በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 11

የአምላክን ቅድስና የሚያንጸባርቅ ሥነ ምግባራዊ የማጥራት ሥራ

የአምላክን ቅድስና የሚያንጸባርቅ ሥነ ምግባራዊ የማጥራት ሥራ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ንጉሡ፣ ተገዢዎቹ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲያከብሩ ያስተማረበት መንገድ

ወደ ታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ውጨኛ ግቢ በሚያስገባው በር ስትገባ በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ

1. ሕዝቅኤል የተመለከተው በአድናቆት እንድንዋጥ የሚያደርግ ራእይ ምንድን ነው?

 ነቢዩ ሕዝቅኤል ከ2,500 ዓመታት በፊት የተመለከተው ዓይነት ራእይ የማየት አጋጣሚ ብታገኝ ምን ይሰማሃል? የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፦ ወደ አንድ ግዙፍና አንጸባራቂ ቤተ መቅደስ እየገባህ ነው እንበል። አንድ ኃያል መልአክ ይህን እጅግ አስደናቂ ቦታ ሊያስጎበኝህ ተዘጋጅቷል። ሰባት ደረጃዎችን ከወጣህ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ ከሚያስገቡት ሦስት በሮች ወደ አንዱ ትደርሳለህ። የቤተ መቅደሱ መግቢያዎች በጣም ያስደምሙሃል። እስከ ጣሪያው ያለው ከፍታ 30 ሜትር ያህል ነው። በሩን አልፈህ ስትገባ የዘብ ጠባቂ ክፍሎች ታያለህ። ዓምዶቹ የዘንባባ ዛፍ ምስሎች በሚያምር መንገድ ተቀርጸውባቸው ነበር።—ሕዝ. 40:1-4, 10, 14, 16, 22፤ 41:20

2. (ሀ) ሕዝቅኤል በራእይ ያየው ቤተ መቅደስ ምን ያመለክታል? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።) (ለ) የቤተ መቅደሱ መግቢያዎች ምን ትርጉም አላቸው?

2 እየተነጋገርን ያለነው ሕዝቅኤል ከመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ጋር በተያያዘ ስለተመለከተው ትንቢታዊ ራእይ ነው። ሕዝቅኤል ይህን ቤተ መቅደስ በተመለከተ ዝርዝር ሐሳቦች ስለጻፈ ከምዕራፍ 40 እስከ ምዕራፍ 48 ያሉት ምዕራፎች የሚያወሱት ስለዚህ ራእይ ነው። ይህ ቤተ መቅደስ ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ያደረገውን ዝግጅት ያመለክታል። እያንዳንዱ የቤተ መቅደሱ ገጽታ በመጨረሻዎቹ ቀናት ከምናቀርበው አምልኮ ጋር የተያያዘ ነው። a ግዙፍ የሆኑት የቤተ መቅደሱ መግቢያዎች ምን ያመለክታሉ? ወደ ቤተ መቅደሱ የሚገቡ ይኸውም ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት የሚካፈሉ ሁሉ፣ ላቅ ካሉትና በጽድቅ ላይ ከተመሠረቱት የአምላክ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ እንዳለባቸው እንድናስታውስ ያደርጉናል። የዘንባባ ዛፎቹ ምስልም ተመሳሳይ መልእክት ያስተላልፋል፤ ምክንያቱም የዘንባባ ዛፎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽድቅን ለማመልከት የተሠራባቸው ጊዜያት አሉ። (መዝ. 92:12) የዘብ ቤቶቹስ የሚያስተላልፉት መልእክት ምንድን ነው? መለኮታዊ መሥፈርቶችን የማያሟሉ ሰዎች ወደዚህ ቤተ መቅደስ እንዲገቡ ይኸውም አስደናቂ በሆነውና ሕይወት በሚያስገኘው በዚህ የንጹሕ አምልኮ ዝግጅት እንዲካፈሉ እንደማይፈቀድላቸው ያሳያሉ።—ሕዝ. 44:9

3. የክርስቶስ ተከታዮች ቀጣይ በሆነ መልኩ መጥራት ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

3 ሕዝቅኤል ያየው ራእይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው? በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ አካባቢ ባለው ጊዜ ውስጥ በክርስቶስ አማካኝነት ሕዝቦቹን ለየት ባለ መንገድ አጥርቷቸዋል። ታዲያ የማጥራቱ ሥራ በዚያ ጊዜ አብቅቷል? በፍጹም! ባለፈው ምዕተ ዓመት ውስጥ ክርስቶስ፣ ቅዱስ የሆኑት የይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲጠበቁ ሲያደርግ ቆይቷል። ተከታዮቹ ቀጣይ በሆነ መልኩ መጥራት አስፈልጓቸዋል። ለምን? ክርስቶስ ተከታዮቹን እየሰበሰበ ያለው በሥነ ምግባር ብልሹ ከሆነው ከዚህ ዓለም ውስጥ ስለሆነ እንዲሁም ሰይጣን እነዚህን ሰዎች በሥነ ምግባር ወደዘቀጠው ዓለም ለመመለስ ጥረት ከማድረግ ምንጊዜም ስለማይቦዝን ነው። (2 ጴጥሮስ 2:20-22ን አንብብ።) እስቲ ክርስቶስ፣ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ቀጣይ በሆነ መንገድ ያጠራባቸውን ሦስት አቅጣጫዎች እንመልከት። በመጀመሪያ በሥነ ምግባር ረገድ ስለተከናወነ የማጥራት ሥራ እንመለከታለን፤ ከዚያም ጉባኤው ንጹሕ ሆኖ እንዲቀጥል ስለተደረገው አስፈላጊ ዝግጅት እንመረምራለን፤ በመጨረሻም ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ ዝግጅቶችን እንመለከታለን።

ባለፉት ዓመታት የተካሄደ ሥነ ምግባራዊ የማጥራት ሥራ

4, 5. ሰይጣን ለረጅም ጊዜ የትኛውን ዘዴ ሲጠቀም ቆይቷል? ምን ስኬትስ አግኝቷል?

