በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 15

የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት መታገል

የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት መታገል

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

የክርስቶስ ተከታዮች ሕጋዊ እውቅና ለማግኘትና የአምላክን ሕጎች የመታዘዝ መብታቸውን ለማስከበር ባደረጉት ትግል ኢየሱስ እነሱን የረዳበት መንገድ

1, 2. (ሀ) የአምላክ መንግሥት ዜጋ ለመሆንህ ማረጋገጫው ምንድን ነው? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች የሃይማኖት ነፃነት ለማግኘት አንዳንድ ጊዜ ትግል ማድረግ ያስፈለጋቸው ለምንድን ነው?

 የአምላክ መንግሥት ዜጋ ነህ? የይሖዋ ምሥክር ከሆንክ የመንግሥቱ ዜጋ እንደሆንክ ጥርጥር የለውም! ሆኖም የዜግነት ማረጋገጫህ ምንድን ነው? ፓስፖርት ወይም ከመንግሥት ያገኘኸው ሌላ ሰነድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዚህ መንግሥት ዜጋ ለመሆንህ ማረጋገጫው ይሖዋ አምላክን የምታመልክበት መንገድ ነው። እውነተኛ አምልኮ፣ በምትማራቸው ነገሮች ማመንን ብቻ ሳይሆን ተግባርን ይኸውም ለአምላክ መንግሥት ሕግጋት ታዛዥ መሆንን ይጨምራል። አምልኳችን፣ ልጆቻችንን የምናሳድግበትን መንገድ አልፎ ተርፎም ከሕክምና ጋር በተያያዘ የምናደርጋቸውን ውሳኔዎች ጨምሮ ሁሉንም የሕይወታችን ዘርፎች ይነካል።

2 ይሁን እንጂ የምንኖርበት ዓለም እኛ ከፍ አድርገን ለምንመለከተው የአምላክ መንግሥት ዜጋ የመሆን መብታችንም ሆነ የዚህ መንግሥት ዜጋ በመሆናችን ለሚጠበቁብን ብቃቶች አክብሮት የለውም። አንዳንድ መንግሥታት በአምልኳችን ላይ ገደብ ለመጣል ወይም አምልኳችንን ከነጭራሹ ለማስቆም ሞክረዋል። የክርስቶስ ተገዢዎች በመሲሐዊው ንጉሥ ሕግጋት መሠረት የመኖር መብታቸውን ለማስከበር መታገል ያስፈለጋቸው ጊዜ አለ። እንዲህ ማድረጋቸው የሚያስገርም ነው? አይደለም። በጥንት ዘመን የኖሩ የይሖዋ አምላኪዎችም ቢሆን እሱን የማምለክ ነፃነት ለማግኘት ብዙ ጊዜ ትግል ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር።

3. የአምላክ ሕዝቦች በንግሥት አስቴር ዘመን ምን ዓይነት ትግል ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር?

3 ለምሳሌ ያህል፣ በንግሥት አስቴር ዘመን የአምላክ ሕዝቦች ሕልውናቸውን ላለማጣት መታገል አስፈልጓቸዋል። ይህ የሆነው እንዴት ነው? ሃማ የተባለው ክፉ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በንጉሡ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ እንዲገደሉ ለፋርስ ንጉሥ ለአሐሽዌሮስ ሐሳብ አቅርቦ ነበር፤ ይህን ሐሳብ ያቀረበው አይሁዳውያን “[የሚመሩበት] ሕግ ከሌሎቹ ሕዝቦች ሁሉ የተለየ” በመሆኑ ነው። (አስ. 3:8, 9, 13) ታዲያ ይሖዋ አገልጋዮቹ ሲጠፉ ዝም ብሎ ይመለከት ይሆን? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ አስቴርና መርዶክዮስ የአምላክን ሕዝቦች ለመታደግ ሲሉ የፋርሱን ንጉሥ ለማነጋገር ያደረጉትን ጥረት ባርኮላቸዋል።—አስ. 9:20-22

4. በዚህ ምዕራፍ ላይ ምን እንመለከታለን?

4 በዘመናችንስ? ቀደም ባለው ምዕራፍ ላይ እንደተመለከትነው መንግሥታት የይሖዋ ምሥክሮችን የተቃወሙባቸው ጊዜያት አሉ። በዚህ ምዕራፍ ላይ ደግሞ እንደ እነዚህ ያሉ መንግሥታት አምልኳችንን ከምናካሂድባቸው መንገዶች በአንዳንዶቹ ላይ እገዳ ለመጣል የሞከሩት እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን። በሚከተሉት ሦስት አቅጣጫዎች ይኸውም (1) ማኅበራችን ሕጋዊ እውቅና እንዲኖረው በማድረግና አምልኳችንን በምንፈልገው መንገድ በማካሄድ መብታችን፣ (2) ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት ጋር የሚስማማ ሕክምና በመምረጥ ነፃነታችን እንዲሁም (3) ወላጆች ከይሖዋ መመሪያ ጋር በሚስማማ መንገድ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ባላቸው መብት ላይ ትኩረት እናደርጋለን። በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ የመሲሐዊው መንግሥት ታማኝ ዜጎች፣ ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን ዜግነት ላለማጣት ከባድ ትግል ያደረጉትና ይሖዋም ይህን ጥረታቸውን የባረከላቸው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።

ሕጋዊ እውቅና እንዲሁም መሠረታዊ ነፃነቶችን ለማግኘት መታገል

5. እውነተኛ ክርስቲያኖች ሕጋዊ እውቅና ማግኘታቸው የሚጠቅማቸው እንዴት ነው?

