በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 12

‘የሰላምን አምላክ’ ለማገልገል መደራጀት

‘የሰላምን አምላክ’ ለማገልገል መደራጀት

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

ይሖዋ ሕዝቡን ደረጃ በደረጃ ያደራጃል

1, 2. የጥር 1895 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ላይ ምን ለውጥ ተደረገ? ወንድሞችስ ምን ተሰማቸው?

 ጆን ቦኔት የተባለው ቀናተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የጥር 1895 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ ሲደርሰው መጽሔቱ ላይ ባየው ነገር በጣም ተደሰተ። የመጽሔቱ ሽፋን ተለውጦ ነበር፤ በሽፋኑ ላይ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ዳርቻ ላይ የመብራት ማማ የሚታይ ሲሆን ከማማው የሚፈነጥቀው ብርሃን የአካባቢውን ጨለማ ገፍፎታል። የመጽሔቱን አዲስ ሽፋን በተመለከተ መጽሔቱ ላይ የወጣው ማስታወቂያ “አዲሱ ልብሳችን” የሚል ርዕስ ነበረው።

2 በመጽሔቱ ሽፋን የተደነቀው ወንድም ቦኔት ለወንድም ራስል በጻፈው ደብዳቤ ላይ “መጠበቂያ ግንብ እንዲህ አምሮበት በማየቴ በጣም ደስ ብሎኛል፤ እጅግ ማራኪ ሆኗል” ብሎ ነበር። ጆን ብራውን የተባለ ሌላ ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “በጣም የሚገርም ነው። ማማው፣ ያ ሁሉ ማዕበልና አውሎ ነፋስ እየመታውም ጸንቶ መቆሙ መሠረቱ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል።” አዲሱ ሽፋን ወንድሞቻችን በዚያ ዓመት ያዩት የመጀመሪያው ለውጥ ነበር፤ ለውጡ ግን በዚህ አላበቃም። በኅዳር ወር ላይ ደግሞ ሌላ ትልቅ ለውጥ እንደተደረገ የሚገልጽ ትምህርት ወጣ። ይሄኛውም ለውጥ በማዕበል ከሚናወጥ ባሕር ጋር የተያያዘ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።

3, 4. የኅዳር 15, 1895 መጠበቂያ ግንብ ስለ የትኛው ችግር ጠቅሶ ነበር? ምን ከፍተኛ ለውጥ እንደሚኖርስ ተገለጸ?

3 የኅዳር 15, 1895 መጠበቂያ ግንብ ስለ አንድ ችግር በሰፊው የሚያወሳ ርዕስ ይዞ ወጥቶ ነበር፤ እንደ ኃይለኛ ማዕበል የሆነው ይህ ችግር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ማኅበር ወይም ድርጅት እየበጠበጠው መሆኑን መጠበቂያ ግንቡ ገልጿል። ‘በጉባኤዎች ውስጥ መሪ መሆን ያለበት ማን ነው?’ የሚለው ጉዳይ በወንድሞች መካከል ይበልጥ አወዛጋቢ እየሆነ ነበር። መከፋፈል የሚፈጥረውን ይህን የፉክክር መንፈስ ለማስወገድ ምን እንደሚያስፈልግ ወንድሞች እንዲገነዘቡ ለመርዳት በመጠበቂያ ግንቡ ላይ ድርጅቱ ከመርከብ ጋር ተመሳስሏል። ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች በመርከብ የተመሰለውን ድርጅት ኃይለኛ ማዕበልን መቋቋም እንዲችል እንዳላዘጋጁት መጠበቂያ ግንቡ ላይ በግልጽ ሰፍሯል። ታዲያ ምን መደረግ ነበረበት?

4 ጥሩ ችሎታ ያለው ካፒቴን፣ ሕይወት አድን መንሳፈፊያዎች መርከቡ ላይ መኖራቸውን እንዲሁም ማዕበል ሲመጣ የመርከቡ ሠራተኞች በመርከቡ ወለል ላይ ያሉትን በሮች ለመዝጋት ዝግጁ መሆናቸውን እንደሚያረጋግጥ መጠበቂያ ግንቡ ገልጾ ነበር። በተመሳሳይም ድርጅቱን የሚመሩት ወንድሞች፣ ሁሉም ጉባኤዎች እንደ ማዕበል አስቸጋሪ የሆኑ ሁኔታዎችን ለመቋቋም ዝግጁ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል። ይህን ለማድረግ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያስፈልግ መጠበቂያ ግንቡ ገለጸ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ “በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ . . . ለመንጋው ‘የበላይ ተመልካች’ የሚሆኑ ሽማግሌዎች እንዲመረጡ” በዚያው መጠበቂያ ግንብ ላይ መመሪያ ተሰጠ።—ሥራ 20:28