4 የይሖዋ ሕዝቦች፣ መልካምና ትክክለኛ ሥነ ምግባር መያዝን ምንጊዜም ቢሆን ትልቅ ቦታ ይሰጡታል። በመሆኑም በዚህ ጉዳይ ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሰጣቸውን ግልጽ የሆነ መመሪያ ተቀብለዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

5 የፆታ ብልግና። የይሖዋ ዓላማ የፆታ ግንኙነት በተጋቡ ሰዎች መካከል ንጹሕና አስደሳች በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ነው። ሰይጣን ግን ይህን አስደሳች የአምላክ ስጦታ ተገቢ ባልሆነና ወራዳ በሆነ መንገድ እንድንጠቀምበት ይፈልጋል፤ በዚህ ስጦታ ተጠቅሞ የይሖዋን ሕዝቦች በመፈተን የአምላክን ሞገስ እንዲያጡ ለማድረግ ይጥራል። ሰይጣን በዚህ ዘዴ በመጠቀም ረገድ በበለዓም ዘመን የተሳካለት ሲሆን ይህም አስከፊ መዘዝ አስከትሏል፤ በመጨረሻዎቹ ቀናት ይህን ዘዴ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እየተጠቀመበት ነው።—ዘኁ. 25:1-3, 9፤ ራእይ 2:14

6. መጠበቂያ ግንብ ላይ ምን የሚል ቃለ መሐላ ወጥቶ ነበር? የአምላክ ሕዝቦች እንዴት ይጠቀሙበት ነበር? ከጊዜ በኋላ የቀረውስ ለምንድን ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)

6 ይህንን የሰይጣን ጥረት ለማክሸፍ ሲባል የሰኔ 15, 1908 መጠበቂያ ግንብ ላይ የሚከተለው ቃለ መሐላ ወጥቶ ነበር፦ “በማንኛውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ከተቃራኒ ፆታ ጋር ብቻዬን ስሆን፣ ሌሎች ሰዎች ባሉበት የማላደርገውን ነገር አላደርግም።” b ይህን ቃለ መሐላ መግባት ግዴታ ባይሆንም ብዙዎች እንዲህ ያደረጉ ከመሆኑም ሌላ ቃለ መሐላውን መቀበላቸውን ለማሳየት በጽዮን በመጠበቂያ ግንብ ላይ በሚወጣው ዝርዝር ውስጥ እንዲካተት ስማቸውን ሰጥተዋል። ይህ ቃለ መሐላ በዚያን ጊዜ የነበሩትን በርካታ ሰዎች የጠቀማቸው ቢሆንም ለደንቡ ያህል ብቻ የሚደረግ ልማድ እየሆነ መምጣቱ ከጊዜ በኋላ ተስተዋለ፤ በመሆኑም እንዲቀር ተደረገ። ያም ቢሆን የይሖዋ ሕዝቦች ከዚህ ቃለ መሐላ በስተ ጀርባ ያሉትን ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምንጊዜም ይከተላሉ።

7. በ1935 መጠበቂያ ግንብ ላይ ስለ የትኛው ችግር ተጠቅሶ ነበር? ክርስቲያኖች የትኛውን መሥፈርት መጠበቅ እንዳለባቸውስ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል?

7 የሰይጣን ጥቃት ግን ተፋፍሞ ቀጠለ። የመጋቢት 1, 1935 መጠበቂያ ግንብ በአምላክ ሕዝቦች መካከል እየተስፋፋ ስለመጣ አንድ ችግር በግልጽ ጠቅሶ ነበር። አንዳንዶች በአገልግሎት እስከተካፈሉ ድረስ በግል ሕይወታቸው የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጠበቅ እንደማያስፈልጋቸው ተሰምቷቸው የነበረ ይመስላል። መጠበቂያ ግንቡ የሚከተለውን ሐሳብ ይዞ ነበር፦ “አንድ ክርስቲያን፣ ከእሱ የሚጠበቀው በምሥክርነቱ ሥራ መካፈል ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርበታል። የይሖዋ ምሥክሮች የእሱ ወኪሎች ናቸው፤ በመሆኑም ይሖዋን እና መንግሥቱን በሚያስከብር መንገድ የመመላለስ ኃላፊነት አለባቸው።” ይህ መጠበቂያ ግንብ ጋብቻንና የፆታ ሥነ ምግባርን በተመለከተ ግልጽ ምክር የሰጠ ሲሆን ይህም የአምላክ ሕዝቦች ‘ከፆታ ብልግና እንዲሸሹ’ ረድቷቸዋል።—1 ቆሮ. 6:18

8. የፆታ ብልግናን የሚያመለክተው የግሪክኛ ቃል ምን ነገሮችን እንደሚያካትት በመጠበቂያ ግንብ ላይ በተደጋጋሚ ጎላ ተደርጎ የተገለጸው ለምንድን ነው?

