ሁሉም ክርስቲያኖች በስብከቱ ሥራ በግለሰብ ደረጃ የመካፈል ኃላፊነት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ጎላ አድርጎ ሲገልጽ ቆይቷል።

8-10. ትላልቅ ስብሰባዎች የስብከቱ ሥራ እንዲቀጣጠል አስተዋጽኦ ያደረጉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (“ የስብከቱ ሥራ ይበልጥ እንዲቀጣጠል ያደረጉ ቀደም ባሉት ዓመታት የተካሄዱ ትላልቅ ስብሰባዎች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

8 በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ የቀረቡ ንግግሮች። መመሪያ ለማግኘት የጓጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከመስከረም 1 እስከ 8, 1919 በሴዳር ፖይንት፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ስብሰባ አደረጉ፤ ይህ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ያደረጉት የመጀመሪያው ትልቅ ስብሰባ ነው። ወንድም ራዘርፎርድ በሁለተኛ ቀን በሰጠው ንግግር ላይ ለተሰብሳቢዎቹ “ክርስቲያኖች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ተልእኳቸው ስለ ጌታ መንግሥት የሚገልጸውን መልእክት ማወጅ ነው” ብሏቸው ነበር።

9 ከሦስት ቀናት በኋላ፣ በዚህ ስብስባ ላይ ጉልህ ስፍራ የያዘውን ንግግር ወንድም ራዘርፎርድ አቀረበ፤ የንግግሩ ርዕስ “ለረዳት ሠራተኞች የቀረበ ጥሪ” የሚል ሲሆን ይህ ንግግር “መንግሥቱን ማስታወቅ” በሚል ርዕስ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል። ወንድም ራዘርፎርድ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “አንድ ክርስቲያን ስለ ሕይወቱ በቁም ነገር በሚያስብበት ወቅት ‘በምድር ላይ የመኖሬ ዓላማ ምንድን ነው?’ ብሎ መጠየቁ አይቀርም። መልሱ ‘ጌታ መለኮታዊውን የማስታረቅ መልእክት ለዓለም እንዳደርስ አምባሳደሩ አድርጎ በጸጋው ሾሞኛል፤ ይህንን መልእክት ማወጅ መብቴም ግዴታዬም ነው’ የሚል ሊሆን ይገባል።”

10 ወንድም ራዘርፎርድ ባቀረበው በዚያ ታሪካዊ ንግግር ላይ፣ ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ! ይባላል) የተባለ አዲስ መጽሔት መታተም እንደሚጀምር አስታወቀ፤ የዚህ መጽሔት ዓላማ ለሰው ዘር ችግሮች ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ ለሰዎች ማሳወቅ ነው። ከዚያም በስብሰባው ላይ ከተገኙት መካከል ይህን መጽሔት ለማሰራጨት ፈቃደኛ የሆኑት ምን ያህል እንደሆኑ ጠየቀ። ስለ ስብሰባው የቀረበ አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል፦ “ተሰብሳቢዎቹ የሰጡት ምላሽ በጣም አስገራሚ ነበር። ስድስት ሺህ ሰዎች ልክ እንደ አንድ ሰው ከተቀመጡበት በአንድነት ተነስተው ቆሙ።” b ከዚህ በግልጽ ለመመልከት እንደሚቻለው ንጉሡ ስለ መንግሥቱ ለማወጅ የሚጓጉ ፈቃደኛ ደጋፊዎች አሉት!

11, 12. ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው ሥራ የሚከናወንበትን ጊዜ በተመለከተ የ1920 መጠበቂያ ግንብ ምን ሐሳብ ይዞ ነበር?

11 ጽሑፎች። ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረው ሥራ ይኸውም የመንግሥቱን ምሥራች የማወጁ ሥራ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በመጠበቂያ ግንብ ላይ በሚወጡ ትምህርቶች አማካኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ። ከ1920ዎቹ ዓመታት መጀመሪያ አካባቢ አንስቶ የወጡ አንዳንድ ትምህርቶችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

