በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’

የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ውጤት—‘አዝመራው ነጥቷል’

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ይሖዋ የመንግሥቱ እውነት ዘር እንዲያድግ አድርጓል

1, 2. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ግራ የተጋቡት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የተናገረው ስለ የትኛው የመከር ሥራ ነው?

 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግራ ተጋብተዋል። ኢየሱስ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” አላቸው። ኢየሱስ እየጠቆማቸው ወዳለው አቅጣጫ ሲመለከቱ ግን ዓይናቸው ውስጥ የገባው የነጣ አዝመራ ሳይሆን አረንጓዴ የሆነ ለምለም የገብስ ቡቃያ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ የትኛው አዝመራ ነው የሚያወራው? መከር ሊገባ ገና የተወሰኑ ወራት ይቀሩ የለም እንዴ?’ ብለው አስበው ሊሆን ይችላል።—ዮሐ. 4:35

2 ኢየሱስ ግን ቃል በቃል ስለሚከናወነው የመከር ሥራ እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በዚህ ወቅት፣ ከመንፈሳዊው የመከር ሥራ ማለትም ሰዎችን ከመሰብሰብ ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ ሁለት ትምህርቶችን ለደቀ መዛሙርቱ እያስተማራቸው ነበር። እነዚህ ትምህርቶች ምንድን ናቸው? መልሱን ለማግኘት እስቲ ይህን ዘገባ በስፋት እንመርምር።

ለሥራ የቀረበ ጥሪ እና የሚገኘው ደስታ

3. (ሀ) ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሎ የተናገረው ለምን ሊሆን ይችላል? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከት።) (ለ) ኢየሱስ፣ የተናገረውን ነገር ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ይህን ውይይት ያደረገው በ30 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ሲሆን ቦታው ሰማርያ ውስጥ በምትገኝ ሲካር የተባለች ከተማ አቅራቢያ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ከተማይቱ ሲገቡ ኢየሱስ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። በዚያም ለአንዲት ሴት መንፈሳዊውን እውነት ነገራት፤ ይህች ሴት፣ ኢየሱስ ያስተማራት እውነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ለመገንዘብ ጊዜ አልወሰደባትም። ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሱስ ሲመለሱ ሴትየዋ የተማረቻቸውን አስደናቂ እውነቶች ለምታውቃቸው ሰዎች ለመናገር በፍጥነት ወደ ሲካር ሄደች። ሴትየዋ የተናገረችው ነገር የሰዎቹን የማወቅ ጉጉት ስለቀሰቀሰው ብዙዎቹ ኢየሱስን ለማግኘት በጥድፊያ ወደ ውኃው ጉድጓድ መጡ። ኢየሱስ አሻግሮ በርቀት ያለውን ሜዳ ሲቃኝ በርካታ ሳምራውያን በብዛት ሆነው ሲመጡ ተመለከተ፤ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ብሎ የተናገረው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። a ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ መንፈሳዊ አዝመራ መሆኑን ለመጠቆም “አጫጁ . . . ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው” በማለት አክሎ ተናገረ።—ዮሐ. 4:5-30, 36

4. (ሀ) ኢየሱስ የመከሩን ሥራ በተመለከተ የትኞቹን ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች አስተምሯል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

