በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 20

የእርዳታ አገልግሎት

የእርዳታ አገልግሎት

የምዕራፉ ፍሬ ሐሳብ

በአስቸጋሪ ወቅቶች በተግባር የታየ ክርስቲያናዊ ፍቅር

1, 2. (ሀ) በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች ምን አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጠማቸው? (ለ) በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች የትኛውን የፍቅር ድርጊት ተመልክተዋል?

 ወቅቱ 46 ዓ.ም. ገደማ ሲሆን ይሁዳ በረሃብ ተጠቅታለች። ከፍተኛ የእህል እጥረት ስላለ የምግብ ዋጋ የማይቀመስ ሆኗል፤ በመሆኑም በይሁዳ ያሉት የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እህል ለመግዛት የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። የምግብ እጥረቱ እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች፣ ማንኛውም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከዚያ በፊት ባላየው መንገድ የይሖዋን እጅ ሊያዩ ነው። እንዴት?

2 በሶርያ፣ አንጾኪያ የሚገኙ አይሁድና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች ባጋጠማቸው ችግር ስላዘኑ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው የሚሆን ገንዘብ አሰባሰቡ። ከዚያም ከመካከላቸው ሁለት ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞችን ይኸውም በርናባስንና ሳኦልን መርጠው እርዳታውን በኢየሩሳሌም ላሉት የጉባኤ ሽማግሌዎች እንዲያደርሱ ላኳቸው። (የሐዋርያት ሥራ 11:27-30⁠ን እና 12:25ን አንብብ።) በይሁዳ ያሉት የተቸገሩ ወንድሞች፣ በአንጾኪያ ያሉ ወንድሞቻቸው ባሳዩዋቸው ፍቅር ልባቸው በጥልቅ ተነክቶ እንደሚሆን አያጠራጥርም!

3. (ሀ) በዘመናችን ያሉ የአምላክ ሕዝቦች በአንጾኪያ የነበሩትን የጥንት ክርስቲያኖች አርዓያ የሚከተሉት እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ። (“ በዘመናችን ያከናወንነው የመጀመሪያው መጠነ ሰፊ የእርዳታ ሥራ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።) (ለ) በዚህ ምዕራፍ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

3 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተከሰተው ይህ ሁኔታ በአንድ ቦታ ያሉ ክርስቲያኖች በሌላ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ወንድሞቻቸውን ለማገዝ ስለላኩት እርዳታ የሚገልጽ የመጀመሪያው በጽሑፍ የሰፈረ ዘገባ ነው። በዛሬው ጊዜ እኛም የአንጾኪያ ወንድሞቻችን የተዉትን ምሳሌ እንከተላለን። በሌላ አካባቢ ያሉ የእምነት ባልንጀሮቻችን በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ችግር ላይ እንደወደቁ ስናውቅ እርዳታ እናደርግላቸዋለን። a እርዳታ ለመስጠት የምናደርገው ጥረት ከሌሎች የአገልግሎት እንቅስቃሴዎቻችን ጋር እንዴት እንደሚያያዝ ለመረዳት እንድንችል የእርዳታ አገልግሎትን በተመለከተ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመረምራለን፦ እርዳታ መስጠትን እንደ አገልግሎት የምንቆጥረው ለምንድን ነው? የእርዳታ ሥራ የምናከናውንበት ዓላማ ምንድን ነው? ከእርዳታ አገልግሎት ምን ጥቅሞች እናገኛለን?

የእርዳታ ሥራ “ቅዱስ አገልግሎት” የሆነው ለምንድን ነው?

4. ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ወንድሞች ስለ ክርስቲያናዊው አገልግሎት ምን ብሏቸዋል?

