በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 10

ንጉሡ ሕዝቦቹን በመንፈሳዊ ያጠራቸዋል

ንጉሡ ሕዝቦቹን በመንፈሳዊ ያጠራቸዋል

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን በመንፈሳዊ ያጠራበትና ያነጻበት ምክንያት እንዲሁም ይህን ያደረገበት መንገድ

1-3. ኢየሱስ ቤተ መቅደሱን የሚያረክስ ነገር እየተከናወነ እንደሆነ ሲመለከት ምን እርምጃ ወሰደ?

 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ለነበረው ቤተ መቅደስ ታላቅ አክብሮት ነበረው፤ ምክንያቱም ይህ ቤተ መቅደስ ምንን እንደሚወክል ያውቅ ነበር። ቤተ መቅደሱ በምድር ላይ ያለው እውነተኛ አምልኮ ማዕከል ሆኖ ለረጅም ዘመናት አገልግሏል። ይሁንና ቅዱስ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ የሚቀርበው አምልኮ ንጹሕና ከርኩሰት የጸዳ መሆን አለበት። ኒሳን 10 ቀን 33 ዓ.ም. ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣበት ወቅት ግን ቤተ መቅደሱን የሚያረክሱ ነገሮች ሲከናወኑ ተመለከተ፤ በዚህ ወቅት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ኢየሱስ የተመለከተው ምን ነበር?—ማቴዎስ 21:12, 13ን አንብብ።

2 በአሕዛብ አደባባይ የነበሩት ስግብግብ ነጋዴዎችና ገንዘብ መንዛሪዎች፣ ለይሖዋ መሥዋዕት ለማቅረብ የሚመጡትን የአምላክ አገልጋዮች እየበዘበዟቸው ነበር። a ኢየሱስ “በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አባረረ፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎች . . . ገለባበጠ።” (ከነህምያ 13:7-9 ጋር አወዳድር።) እነዚህ ራስ ወዳድ ሰዎች የአባቱን ቤት “የዘራፊዎች ዋሻ” ስላደረጉት አወገዛቸው። ኢየሱስ ይህን ማድረጉ ለቤተ መቅደሱም ሆነ ቤተ መቅደሱ ለሚወክለው ነገር አክብሮት እንዳለው ያሳያል። ለአባቱ የሚቀርበው አምልኮ ምንጊዜም ንጹሕ መሆን አለበት!

3 ኢየሱስ ይህን ካደረገ ከበርካታ ዘመናት በኋላ ይኸውም ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ እንደገና አንድን ሌላ ቤተ መቅደስ አንጽቷል፤ ይህ የማንጻት ሥራ በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለክ የሚፈልጉ ሰዎችን ሁሉ የሚመለከት ነው። ታዲያ በዚያ ወቅት ያነጻው የትኛውን ቤተ መቅደስ ነው?

‘የሌዊን ልጆች ማንጻት’

4, 5. (ሀ) ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮቹን ያጠራቸውና ያነጻቸው እንዴት ነው? (ለ) የአምላክን ሕዝቦች የማጥራቱና የማንጻቱ ሥራ በዚያ ጊዜ አበቃ? አብራራ።

4 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው ኢየሱስ በ1914 ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ከአባቱ ጋር ሆኖ መንፈሳዊውን ቤት መቅደስ ይኸውም ለንጹሕ አምልኮ የተደረገውን ዝግጅት ለመመርመር መጥቷል። b ንጉሡ ይህን ምርመራ ሲያደርግ ‘የሌዊ ልጆች’ ይኸውም ቅቡዓን ክርስቲያኖች መጥራትና መንጻት እንደሚያስፈልጋቸው አስተዋለ። (ሚል. 3:1-3) አንጥረኛ የተባለው ይሖዋ፣ ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ ሕዝቦቹ እንዲጠሩና እንዲነጹ ለማድረግ ሲል በተለያዩ መከራዎችና ፈተናዎች ውስጥ እንዲያልፉ ፈቀደ። ደስ የሚለው ነገር እነዚያ ቅቡዓን፣ የደረሱባቸውን እንደ እሳት ከባድ የሆኑ ፈተናዎች በማለፍ ንጹሕ ሆኑ፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ለመሲሐዊው ንጉሥ ድጋፍ ለመስጠት ጓጉተው ነበር!