8 በግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የፆታ ብልግናን ለማመልከት የተሠራበት ፖርኒያ የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ምን እንደሆነ ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ በመጠበቂያ ግንብ ላይ በተደጋጋሚ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ቃሉ የፆታ ግንኙነትን ብቻ የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ፖርኒያ የሚለው ቃል ሥነ ምግባር የጎደላቸውን የተለያዩ ድርጊቶች፣ በጥቅሉ በዝሙት አዳሪ ቤቶች የሚፈጸሙትን የብልግና ድርጊቶች በሙሉ ያመለክታል። የክርስቶስ ተከታዮች ይህን በማወቃቸው በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ወረርሽኝ ከተስፋፋው ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የፆታ ብልግና መጠበቅ ችለዋል።—ኤፌሶን 4:17-19ን አንብብ።

9, 10. (ሀ) የ1935 መጠበቂያ ግንብ ከሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ስለ የትኛው ጉዳይ አንስቶ ነበር? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ ከአልኮል አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ምን ሚዛናዊ ትምህርት ይሰጣል?

9 አልኮልን ያላግባብ መጠቀም። የመጋቢት 1, 1935 መጠበቂያ ግንብ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ሌላም ጉዳይ አንስቶ ነበር፤ መጠበቂያ ግንቡ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶች የአልኮል መጠጥ ጠጥተው በአገልግሎት እንደሚካፈሉና በድርጅቱ ውስጥ ያሏቸውን ሌሎች ኃላፊነቶች እንደሚያከናውኑ ተስተውሏል። በቅዱሳን መጻሕፍት መሠረት ወይን መጠጣት ተገቢ የሚሆነው መቼ ነው? አንድ ሰው በጌታ ድርጅት ውስጥ የሚያከናውነውን አገልግሎት እስከሚያስተጓጉልበት ድረስ ወይን መጠጣቱ ተገቢ ነው?”

10 ለእነዚህ ጥያቄዎች የተሰጠው መልስ፣ የአምላክ ቃል የአልኮል መጠጦችን በተመለከተ ሊኖረን ስለሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት ምን እንደሚል የሚያብራራ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወይንንም ሆነ ሌሎች የአልኮል መጠጦችን መጠጣትን አይከለክልም፤ ሆኖም ስካርን በጥብቅ ያወግዛል። (መዝ. 104:14, 15፤ 1 ቆሮ. 6:9, 10) አልኮል ጠጥቶ በቅዱስ አገልግሎት መካፈልን በተመለከተ የአምላክ አገልጋዮች ስለ አሮን ልጆች የሚገልጸውን ዘገባ እንዲያስታውሱ ተበረታትተዋል፤ የአሮን ልጆች በአምላክ መሠዊያ ላይ ያልተፈቀደውን እሳት በማቅረባቸው አምላክ በሞት ቀጥቷቸዋል። ይህ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ አምላክ፣ ካህናቱ በሙሉ በቅዱስ አገልግሎት በሚካፈሉበት ጊዜ የአልኮል መጠጥ እንዳይጠጡ የሚከለክል ሕግ መስጠቱ የአሮን ልጆች ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። (ዘሌ. 10:1, 2, 8-11) በዛሬው ጊዜ ያሉ የክርስቶስ ተከታዮችም ይህን መሠረታዊ ሥርዓት ግምት ውስጥ በማስገባት ቅዱስ አገልግሎት በሚያከናውኑበት ጊዜ ከአልኮል መጠጥ ጋር በተያያዘ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ያደርጋሉ።

11. የአምላክ ሕዝቦች የአልኮል ሱስን በተመለከተ ተጨማሪ ግንዛቤ ማግኘታቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?

11 ከቅርብ አሥርተ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የክርስቶስ ተከታዮች የአልኮል ሱስን በተመለከተ ተጨማሪ ግንዛቤ አግኝተዋል፤ አንድ ሰው የአልኮል ሱስ አለበት የሚባለው ከመጠን በላይ የመጠጣት ልማድ ካለውና ይህን ልማዱን ማቆም ካቃተው ነው። በሚያስፈልገን ወቅት ለምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ ምስጋና ይግባውና ብዙዎች ለዚህ ችግር መፍትሔ ማግኘትና አልኮል እንዳይቆጣጠራቸው ማድረግ ችለዋል። የሚሰጠን ትምህርት፣ ሌሎች ብዙዎችን ደግሞ እንዲህ ያለውን መጥፎ ልማድ ከማዳበር እንዲጠበቁ ረድቷቸዋል። ማንኛውም ክርስቲያን አልኮልን ያላግባብ መጠቀም ክብሩን እንዳያሳጣው፣ ቤተሰቡን እንዳይበትንበት ከሁሉ በላይ ደግሞ በይሖዋ ንጹሕ አምልኮ የመካፈል መብቱን እንዳያሳጣው መጠንቀቅ ይኖርበታል።

“ጌታችን፣ ትንባሆ ትንባሆ ይሸት ወይም ማንኛውንም የሚያረክስ ነገር ወደ አፉ ያስገባ ነበር ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።” —ቻርልስ ቴዝ ራስል

12. የክርስቶስ አገልጋዮች የመጨረሻዎቹ ቀናት ከመጀመራቸው በፊትም ቢሆን ትንባሆ ስለ መጠቀም ምን አመለካከት ነበራቸው?