4 ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ የክርስቲያኖች አገልግሎት ሁለት ገጽታዎች እንዳሉት ገልጿል። ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ቢሆንም የተናገረው ነገር በዛሬው ጊዜ ላሉ የክርስቶስ “ሌሎች በጎች” ጭምር ይሠራል። (ዮሐ. 10:16) የአገልግሎታችን አንዱ ገጽታ “የማስታረቅ አገልግሎት” ይኸውም የስብከቱና የማስተማሩ ሥራ ነው። (2 ቆሮ. 5:18-20፤ 1 ጢሞ. 2:3-6) ሌላው ገጽታ ደግሞ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስንል የምናከናውነው አገልግሎት ነው። ጳውሎስ ይህን አገልግሎት ‘የእርዳታ አገልግሎት’ በማለት ጠርቶታል። (2 ቆሮ. 8:4) “የማስታረቅ አገልግሎት” እና ‘የእርዳታ አገልግሎት’ በሚሉት በሁለቱም አገላለጾች ላይ “አገልግሎት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ዲያኮኒያ ነው። ታዲያ ይህ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

5. ጳውሎስ የእርዳታ ሥራው፣ አገልግሎት እንደሆነ መናገሩ ትኩረታችንን የሚስበው ለምንድን ነው?

5 ጳውሎስ በሁለቱም ቦታዎች ላይ አንድ ዓይነት የግሪክኛ ቃል መጠቀሙ የእርዳታውን ሥራ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ከሚከናወኑ ሌሎች አገልግሎቶች ጋር እንደፈረጀው የሚያሳይ ነው። ቀደም ሲል እንዲህ በማለት ጽፎ ነበር፦ “ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ሁሉም አገልግሎት የሚቀርበው ግን ለአንድ ጌታ ነው፤ በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሥራዎች አሉ፤ ሆኖም . . . እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው።” (1 ቆሮ. 12:4-6, 11) እንዲያውም ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ የሚከናወኑትን የተለያዩ አገልግሎቶች ‘ከቅዱስ አገልግሎት’ ጋር አያይዞ ገልጿቸዋል። b (ሮም 12:1, 6-8) ከዚህ አንጻር፣ ሐዋርያው የተወሰነ ጊዜውን “ቅዱሳንን ለማገልገል” መመደቡ አስፈላጊ እንደሆነ የተሰማው መሆኑ አያስገርምም!—ሮም 15:25, 26

6. (ሀ) ጳውሎስ እንደተናገረው የእርዳታ ሥራ የአምልኳችን ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የእርዳታ ሥራ የምናከናውነው እንዴት እንደሆነ ግለጽ። (“ አደጋ ሲከሰት!” የሚለውን በገጽ 214 ላይ የሚገኝ ሣጥን ተመልከት።)

6 ጳውሎስ የእርዳታ ሥራ፣ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት አገልግሎትና ለይሖዋ የሚያቀርቡት አምልኮ ክፍል የሆነበትን ምክንያት እንዲገነዘቡ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን ረድቷቸዋል። ያቀረበውን ማስረጃ እንመልከት፦ እርዳታ የሚሰጡ ክርስቲያኖች ይህን የሚያደርጉት “ስለ ክርስቶስ ለሚገልጸው ምሥራች ተገዢዎች [ስለሆኑ]” እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:13) ክርስቲያኖች የክርስቶስን ትምህርት በሥራ ማዋል ስለሚፈልጉ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ይረዳሉ። ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ሲሉ የሚያከናውኑት የደግነት ተግባር “አምላክ [የሰጣቸው] የላቀ ጸጋ” መገለጫ እንደሆነ ተናግሯል። (2 ቆሮ. 9:14፤ 1 ጴጥ. 4:10) ከዚህ አንጻር፣ የታኅሣሥ 1, 1975 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) የተቸገሩ ወንድሞቻችንን ስለማገልገል (የእርዳታ ሥራን ይጨምራል) የሚከተለውን ሐሳብ መስጠቱ የተገባ ነው፦ “ይሖዋ አምላክና ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዚህ ዓይነቱ አገልግሎት ከፍ ያለ ቦታ እንደሚሰጡ ፈጽሞ ልንጠራጠር አይገባም።” በእርግጥም የእርዳታ ሥራ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ‘የቅዱስ አገልግሎት’ ክፍል ነው።—ሮም 12:1, 7፤ 2 ቆሮ. 8:7፤ ዕብ. 13:16