5 ይሖዋን ለማምለክ ከሰብዓዊ መንግሥታት ሕጋዊ እውቅና ማግኘት ያስፈልገናል? በፍጹም። ሆኖም ሕጋዊ እውቅና ማግኘታችን አምልኳችንን ማከናወን ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል፤ ለምሳሌ በራሳችን የመንግሥት አዳራሾችና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች በነፃነት ለመሰብሰብ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማተምና ወደተለያዩ አገሮች ለማስገባት እንዲሁም ምሥራቹን ያለምንም እንቅፋት በነፃነት ለመስበክ ይረዳናል። በበርካታ አገሮች የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ እውቅና ያገኙ ሲሆን ተመሳሳይ እውቅና እንደተሰጣቸው ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ እነሱም የአምልኮ ነፃነት አላቸው። ይሁን እንጂ መንግሥታት ሕጋዊ እውቅና በከለከሉን ወይም መሠረታዊ ነፃነታችንን ለመገደብ በሞከሩበት ወቅትስ ምን አድርገናል?

6. በአውስትራሊያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ምን ዓይነት ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር?

6 አውስትራሊያ። በ1940ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የአውስትራሊያ ዋና አስተዳዳሪ፣ እምነታችን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ የሚደረገውን ጥረት “የሚያሰናክል” እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። በመሆኑም በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እገዳ ተጣለ። የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መሰብሰብም ሆነ መስበክ አልቻሉም፤ በቤቴል የሚከናወኑ ሥራዎች እንዲቆሙ ተደረገ፤ እንዲሁም የመንግሥት አዳራሾች ተወረሱ። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችንን ይዞ መገኘት እንኳ ተከለከለ። በአውስትራሊያ የሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለተወሰኑ ዓመታት ሥራቸውን በድብቅ ሲያከናውኑ ከቆዩ በኋላ በመጨረሻ ነፃነት አገኙ። ሰኔ 14, 1943 የአውስትራሊያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እገዳው እንዲነሳ አደረገ።

7, 8. በሩሲያ የሚኖሩ ወንድሞቻችን የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት ለበርካታ ዓመታት ምን ዓይነት ትግል አድርገዋል?

7 ሩሲያ። የኮሚኒስቱ መንግሥት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እገዳ ጥሎ ነበር፤ በ1991 ግን ሕጋዊ እውቅና አገኙ። የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ከፈራረሰች በኋላ ደግሞ የሩሲያ ፌዴሬሽን በ1992 ሕጋዊ እውቅና ሰጠን። ብዙም ሳይቆይ ግን አንዳንድ ተቃዋሚዎች በተለይም ከሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ንክኪ ያላቸው ሰዎች፣ ቁጥራችን በፍጥነት በመጨመሩ በጣም ተበሳጩ። በመሆኑም ተቃዋሚዎች ከ1995 እስከ 1998 ባሉት ዓመታት ውስጥ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ አምስት የወንጀል ክሶች መሠረቱ። በአምስቱም ጊዜያት የአቃቤ ሕጉ ቢሮ የይሖዋ ምሥክሮች ጥፋተኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማግኘት አልቻለም። እልኸኛ የሆኑት ተቃዋሚዎቻችን ግን በ1998 የፍትሐ ብሔር ክስ መሠረቱ። መጀመሪያ ላይ ለይሖዋ ምሥክሮች ቢፈረድላቸውም ተቃዋሚዎች ውሳኔውን አንቀበልም ብለው ይግባኝ አሉ፤ ከዚያም ግንቦት 2001 በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ተፈረደባቸው። በዚያው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ጉዳዩ እንደገና እንዲታይ የተደረገ ሲሆን በ2004 ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች በሞስኮ የሚጠቀሙበት ሕጋዊ ማኅበር እንዲፈርስ እና እንቅስቃሴው እንዲታገድ ወሰነ።

8 ከዚያም የስደት ማዕበል ተነሳ። (2 ጢሞቴዎስ 3:12ን አንብብ።) የይሖዋ ምሥክሮች ይሰደቡ እንዲሁም ጥቃት ይሰነዘርባቸው ነበር። ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ተወረሱ፤ እንዲሁም ለአምልኮ ሕንፃዎችን መከራየትም ሆነ መገንባት በጥብቅ ተከለከለ። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ምን እንደተሰማቸው መገመት አያዳግትም! የይሖዋ ምሥክሮች በ2001 ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው የነበረ ሲሆን በ2004 ደግሞ ለፍርድ ቤቱ ተጨማሪ መረጃ አቀረቡ። ይህ ፍርድ ቤት በ2010 ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ፣ ሩሲያ በይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ላይ እገዳ የጣለችው በሃይማኖታዊ ጥላቻ ምክንያት እንደሆነ በግልጽ መረዳት ችሏል፤ የትኛውም የይሖዋ ምሥክር መጥፎ ነገር እንደሠራ የሚጠቁም አንድም ማስረጃ ስላልተገኘ ከታች ያሉት ፍርድ ቤቶች የሰጡትን ውሳኔ ለመደገፍ የሚያስችል ምንም ምክንያት እንደሌለም ገልጿል። ፍርድ ቤቱ አክሎም እገዳው የተጣለው የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ መብት ለመንፈግ ተብሎ እንደሆነ ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታዊ ነፃነት የሚያስከብር ነው። አንዳንድ የሩሲያ ባለሥልጣናት የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የሰጠውን ውሳኔ ተግባራዊ ባያደርጉም በዚህች አገር ያሉት የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ያለ ድል በማግኘታቸው በጣም ተበረታትተዋል።

ቲቶስ ማኑሳኪስ (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9-11. በግሪክ የሚገኙ የይሖዋ ሕዝቦች ለአምልኮ የመሰብሰብ ነፃነታቸውን ለማስከበር የታገሉት እንዴት ነው? ምን ውጤትስ አግኝተዋል?