4 ኢየሱስ መንፈሳዊውን የመከር ሥራ በተመለከተ ያስተማራቸው ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው? የመጀመሪያው፣ ሥራው አጣዳፊ ነው የሚለው ነው። “አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” ሲል ተከታዮቹን ለሥራ እንዲንቀሳቀሱ ማበረታታቱ ነበር። ኢየሱስ፣ ሥራው ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ደቀ መዛሙርቱ በደንብ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ሲል “አሁንም እንኳ አጫጁ ደሞዙን እየተቀበለ . . . ነው” አላቸው። በእርግጥም አዝመራው መሰብሰብ ጀምሯል፤ በመሆኑም ዛሬ ነገ ሳይሉ ወዲያውኑ ሥራ መጀመር አለባቸው። ሁለተኛው ትምህርት ደግሞ ሠራተኞቹ ደስተኞች ናቸው የሚለው ነው። ኢየሱስ፣ ዘሪዎቹም ሆኑ አጫጆቹ “በአንድነት ደስ ይላቸዋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 4:35ለ, 36) ኢየሱስ “ብዙ ሳምራውያን በእሱ [በማመናቸው]” ተደስቶ መሆን አለበት፤ ደቀ መዛሙርቱም በመከሩ ሥራ በሙሉ ነፍሳቸው መካፈላቸው ከፍተኛ ደስታ ያስገኝላቸዋል። (ዮሐ. 4:39-42) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተፈጸመው ይህ ታሪክ፣ እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ መንፈሳዊ የመከር ሥራ በሚከናወንበት በዚህ ዘመን የሚኖረውን ሁኔታ የሚያሳይ በመሆኑ በዛሬው ጊዜ ላለን ክርስቲያኖች ልዩ ትርጉም አለው። ታዲያ ይህ ዘመናዊ የመከር ሥራ የጀመረው መቼ ነው? በሥራው የሚካፈሉት እነማን ናቸው? ምን ውጤትስ ተገኝቷል?

ንጉሣችን በታላቁ የመከር ሥራ በቀዳሚነት እየተካፈለ ነው

5. ዓለም አቀፍ የሆነውን ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ቅድሚያውን ወስዶ የሚያከናውነው ማነው? የዮሐንስ ራእይ የሥራውን አጣዳፊነት የሚያጎላው እንዴት ነው?

5 ዓለም አቀፍ በሆነው ሰዎችን የመሰብሰብ ሥራ ኢየሱስ ቅድሚያውን ወስዶ እንዲካፈል በይሖዋ እንደተሾመ ሐዋርያው ዮሐንስ በራእይ ተመልክቷል። (ራእይ 14:14-16ን አንብብ።) በዚህ ራእይ ላይ ኢየሱስ አክሊል ደፍቶና ማጭድ ይዞ ታይቷል። ኢየሱስ “በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል” መድፋቱ ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ያሳያል። ‘በእጁ ስለታም ማጭድ’ መያዙ ደግሞ አዝመራውን በመሰብሰብ ረገድ የሚጫወተውን ሚና ይጠቁማል። ይሖዋ “የምድር መከር ደርሷል” በማለት በአንድ መልአክ አማካኝነት መናገሩ የሥራውን አጣዳፊነት የሚያጎላ ነው። በእርግጥም “የአጨዳው ሰዓት ስለደረሰ” ሥራው ወዲያውኑ መጀመር አለበት! ኢየሱስ፣ “ማጭድህን ስደድ” በማለት አምላክ የሰጠውን መመሪያ በመታዘዝ ማጭዱን ሰድዶ ምድርን ይኸውም በምድር ላይ ያሉትን ሰዎች አጨደ። ይህ አስገራሚ ራእይም “አዝመራው እንደነጣ” ያስታውሰናል። ታዲያ ይህ ራእይ በዓለም ዙሪያ የሚከናወነው የመከር ሥራ መቼ እንደጀመረ ለማወቅ የሚያስችል ፍንጭ ይሰጠናል? አዎን!