ግልጽ ዓላማዎች ያሉት እርዳታ

7, 8. የምናከናውነው የእርዳታ አገልግሎት የመጀመሪያ ዓላማ ምንድን ነው? አብራራ።

7 የእርዳታ አገልግሎት የምንሰጥበት ዓላማ ምንድን ነው? ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቷል። (2 ቆሮንቶስ 9:11-15ን አንብብ።) ጳውሎስ “ሕዝባዊ አገልግሎት” ይኸውም የእርዳታ ሥራ የምናከናውንባቸውን ሦስት ዋና ዋና ዓላማዎች በዚህ ጥቅስ ላይ ጎላ አድርጎ ገልጿል። እስቲ እነዚህን ዓላማዎች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

8 አንደኛ፣ የእርዳታ አገልግሎት መስጠታችን ለይሖዋ ክብር ያመጣል። ጳውሎስ ከላይ በተጠቀሱት አምስት ቁጥሮች ላይ ለወንድሞቹ ስለ ይሖዋ አምላክ ምን ያህል ደጋግሞ እንደተናገረ ልብ በል። ሐዋርያው ‘ለአምላክ ስለሚቀርብ ምስጋና’ እንዲሁም ‘ለአምላክ ስለሚቀርብ ብዙ ምስጋና’ ለወንድሞቹ ገልጾላቸዋል። (ቁጥር 11, 12) የእርዳታ ሥራ፣ ክርስቲያኖች “አምላክን እንዲያከብሩ” እንዲሁም ‘አምላክ የሰጣቸውን የላቀ ጸጋ’ እንዲያደንቁ እንደሚያደርግ ተናግሯል። (ቁጥር 13, 14) ጳውሎስ ስለ እርዳታ አገልግሎት የሰጠውን ሐሳብ የደመደመው “አምላክ የተመሰገነ ይሁን” በማለት ነው።—ቁጥር 151 ጴጥ. 4:11

9. የእርዳታ ሥራ በሰዎች አመለካከት ላይ ምን ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

9 እንደ ጳውሎስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችም የእርዳታ ሥራዎችን የሚመለከቷቸው ለይሖዋ ክብር ለማምጣት እንዲሁም ትምህርቶቹ ውበት እንዲጎናጸፉ ለማድረግ እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገው ነው። (1 ቆሮ. 10:31፤ ቲቶ 2:10) ደግሞም የእርዳታ ሥራ አንዳንዶች ስለ ይሖዋና ስለ ምሥክሮቹ ያላቸውን አሉታዊ አመለካከት ለመቀየር ብዙውን ጊዜ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአውሎ ነፋስ ከባድ ጉዳት በደረሰበት አካባቢ የምትኖር አንዲት ሴት በሯ ላይ “የይሖዋ ምሥክሮች፣ በሬን እንዳታንኳኩ” የሚል ምልክት ለጥፋ ነበር። ከዚያም አንድ ቀን ፈቃደኛ ሠራተኞች ከቤቷ ፊት ለፊት የሚገኘውን በአውሎ ነፋስ ጉዳት የደረሰበት ቤት ሲጠግኑ ተመለከተች። በሠራተኞቹ መካከል ወዳጃዊ መንፈስ እንዳለ በየዕለቱ ታስተውል ስለነበር እነዚህ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ወደ ቦታው ሄደች። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ ስትገነዘብ በጣም ተገረመች። “አሁን እንዳስተዋልኩት ስለ እናንተ የነበረኝ አመለካከት የተሳሳተ ነው” በማለት ተናገረች። ይህች ሴት ምን አድርጋ ይሆን? በሯ ላይ የለጠፈችውን ምልክት አንስታለች።