5. (ሀ) በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች እንዲኖሩ የተደረገው የመጀመሪያ ዝግጅት ወቅታዊ እርምጃ ነበር የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

5 በጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች እንዲኖሩ የተደረገው ይህ የመጀመሪያ ዝግጅት ጠንካራ የሆነ የጉባኤ አደረጃጀት እንዲኖር የሚረዳ ወቅታዊ እርምጃ ነበር። ይህ ዝግጅት ወንድሞቻችን አንደኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን ኃይለኛ ማዕበል ተቋቁመው እንዲያልፉ ረድቷቸዋል። ከዚያ በኋላ ባሉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ በድርጅታዊ አሠራር ረገድ የተደረጉ ተጨማሪ ማስተካከያዎች የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋን ለማገልገል ይበልጥ ብቁ እንዲሆኑ ረድተዋቸዋል። እንዲህ ዓይነት ለውጥ እንደሚኖር የሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የትኛው ነው? አንተ በድርጅታዊ አሠራር ረገድ ምን ለውጦች ሲደረጉ ተመልክተሃል? ከእነዚህ ማስተካከያዎች ጥቅም አግኝተሃል?

‘ሰላምን የበላይ ተመልካቾችሽ አድርጌ እሾማለሁ’

6, 7. (ሀ) በኢሳይያስ 60:17 ላይ ያለው ትንቢት ምን ትርጉም አለው? (ለ) “የበላይ ተመልካቾች” እና “አሠሪዎች” የሚሉት አገላለጾች መጠቀሳቸው ምን ያመለክታል?

6 በዚህ መጽሐፍ ምዕራፍ 9 ላይ እንደተመለከትነው ይሖዋ፣ ሕዝቦቹን ቁጥራቸው እንዲጨምር በማድረግ እንደሚባርካቸው ኢሳይያስ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳ. 60:22) ይሁንና ይሖዋ የገባው ቃል ይህ ብቻ አይደለም። ይህ ትንቢት በተነገረበት ምዕራፍ ላይ እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቷል፦ “በመዳብ ፋንታ ወርቅ፣ በብረት ፋንታ ብር፣ በእንጨት ፋንታ መዳብ፣ በድንጋዮችም ፋንታ ብረት አመጣለሁ፤ ሰላምንም የበላይ ተመልካቾችሽ፣ ጽድቅንም አሠሪዎችሽ አድርጌ እሾማለሁ።” (ኢሳ. 60:17) ይህ ትንቢት ምን ትርጉም አለው? በዘመናችን ፍጻሜውን የሚያገኘውስ እንዴት ነው?

ለውጥ የተደረገው ከመጥፎ ወደ ጥሩ ሳይሆን ከጥሩው ይበልጥ ወደተሻለ ነው

7 የኢሳይያስ ትንቢት አንድ ማዕድን በሌላ ማዕድን እንደሚተካ ይናገራል። ይሁንና ለውጥ የተደረገው ከመጥፎ ወደ ጥሩ ሳይሆን ከጥሩው ይበልጥ ወደተሻለ እንደሆነ ልብ በል። መዳብ በወርቅ መተካቱ መሻሻል ነው፤ ጥቅሱ ላይ ከሚገኙት ሌሎች ነገሮች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ ሕዝቦቹ የሚገኙበት ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ እንደሚሄድ ይህን ምሳሌ በመጠቀም ትንቢት ተናግሯል። ታዲያ ትንቢቱ የሚናገረው ስለ ምን ዓይነት መሻሻል ነው? ይሖዋ “የበላይ ተመልካቾች” እና “አሠሪዎች” የሚሉ አገላለጾችን መጠቀሙ ሕዝቦቹ እንክብካቤ በሚያገኙበትና በሚደራጁበት መንገድ ረገድ ቀስ በቀስ መሻሻል እንደሚኖር የሚጠቁም ነው።

8. (ሀ) በኢሳይያስ ትንቢት ላይ የተጠቀሱትን ማሻሻያዎች የሚያመጣው ማን ነው? (ለ) ከእነዚህ ማሻሻያዎች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? (“ የተሰጠውን እርማት በትሕትና ተቀብሏል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