12 ትንባሆ መጠቀም። የክርስቶስ አገልጋዮች የመጨረሻዎቹ ቀናት ከመጀመራቸው በፊትም ቢሆን ትንባሆ መጠቀምን ያወግዙ ነበር። ቻርልስ ኬፐን የተባሉ አረጋዊ ወንድም በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ከቻርልስ ቴዝ ራስል ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበትን ወቅት ያስታውሳሉ። በወቅቱ የ13 ዓመት ልጅ የነበሩት ወንድም ኬፐን ከሦስት ወንድሞቻቸው ጋር ሆነው በአሌጌኒ፣ ፔንስልቬንያ በሚገኘውና የመጽሐፍ ቅዱስ ቤት ተብሎ በሚጠራው ሕንጻ ደረጃ ላይ ከወንድም ራስል ጋር ተገናኙ። ወንድም ራስል በአጠገባቸው ሲያልፍ “ትንባሆ ይሸተኛል፤ እናንተ ልጆች ታጨሳላችሁ እንዴ?” አላቸው። እነሱም እንደማያጨሱ ገለጹለት። ይህ አጋጣሚ ወንድም ራስል ስለ ትንባሆ ምን አመለካከት እንዳለው በግልጽ እንዳስገነዘባቸው ጥርጥር የለውም። በነሐሴ 1, 1895 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወንድም ራስል 2 ቆሮንቶስ 7:1⁠ን አስመልክቶ እንዲህ የሚል ሐሳብ ሰጥቶ ነበር፦ “አንድ ክርስቲያን በማንኛውም መልኩ ትንባሆ መውሰዱ ለአምላክ ክብር የሚያመጣውም ሆነ ራሱን የሚጠቅመው እንዴት እንደሆነ መረዳት ያዳግተኛል። . . . ጌታችን፣ ትንባሆ ትንባሆ ይሸት ወይም ማንኛውንም የሚያረክስ ነገር ወደ አፉ ያስገባ ነበር ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።”

13. በ1973 በሥነ ምግባር ረገድ ይበልጥ እንድንጠራ የሚያደርግ ምን ትምህርት ወጣ?

13 በ1935 በወጣ መጠበቂያ ግንብ ላይ ትንባሆ “ቆሻሻ አረም” ተብሎ የተጠራ ሲሆን ትንባሆ የሚያኝክ ወይም የሚያጨስ ማንኛውም ክርስቲያን የቤቴል ቤተሰብ አባል መሆን አሊያም የአምላክን ድርጅት ወክሎ አቅኚ ወይም ተጓዥ አገልጋይ መሆን እንደማይችል ተገለጸ። በ1973 ደግሞ በሥነ ምግባር ረገድ ይበልጥ እንድንጠራ የሚያደርግ ትምህርት ወጣ። የሰኔ 1 መጠበቂያ ግንብ የትኛውም የይሖዋ ምሥክር ይህንን ገዳይ፣ የሚያረክስና ፍቅር የማይንጸባረቅበት ልማድ ይዞ በጉባኤ ውስጥ ጥሩ አቋም አለው ሊባል እንደማይችል ገለጸ። ትንባሆን ያላግባብ መጠቀማቸውን ለማቆም ፈቃደኛ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ከጉባኤው እንዲወገዱ ይደረግ ጀመር። c በዚህ መንገድ ክርስቶስ፣ ተከታዮቹን ለማጥራት ሌላ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ወስዷል።

14. ደምን በተመለከተ አምላክ ምን መመሪያ ሰጥቷል? ለሰዎች ደም መስጠት የተለመደ ሕክምና ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

14 ደምን ያላግባብ መጠቀም። በኖኅ ዘመን አምላክ፣ ደም መብላት ስህተት እንደሆነ ተናግሮ ነበር። ለእስራኤል ብሔር በሰጠው ሕግ ላይ ይህን መመሪያ የደገመው ሲሆን የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም “ከደም እንዲርቁ” ታዝዘዋል። (ሥራ 15:20, 29፤ ዘፍ. 9:4፤ ዘሌ. 7:26) ሰይጣን ግን በዘመናችን ብዙዎች ይህንን መለኮታዊ መመሪያ እንዲጥሱ የሚያደርግ ዘዴ ፈጥሯል። ሐኪሞች በ19ኛው መቶ ዘመን ለታካሚዎች ደም ከመስጠት ጋር በተያያዘ ምርምር እያደረጉ ነበር፤ የተለያዩ የደም ዓይነቶች እንዳሉ ከታወቀ በኋላ ግን ይህ ዘዴ በስፋት ይሠራበት ጀመር። በ1937 የለጋሾችን ደም፣ በደም ባንኮች ውስጥ ማስቀመጥ የተጀመረ ሲሆን ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ለታካሚዎች ደም የመስጠት ሕክምና እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ ይህ የሕክምና ዘዴ በዓለም ዙሪያ የተለመደ ሆነ።

15, 16. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ደም መውሰድን በተመለከተ ምን አቋም አላቸው? (ለ) ከደም እና ያለ ደም ከሚሰጡ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ የክርስቶስ ተከታዮች ምን ዓይነት እገዛ ተደርጎላቸዋል? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?