9 ግሪክ። በ1983 ቲቶስ ማኑሳኪስ በኢራክሊዮን፣ ቀርጤስ አንድ ክፍል ተከራየ፤ ይህን ያደረገው በዚያ ያሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች ለአምልኮ እንዲሰበሰቡበት በማሰብ ነው። (ዕብ. 10:24, 25) ብዙም ሳይቆይ ግን አንድ የኦርቶዶክስ ቄስ የይሖዋ ምሥክሮች ክፍሉን ለአምልኮ መጠቀማቸውን በመቃወም ለፖሊስ ክስ አቀረበ። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እምነት የተለየ ስለሆነ ብቻ ነው! የአቃቤ ሕጉ ቢሮ በቲቶስ ማኑሳኪስ እና በሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የወንጀል ክስ መሠረተ። እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የገንዘብ ቅጣት የተጣለባቸው ከመሆኑም በላይ የሁለት ወር እስር ተፈረደባቸው። የአምላክ መንግሥት ታማኝ ዜጎች የሆኑት እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የአምልኮ ነፃነታቸውን የሚጋፋ እንደሆነ ስለተሰማቸው በዚያ አገር ለሚገኙ ፍርድ ቤቶች ከዚያም ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ይግባኝ አሉ።

10 በመጨረሻም በ1996 የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት የንጹሑ አምልኮ ተቃዋሚዎች ፈጽሞ ያልጠበቁትን ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ፣ “የይሖዋ ምሥክሮች በግሪክ ሕግ መሠረት ‘የታወቁ ሃይማኖቶች’ ከሚባሉት መካከል እንደሚቆጠሩ” የገለጸ ሲሆን የታችኞቹ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ “የአመልካቾቹን የሃይማኖት ነፃነት በቀጥታ የሚጋፋ” እንደሆነ ተናግሯል። ፍርድ ቤቱ አክሎም የግሪክ መንግሥት “ሃይማኖታዊ እምነቶች ወይም እነዚህ እምነቶች የሚገለጹባቸው መንገዶች ትክክል መሆን አለመሆናቸውን የመወሰን” መብት እንደሌለው ገልጿል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተላለፈው ፍርድ ውድቅ የተደረገ ሲሆን የአምልኮ ነፃነታቸውም ተከብሮላቸዋል!

11 ታዲያ እንዲህ ያለ ድል መገኘቱ በግሪክ ያለው ችግር እንዲቀረፍ አድርጓል? የሚያሳዝን ቢሆንም ችግሮቹ ቀጠሉ። በካሳንድሪ፣ ግሪክ በተከሰተ ተመሳሳይ ሁኔታ የተነሳ 12 ዓመታት ገደማ የፈጀ የፍርድ ቤት ውዝግብ ሲካሄድ ከቆየ በኋላ በ2012 ጉዳዩ መፍትሔ አግኝቷል። በዚህኛው ጉዳይ ላይ ተቃውሞው እንዲባባስ ያደረገው አንድ የኦርቶዶክስ ጳጳስ ነው። በግሪክ ውስጥ ከፍተኛው የሕግ አካል የሆነው የአገሪቱ ምክር ቤት ለአምላክ ሕዝቦች በመፍረድ ጉዳዩ መፍትሔ እንዲያገኝ አድርጓል። ፍርድ ቤቱ፣ የግሪክ ሕገ መንግሥት የሰጠውን የሃይማኖት ነፃነት የጠቀሰ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች የታወቀ ሃይማኖት አይደሉም በሚል በተደጋጋሚ የሚቀርበውን ክስ ውድቅ አድርጎታል። ፍርድ ቤቱ እንዲህ ብሏል፦ “‘የይሖዋ ምሥክሮች’ የሚያምኑባቸው ነገሮች ከማንም የተደበቁ አይደሉም፤ ስለዚህ ሃይማኖታቸው የታወቀ ሃይማኖት እንደሆነ መግለጽ ይቻላል።” በካሳንድሪ የሚገኘው አነስተኛ ጉባኤ አባላት አሁን በራሳቸው የመንግሥት አዳራሽ ለአምልኮ መሰብሰብ በመቻላቸው ተደስተዋል።

12, 13. በፈረንሳይ ያሉ ተቃዋሚዎቻችን “በሕግ ስም ችግር ለመፍጠር” የሞከሩት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?

12 ፈረንሳይ። የአምላክን ሕዝቦች የሚቃወሙ አንዳንድ ሰዎች “በሕግ ስም ችግር ለመፍጠር [አሲረዋል።]” (መዝሙር 94:20ን አንብብ።) ለምሳሌ በ1990ዎቹ አጋማሽ ላይ የፈረንሳይ ግብር ሰብሳቢ ባለሥልጣናት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በፈረንሳይ ከሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ ማኅበሮች አንዱ የሆነውን የአሶሲያሲዮን ሌ ቴምዋን ደ ዤኦቫ የሒሳብ መዝገብ መመርመር ጀመሩ። የበጀት ሚኒስትሩ ይህ የሒሳብ ምርመራ የተደረገበትን እውነተኛ ዓላማ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦ ‘የሒሳብ ምርመራው ውጤት፣ የማኅበሩ ንብረት በፍርድ ቤት ትእዛዝ ተሽጦ ዕዳው እንዲከፈል ወይም የወንጀል ክስ እንዲመሠረት ያደርግ ይሆናል፤ ይህም የማኅበሩን እንቅስቃሴዎች የሚያዳክም አሊያም በክልላችን የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እንዲያቆም የሚያስገድድ ይሆናል።’ በሒሳብ ምርመራው ወቅት ምንም ዓይነት ችግር ባይገኝም የግብር ሰብሳቢ ባለሥልጣናቱ በማኅበሩ ላይ በጣም ከፍተኛ ግብር ጫኑበት። እቅዳቸው ቢሳካ ኖሮ ወንድሞች ይህንን ከፍተኛ ግብር ለመክፈል ሲሉ ቅርንጫፍ ቢሮውን ለመዝጋትና ሕንፃዎቹን ለመሸጥ ይገደዱ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ያለ ከባድ ጥቃት ቢሰነዘርባቸውም ተስፋ አልቆረጡም። የይሖዋ ምሥክሮች ፍትሐዊ ያልሆነ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው የገለጹ ሲሆን ውሎ አድሮም በ2005 ጉዳዩን ለአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት አቀረቡት።