8 እንዲህ ያለ ድርጅታዊ መሻሻል እንዲመጣ የሚያደርገው ማን ነው? ይሖዋ ‘ወርቅ አመጣለሁ፣’ ‘ብር አመጣለሁ’ እንዲሁም ‘ሰላምን እሾማለሁ’ በማለት ይህን የሚያደርገው እሱ መሆኑን ተናግሯል። በእርግጥም በጉባኤ አደረጃጀት ረገድ ማሻሻያዎች እንዲኖሩ ያደረገው ይሖዋ ራሱ እንጂ ሰዎች አይደሉም። ኢየሱስ፣ ንጉሥ ሆኖ ከተሾመ በኋላ ደግሞ ይሖዋ እንዲህ ያሉ ማሻሻያዎች እንዲኖሩ ያደረገው በልጁ አማካኝነት ነው። ከእነዚህ ለውጦች ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ጥቅሱ እነዚህ ማሻሻያዎች “ሰላምን” እና “ጽድቅን” እንደሚያስገኙ ይናገራል። የአምላክን መመሪያ በመቀበል ማስተካከያዎችን የምናደርግ ከሆነ በመካከላችን ሰላም ይሰፍናል፤ እንዲሁም ለጽድቅ ያለን ፍቅር ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የሰላም አምላክ’ በማለት የጠራውን ይሖዋን እንድናገለግል ያነሳሳናል።—ፊልጵ. 4:9

9. በጉባኤ ውስጥ ሥርዓት እና አንድነት እንዲኖር የሚያስችለው ትክክለኛው መሠረት ምንድን ነው? ለምንስ?

9 ጳውሎስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “አምላክ የሰላም እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም” ብሏል። (1 ቆሮ. 14:33) ጳውሎስ፣ ሁከትን ያነጻጸረው ከሥርዓት ጋር ሳይሆን ከሰላም ጋር እንደሆነ ልብ በል። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ ሥርዓት መኖሩ በራሱ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል ማለት ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ወታደሮች ወደ ጦር ሜዳ ሲዘምቱ ሥርዓት ባለው መንገድ ተሰልፈው ይሄዱ ይሆናል፤ ሆኖም የሚሄዱት ሰላም ለማምጣት ሳይሆን ጦርነት ለመክፈት ነው። እንግዲያው እኛ ክርስቲያኖች ልብ ልንለው የሚገባ አንድ ነገር አለ፦ በሰላም ላይ ያልተመሠረተ ማንኛውም ሥርዓት ይዋል ይደር እንጂ መናዱ አይቀርም። በተቃራኒው ግን አምላክ የሚሰጠው ሰላም ዘላቂ የሆነ ሥርዓት እንዲኖር ያደርጋል። ከዚህ አንጻር፣ ያለንበትን ድርጅት የሚመራውና የሚያጠራው “ሰላም የሚሰጠው አምላክ” በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (ሮም 15:33) አምላክ የሚሰጠው ሰላም፣ በዓለም ዙሪያ ባሉት ጉባኤዎች ውስጥ ለሚታየውና ከፍ አድርገን ለምንመለከተው ጠቃሚ የሆነ ሥርዓታማ አካሄድ ብሎም እውነተኛ አንድነት መሠረት ሆኗል።—መዝ. 29:11

10. (ሀ) በቀደሙት ዓመታት በድርጅታችን ውስጥ ምን ለውጦች ተደርገዋል? (“ ከበላይ ተመልካችነት ጋር በተያያዘ የተደረጉ መሻሻሎች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

10 በቀደሙት ዓመታት በድርጅታችን ውስጥ ነገሮች በሥርዓት እንዲከናወኑ ያደረጉ ጠቃሚ ለውጦች “ ከበላይ ተመልካችነት ጋር በተያያዘ የተደረጉ መሻሻሎች” በሚለው ሣጥን ላይ በአጭሩ ቀርበዋል። ይሁንና ይሖዋ በቅርብ ዓመታት ውስጥ በንጉሣችን አማካኝነት ያደረጋቸው “በመዳብ ፋንታ ወርቅ” እንዲኖር ያስቻሉ ለውጦች የትኞቹ ናቸው? ከበላይ ተመልካችነት ጋር በተያያዘ የተደረጉት እነዚህ ማስተካከያዎች በዓለም ዙሪያ በሚገኙት ጉባኤዎች ውስጥ ያለው ሰላምና አንድነት እንዲጠናከር ያደረጉት እንዴት ነው? እነዚህ ለውጦች ‘የሰላምን አምላክ’ እንድታገለግል የረዱህ እንዴት ነው?

ክርስቶስ ጉባኤውን የሚመራው እንዴት ነው?

11. (ሀ) በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተደረገው ጥናት ወንድሞች ምን ማሻሻያ ማድረግ እንዳለባቸው እንዲገነዘቡ ረዳቸው? (ለ) የበላይ አካሉ አባላት ምን ለማድረግ ቆርጠው ነበር?