12 በማቴዎስ 24:14 ላይ በተነገረው ትንቢት መሠረት የሚታወጀው የትኛው መልእክት ነው? ይህ ሥራ የሚከናወነውስ መቼ ነው? መልእክቱ ምን እንደሆነ የሐምሌ 1, 1920 መጠበቂያ ግንብ “የመንግሥቱ ወንጌል” በሚል ርዕስ አብራርቶ ነበር፤ ርዕሱ እንዲህ ይላል፦ “ምሥራቹ ስለ አሮጌው ሥርዓት ማብቃትና ስለ መሲሐዊው መንግሥት መቋቋም የሚገልጽ ነው።” መጠበቂያ ግንቡ መልእክቱ የሚሰበከው መቼ እንደሆነ ሲጠቁም “ይህ መልእክት መሰበክ ያለበት በታላቁ ጦርነት [በአንደኛው የዓለም ጦርነት] እና ‘በታላቁ መከራ’ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ ነው” ብሏል። በመሆኑም ርዕሱ አክሎ ‘ይህ ምሥራች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በስፋት መታወጅ ያለበት አሁን እንደሆነ’ ገልጿል።

13. የ1921 መጠበቂያ ግንብ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት መንፈስ ተነሳስተው እንዲያገለግሉ ያበረታታቸው እንዴት ነው?

13 የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስ አስቀድሞ የተናገረውን ሥራ የሚያከናውኑት ተገድደው ነው? በፍጹም! መጋቢት 15, 1921 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “አይዟችሁ፣ አትፍሩ” የሚለው ርዕስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በፈቃደኝነት መንፈስ ተነሳስተው እንዲያገለግሉ የሚያበረታታ ነበር። እያንዳንዱ ክርስቲያን “በዚህ ሥራ መካፈል መቻሌ ታላቅ መብት አይደለም? ደግሞስ ይህን የማድረግ ኃላፊነት የለብኝም?” በማለት ራሱን እንዲጠይቅ ተበረታትቶ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “እንዲህ አድርጋችሁ ስታዩት [በዚህ ሥራ መካፈልን እንደ መብት ስትመለከቱት] እንደ ኤርምያስ እንደሚሰማችሁ እርግጠኞች ነን፤ ኤርምያስ የጌታ ቃል በልቡ ውስጥ ‘እንዳለ፣ [በአጥንቶቹም] ውስጥ እንደገባ የሚነድ እሳት’ ስለሆነበት ቃሉን ከመናገር ወደኋላ ማለት አልቻለም።” (ኤር. 20:9) ይህ ሞቅ ያለ ማበረታቻ ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ ታማኝ በሆኑት የመንግሥቱ ደጋፊዎች ምን ያህል እንደሚተማመኑ የሚያሳይ ነው።

14, 15. በ1922 የወጣ መጠበቂያ ግንብ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሰዎች ለመመሥከር በየትኛው መንገድ እንዲጠቀሙ አበረታትቷል?

14 ታዲያ እውነተኛ ክርስቲያኖች የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ማዳረስ የሚችሉት እንዴት ነው? በነሐሴ 15, 1922 መጠበቂያ ግንብ ላይ “አገልግሎት አስፈላጊ ነው” የሚል አጠር ያለ ሆኖም ኃይለኛ መልእክት የያዘ ርዕስ ወጥቶ ነበር፤ ይህ ርዕስ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ጽሑፎችን በቅንዓት ለሰዎች በማድረስና ቤታቸው ሄደው በማነጋገር መንግሥተ ሰማያት መቅረቡን እንዲመሠክሩ’ አበረታትቷል።

15 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ክርስቲያኖች በምድር ላይ ያላቸው መብትና ኃላፊነት የመንግሥቱን መልእክት ማወጅ እንደሆነ ከ1919 ወዲህ ባሉት ዓመታት በተደጋጋሚ ጎላ አድርጎ ለመግለጽ ክርስቶስ በታማኝና ልባም ባሪያው ሲጠቀም ቆይቷል። ታዲያ በቀድሞው ዘመን የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ መንግሥቱ በማወጁ ሥራ እንዲካፈሉ ለተሰጣቸው ማበረታቻ ምን ምላሽ ሰጡ?

‘ታማኝ የሆኑት ክርስቲያኖች ፈቃደኛ ይሆናሉ’

16. ክርስቲያኖች በሙሉ በአገልግሎቱ መካፈል እንዳለባቸው ሲገለጽ ጉባኤው ከመረጣቸው ሽማግሌዎች አንዳንዶቹ ምን ምላሽ ሰጡ?