13 ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ሰኔ 30, 2011 አስታወቀ። የሃይማኖት ነፃነት እስካለ ድረስ መንግሥት ለየት ያሉ ጉዳዮች ካልተፈጠሩ በስተቀር አንድ ሃይማኖት የሚያምንባቸውን ነገሮች ወይም እነዚህ እምነቶች የሚገለጹባቸው መንገዶች ትክክል መሆን አለመሆናቸውን የመመርመር መብት እንደማይኖረው ፍርድ ቤቱ ገልጿል። በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ እንዲህ ብሏል፦ ‘የተጣለው ግብር ማኅበሩ ያለውን ንብረትና ሊያገኝ የሚችለውን ስጦታ የሚያሳጣው ሲሆን ይህም ማኅበሩ፣ የሃይማኖቱ ተከታዮች አምልኳቸውን በነፃነት እንዲያካሂዱ ለመርዳት የሚያደርገውን ጥረት የሚያግድ ነው።’ ፍርድ ቤቱ በሙሉ ድምፅ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረደላቸው! የፈረንሳይ መንግሥት አሶሲያሲዮን ሌ ቴምዋን ደ ዤኦቫ እንዲከፍል አድርጎት የነበረውን ግብር እስከ ወለዱ በመመለሱ እንዲሁም በመያዣነት ይዞት የነበረውን የቅርንጫፍ ቢሮውን ንብረት በፍርድ ቤቱ ትእዛዝ መሠረት በመልቀቁ የይሖዋ ሕዝቦች በጣም ተደስተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የፍትሕ መጓደል እየደረሰባቸው ላሉ መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ አዘውትረህ መጸለይ ትችላለህ

14. የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት በሚደረገው ትግል አንተም የበኩልህን አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችለው እንዴት ነው?

14 በጥንት ዘመን እንደነበሩት እንደ አስቴርና መርዶክዮስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ ሕዝቦችም ይሖዋን እሱ ባዘዛቸው መሠረት የማምለክ ነፃነታቸውን ለማስከበር ትግል ያደርጋሉ። (አስ. 4:13-16) አንተስ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ ማድረግ ትችል ይሆን? አዎን። በአሁኑ ጊዜ የፍትሕ መጓደል እየደረሰባቸው ላሉ መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ አዘውትረህ መጸለይ ትችላለህ። እንዲህ ያለው ጸሎት፣ መከራና ስደት የሚያጋጥማቸው ወንድሞችንና እህቶችን በእጅጉ ሊረዳቸው ይችላል። (ያዕቆብ 5:16ን አንብብ።) ይሁንና ይሖዋ እነዚህን ጸሎቶች ሰምቶ እርምጃ ይወስዳል? በፍርድ ቤት ያገኘናቸው ድሎች ይህን እንደሚያደርግ ያረጋግጣሉ!—ዕብ. 13:18, 19

ከእምነታችን ጋር የሚስማማ ሕክምና የመምረጥ ነፃነት

15. የአምላክ ሕዝቦች ከደም ጋር በተያያዘ የትኞቹን ነገሮች ከግምት ያስገባሉ?

15 በምዕራፍ 11 ላይ እንደተመለከትነው የአምላክ መንግሥት ዜጎች፣ በዛሬው ጊዜ በጣም የተለመደ ከሆነው ደምን ያላግባብ የመጠቀም ልማድ እንዲርቁ የሚያዝዝ ግልጽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 9:5, 6፤ ዘሌ. 17:11፤ የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29ን አንብብ።) እኛም ሆንን ቤተሰቦቻችን ደም መውሰድ ባንፈልግም ከአምላክ ሕግ ጋር የማይጋጭ እስከሆነ ድረስ የተሻለ የተባለውን ሕክምና ማግኘት እንፈልጋለን። የብዙ አገሮች ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፣ ሰዎች ከሕሊናቸውና ከሃይማኖታዊ እምነታቸው አንጻር አንድን የሕክምና ዓይነት የመቀበል ወይም ያለመቀበል መብት እንዳላቸው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ በአንዳንድ አገሮች የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ረገድ ከባድ ፈተና አጋጥሟቸዋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

16, 17. በጃፓን አንዲት እህት ከተሰጣቸው ሕክምና ጋር በተያያዘ በኋላ ላይ ያስደነገጣቸው ምንድን ነው? ጸሎታቸው ምላሽ ያገኘውስ እንዴት ነው?

16 ጃፓን። ሜሳኤ ታኬዳ የተባሉ በጃፓን የሚኖሩ የ63 ዓመት የቤት እመቤት ከባድ ቀዶ ሕክምና ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። እኚህ እህት የአምላክ መንግሥት ታማኝ ዜጋ እንደመሆናቸው መጠን ያለ ደም ሕክምና እንዲደረግላቸው እንደሚፈልጉ ለሐኪሙ ነገሩት። ይሁንና ቀዶ ሕክምናው ከተካሄደ ከወራት በኋላ እህት ታኬዳ በሕክምናው ወቅት ደም እንደተሰጣቸው ሲያውቁ በጣም ደነገጡ። እህት ታኬዳ መብታቸው እንደተጣሰና እንደተታለሉ ስለተሰማቸው ሰኔ 1993 በሐኪሞቹና በሆስፒታሉ ላይ ክስ መሠረቱ። ትሑት የሆኑትና ኃይለ ቃል የማይወጣቸው እኚህ እህት ጽኑ አቋም ነበራቸው። እህት ታኬዳ አቅማቸው ቢዳከምም ሕዝብ ግጥም ባለበት ፍርድ ቤት ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል በድፍረት ምሥክርነት ሰጥተዋል። እህት ታኬዳ ለመጨረሻ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት ከመሞታቸው ከአንድ ወር በፊት ነበር። እኚህ እህት ያሳዩት ድፍረትና እምነት የሚያስደንቅ አይደለም? እህት ታኬዳ በሚያደርጉት ትግል ይሖዋ እንዲረዳቸው በተደጋጋሚ ይጸልዩ እንደነበር ተናግረዋል። ለጸሎታቸውም ምላሽ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ነበሩ። ታዲያ ምላሽ አግኝተው ይሆን?