11 ከ1964 እስከ 1971 ባሉት ዓመታት በበላይ አካሉ አመራር ሥር ጥልቀት ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተካሂዶ ነበር፤ ምርምር ከተካሄደባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል ‘የመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ ሥራውን ያከናውን የነበረው እንዴት ነው?’ የሚለው ይገኝበታል። a ከድርጅታዊ አሠራር ጋር በተያያዘ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጉባኤዎችን በበላይ ተመልካችነት የሚመራው የሽማግሌዎች አካል እንጂ አንድ ሽማግሌ ወይም የበላይ ተመልካች ብቻ እንዳልነበረ መገንዘብ ተቻለ። (ፊልጵስዩስ 1:1ን እና 1 ጢሞቴዎስ 4:14ን አንብብ።) የበላይ አካሉ አባላት ይህ ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ሲሆንላቸው፣ ንጉሣቸው ኢየሱስ የአምላክ ሕዝቦች በሚከተሉት ድርጅታዊ አሠራር ረገድ ማሻሻያ እንዲያደርጉ እየመራቸው መሆኑን ተገነዘቡ፤ በመሆኑም እነዚህ ወንድሞች የንጉሡን አመራር ለመታዘዝ ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። ሽማግሌዎችን ከመሾም ጋር በተያያዘ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረውን አካሄድ በድርጅቱ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሉ ወዲያውኑ ለውጦች ማድረግ ጀመሩ። ታዲያ በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የተደረጉት አንዳንድ ለውጦች የትኞቹ ናቸው?

12. (ሀ) ከበላይ አካሉ ጋር በተያያዘ ምን ማስተካከያ ተደረገ? (ለ) የበላይ አካሉ በአሁኑ ጊዜ የተዋቀረው እንዴት ነው? (“ የበላይ አካሉ ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን የሚያከናውነው እንዴት ነው?” የሚለውን በገጽ 130 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።)

12 የመጀመሪያው ማስተካከያ ከራሱ ከበላይ አካሉ ጋር የተያያዘ ነበር። እስከዚያ ጊዜ ድረስ የበላይ አካሉ አባላት የሚሆኑት ቅቡዓን ወንድሞች፣ ዎች ታወር ባይብል ኤንድ ትራክት ሶሳይቲ ኦቭ ፔንስልቬንያ የተባለው ማኅበር የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የሆኑት ሰባት ሰዎች ነበሩ። ይሁንና በ1971 የበላይ አካሉ አባላት ቁጥር ከ7 ወደ 11 ከፍ ያለ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በበላይ አካሉ እና በማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ መካከል ግልጽ ልዩነት እንዲኖር ተደረገ። የበላይ አካሉ አባላት አንዳቸው ከሌላው እንደሚበልጡ አድርገው አያስቡም፤ አባላቱ በሙሉ ሊቀ መንበር ሆኖ የማገልገል ኃላፊነት በስማቸው የፊደል ቅደም ተከተል መሠረት በየዓመቱ በዙር ይደርሳቸዋል።

13. (ሀ) ከበላይ ተመልካቾች ጋር በተያያዘ ለ40 ዓመታት ያህል የነበረው አሠራር የትኛው ነው? (ለ) የበላይ አካሉ በ1972 ምን አደረገ?

13 ቀጥሎ የተደረገው ማስተካከያ ደግሞ ሁሉንም ጉባኤዎች የሚመለከት ነበር። እንዴት? ከ1932 እስከ 1972 ባሉት ዓመታት ውስጥ በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ በዋነኝነት የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው አንድ ወንድም ነበር። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ እንዲያገለግል የሚሾመው ወንድም እስከ 1936 ድረስ የአገልግሎት ዳይሬክተር ተብሎ ይጠራ ነበር። ከዚያ በኋላ በዚህ ቦታ ላይ የሚያገለግሉ ወንድሞች የቡድን አገልጋይ፣ ቀጥሎም የጉባኤ አገልጋይ በመጨረሻም የጉባኤ የበላይ ተመልካች ተብለው ይጠሩ ነበር። እነዚህ የተሾሙ ወንድሞች የመንጋውን መንፈሳዊ ደኅንነት ለመጠበቅ በትጋት ይሠሩ ነበር። የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው ወንድም ከጉባኤው ጋር የተያያዙ ውሳኔዎችን የሚያደርገው ብዙውን ጊዜ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች አገልጋዮችን (ሽማግሌዎችን) ሳያማክር ነበር። ይሁን እንጂ በ1972 የበላይ አካሉ ታሪካዊ የሆነ ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል እርምጃ ወሰደ። ይህ ለውጥ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

14. (ሀ) ከጥቅምት 1, 1972 ጀምሮ የትኛው አዲስ ዝግጅት ተግባራዊ ሆነ? (ለ) የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ የሚያደርገው እንዴት ነው?