16 በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት አንዳንዶች፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በአገልግሎቱ መካፈል አለባቸው የሚለውን ሐሳብ ተቃውመው ነበር። የኅዳር 1, 1927 መጠበቂያ ግንብ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በዛሬው ጊዜ በቤተ ክርስቲያን [በጉባኤ] ውስጥ የሽማግሌነት ኃላፊነት ያላቸው አንዳንዶች . . . ወንድሞቻቸውን በአገልግሎቱ እንዲካፈሉ ለማበረታታትም ሆነ እነሱ ራሳቸው በአገልግሎቱ ለመካፈል ፈቃደኛ አይደሉም። . . . እነዚህ ሽማግሌዎች የአምላክ፣ የንጉሡና የመንግሥቱ መልእክት ከቤት ወደ ቤት እንዲሰበክ የቀረበውን ሐሳብ ያጣጥላሉ።” መጽሔቱ አክሎም “በአሁኑ ወቅት ታማኝ ክርስቲያኖች እንደ እነዚህ ያሉትን ለይተው ማወቅና ከእነሱ መራቅ ያስፈልጋቸዋል፤ በተጨማሪም እንዲህ ላሉ ሰዎች ከአሁን በኋላ የሽምግልና ኃላፊነትን በአደራ [እንደማይሰጧቸው ሊያሳውቋቸው] ይገባል” በማለት በግልጽ ተናግሯል። c

17, 18. አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት ከዋናው መሥሪያ ቤት ለተሰጣቸው መመሪያ ምን ምላሽ ሰጡ? ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምን ምላሽ ሰጥተዋል?

17 ደስ የሚለው ነገር አብዛኞቹ የጉባኤው አባላት ከዋናው መሥሪያ ቤት የተሰጣቸውን መመሪያ በደስታ ተቀብለውታል። የመንግሥቱን መልእክት በመስበኩ ሥራ መካፈልን እንደ መብት ቆጥረውታል። የመጋቢት 15, 1926 መጠበቂያ ግንብ ስለዚህ ጉዳይ ሲገልጽ “ታማኝ የሆኑት ክርስቲያኖች . . . ይህን መልእክት ለሰዎች ለመናገር ፈቃደኛ ይሆናሉ” የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር። እነዚህ ታማኝ ክርስቲያኖች በመዝሙር 110:3 ላይ የተነገረው ትንቢት እንዲፈጸም ያደረጉ ሲሆን መሲሐዊውን መንግሥት በፈቃደኝነት እንደሚደግፉ አሳይተዋል።

18 ባለፉት 100 ዓመታት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች የማወጁን ሥራ ለማከናወን ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። እነዚህ ሰዎች የስብከቱን ሥራ ያከናወኑት እንዴት እንደሆነ ይኸውም የትኞቹን ዘዴዎችና መሣሪያዎች እንደተጠቀሙ እንዲሁም ምን ውጤት እንዳገኙ በቀጣዮቹ ምዕራፎች ላይ ይብራራል። በመጀመሪያ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራስ ወዳድ በሆነው ዓለም ውስጥ እየኖሩም እንኳ በመንግሥቱ ስብከት ሥራ በፈቃደኝነት የሚካፈሉት ለምን እንደሆነ እንመልከት። እንዲህ የሚያደርጉበትን ምክንያት በምንመረምርበት ወቅት ‘ምሥራቹን ለሌሎች እንድሰብክ የሚያነሳሳኝ ምንድን ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው።

“ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . መፈለጋችሁን ቀጥሉ”

19. ኢየሱስ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . መፈለጋችሁን ቀጥሉ” በማለት የሰጠንን ምክር የምንከተለው ለምንድን ነው?

19 ኢየሱስ፣ ለተከታዮቹ “ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . ፈልጉ” የሚል ምክር ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 6:33) ይህን ምክር የምንከተለው ለምንድን ነው? የአምላክ መንግሥት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይኸውም በአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳለው ስለምንገነዘብ ነው። ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው፣ መንፈስ ቅዱስ ስለ መንግሥቱ የሚገልጹ አስደሳች እውነቶችን ለክርስቲያኖች ቀስ በቀስ ገልጾላቸዋል። እኛም ውድ በሆነው የመንግሥቱ እውነት ልባችን ሲነካ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም እንነሳሳለን።

የተደበቀ ውድ ሀብት ሲያገኝ በደስታ እንደሚሞላ ሰው ክርስቲያኖችም የመንግሥቱን እውነት በማግኘታቸው በጣም ይደሰታሉ (አንቀጽ 20ን ተመልከት)

20. ኢየሱስ ስለ ተደበቀ ውድ ሀብት የተናገረው ምሳሌ፣ ተከታዮቹ አስቀድመው መንግሥቱን መፈለጋቸውን እንዲቀጥሉ ለተሰጣቸው ምክር ምን ምላሽ እንደሚሰጡ የሚጠቁመው እንዴት ነው?