6. (ሀ) ‘የመከሩ ወቅት’ የጀመረው መቼ ነው? (ለ) “የምድር መከር” መሰብሰብ የጀመረው መቼ ነው? አብራራ።

6 በራእይ ምዕራፍ 14 ላይ በሚገኘው ዮሐንስ በተመለከተው ራእይ ላይ አጫጁ ማለትም ኢየሱስ አክሊል ደፍቶ (ቁጥር 14) ስለታየ ራእዩ የተፈጸመው ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ መሆን አለበት። (ዳን. 7:13, 14) ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ አጨዳ እንዲጀምር ትእዛዝ ተሰጠው (ቁጥር 15)። ኢየሱስ ስለ ስንዴው መሰብሰብ በተናገረው ምሳሌ ላይም ነገሮች የተከናወኑበት ቅደም ተከተል ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ በዚህ ምሳሌ ላይ ኢየሱስ “መከሩ የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” እንደሆነ ተናግሮ ነበር። በመሆኑም የመከሩ ወቅት እና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ የሚጀምሩት በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ይኸውም በ1914 ነው። አዝመራውን የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው ግን “በመከር ወቅት” ውስጥ ይኸውም የመከሩ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ ነው። (ማቴ. 13:30, 39) ዛሬ ላይ ሆነን ወደኋላ ስንመለከት፣ የመከሩ ሥራ ወይም አዝመራውን የመሰብሰቡ ሥራ የጀመረው ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ እንደሆነ ማስተዋል እንችላለን። ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹን የማንጻት ሥራ አከናውኗል። (ሚል. 3:1-3፤ 1 ጴጥ. 4:17) ከዚያም በ1919 “የምድር መከር” መሰብሰብ ጀመረ። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ፣ በዚያ ወቅት በተሾመው ታማኝ ባሪያ በመጠቀም ወንድሞቻችን የስብከቱን ሥራ አጣዳፊነት እንዲገነዘቡ አድርጓል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

7. (ሀ) ወንድሞቻችን የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ የረዳቸው ምን ነገር መመርመራቸው ነው? (ለ) ወንድሞቻችን ምን እንዲያደርጉ ማበረታቻ ተሰጣቸው?

7 የሐምሌ 1920 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሏል፦ “ቅዱሳን መጻሕፍትን ስንመረምር፣ ቤተ ክርስቲያን ስለ መንግሥቱ የሚገልጽ መልእክት ለሰዎች የማድረስ ታላቅ መብት እንደተሰጣት መረዳት እንችላለን።” ለምሳሌ የኢሳይያስ ትንቢት፣ ወንድሞች የመንግሥቱን ዜና በዓለም ዙሪያ ማድረስ እንዳለባቸው እንዲያስተውሉ ረድቷቸዋል። (ኢሳ. 49:6፤ 52:7፤ 61:1-3) ይህ ሥራ የሚከናወነው እንዴት እንደሆነ ባያውቁም ይሖዋ መንገዱን እንደሚከፍትላቸው እርግጠኞች ነበሩ። (ኢሳይያስ 59:1ን አንብብ።) የስብከቱ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ በመገኘቱ ወንድሞቻችን አገልግሎታቸውን ይበልጥ እንዲያቀጣጥሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው። ታዲያ ምን ምላሽ ሰጡ?

8. በ1921 ወንድሞቻችን የስብከቱን ሥራ በተመለከተ የትኞቹን ሁለት ነጥቦች አስተዋሉ?

8 የታኅሣሥ 1921 መጠበቂያ ግንብ የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ይህ ዓመት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ዓመት ነው፤ ከዚህ በፊት ከነበሩት ዓመታት ይበልጥ በ1921 በጣም ብዙ ሰዎች የእውነትን መልእክት ሰምተዋል።” መጽሔቱ አክሎም “መሠራት ያለበት ገና ብዙ ነገር አለ። . . . ይህንን ሥራ በደስታ እናከናውን” ብሏል። ኢየሱስ ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ ለሐዋርያቱ የነገራቸውን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ይኸውም ሥራው አጣዳፊ መሆኑን እንዲሁም ሠራተኞቹ በደስታ እንደሚያከናውኑት ወንድሞች ማስተዋላቸውን ልብ በል።

9. (ሀ) በ1954 መጠበቂያ ግንብ ስለ መከሩ ሥራ ምን ብሎ ነበር? ለምንስ? (ለ) ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ በዓለም ዙሪያ የአስፋፊዎች ቁጥር ምን ያህል ጨምሯል? (“ በዓለም ዙሪያ ያለው ጭማሪ” የሚለውን ሠንጠረዥ ተመልከት።)