17 እህት ታኬዳ ካረፉ ከሦስት ዓመት በኋላ የጃፓን ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከፍላጎታቸው ውጭ ደም መሰጠቱ ስህተት እንደነበረ በመግለጽ ለእሳቸው ፈርዶላቸዋል። የካቲት 29, 2000 የተሰጠው ብይን፣ እንደዚህ ባሉ ጉዳዮች ላይ “የመወሰን መብት እንደ ሰብዓዊ መብት ተቆጥሮ መከበር ይኖርበታል” ብሏል። እህት ታኬዳ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ከሠለጠነ ሕሊናቸው ጋር የሚስማማ ሕክምና የመምረጥ መብታቸውን ለማስከበር በቆራጥነት ትግል ማድረጋቸው ዛሬ በጃፓን ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች በግዳጅ ደም ይሰጠናል ብለው ሳይሰጉ የሕክምና እርዳታ መቀበል እንዲችሉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል።

ፓብሎ አልባራሲኒ (ከአንቀጽ 18 እስከ 20 ተመልከት)

18-20. (ሀ) በአርጀንቲና ያለ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት አንድ ሰው የሕክምና መመሪያ ሰነድ በመሙላት ደም መውሰድ እንደማይፈልግ የመግለጽ መብት ያለው መሆኑን ያረጋገጠው እንዴት ነው? (ለ) ከደም ጋር በተያያዘ ለክርስቶስ እንደምንገዛ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

18 አርጀንቲና። የአምላክ መንግሥት ዜጎች፣ ራሳቸውን ስተው ባሉበት ወቅት ምን ዓይነት ሕክምና እንዲሰጣቸው እንደሚመርጡ ለማሳወቅ አስቀድመው ምን ማድረግ ይችላሉ? ስለ እኛ ሆኖ አቋማችንን የሚያሳውቅ ሕጋዊ ሰነድ ይዘን መንቀሳቀስ እንችላለን። ፓብሎ አልባራሲኒ ይህን አድርጓል። ግንቦት 2012 ወንበዴዎች ፓብሎን ሊዘርፉት የሞከሩ ሲሆን በጥይት ደጋግመው መቱት። ሆስፒታል ሲደርስ ራሱን ስቶ ስለነበር ከደም ጋር በተያያዘ ያለውን አቋም ማስረዳት አልቻለም። ሆኖም ከአራት ዓመት በፊት የፈረመውና በሕግ ተቀባይነት ያለው የሕክምና መመሪያ ይዞ ነበር። ሕይወቱ አስጊ ደረጃ ላይ በመሆኑ አንዳንድ ሐኪሞች ሕይወቱን ለማትረፍ ደም ሊሰጠው እንደሚገባ ቢሰማቸውም ሌሎቹ የሕክምና ባለሙያዎች ግን ፍላጎቱን ለማክበር ፈለጉ። ይሁንና የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው የፓብሎ አባት የልጁን ውሳኔ ውድቅ የሚያደርግ የፍርድ ቤት ትእዛዝ ይዞ መጣ።

19 የፓብሎን ሚስት የወከለው ጠበቃ ወዲያውኑ ይግባኝ አለ። በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቱ የታችኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ሕመምተኛው፣ በሕክምና መመሪያው ላይ የገለጸው ፍላጎቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ፈረደ። የፓብሎ አባት ለአርጀንቲና ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ ፓብሎ ደም እንደማይወስድ የሚገልጽ ሐሳብ በሕክምና መመሪያ ሰነዱ ላይ ያሰፈረው “በማስተዋል፣ አስቦበትና ጫና ሳይደረግበት እንደሆነ የሚያጠራጥር ምንም ምክንያት” እንደሌለ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ እንዲህ ብሏል፦ “ክፉና ደጉን ለይቶ የሚያውቅና ለአቅመ አዳም የደረሰ ማንኛውም ሰው ስለ ጤናው አስቀድሞ መመሪያ ማስፈር እንዲሁም አንዳንድ የሕክምና ዓይነቶችን መቀበል ወይም አለመቀበል ይችላል። . . . በጽሑፍ ያሰፈረውን ይህን መመሪያ ሐኪሙ ተግባራዊ ሊያደርገው ይገባል።”

የሕክምና መመሪያ ሰነድ አለህ?

20 ወንድም ፓብሎ አልባራሲኒ ከዚያ ወዲህ ጤንነቱ ሙሉ በሙሉ ተስተካክሏል። ፓብሎ ይህን የሕክምና መመሪያ ሰነድ አስቀድሞ በመሙላቱ እሱም ሆነ ባለቤቱ ደስተኞች ናቸው። ይህ ወንድም፣ እንዲህ ያለ ቀላል ሆኖም አስፈላጊ እርምጃ በመውሰዱ በክርስቶስ ለሚመራው የአምላክ መንግሥት ተገዢ መሆኑን አሳይቷል። አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ተመሳሳይ እርምጃ ወስዳችኋል?

ኤፕርል ካዶሬ (ከአንቀጽ 21 እስከ 24 ተመልከት)

21-24. (ሀ) የካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከትናንሽ ልጆችና ከደም ጋር በተያያዘ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ እንዲያስተላልፍ ምክንያት የሆነው ምንድን ነው? (ለ) ይህ ሁኔታ የይሖዋ አገልጋይ የሆኑ ልጆችን የሚያበረታታቸው እንዴት ነው?

21 ካናዳ። በአጠቃላይ ሲታይ ፍርድ ቤቶች፣ ወላጆች ለልጆቻቸው የተሻለ የሚሉትን ሕክምና የመምረጥ መብት እንዳላቸው ይቀበላሉ። እንዲያውም ፍርድ ቤቶች፣ ብስለት ያላቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆች ከሕክምና ጋር በተያያዘ ራሳቸው የሚያደርጉት ውሳኔ እንዲከበርላቸው የፈቀዱባቸው ጊዜያት አሉ። ኤፕርል ካዶሬ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟት ነበር። ኤፕርል በ14 ዓመቷ ሰውነቷ ውስጥ ደም በመፍሰሱ ሆስፒታል ገባች። ከጥቂት ወራት በፊት ኤፕርል የሕክምና አሰጣጥን የሚመለከት ማሳሰቢያ የሚል ሰነድ በመሙላት ድንገተኛ ሁኔታ ቢያጋጥማት እንኳ ደም እንዲሰጣት እንደማትፈልግ ገልጻ ነበር። የሕክምና እርዳታ የሚያደርግላት ሐኪም ግን የኤፕርልን ፍላጎት የሚጠቁመውን በግልጽ የሰፈረ መመሪያ ችላ በማለት ደም እንዲሰጣት የሚያዝዝ የፍርድ ቤት ፈቃድ አወጣ። በመሆኑም ለኤፕርል ያለ ፍላጎቷ ደም ተሰጣት። ከጊዜ በኋላ ኤፕርል ሁኔታውን ተገድዶ ከመደፈር ጋር አመሳስላዋለች።