5 ታዲያ የአምላክ ሕዝቦችን የማጥራቱና የማንጻቱ ሥራ በዚህ አበቃ? አላበቃም። ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆኑ በመሲሐዊው ንጉሥ አማካኝነት ሲረዳቸው ቆይቷል፤ ንጽሕናቸውን መጠበቃቸው ከመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ እንዳይወጡ ይረዳቸዋል። ይሖዋ፣ ከሥነ ምግባርም ሆነ ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ ያጠራቸው እንዴት እንደሆነ በሚቀጥሉት ሁለት ምዕራፎች ላይ እንመረምራለን። እስቲ መጀመሪያ ስለ መንፈሳዊው የማንጻት ሥራ እንመልከት። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ ለመርዳት ሲል በግልጽ በሚታዩ መንገዶችም ሆነ እምብዛም በማይስተዋሉ መንገዶች ያከናወናቸውን ነገሮች መመልከቱ እምነታችንን የሚያጠናክር ነው።

“ንጽሕናችሁን ጠብቁ”

6. ይሖዋ፣ በባቢሎን በግዞት ለነበሩት አይሁዳውያን የሰጠው ትእዛዝ መንፈሳዊ ንጽሕና ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?

6 መንፈሳዊ ንጽሕና ሲባል ምን ማለት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በግዞት የነበሩት አይሁዳውያን በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ከባቢሎን ለመውጣት ሲዘጋጁ ይሖዋ ምን እንዳላቸው እንመርምር። (ኢሳይያስ 52:11ን አንብብ።) እነዚህ አይሁዳውያን ወደ ትውልድ አገራቸው ወደ ኢየሩሳሌም የሚመለሱበት ዋነኛ ዓላማ ቤተ መቅደሱን እንደገና መሥራትና እውነተኛውን አምልኮ መልሶ ማቋቋም ነው። (ዕዝራ 1:2-4) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ከባቢሎናውያን ሃይማኖት ጋር ከተያያዘ ከማንኛውም ነገር እንዲርቁ ፈልጎ ነበር። “ከዚያ ውጡ፣” “ማንኛውንም ርኩስ ነገር አትንኩ” እና “ንጽሕናችሁን ጠብቁ” የሚሉ ትእዛዞችን እንደሰጣቸው ልብ በል። ንጹሕ የሆነው የይሖዋ አምልኮ በሐሰት አምልኮ መበከል የለበትም። ታዲያ ከዚህ ምን እንረዳለን? በመንፈሳዊ ንጹሕ መሆን ሲባል ከሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችና ልማዶች ሙሉ በሙሉ መራቅ ማለት ነው።

7. ኢየሱስ፣ በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ እንዲሆኑ ተከታዮቹን የረዳቸው በማን አማካኝነት ነው?

7 ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ ብዙም ሳይቆይ፣ ተከታዮቹ በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ ለመርዳት የሚጠቀምበትን በግልጽ ተለይቶ የሚታወቅ መስመር አዘጋጀ። ይህ መስመር ክርስቶስ በ1919 የሾመው ታማኝና ልባም ባሪያ ነው። (ማቴ. 24:45) የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ እስከዚያ ዓመት ድረስ በርካታ የሐሰት ሃይማኖት ትምህርቶችን በማስወገድ ራሳቸውን አንጽተው ነበር። ያም ቢሆን በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ ለመሆን ሊያደርጉት የሚገባ ሌላም ነገር ነበር። ክርስቶስ በታማኙ ባሪያው አማካኝነት፣ ተከታዮቹ ሊያስወግዷቸው የሚገቡ የተለያዩ በዓላትና ልማዶች እንዳሉ ቀስ በቀስ እንዲገነዘቡ አድርጓል። (ምሳሌ 4:18) እስቲ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹን እንመልከት።

ክርስቲያኖች ገናን ማክበር ይኖርባቸዋል?

8. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ገናን በተመለከተ ከረጅም ጊዜ በፊት ምን ተገንዝበው ነበር? ይሁን እንጂ በግልጽ ያልተገነዘቡት ነገር ምንድን ነው?