9 በ1930ዎቹ ዓመታት ወንድሞቻችን፣ የሌሎች በጎች አባላት የሆኑት እጅግ ብዙ ሕዝብ የመንግሥቱን መልእክት እንደሚቀበሉ ከተገነዘቡ በኋላ የስብከቱ ሥራ ይበልጥ ተፋፋመ። (ኢሳ. 55:5፤ ዮሐ. 10:16፤ ራእይ 7:9) ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? በ1934 የመንግሥቱን መልእክት የሚሰብኩት ክርስቲያኖች ቁጥር 41,000 የነበረ ሲሆን በ1953 ቁጥራቸው 500,000 ደረሰ! በእርግጥም የታኅሣሥ 1, 1954 መጠበቂያ ግንብ “ይህ ዓለም አቀፋዊ ታላቅ የመከር ሥራ ሊከናወን የቻለው በይሖዋ መንፈስ እና ቃሉ ባለው ኃይል የተነሳ ነው” ማለቱ ተገቢ ነበር። bዘካ. 4:6

 

በዓለም ዙሪያ ያለው ጭማሪ

አገር

1962

1987

2013

አውስትራሊያ

15,927

46,170

66,023

ብራዚል

26,390

216,216

756,455

ፈረንሳይ

18,452

96,954

124,029

ጣሊያን

6,929

149,870

247,251

ጃፓን

2,491

120,722

217,154

ሜክሲኮ

27,054

222,168

772,628

ናይጄሪያ

33,956

133,899

344,342

ፊሊፒንስ

36,829

101,735

181,236

ዩናይትድ ስቴትስ

289,135

780,676

1,203,642

ዛምቢያ

30,129

67,144

162,370

 

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች

1950

234,952

1960

646,108

1970

1,146,378

1980

1,371,584

1990

3,624,091

2000

4,766,631

2010

8,058,359

የመከሩ ሥራ የሚያስገኘው ውጤት ግሩም በሆነ ምሳሌ አስቀድሞ ተነግሯል

10, 11. ስለ ሰናፍጭ ዘር በሚገልጸው ምሳሌ ላይ ከዘሯ እድገት ጋር በተያያዘ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

10 ኢየሱስ ስለ መንግሥቱ በተናገራቸው ምሳሌዎች ላይ የመከር ሥራው የሚያስገኘውን ውጤት ግሩም በሆነ መንገድ አስቀድሞ ገልጾታል። ስለ ሰናፍጩ ዘር እና ስለ እርሾው የሚናገሩትን ምሳሌዎች እስቲ እንመልከት። እነዚህ ምሳሌዎች በመጨረሻው ዘመን ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ በትኩረት እንመረምራለን።

11 የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ። አንድ ሰው የሰናፍጭ ዘር ዘራ። ከዚያም ዘሯ አድጋ ትልቅ ዛፍ ሆነች፤ በመሆኑም እዚህች ዛፍ ላይ ወፎች ይሰፍሩ ጀመር። (ማቴዎስ 13:31, 32ን አንብብ።) ከዘሯ እድገት ጋር በተያያዘ በዚህ ምሳሌ ላይ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? (1) የሰናፍጯ ዘር ምን ያህል እንዳደገች ማየቱ አስገራሚ ነው። በምድር ላይ ካሉት “ዘሮች ሁሉ እጅግ የምታንስ” የተባለችው ዘር አድጋ “ትላልቅ ቅርንጫፎች” ያሉት ዛፍ ሆነች። (ማር. 4:31, 32) (2) ዘሯ እንደምታድግ የተረጋገጠ ነው። የሰናፍጯ ዘር ‘ከተዘራች በኋላ ታድጋለች።’ ኢየሱስ፣ ይህችን ዘር በተመለከተ “ታድግ ይሆናል” አላለም። ከዚህ ይልቅ ዘሯ ‘እንደምታድግ’ ተናግሯል። እድገቷን ሊገታ የሚችል ነገር አይኖርም። (3) ዛፏ ማደጓ የተለያዩ ፍጥረታትን የሚስብ ሲሆን መስፈሪያም ትሆንላቸዋለች። “የሰማይ ወፎች በጥላዋ ሥር መስፈሪያ ያገኛሉ።” እነዚህ ሦስት ነጥቦች በዘመናችን ከሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ጋር የሚያያዙት እንዴት ነው?

