በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምዕራፍ 9

በናዝሬት አደገ

በናዝሬት አደገ

ማቴዎስ 13:55, 56 ማርቆስ 6:3

  • የዮሴፍና የማርያም ቤተሰብ ቁጥር ጨመረ

  • ኢየሱስ ሙያ ተማረ

ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ነው፤ ናዝሬት ያን ያህል ቦታ የማይሰጣት ትንሽ ከተማ ነበረች። ይህች ከተማ የምትገኘው ገሊላ በምትባለው ከይሁዳ በስተ ሰሜን ያለች ኮረብታማ አካባቢ ሲሆን የገሊላ ባሕር ተብሎ ከሚጠራው ትልቅ ሐይቅ በስተ ምዕራብ ናት።

ዮሴፍና ማርያም ኢየሱስን ከግብፅ ወደዚህ ስፍራ ይዘውት ሲመጡ ሁለት ዓመት ገደማ ሳይሆነው አይቀርም። በወቅቱ ሌላ ልጅ የነበራቸው አይመስልም። ከጊዜ በኋላ ግን ያዕቆብ፣ ዮሴፍ፣ ስምዖንና ይሁዳ የተባሉት ወንድሞቹ ተወለዱ። ዮሴፍና ማርያም ሴቶች ልጆችም ወልደዋል። ስለዚህ ኢየሱስ ቢያንስ ስድስት ታናናሽ ወንድሞችና እህቶች አሉት

ኢየሱስ ሌሎች ዘመዶችም አሉት። ስለ ኤልሳቤጥና ስለ ልጇ ዮሐንስ ቀደም ሲል ተመልክተናል። የሚኖሩት ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በስተ ደቡብ በምትገኘው በይሁዳ ነው። ኢየሱስ፣ ያን ያህል ብዙም ሳትርቅ በገሊላ የምትኖር ሰሎሜ የምትባል ዘመድም አለችው። ሰሎሜ የማርያም እህት ሳትሆን አትቀርም፤ ከሆነ የኢየሱስ አክስት ናት ማለት ነው። የሰሎሜ ባለቤት ዘብዴዎስ ይባላል። በመሆኑም ሁለቱ ልጆቻቸው ማለትም ያዕቆብና ዮሐንስ ለኢየሱስ የአክስቱ ልጆች ሊሆኑ ይችላሉ። ኢየሱስ በልጅነቱ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ምን ያህል ጊዜ ያሳልፍ እንደነበር አናውቅም፤ ከጊዜ በኋላ ግን የቅርብ ጓደኞቹ አልፎ ተርፎም ሐዋርያቱ ሆነዋል።

ዮሴፍ በቁጥር እየጨመረ የመጣውን ቤተሰቡን ለማስተዳደር ተግቶ መሥራት አለበት። ዮሴፍ አናጺ ነው። ኢየሱስን እንደ ራሱ ልጅ አድርጎ ስላሳደገው ኢየሱስ “የአናጺው ልጅ” ተብሎ ተጠርቷል። (ማቴዎስ 13:55) ዮሴፍ ኢየሱስንም አናጺነት አስተምሮታል፤ ኢየሱስም በዚህ ሙያ የተካነ ሆኗል። ከጊዜ በኋላ ሰዎች ኢየሱስን “አናጺው” ብለው ጠርተውታል።—ማርቆስ 6:3

ዮሴፍና ቤተሰቡ ሕይወታቸው በይሖዋ አምልኮ ላይ ያተኮረ ነው። ዮሴፍና ማርያም፣ የአምላክ ሕግ በሚያዘው መሠረት ‘በቤታቸው ሲቀመጡ፣ በመንገድ ላይ ሲሄዱ፣ ሲተኙና ሲነሱ’ ለልጆቻቸው መንፈሳዊ ነገሮች ያስተምሯቸዋል። (ዘዳግም 6:6-9) ናዝሬት ውስጥ ምኩራብ አለ። ዮሴፍ በዚያ ይሖዋን ለማምለክ ዘወትር ቤተሰቡን ይዞ እንደሚሄድ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ ‘እንደ ልማዱ በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ እንደገባ’ የሚገልጽ ዘገባ እናገኛለን። (ሉቃስ 4:16) ቤተሰቡ፣ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ዘወትር በሚያደርገው ጉዞም በጣም ይደሰታል።