በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 18

የመንግሥቱ ሥራዎች ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ

የመንግሥቱ ሥራዎች ወጪ የሚሸፈንበት መንገድ

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

የይሖዋ ሕዝቦች ከመንግሥቱ ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን በገንዘብ የሚደግፉበት ምክንያትና ይህን የሚያደርጉበት መንገድ

1, 2. (ሀ) ወንድም ራስል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሥራቸውን ለማካሄድ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ ለጠየቀው አንድ አገልጋይ ምን ምላሽ ሰጥቶታል? (ለ) በዚህ ምዕራፍ ላይ የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?

 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ሥራቸውን ለማካሄድ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ የተሃድሶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ የሆነ አንድ ሰው ወንድም ቻርልስ ቴዝ ራስልን ጠይቆት ነበር።

ወንድም ራስል “ገንዘብ አንሰበስብም” በማለት መለሰለት።

አገልጋዩም “ታዲያ ከየት ታገኛላችሁ?” ብሎ ጠየቀ።

ወንድም ራስል “እውነቱን ብነግርህ አታምነኝም” አለው። አክሎም እንዲህ አለው፦ “ሰዎች ወደ ስብሰባዎቻችን ሲመጡ ሙዳየ ምጽዋት አይዞርላቸውም። ይሁን እንጂ ወጪዎች እንደሚኖሩ ይገነዘባሉ። በመሆኑም ‘በዚህ አዳራሽ መጠቀም ወጪ ያስወጣል። . . . ታዲያ እኔ አስተዋጽኦ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ ብለው ያስባሉ።”

አገልጋዩ ወንድም ራስልን እንዳላመነው አስተያየቱ ያስታውቃል።

ቀጥሎም ወንድም ራስል እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ የነገርኩህ ሐቁን ነው። . . . ሰዎች ‘ለዚህ ሥራ አስተዋጽኦ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?’ ብለው ይጠይቁኛል። አንድ ሰው ከተባረከና የሚሰጠው ነገር ካለው ይህን ንብረቱን ለጌታ አገልግሎት ሊጠቀምበት ይፈልጋል። ምንም ነገር ከሌለው ግን አምጣ ብለን ለምን እንጎተጉተዋለን?” a

2 በእርግጥም ወንድም ራስል የተናገረው “ሐቁን” ነበር። ከጥንትም ጀምሮ የአምላክ ሕዝቦች እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍ በፈቃደኝነት መዋጮ ያደርጉ ነበር። ይህ ምዕራፍ፣ በዚህ ረገድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንዲሁም በዘመናችን የተፈጸሙ ነገሮችን ይዳስሳል። በዛሬው ጊዜ የመንግሥቱን ሥራዎች ለማካሄድ የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኘው እንዴት እንደሆነ ስንመረምር እያንዳንዳችን ‘መንግሥቱን እንደምደግፍ ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው።

‘ልቡ ያነሳሳው ማንኛውም ሰው መዋጮ ያምጣ’

3, 4. (ሀ) ይሖዋ፣ በአገልጋዮቹ ላይ ምን ዓይነት እምነት አለው? (ለ) እስራኤላውያን የማደሪያው ድንኳን ሲሠራ ድጋፍ ያደረጉት እንዴት ነው?

3 ይሖዋ በእውነተኛ አገልጋዮቹ ላይ እምነት አለው። አጋጣሚውን ካገኙ በፈቃደኝነት በመስጠት ለእሱ ያላቸውን ፍቅር እንደሚያሳዩ ያውቃል። እስቲ በዚህ ረገድ በእስራኤላውያን ዘመን የተፈጸሙ ሁለት ምሳሌዎችን እንመልከት።