12. የሰናፍጯ ዘር ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ከሚከናወነው የመከር ሥራ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (“ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች” የሚለውን ሠንጠረዥም ተመልከት።)

12 (1) ምን ያህል እንዳደገች፦ ምሳሌው፣ የመንግሥቱ መልእክት እና የክርስቲያን ጉባኤ እድገት ማድረጋቸውን ያጎላል። ቀናተኛ የሆኑ የመከሩ ሠራተኞች ከ1919 ጀምሮ፣ ክርስቶስ ወዳነጻው የክርስቲያን ጉባኤ ተሰብስበዋል። በዚያ ወቅት የሠራተኞቹ ቁጥር ጥቂት የነበረ ቢሆንም ቁጥራቸው በፍጥነት እያደገ ሄደ። በእርግጥም በ1900ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የነበረው ቁጥር አድጎ በዛሬው ጊዜ ምን ያህል እንደደረሰ መመልከት አስገራሚ ነው። (ኢሳ. 60:22) (2) የተረጋገጠ መሆኑ፦ የክርስቲያን ጉባኤ እድገት ሊገታ እንደማይችል ታይቷል። የአምላክ ጠላቶች ትንሿን ዘር ለማጥፋት እንደ ዓለት ከባድ የሆነ የስደት ናዳ ቢጭኑባትም ዘሯ ማንኛውንም መሰናከል ተቋቁማ ማደጓን ቀጥላለች። (ኢሳ. 54:17) (3) መስፈሪያ መሆኗ፦ በዛፏ ላይ የሰፈሩት “የሰማይ ወፎች” ወደ 240 ገደማ ከሚሆኑ አገሮች የተውጣጡና የክርስቲያን ጉባኤ አባል በመሆን ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ የሰጡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦችን ያመለክታሉ። (ሕዝ. 17:23) እነዚህ ሰዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በመንፈሳዊ ሁኔታ ምግብ፣ እረፍትና እና ጥበቃ አግኝተዋል።—ኢሳ. 32:1, 2፤ 54:13

የሰናፍጩ ዘር ምሳሌ፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የታቀፉ ሰዎች ማረፊያና ጥበቃ እንደሚያገኙ ያሳያል (አንቀጽ 11, 12⁠ን ተመልከት)

13. በእርሾው ምሳሌ ላይ ከእድገት ጋር በተያያዘ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው?

13 የእርሾው ምሳሌ። አንዲት ሴት ዱቄት ውስጥ እርሾ በመጨመር ደባለቀችው፤ እርሾውም ሊጡ በሙሉ እንዲቦካ አደረገ። (ማቴዎስ 13:33ን አንብብ።) በዚህ ምሳሌ ላይ ከእድገት ጋር በተያያዘ የጎሉት ነጥቦች የትኞቹ ናቸው? እስቲ ሁለቱን ነጥቦች እንመርምር። (1) እድገት ለውጥ ያስከትላል። እርሾው በሊጡ ውስጥ በመሰራጨቱ “ሊጡ በሙሉ [ቦክቷል]።” (2) እድገቱ ብዙ ቦታዎችን የሚያዳርስ ነው። እርሾው ‘በሦስት ትላልቅ መስፈሪያ’ የተሰፈረው ዱቄት በሙሉ እንዲቦካ አድርጓል። እነዚህ ሁለት ነጥቦች በዘመናችን ከሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ጋር የሚያያዙት እንዴት ነው?

