በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በስተ ግራ፦ አንድ ወንድም በመስበኩ ምክንያት በፖሊስ ሲያዝ፣ ኣይንትሆቨን፣ ኔዘርላንድ፣ 1945፤ በስተ ቀኝ፦ አንተ በምትኖርበት አካባቢ፣ ሕጉ የመስበክ ነፃነት ይሰጣል?

ክፍል 4

መንግሥቱ የተቀዳጃቸው ድሎች—ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ

መንግሥቱ የተቀዳጃቸው ድሎች—ምሥራቹ በሕግ የጸና እንዲሆን ማድረግ

ከቤት ወደ ቤት እያገለገልክ ሳለህ ከርቀት ፖሊሶች ሲመጡ ተመለከትህ። አንተና የአገልግሎት ጓደኛህ፣ ወደሚቀጥለው ቤት ሄዳችሁ የቤቱን ባለቤት ማነጋገር ስትጀምሩ ጓደኛህ፣ ፖሊሶቹ የሚመጡት ወደ እናንተ እንደሆነ ስላስተዋለ ትኩረቱ ተከፋፈለ። ፖሊሶቹም አጠገባችሁ ሲደርሱ እንዲህ አሏችሁ፦ “በየቤቱ እየሄዳችሁ የምታንኳኩት እናንተ ናችሁ? የሰዎችን ቤት እያንኳኳችሁ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንደምትሰብኩ ጥቆማ ደርሶን ነው የመጣነው!” እናንተም የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆናችሁ በአክብሮት ትነግሯቸዋላችሁ። ከዚያ በኋላስ ምን ይሆናል?

የዚህ ጥያቄ መልስ በአብዛኛው የተመካው ባለህበት አገር ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ባሳለፉት ታሪክ ላይ ነው። የምትኖርበት አገር መንግሥት፣ ባለፉት ዓመታት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ይመስላል? በተወሰነ መጠንም ቢሆን የሃይማኖት ነፃነት አለ? ከሆነ ለዚህ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተው መንፈሳዊ ወንድሞችህና እህቶችህ ባለፉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ “ለምሥራቹ [ለመሟገትና] በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ” ብዙ ጥረት ማድረጋቸው ሊሆን ይችላል። (ፊልጵ. 1:7) የምትኖረው የትም ሆነ የት፣ የይሖዋ ምሥክሮች በፍርድ ቤት ስላገኟቸው ድሎች የሚገልጹ ዘገባዎችን መመርመርህ እምነትህን በእጅጉ ያጠናክርልሃል። በዚህ ክፍል ውስጥ ከእነዚህ አስገራሚ ዘገባዎች መካከል አንዳንዶቹን እንመለከታለን። ያገኘናቸው ድሎች የአምላክ መንግሥት እውን እንደሆነ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ናቸው፤ ምክንያቱም በራሳችን አቅም ብቻ ቢሆን እንዲህ ያለ ስኬት ማግኘት አንችልም ነበር!

በዚህ ክፍል ውስጥ

ምዕራፍ 13

የመንግሥቱ ሰባኪዎች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይላቸው አደረጉ

በዛሬው ጊዜ ባሉ አንዳንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ውስጥ ያሉ ዳኞች በጥንት ዘመን እንደነበረው ገማልያል የተባለ የሕግ አስተማሪ ዓይነት አመለካከት አላቸው።

ምዕራፍ 14

የአምላክን መንግሥት ብቻ በታማኝነት መደገፍ

የይሖዋ ምሥክሮች ከፖለቲካዊ ጉዳዮች ገለልተኛ በመሆናቸው ምክንያት ያጋጠማቸውን የስደት “ወንዝ” ያልተጠበቀ ወገን ውጦታል።

ምዕራፍ 15

የአምልኮ ነፃነት ለማግኘት መታገል

የአምላክ ሕዝቦች የአምላክን መንግሥት ሕጎች የመታዘዝ መብታቸውን ለማስከበር ሲሉ መታገል አስፈልጓቸዋል።