4 ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ካወጣቸው በኋላ በቀላሉ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችል ለአምልኮ የሚያገለግል ድንኳን እንዲሠሩ ነግሯቸው ነበር። ይህን ድንኳን ለመሥራትና ለማሳመር የሚያስፈልጉት ነገሮች እንዲሟሉ ብዙ ቁሳቁሶች ያስፈልጉ ነበር። ይሖዋ ‘ልቡ ያነሳሳው ማንኛውም ሰው ለይሖዋ መዋጮ ያምጣ’ የሚል መመሪያ ለሙሴ በመስጠት ሕዝቡ ሥራውን የመደገፍ አጋጣሚ እንዲያገኙ አደረገ። (ዘፀ. 35:5) ታዲያ “ማንኛውንም ዓይነት የባርነት ሥራ በማሠራት በጭካኔ ያንገላቷቸው” ከነበሩት ከግብፃውያን ነፃ ከወጡ ብዙም ያልቆዩት እስራኤላውያን ምን ምላሽ ሰጡ? (ዘፀ. 1:14) እስራኤላውያን ወርቅ፣ ብርና ሌሎች የከበሩ ነገሮችን በፈቃደኝነት በመስጠት ለሥራው ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል፤ አብዛኞቹን ነገሮች ያገኙት የቀድሞ ጌቶቻቸው ከነበሩት ግብፃውያን ሳይሆን አይቀርም። (ዘፀ. 12:35, 36) እስራኤላውያን የሰጡት ያስፈልግ ከነበረው በላይ ስለሆነ ከዚያ በኋላ ‘ምንም ነገር እንዳያመጡ ተገቱ’ ወይም ተከለከሉ።—ዘፀ. 36:4-7

5. እስራኤላውያን ለቤተ መቅደሱ ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ዳዊት አጋጣሚ ሲሰጣቸው ምን አደረጉ?

5 ይህ ከተፈጸመ 475 ከሚያህሉ ዓመታት በኋላ ደግሞ ዳዊት የቤተ መቅደሱን ሥራ በገንዘብ ለመደገፍ ሲል ‘ከግል ሀብቱ’ ስጦታ ሰጥቷል፤ ይህ ቤተ መቅደስ በምድር ላይ የመጀመሪያው ቋሚ የሆነ የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነበር። ከዚያም ዳዊት “ዛሬ ለይሖዋ የሚሰጥ ስጦታ በእጁ ይዞ ለመቅረብ ፈቃደኛ የሆነ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ በማቅረብ እስራኤላውያንም ተመሳሳይ ነገር እንዲያደርጉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል። ሕዝቡም ‘በፈቃደኝነት ተነሳስተው ለይሖዋ በሙሉ ልባቸው መባ ሰጡ።’ (1 ዜና 29:3-9) ዳዊት “ሁሉም ነገር የተገኘው ከአንተ ነውና፤ የሰጠንህም ከገዛ እጅህ የተቀበልነውን ነው” የሚል ጸሎት ለይሖዋ በማቅረብ የሰጡትን ነገር ያገኙት ከማን እንደሆነ መገንዘቡን አሳይቷል።—1 ዜና 29:14

6. በዛሬው ጊዜ መንግሥቱ ለሚያከናውነው ሥራ ገንዘብ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?

6 ሙሴም ሆነ ዳዊት፣ የአምላክ ሕዝቦች ስጦታ እንዲሰጡ ግፊት አላደረጉም። ከዚህ ይልቅ ሕዝቡ የሰጡት ልባቸው ስላነሳሳቸው ነው። ዛሬስ? የአምላክ መንግሥት የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ለማስኬድ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ እናውቃለን። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ለማተምና ለማሰራጨት፣ የአምልኮ ቦታዎችንና ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመገንባት ብሎም ለመንከባከብ እንዲሁም አደጋ በሚከሰትበት ወቅት ለእምነት ባልንጀሮቻችን አስቸኳይ እርዳታ ለማቅረብ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያስፈልጋል። በመሆኑም የሚከተሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ፦ ለሥራው የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኘው እንዴት ነው? መዋጮ እንዲያደርጉ የንጉሡን ተከታዮች መጎትጎት ያስፈልጋል?

“ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም አይለምንም ወይም አይማጠንም”

7, 8. የይሖዋ ሕዝቦች ገንዘብ ለማግኘት የማይለምኑት ለምንድን ነው?