15 ደም መውሰድ፣ ደም ከመብላት ተለይቶ እንደማይታይ በ1944 እንኳ መጠበቂያ ግንብ ላይ ተገልጾ ነበር። በቀጣዩ ዓመት ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ይበልጥ የሚያጠናክርና ግልጽ የሚያደርግ ሐሳብ ወጣ። በ1951 የአምላክ ሕዝቦች ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ሲነጋገሩ ሊረዷቸው የሚችሉ በርካታ ጥያቄዎችንና መልሶችን የያዘ ሐሳብ መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል። በዓለም ዙሪያ ያሉ የክርስቶስ ታማኝ ተከታዮች በዚህ ረገድ በድፍረት አቋማቸውን ጠብቀዋል፤ በዚህ ምክንያት ብዙውን ጊዜ ፌዝ ያጋጥማቸው፣ ይጠሉ አልፎ ተርፎም ቀጥተኛ ስደት ይደርስባቸው ነበር። ይሁንና ክርስቶስ፣ ድርጅቱ ለሕዝቦቹ የሚያስፈልገውን እገዛ እንዲያቀርብ መርዳቱን ቀጥሏል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዝርዝር መረጃዎችን የያዙና ጥልቅ ምርምር የተደረገባቸው ብሮሹሮችና ርዕሶች ወጥተዋል።

16 በ1979 አንዳንድ የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ወደ ሆስፒታሎች በመሄድ ሐኪሞችን ማነጋገር ጀመሩ፤ ወንድሞች እንዲህ ማድረጋቸው በርካታ ሐኪሞች ስለ ደም ያለንን አቋም፣ ይህን አቋም እንድንይዝ ያደረገንን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማስረጃ እንዲሁም በደም ምትክ የሚሰጡ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን ይበልጥ እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። በ1980 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ39 ከተሞች የሚገኙ ሽማግሌዎች ለዚህ ሥራ ልዩ ሥልጠና ተሰጣቸው። ከጊዜ በኋላ የበላይ አካሉ በዓለም ዙሪያ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች እንዲቋቋሙ ፈቃድ ሰጠ። እንዲህ ያለ ጥረት መደረጉ ባለፉት ዓመታት ያስገኘው ለውጥ አለ? በአሁኑ ጊዜ ዶክተሮችን፣ የቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን እና ማደንዘዣ የሚሰጡ ሐኪሞችን ጨምሮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ የሕክምና ባለሙያዎች የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ታካሚዎችን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው፤ ያለ ደም ለመታከም ያደረጉትን ውሳኔ እንደሚያከብሩላቸው በዚህ መንገድ አሳይተዋል። ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሆስፒታሎች ያለ ደም ሕክምና የሚሰጡ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ እንዲህ ያለውን ሕክምና ከሁሉ የተሻለው የሕክምና ዘዴ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል። ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን ሰይጣን እንዳይበክላቸው ለመከላከል ሲል ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ማወቁ የሚያስደስት አይደለም?—ኤፌሶን 5:25-27ን አንብብ።

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሆስፒታሎች ያለ ደም ሕክምና የሚሰጡ ሲሆን እንዲያውም አንዳንዶቹ እንዲህ ያለውን ሕክምና ከሁሉ የተሻለው የሕክምና ዘዴ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል

17. ክርስቶስ፣ ተከታዮቹን ለማጥራት የወሰዳቸውን እርምጃዎች እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 እንግዲያው ‘ክርስቶስ ተከታዮቹን በማጥራት የይሖዋን ከፍ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች በጥብቅ እንድንከተል እኛን ለማሠልጠን ላደረገው ዝግጅት አድናቆት አለን?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ሰይጣን፣ አምላክ ያወጣቸውን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አቅልለን እንድንመለከት በማድረግ እኛን ከይሖዋና ከኢየሱስ ለማራቅ ጥረት ማድረጉን እንደማያቋርጥ ምንጊዜም መዘንጋት የለብንም። ይህንን ተጽዕኖ መቋቋም እንድንችል የይሖዋ ድርጅት ይህ ዓለም ምን ያህል በሥነ ምግባር እየተበላሸ እንደሆነ አዘውትሮ ማሳሰቢያዎችና ማስጠንቀቂያዎች እየሰጠን ነው። እንዲህ ያለውን ፍቅር የሚንጸባረቅበትና ጠቃሚ ምክር በንቃት በመከታተል በአፋጣኝ እርምጃ እንውሰድ።—ምሳሌ 19:20

ጉባኤውን ከሥነ ምግባራዊ ነቀፋ መጠበቅ

18. የአምላክን መሥፈርቶች ሆን ብለው ከሚጥሱ ሰዎች ጋር በተያያዘ የሕዝቅኤል ራእይ ምን ይጠቁመናል?

18 በሥነ ምግባር ረገድ የማጥራት ሥራ የተካሄደበት ሁለተኛው አቅጣጫ የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ጋር የተያያዘ ነው። የይሖዋን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተቀብለው ራሳቸውን ለአምላክ ከወሰኑት ሰዎች መካከል ከእሱ ጎን በታማኝነት ጸንተው የማይቀጥሉ መኖራቸው የሚያሳዝን ነው። አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ አቋማቸውን በመለወጥ እነዚህን መሥፈርቶች ሆን ብለው ይጥሳሉ። ታዲያ እንዲህ ያሉ ሰዎች ምን እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል? በዚህ ምዕራፍ መግቢያ ላይ ያነሳነው ሕዝቅኤል በራእይ የተመለከተው መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ በዚህ ረገድ ፍንጭ ይሰጠናል። እነዚያን ግዙፍ መግቢያዎች አስታውስ። በእያንዳንዱ መግቢያ ላይ የዘብ ቤቶች አሉ። ጠባቂዎቹ በዚያ የቆሙት “ልቡን . . . ያልተገረዘ” ሰው ወደ ቤተ መቀደሱ እንዳይገባ ለመከልከል እንደሆነ ግልጽ ነው። (ሕዝ. 44:9) ይህ ሁኔታ፣ ወደ እውነተኛው አምልኮ መምጣት በይሖዋ ንጹሕ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መሠረት ለሚመላለሱ ብቻ የሚሰጥ መብት እንደሆነ በግልጽ ይጠቁመናል። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ሆኖ ይሖዋን ማምለክ ማንኛውም ሰው የሚያገኘው መብት አይደለም።