14 በእያንዳንዱ ጉባኤ ውስጥ የጉባኤ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግለው አንድ ወንድም ብቻ መሆኑ ቀርቶ ቅዱስ ጽሑፋዊውን ብቃት ያሟሉና በቲኦክራሲያዊ መንገድ የተሾሙ ሌሎች ወንድሞችም በአንድ ላይ ሆነው ጉባኤውን በበላይ ተመልካችነት መምራት ጀመሩ፤ እነዚህን ወንድሞች ያቀፈው ቡድን የሽማግሌዎች አካል ተብሎ ይጠራል። ከሽማግሌዎች ጋር በተያያዘ የተደረገው ይህ አዲስ ዝግጅት ከጥቅምት 1, 1972 ጀምሮ ተግባራዊ ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ ሆኖ የሚያገለግል አንድ ወንድም ራሱን የሚቆጥረው ከሌሎቹ ሽማግሌዎች እንደሚበልጥ ሳይሆን “እንደሚያንስ” አድርጎ ነው። (ሉቃስ 9:48) እነዚህ ትሑት ወንድሞች ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር ትልቅ በረከት ናቸው!—ፊልጵ. 2:3

ንጉሣችን ለተከታዮቹ አስፈላጊ የሆኑትን እረኞች በትክክለኛው ጊዜ ሰጥቷል፤ በእርግጥም ይህ ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ነው

15. (ሀ) በጉባኤዎች ውስጥ የሽማግሌዎች አካል እንዲኖር የተደረገው ዝግጅት ምን ጥቅሞች አስገኝቷል? (ለ) ንጉሣችን ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ እንደወሰደ የሚያሳየው ምንድን ነው?

15 የጉባኤ ኃላፊነቶችን የሽማግሌዎች አካል አባላት ተከፋፍለው እንዲያከናውኑ ዝግጅት መደረጉ ትልቅ ለውጥ እንዳመጣ ማየት ይቻላል። እስቲ ይህ መሻሻል ያስገኛቸውን ሦስት ጥቅሞች እንመልከት፦ አንዱና ዋነኛው ጥቅም፣ ሁሉም የጉባኤው ሽማግሌዎች ያላቸው ኃላፊነት ምንም ይሁን ምን የጉባኤው ራስ ኢየሱስ መሆኑን እንዳይዘነጉ የሚረዳቸው መሆኑ ነው። (ኤፌ. 5:23) ሁለተኛ፣ ምሳሌ 11:14 እንደሚለው “ብዙ አማካሪዎች ባሉበት . . . ስኬት ይገኛል።” ሽማግሌዎች፣ የጉባኤውን መንፈሳዊነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እርስ በርስ መመካከራቸውና የሁሉንም ሐሳብ ከግምት ማስገባታቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎች ላይ ለመድረስ ያስችላቸዋል። (ምሳሌ 27:17) ይሖዋ እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን የሚባርክ ሲሆን እነዚህ ውሳኔዎችም ስኬት ያስገኛሉ። ሦስተኛ፣ ብቃት ያላቸው ተጨማሪ ወንድሞች ሽማግሌዎች ሆነው እንዲያገለግሉ መደረጉ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጉባኤዎች የሚያስፈልጓቸውን ተጨማሪ የበላይ ተመልካቾችና እረኞች ለማግኘት አስችሏል። (ኢሳ. 60:3-5) እስቲ አስበው፦ በ1971 በዓለም ዙሪያ ከ27,000 በላይ የነበረው የጉባኤዎች ቁጥር በ2013 ከ113,000 በላይ ሆኗል! ንጉሣችን ለተከታዮቹ አስፈላጊ የሆኑትን እረኞች በትክክለኛው ጊዜ ሰጥቷል፤ በእርግጥም ይህ ጥበብ የሚንጸባረቅበት እርምጃ ነው።—ሚክ. 5:5

‘ለመንጋው ምሳሌ መሆን’

16. (ሀ) ሽማግሌዎች ምን ኃላፊነት አለባቸው? (ለ) ኢየሱስ “ግልገሎቼን ጠብቅ” በማለት የሰጠውን ምክር የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች እንዴት ይመለከቱታል?