8 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ገና ከአረማዊ አምልኮ የመጣ በዓል እንደሆነና ኢየሱስ ታኅሣሥ 25 እንዳልተወለደ ከተገነዘቡ ቆይተዋል። የታኅሣሥ 1881 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ የመጡት አረማዊ አምልኮን ትተው ነው። ይሁንና አብዛኞቹ ያደረጉት የስም ለውጥ ብቻ ነው፤ ምክንያቱም የአረማዊ አምልኮ ካህናት የክርስትና ካህናት ሆነዋል፤ አረማዊ በዓላትም ክርስቲያናዊ ስም ተሰጥቷቸዋል፤ ከእነዚህ በዓላት አንዱ ገና ነው።” በ1883 በወጣ አንድ መጠበቂያ ግንብ ላይ “ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነው?” የሚል ርዕስ የሚገኝ ሲሆን ይህ ርዕስ ኢየሱስ የተወለደው በጥቅምት ወር መጀመሪያ አካባቢ እንደሆነ የሚጠቁም ሐሳብ ይዟል። c ያም ቢሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ ገናን ማክበራቸውን ማቆም እንዳለባቸው በዚያ ወቅት በግልጽ አልተገነዘቡም ነበር። የብሩክሊን ቤቴል ቤተሰብ አባላትም እንኳ የገና በዓልን ማክበራቸውን ቀጥለው ነበር። ከ1926 በኋላ ግን ሁኔታዎች መቀየር ጀመሩ። ለምን?

9. የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ገናን በተመለከተ ምን ተገነዘቡ?

9 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ ጉዳዩን በጥንቃቄ ሲመረምሩ የገና በዓል አመጣጥም ሆነ ከዚህ በዓል ጋር የተያያዙት ልማዶች አምላክን የሚያስከብሩ እንዳልሆኑ ተገነዘቡ። በታኅሣሥ 14, 1927 ወርቃማው ዘመን ላይ የወጣው “የገና በዓል አመጣጥ” የሚለው ርዕስ ገና የአረማውያን በዓል እንደሆነ እንዲሁም በፈንጠዝያ ላይ ያተኮረና ጣዖት አምልኮን የሚያካትት ክብረ በዓል እንደሆነ ገልጾ ነበር። ይህ ርዕስ፣ ክርስቶስ ገናን እንድናከብር እንዳላዘዘ ከገለጸ በኋላ ገናን በተመለከተ የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቷል፦ “ይህ በዓል እንዲኖር የሚፈልጉትና እንዲከበር የሚያበረታቱት ዓለምና ሥጋችን እንዲሁም ዲያብሎስ መሆናቸው፣ ራሳቸውን ለይሖዋ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ የወሰኑ ሰዎች ይህን በዓል ሊያከብሩ እንደማይገባ የሚጠቁም ግልጽና የማያሻማ ማስረጃ ነው።” ከዚህ አንጻር የቤቴል ቤተሰብ አባላት፣ በዚያ ዓመትም ሆነ ከዚያ በኋላ የገናን በዓል አለማክበራቸው አያስገርምም!

10. (ሀ) ታኅሣሥ 1928 ስለ ገና እውነቱን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ ምን ትምህርት ወጣ? (“ የገና አመጣጥና ዓላማው” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።) (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ሊርቋቸው ስለሚገቡ ሌሎች በዓላት ማወቅ የቻሉት እንዴት ነው? (“ የሌሎች ክብረ በዓላትን አመጣጥ ማጋለጥ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 በቀጣዩ ዓመት ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ ገና እውነቱን ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ ትምህርት አገኙ። የዋናው መሥሪያ ቤት አባል የሆነው ወንድም ሪቻርድ ሃርቪ ባርበር የገና በዓል ርኩስ ከሆኑ ልማዶች የመጣ እንደሆነ የሚያብራራ ንግግር ታኅሣሥ 12, 1928 በሬዲዮ አቀረበ። የአምላክ ሕዝቦች ከዋናው መሥሪያ ቤት ለተላለፈው ለዚህ ግልጽ መመሪያ ምን ምላሽ ሰጡ? ወንድም ቻርልስ ብራንድላይን እሱና ቤተሰቡ የገናን በዓል ማክበር ያቆሙበትን ጊዜ አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ከአረማዊ አምልኮ የመጡትን ነገሮች ማስወገድ ከብዶን ነበር? በፍጹም! . . . ሁኔታው አንድን የቆሸሸ ልብስ አውልቆ እንደመጣል ነበር።” ከጊዜ በኋላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለው ወንድም ሄንሪ ካንትዌልም ተመሳሳይ ስሜት እንደነበረው ሲገልጽ “ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ለማሳየት ስንል አንድን ነገር መተዋችን አስደስቶን ነበር” ብሏል። የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግና ርኩስ ከሆነ አምልኮ የመጣውን ይህን በዓል ማክበራቸውን ለማቆም ፈቃደኞች ነበሩ። dዮሐ. 15:19፤ 17:14