19, 20. (ሀ) ክርስቶስ፣ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎች ጉዳይ የሚታይበትን መንገድ በተመለከተ ተከታዮቹ የተሻለ አሠራር እንዲከተሉ ቀስ በቀስ የረዳቸው እንዴት ነው? (ለ) ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች እንዲወገዱ የሚደረጉባቸው ሦስት ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

19 በ1892 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “ክርስቶስ ራሱን ለሁሉም ሰው ቤዛ [ተመጣጣኝ ክፍያ] አድርጎ መስጠቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚክዱ ክርስቲያኖችን የማስወገድ ኃላፊነት አለብን።” (2 ዮሐንስ 10ን አንብብ።) በ1904 አዲስ ፍጥረት (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ፣ መጥፎ ምግባራቸውን ለማስተካከል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የጉባኤውን ሥነ ምግባር ሊያበላሹ ስለሚችሉ አደገኛ መሆናቸውን ገልጾ ነበር። በዚያ ወቅት፣ ከባድ ኃጢአት የፈጸመን ሰው ጉዳይ ለማየት መላው ጉባኤ “የቤተ ክርስቲያን ሸንጎ” ተብሎ በሚጠራው ሂደት ይካፈል ነበር። ይሁንና እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚፈጠረው አልፎ አልፎ ነበር። በ1944 መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መከታተል ያለባቸው ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ብቻ እንደሆኑ የሚገልጽ ሐሳብ ወጣ። የፍርድ ጉዳዮች ስለሚያዙበት ቅዱስ ጽሑፋዊ መንገድ የሚገልጽ ሐሳብ መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው በ1952 ሲሆን መጽሔቱ ንስሐ የማይገቡ ሰዎች የሚወገዱበት ዋነኛ ምክንያት የጉባኤውን ንጽሕና ለመጠበቅ እንደሆነ ጎላ አድርጎ ገልጿል።

20 ከዚያ በኋላ ባሉት አሥርተ ዓመታት ክርስቶስ፣ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ ሰዎች ጉዳይ የሚታይበትን መንገድ በተመለከተ ተከታዮቹ ይበልጥ ግልጽና የተሻለ አሠራር እንዲከተሉ ረድቷቸዋል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች ፍርድ ነክ ጉዳዮችን ሲመለከቱ ጉዳዩን ይሖዋ በሚያይበት መንገድ ይኸውም ፍትሕንና ምሕረትን በማንጸባረቅ እንዲይዙት የሚረዳ ጥሩ ሥልጠና አግኝተዋል። በዛሬው ጊዜ፣ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤ እንዲወገዱ የሚደረጉባቸውን ቢያንስ ሦስት ምክንያቶች መገንዘብ ችለናል፦ (1) የይሖዋን ስም ከነቀፋ ነፃ ለማድረግ፣ (2) የተፈጸመው ከባድ ኃጢአት ጉባኤውን እንዳይበክል ለመከላከል እና (3) ከተቻለ ኃጢአተኛው ንስሐ እንዲገባ ለማነሳሳት።

21. የውገዳ ዝግጅት ለአምላክ ሕዝቦች በረከት ያስገኘላቸው እንዴት ነው?

21 የውገዳ ዝግጅት በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ የክርስቶስ ተከታዮች በረከት ያስገኘላቸው እንዴት እንደሆነ አስተዋልክ? በጥንቷ እስራኤል ኃጢአተኞች ብዙውን ጊዜ ሕዝቡን ይበክሉ ነበር፤ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የእነዚህ ሰዎች ቁጥር ይሖዋን ከሚወዱና ትክክለኛውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ካላቸው ሰዎች ይበልጥ ነበር። በዚህም ምክንያት ብሔሩ በተደጋጋሚ ጊዜያት በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣ ሲሆን የእሱን ሞገስም አጥቷል። (ኤር. 7:23-28) በዛሬው ጊዜ ግን ይሖዋ የሰበሰበው መንፈሳዊ የሆኑ ወንዶችንና ሴቶችን ነው። ልበ ደንዳና የሆኑ ኃጢአተኞች ከመካከላችን ስለሚወገዱ ሰይጣን ጉባኤውን ይበልጥ ለመጉዳትና ንጽሕናውን ለማበላሸት ሊጠቀምባቸው አይችልም። በመሆኑም የሚያሳድሩት ተጽዕኖ በጣም ውስን ነው። እንዲህ ያለ እርምጃ በመወሰዱ በቡድን ደረጃ ሲታይ የይሖዋን ሞገስ አላጣንም። ይሖዋ “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” ብሎ ቃል እንደገባ አስታውስ። (ኢሳ. 54:17) ታዲያ የፍርድ ጉዳዮችን የመመልከት ከባድ ኃላፊነት ያለባቸውን ሽማግሌዎች በታማኝነት እንደግፋቸዋለን?

እያንዳንዱ ቤተሰብ ስያሜውን ያገኘበትን አምላክ ከፍ ከፍ ማድረግ

22, 23. በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ላሳዩት መንፈስ አመስጋኞች የሆንነው ለምንድን ነው? ከቤተሰብ ጋር በተያያዘ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ አስፈላጊ እንደነበር የሚጠቁመው ምንድን ነው?