16 ቀደም ባሉት ዘመናት በነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መካከል የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው የአምላክ አገልጋዮች ሆነው እንዲቀጥሉ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው ነበር። (ገላትያ 6:10ን አንብብ።) በ1908 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ኢየሱስ “ግልገሎቼን ጠብቅ” በማለት የሰጠውን ምክር የሚያብራራ ነበር። (ዮሐ. 21:15-17) በዚህ ርዕስ ላይ ለሽማግሌዎች የሚከተለው ምክር ተሰጥቷል፦ “ጌታ ከመንጋው ጋር በተያያዘ የሰጠን ተልእኮ በልባችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ሊይዝ ይገባል፤ በተጨማሪም የጌታን ተከታዮች መመገብንና መንከባከብን እንደ ታላቅ መብት መመልከት ይኖርብናል።” የ1925 መጠበቂያ ግንብ ላይም እረኛ ሆኖ ማገልገል ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ነገር መሆኑን ሽማግሌዎችን ለማስታወስ የሚከተለው ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “ቤተ ክርስቲያን የአምላክ ንብረት ናት፤ . . . አምላክ፣ ወንድሞቻቸውን የማገልገል መብት የተሰጣቸውን ሁሉ በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል።”

17. የበላይ ተመልካቾች ብቃት ያላቸው እረኞች እንዲሆኑ እርዳታ ያገኙት እንዴት ነው?

17 የይሖዋ ድርጅት፣ ሽማግሌዎች እረኝነት የማድረግ ችሎታቸው እንዲሻሻል ማለትም ‘ከብረት ወደ ብር’ እንዲለወጥ የረዳቸው እንዴት ነው? ሥልጠና በመስጠት ነው። በ1959 በመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ለበላይ ተመልካቾች ሥልጠና ተሰጠ። በትምህርት ቤቱ ውስጥ ከነበሩት ክፍሎች አንዱ “በግለሰብ ደረጃ ትኩረት መስጠት” የሚል ርዕስ ነበረው። እነዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች “አስፋፊዎችን ቤታቸው ሄደው ለመጠየቅ ፕሮግራም እንዲያወጡ” ተበረታትተዋል። በትምህርት ቤቱ ፕሮግራም ላይ፣ እረኞች እንዲህ ያለውን ጉብኝት የሚያንጽ ማድረግ የሚችሉባቸው የተለያዩ መንገዶች ተብራርተዋል። በ1966 የተሻሻለ የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት መሰጠት ጀመረ። በዚህ ትምህርት ቤት ከቀረቡት ትምህርቶች አንዱ “የእረኝነት ሥራ አስፈላጊነት” የሚል ርዕስ ነበረው። በዚህ ትምህርት ላይ የተላለፈው ዋና ሐሳብ ምን ነበር? ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች “የአምላክን መንጋ በፍቅር በመንከባከቡ ሥራ ሲካፈሉ ለቤተሰባቸውና ለመስክ አገልግሎት ተገቢውን ትኩረት መስጠታቸውን መዘንጋት” እንደሌለባቸው የሚገልጽ ነበር። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ሽማግሌዎች በዚህ ትምህርት ቤት በተለያዩ ጊዜያት ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል። ታዲያ በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት የሚሰጠው ቀጣይ የሆነ ሥልጠና ምን ውጤት አስገኝቷል? በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ እረኞች ሆነው የሚያገለግሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ብቃት ያላቸው ወንድሞች እንዲኖሩ አድርጓል።

የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት በፊሊፒንስ፣ 1966

18. (ሀ) ሽማግሌዎች በአደራ የተሰጣቸው ከባድ ኃላፊነት ምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ እና ኢየሱስ በትጋት የሚሠሩ ሽማግሌዎችን የሚወዷቸው ለምንድን ነው?

18 ክርስቲያን ሽማግሌዎችን በንጉሣችን በኢየሱስ አማካኝነት የሾማቸው ይሖዋ ሲሆን ከባድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ይህ ኃላፊነት ምንድን ነው? በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ በሆነው በዚህ ዘመን የአምላክን በጎች መምራት ነው። (ኤፌ. 4:11, 12፤ 2 ጢሞ. 3:1) በትጋት የሚሠሩት ሽማግሌዎች “በአደራ የተሰጣችሁን የአምላክ መንጋ . . . በፈቃደኝነት፣ . . . ለማገልገል በመጓጓት፣ . . . [እና] ለመንጋው ምሳሌ በመሆን ጠብቁ” የሚለውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ተግባራዊ ስለሚያደርጉ ይሖዋ እና ኢየሱስ ለእነሱ ጥልቅ ፍቅር አላቸው። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ክርስቲያን እረኞች ለመንጋው ምሳሌ ከሚሆኑባቸውና ለጉባኤው ሰላም ብሎም ደስታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉባቸው በርካታ መንገዶች መካከል እስቲ ሁለቱን እንመልከት።

ሽማግሌዎች በዛሬው ጊዜ የአምላክን መንጋ የሚጠብቁት እንዴት ነው?

19. ሽማግሌዎች አብረውን ሲያገለግሉ ምን ይሰማናል?