11. መሲሐዊውን ንጉሥ እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

11 በእርግጥም እነዚያ ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ግሩም ምሳሌ ትተውልናል! እኛም በእነሱ ምሳሌ ላይ ማሰላሰልና እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቃችን አስፈላጊ ነው፦ ‘ከታማኙ ባሪያ የሚሰጠንን መመሪያ የምመለከተው እንዴት ነው? ለተሰጠኝ መመሪያ አመስጋኝ በመሆን የተማርኩትን ነገር ተግባራዊ አደርጋለሁ?’ መመሪያውን በፈቃደኝነት መታዘዛችን፣ በታማኝ ባሪያው አማካኝነት ወቅታዊ የሆነ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን ያለውን መሲሐዊ ንጉሥ እንደምንደግፍ ያሳያል።—ሥራ 16:4, 5

ክርስቲያኖች መስቀልን መጠቀም ይኖርባቸዋል?

መስቀልና ዘውድ ያለበት ምልክት (አንቀጽ 12ን እና 13ን ተመልከት)

12. ለበርካታ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ስለ መስቀል ያላቸው አመለካከት ምን ነበር?

12 ለበርካታ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ መስቀል ተቀባይነት ያለው የክርስትና ምልክት እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ የጣዖት አምልኮ ስህተት እንደሆነ ስለተገነዘቡ መስቀል ሊመለክ ይገባል የሚል እምነት አልነበራቸውም። (1 ቆሮ. 10:14፤ 1 ዮሐ. 5:21) የ1883 መጠበቂያ ግንብ “ማንኛውም የጣዖት አምልኮ በአምላክ ፊት አስጸያፊ ድርጊት ነው” የሚል ግልጽ ሐሳብ ይዞ ወጥቷል። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መጀመሪያ አካባቢ፣ መስቀልን ተገቢ ብለው ባሰቡት መንገድ መጠቀሙ ምንም ስህተት እንደሌለው ይሰማቸው ነበር። ለምሳሌ ማንነታቸውን ለማሳወቅ፣ መስቀልና ዘውድ ያለበት የደረት ጌጥ ያደርጉ ነበር። ይህ ምልክት፣ እስከ ሞት ታማኝ ከሆኑ የሕይወትን አክሊል እንደሚያገኙ የሚጠቁም እንደሆነ ይሰማቸው ነበር። መስቀልና ዘውድ ያለበት ምልክት ከ1891 አንስቶ መጠበቂያ ግንብ ሽፋን ላይ መውጣት ጀመረ።

13. የክርስቶስ ተከታዮች በመስቀል መጠቀምን በተመለከተ ምን ግንዛቤ አገኙ? (“ በመስቀል መጠቀምን በተመለከተ ቀስ በቀስ የተገኘ ትክክለኛ ግንዛቤ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

13 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ መስቀልና ዘውድ ያለበትን ምልክት ይወዱት ነበር። ከ1920ዎቹ መጨረሻ አካባቢ አንስቶ ግን የክርስቶስ ተከታዮች በመስቀል መጠቀምን በተመለከተ ቀስ በቀስ ትክክለኛ ግንዛቤ አገኙ። ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ግራንት ሱተር በ1928 በዲትሮይት፣ ሚሺገን፣ ዩናይትድ ስቴትስ የተደረገውን ትልቅ ስብሰባ አስታውሶ እንዲህ ብሏል፦ “መስቀልና ዘውድ ያለበት ምልክት አላስፈላጊ እንደሆነ እንዲያውም ጨርሶ ተገቢ እንዳልሆነ በዚያ ስብሰባ ላይ ተገለጸ።” በቀጣዮቹ ዓመታት ደግሞ ተጨማሪ እውቀት ተገኘ። ከርኩሰት የጸዳና በመንፈሳዊ ንጹሕ የሆነ አምልኮ ለማቅረብ ከፈለግን በመስቀል መጠቀማችንን ማቆም እንዳለብን ግልጽ ሆነ።

14. የአምላክ ሕዝቦች መስቀልን በተመለከተ ቀስ በቀስ ላገኙት ግንዛቤ ምን ምላሽ ሰጡ?