7 ወንድም ራስልና አጋሮቹ በሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በሰፊው የሚሠራበትን የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ መከተል አልፈለጉም። ወንድም ራስል፣ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሁለተኛ እትም ላይ “‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብን’ ትፈልጋለህ?” በሚለው ርዕስ ሥር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “‘የጽዮን መጠበቂያ ግንብ’ ደጋፊ ይሖዋ ራሱ እንደሆነ እናምናለን። ይህ በመሆኑም መጠበቂያ ግንብ፣ ከሰዎች ድጋፍ ለማግኘት በፍጹም አይለምንም ወይም አይማጠንም። ‘የተራሮች ወርቅና ብር ሁሉ የእኔ ነው’ ያለው አምላክ የሚያስፈልገንን ገንዘብ ማስገኘት ካቃተው ያን ጊዜ መጽሔቱን ማተም ማቆም እንደሚኖርብን እናውቃለን።” (ሐጌ 2:7-9) ከ130 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላም መጠበቂያ ግንብ በስፋት እየተሰራጨ ሲሆን መጽሔቱን የሚያሳትመው ድርጅትም ቢሆን ተጠናክሮ ቀጥሏል።

8 የይሖዋ ሕዝቦች ገንዘብ ለማግኘት አይለምኑም። ሙዳየ ምፅዋት አያዞሩም፤ ወይም ሰዎች ገንዘብ እንዲያዋጡ አይጠይቁም። አሊያም ደግሞ የንግድ እንቅስቃሴዎችን አያካሂዱም። ከብዙ ዓመታት በፊት መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን የሚከተለውን ሐሳብ ተግባራዊ ያደርጋሉ፦ “ብዙዎች እንደሚያደርጉት በጌታ ስም መለመን ተገቢ እንደሆነ አይሰማንም፤ . . . የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ በጌታ ስም ገንዘብ መለመን ጌታን የሚያዋርድ ሲሆን በእሱ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው ይሰማናል፤ ጌታ ሰጪውንም ሆነ በዚህ ገንዘብ የሚከናወነውን ሥራ አይባርከውም።” b

“እያንዳንዱ ሰው . . . በልቡ ያሰበውን ይስጥ”

9, 10. በፈቃደኝነት መዋጮ የምናደርግበት አንዱ ምክንያት ምንድን ነው?

9 በዛሬው ጊዜ ያለነው የመንግሥቱ ተገዢዎችም ገንዘብ እንድንሰጥ መጎትጎት አያስፈልገንም። ከዚህ በተቃራኒ የመንግሥቱን እንቅስቃሴዎች ለመደገፍ ገንዘባችንንም ሆነ ሌሎች ንብረቶቻችንን በደስታ እንሰጣለን። ይሁንና ለመስጠት ይህን ያህል ፈቃደኛ የሆንነው ለምንድን ነው? እስቲ ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት።

10 አንደኛ፣ ይሖዋን ስለምንወድና “በፊቱ ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች” ማድረግ ስለምንፈልግ በፈቃደኝነት መዋጮ እናደርጋለን። (1 ዮሐ. 3:22) ይሖዋ፣ ከልቡ ተነሳስቶ ደስ እያለው በሚሰጥ አገልጋዩ ይደሰታል። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖች ስለሚሰጡት ስጦታ የጻፈውን ሐሳብ እስቲ እንመርምር። (2 ቆሮንቶስ 9:7ን አንብብ።) አንድ እውነተኛ ክርስቲያን የሚሰጠው ቅር እያለው ወይም ግድ ስለሆነበት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ስጦታ የሚሰጠው ‘በልቡ ስላሰበ’ ወይም ልቡ ስለፈቀደ ነው። c በሌላ አባባል ልግስና የሚያደርገው ምን እንደሚያስፈልግና ይህንን ለማሟላት ምን ማድረግ እንደሚችል ካሰበበት በኋላ ነው። “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ” እንዲህ ያለ ሰጪ በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅ ነው። አንድ ሌላ ትርጉም “አምላክ መስጠት የሚወዱ ሰዎችን ይወዳል” ይላል።

በመካከላችን ያሉ ልጆች ጭምር መስጠት ያስደስታቸዋል፣ ሞዛምቢክ

11. ለይሖዋ ምርጣችንን ለመስጠት የሚያነሳሳን ምንድን ነው?