10, 11. (ሀ) የእርዳታ ሥራችን ሁለተኛ ዓላማ ግቡን እየመታ እንዳለ የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ? (ለ) የእርዳታ ሠራተኞችን የሚያግዝ ምን ጽሑፍ ተዘጋጅቷል? (“ የእርዳታ ሠራተኞችን የሚጠቅም ተጨማሪ መሣሪያ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

10 ሁለተኛ፣ የእምነት ባልንጀሮቻችን “የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እንዲሟሉላቸው” እናደርጋለን። (2 ቆሮ. 9:12ሀ) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በአፋጣኝ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ለማሟላትና ሥቃያቸውን ለማስታገስ እንፈልጋለን። ለምን? ምክንያቱም የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ ‘አንድ አካል’ ስለሆኑ “አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ።” (1 ቆሮ. 12:20, 26) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸው ችግር እንዳጋጠማቸው ሲያውቁ ወዲያውኑ ሁሉን ነገር ትተው የሚያስፈልጋቸውን መሣሪያ ብቻ በመያዝ እርዳታ ለመስጠት በአደጋ ወደተጠቁ ቦታዎች እንዲሄዱ የሚያነሳሳቸው ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅርና ርኅራኄ ነው። (ያዕ. 2:15, 16) ለምሳሌ ያህል፣ ጃፓን በ2011 በሱናሚ በተመታች ጊዜ የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ለሚገኙ የአካባቢ የግንባታ ኮሚቴዎች ደብዳቤ በመጻፍ ጃፓን ሄደው የመንግሥት አዳራሾችን እንደገና መገንባት የሚችሉ “ብቃት ያላቸው ጥቂት ወንድሞች” ማግኘት ይቻል እንደሆነ ጠየቀ። ታዲያ ምን ምላሽ ተገኘ? በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወደ 600 ገደማ ፈቃደኛ ሠራተኞች በራሳቸው ወጪ ወደ ጃፓን ተጉዘው እርዳታ ለመስጠት ራሳቸውን አቀረቡ! የዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ “ያገኘነው ምላሽ ከጠበቅነው በላይ ሆኖብናል” ብሏል። በጃፓን የሚኖር አንድ ወንድም፣ እርዳታ ለመስጠት ከሌላ አገር የመጣን ወንድም ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ ሲጠይቀው “በጃፓን ካሉ ወንድሞቻችን ጋር ‘አንድ አካል’ ነን። በመሆኑም ሥቃያቸውና ችግራቸው እኛንም ይሰማናል” የሚል ምላሽ ሰጥቶታል። ፈቃደኛ ሠራተኞቹ፣ ሕይወታቸውን እንኳ አደጋ ላይ ጥለው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን የረዱባቸው ጊዜያትም አሉ፤ ይህም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግ ፍቅር እንዳላቸው ያሳያል። c1 ዮሐ. 3:16

11 የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም የምናከናውነውን የእርዳታ ሥራ እንደሚያደንቁ ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ2013 በአርከንሶ፣ ዩናይትድ ስቴትስ አደጋ በተከሰተ ጊዜ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሰጡትን ፈጣን ምላሽ በተመለከተ አንድ ጋዜጣ እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች ፈቃደኛ ሠራተኞቻቸውን በሚገባ ስላደራጇቸው አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች እርዳታ የሚሰጡት በተቀላጠፈና ውጤታማ በሆነ መንገድ ነው።” በእርግጥም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻችን “የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሚገባ እንዲሟሉላቸው” እናደርጋለን።

12-14. (ሀ) የእርዳታ ሥራችንን ሦስተኛ ዓላማ ማሳካታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ወንድሞች ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸው መመለሳቸው ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳዩት የትኞቹ አስተያየቶች ናቸው?