22 የክርስቶስ ተከታዮች፣ ኢየሱስ ካከናወነው ቀጣይ የሆነ የማጥራት ሥራ ጥቅም ያገኙበት ሦስተኛው አቅጣጫ ከጋብቻና ከቤተሰብ ሕይወት ጋር የተያያዘ ነው። ባለፉት ዓመታት ከቤተሰብ ሕይወት ጋር በተያያዘ ያለን አመለካከት እየጠራ ሄዷል? አዎ። ለምሳሌ ያህል፣ በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ስላሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ስናነብ ከመገረም አልፈን በጣም እንደነቃለን። ለአምላክ የሚያቀርቡትን ቅዱስ አገልግሎት በሕይወታቸው ውስጥ ከማንኛውም ነገር በላይ አስበልጠው በመመልከታቸው አመስጋኞች ነን። ያም ቢሆን በወቅቱ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ እንደነበረባቸው እንገነዘባለን። ይህን የምንለው ለምንድን ነው?

23 ወንድሞች በተሰጣቸው የአገልግሎት ምድብ ወይም በጉብኝት ሥራ ምክንያት ለበርካታ ወራት ከቤተሰባቸው ርቀው መቆየታቸው የተለመደ ነገር ነበር። ጋብቻ አይበረታታም ነበር፤ እንዲያውም በዚህ ረገድ የነበረው አመለካከት በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ከሰፈረው ይበልጥ ጥብቅ ነበር። ላገቡ ክርስቲያኖች ደግሞ ትዳራቸው ጠንካራ እንዲሆን የሚረዳ ትምህርት ያን ያህል አይወጣም ነበር። በዛሬው ጊዜ ባሉ የክርስቶስ ተከታዮች ዘንድ ያለው ሁኔታስ ተመሳሳይ ነው? በፍጹም!

አንድ ክርስቲያን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል የቤተሰብ ኃላፊነቱን ችላ ማለቱ ተገቢ አይደለም

24. ክርስቶስ፣ ታማኝ ተከታዮቹን ስለ ትዳርም ሆነ ስለ ቤተሰብ ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት እንዲያዳብሩ የረዳቸው እንዴት ነው?

24 በዛሬው ጊዜ አንድ ክርስቲያን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ሲል የቤተሰብ ኃላፊነቱን ችላ ማለቱ ተገቢ እንዳልሆነ ተገንዝበናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:8ን አንብብ።) በተጨማሪም ክርስቶስ፣ በምድር ያሉ ታማኝ ተከታዮቹ ስለ ጋብቻና ስለ ቤተሰብ ሕይወት ቀጣይ የሆነ ጠቃሚ፣ ሚዛናዊና ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር እንዲያገኙ አድርጓል። (ኤፌ. 3:14, 15) የቤተሰብህን ኑሮ አስደሳች አድርገው የተባለ መጽሐፍ በ1978 ወጣ። ከ18 ዓመታት ገደማ በኋላ ደግሞ ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለው መጽሐፍ ተዘጋጀ። ከዚህም ሌላ ባለትዳሮች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በትዳራቸው ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የሚረዱ በርካታ ርዕሶች በመጠበቂያ ግንብ ላይ ሲወጡ ቆይተዋል።

25-27. ባለፉት ዓመታት ውስጥ በተለያየ ዕድሜ ላይ ለሚገኙ ልጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ ትኩረት የተሰጠው እንዴት ነው?

25 ከልጆች ጋር በተያያዘስ? ባለፉት ዓመታት ለእነሱም ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ ትኩረት እየተሰጣቸው ነው። የይሖዋ ድርጅት፣ በተለያየ ዕድሜ ለሚገኙ ልጆች ጠቃሚ ነገሮችን ሲያወጣ ቆይቷል፤ ይሁንና በአንድ ወቅት፣ ጠብ ጠብ እንደሚል ውኃ በጥቂቱ ይቀርብ የነበረው ትምህርት ዛሬ እንደማያቋርጥ ጅረት ሆኗል ማለት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ ወርቃማው ዘመን በተባለው መጽሔት ላይ ከ1919 እስከ 1921 ባሉት ዓመታት “የልጆች የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያ” የተባለ ዓምድ ይወጣ ነበር። ከዚያም በ1920 የወርቃማው ዘመን ሀሁ (እንግሊዝኛ) የተባለ ብሮሹር በ1941 ደግሞ ልጆች (እንግሊዝኛ) የተባለ መጽሐፍ ወጣ። በ1970ዎቹ ዓመታት ታላቁን አስተማሪ ማዳመጥ፣ ወጣትነትህን ከሁሉ በተሻለ መንገድ ተጠቀምበት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባሉትን መጻሕፍት አገኘን። ከ1982 አንስቶ ንቁ! ላይ “የወጣቶች ጥያቄ” የሚል ዓምድ መውጣት ጀመረ፤ ከዚያም በ1989 ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች የተባለው መጽሐፍ ወጣ።

መጽሐፍ ቅዱስ መማሪያዬ የተባለው ብሮሹር በጀርመን በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ሲወጣ ተሰብሳቢዎቹ በጣም ተደስተዋል