14. የእርሾው ምሳሌ በዘመናችን ከሚከናወነው የመከር ሥራ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

14 (1) ለውጥ፦ እርሾው የመንግሥቱን መልእክት ሲወክል ዱቄቱ የሰውን ዘር ያመለክታል። ዱቄት ከእርሾ ጋር ሲቦካ ሊጡ ላይ ለውጥ እንደሚታይ ሁሉ ሰዎችም የመንግሥቱን መልእክት ሲቀበሉ ልባቸው ይለወጣል። (ሮም 12:2) (2) ብዙ ቦታዎችን የሚያዳርስ፦ እርሾው መላውን ሊጥ ማዳረሱ የመንግሥቱ መልእክት መላውን ምድር እንደሚያዳርስ ይጠቁማል። እርሾው ሊጡ በሙሉ እስኪቦካ ድረስ ይሰራጫል። በተመሳሳይም የመንግሥቱ መልእክት “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰራጭቷል። (ሥራ 1:8) ከዚህም በተጨማሪ ከእርሾው ምሳሌ ጋር በተያያዘ የሚጎላው ሁለተኛው ነጥብ፣ ሥራችን በታገደባቸው አገሮች የስብከቱ ሥራ እንደሚከናወን ብዙዎች ባያስተውሉም በእነዚህ ቦታዎችም እንኳ የመንግሥቱ መልእክት እንደሚስፋፋ ይጠቁማል።

15. በኢሳይያስ 60:5, 22 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? (በገጽ 93 ላይ የሚገኘውን “ ይሖዋ እንዲቻል አድርጓል” የሚለውን ሣጥን እና ከገጽ 96-97 ላይ የሚገኘውን “ ‘ትንሽ የሆነው፣ ኃያል ብሔር’ የሆነው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

15 ኢየሱስ እነዚህን ምሳሌዎች ከመናገሩ ከ800 ዓመታት በፊት ይሖዋ፣ በዘመናችን የሚከናወነው መንፈሳዊ የመከር ሥራ ምን ያህል ስፋት እንደሚኖረው እንዲሁም ይህ የመከር ሥራ ደስታ እንደሚያስገኝ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት በማይረሳ መልኩ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። c ይሖዋ፣ ሰዎች “ከሩቅ” አካባቢዎች ወደ ድርጅቱ እንደሚጎርፉ ገልጿል። በዛሬው ጊዜ ምድር ላይ ያሉትን ቅቡዓን ቀሪዎች በአንዲት ሴት በመመሰል ይሖዋ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ታያለሽ፤ ፊትሽም ይፈካል፤ ልብሽ በኃይል ይመታል፤ በደስታም ይሞላል፤ ምክንያቱም የባሕር ብልጽግና ወደ አንቺ ይጎርፋል፤ የብሔራትም ሀብት ወደ አንቺ ይመጣል።” (ኢሳ. 60:1, 4, 5, 9) በእርግጥም ይህ ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል! በዛሬው ጊዜም ይሖዋን ለብዙ ዓመታት ሲያገለግሉ የቆዩ አገልጋዮቹ፣ ባሉበት አገር ውስጥ የነበሩት ጥቂት የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥራቸው ጨምሮ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መሆናቸውን ሲመለከቱ ልባቸው በደስታ ይሞላል።

ሁሉም የይሖዋ አገልጋዮች የሚደሰቱበት ምክንያት

16, 17. ‘ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት እንዲደሰቱ’ የሚያደርጋቸው አንዱ ምክንያት ምንድን ነው? (“ በአማዞን የሁለት ሰዎችን ልብ የነኩ ሁለት ትራክቶች” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

16 ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “አጫጁ . . . ለዘላለም ሕይወት ፍሬ እየሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ ዘሪውም ሆነ አጫጁ በአንድነት ደስ ይላቸዋል” እንዳላቸው ታስታውስ ይሆናል። (ዮሐ. 4:36) ይሁንና በዓለም አቀፉ የመከር ሥራ “በአንድነት ደስ [የሚለን]” ለምንድን ነው? የተለያዩ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። እስቲ ሦስቱን እንመልከት።