11 ሁለተኛ፣ በቁሳዊ ነገሮች አስተዋጽኦ የምናደርገው ይሖዋ ለሰጠን ስፍር ቁጥር የሌላቸው በረከቶች አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ የሚገኘውን ልብን ለመፈተሽ የሚያነሳሳ መሠረታዊ ሥርዓት እንመልከት። (ዘዳግም 16:16, 17ን አንብብ።) እያንዳንዱ እስራኤላዊ በሦስቱ ዓመታዊ በዓላት ላይ በሚገኝበት ጊዜ ‘ይሖዋ በባረከው መጠን’ ስጦታ መስጠት ነበረበት። ይህ ሲባል እያንዳንዱ እስራኤላዊ በዓሉ ላይ ከመገኘቱ በፊት፣ ያገኛቸውን በረከቶች መለስ ብሎ ማሰብ ከዚያም ልቡን መርምሮ ሊሰጥ የሚችለውን የላቀ ስጦታ መወሰን ነበረበት ማለት ነው። በተመሳሳይ እኛም ይሖዋ በየትኞቹ መንገዶች አትረፍርፎ እንደባረከን ስናስብ በተቻለ መጠን ምርጣችንን ለእሱ ለመስጠት እንነሳሳለን። ቁሳዊ ልግስናን ጨምሮ በሙሉ ልባችን የምንሰጠው ስጦታ ከይሖዋ ያገኘነውን የተትረፈረፈ በረከት ምን ያህል እንደምናደንቅ የምናሳይበት መንገድ ነው።—2 ቆሮ. 8:12-15

12, 13. በፈቃደኝነት የምናደርገው መዋጮ ለንጉሡ ያለንን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት ነው? አንድ ሰው መስጠት ያለበት ምን ያህል ነው?

12 ሦስተኛ፣ በፈቃደኝነት መዋጮ ስናደርግ ንጉሡን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደምንወድ እናሳያለን። እንዴት? ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን እንመልከት። (ዮሐንስ 14:23ን አንብብ።) ኢየሱስ “ማንም ሰው እኔን የሚወደኝ ከሆነ ቃሌን ይጠብቃል” ብሎ ነበር። የኢየሱስ ‘ቃል’ የመንግሥቱን ምሥራች በመላው ምድር እንድንሰብክ የሰጠንን ትእዛዝ ይጨምራል። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) የመንግሥቱን ስብከት ሥራ ለማከናወን የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ይኸውም ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንና ቁሳዊ ሀብታችንን በመጠቀም የኢየሱስን ‘ቃል’ እንጠብቃለን። በዚህ መንገድ መሲሐዊውን ንጉሥ እንደምንወደው እናሳያለን።

13 በእርግጥም ታማኝ የመንግሥቱ ተገዢዎች እንደመሆናችን መጠን የገንዘብ አስተዋጽኦ በማድረግ መንግሥቱን በሙሉ ልባችን እንደምንደግፍ እናሳያለን። ይህን የምናደርገው እንዴት ነው? ይህ ለእያንዳንዱ ግለሰብ የተተወ ውሳኔ ነው። ሁሉም ሰው አቅሙ የፈቀደለትን ያህል ይሰጣል። እርግጥ ነው፣ አብዛኞቹ የእምነት ባልንጀሮቻችን ብዙ ቁሳዊ ንብረት የላቸውም። (ማቴ. 19:23, 24፤ ያዕ. 2:5) ያም ቢሆን እነዚህ ሰዎች፣ ይሖዋና ልጁ ከልብ የሚደረግን አነስተኛ መዋጮ እንኳ ከፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ማወቃቸው ያጽናናቸዋል።—ማር. 12:41-44

ገንዘብ የምናገኘው እንዴት ነው?

14. ለበርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን የሚያበረክቱት እንዴት ነበር?