12 ሦስተኛ፣ አደጋ የደረሰባቸው ወንድሞቻችን ወደ ቀድሞው መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው እንዲመለሱ እንረዳቸዋለን። ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጳውሎስ እርዳታ የሚደረግላቸው ሰዎች ‘ለአምላክ ብዙ ምስጋና ለማቅረብ’ እንደሚነሳሱ ገልጿል። (2 ቆሮ. 9:12ለ) ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞች በተቻለ ፍጥነት ወደ መንፈሳዊ እንቅስቃሴያቸው ከመመለስ በላይ ለይሖዋ ያላቸውን አድናቆት የሚገልጹበት ምን የተሻለ መንገድ ሊኖር ይችላል? (ፊልጵ. 1:10) የ1945 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጳውሎስ መዋጮ እንዲሰበሰብ የተስማማው . . . መዋጮው ችግር ላይ የወደቁ . . . ወንድሞች በቁሳዊ ረገድ የተወሰነ እርዳታ እንዲያገኙና በዚህም ምክንያት ስለ ሥጋዊ ነገር ሳይጨነቁ ሙሉ ኃይላቸውን ስለ ይሖዋ በመመሥከሩ ሥራ ላይ እንዲያደርጉ ስለሚረዳቸው ነው።” ዛሬም ዓላማችን ይኸው ነው። ወንድሞቻችን ወደ ስብከቱ ሥራ መመለሳቸው የተጨነቁ ሰዎችን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ያበረታታቸዋል።—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4ን አንብብ።

13 በጣም ያስፈልጋቸው የነበረውን እርዳታ ካገኙ በኋላ በአገልግሎት መካፈላቸውን የቀጠሉ አንዳንዶች እንዲህ ማድረጋቸው እንዴት እንዳበረታታቸው የሰጡትን አስተያየት እንመልከት። አንድ ወንድም “ቤተሰባችን በአገልግሎት መካፈሉ በረከት ሆኖለታል” ብሏል። አክሎም “ሌሎችን ለማጽናናት ጥረት ማድረጋችን ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ስለ ራሳችን ጉዳዮች በማሰብ እንዳንጨነቅ ረድቶናል” በማለት ተናግሯል። አንዲት እህት ደግሞ “በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮሬ በአካባቢዬ ስለደረሰው ውድመት እንዳላስብ አድርጎኛል። የደኅንነት ስሜት እንዲሰማኝ ረድቶኛል” ብላለች። አንዲት ሌላ እህትም እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ነገሮች ከእኛ አቅም በላይ ቢሆኑም አገልግሎት፣ ቤተሰባችን በተስፋችን ላይ እንዲያተኩር ረድቶታል። አዲሱን ዓለም በተመለከተ ስላለን ተስፋ ለሌሎች መናገራችን ሁሉም ነገር አዲስ እንደሚሆን ያለንን እምነት አጠናክሮልናል።”

14 አደጋ የደረሰባቸው የእምነት ባልንጀሮቻችን በተቻለ ፍጥነት ሊቀጥሉት የሚገባው ሌላው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። ኪዮኮ የተባሉ እህት ምን እንዳጋጠማቸው እንመልከት። የሚኖሩበት አካባቢ በሱናሚ በተመታበት ወቅት በ50ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የነበሩት እህት ኪዮኮ ከለበሱት ልብስና ካደረጉት ጫማ በቀር ሁሉን ነገር አጡ፤ በመሆኑም ምን እንደሚያደርጉ ግራ ገብቷቸው ነበር። ከዚያም አንድ ሽማግሌ፣ መደበኛ ክርስቲያናዊ ስብሰባቸውን በእሱ መኪና ውስጥ እንደሚያደርጉ ነገራቸው። እህት ኪዮኮ እንዲህ ብለዋል፦ “መኪናው ውስጥ አንድ የጉባኤ ሽማግሌና ሚስቱ እንዲሁም እኔና አንዲት ሌላ እህት ነበርን። ስብሰባው አጠር ያለ ቢሆንም የሱናሚው ሐሳብ ከአእምሮዬ በንኖ ጠፋ፤ ይህ ተአምር ነበር። የአእምሮ ሰላም አገኘሁ። ይህ ስብሰባ፣ ክርስቲያኖች አንድ ላይ መሰብሰባቸው ምን ያህል ጥቅም እንዳለው አስገንዝቦኛል።” አንዲት ሌላ እህት አደጋ ከደረሰ በኋላ ስለተገኘችባቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ስትናገር “በጽናት እንድቀጥል ረድተውኛል” ብላለች።—ሮም 1:11, 12፤ 12:12