14 ታዲያ የአምላክ ሕዝቦች መስቀልን በተመለከተ ቀስ በቀስ ላገኙት ግንዛቤ ምን ምላሽ ሰጡ? ይወዱት የነበረውን መስቀልና ዘውድ ያለበትን ምልክት መጠቀማቸውን ቀጠሉ? ሊላ ሮበርትስ የተባለች ይሖዋን ለረጅም ዓመታት ያገለገለች እህት “[ይህ ምልክት] ምን እንደሚያመለክት ስንገነዘብ ለመተው አልተቸገርንም” በማለት ተናግራለች። ኧርሰላ ሰሬንኮ የተባለች ሌላ ታማኝ እህት ደግሞ እንዲህ በማለት የብዙዎችን ስሜት ገልጻለች፦ “የጌታችን ሞትና የክርስቲያናዊ ታማኝነታችን ምልክት እንደሆነ አድርገን በማሰብ በአንድ ወቅት ትልቅ ቦታ እንሰጠው የነበረው ነገር ከአረማዊ አምልኮ የመጣ ምልክት እንደሆነ ተገነዘብን። በምሳሌ 4:18 መሠረት መንገዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይበልጥ እየበራ በመሄዱ አመስጋኞች ነበርን።” የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች ርኩስ ከሆኑ የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዲኖራቸው አልፈለጉም!

15, 16. የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባዮች ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆኑ ማድረግ ቁርጥ ውሳኔያችን መሆኑን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

15 እኛም የእነዚህ ክርስቲያኖች ዓይነት አቋም አለን። ክርስቶስ ሕዝቡ ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ ለመርዳት ሲል በግልጽ ተለይቶ በሚታወቅ መስመር ይኸውም በታማኝና ልባም ባሪያው ሲጠቀም እንደቆየ እንገነዘባለን። በመሆኑም በሚቀርብልን መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት፣ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ስላላቸው በዓላትና ልማዶች ወይም ባሕሎች ማሳሰቢያ ሲሰጠን ታዛዥ በመሆን ወዲያውኑ ምክሩን ተግባራዊ እናደርጋለን። በክርስቶስ መገኘት መጀመሪያ አካባቢ እንደነበሩት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሁሉ እኛም የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባዮች ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆኑ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል።

16 ከዚህም በተጨማሪ በመጨረሻዎቹ ቀናት በሙሉ ክርስቶስ፣ የይሖዋ ሕዝቦችን ጉባኤ በመንፈሳዊ ሊበክሉ ከሚችሉ ግለሰቦች ለመጠበቅ እኛ እምብዛም በማናስተውለው ሁኔታ ሲሠራ ቆይቷል። ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

“ክፉዎችን ከጻድቃን” መለየት

17, 18. ስለ መረቡ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ (ሀ) የመረቡ መጣል (ለ) “የተለያየ ዓይነት ዓሣ” መሰብሰቡ (ሐ) ጥሩ ጥሩው ዓሣ ተለይቶ በዕቃ ውስጥ መቀመጡ እንዲሁም (መ) መጥፎ መጥፎው ዓሣ መጣሉ ምን ያመለክታል?

17 ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ በምድር ዙሪያ ያሉትን የአምላክ ሕዝቦች ጉባኤዎች ሁኔታ በትኩረት ይከታተላል። ክርስቶስና መላእክት፣ እኛ ሙሉ በሙሉ ልንረዳው በማንችለው መንገድ የመለየቱን ሥራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ኢየሱስ ይህን ሥራ ስለ መረቡ በተናገረው ምሳሌ ላይ ጠቅሶታል። (ማቴዎስ 13:47-50ን አንብብ።) ይህ ምሳሌ ምን ትርጉም አለው?

መረቡ፣ በሰው ዘር ባሕር ውስጥ የሚከናወነውን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ያመለክታል (አንቀጽ 18ን ተመልከት)

18 ‘መረቡን ወደ ባሕር መጣል።’ መረቡ፣ በሰው ዘር ባሕር ውስጥ የሚከናወነውን የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ያመለክታል። “የተለያየ ዓይነት ዓሣ” መሰብሰብ። ምሥራቹ የተለያዩ ዓይነት ሰዎችን ይኸውም እርምጃ ወስደው እውነተኛ ክርስቲያን የሚሆኑ ግለሰቦችንና መጀመሪያ ላይ ለመልእክቱ የተወሰነ ፍላጎት ቢያሳዩም ከእውነተኛው አምልኮ ጎን ለመቆም እርምጃ የማይወስዱ በርካታ ሰዎችን ይስባል። e “ጥሩ ጥሩውን እየለዩ በዕቃ ውስጥ” ማስቀመጥ። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በዕቃ ወደተመሰሉት የክርስቲያን ጉባኤዎች የሚሰበሰቡ ሲሆን በዚያም ለይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ያቀርባሉ።“መጥፎ መጥፎውን” ዓሣ መጣል። በመጨረሻዎቹ ቀናት በሙሉ ክርስቶስና መላእክት፣ “ክፉዎችን ከጻድቃን” ሲለዩ ቆይተዋል። f ይህም ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የሌላቸው ሰዎች ማለትም የተሳሳቱ እምነቶችንና ልማዶችን ለመተው ፈቃደኛ ያልሆኑ ግለሰቦች ጉባኤዎችን እንዳይበክሉ ለማድረግ አስችሏል! g

19. ክርስቶስ፣ የአምላክ ሕዝቦች ምንጊዜም ንጹሕ እንዲሆኑ ለማድረግና የእውነተኛው አምልኮ ንጽሕና እንዳይበከል ለመከላከል እርምጃ በመውሰዱ ምን ይሰማሃል?