19 አንደኛ፣ ሽማግሌዎች ከጉባኤው አባላት ጋር ያገለግላሉ። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የአምላክን መንግሥት ምሥራች እየሰበከና እያወጀ ከከተማ ወደ ከተማ እንዲሁም ከመንደር ወደ መንደር ተጓዘ። አሥራ ሁለቱም ከእሱ ጋር ነበሩ።” (ሉቃስ 8:1) ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር አብሮ እንደሰበከ ሁሉ በዛሬው ጊዜም ምሳሌ የሚሆኑ ሽማግሌዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር በስብከቱ ሥራ ይካፈላሉ። ይህን ማድረጋቸው በጉባኤው ውስጥ ጥሩ መንፈስ እንዲሰፍን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ይገነዘባሉ። የጉባኤ አባላት እንደ እነዚህ ስላሉት ሽማግሌዎች ምን ይሰማቸዋል? በ80ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኙ ዣኒን የተባሉ እህት “ከአንድ ሽማግሌ ጋር ሳገለግል ከእሱ ጋር ለመጨዋወትና እሱን ይበልጥ ለማወቅ ጥሩ አጋጣሚ አገኛለሁ” ብለዋል። በ30ዎቹ አጋማሽ ላይ የሚገኝ ስቴቨን የተባለ ወንድም ደግሞ “አንድ ሽማግሌ ከቤት ወደ ቤት አብሮኝ ሲያገለግል እኔን ለመርዳት እንደሚፈልግ ይሰማኛል። እንዲህ ዓይነት እርዳታ በማግኘቴ በጣም እደሰታለሁ” ብሏል።

እረኛው የጠፋችበትን በግ እንደሚፈልግ ሁሉ ሽማግሌዎችም ከጉባኤ የራቁትን ለማግኘት ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ

20, 21. ሽማግሌዎች ኢየሱስ የጠቀሰውን እረኛ ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (“ ውጤታማ የሆነ ሳምንታዊ ጉብኝት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

20 ሁለተኛ፣ የይሖዋ ድርጅት ከጉባኤው ለራቁ ክርስቲያኖች አሳቢነት እንዲያሳዩ ሽማግሌዎችን አሠልጥኗቸዋል። (ዕብ. 12:12) ሽማግሌዎች እንደ እነዚህ ያሉትን በመንፈሳዊ የደከሙ ሰዎች መርዳት ያለባቸው ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የሚችሉትስ እንዴት ነው? ኢየሱስ ስለ አንድ እረኛ እና ስለጠፋችው በጉ የተናገረው ምሳሌ ለዚህ መልስ ይሰጠናል። (ሉቃስ 15:4-7ን አንብብ።) በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው እረኛ በጉ እንደጠፋች ሲያስተውል፣ ሌላ በግ የሌለው ይመስል የጠፋችውን በግ አጥብቆ ይፈልጋታል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የዚህን እረኛ ምሳሌ የሚከተሉት እንዴት ነው? የጠፋችው በግ በእረኛው ዘንድ ውድ እንደነበረች ሁሉ ከአምላክ ሕዝቦች የራቁትን ሰዎችም ሽማግሌዎች እንደ ውድ አድርገው ይመለከቷቸዋል። በመንፈሳዊ የደከሙትን ግለሰቦች ልክ እንደ ጠፋ በግ አድርገው ያዩዋቸዋል እንጂ እነሱን መርዳት ጊዜ እንደማባከን ሆኖ አይሰማቸውም። በተጨማሪም እረኛው “የጠፋችውን እስኪያገኝ ድረስ [እንደሚፈልጋት]” ሁሉ ሽማግሌዎችም በመንፈሳዊ የደከሙትን ሰዎች ለማግኘትና ለመርዳት ቅድሚያውን ወስደው ጥረት ያደርጋሉ።

21 በምሳሌው ላይ የተጠቀሰው እረኛ በጓን ሲያገኛት ምን ያደርጋል? በቀስታ አንስቶ “በጫንቃው ላይ [በመሸከም]” ወደ መንጋው ይመልሳታል። በተመሳሳይም አንድ ሽማግሌ በመንፈሳዊ ለደከመው ግለሰብ ከልብ የመነጨ አሳቢነት ማሳየቱ ግለሰቡን በቀስታ የማንሳት ያህል ሊያበረታታውና ወደ ጉባኤው እንዲመለስ ሊረዳው ይችላል። ቪክተር የተባለ በአፍሪካ የሚኖርና ከጉባኤ የራቀ አንድ ወንድም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞታል። “ከጉባኤ በራቅኩባቸው ስምንት ዓመታት ውስጥ ሽማግሌዎች እኔን ለመርዳት ጥረት ማድረጋቸውን አላቆሙም ነበር” ብሏል። በተለይ የቪክተርን ልብ የነካው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት አብሮኝ የተካፈለ ጆን የተባለ ሽማግሌ አንድ ቀን ሊጠይቀኝ መጣ፤ ይህ ወንድም በትምህርት ቤቱ ላይ አብረን የተነሳናቸውን አንዳንድ ፎቶግራፎች አሳየኝ። ፎቶግራፎቹን ስመለከት በርካታ ግሩም ትዝታዎች ወደ አእምሮዬ መጡ፤ ይህ ደግሞ ይሖዋን በማገለግልበት ወቅት የነበረኝን ደስታ መልሼ ለማግኘት እንድጓጓ አደረገኝ።” ጆን ካነጋገረው ብዙም ሳይቆይ ቪክተር ጉባኤ መምጣት ጀመረ። አሁን እንደ ቀድሞው በጉባኤ ውስጥ አቅኚ ሆኖ ያገለግላል። በእርግጥም አሳቢ የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለደስታችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።—2 ቆሮ. 1:24 b