የእርዳታ አገልግሎት ዘላቂ ጥቅሞች ያስገኛል

15, 16. (ሀ) በቆሮንቶስም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ያሉ ክርስቲያኖች ከእርዳታ ሥራ ምን ጥቅም አግኝተዋል? (ለ) እኛስ በዛሬው ጊዜ ከሚከናወነው የእርዳታ ሥራ ተመሳሳይ ጥቅም የምናገኘው እንዴት ነው?

15 ጳውሎስ የእርዳታ አገልግሎትን በተመለከተ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በሰጠው ሐሳብ ላይ እነሱም ሆኑ ሌሎች ክርስቲያኖች ከዚህ ሥራ ስለሚያገኙት ጥቅምም ገልጿል። እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ከሰጣችሁ የላቀ ጸጋ የተነሳ ስለ እናንተ ምልጃ እያቀረቡ [እርዳታ የተደረገላቸው በኢየሩሳሌም ያሉ አይሁዳዊ ክርስቲያኖች] ለእናንተ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ።” (2 ቆሮ. 9:14) በእርግጥም የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ያሳዩት ልግስና፣ በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች በቆሮንቶስ ላሉ ወንድሞቻቸው (ከአሕዛብ የመጡትንም ይጨምራል) እንዲጸልዩ አነሳስቷቸዋል፤ እንዲሁም ለእነሱ ያላቸው ፍቅር እንዲጨምር አድርጓል።

16 የታኅሣሥ 1, 1945 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ጳውሎስ የእርዳታ ሥራ ያለውን ጥቅም አስመልክቶ የተናገረው ሐሳብ በዘመናችን እንዴት እንደሚሠራ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በአንድ አካባቢ ያሉ ራሳቸውን የወሰኑ የአምላክ ሕዝቦች በሌላ አካባቢ ያሉ የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን መርዳታቸው ምን ያህል አንድነት ሊፈጥር እንደሚችል አስቡ!” በዛሬው ጊዜ ያሉ የእርዳታ ሥራ የሚያከናውኑ ወንድሞችም የሚሰማቸው እንዲሁ ነው። በጎርፍ ለተጠቁ ወንድሞች እርዳታ ያደረገ አንድ ሽማግሌ “በእርዳታ ሥራው መካፈሌ ከመቼውም የበለጠ ከወንድሞቼ ጋር እንደተቀራረብኩ እንዲሰማኝ አድርጓል” ብሏል። እርዳታ የተደረገላት አንዲት እህት አመስጋኝነቷን ስትገልጽ “የወንድማማች ፍቅራችን ምድር ገነት በምትሆንበት ወቅት ምን ሁኔታ እንደሚኖር የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ ነው” ብላለች።—ምሳሌ 17:17ን አንብብ።

17. (ሀ) ኢሳይያስ 41:13 ከእርዳታ ሥራ ጋር በተያያዘ ፍጻሜ የሚያገኘው እንዴት ነው? (ለ) የእርዳታ ሥራ ይሖዋን የሚያስከብረውና ከወንድሞቻችን ጋር ያለንን አንድነት የሚያጠናክረው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ አንዳንድ ምሳሌዎችን ጥቀስ። (“ በዓለም ዙሪያ ያሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች እፎይታ ያስገኛሉ” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