20 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ አስቀድመው መንግሥቱን መፈለጋቸውን እንዲቀጥሉ ለተሰጣቸው ምክር ምን ምላሽ እንደሚሰጡ ያውቅ ነበር። ስለ አንድ የተደበቀ ውድ ሀብት የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት። (ማቴዎስ 13:44ን አንብብ።) በምሳሌው ላይ የተገለጸው ሠራተኛ የዕለት ተዕለት ሥራውን እያከናወነ ሳለ የተደበቀ ውድ ሀብት አገኘ፤ ያገኘው ነገር ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለማወቅ ጊዜ አልወሰደበትም። ታዲያ ምን አደረገ? “ከመደሰቱም የተነሳ ሄዶ ያለውን ሁሉ በመሸጥ እርሻውን ገዛው።” ይህ ምሳሌ ምን ትምህርት ይዞልናል? የመንግሥቱን እውነት ስናገኝና ያለውን ዋጋ ስንገነዘብ ከዚህ መንግሥት ጋር ለተያያዙ ነገሮች ተገቢውን ቦታ ይኸውም በሕይወታችን ውስጥ አንደኛውን ቦታ ለመስጠትና ይህን ማድረጋችንን ለመቀጠል እንጥራለን፤ ለዚህም ስንል ምንም ቅር ሳይለን አስፈላጊውን መሥዋዕት ሁሉ እንከፍላለን። d

21, 22. ታማኝ የመንግሥቱ ደጋፊዎች አስቀድመው መንግሥቱን እንደሚፈልጉ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

21 ታማኝ የመንግሥቱ ደጋፊዎች አስቀድመው መንግሥቱን እንደሚፈልጉ የሚያሳዩት በንግግራቸው ብቻ ሳይሆን በተግባራቸው ጭምር ነው። ችሎታቸውንና ንብረታቸውን ጨምሮ መላ ሕይወታቸውን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለመደገፍ ይጠቀሙበታል። ብዙዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ በርካታ መሥዋዕቶችን ከፍለዋል። በፈቃደኝነት ራሳቸውን ያቀረቡት እነዚህ ሰባኪዎች በሙሉ ይሖዋ፣ መንግሥቱን ያስቀደሙ ሰዎችን እንደሚባርካቸው በሕይወታቸው ተመልክተዋል። ቀደም ባሉት ዓመታት ከነበሩት እንዲህ ያሉ ክርስቲያኖች መካከል እስቲ የአንዳንዶቹን ምሳሌ እንመልከት።

22 ኤቨሪ እና ሎቪንያ ብሪስቶ የተባሉ ባልና ሚስት ከ1920ዎቹ ዓመታት መጨረሻ አካባቢ አንስቶ በደቡብ ዩናይትድ ስቴትስ ኮልፖርተሮች (አቅኚዎች) ሆነው ያገለግሉ ነበር። ከዓመታት በኋላ ሎቪንያ እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ኤቨሪ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በአቅኚነት በርካታ አስደሳች ዓመታት አሳልፈናል። ለነዳጅም ሆነ ለምግብ የሚያስፈልገንን ገንዘብ የምናጣባቸው ብዙ ጊዜያት ነበሩ። ያም ቢሆን ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ተጠቅሞ የሚያስፈልገንን ነገር ሁልጊዜ ይሰጠን ነበር። እኛም አቅኚነታችንን አላቆምንም። መቼም ቢሆን የሚያስፈልገንን አጥተን አናውቅም።” በፔንሲኮላ፣ ፍሎሪዳ እያገለገሉ እያለ በአንድ ወቅት ገንዘብ እንዳጠራቸውና ቤት ውስጥ ምግብ እንዳልነበራቸው ሎቪንያ ታስታውሳለች። ወደ ተጎታች ቤታቸው ሲመለሱ በሁለት ትላልቅ መያዣዎች ሙሉ ምግብ ተደርጎ “አፍቃሪ ወንድሞቻችሁ፣ ከፔንሲኮላ ጉባኤ” ከሚል ማስታወሻ ጋር ተቀምጦ አገኙ። ሎቪንያ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳለፈችውን ጊዜ መለስ ብላ ስታስታውስ “ይሖዋ አንድም ቀን ትቶን አያውቅም፤ በእሱ ላይ እምነት በመጣላችን አላሳፈረንም” ብላለች።

23. የመንግሥቱን እውነት በማግኘትህ ምን ይሰማሃል? ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