14 ለበርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮች ጽሑፎችን የሚያበረክቱት፣ ሰዎችን የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ እያስከፈሉ ነበር። በእርግጥ፣ አቅማቸው ውስን የሆነ ሰዎችም እንኳ ጽሑፎችን መውሰድ እንዲችሉ ሲባል ለጽሑፎቻችን የምንጠይቀው ገንዘብ በጣም አነስተኛ ነበር። አንድ ሰው ጽሑፍ መውሰድ ፈልጎ መዋጮውን ለማድረግ አቅም ባይኖረው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ጽሑፉን አይከለክሉትም። ዋናው ፍላጎታቸው፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ጽሑፎችን እንዲያገኙና አንብበው እንዲጠቀሙ ነው።

15, 16. (ሀ) በ1990 የበላይ አካሉ፣ ጽሑፎችን በምናበረክትበት መንገድ ላይ ምን ማስተካከያ ማድረግ ጀመረ? (ለ) ሰዎች በፈቃደኝነት መዋጮ የሚያደርጉት እንዴት ነው? (“ የምናደርገው መዋጮ ጥቅም ላይ የሚውለው እንዴት ነው?” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

15 በ1990 የበላይ አካሉ፣ ጽሑፎችን ለሰዎች በምናበረክትበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ጀመረ። ከዚያ ዓመት ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ያሉ ወንድሞች፣ ሁሉንም ጽሑፎቻችንን ሲያበረክቱ ሰዎች በፈቃደኝነት የፈለጉትን ያህል የገንዘብ መዋጮ እንዲያደርጉ ከመጋበዝ ውጪ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲሰጡ መጠየቅ አቆሙ። በዚያ አገር ለሚገኙ ለሁሉም ጉባኤዎች የተላከው ደብዳቤ እንዲህ ይላል፦ “አስፋፊዎችም ሆኑ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች መጽሔቶችንና ጽሑፎችን መውሰድ ሲፈልጉ የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲሰጡ አይጠየቁም፤ ሌላው ቀርቶ እንዲህ እንዲያደርጉ ሐሳብ እንኳ አይቀርብላቸውም። . . . የማስተማር ሥራችንን በገንዘብ መደገፍ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ይህን ማድረግ የሚችል ቢሆንም መዋጮ አደረገም አላደረገ ጽሑፍ ማግኘት ይችላል።” ይህ ዝግጅት፣ በፈቃደኝነት በሚደረግ መዋጮ እየተደገፈ ሥራውን የሚያከናውን ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዳለንና ‘የአምላክን ቃል እንደማንሸቃቅጥ’ ግልጽ እንዲሆን አድርጓል። (2 ቆሮ. 2:17) ቀስ በቀስ ይህ ዝግጅት በዓለም ዙሪያ ባሉ በሁሉም ቅርንጫፍ ቢሮዎች ተግባራዊ እንዲሆን ተደረገ።

16 ሰዎች በፈቃደኝነት መዋጮ የሚያደርጉት እንዴት ነው? በይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥት አዳራሾች ውስጥ የመዋጮ ሣጥኖች ይቀመጣሉ። ግለሰቦች መዋጯቸውን በእነዚህ ሣጥኖች ውስጥ መጨመር አሊያም የይሖዋ ምሥክሮች ከሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ ማኅበሮች ወደ አንዱ በቀጥታ መላክ ይችላሉ። እንዲህ ያሉ የፈቃደኝነት መዋጮዎችን ማድረግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ በየዓመቱ መጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣል።

ገንዘቡ ሥራ ላይ የሚውለው እንዴት ነው?

17-19. ከመዋጮ የተገኘው ገንዘብ (ሀ) ለዓለም አቀፉ ሥራ፣ (ለ) ለዓለም አቀፉ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ እና (ሐ) ለጉባኤ ወጪዎች የሚውለው እንዴት እንደሆነ አብራራ።