17 እርዳታ የሚሰጡ ወንድሞች በአደጋ ለተጠቁት ወንድሞች ሲደርሱላቸው በአካባቢው ያሉት ክርስቲያኖች አምላክ “‘አትፍራ። እረዳሃለሁ’ የምልህ እኔ፣ አምላክህ ይሖዋ ቀኝ እጅህን ይዣለሁ” በማለት የገባውን ቃል እውነተኝነት ለየት ባለ መንገድ ማየት ችለዋል። (ኢሳ. 41:13) ከአደጋ የተረፈች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “የደረሰውን ውድመት ስመለከት ተስፋ ቆርጬ ነበር፤ ይሖዋ ግን እጁን ዘረጋልኝ። ከወንድሞች ያገኘሁት እርዳታ በቃላት ሊገለጽ አይችልም።” ሁለት ሽማግሌዎች፣ የሚኖሩበት አካባቢ በአደጋ ከተጠቃ በኋላ ጉባኤዎቻቸውን ወክለው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “የምድር መናወጡ ከፍተኛ ሥቃይ ቢያስከትልም በወንድሞቻችን አማካኝነት የይሖዋን እጅ ማየት ችለናል። ስለ እርዳታ ሥራ አንብበን እናውቃለን፤ አሁን ግን እንዲህ ዓይነት እርዳታ ሲደረግ በገዛ ዓይናችን መመልከት ችለናል።”

የበኩልህን ድርሻ ማበርከት ትችላለህ?

18. በእርዳታ ሥራ መካፈል ከፈለግህ ምን ማድረግ ትችላለህ? (“ ሕይወቱን አቅጣጫ አስይዞለታል” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

18 በእርዳታ ሥራ መካፈል የሚያስገኘውን ደስታ መቅመስ ትፈልጋለህ? ከሆነ የእርዳታ ሠራተኞች በአብዛኛው የሚመረጡት በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ከሚካፈሉት መካከል እንደሆነ አስታውስ። ስለዚህ በዚህ ሥራ ለመካፈል ማመልከት እንደምትፈልግ ለጉባኤህ ሽማግሌዎች ንገራቸው። በእርዳታ ሥራ የረጅም ጊዜ ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ እንዲህ የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል፦ “አደጋ ወደደረሰበት ቦታ መጓዝ ያለብህ የእርዳታ ሰጪ ኮሚቴው እንዲህ እንድታደርግ ግብዣ ካቀረበልህ ብቻ ነው።” እንዲህ ካደረግን የእርዳታውን ሥራ ሥርዓት ባለው መንገድ ማከናወን እንችላለን።

19. የእርዳታ ሠራተኞች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን በግልጽ የሚያሳዩት እንዴት ነው?

19 በእርግጥም የእርዳታ ሥራ ክርስቶስ “እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” በማለት የሰጠንን ትእዛዝ የምንፈጽምበት አንዱ መንገድ ነው። እንዲህ ዓይነት ፍቅር በማሳየት የክርስቶስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን እናስመሠክራለን። (ዮሐ. 13:34, 35) በዛሬው ጊዜ፣ የአምላክ መንግሥት ታማኝ ደጋፊዎች አደጋ በሚያጋጥማቸው ወቅት የእርዳታ አገልግሎት በመስጠት ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ በርካታ ፈቃደኛ ሠራተኞች በመካከላችን መኖራቸው እንዴት ያለ በረከት ነው!

a በዚህ ምዕራፍ ላይ የምንመረምረው ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስለምንሰጠው የእርዳታ አገልግሎት ነው። ሆኖም በምንሰጠው እርዳታ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎችም የተጠቀሙባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ።—ገላ. 6:10

b ጳውሎስ ስለ ‘ጉባኤ አገልጋዮች’ ሲናገር የተጠቀመው ዲያኮኖስ (አገልጋይ) የሚለውን ቃል ብዙ ቁጥር ነው።—1 ጢሞ. 3:12

c በኅዳር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 23-27 ላይ የወጣውን “በቦስኒያ የሚኖሩትን የእምነት ቤተሰቦቻችን መርዳት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።