23 ሁላችንም በስብከቱ ሥራ ላይ የምናደርገው ተሳትፎ እኩል ሊሆን አይችልም። ያለንበት ሁኔታ ይለያያል። ይሁንና ማናችንም ብንሆን ምሥራቹን በሙሉ ነፍሳችን የማወጅ መብት አለን። (ቆላ. 3:23) ያገኘነውን ውድ የመንግሥቱ እውነት ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን፤ በመሆኑም አቅማችን በፈቀደው መጠን በአገልግሎቱ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግ ስንል ማንኛውንም መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች ከመሆናችንም በላይ ይህን ለማድረግ እንጓጓለን። አንተስ ቁርጥ ውሳኔህ ይህ አይደለም?

24. የአምላክ መንግሥት በመጨረሻዎቹ ቀናት ካከናወናቸው ታላላቅ ነገሮች አንዱ ምንድን ነው?

24 ንጉሡ በማቴዎስ 24:14 ላይ የተናገረው ትንቢት ባለፈው ምዕተ ዓመት ፍጻሜውን እንዲያገኝ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህንንም ያደረገው ማንንም ሳያስገድድ ነው። ተከታዮቹ፣ ራስ ወዳድነት ከተስፋፋበት ከዚህ ዓለም ከተለዩ በኋላ የስብከቱን ሥራ ለማከናወን ራሳቸውን በፈቃደኝነት አቅርበዋል። በዓለም ዙሪያ የሚያከናውኑት ምሥራቹን የመስበክ ሥራ፣ ኢየሱስ በመንግሥታዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚጠቁመው ምልክት አንዱ ገጽታ ነው፤ ከዚህም ሌላ ይህ መንግሥት በመጨረሻዎቹ ቀናት ካከናወናቸው ታላላቅ ነገሮች አንዱ ነው።

a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጠል ከመትረፍረፍ ጋር ተያይዞ ተገልጿል።—ዘፍ. 27:28፤ ሚክ. 5:7

b ሥራው በኃላፊነት ለተሰጣቸው ሁሉ (እንግሊዝኛ) የተሰኘ በ1919 የታተመ ቡክሌት እንዲህ ይላል፦ “ወርቃማው ዘመን የተባለውን መጽሔት የምናሰራጨው የመንግሥቱን መልእክት ከቤት ወደ ቤት ለማድረስ ነው። . . . በእያንዳንዱ ቤት መልእክቱን ከተናገርን በኋላ የቤቱ ባለቤቶች የመጽሔት ኮንትራት ገቡም አልገቡ ወርቃማው ዘመን የተባለውን መጽሔት እንሰጣቸዋለን።” ከዚያ በኋላ ለብዙ ዓመታት ወንድሞች፣ ወርቃማው ዘመን እና መጠበቂያ ግንብ የተባሉትን መጽሔቶች ኮንትራት እንዲያስገቡ ይበረታቱ ነበር። ከየካቲት 1, 1940 አንስቶ የይሖዋ ሕዝቦች የእነዚህን መጽሔቶች ነጠላ ቅጂዎች እንዲያበረክቱና ያበረከቱትን ቁጥር ሪፖርት እንዲያደርጉ ማበረታቻ ይሰጣቸው ጀመር።

c በዚያን ጊዜ ጉባኤው፣ ሽማግሌዎችን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ይመርጥ ነበር። በመሆኑም አንድ ጉባኤ፣ በአገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ላልሆኑ ወንድሞች ድምፅ አለመስጠት ይችል ነበር። ሽማግሌዎችን በቲኦክራሲያዊ መንገድ መሾም ስለተጀመረበት መንገድ በምዕራፍ 12 ላይ ይብራራል።

d ኢየሱስ፣ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ዕንቁ ለመፈለግ ስለሄደ ተጓዥ ነጋዴ የተናገረው ምሳሌም ተመሳሳይ ትምህርት ይዟል። ነጋዴው ዕንቁውን ሲያገኘው ያለውን ሁሉ ሸጦ ገዛው። (ማቴ. 13:45, 46) ሁለቱ ምሳሌዎች የመንግሥቱን እውነት የምንማርበት መንገድ ሊለያይ እንደሚችልም ያሳያሉ። አንዳንዶች እውነትን የሚያገኙት በአጋጣሚ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ፈልገው ያገኙታል። እውነትን ያገኘንበት መንገድ ምንም ይሁን ምን በሕይወታችን ውስጥ መንግሥቱን ለማስቀደም ስንል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኞች ነን።