19 ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእሱ ሥር ያሉትን እንደሚጠብቃቸው ማወቁ የሚያጽናና አይደለም? በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. ቤተ መቅደሱን ሲያነጻ ለእውነተኛ አምልኮ እና ለእውነተኛ አምላኪዎች የነበረው ዓይነት ቅንዓት አሁንም እንዳለው ማወቁስ የሚያበረታታ አይደለም? ክርስቶስ፣ የአምላክ ሕዝቦች ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ ለማድረግና የእውነተኛው አምልኮ ንጽሕና እንዳይበከል ለመከላከል እርምጃ በመውሰዱ ምንኛ አመስጋኞች ነን! እኛም ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳይኖረን በመጠንቀቅ ንጉሡንና መንግሥቱን እንደምንደግፍ እናሳያለን።

a ከሌሎች አገሮች ወደ ቤተ መቅደሱ የሚመጡ አይሁዳውያን የቤተ መቅደሱን ዓመታዊ ግብር የሚከፍሉት በአካባቢው በሚሠራበት ገንዘብ መሆን ነበረበት፤ በመሆኑም ገንዘብ መንዛሪዎች የተወሰነ ዋጋ በማስከፈል ገንዘባቸውን ይቀይሩላቸው ነበር። በተጨማሪም ሰዎቹ መሥዋዕት ለማቅረብ እንስሳት መግዛት ያስፈልጋቸው ይሆናል። ኢየሱስ ነጋዴዎቹን “ዘራፊዎች” በማለት የጠራቸው ለሚሰጡት አገልግሎት በጣም የተጋነነ ዋጋ ይጠይቁ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም።

b በምድር ላይ ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ይሖዋን የሚያመልኩት በታላቁ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ነው።

c ይህ ርዕስ፣ ኢየሱስ በቅዝቃዜው ወቅት እንደተወለደ የሚገልጸው ሐሳብ “እረኞች ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ እንዳደሩ ከሚናገረው ዘገባ ጋር እንደማይስማማ” ገልጿል።—ሉቃስ 2:8

d ወንድም ፍሬድሪክ ዊልያም ፍራንዝ ኅዳር 14, 1927 በጻፈው ደብዳቤ ላይ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ ዓመት ገናን አናከብርም። የቤቴል ቤተሰብ ገናን ላለማክበር ወስኗል።” ወንድም ፍራንዝ ከጥቂት ወራት በኋላ ማለትም የካቲት 6, 1928 በጻፈው ደብዳቤ ላይ “ጌታ፣ የዲያብሎስ ድርጅት ከሆነችው ከባቢሎን ስህተቶች ቀስ በቀስ እንድንነጻ አድርጓል” ብሎ ነበር።

e ለምሳሌ ያህል፣ በ2013 ከፍተኛው የአስፋፊዎች ቁጥር 7,965,954 ሲሆን በዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙት ሰዎች 19,241,252 ያህል ነበሩ።

f ጥሩውን ዓሣ ከመጥፎው ዓሣ የመለየቱ ሥራ በጎችን ከፍየሎቹ ከመለየቱ ሥራ ጋር አንድ አይደለም። (ማቴ. 25:31-46) በጎቹ ከፍየሎቹ የሚለዩት ማለትም የመጨረሻው ፍርድ የሚከናወነው በመጪው ታላቅ መከራ ወቅት ነው። እስከዚያው ድረስ ግን በመጥፎ ዓሣ የተመሰሉት ሰዎች ወደ ይሖዋ መመለስና በዕቃ በተመሰሉት ጉባኤዎች ውስጥ መሰብሰብ ይችላሉ።—ሚል. 3:7

g መጥፎዎቹ ዓሦች ውሎ አድሮ ወደ እቶን እሳት ይጣላሉ፤ ይህ ወደፊት የሚጠብቃቸውን ጥፋት ያመለክታል።