22 ኤፕርል እና ወላጆቿ ፍትሕ ለማግኘት ወደ ፍርድ ቤት ሄዱ። ከሁለት ዓመት በኋላ ጉዳዩ በካናዳ ጠቅላይ ፍርድ ቤት መታየት ጀመረ። ፍርድ ቤቱ፣ ከካናዳ ሕገ መንግሥት ጋር በተያያዘ በተደረገው ክርክር ለኤፕርል ባይፈርድላትም በሙግቱ ወቅት ያወጣችው ወጪ እንዲከፈላት አዝዟል፤ እንዲሁም ኤፕርልም ሆነች ብስለት ያላቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ሌሎች ልጆች የሚፈልጉትን ሕክምና ራሳቸው የመምረጥ መብታቸው እንዲከበር የሚያደርግ ውሳኔ አስተላልፏል። ፍርድ ቤቱ እንዲህ ብሏል፦ “ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች ስለ አንድ ዓይነት ሕክምና ያደረጉት ውሳኔ በሌሎች ተጽዕኖ ተደርጎባቸው ሳይሆን ራሳቸው አገናዝበው የወሰኑት እና ብስለት እንዳላቸው የሚያንጸባርቅ መሆኑን ማሳየት እንዲችሉ አጋጣሚ ሊሰጣቸው ይገባል።”

23 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያሳለፈው ይህ ውሳኔ፣ ብስለት ያላቸው ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን ሕገ መንግሥታዊ መብት ያስከበረ በመሆኑ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ይህ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት በካናዳ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች፣ አንድ ዓይነት ሕክምና ከ16 ዓመት በታች ለሆነ ልጅ አስፈላጊ እንደሆነ ከተሰማቸው ሕክምናው ለልጁ እንዲሰጠው ትእዛዝ ማስተላለፍ ይችሉ ነበር። ከዚህ ብይን በኋላ ግን ከ16 ዓመት በታች የሆናቸው ልጆች የራሳቸውን ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ብስለት እንዳላቸው ለማሳየት አጋጣሚ ሳይሰጣቸው አንድ ዓይነት ሕክምና እንዲቀበሉ ፍርድ ቤቶች ማዘዝ አይችሉም።

“የአምላክን ስም በማስከበርና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን በማረጋገጥ ረገድ አነስተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ”

24 ለሦስት ዓመት የተካሄደው ይህ የፍርድ ቤት ሙግት ውጤቱ የሚክስ ነበር? ኤፕርል “አዎ!” ብላለች። በአሁኑ ጊዜ ሙሉ ጤንነት ያላትና በአቅኚነት የምታገለግለው ኤፕርል እንዲህ ብላለች፦ “የአምላክን ስም በማስከበርና ሰይጣን ውሸታም መሆኑን በማረጋገጥ ረገድ አነስተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ።” የኤፕርል ተሞክሮ እንደሚጠቁመው በመካከላችን ያሉ ልጆች ቆራጥ አቋም በመውሰድ የአምላክ መንግሥት እውነተኛ ዜጎች መሆናቸውን ማሳየት ይችላሉ።—ማቴ. 21:16

ልጆችን በይሖዋ መሥፈርቶች መሠረት የማሳደግ መብት

25, 26. ወላጆች ከተፋቱ በኋላ አንዳንድ ጊዜ ምን ዓይነት ሁኔታ ይፈጠራል?

25 ይሖዋ፣ ልጆችን በእሱ መሥፈርቶች መሠረት የማሳደግ ኃላፊነትን ለወላጆች ሰጥቷል። (ዘዳ. 6:6-8፤ ኤፌ. 6:4) ይህን ኃላፊነት መወጣት በራሱ ተፈታታኝ ነው፤ በተለይ ደግሞ ወላጆች ሲፋቱ ሁኔታው ይበልጥ ከባድ ይሆናል። ወላጆች ስለ ልጆቻቸው አስተዳደግ ያላቸው አመለካከት በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነ ወላጅ ልጁን በክርስቲያናዊ መሥፈርቶች ኮትኩቶ ማሳደግ እንዳለበት ይሰማው ይሆናል፤ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ወላጅ ደግሞ በዚህ ላይስማማ ይችላል። እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ወላጅ የጋብቻው ጥምረት በፍቺ ቢፈርስም የልጁ አስተዳደግ ሁለቱንም ወላጆች እንደሚመለከታቸው በመገንዘብ የሌላኛውን ወላጅ መብት ሊያከብርለት ይገባል።

26 የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ወላጅ፣ ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ልጆቹን በሚፈልገው መንገድ ለማሳደግ ሲል ፍርድ ቤት የአሳዳጊነት መብት እንዲሰጠው ይጠይቅ ይሆናል። ልጆች በይሖዋ ምሥክሮች እምነት ውስጥ ማደጋቸው እንደሚጎዳቸው አንዳንዶች ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያሳድጓቸው ልጆች የልደት በዓላቸው እንደማይከበርላቸው፣ ሌሎች በዓላትን እንደማያከብሩ ሌላው ቀርቶ ሕይወታቸው አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ እንኳ “ሕይወት አድን” የሆነው ደም እንደማይሰጣቸው ይገልጻሉ። ደስ የሚለው ነገር፣ አብዛኞቹ ፍርድ ቤቶች ትኩረት የሚያደርጉት ለልጁ ይበልጥ በሚጠቅመው ነገር ላይ እንጂ የአንደኛው ወላጅ ሃይማኖት ጎጂ ስለ መሆኑ ባላቸው አመለካከት ላይ አይደለም። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

27, 28. አንድ ልጅ በይሖዋ ምሥክሮች እምነት ውስጥ ማደጉ እንደሚጎዳው ለቀረበው ክስ የኦሃዮ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምን ምላሽ ሰጠ?