ከበላይ ተመልካችነት ጋር በተያያዘ የተደረገው መሻሻል የአምላክ ሕዝቦችን አንድነት አጠናክሮታል

22. ጽድቅና ሰላም የክርስቲያን ጉባኤን አንድነት የሚያጠናክሩት እንዴት ነው? (“ በጣም ተደነቅን” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

22 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ በሕዝቦቹ መካከል ያለው ጽድቅና ሰላም ሁልጊዜ እየጨመረ እንደሚሄድ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 60:17) እነዚህ ባሕርያት በጉባኤዎች ውስጥ ያለው አንድነት እንዲጠናከር ያደርጋሉ። እንዴት? ከጽድቅ ጋር በተያያዘ “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው” የሚለውን ጥቅስ ማሰብ እንችላለን። (ዘዳ. 6:4) ጉባኤዎች የሚመሩባቸው የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ከአገር ወደ አገር አይለያዩም። ትክክል ወይም ስህተት ለሆነው ነገር ያወጣቸው መሥፈርቶችም ቢሆኑ አንድ ይኸውም “በቅዱሳን ጉባኤዎች ሁሉ” ተመሳሳይ ናቸው። (1 ቆሮ. 14:33) በመሆኑም አንድ ጉባኤ እድገት የሚያደርገው የአምላክን መሥፈርቶች ተግባራዊ ካደረገ ብቻ ነው። ከሰላም ጋር በተያያዘ ደግሞ ንጉሣችን በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲኖር ብቻ ሳይሆን “ሰላም ፈጣሪዎች” እንድንሆንም ጭምር ይፈልጋል። (ማቴ. 5:9) እንግዲያው “ሰላም የሚገኝበትን . . . ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።” በመካከላችን አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ ቅድሚያውን ወስደን ችግሩን እንፍታ። (ሮም 14:19) በዚህ መንገድ ለጉባኤው ሰላምም ሆነ አንድነት አስተዋጽኦ እናደርጋለን።—ኢሳ. 60:18

23. የይሖዋ አገልጋዮች በዛሬው ጊዜ ምን የሚያስደስተን ነገር አለ?

23 በኅዳር 1895 መጠበቂያ ግንብ ላይ ሽማግሌዎች የሚሾሙበት ዝግጅት መጀመሩን የሚገልጽ ማስታወቂያ በወጣበት ጊዜ፣ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ከልባቸው የሚፈልጉት ነገር እንዳለም ገልጸው ነበር። የሚፈልጉት ነገር ምን ነበር? በድርጅቱ ውስጥ የተደረገው ይህ አዲስ ዝግጅት የአምላክን ሕዝቦች “ወደ እምነት አንድነት በቶሎ እንዲደርሱ” የሚረዳቸው እንዲሆን ይመኙና ይጸልዩ ነበር። ያለፉትን አሥርተ ዓመታት መለስ ብለን ስንመለከት ይሖዋ በንጉሣችን አማካኝነት ከበላይ ተመልካችነት ጋር በተያያዘ ደረጃ በደረጃ ያከናወነው የማጥራት ሥራ የአምልኮ አንድነታችንን በማጠናከሩ አመስጋኞች ነን። (መዝ. 99:4) በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የምንገኝ የይሖዋ ሕዝቦች በሙሉ “በአንድ መንፈስ” በመመላለሳችን፣ ‘አካሄዳችን አንድ’ በመሆኑ እንዲሁም ‘እጅ ለእጅ ተያይዘን’ ‘የሰላምን አምላክ’ በማገልገላችን እንደሰታለን።—2 ቆሮ. 12:18፤ ሶፎንያስ 3:9ን አንብብ።

a የዚህ ጥልቀት ያለው ምርምር ውጤት ኤድ ቱ ባይብል አንደርስታንዲንግ (መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያግዝ መሣሪያ) በተባለው የማመሳከሪያ መጽሐፍ ላይ ወጥቷል።