17 አንደኛ፣ ከዚህ ሥራ ጋር በተያያዘ ይሖዋ የሚያከናውነውን ነገር መመልከታችን ያስደስተናል። የመንግሥቱን መልእክት ስንሰብክ ዘሩን እየዘራን ነው። (ማቴ. 13:18, 19) አንድ ሰው፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንዲሆን ስንረዳ ደግሞ ፍሬ እየሰበሰብን ነው። ይሖዋ የመንግሥቱ ዘር ‘እንዲበቅልና እንዲያድግ’ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ስንመለከት ሁላችንም በጣም እንደሰታለን። (ማር. 4:27, 28) ከዘራነው ዘር መካከል የተወሰነው የሚያድገው ቆየት ብሎ በመሆኑ የሚሰበስቡት ሌሎች ናቸው። ምናልባት አንተም እንደ እህት ጆን ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ ይሆናል፤ በብሪታንያ የሚኖሩት እህት ጆን የተጠመቁት ከ60 ዓመታት በፊት ነው። እንዲህ ብለዋል፦ “አንዳንዶች፣ ምሥራቹን በመስበክ ከዓመታት በፊት በልባቸው ውስጥ የእውነትን ዘር የዘራሁት እኔ እንደሆንኩ ነግረውኛል። እነዚህ ሰዎች እኔ ሳላውቅ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን አጥንተው የይሖዋ አገልጋዮች ሆነዋል። የዘራሁት ዘር በማደጉና ለፍሬ በመብቃቱ ደስተኛ ነኝ።”—1 ቆሮንቶስ 3:6, 7ን አንብብ።

18. በ1 ቆሮንቶስ 3:8 ላይ ለደስታችን ምክንያት የሚሆን ምን ነገር ተጠቅሷል?

18 ሁለተኛ፣ ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል” በማለት የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳችን በሥራችን ደስተኛ ሆነን እንድንቀጥል ይረዳናል። (1 ቆሮ. 3:8) ሽልማት የምናገኘው ሥራችን ባስገኘው ውጤት መሠረት ሳይሆን በሥራችን መጠን ነው። ብዙም ውጤት በማይገኝበት አካባቢ ለሚሰብኩ ክርስቲያኖች ይህ ማረጋገጫ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! አምላክ፣ ዘር በመዝራቱ ሥራ በሙሉ ልቡ የሚካፈልን እያንዳንዱን የይሖዋ ምሥክር “ብዙ ፍሬ [እንደሚያፈራ]” አድርጎ ይመለከተዋል፤ ይህ ደግሞ ሁላችንም ደስተኛ እንድንሆን ያደርገናል።—ዮሐ. 15:8፤ ማቴ. 13:23

19. (ሀ) በማቴዎስ 24:14 ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት ከደስታችን ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? (ለ) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ባይሳካልንም እንኳ የትኛውን ነጥብ ማስታወስ ይኖርብናል?

19 ሦስተኛ፣ ሥራችን ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርግ መሆኑ ያስደስተናል። የኢየሱስ ሐዋርያት “የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” ብለው ሲጠይቁት ኢየሱስ የሰጣቸውን መልስ እንመልከት። ኢየሱስ የምልክቱ አንዱ ገጽታ በዓለም ዙሪያ የሚካሄድ የስብከት ሥራ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ይህን ሲል ደቀ መዛሙርት ስለማድረጉ ሥራ መናገሩ ነበር? አይደለም። “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ብሏል። (ማቴ. 24:3, 14) ከዚህ አንጻር የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ማለትም ዘር የመዝራቱ ሥራ የምልክቱ አንድ ገጽታ ነው። በመሆኑም የመንግሥቱን ምሥራች ስንሰብክ ደቀ መዛሙርት ማድረግ ባንችል እንኳ ‘ምሥክርነት’ በመስጠቱ ሥራ እየተሳካልን እንደሆነ ሁልጊዜ ማስታወስ ይኖርብናል። d በእርግጥም ሰዎች የሚሰጡት ምላሽ ምንም ይሁን ምን የኢየሱስን ትንቢት በመፈጸም ረገድ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን፤ በተጨማሪም “ከአምላክ ጋር አብረን [የመሥራት]” መብት አለን። (1 ቆሮ. 3:9) ይህም እንድንደሰት የሚያደርግ ትልቅ ምክንያት ነው!

“ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ”

20, 21. (ሀ) በሚልክያስ 1:11 ላይ የሚገኘው ትንቢት እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ከመከሩ ሥራ ጋር በተያያዘ ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው? ለምንስ?

20 በመጀመሪያው መቶ ዘመን፣ ኢየሱስ የመከሩ ሥራ ምን ያህል አጣዳፊ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ሐዋርያቱን ረድቷቸዋል። ከ1919 ወዲህም ኢየሱስ በዛሬው ጊዜ ያሉ ደቀ መዛሙርቱን ይህንኑ እውነታ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። የአምላክ ሕዝቦችም ሥራቸውን ይበልጥ አጠናክረው ቀጥለዋል። ደግሞም የመከሩን ሥራ ማንም ሊያስቆመው እንደማይችል ታይቷል። ነቢዩ ሚልክያስ አስቀድሞ እንደተናገረው በዛሬው ጊዜ የስብከቱ ሥራ “ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ” እየተካሄደ ነው። (ሚል. 1:11) በእርግጥም ከፀሐይ መውጫ አንስቶ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ይኸውም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያሉ ዘሪዎችና አጫጆች የሚኖሩት የትም ይሁን የት፣ በአንድ ላይ እየሠሩና እየተደሰቱ ነው። በተጨማሪም ከፀሐይ መውጫ እስከ ፀሐይ መግቢያ ድረስ ማለትም ከጠዋት እስከ ማታ ወይም ቀኑን ሙሉ በጥድፊያ ስሜት እንሠራለን።

21 ወደ 100 የሚጠጉ ዓመታት ወደኋላ መለስ ብለን ስንመለከት፣ ጥቂት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በዝተው “ኃያል ብሔር” እንደሆኑ ማወቃችን ‘ልባችን በኃይል እንዲመታና በደስታ እንዲሞላ’ ያደርጋል። (ኢሳ. 60:5, 22) ይህ ደስታ እንዲሁም “የመከሩ ሥራ ኃላፊ” ለሆነው ለይሖዋ ያለን ፍቅር ሁላችንም እስከ ዛሬ ከተካሄዱት ሁሉ በሚበልጠው ታላቅ የመከር ሥራ የበኩላችንን ድርሻ ለማበርከት ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል የሚያነሳሳን ይሁን!—ሉቃስ 10:2

a ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ” የተናገረው በርካታ ሳምራውያን ነጭ ልብስ ለብሰው ወደ እሱ እየመጡ መሆናቸውን ስለተመለከተ ሊሆን ይችላል።

b ስለ እነዚህ ዓመታትና ከዚያ በኋላ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ስለተከናወነው ነገር ለማወቅ የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 425-520 እንድታነብብ እናበረታታሃለን፤ እዚያ ላይ ከ1919 እስከ 1992 ባሉት ዓመታት ውስጥ የመከሩ ሥራ ምን ውጤት እንዳስገኘ የሚገልጽ ዘገባ ይገኛል።

c ይህን አስገራሚ ትንቢት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኢሳይያስ ትንቢት—ለመላው የሰው ዘር የፈነጠቀ ብርሃን፣ ጥራዝ 2 የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 303-320 ተመልከት።

d በቀደሙት ዘመናት የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ይህን ወሳኝ እውነት ተረድተው ነበር። የኅዳር 15, 1895 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “ጥቂት ስንዴ መሰብሰብ ከተቻለ ስለ እውነት ብዙ ምሥክርነት ተሰጥቷል ማለት ይቻላል። . . . ሁሉም ወንጌሉን መስበክ ይችላሉ።”