27 ዩናይትድ ስቴትስ። የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ አንድ አባት፣ ልጁ በይሖዋ ምሥክሮች እምነት ውስጥ ማደጉ ሊጎዳው እንደሚችል በመግለጽ ያቀረበውን ክስ በ1992 የኦሃዮ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተመለከተው። የታችኛው ፍርድ ቤት በአባትየው ሐሳብ በመስማማት የአሳዳጊነት መብት ሰጥቶት ነበር። የልጁ እናት የሆነችው ጄኒፈር ፔተር፣ ልጇን ሄዳ መጠየቅ ቢፈቀድላትም “ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እምነት በምንም ዓይነት መንገድ እንዳታስተምረው” መመሪያ ተሰጥቷት ነበር። የታችኛው ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ይህ ትእዛዝ፣ እህት ፔተር ከልጇ ከቦቢ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ወይም በውስጡ ስለሚገኙት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች እንኳ ማውራት እንደማትችል የሚገልጽ እንደሆነ ተደርጎ ሊተረጎም ይችላል! እህት ፔተር ምን ተሰምቷት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? ይህች እናት በሁኔታው በጣም ብታዝንም ታጋሽ መሆንን እና ይሖዋ እርምጃ እስኪወስድ መጠበቅን እንደተማረች ተናግራለች። “ይሖዋ ምንጊዜም አጠገቤ ነበር” ብላለች። የእህት ፔተር ጠበቃ ከይሖዋ ድርጅት ድጋፍ እየተደረገላት ለኦሃዮ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለች።

28 ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የታችኛው ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ እንደማይስማማ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆች፣ ልጆቻቸውን የማስተማር መሠረታዊ መብት አላቸው፤ ይህም ሥነ ምግባራዊና ሃይማኖታዊ እሴቶቻቸውን የማስተማር መብትን ይጨምራል።” የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እሴቶች የልጁን አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤንነት እንደሚጎዱ ማረጋገጥ እስካልተቻለ ድረስ ፍርድ ቤቱ አንድ ወላጅ በያዘው ሃይማኖት ምክንያት ልጁን የማሳደግ መብቱ እንዲነፈግ የመፍረድ ሥልጣን እንደሌለው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ገልጿል። ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ እምነት የልጁን አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤንነት እንደሚጎዳ የሚያረጋግጥ ምንም ማስረጃ አላገኘም።

ብዙ ፍርድ ቤቶች ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸውን የማሳደግ መብት እንዳይነፈጉ የሚከላከል ብይን ሰጥተዋል

29-31. በዴንማርክ ያለች አንዲት እህት ልጇን የማሳደግ መብት ያጣችው ለምን ነበር? የዴንማርክ ጠቅላይ ፍርድ ቤትስ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ውሳኔ አስተላልፏል?

29 ዴንማርክ። አኒታ ሃንሰንም ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሟት ነበር፤ የቀድሞ ባለቤቷ የሰባት ዓመት ልጃቸውን አማንዳን የማሳደግ መብት እንዲሰጠው ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር። በ2000 የአውራጃው ፍርድ ቤት ለእህት ሃንሰን ልጇን የማሳደግ መብት የሰጣት ቢሆንም የአማንዳ አባት ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ አለ፤ ፍርድ ቤቱም የታችኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሻር ለአባትየው የአሳዳጊነት መብት ሰጠው። ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ እነዚህ ወላጆች በሃይማኖታቸው ምክንያት ስለ ሕይወት ያላቸው አመለካከት የተለያየ በመሆኑ ልጅቷን አባቷ ቢያሳድጋት የተሻለ እንደሚሆን ገልጿል። ከዚህ አንጻር እህት ሃንሰን፣ አማንዳን የማሳደግ መብቷን እንድታጣ ያደረጋት ዋነኛው ምክንያት የይሖዋ ምሥክር መሆኗ ነበር!

30 በዚህ አስቸጋሪ ወቅት እህት ሃንሰን አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመጨነቋ የተነሳ ምን ብላ እንደምትጸልይ እንኳ ግራ ይገባት ነበር። “ያም ቢሆን በሮም 8:26 እና 27 ላይ ያለው ሐሳብ በእጅጉ አጽናንቶኛል” ብላለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ምን ለማለት እንደፈለግኩ እንደሚያውቅ ሁልጊዜ ይሰማኝ ነበር። ምንጊዜም ዓይኑ በእኔ ላይ እንደሆነና መቼም ቢሆን እንደሚረዳኝ አውቅ ነበር።”—መዝሙር 32:8ን እና ኢሳይያስ 41:10ን አንብብ።

31 እህት ሃንሰን ጉዳዩን ለዴንማርክ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለች። ፍርድ ቤቱ የሰጠው ብያኔ እንዲህ ይላል፦ “ልጅን የማሳደግ መብት መወሰን ያለበት ለልጁ ይበልጥ የሚጠቅመው ምን እንደሆነ በሚገባ በማጤን መሆን ይኖርበታል።” ፍርድ ቤቱ አክሎም ልጅ ከማሳደግ መብት ጋር በተያያዘ የሚደረገው ውሳኔ መመሥረት ያለበት እያንዳንዱ ወላጅ ግጭቶችን በሚፈታበት መንገድ ላይ እንጂ በይሖዋ ምሥክሮች “ትምህርትና አቋም” ላይ እንዳልሆነ ገልጿል። ፍርድ ቤቱ፣ እህት ሃንሰን የወላጅነት ኃላፊነቷን የመወጣት ብቃት እንዳላት በመገንዘብ አማንዳን የማሳደግ መብት እንዲሰጣት መወሰኑ ይህችን እናት በጣም አስደስቷታል።

32. የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት፣ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች መድልዎ እንዳይፈጸምባቸው የተከላከለላቸው እንዴት ነው?