17 ለዓለም አቀፉ ሥራ። ለዚህ ዓላማ የሚዋጣው ገንዘብ ዓለም አቀፉን የስብከት ሥራ ለማከናወን የወጣውን ወጪ ለመሸፈን ይውላል። ይህም በዓለም ዙሪያ የሚሰራጩትን ጽሑፎች ለማዘጋጀት፣ ቅርንጫፍ ቢሮዎችንና የቤቴል ቤቶችን ለመገንባት ብሎም በዚያ የሚከናወነውን ሥራ ለማስኬድ እንዲሁም ለተለያዩ ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች የሚወጣውን ወጪ ይጨምራል። በተጨማሪም ገንዘቡ የሚስዮናውያንን፣ የተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንና የልዩ አቅኚዎችን ወጪ ለመሸፈን ያገለግላል። የምናዋጣው ገንዘብ፣ በተፈጥሮ አደጋዎችና በሌሎች ምክንያቶች ችግር ላይ ለወደቁ የእምነት ባልንጀሮቻችን አስቸኳይ እርዳታ ለመስጠትም ይውላል። d

18 ለዓለም አቀፉ የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ። ለዚህ ዓላማ የሚዋጣው ገንዘብ፣ የመንግሥት አዳራሽ መሥራት ወይም ማደስ የሚያስፈልጋቸው ጉባኤዎችን ለመርዳት ይውላል። ጉባኤዎች መዋጮ ሲያደርጉ ገንዘቡ ሌሎች ጉባኤዎችን ለመርዳት ያገለግላል። e

19 ለጉባኤ ወጪዎች። ለዚህ ዓላማ የሚዋጣው ገንዘብ፣ ለመንግሥት አዳራሹ በየጊዜው የሚወጡ ወጪዎችን ለመሸፈንና አዳራሹ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ያገለግላል። ሽማግሌዎች፣ ዓለም አቀፉን ሥራ እንዲያግዝ ከዚህ ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ለመላክ ሐሳብ ሊያቀርቡ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ሽማግሌዎች፣ ጉባኤው በጉዳዩ ላይ ድምፀ ውሳኔ እንዲያደርግ ይጠይቃሉ። ጉባኤው በሐሳቡ ከተስማማ ገንዘቡ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ይላካል። ከጉባኤው ሒሳብ ጋር የተያያዘውን ሥራ የሚያከናውነው ወንድም በየወሩ የሒሳብ ሪፖርት የሚያዘጋጅ ሲሆን ይህም ለጉባኤው ይነበባል።

20. ይሖዋን “ባሉህ ውድ ነገሮች” ማክበር የምትችለው እንዴት ነው?

20 በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ጋር በተያያዘ ምን ያህል ሰፊ እንቅስቃሴ እንደሚካሄድ መመልከታችን ይሖዋን ‘ባሉን ውድ ነገሮች ለማክበር’ ያነሳሳናል። (ምሳሌ 3:9, 10) ካሉን ውድ ነገሮች መካከል ጉልበታችን፣ አእምሯችን እንዲሁም ከመንፈሳዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ ችሎታዎቻችን ይገኙበታል። እነዚህን ነገሮች ለመንግሥቱ ሥራ ሙሉ በሙሉ ማዋል እንደምንፈልግ ጥያቄ የለውም። ያሉን ውድ ነገሮች፣ ቁሳዊ ንብረታችንንም እንደሚጨምሩ አንዘንጋ። በምንችልበት ጊዜ የምንችለውን ያህል ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በፈቃደኝነት የምናደርገው መዋጮ ለይሖዋ ክብር የሚያመጣ ከመሆኑም ሌላ መሲሐዊውን መንግሥት እንደምንደግፍ የሚያሳይ ነው።

a መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 15, 1915 (እንግሊዝኛ) ከገጽ 218-219

b መጠበቂያ ግንብ ነሐሴ 1, 1899 (እንግሊዝኛ) ገጽ 201

c አንድ ምሁር እንደተናገሩት እዚህ ጥቅስ ላይ “ያሰበውን” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አስቀድሞ መወሰን የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል።” አክለውም “መስጠት በማንኛውም ጊዜ ደስታ የሚያስገኝ ቢሆንም ስጦታው አስቀድሞ የታሰበበትና ዝግጅት የተደረገበት ሊሆን ይገባል” ብለዋል።—1 ቆሮ. 16:2

d ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስለምንሰጠው የእርዳታ አገልግሎት ተጨማሪ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 20ን ተመልከት።

e ስለ መንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሰፊ ሐሳብ ለማግኘት ምዕራፍ 19ን ተመልከት።