በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 1

ከአምላክ የተላኩ ሁለት መልእክቶች

ከአምላክ የተላኩ ሁለት መልእክቶች

ሉቃስ 1:5-33

  • መልአኩ ገብርኤል፣ መጥምቁ ዮሐንስ እንደሚወለድ ተናገረ

  • ገብርኤል፣ ኢየሱስ እንደሚወለድ ለማርያም ነገራት

መላው መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ የተላከ መልእክት ነው ማለት ይቻላል። በሰማይ የሚገኘው አባታችን ይህን መልእክት የላከው ለእኛ መመሪያ እንዲሆን ነው። የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ የተላኩ ሁለት ልዩ መልእክቶችን እንመልከት። እነዚህን መልእክቶች ይዞ የመጣው ‘በአምላክ አጠገብ በፊቱ የሚቆም’ ገብርኤል የተባለ መልአክ ነው። (ሉቃስ 1:19) ገብርኤል እነዚህን በጣም አስፈላጊ መልእክቶች ባደረሰበት ወቅት የነበሩት ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ?

ጊዜው 3 ዓ.ዓ. ገደማ ነው። ገብርኤል የመጀመሪያውን መልእክት ያደረሰው የት ነው? መልእክቱን ይዞ የሄደው ወደ ይሁዳ ኮረብቶች ሲሆን ቦታው የሚገኘው በኢየሩሳሌም አቅራቢያ ሳይሆን አይቀርም፤ በዚያ ዘካርያስ የተባለ የይሖዋ ካህን ይኖራል። ዘካርያስም ሆነ ሚስቱ ኤልሳቤጥ ዕድሜያቸው የገፋ ሲሆን ልጅ የላቸውም። ዘካርያስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው የአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ በክህነት የሚያገለግልበት ተራ ደርሷል። ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ እያገለገለ ሳለ ገብርኤል በዕጣን መሠዊያው አጠገብ በድንገት ተገለጠ።

በዚህ ጊዜ ዘካርያስ በጣም ፈራ። ሆኖም መልአኩ እንዲህ በማለት አረጋጋው፦ “ዘካርያስ፣ አትፍራ፤ ምክንያቱም አምላክ ያቀረብከውን ምልጃ ሰምቷል፤ ሚስትህ ኤልሳቤጥም ወንድ ልጅ ትወልድልሃለች፤ ስሙንም ዮሐንስ ትለዋለህ።” ገብርኤል አክሎም “በይሖዋ ፊት ታላቅ ይሆናል” እንዲሁም ‘ሰዎችን ለይሖዋ ያዘጋጃል’ ሲል ስለ ዮሐንስ ተናገረ።—ሉቃስ 1:13-17

ዘካርያስ ግን ይህ ፈጽሞ የማይታመን ነገር እንደሆነ ተሰማው። ለምን? እሱና ኤልሳቤጥ ዕድሜያቸው ስለገፋ ነው። በመሆኑም ገብርኤል “ቃሌን ስላላመንክ ይህ ነገር እስኪፈጸም ድረስ ዱዳ ትሆናለህ! መናገርም አትችልም” አለው።—ሉቃስ 1:20

በዚህ መሃል፣ ውጭ ቆመው የነበሩት ሰዎች ዘካርያስ ይህን ያህል የቆየው ለምን እንደሆነ ግራ ገብቷቸዋል። በመጨረሻ ከቤተ መቅደሱ ሲወጣም በእጆቹ ምልክት ከመስጠት በስተቀር መናገር አልቻለም። ይህን ሲያዩ፣ ዘካርያስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ሳለ ተአምራዊ የሆነ ነገር እንደተመለከተ ተገነዘቡ።

ዘካርያስ በቤተ መቅደስ የሚያከናውነውን አገልግሎት ሲፈጽም ወደ ቤቱ ተመለሰ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኤልሳቤጥ ፀነሰች! ኤልሳቤጥ ለአምስት ወራት ያህል ከሰዎች ተገልላ ቤት ውስጥ በመቆየት የምትወልድበትን ጊዜ ትጠባበቅ ጀመር።

ከጊዜ በኋላ ገብርኤል እንደገና ተገለጠ። በዚህ ጊዜ መልእክቱን ያደረሰው ለማን ነው? ማርያም ለተባለች ያላገባች ወጣት ነው፤ ማርያም የምትኖረው ከኢየሩሳሌም በስተ ሰሜን በምትገኝ ገሊላ በተባለች ክልል ውስጥ ባለችው በናዝሬት ከተማ ነው። ታዲያ መልአኩ ምን ነገራት? ‘በአምላክ ፊት ሞገስ አግኝተሻል’ አላት። ገብርኤል አክሎም እንዲህ አለ፦ “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ፤ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፤ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ። እሱም ታላቅ ይሆናል፤ የልዑሉም አምላክ ልጅ ይባላል፤ . . . በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል፤ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።”—ሉቃስ 1:30-33

ገብርኤል እነዚህን ሁለት መልእክቶች እንዲያደርስ የተሰጠውን ተልእኮ እንደ ታላቅ መብት እንደቆጠረው መረዳት አያዳግትም። ስለ ዮሐንስና ስለ ኢየሱስ ይበልጥ እያነበብን ስንሄድ እነዚህ ከሰማይ የተላኩ መልእክቶች እጅግ አስፈላጊ የሆኑበትን ምክንያት በሚገባ እንገነዘባለን።