32 የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች። የልጆች አሳዳጊ ከመሆን ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ውዝግቦችን ለመፍታት በአንዳንድ አገሮች ከሚገኙት የመጨረሻ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች አልፎ መሄድ ያስፈለገባቸው ጊዜያት አሉ። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እንዲህ ያሉ ጉዳዮችንም ተመልክቷል። ይህ ፍርድ ቤት ከሁለት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ በየአገራቱ ያሉት ፍርድ ቤቶች የይሖዋ ምሥክር በሆኑትና ባልሆኑት ወላጆች መካከል በሃይማኖታቸው የተነሳ ልዩነት እንዳደረጉ ገልጿል። የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት እንዲህ ያለው አካሄድ መድልዎ የተንጸባረቀበት እንደሆነ በመግለጽ “በሃይማኖት ላይ ብቻ ተመሥርቶ ልዩነት ማድረግ ተቀባይነት የለውም” የሚል ውሳኔ አስተላልፏል። ይህ ፍርድ ቤት በሰጠው እንዲህ ያለ ውሳኔ የተጠቀመች አንዲት የይሖዋ ምሥክር እናት ደስታዋን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች፦ “ለልጆቼ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ የማስበውን ነገር በማድረጌ ይኸውም በክርስቲያናዊ መንገድ ለማሳደግ በመሞከሬ ልጆቼን እንደምጎዳ ተደርጌ መከሰሴ ስሜቴን በጣም ጎድቶት ነበር።”

33. የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ወላጆች በፊልጵስዩስ 4:5 ላይ ያለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

33 እርግጥ ነው፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በልጆቻቸው ልብ ውስጥ ቀርጸው ከማሳደግ መብታቸው ጋር በተያያዘ በፍርድ ቤት መከራከር ያስፈለጋቸው የይሖዋ ምሥክር ወላጆችም ምክንያታዊ መሆን ይኖርባቸዋል። (ፊልጵስዩስ 4:5ን አንብብ።) እነሱ ልጆቻቸውን በአምላክ መንገድ የማሠልጠን መብት እንዳላቸው ሁሉ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነው ወገንም ከፈለገ የወላጅነት ኃላፊነቱን ለመወጣት የበኩሉን የማድረግ መብት እንዳለው ሊገነዘቡ ይገባል። ይሁንና የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ወላጅ፣ ልጆቹን የማሠልጠኑን ኃላፊነት ምን ያህል አክብዶ መመልከት ይኖርበታል?

34. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን ወላጆች በነህምያ ዘመን ከነበሩት አይሁዳውያን ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

34 በነህምያ ዘመን የተፈጸመው ሁኔታ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል። አይሁዳውያን የኢየሩሳሌምን ቅጥር ለማደስና እንደገና ለመገንባት በትጋት እየሠሩ ነው። እንዲህ ማድረጋቸው እነሱንም ሆነ ቤተሰባቸውን በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው እንደሚጠብቃቸው ተገንዝበዋል። በዚህም ምክንያት ነህምያ “ለወንድሞቻችሁ፣ ለወንዶች ልጆቻችሁ፣ ለሴት ልጆቻችሁ፣ ለሚስቶቻችሁና ለቤታችሁ ተዋጉ” በማለት አሳሰባቸው። (ነህ. 4:14) እነዚያ አይሁዳውያን በዚህ ውጊያ ላይ የሚከፍሉት ማንኛውም መሥዋዕትነት የሚያስቆጭ አልነበረም። በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የይሖዋ ምሥክር ወላጆች ልጆቻቸውን በእውነት ጎዳና ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። ልጆቻቸው መጥፎ ነገሮችን እንዲያደርጉ በትምህርት ቤትም ሆነ በአካባቢያቸው ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚደረግባቸው ያውቃሉ። እንዲህ ያሉ ተጽዕኖዎች በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ቤታቸው ድረስ እንኳ ሊመጡ ይችላሉ። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ከመጥፎ ተጽዕኖዎች ተጠብቀው በመንፈሳዊ እንዲያድጉ የሚያስችላቸው ሁኔታ ቤታችሁ ውስጥ ለመፍጠር የምታደርጉት ማንኛውም ጥረት የሚክሳችሁ እንደሆነ አትርሱ።

ይሖዋ እውነተኛውን አምልኮ እንደሚደግፈው ተማመኑ

35, 36. የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ መብታቸውን ለማስከበር ያደረጉት ትግል ምን ጥቅሞች አስገኝቶላቸዋል? ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

35 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ባለው ድርጅቱ ውስጥ ያሉ አገልጋዮቹ የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት ያደረጉትን ትግል እንደባረከው ምንም ጥርጥር የለውም። የአምላክ ሕዝቦች ሕጋዊ መብታቸውን ለማስከበር ሲታገሉ ብዙውን ጊዜ በፍርድ ቤቶችም ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ ጥሩ ምሥክርነት መስጠት ችለዋል። (ሮም 1:8) በፍርድ ቤት ያገኘናቸው እነዚህ ድሎች ያስገኙት ሌላው ጥቅም ደግሞ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ሰዎች መብትም እንዲከበር ማድረጋቸው ነው። ይሁንና የአምላክ ሕዝቦች የማኅበራዊ ለውጥ አራማጆች አይደለንም፤ ወይም የሚያሳስበን ትክክለኛ መሆናችንን ማረጋገጥ አይደለም። የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ መብታቸውን በፍርድ ቤት ለማስከበር ጥረት የሚያደርጉበት ዋነኛው ምክንያት እውነተኛው አምልኮ በሕግ የጸና እንዲሆንና እንዲስፋፋ ስለሚፈልጉ ነው።—ፊልጵስዩስ 1:7ን አንብብ።

36 ይሖዋን በነፃነት ለማምለክ ሲሉ ትግል ያደረጉ ወንድሞችና እህቶች ከተዉት የእምነት ምሳሌ የምናገኘውን ትምህርት ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም! እኛም፣ ይሖዋ ሥራችንን እየደገፈው እንደሆነና የእሱን ፈቃድ ማድረጋችንን እንድንቀጥል ምንጊዜም ብርታት እንደሚሰጠን በመተማመን ታማኝ ሆነን እንቀጥል።—ኢሳ. 54:17