26 በአሁኑ ጊዜ የወጣቶች ጥያቄ የተባለው መጽሐፍ በሁለት ጥራዞች የሚገኝ ሲሆን እነዚህ መጻሕፍት በዚህ ዘመን ላሉ ወጣቶች የሚሆኑ ሐሳቦችን ይዘዋል። በተጨማሪም የወጣቶች ጥያቄ የሚለው ዓምድ jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ መውጣቱን ቀጥሏል። ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባለ መጽሐፍም አለን። ድረ ገጻችን ለልጆች የሚሆኑ በርካታ ነገሮችን የያዘ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ካርዶች፣ ከፍ ላሉና ለትናንሽ ልጆች የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መልመጃዎች፣ የሥዕል ጨዋታዎች፣ ቪዲዮዎችና ሥዕላዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ብሎም ሦስት ዓመትና ከዚያ በታች ለሆናቸው ልጆች የተዘጋጁ የመጽሐፍ ቅዱስ መማሪያዎች ይገኙበታል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቶስ፣ ትናንሽ ልጆችን ባቀፋቸው ጊዜ ለእነሱ የነበረው አመለካከት ዛሬም እንዳልተለወጠ ምንም ጥያቄ የለውም። (ማር. 10:13-16) በመካከላችን ያሉት ልጆች እንደምንወዳቸው እንዲሰማቸውና በመንፈሳዊ በደንብ እንዲመገቡ ይፈልጋል።

27 ኢየሱስ፣ ልጆች ከጉዳት እንዲጠበቁም ይፈልጋል። ዓለም በሥነ ምግባር ይበልጥ እየዘቀጠ ሲሄድ በልጆች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም እንደ ወረርሽኝ ተስፋፍቷል። በመሆኑም ወላጆች፣ ልጆቻቸውን እንዲህ ካለው አረመኔያዊ ድርጊት እንዲጠብቁ የሚረዷቸው ግልጽና ቀጥተኛ የሆኑ ትምህርቶች ወጥተዋል። d

28. (ሀ) ሕዝቅኤል በራእይ ወደተመለከተው ቤተ መቅደስ ለመግባት ይኸውም በንጹሕ አምልኮ ለመካፈል ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል? (ለ) ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

28 ክርስቶስ ተከታዮቹን ለማጥራት ቀጣይ የሆኑ እርምጃዎችን በመውሰድ የይሖዋን የላቁ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንዲያከብሩ፣ ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲሁም ከእነዚህ መሥፈርቶች ጥቅም እንዲያገኙ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ መመልከቱ የሚያስደስት አይደለም? ሕዝቅኤል በራእይ ያየውን ቤተ መቅደስ እስቲ እንደገና መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። ግዙፍ የሆኑትን የቤተ መቅደሱን መግቢያዎችም ለማስታወስ ሞክር። እርግጥ ነው፣ ይህ ቤተ መቅደስ ቃል በቃል ያለ ሳይሆን መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ ነው። ያም ቢሆን ይህን ቤተ መቅደስ እውን እንደሆነ አድርገን እናየዋለን? ወደ መንግሥት አዳራሽ ስለሄድን ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ስላነበብን አሊያም ከቤት ወደ ቤት ስላገለገልን ብቻ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብተናል ማለት አይቻልም። እነዚህ ድርጊቶች ከሚታዩ ነገሮች ጋር የተያያዙ ናቸው። ግብዝ የሆነ ሰው እነዚህን ነገሮች እያደረገም እንኳ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ላይገባ ይችላል። በሌላ በኩል ግን እነዚህን ነገሮች እያደረግን ከይሖዋ ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ የምንመላለስ እንዲሁም በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተን በንጹሕ አምልኮ የምንካፈል ከሆነ ከሁሉ በላይ ቅዱስ ወደሆነው ወደዚህ ስፍራ ገብተናል እንዲሁም በዚያ እያገለገልን ነው ሊባል ይችላል፤ በሌላ አባባል ይሖዋ አምላክ ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት እየተካፈልን ነው። እንግዲያው ምንጊዜም ይህን ውድ መብት ከፍ አድርገን እንመልከተው። እንዲሁም የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች በማክበር የእሱን ቅድስና ለማንጸባረቅ የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችንን እንቀጥል!

a ቪንዲኬሽን፣ ጥራዝ 2 የተባለው መጽሐፍ የአምላክ ሕዝቦች ወደ ትውልድ አገራቸው ስለመመለሳቸው የሚያወሱት ትንቢቶች ዘመናዊ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት በሥጋዊ ሳይሆን በመንፈሳዊ እስራኤላውያን ላይ መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በ1932 ገልጿል። ትንቢቶቹ ንጹሕ አምልኮ መልሶ እንደሚቋቋም ይጠቁማሉ። የመጋቢት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ሕዝቅኤል ስለ ቤተ መቅደሱ የተመለከተው ራእይ እንደነዚህ ካሉት ትንቢቶች አንዱ በመሆኑ በመጨረሻዎቹ ቀናት በመንፈሳዊ ሁኔታ ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ገልጿል።

b ይህ ቃለ መሐላ፣ አንድ ወንድና አንዲት ሴት የትዳር ጓደኛሞች ወይም የቅርብ ዘመዳሞች ካልሆኑ በቀር በአንድ ክፍል ውስጥ ብቻቸውን ከሆኑ በሩን ወለል አድርገው መክፈት እንዳለባቸው ይገልጻል። ለተወሰኑ ዓመታት ይህ ቃለ መሐላ ቤቴል ውስጥ በማለዳ አምልኮ ላይ በየዕለቱ ይነበብ ነበር።

c ትንባሆን ያላግባብ መጠቀም ሲባል ትንባሆ ማጨስን፣ ማኘክን ወይም ለዚህ ዓላማ ትንባሆ ማልማትን ያጠቃልላል።

d ለምሳሌ ያህል፣ ከታላቁ አስተማሪ ተማር የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 32 እንዲሁም የጥቅምት 2007 ንቁ! መጽሔት ከገጽ 3-11 ተመልከት።